Friday, March 9, 2012

የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እንዲከላከሉ ተወሰነባቸው!

 ሊቀ ትጉሃን ተሾመ ኃይለ ማርያም በ"ማኅበረ ቅዱሳን" ሤራ በፖሊስ ተይዘው ወደ ነጌሌ ቦረና ተወሰዱ

በቆሞስ መልአከ ገነት አባ ሙሉጌታ ታዬ የክብረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ ከሸፈ

የካቲት 16 ቀን 2004 ዓ.ም በክብረ መንግሥት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ የሚከበረውን የቅድስት ኪዳነ ምሕረት በዓለ ንግስ በመረበሽ ያስተጓጎሉት ሃያ አምስት የማኅበረ ቅዱሳን አባላትና አፍቃሬ ማኅበረ ቅዱሳን ተከሳሾች ለመጋቢት 19 ቀን 2004 ዓ.ም ቀነ ቀጠሮ ቀርበው እንዲከላከሉ ተበይኖባቸዋል፡፡ ዐቃቤ ሕግ አሥራ ሦስት ምሥክሮችን ያሰማ ሲሆን ክሱን በጽሑፍ፣ በሰውና በምስል ማስረጃ አጠናቅሮ አስረድቷል፡፡ በተጨማሪም ሰባት ምሥክሮች ቃለ መሐላ ከፈጸሙ በኋላ ዐቃቤ ሕጉ በቃኝ ሳይሉ ምክንያቱ በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት ዳኛው አቶ ጉዩ እንዳይመሠክሩ አስቁመዋል ተብሏል፡፡  
በዚህም ሳቢያ ስምንት ቀንደኛ በጥባጮች በዚያው ዕለት 29/6/2004 ዓ.ም በነፃ አሰናብተዋቸዋል ተብሏል፡፡ ከነዚህ ስምንት ቀንደኛ መሪዎች ውስጥ መሪጌታ መዝገቡ ጌታነህ፣ ቄስ መኮንን ጉቴሳ (የአንድ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የታሪክ መምህር)፣ ወ/ሮ ሃይማኖት ጥላሁን፣ ወ/ሮ መቅደስ፣ ዲ/ን እንዳሻው፣ ዲ/ን ብንያም፣ ዮናስና ጌትነት የተባሉት መሆናቸው ታውቋል፡፡ በተለይም የእነዚህ ቀንደኛ በጥባጮች መለቀቅ፣ የከተማውን ኅብረተሰብ፣ የፍትሕና የፀጥታ አካላትን ማስቆጣቱ ተመልክቷል፡፡
ይሁን እንጂ በእነዚህ ሰዎች በቂ የሰውና የምስልና የድምፅ ማስረጃ እያለ እና ዐቃቤ ሕግ ተጨማሪ ሰባት ምስክሮችን አስመዝግቦ ቃለ መሐላ ከፈጸሙ በኋላ ዳኛው አቶ ጉዩ የክስ መስማት ሂደቱን በድንገት ማቋረጣቸው ፍትሐዊ ሂደቱን አጠያያቂ እንዳደረገው ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ሌሎች 12 ተከሳሾች ፍርድ ቤት መቅረብ ሳያስፈልጋቸው በፖሊስ ማጣሪያ ቀደም ባሉት ቀናት በነፃ መሰናበታቸውን የደረሰን ማስረጃ ያመለክታል፡፡

በሌላ በኩል ዛሬ የካቲት 30 ቀን 2004 ዓ.ም የጉጂ ቦረና ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉሃን ተሾመ ኃይለ ማርያም በሕገ ወጡ ሲያምር ተክለ ማርያም የማጭበርበሪያ ክስ በፖሊስ ተይዘው ወደ ነጌሌ ቦረና መወሰዳቸው ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ሲያምር ተክለ ማርያም በተደጋጋሚ እንደዘገብንላችሁ ከስድስት ወራት በፊት ወደ አዲሰ አበባ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የተዛወረ ሲሆን የጠቅላይ ቤተክህነትን የዝውውር መመሪያ አልቀበልም፤ በማለት በእርሱ ምትክ ለተመደቡት ሊቀ ትጉሃን ተሾመ ኃይለ ማርያም፣ ጽ/ቤቱን፣ መኪናውንና ማኅተሙን አላስረክብም ብሎ ከአካባቢው መሰወሩን ገልጸንላችኋል፡፡

ሲያምር ተክለ ማርያም በ"ማኅበረ ቅዱሳን" ቅንብር ከጊዜ በኋላ ከተሰወረበት መጥቶ ጽ/ቤቱ ውስጥ ጉብ ያለ ሲሆን፣ ምንም ነገር እንዳልተከሰተ በማስመሰል በሕገ ወጥ መንገድ ማኅተሙን ሲጠቀምበት በመገኘቱ፣ ጠቅላይ ቤተክህነት እንዳያንቀሳቅሰው ወስኖበት፣ የሀገረ ስብከት ጽ/ቤቱንም በጊዜያዊነት ወደ ክብረ መንግሥት እንዲያዛውሩ የተፈቀደላቸው መሆኑ ታውቋል፡፡

ይሁን እንጂ ሲያምር ተክለ ማርያም የቅድስት ኪዳነ ምሕረት በዓለ ንግስን ማስተጓጎሉ ሳያንስ ማኅተሙን አግደውብኛል፤ ያልተፈቀደ የሀገረ ስብከት ጽ/ቤትም ወደ ክብረ መንግሥት አዛውረውብኛል በሚል የሐሰት ክስ አቀነባብሮ ቅዳሜና እሁድ የማይካስ ጉዳት እንዲያገኛቸው በማሰብ ዛሬ ዐርብ ከሰዓት በኋላ በፖሊስ አስይዞ መውሰዱን እማኞቻችን አረጋግጠዋል፡፡

በጉጂ ቦረና ዞን መስተዳድር የሊበን ወረዳ ፍርድ ቤት ከስድስት ወራት በፊት ወደ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የተዛወረውን ሕገ ወጡን ሲያምር ተክለ ማርያም በመደገፍና "ማኅበረ ቅዱሳን"ን ለማስደሰት ሲል ሕጋዊውን አካል ተይዞ እንዲቀርብ ማድረጉና በጠራራ ፀሐይ ፍትሕ መጨፍለቁን ብዙዎች በግርምት ተመልክተውታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የክብረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት ቆሞስ መልአከ ገነት አባ ሙሉጌታ ታዬን የተደራጁ ቡድኖች በረቀቀ ስልት አፍነው በጩቤ ለመግደል ያደረጉት ሙከራ በአካባቢው በነበሩ ሰዎች ርዳታ መክሸፉን ከወደ ስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ቆሞስ መልአከ ገነት ሙሉጌታ የግድያ ሙከራው የተደረገባቸው የዕለተ ቅዱስ ባለወልድን ቅዳሴ ቀድሰውና አስተምረው እንዳበቁ እዚያው ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ከቀኑ በግምት 9፡30 ላይ ነበር ተብሏል፡፡ ፖሊስ በተጠርጣሪዎች ላይ አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ ላይ ሲሆን በቅርቡ ለፍርድ ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ምንጭ፣ http://dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com/2012/03/25.html