(ደጀብርሃን ብሎግ ለሐዋሳ ምእመናን አድናቆቱንና አክብሮቱን ይገልጻል)
ከወንጌል፣ ከሠላምና ከልማት ውጪ የተለየ አጀንዳ እንደሌላቸው በድጋሚ አረጋገጡ
አቡነ
ገብርኤል የተከፈለም ሆነ የተሰደደ ሕዝብ የለም ያሉት የሀዋሳ ምዕመናን የደብረ ዘይትን በዓል አስመልክቶ ታላቅ
መንፈሳዊ ጉባዔ ማዘጋጀታቸውን የደረሰን መረጃ ያረጋግጣል፡፡ ይኸው ለሁለተኛ ጊዜ የተዘጋጀው ታላቅና ደማቅ መንፈሳዊ
ጉባዔ በየዕለቱ በሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ እንደተከታተለው ታውቋል፡፡
እንደወትሮው
ሁሉ ገቢው የነጠፈባቸው አሥር የማይሞሉ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎችና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ስድስቱን አጥቢያ
ቤተክርስቲያናት በማሰተባበር ጉባዔውን ለማደናቀፍ እና ሕዝቡን ለመበተን አውደ ምሕረት ላይ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ
በመንዛት፣ ሲመቻቸው ደግሞ ዱርዬዎችን በመላክ፣ በሉ ሲላቸው ደግሞ ሕጋዊ በመምሰል በየፍትሕ እና ፀጥታ መሥሪያ ቤቱ
በመዞር አስቁሙልን እያሉ ሲውተረተሩ ከርመዋል ተብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ግፉአኑ እምነታቸውን በነፃነት የማራመድ
ካላቸው ሕገ መንግሥታዊ መብት አንፃር መንግሥት ተረድቶላቸው ጉባዔውን ሊያኪያሂዱ መቻላቸው ታውቋል፡፡
ከመጋቢት
7 እስከ መጋቢት 9/ 2004 ዓ.ም ለሦስት ቀናት በተካሄደው በዚህ ጉባዔ ተጋባዥ ሰባክያነ ወንጌል እና መዘምራን
ተገኝተው ያገለገሉ ሲሆን፣ በጠላት ዲያብሎስ ሤራ ተዳክሞ የነበረው የወንጌል አገልግሎት እንደገና ትንሣኤ ያገኘበት
ታላቅ የሐሴት ጉባዔ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በጉባዔው ማጠቃለያ ላይ የጉባዔው አዘጋጆች ለተሰበሰበው ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፣ "ከእነ አቡነ ገብርኤል ጋር ያለን ልዩነት በአስተዳደር እና ስለወንጌል ባለን አቋም ነው" ብለዋል፡፡ዝርዝሩንም ሲያስረዱ "እነርሱ በተከታታይ የወጡ የሲኖዶስ ውሳኔዎችን እየጣሱ የቤተክርስቲያንን መዋቅር ከላይ እስከታች በማኅበረ ቅዱሳን አስወርረዋል፡፡ እኛ የምንለው የሲኖዶስ ውሳኔ ይከበር ቤተክርስቲያን የሁሉም ናት መዋቅሩ ከማኅበራት ንክኪ ነፃ ይሁን ነው፡፡
እነርሱ
የቤተክርስቲያንን ልማት ያለ ቁጥጥር እና ለሙስና በተጋለጠ መልኩ በደመ ነፍስ ይመራሉ፡፡ የቤተክርስቲያኗ ልማት
ከሰባት ዓመታት በላይ ኦዲት አያውቀውም፣ ቁጥጥር አይደረግበትም፤ በሕግ አይመራም፡፡ እኛ ደግሞ የቤተክርስቲያን
ልማት በግልጸኝነትና በተጠያቂነት ላይ ተመሥርቶ ይመራ፡፡ በዕቅዱም ሆነ በአስተዳደሩ ሕዝብ ይሳተፍበት፣ እንላለን፡፡
እነርሱ
ሊቃውንት ጉባዔ ያልመከረበትና ቅዱስ ሲኖዶስ ለይቶ ያላወገዛቸውን አገልጋዮች በቤተክርስቲያን አያገለግሉም በማለት
ከልክለው፣ በምትካቸው ከቤተክርስቲያን መዋቅር ውጪ የሆኑትንና የቅዱስ ሲኖዶስን ሕልውና የማይቀበሉ አገልጋዮችን
ከአሜሪካ ጭምር ጠርተው ያሰብካሉ፡፡ እኛ ደግሞ በቅዱስ ሲኖዶስ፣ በጠቅላይ ቤተክህነት እስከታወቁ ድረስ ሁሉም
አገልጋዮች የቤተክርስቲያን ልጆች ናቸው፤ በተሰጣቸው ፀጋ እኩል የማገልገል መብት አላቸው እንላለን፡፡
እነርሱ
ከቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውጪ ወንጌል መሰበክ የለበትም፣ የተቀደሰው ሥፍራ ይህ ብቻ ነው፤ ንዋየ ቅዱሳቱም
ታቦቱም ያለው እዚሁ ቤተክርስቲያን ውስጥ ብቻ ነው ይላሉ፡፡ እኛ ደግሞ ወንጌል በቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ብቻ
ሳይሆን በውጪም ጭምር መሰበክ አለበት እንላለን፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን እየመጣ ወንጌል የሚሰማ ሕዝብን ከመጠበቅ
ይልቅ ወንጌል ወደ ሕዝቡ እየሄደ መሰማት፣መሠራጨት አለበት እንላለን፡፡ ይህንኑ እምነታችንንም ብፁዕ አቡነ
ጎርጎርዮስ-ካልዕ
ሲያጠናክሩ ወንጌል በለቅሶ ቤት፣ በሠርግ ቤት፣ በእሥር ቤት፣ ሕዝብ በተሰበሰበበት ሥፍራ ሁሉ መሰበክ እንዳለበት
አስተምረዋል፡፡ ሕገ ቤተክርስቲያናችንም ይህንኑ ትደግፋለች፡፡ ወንጌል እንደ ቅዳሴ ታቦቱ ባለበት ሥፍራ ብቻ መሰበክ
አለበት ሊባል አይችልም፡፡ የወንጌል ተልዕኮ በዓለም ውስጥ ሄዶ መሠራጨት ያለበትና ስለ እግዚአብሔር ታላቅነት
ገልጾ የተማሩትና ያመኑበት ወደ ቤተክርስቲያን ሄደው እንዲጠመቁና ሥጋ ወደሙ እንዲቀበሉ ማብቃት ነው፡፡ ስለዚህ፣
ስለወንጌል ያለን እምነት የማይለወጥ ነው"፤ በማለት አበክረው አስረድተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር አያይዘውም፣ "በእነዚህ
ልዩነቶቻችን ምክንያት እኛ በስደት ላይ፣ እነርሱ ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳንን አቅፈው፣ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት በሌለው
መንገድ ቤተክርስቲያንን እየመሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ አንድ ነገር ሆኖ፣ እነርሱ እውነቱን ለመሸፋፈን እና የራሳቸውን
ችግር በሌላው ለመላከክ እኛን "ተሀድሶዎች ናቸው"፣ "መናፍቃን ናቸው"፣ "ወደ እነርሱ አትሂዱ"
በማለት ሕዝቡን በማወናበድ ላይ ናቸው፡፡ ለዚህ ሕዝብ ከራሱ በላይ ማንም ምሥክር ሆኖ ሊመጣለት አይችልም፡፡
ትላንት፣ ዛሬ፣ ነገም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ ያለን እምነት የጸና ነው፡፡
በዚህ
እምነታችን ለወደፊቱም ተጠናክረን እግዚአብሔርን እናመልካለን፣እንደ ዜጋም ሀገራችን በምትነድፋቸው የልማት ዕቅዶች
በመሳተፍ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን፡፡ ከወንጌል፣ ከሠላምና ከልማት ውጪ የተለየ አጀንዳ የለንም" በማለት አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ይህ
በእንዲህ እንዳለም የጉባዔው አዘጋጆች እንደገለጹት ከቦታ ጥበት አንፃር በጉባዔው ላይ መሳተፍ ላልቻለውና ከዚህ
በእጥፍ ለሚልቅ፣ በየቤቱ ለቀረው ሕዝብ ሰፋ ባለ ቦታ ታላላቅ ጉባዔዎች እንደሚዘጋጁ አስታውቀዋል፡፡
እግዚአብሔር የሀዋሳን ሕዝብ ያጽናናልን!!!
ለአሳዳጆቻቸውም ልቦና ይስጥልን!!!
የእግዚአብሔር ምሕረት፣ ቸርነትና ጥበቃው አይለየን!!!
አሜን!!!Source- http://dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com