መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው።
ሰሞኑም መታመማቸውን ከሰማን ጊዜ ጀምሮ ሞታቸው እንዲቃረብ ከሚጸልዩት ጀምሮ ፤ በሀገሪቱ ውስጥ እየታየ ባለው የልማት እንቅስቃሴ
ላይ አንድ ምዕራፍ ላይ ሳያደርሱ በሞት እንዳይሉ እስከሚማጸኑት ድረስ አይተናል። ከዚህ በተለየም በሦስተኛው ረድፍ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት የማይመኙ ነገር ግን በሀገሪቱ ውስጥ
ብዙ በደል ስላደረሱ፤ ከህመም ኃያልነት የተነሳ ጠላቶቼ ከሚሏቸው ወይም ከሚጠሏቸው ጋር እርቅን የሚፈጽሙበት ጊዜ እንዲሆንላቸው የሚመኙትንም ተመልክተናል።
እንደሚታወቀው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በታሪክ
አጋጣሚ የኢትዮጵያ መሪ ናቸው። መሪነትና የፖለቲካ ስልት እንደማይነጣጠሉ ሁሉ ከፖለቲካ አስተሳሰብ በሚመነጭ አመራር ሀገሪቱን እየመሩ
21 ዓመታትን አሳልፈዋል። በዚህ የአመራር ዘመን ያልተደሰቱ እንዳሉ ሁሉ በእሳቸው አመራር የሚመኩ መኖራቸው አይካድም። የዚህ ጽሁፍ
ዓላማ የተደሰቱባቸውና ያዘኑባቸውን ሰዎች ማንነትና የፖለቲካ ልዩነት፤ ምንነቱንና አፈታቱን ለማብራራት ስላልሆነ ያንን ለሚተነትኑ
ሰዎች ትተን በጤናቸው ዙሪያ ማለት በሚገባን ላይ ለማተኰር ነው።
እንደእኛ እምነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህመም ወይም በሌላ ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩ የኢትዮጵያ ችግር ሁሉ አብሯቸው
ይወገዳል ብለን አናስብም። የጠቅላይ ሚኒስትሩም በህይወት ረጅም ዘመን መኖርም እንደዚሁ የሀገሪቱ የተጠራቀመ የዘመናት ችግርና ውስብስብ
የፖለቲካ ባህል ባንድ ጊዜ ያበቃለታል ብለን አንጠብቅም።
ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያን ሁኔታ ከእሳቸው መኖርና
መሞት ጋር በሚያዛምዱ ሰዎች ዘንድ ያለን ልዩነት ከነባራዊ ሁኔታ የሚነሳ ስለሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መታመም እንደ መልካም አጋጣሚ
በመመልከት ሞታቸውን በሚጠባበቁ ሰዎች በጣም እናዝናለን። ስለሞቱ
ማንም ምስጥ ሆኖ አይበላቸውም። በሕይወት ቢኖሩም ማንም ቤተመንግሥት
ገብቶ በምኞት ወንበሩን አይረከብም።
ለሁሉም ጊዜ አለው እንዳለው ሰሎሞን!
የሚወዳቸውም ቢኖር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጥላቻ
ላላቸው ሰዎች ማማካሻ መስጠት ስለማይችል፤ ለጥላቻችንም ሆነ ለፍቅራችን እንደሰብአዊ ፍጡር ዳርቻ ቢኖረው ጥሩ ነው። ሚዛናዊ ሰዎች ብንሆን እግዚአብሔር በዚህ አመለካከት ይደሰታል እንጂ
ቅር አይሰኝም።
አንዳንድ ጊዜ በአጭሩ የምንመኘው ነገር ረጅም ጠባሳ ሊያደርስ ይችላል። ለምሳሌ
ያህል የኢራቁ መሪ ሳዳም ሁሴን ግንድ ላይ በስቅላት በመቀጣቱ ተበድናል ያሉቱ ተደስተው ነበር። የሚወዱት ደግሞ በሞቱ እጅጉን አዝነው
እንደነበር አይዘነጋም። ሳዳም ያልፈጠራቸውን ሰዎች እየገደለ ነፍስና ሥጋቸውን በመለየቱና ለዚህ ድርጊቱ እሱም የእጁን ማግኘት አለበት
በማለት በተመሳሳይ መንገድ ያልፈጠሩት ሰዎች የሳዳምን ነፍስና ሥጋ
ግንድ
ላይ በሞት ለይተዋል። ሳዳም ያልፈጠራቸውን ሰዎች ገደለ፤ ሳዳምንም ያልፈጠሩት ሰዎች ገደሉት። ሁለቱም ያልፈጠሩትን ሰው በመግደል አንድ ናቸው።
እንደዚሁ ሁሉ ለአቶ መለስ ስህተቶች፤ ሞታቸው ለእኛ
ማካካሻ ይሆናል ማለት የደካማ አስተሳሰብ ውጤት ነው። ምክንያቱም
በሳዳም ሞት ምክንያት ያልፍልናል የሚል አስተሳሰብ የነበራቸው ኢራቃውያን
እንኳን ሳይቀሩ 117,000 ሞተዋል። 4 ሚሊዮን ኢራቅን ጥለው ተሰደዋል። ሳዳም ከበደላቸው ይልቅ የሳዳም
ድንገተኛ ስቅላት የፈጠረው የኢራቅ ቀውስ ከባድ ነው። ዛሬም አላባራም። በሀገራችንም አፄውን ሌባ ሌባ ያሉና በሞታቸው እልል ያለ ሁሉ በቀይ ሽብር ወዮ! ወዮ! ለማለት
ዓመት አልፈጀባቸውም። ስለዚህ አሁን ይሆን ዘንድ የምንመኘውን ነገር ቆይቶ ምን ይከተለዋል ማለቱ ጠቃሚ ነው።
እንደዚሁ ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንደህልም አላሚዎቹ በድንገት
ቢሞቱ፤ በሚፈጠረው ክፍተት ሀገሪቱ ችግር ላይ አትወድቅም ብሎ ማሰብ የዋህነት ይሆናል። ሥልጣናቸውን የሚመኝ ማንም ስለተመኘ አያገኝም።
በድንገተኛ ሞት ምክንያት በሚፈጠር ቀውስ ሥልጣን ወደ ደም ማፋሰስ ሊያመራ፤ ሕዝቡንም ሊያቃውስ ይችላል። ቢያንስ ቢያንስ፤ የመተካካት
ሁኔታ እስኪኖር የሃሳብና የአመለካከት ሽኩቻ መኖሩን የማይጠረጥር ቢኖር እሱ የዋህ ነው። ለሀገርና ለሕዝብ የሚያስብ ሰው በአቶ
መለስ ሞት ሳይሆን ሥልጣን በሕጋዊ መንገድ በሕይወት ሳሉ እንዲሸጋገር መመኘት የተሻለ መሆኑን ማሰብ እንጂ ህመማቸው አጣድፎ ሞታቸውን
እንዲያቃርብ ማለም ከጤነኛ አእምሮ የሚመነጭ አይደለም።
ሥልጣን ምን ጊዜም በሕዝብ ፍላጎትና ምርጫ በሰላማዊ መንገድ ሽግግር እስካልተደረገበት ድረስ ቀውስና
ብጥብጥ ሊከተለው ይችላል። ስለዚህ እንደ ደጀ ብርሃን ብሎግ እምነት፤
1/ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንደ ማንኛውም
ሰብአዊ ፍጡር ከደረሱበት ህመም ድነው ፈውስና ጤንነት እንዲጎበኛቸው እንጸልያለን። ለታሰሩ፤ ለተሰደዱና በሀገሪቱ ውስጥ በሰላም
መኖር ለሚፈልጉ ሁሉ መንግሥት አባት ነውና ይቅር እንዲሉም እንመኛለን።
2/ አንዳንዴ ከዚህ ዓለም ገዢ የፖለቲካ መንፈስ ወጣ ብለው፤ ከሞት በኋላ ስለሚኖረው
ህይወት በማሰብ ቢያሳልፉ ይጠቀማሉ እንጂ አይጎዱም እንላቸዋለን።
በጤንነት ዘመን መሪነት እንዳለ ሁሉ በጤንነት መጣት አልጋ ላይ መዋል፤ ሞትና ከሞት በኋላ ስላለው ነገር ማሰቡን ባይረሱ ምክራችን ነው።
3/ ለመሥራትም፤ ለመስማማትም፤ ይቅርም ለማለትና ከፖለቲካው መንፈስ ለመውጣትም
ቢሆን የእርስዎ ጤና መሆን አስፈላጊ ነውና እግዚአብሔር ጤናውን እንዲያድልዎ ጸሎታችን ነው።
ለሁሉም ነገር መልካም ጤንነትና የቀና ሃሳብ መጻዒ ጊዜ ይሁንልዎ!