Wednesday, March 28, 2012

ፍጹም ከቅጣቱ!


ማን ይገኝ ነበረ?


(By dejebirhan)     to read in PDF (click here)
በከንቱ አትጥራኝ፤ ስሜን ባንተ ይክበር
ኢታምልክን ጠብቅ፣ ምልክት አታስቀር
ባልንጀራን ውደድ፤በሀሰት አትመስክር
እድሜህ እንዲረዝም፤ ወላጅህን አክብር
ገላህንም ቀድስ፣ክልክል ነው ማመንዘር
አድርግና ጠብቅ፣ የቆመውን አጥር
ያልሰማ ማን አለ? ኦሪት ስትናገር?
በከንቱ የጠራው በደለኛ ይሆናል፤ (ዘጸ ፳፣፯)
ከአምላኩ መጽሐፍ፤ ከርስቱ ይፋቃል፤ (ዘጸ ፴፪፣፴፫)
ቢሰግድና ቢወድቅ ለቀረጸው ምስል
ቢያሸው፤ ቢዳብሰው ሥሩ ቢንከባለል
የአምላኩ መልክ ሆኖ ከፊቱ ቢተከል፣
ኢታምልክን ሽሯል ትለዋለች ኦሪት
ሕጓን ትጠቅስና፣ ታወርዳለች ቅጣት
...................ከቶ ያየኝ የለም፤
አይቶኝም የሚቆም፣ (ዘጸ ፴፫፣፳)
ምስሌ ምንድነው፣ ከማን ጋር ልተያይ? (ኢሳ ፵፮፣፭)
ከቶ ማን አይቶኛል? ከደመናት በላይ፣ (ዘዳ ፴፫፣፳፮)
በምድር የተካኝ ፣እኔነቴን ወካይ፣
ከወዴት ተገኘ፣ሴትና ወንድ መሳይ? (ዘዳ ፬፣፲፮)
 ኦሪት ስትናገር፣ ቃሉን ለተቀባይ (ዘሌ ፳፮፣፩)
ያልጠበቀላትን ሕጓን ሻሪ፤ ነቃይ
ተለይቶ ይጥፋ፤ አዋጅ ባደባባይ።
በመዳፈር ቢሆን ወይም በመታበይ፤ (ዘኁ ፲፪፣፲)
የበደለ ቢኖር የሰው ግብረ ሀካይ፣
ለምጽ ይብቀልበት ጥፋቱ እንዲታይ፣ (፪ኛ ነገ ፳፮፣፲፰-፲፱)
ታውጆ ነበረ፣ ጥንት በኦሪቱ፣
አምላክ እንዲፈራ፣ እንዲታይ ክብረቱ፣
ለዓይን ዓይን ይከፈል፣ለጥርስም ይነቀል፣
የጣሰ ይወገር፣ የሻረ ይገደል፣
ቢሆን ኖሮ ሕጉ ዛሬም እንደጥንቱ፣
ማን ይኖር ነበረ ፣ሳይደርስ ለቅጣቱ?
ለምጽ ቢወጣበት በቆዳው በፊቱ፤
ጥቁር ፈረንጅ ሆኖ፣ ፈረንጅም በረዶን፣
ይለወጥ ነበረ፣ ያዳም ሰው መምሰልን፣
ተወግሮ ቢገደል፣ በድንጋይ ውርወራ፣
ሜዳውም ኰረብታ፣ ኮረብታም ተራራ፣
ይሞላው ነበረ የመቃብር ስፍራ።
ቢሆን ኖሮ ሕጉ፣ ዛሬም እንደጥንቱ፣
ማን ይገኝ ነበረ፣ ሳይደርሰው ቅጣቱ?
ቢሆን ኖሮ ሕጉ፣ ዛሬም እንደጥንቱ፣
ማን ይገኝ ነበረ፣ ፍጹም ከቅጣቱ?