Tuesday, March 20, 2012

አንድ ጥያቄ አለኝ!

ስሙ ያልገለጸ ጠያቂ፣
እንደ ሮም፣ምዕራፍ 8 ሃሳብ ልጅነት ምንድን ነው?ስንት አይነት ልጅነትስ አለ?

የደጀብርሃን መልስ፣

 
ሰው ሁለት ልደት እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። መጀመሪያ ከእናትና ከአባት የምንወለድበት ሥጋዊ ልደትና ቀጥሎም ከእግዚአብሔር የምንወለድበት መንፈሳዊ የእግዚአብሔር ልጅነት ናቸው።

«ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው» ዮሐ 3፣6

ሥጋዊውን ልጅነት አይሁዳዊው ይሁን አረማዊው፤ ግሪካዊ ይሁን ሲሮፊኒቃዊ ሁሉም ይህን የሥጋ ልደት ያለ ልዩነት ያገኙታል። መንፈሳዊውን ልጅነት ግን በእምነት ብቻ የሚያገኙት ስጦታ ነው።
ሥጋዊው ልደት ምድራዊ ሲሆን መንፈሳዊው ልደት ሰማያዊ ነው። ሥጋዊውን ልደት የእግዚአብሔርን ሕልውና ቢያውቅም ባያውቅም፣ ቢያምንም ቢያምንም ሊያገኝ ይችላል። መንፈሳዊውን ልደት ግን በአንድያ ልጁ ያላመነ ማንም ቢሆን ሊያገኘው የሚችለው ልጅነት አይደለም።

«ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው» ዮሐ 3፣3
ሰው ይህንን መንፈሳዊ ልጅነት እንዴት ሊያገኝ ይችላል?
እስራኤላውያን ከምድረ ግብጽ ከወጡ በኋላ የሖር ተራራን አልፈው ወደ ከነዓን ምድር ሲደርሱ እንዲህ ሲሉ በእግዚአብሔር ላይ አጉረመረሙ።

«ሕዝቡም በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ። በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? እንጀራ የለም፥ ውኃ የለም ሰውነታችንም ይህን ቀላል እንጀራ ተጸየፈ ብለው ተናገሩ» ዘኁ 21፣5

ይህን ቀላል እንጀራ ሰውነታችን ተጸየፈ አሉ። ሳያቦኩና ሳይጋግሩ የሚበሉትን የሰማይ እንጀራ የሆነውን መና ተጸየፉት። ከሰማይ የወረደውን መና የጠሉ ሁሉ መጨረሻቸው ሞት ነውና በእነዚህ ሰዎች ላይ የሞት መርዝ ያለው ጠላት እባብ ገባባቸው።

«እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ እባቦችን ሰደደ፥ ሕዝቡንም ነደፉ ከእስራኤልም ብዙ ሰዎች ሞቱ» ዘኁ21፣6
ከዚህ ሞት መዳን የቻሉት ከናስ የተሰራ የተሰቀለውን እባብ ማየት ሲችሉ ብቻ ነበር።

ዛሬም እግዚአብሔር ከሰማይ የወረደውን የሕይወት እንጀራ ለሰው ልጆች ልኳል። ይህ የሕይወት እንጀራ ፤ጠላት የነደፈውን ሁሉ ሊያድን እንደናሱ እባብ ቀራንዮ ላይ ተሰቅሏል። እሱን ያየ ሁሉ ይድናል።

«ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል» ዮሐ 3፣14

የእስራኤሎቹ መና ከሰማይ የወረደ ይሁን እንጂ በልተውት በዚሁ ምድር የሚቀር ነው።
የአዲስ ኪዳኑ መና ግን ከሰማይ የወረደና ወደሰማይ የወጣ ብቸኛው መድኃኒት ነው።

«ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው»
በዚህ አዳኝ ማመን ማለት መንፈሳዊ ልጅነትን ማግኘት ማለት ነው። ይህ ነገር ለአይሁድ መምህር ለኒቆዲሞስ መረዳት ከብዶት እንደነበረ እናነባለን። መንፈሳዊ ልጅነት በእምነት የሚገኝ ስጦታ በመሆኗ ነውና።

«በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል» ዮሐ 3፣18

በእምነት ክርስቶስን የተቀበሉ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉ።

«በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና» ገላ 3፣26
መንፈሳዊ ልጅነት በክርስቶስ ኢየሱስ ባለን እምነት የምናገኘው ስጦታ ነው።
ብዙ ዓይነት ልጅነት የለም። ድነት አንዲት ናት። ልጅነትም እንዲሁ!
ያመነ፤ የተጠመቀ ይድናል። ያላመነ ይፈረድበታል። እውነታው ይሄ ነው። በክርስቶስ ኢየሱስ ያመኑ የእግዚአብሔር ልጆች የትንሳዔ ሞትን አያዩም። እንደመላእክት ይኖራሉ እንጂ።
«ሊሞቱም ወደ ፊት አይቻላቸውም፥ የትንሣኤም ልጆች ስለ ሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው» ሉቃ 20፣36
የእግዚአብሔር ልጅነት ማለት ይሄ ነው።