Wednesday, March 14, 2012

ሃይማኖት፤ፍልስፍናና ሳይንስ!

ሃይማኖት፣ፍልስፍና እና ሳይንስ ምንና ምን ናቸው?

የካቲት 28/2012
ሃይማኖት፣ ፍልስፍና እና ሳይንስ ግኑኝነት ያላቸው ፅንሳተ ሐሣባት ናቸው ወይስ የተለያዩና የማይገናኙ? ተያያዥ ፅንሳተ ሐሣብ ከኾኑ ግኑኝነታቸው እንዴት ነው? በተመጋጋቢነት ወይስ በሌላ? በተመጋጋቢነት ከኾነ የትኛው መሠረት የትኛው ደግሞ ቅርንጫፍ ይሆናል? (የትኛው ለየትኛው መጋቢ ይሆናል?) የተለያዩ ከኾኑስ ተቃራኒ ናቸው ወይስ ሌላ ነው የመለያየታቸው ምሥጢር?
የሃይማትን፣ የፍልስፍናን እና የሳይንስን ግንኙነትና መለያየት ለማሳየት ብዙዎች ሦስቱን የሥነ አመክንዮ ሕግጋት እንደሚጠቀሙ ይታወቃል፡፡ በተለይም ሃይማኖትን ከፍልስፍና እና ከሳይንስ ጋር ይቀረናል ለማለት የሚጠቀሙት ያለ መቃረን ሕግን (Law of non-contradiction) ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ጽሑፍ መጀመሪያ የፍልስፍናን እና የሃይማኖትን ልዩነትና አንድነት በእነዚህ ሕግጋት በመገምገም፤ የሳይንስንና የሃይማትን ወይም የፍልስፍናንና የሳይንስ ግንኙነት በዚያ መንፈስ ወስደን አጠቃላይ ያላቸው ግንኙነት ምን እንደሚመስል በማነጻጸር እንመለከታለን፡፡
በዚህ መሠረት ሦስቱን የሥነ አመክንዮ ሕግጋትን በመጠቀም የሃይማትንና የፍልስፍና ግንኙነትና ልዩነት ምን እንደሚመስል እንቃኝ፡፡ ለማስታወስ ያህል እነዚህ የሥነ አመክንዮ ሕግጋት ሦስቱ የአስተምህሮ ሕግጋት (Laws of thought) በመባል ይታወቃሉ፡፡ በእንጊሊዘኛው በአንድነት አስቀምጠን ብናያቸው ‹‹“A” is “A” or “A” is not “non-A” but “A” can not be “A” and “non-A” at the same time and the same respect.›› የሚል ዐ.ነገር ይኖራቸዋል፡፡
  1. የኑባሬ ሕግ- Law of identity
በዚህ ሕግ መሠረት አንድ ነገር በተመሳሳይ ጊዜ፣ ኹኔታና ቦታ መኾን የሚችለው ያው ራሱን ብቻ ነው፡፡ በፊደል ብንወክለው ‹ሀ› ማለት ‹ሀ› ነው ማለት ይሆናል፡፡ ወይም ‹‹“A” is “A” or “A” is not “non-A”›› ማለት ነው፡፡
በዚህ ሕግ መሠረት ሃይማኖትና ፍልስፍና የሚኖራቸው ገለጻ ‹‹ሃይማኖት› ማለት ሃይማኖት ነው፡፡›› የሚል ወይም ‹‹ፍልስፍና› ማለት ፍልስፍና ነው›› የሚል ይዘት ነው፡፡ በሌላ በኩልም ቢኾን ‹‹ሃይማኖት› ማለት ‹ሃይማኖት ያልኾነ› ማለት አይደለም፡፡›› ተብሎ ሊገለፅ ይችላል፡፡ ‹ሃይማኖት ያልኾነ አይደለም› ማለት ‹ሃይማኖት ነው› ማለት ነው፡፡ የፍልስፍናም በዚህ መልክ ይገለጻል፡፡ ስለኾነም ሕጉ የሚገልጸው አንድን ፅንሰ-ሐሳብን ብቻ ነው፡፡ በዚህ ሕግ ተመሥርቶም የሃይማኖት ምንነት ብቻ ወይም የፍልስፍና ምንነት ብቻ ማብራራት ይቻላል እንጂ ሁለቱን ፅንሳተ-ሐሳብ በማነፃፀር ወይም በማቃረን መግለፅ አይቻልም፡፡ ይህ በመኾኑም ይህንን ሕግ ተጠቅመን ሃይማኖትና ፍልስፍናን መከፋፈል አንችልም፡፡
  1. ያለ መቃረን ሕግ- Law of non-contradiction
አንድ ነገር (ሰው፣ ፍጥረት፣ ክስተት፣…) በአንድ ጊዜ፣ ኹኔታና ሥፍራ ራሱንና ሌላውን መኾን አይችልም፡፡ በፊደል ሲቀመጥ ‹‹ሀ› ራሱን ‹ሀ›ን እና ‹ሀ ያልኾነ›ውን መኾን አይችልም፡፡› ማለት ይሆናል፡፡ ወይም ‹‹“A” can not be “A” and “non-A” at the same time and in the same respect.›› የሚል ገለጻ አለው፡፡
በዚህ ሕግ መሠረት ሃይማትና ፍልስፍና የሚኖራቸው ግኑኝነት‹‹ሃይማኖት›ራሱን ሃይማኖትና ‹ሃይማኖት ያልኾነ› መኾን አይችልም፡፡› ወይም ‹‹ፍልስፍና› ራሱን ፍልስፍና እና ‹ፍልስፍና ያልኾነ›ን መኾን አይችልም›› ማለት ይሆናል፡፡ ብዙን ጊዜ ግን በተለምዶ ‹ፍልስፍና እና ሃይማኖት ተቃራኒ ናቸው› በሚል ለመከራከር ይህንን ያለ መቃረን ሕግ ሰዎች ይጠቀሙበታል፡፡ አቃርኖ ማስቀመጥ ግን ትክክል አይደለም፡፡ ምክንያቱም፡-
i. ‹ሃይማኖት ያልኾነ› የሚለው ሐረግም ከሃይማኖት ውጭ ያሉ ፅንሳተ-ሐሳብን ይወክላል እንጂ ‹ፍልስፍና› ማለትን ብቻ አይገልፅም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ‹ፍልስፍና ያልኾነ› የሚለው ፅንሰ-ሐሣብም ከፍልስፍና ውጭ ያሉ ፅንሣተ-ሐሣብ ሁሉ ይወክላል እንጂ ‹ሃይማኖት› ማለትን አይገልፅም፡፡ ‹ፍልስፍልና ያልኾነ ሃይማኖት ነው› ወይም ‹ሃይማኖት ያልኾነ ፍልስፍና ነው› ማለትም ሕጋዊ አገላለጽ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ‹ሀ ያልኾነ› ‹ለ› ነው ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ‹ሀ ያልኾነ› ማለት ከ‹ሀ› ውጭ ያሉትን ሁሉንም ወይም የተወሰኑትን ፊደላት ሊወክል ይችላልና፡፡ ስለዚህ የፍልስፍና እና የሃይማኖት ፅንሣተ ሐሳብን በተቃራኒት መግለፅ መርሃዊ አጠቃቀም አይደለም፡፡
ii. ፍልስፍና እና ሃይማኖት ተያያዥ ፅንሣተ ሐሣብ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ሥነ መለኮት (Theology) የሚባለው የሃይማት አስተምህሮ ከፍልስፍና ትምህርት ክፍላት አንዱ መኾኑ ይታወቃል፤ ሞራላዊነትም የሃይማኖት ክፍል የኾነ የፍልስፍና ቅርንጫፍ ነው፤ እንዲሁም በምሥጢረ ህላዌ(Ontology) ሁለቱም ፅንሣተ ሐሣብ ግንኙነታቸው የጠበቀ ነው፡፡ ይህ በኾነበት ምንም ዓይነት የፅንሠ ሐሣብ ግንኙነትና አንድነት የሌላቸው አድርጎ ‹ፍልስፍና ያልኾነ ሃይማኖት ነው› ወይም ‹ሃይማኖት ያልኾነ ፍልስፍና ነው› የሚል አቀራረብ አግባባዊ የኾነ ያለ መቃረን ሕግ መሠረት የለውም፡፡
  1. የማዕከል መገለል ሕግ- Law of excluded middle
አንድ ነገር ወይ እሱው ያ ነገር ነው ወይም እርሱን ያልኾነ ነገር ነው፡፡ በፊደል ሲቀመጥ ‹‹ሀ› ወይ ‹ሀ› ወይም ‹ሀ ያልኾነ› ነው›› የሚል ይሆናል፡፡ በእንግሊዘኛው ለማሳየት ‹‹“A” is “A” or “non-A”›› የሚል ዐ.ነገር ይሠጠናል፡፡ ስለዚህ አንድ ነገር ወይ ራሱን መኾን ወይም ያለመኾን ኹለት አማራጮች ብቻ ይኖሩታል ማለት ይሆናል፡፡ የዚህ ሕግ ፅንሠ ሐሳብ ከሁለት አማራጮች ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ አድርጎ በመለያየት ያስቀምጣል፡፡ ለምሳሌ ‹ጥቁር ወይም ጥቁር ያልኾነ›፣ ‹ወይ እውነት ወይም ሐሰት›፣ ‹ሃይማኖት ወይም ሃይማኖት ያልኾነ›… ዓይነት አገላለፅ ነው ያለው፡፡
ይህንን ሕግ ተጠቅሞም ሃይማኖትና ፍልስፍናን መለያየት አስቸጋሪ ነው የሚኾነው፡፡ ምክንያቱም የሁለቱን ፅንሣተ ሐሣብ ግንኙነትና መለያየት በአግባብ ለማስቀመጥ አያስችልም፡፡ ‹ሃይማኖትና ፍልስፍና ግንኙነት አላቸው ወይስ የላቸውም?› የሚል ጥያቄ ብናነሣ መልሳችን ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም የሚል ሊኾን አይችልም፡፡ የተወሰነ ግንኙነት የሚኖራቸው ከኾነም ሕጉ የሃይማኖትና ፍልስፍናን መገናኛ በጥሶ አንዱን እውነት ሌላውን ግን ሐሰት በማለት ማስፈረጅ አያስችልም ማለት ነው፡፡ ፍልስፍና እና ሃይማኖት ደግሞ (ከላይ በመቃረን ሕግ እንደጠቀስነው) የሚገናኙባቸው የዕውቀት (አስተምህሮ) ክፍሎች አሏቸው፡፡ ስለዚህ ሌላ ፅንሠ ሐሣብ እንደሌለ በመቁጠር ሁለቱን ብቻ ባማራጭነት ወስዶ አንዱን እውነት ሌላውን ግን ሐሰት፤ አንዱን ትክክል ሌላውን ግን ስህተት አድርጎ መፈረጅ አግባብነት የለውም፡፡
ከዚህ በላይ ባየነው መሠረት ሃይማኖትና እና ፍልስፍናን አቃርኖ መከራከር አይቻልም፡፡ ስለዚህ ሥነ አመክንዮዊ የአስተምህሮ ሕግጋት ተጠቅሞ ሃይማኖትና ፍልስፍና የሚቃረኑ ወይም ምንም ግንኙነት የሌላቸው አስመስሎ ማቅረብ አግባብ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ሕግጋቱ የአንድን ፅንሠ ሐሣብ ኑባሬ፣ ከሌሎች ፅናሣተ ሐሣብ መለየትና ያለውን አማራጭነት ያስቀምጣሉ እንጂ ከሌላ አንድ ፅንሠ ሐሣብ ጋር የሚኖረውን የግንኙነት መስተጋብር እና ቀጥታ መቃረን መቻል አይገልፁም፡፡ ስለዚህ ሃይማኖትና ፍልስፍና ይቃረናሉ፣ ፍልስፍና ካነበብክ ሃይማኖትህን ትክዳለህ እና የመሳሰሉ ገለጻዎች ሥነ አመክንዮአዊ መሠረት የሌላቸው ያለማወቅ አገላለፆች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ መልክ ‹የሃይማኖትንና የሳይንስን›፣ ‹የፍልስፍና እና የሳይንስን› ፅንሣተ ሐሣብ መተንተንና ማብራራትም ይቻላል፡፡ ኾኖም ያንንም ከዚህ በላይ በተመለከትነው መንፈስ መቃኘትና መረዳት ይገባናል፡፡ ያለበለዚያ የአገላለፅ ድግግሞሽ ይኾንብናል፡፡ ዋናው የሕግጋቱን አጠቃቀም መረዳት ነው፡፡
ይህ ከኾነ የሃይማኖት፣ የፍልስፍና እና የሳይንስ ግንኙነት ምን ይመስላል?› ለሚለው ጥያቄ የሚከተለው ሰንጠረዥ በማነፃፀሪያነት ማየት ይቻላል፡፡
መሠረቱ
ሃይማኖት
ፍልስፍና
ሳይንስ
መሠረታዊ ትርጉሙ
መሠረታዊ ትርጉሙ ማመንና መታመን ነው፡፡
ጥበብን (እውነትን፣ ዕውቀትን) ማፍቀርና መሻት ወይም በጥበብ መደነቅ ነው፡፡
የቁስ አካል አፈጣጠርንና አሠራርን የማስተዋል፣ የመፈተንና የመተንተን ሥርዓታዊ አስተሳሰብ ነው፡፡
መሠረታዊ ጥያቄው
በማን?› በሚል ጥያቄ መልስ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡
ምን?› የሚለው ጥያቄ መነሻው ነው፡፡
እንዴት?› የሚለው የፍልስፍና ጥያቄ መልስ ማረጋገጪያ ነው፡፡
የጥናት ወሰኑ (አድማሱ)
ረቂቃንና ግዙፋን አካላት መኖራቸውን ይቀበላል፡፡ እምነትን፣ ዕውቀትን፣ ሥነ-ምግባርንና አተገባበሩን ያጠቃልላል፡፡
የጥናቱ መሠረት ምሥጢረ ህላዌ (ontology)፣ የጥናት ስልቱ የሥነ አመክንዮ ሕግጋት፣ መቋጫውም ሳይንሳዊ ማረጋገጫ ያለው መልስ ነው፡፡ መልስ ላልተሰጠው ለየትኛውም የሳይንስ ዕውቀት መሠረት ነው፡፡
የግዙፋን አካላት (ፍጥረታት) መኖርና ቁሳዊ ጥቅሞች ላይ ብቻ ያተኩራል፡፡ የእነሱም ዕውቀትና አተገባበር ያካልላል፡፡
የዕውቀት ምንጩ
ዕውቀት የሚገኘው በራስ በሚደረግ ምርምር ብቻ ሳይኾን በአምላክ ገላጭነትም ጭምር ነው ይላል፡፡
እንደይታው ይሆናል፡- በሰው ልጅ ላይ ቀድሞ ተጽፎበታል ወይም በልምድ ይሰበስበዋል ወይም በሁለቱም ማግኘት ይችላል የሚል፡፡
ዕውቀትን ማግኘት የሚቻለው በራስ በሚደረግ መመራመር ብቻ ነው ብሎ ያምናል፤ በተለይም በልምድ በመሰብሰብ፡፡
የመኖር ዋስትናው (ግቡ)
ከሞት በኋላ ሕይወት ይኖራል ይላል፡፡
በአብዛኛው እርግጠኛ መኾን አይቻልም፡፡
ከሞት በኋላ ሕይወት መኖሩን አይቀበልም፡፡
መሠረታዊ ዶግማዎች
ቋሚ የማይለወጡ ዶግማዎች አሉት፡፡ ለምሳሌ የእግዚአብሔር መኖር፣ ፍጥረትን መፍጠሩ፣ ጠባቂነቱና መግቦቱ፡፡
በየትኛው ነገር ህልውና፣ ተፈጥሮ፣ አሠራር እና አረዳድ (ዕውቀት) ላይ ጥያቄ ያነሳል፡፡ እርግጠኛ ባለመኾን በሃይማትና በሳይንስ መሃል ይዋዥቃል፡፡
እንደ ሁኔታው መሻሻል ወይም መለወጥ መሠረታዊ መርሁ ነው፡፡


ከዚህ በላይ በሰንጠረዥ የተቀመጡትን ነጥቦች በተወሰነ ደረጃ እያብራራን እናነጻጽራቸው፡፡
ሥርዎ ቃላዊ ትርጉም፡-
በዚህም ሃይማኖት ማለት ማመንና መታመን የሚል ትርጉም ያለው መኾኑ ተገልጻል፡፡ በሃይማኖት ማመንም ከዓለመ-ፍጥረቱ ውጭ ያለ አካል መኖሩን፣ ፍጥረታትን መፍጠሩንና ከፍጥረቱም ጋር ግንኙነት እንዳለው አምኖ መቀበል ሲኾን መታመን ደግሞ ከዓለመ-ፍጥረቱ ውጭ ያለው አካል የሰጠውን አደራ መጠበቅ ነው፡፡ በመኾኑም ሃይማኖት ከአምላክ ጋር የሚደረግ ግንኙነት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በማመንም ከአምላክ ጋር ግኑኝነት የሚያደርገው ምክንያታዊ አእምሮ ያለው ሰው ነው፡፡ ስለኾነም የሰው እምነት ግልፅ ኾነው በታወቁና በግልፅነት ባልታወቁ ማስረጃዎችና ምክንያት ላይ ይመሠረታል፡፡ ስለኾነም ነው ዕምነት የምክንያታዊ ተጠየቅ እሳቤዎች መደምደሚያ ነው የሚባለው፡፡
ፍልስፍና ደግሞ ጥበብን አፍቅሮ ምንነቷን መመርመር በምርምሩም እውን የኾነችውን እውነት ማግኘት ነው፡፡ ይችም እውነት የመሠረታዊ ህልው ነገር ወካይ ናት፡፡ ፍልስፍናም የሚመረምረው ይችን የሁሉም ነገር ምንጭ፣ ምክንያተ ህልዌና የአኗኗር ዋስትና ለይቶ በማወቅ ከሌሎች ብዙ ህልውን ነገሮች ጋር ያላትን ግኑኝነት ለመረዳት ነው፤ የዚችም መሠረታዊ እውነትና ከሌሎች ጋር ያላት ግኑኝነት መታወቅ ጥበብን ፍፁም፣ ምሥጢሯ የተፈታና ግልጽ ያደርጋታል፡፡ እሷ ተለይታና ተሟልታ ከታወቅችም የህልውነት ምሥጢር ሁሉ ይፈታል፡፡ ይህ ከኾነም የፍልስፍና መሠረታዊ ጥያቄ ተመልሶ ጥበብ (እውነት) የምትታመን ኾነች ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከሃይማኖት መሠረታዊ ትርጉሞች አንዱ ከኾነው ማመን ጋር ይገናኛል፡፡
በሌላ በኩል ሳይንስ ነገሮችን በመፈተሽ፣ በመመርመር፣ በመፈተንና በማስተዋል ለማረጋገጥ የሚረዳ ሥርዓታዊ አስተሳሰብና ትግበራ ነው፡፡ ሥርዓታዊ አስተሳሰብም መደምደሚያ ወይም መቋጫ ሊኖረው የሚችለው ተዓማኒነት ሲያገኝ ነው፡፡ ተዓማኒነት ካለም ዕምንት ይኖራል፡፡ በዚህ የተነሳ ሳይንስ የዕምነት ማስገኛ ዕውቀት እንጂ ከእሱ ውጭ የኾነ ፅንሰ ሐሳብ አይደለም፡፡ ሳይንስ የፍልስፍና ጥያቄም ማረጋገጫ መልስ በመስጠት የሃይማኖት መጋቢ ዕውቀት መሣሪያው መኾን ይችላል፡፡
መሠረታዊ ጥያቄው፡-
በሰንጠረዡ በሁለተኛ ነጥብነት እንደተቀመጠው ሃይማኖት ዓለመ-ፍጥረቱ ‹በማን?› ተመፈጠረ በሚል ጥያቄ መልስ ላይ ይመሠረታል፤ መልሱም ግልፅ ነው በልዕለ ኃያል እግዚአብሔር የሚል፡፡ ይህንን መልስም መሠረት በማድረግ ‹ይህ ዓለም ( መንፈሳዊና ቁሳዊ ፍጥረታት በሙሉ) ምንድነው? እንዴት ተሠራ? ለምን ሊፈጠር ቻለ? …› የሚሉ ጥያቄዎችን ጠይቆ መልሳቸውን ለማግኘት ይጥራል፡- ከምርምር አኳያ፡፡ መልሳቸውንም ፍጥረታትን በመመልከት፣ አምላክ ለሰዎች ያደረጋቸውን መገለጦች መዝግቦ በማገናዘብና ከመሳሰሉት ያገኛል፡፡ የፍጥረቱን በጥበብ መሠራትና የአምላኩን መገፅ እያደነቀም ከፈጣሪው ጋር ግኑኝነት በማድረግ ይኖራል፡፡
የፍልስፍና መሠረታዊ ጥያቄም ‹ምን?› የሚለው የህልውነት(existence) ጥያቄ ነው፡፡ በዚህ ጥያቄ ላይ ተመሥርቶም ‹ለምን?›፣ ‹በማን?›፣ ‹እንዴት?› እና ‹ መቼ?› የሚሉ ጥያቄዎችን በቅደም ተከተላቸው መሠረት እያነሣ በመጠየቅ መልሳቸውን ለማግኘት ይጥራል፡፡ ኾኖም በፍልስፍና የመጀመሪያዋን ጥያቄ እንኳን የተሟላ መልስ ለማግኘት ስለሚያስቸግር ፍልስፍና በአብዛኛው በጥያቄ እንደተንጠለጠለ ይኖራል፡፡ ኾኖም ፍልስፍና በጊዜ ቆይታ ሳይንስን ወልዷል፡፡ በሳይንስም ብዙ መልሶችን ማግኘት ችሏል፡፡
ሳይንስ ደግሞ ‹እንዴት?. ለሚለው የፍልስፍና ጥያቄ ማረጋገጫ መልስ ይሰጣል፡፡ መልሱን የሚያረጋግጠውም የተፈጥሮ ሥሪትን፣ ሕግጋትንና አኗኗርን መሠረት አድርጎ በመመርመር ነው፡፡ ለምሳሌ ፍልስፍና ‹ሰው ለምን በመሬት ላይ ተጣብቆ ይኖራል? ወይም ከመሬት ወደ ከባቢ አየር የምንወረውራቸው ድንጋዮች ለምን ተመልሰው መሬት ላይ ያርፋሉ?…› የሚል ጥያቄን በመጠየቅ የተለያየ ግምታዊ መልሶችን ለመስጠት ሲሞክር ኖርዋል፡፡ ሳይንስ በመሬት ስበት አማካይነት እንደኾነ በፍተና ፈትኖ ማረጋገጫ ከሰጠው በኋላ ግን የፍልስፍና ጥያቄ ማጠንጠኛ መኾኑ ቀርቶ የሳይንስ ዕውቀት ክፍል ሊኾን ችሏል፡- በስበተ መሬት ንድፈ ሐሣብ መሠረት፡፡ ስለኾነም ሳይንስ ይህ ዓለም እንዴት እንደተሠራ ማወቂያ የሚኾን የፍልስፍና መሣሪያ (ዕውቀት) ነው፡፡ የሳይንስ ውጤትም አሳማኝ ኾኖ ሲገኝ ተቀባይነት ያገኛል፤ ይታመንበታል፡፡ በዚህ አንጻር ከዕምነት (ሃይማኖት) ጋር አይጣላም፡፡ ይህንን በዚህ ላይ አቁመን ወደ 3ኛው ነጥብ እንሻጋገር፡፡
የጥናት ወሰኑ፡-
ሃይማኖት የረቂቃንና የግዙፋን አካላት (ፍጥረታት) መኖርን አምኖ በመቀበል ላይ የተመሠረተ እሳቤ ነው፡፡ በሃይማኖት ረቂቃን (መንፈሳዊ) የኾኑት እግዚአብሔር፣ መልአክት፣ የሰው ነፍስ፣ እርኩሳን መናፍስ… መኖራቸው የታመበት ነው፡፡ እንዲሁም ገነትንና ሲዖልን፣ መንግሥተ ሰማያትንና ገሐነብ እሳትን… የመሳሰሉ የተለዩ ሥፍራዎች እንዳሉ ይታመናል፡፡ ስለዚህ በሃይማኖት መንፈሳዊ እና ግዙፋዊ ፍጥረታት መኖራቸው የታመነበት እውነት ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይኾን ሃይማኖት በውስጡ እምነት፣ ዕውቀትና ሥነ-ምግባርን እንዲሁም የማኅበራዊ ትስስሮችን ያካትታል፡፡ በዚህ የተነሣ ሃይማኖት ‹ሁሉን ፈትኑ መልካሙን ያዙ፡፡› ይላል እንጂ ዝም ብላችሁ በምርምር ዛቁኑ አይልም፡፡ ሥነ ምግባር አልባ ምርምርም ዋጋ የለውም፡፡
በፍልስፍና ግን ሃይማኖት ራሱ የክርክር መድረክ ነው፡፡ ለምሳሌ ‹የእግዚአብሔር ህልውነት› አንድ ፍልስፍና የክርክር ክፍል ነው፡፡ ‹መንፈሳዊ ረቂቃን ፍጥረታትስ በህልውነት የሚገኙ ናቸው አይደለም?› ሌላው የፍልስፍና መከራከሪያ ርእስ ነው፡፡ ፍልስፍና የማልዳስሰው የዕውቀትና የህልውነት ክፍል የለም የሚል አቋም ስላለው፤ ትኩረቱም ከመልስ ይልቅ ጥያቄ ላይ ስለኾነ ከሃይማኖት እሳቤ ግማሽ ክፍል ይወስዳል፡፡ በጥቅሉም ፍልስፍና የምሥጢረ ህላዌ ጥያቄ በማንሳት ተጀምሮ በሳይንሳዊ መልስ ማረጋገጫ በመስጠት ይቋጫል፡፡ በእነዚህ የጥናት አድማሶች ውስጥም የማያነሳው ጥያቄና የማይሠጠው መላምት የለም፡፡ በዚህ የተነሣም ከሳይንስ መሠረት ጋር የተያያዘ ጥናት ለመኾንም ይገደዳል ማለት ነው፡፡
ሳይንስ ግን በግዙፋን ( በቁስ) አካላት ላይ ብቻ የሚደረግ ተፈጥሮንና ጥቅምን መመርመሪያ መሣሪያ ነው፡፡ ምክንያቱም ሳይንስ በዓይን አስተውሎ እና በመሣሪያ ተጠቅሞ ፈትኖ ማረጋገጥን የሚፈልግ ጥበብ ነው፡፡ በመኾኑም ሳይንስ ‹ሃይማኖት አሉ› ከሚላቸው አካላት ውስጥ የተወሰኑትን ፍጥረታት ብቻ ይመረምራል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ስለ የሰው ነፍስ፣ መልአክት፣ እርኩሳን መናፍስት፣ ጥንቆላና መተት፣ እግዚአብሔር፣… ሳይንስ የሚያነሳው ነገር የለም፡፡ እንዚህ ነገሮችን በፍተና፣ በአስተውሎት፣ በቅንብርና በመሳሰሉት የማጥኛ ስልቶች ተጨባጭ አድርጎ ማረጋገጥ አይቻልምና፡፡ እንዲሁም ሳይንስ ከሚታወቅ፣ ከሚታይና ከሚዳሰስ ነባራዊ ዓለም (ነገር) ተነስቶ ያጠናል እንጂ በመገለጥ ተጠቅሞ ስውርና የማይጨበጡ ነገሮችን በማጥናት ስለ እነሱ ተፈጥሮና አኗኗር ማረጋገጫ አይሰጥም፡- ስልቱና አድማሱ ካልተቀየረ በስተቀር፡፡ ይህ ከኾነም የሳይንስ ምርምር በተፈጥሮ ሥሪት ላይ ብቻ ከተወሰነ ስለ እግዚአብሔርና ስለረቂቃን ነገሮች መመስከር አይችልም፡፡ ከአድማሱ ውጭ ነው፡፡ በጥቅሉ ሳይንስ ‹ሁሉን በጥልቀት መርምሮ ማረጋገጥ› የሚል መርህ ይከተላል፡፡ በቁስ አካላት ላይ በሚያደርገው ጥልቅ ምርምርም ለዕምነት ግብዓት ይሆናል፡፡ ከዚህ አንጻር በሃይማኖት አድማስ ውስጥ ይካተታል፡፡
የዕውቀት ምንጩ:-
ወደ አራተኛው ነጥባችን ስንሸጋገር በሃይማኖት ዕውቀት በአምላክ ገላጭነትና ከራስ በሚደረግ ምርምር በሁለት መንገዶች ይገኛል፡፡ ምክንያቱም ይህ ዓለመ ፍጥረት (universe) በእግዚአብሔር ተፈጥሮ እየተጠበቀ ይገኛል፤ እንዲሁም የፈጠረው ፈጣሪው የእሱን ህልውነት በፍጥረቶቹ ላይ ገልጽዋል፤ በተለይ የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጥረታት የተለየ የዕውቀትና የሞራል ሀብታትን የታደለ (የተቸረው) ስለኾነ አምላኩ ራሱን በተለያየ መልክና ሁኔታ እየገለፀ አሳውቆታል፤ ያሳውቀዋልም የሚል የዕውቀት ማግኛ መንገድን ይገልጻል፡፡ ይህ ብቻ ሳይኾን የሰው ልጅ በተፈጥሮው ዕውቀት እስከቻለው ድረስ በመመራመር ዕውቀትን ገንዘቡ ያደርጋል፤ ኾኖም ሁሉን ዕውቀት በራሱ በሚያደርገው ምርምር ብቻ መረዳትና ማረጋገጥ ስላማይችል (የዕውቀት ውስንነት ስላለበትና ስህተት ፈፅሞ የሚገኝበት ዘመን ውስጥ ስላለ) የእግዚአብሔር ገላጭነት ያስፈልገዋል የሚል አቋም አለው፡- ሃይማኖት፡፡
በፍልስፍና ዕውቀት የሚገኘው በአብዛኛው በአንድ በኩል በሰው ልጅ አስተውሎታዊ ምርምር ነው፡፡ በዚሁ መንገድም በምንጭነት የሚወሰዱ ሁለት ዓይነት የዕውቀት መገኛዎች አሉ፡፡ አንደኛው የሰው ልጅ በተፈጥሮው ዕውቀት ተጽፎበታል፤ ትምህርትም የሚያስፈልገው ይህንን የተጻፈበትን ዕውቀት ገልጾ ለመጠቀም ነው የሚል ሲኾን፤ ሁለተኛ ደግሞ ዕውቀት በሰው ልጅ ላይ በተፈጥሮው የተጻፈበት ሳይኾን በልምድ በማጠራቀም የሚያውቀው እንጂ አእምሮው እንደ ነጻ ወረቅ ኾኖ የሚወለድ ነው ይላል፡፡ የሁለቱን የዕውቀት መገኛ ምንጮች በማመቻመች የሚሞክር ክፍልም አለ፡፡ በየትም ቢኾን የሰው ልጅ ዕውቀት ከሌላ አካል በችሮታ የሚሠጠው ሳይኾን ባራስ ምርምርና ጥረት የሚገኘው ነው ባይ ነው፡- ፍልስፍና፡፡
ልክ እንደ ፍልስፍና በሳይንስም ዕውቀትን ማግኘት የሚቻለው ከራስ በሚደረግ ምርምር በአንድ መንገድ ብቻ ነው፡፡ በአብዛኛውም ከፍልስፍና አስተምህሮ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ኾኖም ሳይንስ የነገሮችን መስተጋብራዊ ሁኔታና ግንኙነት በማስተዋል፣ በመፈተንና በማነጻጸር የሚያጠና ስለኾነ የሰው ልጅ ቀድሞ በተፈጥሮው ዕውቀት ተጽፎበት ይገኛል አይልም፡፡ ከዚህ ይልቅ በልምድ የሚሰበሰብ ዕውቀት ትኩረቱ ነው፡፡ ስለዚህ ሳይንስ በፍልስፍና የዕውቀት ማግኛ መንገዶች አንደኛውን በልምድ የሚገኘት ዕውቀትን ይደግፋል ማለት ነው፡፡
ይሁንና እንደሚታወቀው የዓለመ-ፍጥረቱ ፍጥረታት መገኘትና ህልውና በሰዎች አስተሳሰብ የማይፈታ እንቆቅልሽ እንደኾነ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳን አንዳንድ ግምታዊ መላምቶች በሳይንቲስቶች ቢሠጡም ከማወናበድ ያለፈ አጥጋቢነት ያለው ንድፈ-ሐሳብ ማቅረብ አልቻሉም፡፡ እንኳን የዓለመ-ፍጥረቱን ምንነት የሰውን አዕምሮ ሥሪትና የአስተሳሰብ አድማስ ለይቶ ማወቅ የቻለ ተመራማሪ (ሳይንቲስት) አልተገኘም፡፡ በዚህ የተነሣ በሃይማኖት ስለ ፍጥረታት አጋኛኘትና አኗኗር ማወቅ የሚቻለው በሰዎች በሚደረግ ምርምር ብቻ ሳይኾን ከፍጥረት ውጭ ባለ አካል ገላጭነት ጭምር ሊኾን ግድ ነው፡፡ ይህንን የተረዱ አንዳንድ ሳይንቲስቶችም የዓለመ-ፍጠረቱ መገኘት እንቆቅልሽን ለመፍታት የሃይማኖት መጻሕፍትን ጭምር በመመርመር ላይ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ‹እግዚአብሔር በመጀመሪያው ቀን ሰማይና ምድርን ፈጠረ፡፡› በማለት የጊዜን፣ የሥፍራንና የፍጥረታትን በአንድ ላይ ከእነሱ ውጭ በኾነ አካል እንደተገኙ ተደርጎ መገለፁ የእንቆቅልሹ መፍቻ ውል ሊኾን ይችላል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ስለዚህ ዕውቀት በህዋሳታችን በራሳችን ሰብስበን የምንዘልቀው ብቻ ሳይኾን በውጭ አካል ገልጾ ያሳወቀንን አምኖ በመቀበል የምናገኘውም የሚኾን ይመስላል፡፡
የሰው ልጅ ሕይወት ዋስትና፡-
በአምስተኛው ነጥብ እንደተገለፀው በሃይማኖት የሰው ልጅ ከሞተ በኋላ ሌላ ሕይወት አለው፡፡ ማለትም ሰው የማትሞት ነፍስ አለችው፡፡ ስለኾነም ከዚህ ዓለም ውጭ ለነፍስ መኖሪያ የሚኾን ሥፍራ አለ፡፡ በፍልስፍና ግን በአብዛኛው እርግጠኛ መኾን አይቻልም፡፡ በሳይንስም ነፍስ መኖር ተቀባይነት የለውም፡፡ ምክንያቱም ‹ሰው ነፍስ አለው› የሚለውን ሳይንሳዊ ማረጋገጫ መስጠት አይቻልም፤ እንዲሁም ከሞት በኋላ ሕይወት ሊኖር ይችላል የሚለውን ማረጋገጥ ከባድ ነው፡፡ ስለኾነም ፍልስፍና ሳይንስ የሚቀበሉት የሰው ልጅ እስከሚሞት ድረስ በሕይወት መኖሩን ብቻ ነው፡፡ እስከሚሞት ድረስ በሕይወት መኖሩ ደግሞ በሃይማኖትም ተቀባይነት ስላለው ሳይንስ የሃይማኖትን አንዱን ክፍል ብቻ ወስኖ የሚያጠና መኾኑ እርግጥ ነው፡፡
መሠረታዊ ዶግማ፡-
በመጨራሻም ሃይማኖት መሠረታተ-እምነት (doctrines or dogmas) አሉት፡፡ ለምሳሌ የፈጣሪ መኖር፣ ፍጥረቱን መፍጠሩ፣ ከፍጥረቱ ጋር ግንኙነት ማድረጉ፣ ሰው ነፍስ ያለው መኾኑ፣ ከሞት በኋላ ሕይወት ያለ መኾኑና የመሳሰሉት መሠረታተ-እምነት አይለወጡም፤ አይቀያየሩም፡፡ ፍልስፍና መጠየቅ መርሁ ስለኾነ የተረጋጋ ዶግማ የለውም፡፡ መጠራጠር ነው የሚሉ ግን አሉ፤ አባባላቸው አጥጋቢነት ባይኖረውም፡፡ ወደ ሳይንስ ስነዞር እሳቤው የተመሠረተው በመሻሻል ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ ስንት የተወራለት የዳሪዊን የዝግመተ-ለውጥ ንደፈሐሳብ ቀውስ ውስጥ ስለገባ (theory in crises) እየተጣለ መጥቷል ይባላል፡፡ ስለዚህ የተሻለ አሳማኝ ንድፈ-ሐሳብ ሲቀርብ በሌላ እየተተካ መሔድ የሳይንስ ግደታ ነው፤ መሻሻልም አለበት፡፡ በዚህ መልክ እየተሻሻለ አሳማኝነት ሲኖረውም ወደ እምነት ግብዓትነት ያድጋል፡፡ ሃይማኖት ግን መሠረታዊ ዶግማዎቹን አይቀይርም፡፡ ቆይ! ይሻሻልስ ቢባል የእግዚአብሔር መኖር በምን ዓይነት መልኩ ሊለወጥ ይችላል? ፍጥረቱን ፈጥሯል ማለት አልፈጠረም በሚል ነው የሚቀየረው? መሻሻል ስንልስ የመንፈሳዊ ነገሮችን መኖር መካድ የቁስ አካላትን መኖር ብቻ መቀበል ማለት ነው? … ስለኾነም የሃይማኖት መሠረታተ-እምነት ቋሚ የማይለወጡ መሆናቸው ቢያንስ እምነት ባላቸው ሰዎች ዕይታ ትክክል ነው፡፡ በፈላስፎችና በሳይንቲስቶች አንጻር ደግሞ ማወቂያና ማሻሻያ መርህ ይሆናሉ፡፡

በአጠቃላይ ከዚህ በላይ የተመለከትናቸው ነጥቦች ሳይንስ ውስን ክፍሉን በጥልቀት የሚመረምር ጥበብ ስለኾነ ለሃይማኖት ግብዓት መኾን እንደሚችል ያስገነዝበናል፡፡ ፍልስፍናም በጠያቂነት ጠባዩ የሃይማኖት መመዘኛ ይሆናል፡፡ ስለኾነም ነው እንጂ ብዙ ተመራማሪ ሳይንቲስቶችና ፈላስፎች የሃይማኖት ሰዎችም የኾኑት አንዳንድ ተችዎች እንደሚሉት የእንቆቅልሽ አመክንዮ እይተገበሩ አይደለም፡፡ እምነትን መሠረት አድርገው ከሚመረመሩ ሳይንቲስቶች መካከል የነበረው (ቢያንስ 100 ዓመታት የዓለማችንን ሥልጣኔ ወደ ፊት እንዲራመድ አድርጓል የተባለለት) የአርበት አይንስታይን ዓለመ-ፍጥረቱን ለመመርመር ያነሳሳውን ምክንያት መጥቀስ እዚህ ላይ የተሻለ ይሆናል፡፡ እሱ እንዳለው ከኾነ የሚመራመረው እግዚአብሔር ዓለምን እንዴት አድርጎ እንደሠራት ለማወቅ ነው፡፡ ‹‹I want to know how God created this world, I am not interested in this and that phenomena in the spectrum of this or that element. I want to know this thought; the rests are detail.›› ነበር ያለው፡፡ እንደ አይንስታይን ያሉ ተመራማሪዎች ደግሞ አሁንም ብዙ ናቸው፤ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ በቅርብ ጊዜ በተደረገ ጥናት አሜሪካ ውስጥ ከሚገኙ ሳይንቲስቶች መካከል ከ60 በመቶ በላይ የሚኾኑት በእግዚአብሔር መኖር አምነው ምርምራቸውን እንደሚያከናውኑ ማወቅ ተችሏል፡፡ ጥልቅ የፍልስፍና እሳቤዎችን በማቅረብ የታወቁ ፈላስፎችም ምርምራቸው የእግዚአብሔርን ሀልዎት ያረጋገጠ ኾኖ ነው የሚገኘው፡፡ ‹እግዚአብሔር የለም› በማለት የሚፎክሩት ‹በከመ ይቤ› መርህን የሚከተሉ ፈላስፎች ናቸው፡፡
ማሳረጊያ
አንድ የሳይንስ ተመራማሪም (ሳይንቲስት) ሥራው በምክንያታዊ ተጠየቅ የተሠራችውን ተፈጥሮ ውል ለይቶ ማወቅ ነው፡፡ ሳይንስም ፍልስፍና ለጠየቀው የተፈጥሮ ክስተት ሥሪት፣ ምክንያተ-ሥሪት፣ ትስስራዊ ግንኙነትና ውጤታዊ ምንነት መልስ ማረጋገጫ መሣሪያ የኾነ ዕውቀት ነው፡፡ ስለኾነም ፍልስፍናዊ መሠረት የሌለው ሳይንስ የለም፡፡ ፍልስፍናም ተጠየቃዊ እሳቤን የሚጠይቅ ጥበብ ሲኾን መቋጫውም እምነት ነው፡፡ ፍራንስስ ባኮን እንዳለው ‹‹ ትንሽ የፍልስፍና ዕውቀት የሰውን ኅሊና ወደ ኢ-አማኝነት ይወስዳል፤ የፍልስፍና ጥልቅ ግንዛቤ መኖር ግን ኅሊናን ወደ ሃይማኖት አማኝነት ያደርሰዋል፡፡› ስለዚህ ሳይንስ የፍልስፍና ጥያቄ መልስ ማረጋገጫ ሲኾን ፍልስፍና ደግሞ የዕምነት ግብዓት ነው፤ እምነት ደግሞ የሃይማኖት መሠረት፡፡ በመኾኑም ሳይንስ፣ ፍልስፍና እና ሃይማኖት ተጠየቃዊ ግንኙነት ያላቸው ተመጋጋቢ እሳቤዎች እንጂ ተቃራኒዎች አይደሉም፡፡
አይንስታይን እንዳለውም ‹ሳይንስ ያለ ሃይማኖት ሽባ ነው፤ ሃይማኖትም ያለ ሳይንስ እውር ነው፡፡› ስለዚህ የሁለቱ እሳቤዎች ግንኙነት እንዳበትና ልጅ ያለ ዝምድና አለው፡፡ ሳይንስን ሃይማኖት ከፍልሰፍና ጋር ተጋብቶ ወልዶታል፡፡ ከሃይማኖት ውጭ የተወለደ ሳይንስ ግን የፍልስፍና ድቃላ ስለኾነ ባለጌ (ሥነ-ምግባር አልባ) ጥበብ ይሆናል፡፡የዚህም ትረፉ ጥፋት ነው፡፡ ስለኾነም ከሃይማኖት እሳቤ ውጭ የኾነ ሣይንስ የለም፤ ከዕምነት ክበብ የወጣሁ መስሎት አቅጣጫና መድረሻ በሌለው መንግድ ‹ሳይንስ!›፣ ‹ሳይንስ!› በማለት የሚለፍፍ ሳይንቲስትም የጥፋት መልዕክተኛ እንጂ ስብዕና ያለው ተመራማሪ አይደለም፡፡ ‹ይቤ ሳይንስ› ብለው የሚለፍፉ ፈላስፎችም እንደዚሁ፡፡
በጥቅሉ የሰው ልጅ አዕምሮ የተፈጥሮ ክስተቶችን በምክንያት እያገናዘበ ያስባል፡፡ ምክንያታዊ እሳቤውም አሳማኝነት ያለው መቋጫ ያስፈልገዋል፡፡ አሳማኝ መደምደሚያ ሲያገኝም ያምናል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ወ/ሕይወት ‹‹ለማመን እንጂ ላለማመን ምክንያት አያስፈልግም፡፡›› እንዳለው እምነት የተጠየቃዊ እሳቤ ውጤት ነው፡፡ ተጠየቃዊ እሳቤ ደግሞ የፍልስፍና የደም ስርስ ሲኾን ሳይንስም በዚህ የደም ሥር ሕይወትነት አግኝቷል፡፡ በዚህ የተነሣም ሃይማኖት፣ ፍልስፍና እና ሳይንስ ተመጋጋቢ ፅንሣተ ሐሣብ ናቸው ማለት እንችላለን፡፡
source- kassahunalemu.wordpress.com