Thursday, March 8, 2012

ትንቅንቅ!

 በእውነተኛ ራእይ ላይ የተመሠረተ፣

ርእስ- የመጨረሻው ትንቅንቅ
            ደራሲ- ሪክ ጆይነር
          ተርጓሚ ሰሎሞን አሰፋ
                                                            ናዝሬት፣ 2004 /
                          ክፍል ፩

የሲኦል ኃይላት እየተመሙ ናቸው

አጋንንታዊ ሠራዊቱ በዓይኔ ማየት እስኪሳነኝ ድረስ እጅግ ብዙ ሲሆኑ እያንዳንዳቸውም የተለያዩ ሰንደቅ ዓላማዎችን ተሸክሞ በተሰለፈ ክፍለ ጦር ስር ተከፋፍለው ተሰልፈው ነበር። ትላልቆቹ ክፍለ ጦሮች ትዕቢት፣ራስን ማጽደቅ፣ ስምን ማስጠራት፣ ራስ ወዳድነት፣ በጭፍን መፍረድና ቅናት የሚሉ ሰንደቅ ዓላማዎችን በያዘ ጦር ስር ተሰልፈው ነበር። በዓይኔ ማየት ከምችላቸው ከእነዚህም ሌላ እጅግ በርካታ ሌሎች ክፍለ ጦሮችም ተሰልፈው ነበር። ይሁንና ከገሃነም እየወጣ ከመጣው ከዚህ አስፈሪ መንጋ ፊት በግንባር ቀደምትነት የተሰለፉት ግን እጅግ ኃያላን ይመስሉ ነበር። የዚህ ሠራዊት መሪ ደግሞ የወንድሞች ከሳሽ የሆነው ራሱ ሰይጣን ነበር።
ይህ መንጋ ሠራዊት የታጠቃቸው የጦር መሣሪያዎች በላያቸው ላይ ስሞቻቸው ተጽፎባቸው ነበር። ሰይፎቹም ዛቻ፣ ጦሮቹ ክህደት፣ ቀስቶቹ ሀሰት፣ ክስና ስም ማጥፋት ይባሉ ነበር። መራርነት፣ አለመቀባበል፣ ትዕግስት ማጣት፣ ይቅር አለማለት የተባሉ ስሞች ያሏቸው ጥቂት የአጋንንቱ ቡድን አባላትም ለዋናው ውጊያ ከዚህ ሠራዊት ፊት ቀድመው እንዲጓዙ ተልከው ነበር።

እነዚህ የአጋንንቱ ቡድን አባላት ቁጥራቸው አናሳ ቢሆንም ኃይላቸው ግን ከኋላቸው ተሰልፎ ከሚገሰግሰው በርካታ ክፍለ ጦር የሚተናነስ አልነበረም። ቁጥራቸው አናሳ የሆነው ደግሞ ለስልታዊ ምክንያት ብቻ ነበር። እነዚህ ጥቂት አጋንንታዊ ቡድኖች ልክ ዮሐንስ መጥምቁ ሕዝቡን በጥምቀት ለጌታ ለማዘጋጀት ብቻውን የተለየ ቅባት እንደተሰጠው ዓይነት እነዚህም ህዝቡን ለጥፋት ለማዘጋጀት «ብዙሃኑን ሕዝብ ለማጥመቅ» ልዩ አጋንንታዊ ኃይልን የለበሱ ነበሩ። አንዱ የመራርነት አጋንንት በሕዝብ ወገን ሁሉ ወይም ባህሎች ላይ እንኳን ሳይቀር መርዙን መርጨት ይችል ነበር። የርኩሰት አጋንንቱ ደግሞ ከአንድ የቴአትር፣ የፊልም ወይም የንግድ ምርት አስተዋዋቂ ተዋንያን ጋር ራሱን በማቆራኘት ቁጥሩ እጅግ በርካታ የሆነውን ሕዝብ እንደኤሌክትሪክ ያለ ኃይል እየላከ በመምታት ያፈዛቸውና ያደነዝዛቸው ነበር። ይሄ ሁሉ ደግሞ ቀጥሎ ለሚመጣው ለታላቁ የክፋት መንጋ መንገድ ጠርጎ ለማዘጋጀት ነበር።


ይህ ሠራዊት እየገሰገሰ ያለው በተለይ ቤተክርስቲያንን ለማጥቃት ቢሆንም ጥቃቱን ግን በተቻለው ሁሉ መንገድ ላይ ባገኘው ላይም ይሰነዝር ነበር። ይህ ደግሞ ብዙ ሕዝብ በንስሃ ወደ ቤተእግዚአብሔር መልሶ ለማፍለስ የተወሰነውን መጪውን የእግዚአብሔር ሥራ አስቀድሞ ለማሰናከል የተደረገ ጥረት እንደሆነ ተረዳሁ።

የዚህ ሠራዊት ቀዳሚ ስልቱ በየትኛውም የግንኙነት ደረጃ ላይ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን እርስ በእርሳቸው ማጋጨት፣ ባሎችን ከሚስቶቻቸው፣ ልጆችን ከወላጆቻቸው፣ማጣላትና ማበጣበጥ ነበር።የዚህ ቡድን ሰራዊት አባላት ግለሰቦችን በማጥመድ መራር እንዲሆኑ፣ ሌላውን እንዲገፉ፣እንዲጠሉ፣ ክፋትን እንዲያስቡ የሚያደርግ መንፈሱን በመልቀቅና በመሙላት በየአብያተ ክርስቲያናቱና በየቤተሰባዊ ኑሮው ውስጥ የክፋት ክፍተቱን ይሞላ ነበር። ከዚያም ቀጣዮቹ ክፍለ ጦሮች የዚህን ጦርነት ሰለባዎች ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር ለማዋል በተከፈተላቸው ክፍተት ሁሉ አልፈው ይገባሉ።

የዚህ ራእይ አስደንጋጩ አካል ደግሞ ይህ የክፋት መንጋ የሚጋልበው በፈረስ ሳይሆን በክርስቲያኖች ላይ መሆኑ ነበር። እነዚህ ክርስቲያኖች አብዛኛዎቹ ጥሩ ጥሩ ልብስ የለበሱ፣ የተማሩ፣ ጸባየ ሸጋዎችና ከየትኛውም ዓይነት የሕይወት ምልልስ የተወከሉ ናቸው። እነዚህ ወገኖች የክርስትና እውነቶችን በአንደበታቸው እየተናገሩ ኅሊናቸውን የሚሸነግሉ ስመ ክርስቲያኖች ናቸው። ከነዚህ የተነሳም ሕይወታቸው ለጨለማው ኃይላት ተስማሚ በመሆኑ ለእነርሱ የተመደቡት አጋንንት ይበልጥ እየበዙ ተልዕኳቸውን በቀላሉ ይፈጽሙባቸው ነበር።

ከእነዚህ ስመ ክርስቲያኖች መካከል አብዛኛዎቹ ከአንድ በላይ የሆነ አጋንንትን የሚያስተናግዱ ሲሆኑ ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠሯቸውም በሰልፍ ሆነው ወደውስጣቸው ዘልቀው መግባት ፍላጎታቸውን በኃይል ማሳየት የሚችሉ የየትኛውም ክፍለ ጦር አጋንንት ሁሉ ነበሩ። ምንም እንኳን ሁሉ ሠራዊት ዓላማቸው አንድ የሆኑው ሰውን ለማጥፋት ቢሆንም እርስ በእርሳቸው የተተራመሱ ነበሩ። ለምሳሌ ጥላቻን የሚዘራው አጋንንት የሚያጠቃውን ሰው የሚጠላውን ያህል ለሌላ ተልእኮ የሚመጣውን አጋንንትም ይጠላ ነበር። የቅናት መንፈስ የሚዘራው አጋንንት የቂም መንፈስ የሚዘራውን አጋንንት ይጠላዋል። አንዱ ከአንዱ ለመብለጥ ይመቀኛኙ ነበር።
አጋንንቱ ክርስቲያን የተባሉትን የሚያጠቃው የቂም፣ የበቀል፣ የጥላቻ፣ የሃሜት፣ የሀሰትና የነቀፋ ጨረር እየወረወረባቸው ሲሆን አልሳካ ብሎ ዓላማው ሲጨናገፍበት በብስጭት እርስ በእርሱ ይጣላ ነበር።
አጋንንቱ በስመ ክርስቲያኖቹ ላይ በልዩ ልዩ መንገድ እየገቡባቸው ይጋልቡባቸው እንጂ ክርስትናን በማያውቁት ላይ ሰፍረው እንደሚያድሩት በእነርሱ ውስጥ እንደማያድሩባቸው ተመለከትሁ። ክርስቲያን በሆነው ላይ አጋንንቱ የጨረር ጦሩን ሲወረውርበት መቃወም ሲጀምርና ይህንን መንፈስ ለመመከት ሲታገል አጋንንቱ ከመቅጽበት ኃይሉን ሲያጣ አየሁ። ሁልጊዜ መዋጋት ቢችል ኖሮ ስመ ክርስቲያኑ የአጋንንቱ ማደሪያ መሆን እንደማይችል ተረዳሁ። በክርስቲያኑ የተጠቃው አጋንንት ሊሸነፍ ሲጀምር ድምጹን ያስተጋባና ለእርዳታ ይጮሃል። ያኔም የአጋንንቱ ክፍለጦር አለቃ በፍጥነት ደርሶ ሠራዊቱን በማሰለፍ በመራርነት መንፈስ ይዋጋው ዘንድ ይጀምራል። ይህም ካልሰራለት ደግሞ አቅጣጫውን ቀይሮ የጭከና መንፈስ ይወረውር ዘንድ ይጀምራል። የመራርነት፣ የክስ፣ የክፋት መንፈስ ሆነው ውጊያቸውን እንዲንቀው ወይም ውጊያ እንዳልሆነ እንዲያስብ ለማድረግና ለማዘናጋት የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጉም አጣመው መጥቀስ ይጀምራሉ።

የአጋንንቱ ሙሉ ኃይል ስር የሚሰደውና ቁጥጥራቸውን የሚያጠነክርላቸው ዋናው መንገድ በዚህ መንገድ በማሳት ነው። ስመ ክርስቲያኖቹ እግዚአብሔር እየተጠቀመባቸው እንደሆነ ያስቡ ዘንድ በዚህ የስህተት መንፈስ ያሳምናቸዋል። እንዲይዙ የሚያደርጋቸው ሰንደቅ ዓላማ «ራስን ማጽደቅ»የሚል ጽሁፍ ያለበትን ዓርማ የተሸከሙ ናቸው። ያኔ የነሱ መንገድና ዓርማ ትክክል መሆኑን አምነው ይቀበሉና እውነተኛውን መንገድ የስህተት መንገድ አድርገው እንዲያስቡ አድርጎ ይቆጣጠራቸዋል።
ከኋላም «የወንድሞች ከሳሽ» የተባለውን ከነሠራዊቱ አየሁ። ይህም «እርስ በእርሷ የምትለያይ ቤት እንደማትጸና» ስለሚያውቅ ቤተክርስቲያን ሙሉ በሙሉ ከጌታ ጸጋ ትጎድል ዘንድ በመካከሏ መለያየትን ለማምጣት ይተጋል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ክርስቲያኖች፣ በክርስቲያን ወንድሞቻቸው ላይ እንዲነሳሱ በማድረግ ነው። ክርስቲያኖች እርስ በእርሳቸው ሲጠላሉ የከሳሹ ሠራዊት ኃይል ይታደሳል። ያኔም የበለጠ ወደፊት ይገሰግሳል። ውጤታማ መሆኑን በመተማመን ሲሰራ ተመለከትሁ። ስመ ክርስቲያኖቹ በክፉው መንፈስ ውጊያ ሲሸነፉ ወይም ሲዳከሙ አጋንንቱ ኃይላቸው ሲያድግ፣ እንዲሁም ስመ ክርስቲያኖቹ ጠንክረው መዋጋት ሲጀምሩ ወይም ሲበረቱ የኣንንቱ ኃይል ሲዳከም ተመለከትሁ። ዋናው ችግር ስመ ክርስቲያኖቹ ከክፉው አካሄድ ጋር አብረው መስማማታቸው ነበር።
                                      
                                            ምርኰኞቹ፣

ይቀጥላል....