Tuesday, July 3, 2012

ትውልድ ያላወቀው ኢትዮጵያዊው ሰው!



ብዙዎቻችን ኢትዮጵያዊ መሆን ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ መወለድ ብቻ አድርገን እንቆጥራለን። ያ ግን ከእውነታው ብዙ የራቀ አስተሳሰብ ነው። በምንም መመዘኛ ኢትዮጵያ ውስጥ መወለድና ኢትዮጵያ ዜጋ መያዝ ማለት ኢትዮጵያዊ ማለት አይደለም የሚል አቋም አለኝ። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ማለት በኑሮው፤ በባህሉ፤ በወጉ፤ በቋንቋው፤ በእምነቱ፤ በታሪኩ፤ በድርጊቱ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ሆኖ መገኘት ነውና። ባህሉን፤ አኗኗሩን፤ ወጉን፤ ቋንቋውን ታሪኩንና እምነቱን፤ትውፊቱን ሁሉ ከኢትዮጵያዊነት አተያይ ውጪ ያደረገ ትውልድ እንደ ሸቀጥ /Made in………/ ተብሎ ኑረቱ የሚገለጽበትን የባእድ ሀገር የማንነት ስያሜ ይሰጠዋል እንጂ ኢትዮጵያዊ ሰው ሊባል የተገባው አይደለም። ኢትዮጵያዊ ሆኖ ከመኖር ውጪ ኢትዮጵያዊነት ሊኖር አይችልምና። ያ ማለት ግን ከሌላው ዓለም ሚዛን ጋር ራሱን እየጠበቀ፤ የጎደለውን እየሞላ፤ የጎዳውን እያረመ አይሄድም ማለት ሳይሆን ማንነቱን በሌሎች ማንነት ውስጥ በመለወጥ፤ በመተካት ወይም በመደረት  ኢትዮጵያዊ መባል እንዳይቻል  ለማሳየት ተፈልጎ ነው።

ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የተጻፉ ሰፋፊ ጥናቶች እንደተጠበቁ ሆነው በዚህ ጽሁፍ ለመዳሰስ የተፈለገው በርእሱ ላይ የተጠቀሰውን «ትውልድ ያላወቀው ኢትዮጵያዊውን ሰው» በተመለከተ በአጭር ምልከታ ለማብራራት ነው።
«ትውልድ ያላወቀው ኢትዮጵያዊ ሰው» በብዙዎች ዘንድ መምሩ/መምሬ/ ወይም ቄስ ተብሎ በማእረገ ክህነቱ የሚጠራው የኢትዮጵያው የገጠር ቤተክርስቲያን አገልጋይ /ካህን/ ነው። በእርግጥ ዘመኑ መምሩ/ መምሬ/ ወይም ቄስ የሚለውን ስመ ተጸውኦ ሲያዘምነው በከተሜው ዘንድ «ቀሲስ» መባሉ ቢታወቅም ያ የገጠሩ ቄስ/ መምሩ/፤ ከዚህ እንግዳ የዝመና ጥሪ ጋር ብዙም ትውውቅ ስለሌለው ያችን ከምንም በላይ የሚያከብራትን፤ የሚወዳትንና የሚጠብቃትን የ«መምሬ» እገሌን ጥሪ እስከዛሬ ሳይለቅ እንደያዘ ይገኛል። ቄስ እገሌ ወይም መምሬ እገሌ ተብሎ መጠራታቸው ለእነርሱ ኩራታቸውና ክብራቸው  ስለመሆኑ በቅርብ የምናውቃቸው ዘመዶቻችን እንደሚናገሩ  ለዚህ ዋቢዎች ነን።


እነ መምሩ/መምህሩ/ የሚከበሩትና  የሚወደዱት ገጠር ስለኖሩ ሳይሆን ለነግህ ኪዳን፣ ለሰርክ ጸሎት የሚተጉ ከመሆናቸው ባሻገር እንደ ተራው ህዝብ ኑረትን ኖረው፤አርሰው ቆፍረውና ጎልጉለው የሚተዳደሩ፤ የተጣሉትን አስታርቀው፤ የታመሙትን ጠይቀው፤ በቤታቸው፤ በጎረቤታቸውና በአካባቢያቸው ፈሪሃ እግዚአብሔርን ኖረውትና አስተምረው፤ ሕዝቡ በግብረ ገብነትና በመከባበር ማኅበራዊ ኑሮውን በኅሊና ዳኝነት እንዲገፋ በማድረግ ከማንም በላይ ኢትዮጵያዊነት የሚታይባቸው የሕብረተሰብእ አንጓዎች በመሆናቸው ነው።
እነመምሩ በቀደሙት ዘመናት ከቤተክርስቲያን የምትሰጣቸውን 10 ብርና 20 ብር ወይም በቁና የምትሰፈርላቸውን የእህል  የድርጎ መዋጮ እንደክፍያ ቆጥረው ሳይሆን ኃላፊነትና ግዴታቸውን አውቀው በማኅሌቱ፤ በሰዓታቱ ቆመው ሲያድሩ ብርታታቸውና ጥንካሬአቸው በእውነቱ ያስገርማል። የሀገር ዳኛ ሳለ እነመምሩ የምእመናን ዳኛ ናቸው። ቃላቸው ይፈራል፤ ይከበራል። ምክራቸውና ተግሳጻቸው በሁሉም ዘንድ ቅቡል ነው።


እነመምህሩ ለሕዝቡ እንደሕግ ምንጭ ሆነው ያገለግላሉ። ከትምህርቱ ጋር ቅርበት የሌለው ሕዝቡ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን  የሚማረው ከእነመምሩ ነው። ብዙው ሰው ፊደሉን፤ ባህሉ፣ ታሪኩን፤ ትውፊትና ወጎችን በቤተሰባዊ ትስስሩ ውስጥ ያሳደገው ከእነዚሁ ቄሶች ባገኘው እውቀት  ነው። በዝክር፤ በክርስትና፤በሰርግና በበዓላት ወቅት እነመምሩ ተገኝተው የዝግጅቱ ድምቀት ከመሆናቸውም በላይ የትውፊት፤ የታሪክና፤ የትምህርት መድረኮች ሆነው ሲያገለግሉ ዘመናት አልፈዋል፤ ዛሬም በድብዝዙ ይገኛል።
በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታየው የይሉኝታ፤ የመተፋፈር፤ ቀድሞ ያለመናገር፤ የማዳመጥ፤ ታላቅን የማክበር፤ ከጸያፍ ቃል ምላስን የመቆጠብ፤ እኩያንና ብጤን የማወቅ፤ ለወግና ለሥርዓት የመገዛት ስልቶችን  ሰርጸው የተገኙት ዝም ብለው ከሜዳ ወይም ከፕሮቴስታኒዝምና ከእስላሚዝም መገኘት ጋር የመጡ ልምምዶች ሳይሆኑ እነመምሩ በሕብረተሰብ ህንጻ ውስጥ መስርተው ባቆዩት ጥንታዊ የኢትዮጵያዊ ማንነት ስር  መሆኑን መረዳት የግድ ይላል። 

ይሁን እንጂ ዛሬ ላይ በእነ መምሩ የገጠር ኢትዮጵያዊ መሠረቶች ታንጸው የቆዩ ማንነቶች፤ በዘመነኞች እየተደፈጠጠ ማየቱ አስደንጋጭ ነገር ነው። ይሉኝታ እንደ ጅልነት ተቆጥሯል። መተፋፈር ቀርቶ፤ ዛሬ ከንፈር ለከንፈር መሳሳሙ ከጓዳ ወደ አደባባይ ወጥቷል። ቀድሞ መናገር እንደ አዋቂነት፤ በእድሜ የገፋውን ከማክበር፤ በሰው እድሜ የሚኖር ሰው መባሉ ይሰማል። ጸያፍ ቃል  እውቀት ሆኗል። የወለደች «እናት…» የጸያፍ ስድብ አፍ መክፈቻ ሆኗል።  የሴት ልጅ ሱሪ መልበስ አስገርሞ የነበረበትና በስንት አማላጅ ሽማግሌ የሚጠየቅ የሰብእና  ዘመን በስይጣኔ ተተክቶ ሴት ገላዋን ያለማንም ጠያቂ  በግላጭ እንብርትና ጭንዋን በአደባባይ ከምታስመርቅበት ወቅት ላይ ተደርሷል ። ሎቲ አንበሳና ዝሆን ገዳይ የሚያስርበት ዘመን ተረት ተረት ሆኖ ዛሬ በሁለት ጆሮ ጉትቻ ማንጠልጠል የወንዶች የስልጣኔ እድገት መገለጫነት ሆኖ እየተቆጠረ ይገኛል።  ሱሪው ከመቀመጫው ካልወረደ ምእራባዊ የሆነ የማይመስለውና  የወንድ እህትነት ነግሶ ሹሩባ መሰራቱ ዛሬ አያሳፍርም። አሳዛኙ ነገር ደግሞ ምዕራባዊ የጨቀየ ባህልን በመገልበጥ ሰዶማዊነትን እስከማራመድ መደረሱ ነው።

እንግዲህ ይህ ሁሉ የማንነት መናጋት የመጣው ከዚያ ከኢትዮጵያውያን የገጠር መሠረቶች ከሆኑት ከእነመምሩ አካባቢ የሆነ ነገር ጎድሏል ብለን መጠርጠር ተገቢ ነው። ከተሜው ለመጤ ነገር ሁሉ ቅርብ የመሆኑን ያህል በኢትዮጵያ ደረጃ አብዛኛው ከተሜ መነሻው ገጠር እንደመሆኑ መጠን በእነመምሩ ሥርዓት ውስጥ ያለፈ ስለሆነ የገጠሩ ምልከታችን እሱንም ያጠቃልላል።

 አዎ! እነ መምሩ እንደቀደመው ዘመን በየአድባራቱ ብዙም  የሉም። ያሉትም ቢሆኑ ሳይሞቱ ሞተናል በሚሉ «በእነአባ» ስር ወድቀዋል።  እነአባ አያርሱም፤ አይቆፍሩምና የቤተሰብ አስተዳሪ በሆኑትና በሁለት ወገን ኑሮን በሚገፉ በእነመምሩ እግር ተተክተዋል። ጥንት አንድም መነኩሴ ያልነበረበት ቤተክርስቲያን ሳይቀር ዛሬ አስተዳደሩ ጭምር በእነአባ ተወሮ  የእነመምህሩ መሰረትነት ተነቅሏል።ድሮ ድሮ የመምሩ ልጅ መምሩ ነበር። ዛሬ ግን ያ አይስተዋልም።  እነመምሩም ልጆቻቸውን በእነርሱ እግር በደብራቸው እንዳይተኩ የደረሰባቸው እንዳይደርስ ልጆቻቸውን ወደአስኳላ ልከዋል። የኑሮው መክበድና ቤተሰባዊ ሕይወትን በዚያ መልኩ የመግፋቱ ነገር ሲያስቸግር እነመምሩ ወደአስኳላው ልጆቻቸውን ቢልኩ አይደንቅም። የእነመምሩን መንገድ ያዩ ምእመናንም ልጆቻቸውን ወደአስኳላ ቢሰዱ አያስገርምም። አስኳላ መላኩ በራሱ ችግር ባይሆንም ልጅ በቤተሰባዊና በኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ የተመሰረተ እኔነት ሳይኖረው ከአስኳላው ጋር ሲገኛኝ ያገኘውን ሁሉ  እንዳለ ለመቀበል ይገደዳል። የሚያጣራበት  የማንነት ወንፊት ስለሌለው ሁሉን መሞከር ይፈልጋል። በዚህ ምክንያት ያልሆነውን ኢትዮጵያዊነት፤ ካገኘው ምእራባዊነት ጋር ለመደረብ ይገደዳል። አስኳላውም ሥርዓተ ትምህርቱ  ከትምህርተ ግብረ ገብነት ይልቅ አፈራርቆ ስለመውለድና ያልተፈለገ እርግዝናን በመከላከል እንዴት ወሲብ መፈጸም እንደሚቻል በማስረጽ ላይ ያነጣጠረ ስለሆነ ሕብረተሰባዊ ማንነትን በመገንባት ላይ ይህ ነው የሚባል ነገር አላደረገም።

ስለዚህ ትውልዱ ከእነ መምሩ መሠረታዊ የኢትዮጵያዊ ማንነት አስተምህሮዎች መስመር ውጪ በዘመናዊ ባህል ውቅያኖስ ውስጥ የሚዋኝ ሆኗል። ሊወጣው ከማይችለው ውቅያኖስ ውስጥ የሚዋኝ ትውልድ መጨረሻው ምን ይሆን? ኢትዮጵያዊ ወይስ ኢትዮሜሪካኒዝም?
ስናጠቃልል በመግቢያችን ላይ እንደጠቀስነው ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊነት ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ መወለድ ማለት አይደለም። ኢትዮጵያዊ መሠረትና ማንነት ያለው ማለት እንጂ!  ኢትዮጵያዊ ማንነትና መሰረት ደግሞ ቀደምት እነመምሩ ባነጠፉት እምነትና ግብረ ገብነት ውስጥ በተገነባው የሕብረተሰብ ሥርዓት ላይ የቆመ ኢትዮጵያዊነት ማለታችን ነው። ያ መሠረት እየተናደ ከሄደ ኢትዮጵያዊነት  አሜሪካኒዝምን  መምሰል ነው የሚል ትውልድ እንዲፈጠር ያደርጋል። እያየነው ያለነው ነገር ያንን ያመላክታል።

 መምሩ ትውልድ ያላወቀው ኢትዮጵያ ሰው ነው። ነጭ ጥምጥም አድርጎ፤ ባደፈ ልብሱ ላይ ያንን የገጠር ሕዝብ እየመራ የቆየው ባለአገር ቄስ ቤተክርስቲያን ከመክፈትና ከመዝጋት ጋር ብቻ አያይዘን በጠባብ ዓይን ካየነው ተሳስተናል። ኢትዮጵያዊ መሰረትን ተከታይ ልጆቹ ውስጥ በመጣል ግንባር ቀደም ሰው መሆኑ ልናውቅ ይገባል። ያ ቤተሰብ፤ ሕብረተሰብና ማኅበረሰብ ሆኖ በማደግ ነው ኢትዮጵያ የሚሰኘው ሀገር የተገነባው። ከዚህ እውነታ ውጪ  ሌላ ነገር የለም። የዚያ መሰረት አንጓው ሲዳከም ኢትዮጵያዊው የገጠር ቤተሰብ ይዳከማል። ራስ ወዳድነት፤ስግብግብነት፤ ስርቆትና ውሸት እየሰረጸ ኢትዮጵያዊ የመሰኘት ማንነት ይጠፋል። «የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ» የሚለው ለእውነት የመቆም ባህል ታሪክ ይሆናል።  ይህን ኢትዮጵያዊ ማንነት በመገንባት እነመምሩ ታላቅ ሰው ነበሩ። ጆሮአችንን ይመዠልጉ የነበሩት  መምህር መቼም አይረሱንም ።በመዠለጉን  ጆሮአችን የገባው እውቀት ዛሬ ላይ  በእግዚአብሔር የሕይወት መንገድ ላይ ስላቆሙን ምስክሮቻቸው ነን።

ኢትዮጵያዊነትህ በዚያ መሰረት ላይ ካልታነጸ እስላም ብትሆን  ዐረባዊ ነህ። ፕሮቴስታንት ብትሆን ምዕራባዊ ነህ።   በእርግጥ የእነመምሩን ሃይማኖት ለመያዝ ላትገደድ ትችል ይሆናል። የእነመምሩን ኢትዮጵያዊነት ትተህ ኢትዮጵያዊ መሆን ግን በፍጹም እንደማትችል አስረግጬ እነግርሃለሁ። እነመምሩ በኢትዮጵያዊ ሕዝብ ውስጥ ያነጹት ኢትዮጵያዊ  እምነት ብቻ ሳይሆን ግብረ ገብነት፤ ሥነ ምግባር፤ ባህል፤ ትውፊት፤ ታሪክ፤ ክብር፤ ወግና ሥርዓት በመሆኑ ይህንን ትቶ ኢትዮጵያዊ መሆን የሚያስችል ምዕራባዊ ወይም ሩቅ ምስራቃዊ የለም። ትውልዱ ያጣው ማንነት ያንን እላለሁ።
«ደግሞም ለእኔ ትውልድ የዘነጋቸው ፍጹም ኢትዮጵያዊያን እነመምሩ ናቸው»