Thursday, March 15, 2012

ወሲብን መፈለግና ውጤቱን መጥላት አይቻልም!

ዝሙትና ማመንዘር፣ዘርን መዝጋትና ወሲብ እፈልጋለሁ! በስጋም ሆነ በነፍስ የሚታጨደውን ዋጋ ግን አልፈልግም?
«እንጀራ እበላለሁ፣ ውሃን  መጠጣት ግን  አልፈልግም»እንደማለት ነው።
ይሄ ነገር ይቻል ይሆን? እስካሁን እኔ አልሰማሁም፣ አላነበብኩምም። የቻለ ካለ ወይም  ወይም በዓለም አስደናቂ ታሪኮች መዝገብ ላይ ሰፍሮ አይቻለሁ የሚል ጽፎልን ሊያስደንቀን ይችላል። በእርግጥ ቢጽፍልንም አናምነውም። ምክንያቱም የሰው ሰውነት 66% የተገነባው በደም ነው። ደም ደግሞ ያለውሃ ደም ሳይሆን እንጨት ነው። ይደርቃል ማለት ነው። ስለዚህ «እንጀራ እበላለሁ፣ ውሃ ግን መጠጣት  አልፈልግም» የሚል ቢኖር ጤንነቱን ልንጠራጠር የግድ ይሆናል። እናንተስ ምን ትሉት ይሆን? ለመንደርደሪያ ተጠቀምኩኝ እንጂ  ስለእንጀራ መብላትና ውሃን ለመጠጣት አለመፈለግ ጉዳይ ሳይንሳዊ ትንተናን ለመስጠት የጽሁፌ ዓላማ አይደለም። ግን እንደዚያ ከማለት ተለይቶ የማይታይ  ሃሳብን በአንጻራዊነት ለመቃኘት በመፈለግ ነው። ልክ «እንጀራ እበላለሁ፣ ውሃ ግን መጠጣት አልፈልግም» እንደማለት ዓይነት የሚነገር የሰው ሃሳብ!! ይህን ሃሳብ ብዙ መንፈሳውያን ሰዎች ሲያስተምሩት አይሰማም። ምናልባትም በእነሱም ዘንድ አለመነሳቱ እነሱም ይህንኑ ሃሳብ በሕይወታቸው ውስጥ እየተለማመዱት ይሆናል። ታዲያ ምን እንበል? እግዚአብሔር እንድንበላ ፈቅዶ ውሃ መጠጣትን የሚከለክል እቅድ የለውም፣ አልነበረውም። በሰዎች ዘንድ እየሆነ ያለው መንፈሳዊ ጥፋት ይህንን የሚናገር ነው። እስኪ ወደጉዳዩ እንግባ።
1/ ዝሙትና ማመንዘር(Fornication & Adultery)
ማመንዘር  ሰው ከጋብቻ በፊት የሚፈጽሙት ተራክቦ  ነው። ይህ ደግሞ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ሥራ ነው።ዝሙት ደግሞ በጋብቻው ውስጥ እያለ ከሌላ ሰው ጋር የሚፈጽመው ተግባር ነው።
ሮሜ 618
«ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል»

ዛሬ በዓለማችን ላይ ዝሙት ነግሷል። ዝሙት በሰው ሥጋ ላይ እንዲነግስ የበለጠ ማበረታቻና ዘዴ እየተፈጠረለት ሰው በሕይወቱ ውስጥ እንደአስፈላጊ ልምምድ እንዲወስደው ተደርጓል። አሁን አሁን መንፈሳዊ ነን የሚሉቱ ሁሉ የሚፈጽሙት ሆኗል።

1.1/ ከጋብቻ በፊት የሚደረግ ማመንዘር፣ (Adultery)
ከብሉይ ኪዳን ትእዛዛት አንዱ አታመንዝር ነው።
ይህ የማመንዘር ድርጊት በየትኛውም ደረጃና ዓይነት ውስጥ ቢሆኑም ሁለት ተቃራኒ ጾታዎች ከጋብቻ ውጪ የሚያደርጉት ወሲባዊ ድርጊትን ሁሉ ያጠቃልላል። ዛሬ ዛሬ በምላስ ዋጋ የሚገበያዩበት የስጋ ገበያ ሆኗል። አንዳንዶቹ ተጫጭተናል፣ በጓደኝነት ተጠናንተናል፣በፍቅር ጓደኝነት ተሳስረናል የሚሉትና በአላፊ አግዳሚ የዓይን ፍቅር ወደቅን፣ ለወሲብ ተፈላለግን፣ በጊዜያዊ ስሜት ወደቅን ወዘተ ምክንያት ያላቸው ሁሉ ከጋብቻ በፊት የሚያደርጉት ወሲባዊ ተራክቦ ሁሉ ማመንዘር ነው። ወይም በገንዘብ የሚለዋወጡትም ሸቀጥ መስሏል።

ሕዝ 16፣33
«ለጋለሞቶች ሁሉ ዋጋ ይሰጡአቸዋል አንቺ ግን ለውሽሞችሽ ሁሉ ዋጋ ትሰጫለሽ፥ ከአንቺም ጋር ለማመንዘር በዙሪያሽ ይገቡብሽ ዘንድ መማለጃ ትሰጫቸዋለሽ»

ይህንን የሚያደርጉ ሁሉ እግዚአብሔርን አያውቁም።
«ከዝሙት እንድትርቁ፥ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት አይደለም እንጂ፥ ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ እንዲያውቅ»1ኛ ተሰ4፣4-5
በሌላ ቦታም እንዲህ የሚል ገላጭ ቃል ተጽፎ እናገኛለን።
ቆላ 3፥5 «እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፥ እነዚህም ዝሙትና ርኵሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣኦትንም ማምለክ የሆነ መጎምጀት ነው»
ከጋብቻ በፊት የሚደረገው የማመንዘር ተግባር ከጊዜ ወደጊዜ እየተስፋፋና የሁሉም ሰው ልምምድ እየሆነ በመምጣቱ የተነሳ በድንግልና ቆይቶ ጋብቻን መፈጸም እንደእድል የሚቆጠር ሆኗል። እንዲያውም ዛሬ «ድንግልናና ፈንጣጣ ከጠፋ ቆይቷል» በሚል አባባል ስለድንግልና ማሰብ እንደስንፍናና አለማወቅ እንዲቆጠር አድርጎታል። ይህ የሚባለው ዝሙት እንዲበረታታ ጠላት በሰው አፍ ያስቀመጠው ቃል እንጂ  እግዚአብሔር ግን ሥራውን አቁሞ አይደለም።
በዘማነት የተገኘ ማንኛውንም ሰው ወይም ድንግልናዋን ያጣችን ሴት የኦሪቱ ሕግ በድንጋይ ተወግረው እንዲገደሉ ያዛል። (ዘዳ 22፣21) (ዘጸ 20፣14) (ዘሌ 18፣6-29)
በዚህ ዘመን የእግዚአብሔር ጸጋው ባይበዛና እንደኦሪቱ ሥርዓት ይህ ቢፈጸም ኖሮ ምድሪቱ ባዶ ትቀር ነበር። በአንድ ወቅት አንድ መንፈሳዊ ገጣሚ ሰው በኢትዮጵያ ውስጥ ስለተስፋፋው ውሸትና ውሸት እንደባህል እየተቆጠረ መምጣቱን በማስመልከት ባቀረበው ሥነ ግጥም ይህንን የመሰለ መልእክት አስተላልፎ ነበር። «እንደኦሪቱ ሕግ የዋሸ ሁሉ በሰውነቱ ላይ ለምጽ የሚታይ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዛኛው ፈረንጅ በመሰለ ነበር» ያለው ቀልድ መሰል ቁምነገር ያስታወሰኝ ነገር «ድንግልና የሌላት ወይም ሲያመነዝር የተገኘ ሰው እንደኦሪቱ በድንጋይ ተወግሮ ቢገደል ኖሮ ሰው የሚተርፍ አይመስለኝም»ነበር።
ድንግልናን መጠበቅ ዋጋ የሌለው አድርጎ ማሰብ ትልቅ ስህተት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በጋብቻ ድንግልን ያገባ እንደሆነ መልካም እንደሆነ ተናግሯል።

1ኛ ቆሮንቶስ ሰዎች7፥38 እንዲሁም ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ ያላገባም የተሻለ አደረገ።

 ስለዚህ ለመንፈሳዊ ጋብቻ ድንግልና እንደጠፋ ፈንጣጣ መታየት የለበትም። ይህ ሲባል ግን ድንግልናውን ያጣ ንስሐ ከገባ ወይም የቀደመ ኃጢአቱን ከተወ የተቀደሰ ጋብቻ መፈጸም አይችልም ማለት እንዳልሆነ ግንዛቤ  እንዲያዝ ያስፈልጋል። መዳን በእምነት እንጂ በድንግልና ስላልሆነ ማለት ነው። በጉዳዩ ላይ ሊሰመርበት የተፈለገው ነገር የሥጋችን ቅድስናና ንጽህና እንደቀላል ነገር ቆጥረን በማርከስ ልምምድ ውስጥ በመክተትና በሰውኛ ጥበብ ስጋዊ አምሮታችንን ለመፈጸም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጪ መውጣት ትክክል አይደለም ለማለት ተፈልጎ ብቻ ነው።
ሰው በሥጋው ከእግዚአብሔር ጋር ከመጣላቱም በላይ  ከጋብቻ በፊት የሚደረጉ የአመንዝራነት ተግባራት  ለጋብቻ ከመብቃት በፊት መዘግየትን ወይም መዘናጋትን ያስከትላሉ። ያልተፈለገ ውርጃን ወይም ወሊድን ሊያመጣ ይችላል። የዝሙት ጠንቅ በሽታዎችን፣ ጸያፍ ወሲባዊ ልምምዶችን እንደሚያስከትል በብዙ ጥናት የተረጋገጠ ሀቅ ነው።
 «አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና» ገላ6፣7

1.2/በጋብቻ ላይ የሚደረግ ዝሙት፤(Fornication)
ሰዎች ማመንዘርን የሚፈጽሙት ከጋብቻ በፊት ብቻ አይደለም። በጋብቻ ውስጥ እያሉም ቢሆን ከተጋቢዎቹ መካከል ከሁለት አንዳቸው ወይም ሁለታቸውም በተለያየ ጎዳና ዝሙትን ከሌላ ሰው ጋር ሊፈጽሙ ይችላሉ። የሚያሳዝነው ደግሞ በክርስቶስ አለን እያሉና የትዳር ፍሬ ልጆችን ካፈሩ በኋላም ይህ መከሰቱ ነው።  በጋብቻ ውስጥ እያሉ የሚፈጽሙት ዝሙት ማኅበራዊ ኑሮን  በማቃወስ ከፍተኛ ድርሻ አለው። ሰው በዝሙት ምክንያት ሚስቱን ወይም ባሏን ልትፈታ ትችላለች። በዝሙቱ ምክንያት ለበሽታ እንዲያውም ለጋራ በሽታ ሊጋለጡ ይችላሉ። በዚሁ ሳቢያ ብዙዎች ወደሞት መቃብር ወርደዋል። በሕይወት ካሉትም ብዙዎች ለማይድን በሽታ ተዳርገዋል። ጋብቻቸው የፈረሰ፣ ልጆቻቸው ሜዳ ላይ የተበተኑ አያሌ ናቸው።
በነፍስም ቢሆን የተነገረው ይህንን ነው።
 «ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ» ሁሉ ዋጋቸው የነፍስ ሞት ነው። 1ኛ ቆሮ 6፤9
2/ «እንጀራ እበላለሁ፣ ውሃ ግን አልፈልግም» ብሂል
ሰዎች አዳማዊ ተፈጥሮ በሆነው ሥጋዊ ባህርይ እና ጠላት የሰዶምን ሕዝብ እንዳነሳሳው ሁሉ ዛሬም እንደዚያው እየገፋፋ ከጋብቻ በፊትም ሆነ ከጋብቻ በኋላ ዝሙትን በልዩ ልዩ ፍርሃት እንዳያቋርጡ ወይም ድርጊታቸውና እንዳይገቱ ለማበረታታት ተስፋ ሰጪ መሰል መንገዶችን አዘጋጅቷል። ሰይጣን ዘመኑ እንዳለቀ ስለሚያውቅ ሰዎች ወደሞት ከማምራታቸው በፊት ለዘላለማዊ ሞት የሚያበቃቸውን ተግባር እስከእለታቸው ፍጻሜ እንዲፈጽሙ ይዋጋል።
ዝሙት ወይም ዝሙት መሰል ወሲብ እንዳይቋረጥ የተዘረጉ መንገዶች፣
2.1/ኮንዶም
ኮንዶም ለሴትም ለወንድም ተፈብርኳል። ይህ እንግዲህ ዝሙቱ ከሚያመጣው ጠንቅ የተነሳ የሰው ልጅ ከዝሙት ጋር ያለውን ቁርኝት እንዳያቋርጥ የተዘየደ ምድራዊ ጥበብ ነው። ዝሙቱ ይፈለጋል ፣ ዝሙቱ የሚያመጣውን ጣጣ በዚህ የፕላስቲክ ጋሻ ለመመከት ወደዝሙት ውጊያ ይገባል። የሚያሳዝነው ግን  ኮንዶም ከነፍስና ስጋ ሞት ዋስትና የሌለው ማታለያ  ፕላስቲክ መሆኑን አለመገንዘባችን ነው። ከዚያም በላይ ሰው ዘሩን እግዚአብሔር ከፈጠረበት ዓላማ ውጪ በማፍሰስ  ከዝሙቱ ድርጊት በተጨማሪ ኃጢአትን መሸከም ምንኛ አሳዛኝ ነው።
« አውናንም ዘሩ ለእርሱ እንዳይሆን አወቀ ወደ ወንድሙ ሚስት በገባ ጊዜ ለወንድሙ ዘር እንዳይሰጥ ዘሩን በምድር ያፈስስው ነበር፣ ይህም ሥራው በእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ ሆነበት፥ እርሱንም ደግሞ ቀሠፈው»ዘጸ 38፣9-10
ኮንዶምን ከጋብቻ በፊት ብዙዎች ይጠቀሙታል። ሴቶችም ለራሳቸው መከላከያ ይህንን ላስቲክ ይለብሳሉ። ይህ ላስቲክ ምናልባት ለሚፈልጉት አገልግሎት ጠቅሞ ሊሆን ይችላል። ግን የስጋን እድፈት አያጠራም፣ የኃጢአትን ፍዳም አይከላከልም።
2.1/ የወሊድ መቆጣጠሪያ ክኒን፣ ሉፕ እና ሌሎችም
ወሊድ መቆጣጠሪያ ክኒን እና ሉፕን ከጋብቻ በፊት ያሉትም ሆነ በጋብቻ ውስጥ ያሉ ይጠቀሙታል።አገልግሎታቸው በሽታን ለመከላከል ሳይሆን ሊመጣ የሚችለውን የልጅ ጣጣ በማስቀረት ማመንዘርን፣ወሲብን ወይም ዝሙትን ሳይጨናነቁ ተዝናንቶ ለመፈጸም ነው። በጋብቻ ውስጥ ይህንን ስለመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስ አንድም ቦታ አበረታትቶ አያውቅም። የወንድ ዘርን ስለማፍሰስ የተነገረው ግን ጋብቻንም ይመለከታል እንላለን። ምክንያቱም ጋብቻ ዓላማው ዘርን መተካት እንጂ ዘርን በማፍሰስ ወይም ዘርን በዘዴ በመግደል ወይም ከሰጪና ከተቀባይ መካከል እንዲሞት በማድረግ የሚኖሩበት የሥጋዊ ጥበብ ተቋም አይደለምና ነው። ነገሩ በጽሁፋችን ርእስ እንደገለጽነው «እንጀራ እበላለሁ፣ ውሃ ግን አልፈልግም» እንደማለት ነው።
ወሲብ በዚህም ይሁን በዚያ አይቅርብን፤ ወሲብ የሚያጣውን ጣጣ ግን አንፈልግም ማለት የጤናማ ሰው ወይም ሕብረተሰብ ዓላማ አይደለም። እንደዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር የሚችሉበት የዓላማ ካርታ የላቸውም። 
በእግዚአብሔር ፈቃድ ሥር ያለ የጋብቻ ጥሪ እንደምድራዊ ጥበበኞች ጥበብ ለመኖር አይደለም።
1ኛ ቆሮ 1፣26
ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁን ተመልከቱ፤ እንደ ሰው ጥበብ ፣ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፥ ኀያላን የሆኑ ብዙዎች፥ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም።

በቅድሚያ ከዝሙት ወይም ካልተፈለገ ከወሲባዊ ማመንዘር  በመጠበቅ፣ ፈተናን ለመቋቋምም ጋብቻን መመስረትና በዚያው ላይ እንደእግዚአብሔር አሰራር መኖር ሲገባ ዋጋ በሚያስከፍል አኗኗርር ውስጥ በመገኘት፦ ዝሙቱም፣ወሲቡም፤ መዳራቱም፣ማመንዘሩን ሳይቀርብን በስጋችን ደስ ተሰኝተንበት፤ የሚያስከትለውን ውጤት ግን በመግደልም ፤ በማፍሰስም፣ በመዝጋትም ይሁን በመገደብ ሳንጨነናነቅ መፈጸም ነው በሚል ዘዴና የብልጠት መንገድ መጓዝ ትርፉ ሞት ነው።
ይህም ሆኖ በኃጢአታችን ተስፋ ቆርጠን ለጠላት እድል ፈንታ በመስጠት ውስጥ መኖር የለብንም።
በእርግጥ እግዚአብሔር ፍቅር ነው። ይህ ሁሉ ሆኖ እግዚአብሔር ኃጢአትን እንጂ ኃጢአተኛውን አይጠላም።በየትኛውም ኃጢአት ውስጥ ሆነን ብንቆይ እግዚአብሔር  ወደህይወት መንገድ ኃጢአተኛውን ባለመጥላት ፍቅሩ ሊጠራው እንደሚችል ብናውቅም ለኃጢአታችን  መንገድ የሚያጠናክሩ ተግባራትን ከመፈጸም ዛሬውኑ መውጣት ይገባናል።
«በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና» 2ኛ ቆሮ 2፣11
«እንጀራ እበላለሁ፣ ውሃ ግን አልጠጣም» ማለት ከማታለል የተለየ አይደለምና ንስሐ እንግባ በባለፈው ኃጢአታችን እንጸጸት። ወደእግዚአብሔር እንቅረብ፣ይቅር ሊለን እሱ የፍቅር እጆቹን ዛሬም ቢሆን እንደዘረጋ ነው!