የጽሁፍ ምንጭ፤ ቤተፍቅር/www.betefikir.blogspot.com/
ከምድራችን ጩኸት አንዱ የመልካም
ያለህ የሚለው ነው፡፡
በጎውን ማድረግ ሰው የተፈጠረበት ዓላማ
ሆኖ ሳለ ዛሬ
አንድ መልካም ማግኘት
የአንድ በዓልን ያህል የሚያስቦርቅ ሆኖአል፡፡
በእርግጥም በክፉ በተያዘው ዓለም
ክፉዎች አይደንቁንም፡፡ ጥሩ ነገር ከሰዎች
ልቦና በተንጠፋጠፈበት፣ ለዓመጽ የተዘረጉ፤
ለመታደግ የታጠፉ እጆች በበረከቱበት፣ ለመርዶ የሚፋጠኑ፤
ለምስራች ሽባ የሆኑ እግሮች
በሚስተዋሉበት፣ አደበት ሁሉ ስንፍናን አብዝቶ
በሚያወራበት ዓለም መልካምነት ጌጡ
የሆነ ሰው ሲገኝ
ከዚህም በላይ ያስደስታል፡፡ ልብ ብለነው
ከሆነ ግን መልካም
መሆን፤ በጎ ማድረግ ብቻ
ሳይሆን በዚያ መልካም ላለመበደል፣
በዚያ በጎ ላለመሳት
መጠንቀቅም እንደ እግዚአብሔር አሳብ
ሊኖሩ ለሚፈልጉና ከሕሊና
ውቅሻ ማምለጥ ለሚሹ
ሁሉ የተገባ ነው፡፡
አብዛኛውን ጊዜ በውጪው ዓለም
ላይ በሥራ የሚሰማሩ
ወገኖቻችን የኑሮአቸውን ያህል የሚኖሩት ለቤተሰብና
ለዘመዶቻቸው ጭምር ነው፡፡ አንዳንዴም
የራሳቸውን እስኪረሱ ለቤተሰብ የሚኖሩ፣ የሚለፉ ሰዎችን አስተውለናል፡፡ አገር ቤት ያለውን
ነገር ስንመለከተው ደግሞ
በእህትና ዘመድ ልፋት ሳይማሩ፣
ሳይሠሩ፣ ሳይጥሩ የሰው ወዝ ባመጣው
የሚኖሩ ወጣቶችንና ወላጆችን ታዝበናል፡፡ ነገር ግን ረጂዎቹ
አስተውለውት ከሆነ በመልካምነት እየበደሉ
ነው፡፡ መስጠት ስላለብን እንጂ ብር ስላለን
ብቻ አንሰጥም፡፡ መርዳት
ስላለብን እንጂ መርዳት ስለቻልን
ብቻ አንረዳም፡፡ ምናልባት
ይህንን ከመንፈሳዊው ጎን ተመልክታችሁ ልክ
ያልሆነ አባባል እንደሆነ ሊሰማችሁ ይችል ይሆናል፡፡ ዳሩ
ግን መንፈስ ሁሉን
ይመረምራል፡፡ የእግዚአብሔር አሳብም ሞኝነትን አያበረታታም፡፡ ሁሉን ለማነጽ እንድናደርገው
ታዘናል፡፡
የዋህነት የሚለው መንፈሳዊ አሳብ ሞኝነትን ከምንተረጉምበት
መንገድ በእጅጉ የራቀ ነው፡፡ በቂ
ብር ከተላከልኝ አልማርም
አልሠራም ለሚል ሁሉ እያወቁ
ማድረግ የዋህ አያስብልም፡፡ የምናደርገው ነገር
ሰውየውን የተሻለ እንዲያስብ፣ የበለጠ እንዲያይ፣ ካለፈው በበረታ ሁኔታ እንዲጣጣር ካላደረገው
እኛም ይህንን መመዘን
ካልቻልን በምናደርገው በጎ ነገር እየበደልንበት
ነው፡፡
በመልካም መበደል ማለት የምናደርገው ጥሩ
ነገር በተቀባዩ ላይ
እየፈጠረ ያለውን አሉታዊ ተጽእኖ በግልጥ እያወቅን እርምጃ አለመውሰድ ነው፡፡ ከዚህ የሚከፋው ትርጉም
ደግሞ ሆን ተብሎ
በታቀደና በተቀናበረ እንዲሁም በታሰበበት መንገድ መልካሙን ነገር ለክፋት ማዋል
አልያም በበጎ ውስጥ በክፋት
መሸመቅ ማለት ነው፡፡ ሁለቱንም
አንድ የሚያደርጋቸው ነገር መልካምነታቸው
ውስጥ በደል መኖሩ
ነው፡፡ በእርግጥ አንጻራዊ በሆነ መንገድ ካልሆነ
በቀር ሰው በጎነቱ
ውስጥም እድፍ አለ፡፡ እግዚአብሔር
የወዳው ቅንነታችንን የሁል ጊዜ ያህል
እየቆጠረው ካልሆነ የፈረቃ መልካምነታችን ያውና ሕያው በሆነው
ጌታ ፊት መርገም
ባስታቀፈን ነበር፡፡
በመልካም መበደልን ስናስብ በነቢዩ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ያለና የነበረ እግዚአብሔር
የተናገረውን ብርቱ ቃል እናስታውሳለን፡፡
“የሰው ልጅ ሆይ
እነሆ የአይንህን አምሮት
በመቅሰፍት እወስድብሃለሁ፤ አንተም ወይ አትበል አታልቅስም፤
እንባህንም አታፍስስ (ሕዝ. 24÷16)” በጋብቻ ውስጥ ብቻ ሳይሆን
በማንኛውም የኑሮ ሁኔታ እግዚአብሔርን
ማየት በዋጋ የማይተመን
ትርፍ አለው፡፡ ከእግዚአብሔር
ውጪ የምናያቸው ነገሮች
ሁሉ በራሳቸው ተስፈኛ
ስለሆኑ የእኛን እምነት የመሸከም አቅም የላቸውም፡፡ ራሳችን
እንኳን በራሳችን ያፈርንበት ጊዜ ትንሽ አይደለም፡፡
እባካችሁ አይናችሁን ከሰው ላይ አንሱ!
ለየትኛውም ነገር መስፈርታችን እግዚአብሔርን
ማስቀደም አለበት፡፡ ፍቅር እንኳን ቢሆን፤
እግዚአብሔርን መርጦ ጥላቻን ማስተናገድ
እጅግ ማትረፊያ ነው፡፡
እኛ በእኔ ጉዳይ
ማን ያገባዋል? የወደድኩትን
የትኛውንም ያህል ብወድድ ጠያቂ
ማነው? ልንል እንችላለን፡፡
ነገር ግን ነቢዩ
የገዛ ሚስቱ የአይኑ
አምሮት ሆናበት ስለነበር እግዚአብሔር በሞት ከፊቱ አስወገዳት፡፡
ሰውን ስንጠላ ብቻ
ሳይሆን የአይንና የልባችን አምሮት አድርገን ስንወድም እንበድላለን፡፡ ነቢዩ ሚስቱ የጣዖት
ያህል እንደሆነችበትና የፍላጎቱ ሙላት
እንዳደረጋት ልናስተውል እንችላለን፡፡ ሚስት ማግባት ደግሞም
ከእርሷ ጋር በፍቅር መኖር
ኃጢአት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር መልካም እንደሆነ ካየውና ደስ ከተሰኘበት ትልቅ
ነገር አንዱ ጋብቻ
ነው፡፡ የትዳር መስራች፣ አክባሪና የበላይ ጠባቂም እርሱ ነው፡፡ ነገር
ግን እንዲህ ባለው
መልካም ነገር ሕዝቅኤል በአይን
አምሮት ተያዘ፡፡ እንግዲህ በደሉ ያለው ጋብቻው
ላይ ሳይሆን “የአይን
አምሮት” ላይ ነው፡፡ ምን
ጊዜም ቢሆን ለሰጪው
ሳይሆን ለስጦታው ስንሸነፍለት የሚሆነው እንደዚህ ነው፡፡ እግዚአብሔር የአይናችን አምሮት የሆነውን ሁሉ ይወስዳል፡፡ በመልካሙም
መበደል ያስቀጣል፡፡
ሀብትም፣ ንብረትም፣ ሰውም ጭምር ከእግዚአብሔር
ጋር በአማራጭነት ሊቆም
አልያም ስፍራውን ሊወስድ ከቶ አይችልም፡፡ እነዚህ
ነገሮች በራሳቸው መጥፎ አይደሉም፡፡ ጌታን
በገንዘባቸው፣ በሥልጣናቸው፣ በእውቀታቸው፣ በጉብዝናቸው ላይ ሾመውት ያገለገሉ
ብዙ ሰዎችን እናውቃለን፡፡
ነገር ግን እውቀት
ያለው የእግዚአብሔርን ያህል አያውቅም፡፡
ብር ያለውም የእግዚአብሔርን
ያህል ሀብት አይሆንም፡፡
ሀብት ብልና ዝገት
ያጠፋዋል፡፡ እውቀት በእብደት ሞኝነት ይሸፈናል፡፡ ደም ግባትም እንደ
ደረቀ ቅጠል ይረግፋል፣
ሥልጣን በሚበልጥ ሥልጣን ይሻራል፡፡ ጉብዝናን ሽምግልና ይከተለዋል፡፡ ጌታ ግን ማለዳ
ማለዳ አዲስ እንደሆነ
በማይዝል ብርታት ይኖራል፡፡
ነቢዩ ወይ እንዳይል
እንዳያለቅስም ታዟል፡፡ እግዚአብሔር በእውነቱ ልክ ትክክል ነው፡፡
ሲያኖር ብቻ ሳይሆን ሲገልም
እውነተኛ ነው፡፡ ምን ያህሎቻችን ባሉን
መልካም ነገሮች እየበደልን ነው? ሚስት መልካም
ናት የአይናችን አምሮት
ከሆነች ግን እንበድልባታለን፡፡ ልጆች የእግዚአብሔር
ስጦታዎች ናቸው የልባችን ሙላት
ካደረግናቸው ግን በእግዚአብሔር ስጦታ እንበድላለን፡፡
ከባል ጋር መኖር
የተወደደ ነው፡፡ ዳሩ ግን ሁለ
ነገራችን እርሱ እንደሆነ የምናስብ
ደግሞም ያለ እርሱ መኖር
የማንችል ያህል ከተሰማን በመልካሙ
እንበድልበታለን፡፡ ተወዳጆች ሆይ በጎ መሆን
ለሌላውም ማሰብ ነው፡፡ ሰዎች
የአይናችን አምሮት እስኪሆኑ ድረስ ስንወዳቸው እንደ
ሕዝቅኤል ሚስት በተለያየ ምክንያት
በርቀት ሲከፋም በሞት እንዲወሰዱ ምክንያት
እንሆናቸዋለን፡፡ እኛም በዚያው መጠን
የሰው አይን አምሮት
ለመሆን በጣርን ቁጥር ለእግዚአብሔር ቁጣ እንጠጋለን፡፡