Tuesday, March 13, 2012

ሰበር ዜና; ነጭ ለባሹ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ሠራዊት አቡነ ገብርአልን ለማስወገድ የመከረ አስቸኳይ ስብሰባ አካሄደ



በሀዋሳ የተሰደዱት ምዕመናንና ምዕመናት ላይ አስቸኳይ ርምጃ ለመውሰድ ዝቷል

"ማኅበረ ቅዱሳን" የልዩ ልዩ የጥዋ ማኅበራት ሰብሳቢዎችን (ሙሴዎችን) እና የሀዋሳ ማዕከል ኃላፊዎችን ያካተተ ነጭ ለባሽ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ሠራዊት ባደረገው ድንገተኛ አስቸኳይ ስብሰባ፣ አቡነ ገብርአልን ለማስወገድ ሤራ መቋጨቱን ውስጥ ዐዋቂ ምንጮች ከወደ ሥፍራው መረጃ አድርሰውናል፡፡ ትላንት ከምሽቱ ከ12፡00 እስከ 3፡00 ሰዓት  በሀዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የክርስትና ማጥመቂያ አዳራሽ ውስጥ በተካሄደው ስብሰባ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ይትባረክ ታጠቅ ተገኝተዋል፡፡

መልአከ ብርሃን ይትባረክ ታጠቅ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" አባልና የ"ማኅበሩ" ልሳን የሆነው የስምዓ ፅድቅ ጋዜጣ ተከፋይ ዐምደኛ መሆናቸው ሲታወቅ "ማኅበረ ቅዱሳን" በድርጅታዊ አሠራር አቡነ ገብርኤልን ካስመጣ በኋላ ለሥራ አስኪያጅነት አጭቶ ያሾማቸው ምርጥ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ተላላኪ ናቸው፡፡

በዚህ መሠረት ይትባረክ ታጠቅ በስብሰባው ላይ ተገኝተው ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን፣ በንግግራቸው ማጠቃለያም እርሳቸው የሚፈርሙትን አቡነ ገብርኤል እየሻሩባቸው፣ ቀጣሁ ያሉትን እየማሩባቸው፣ ሻርኩ ያሉትን እየሾሙባቸው፣ አባረርኩ ያሉትን እያመጡባቸው በየዕለቱ የሚፈርሙትን ውሳኔ ፍጹም በተቃራኒው መንገድ እየቀለበሱባቸው መቸገራቸውን ገልጸው፣ ትዕግሥታቸው ፈጽሞ ማለቁንና ሥራቸውን ለቀው አቡነ ገብርኤልን ከማያዩበት የትኛውም ቦታ ለመሄድ መወሰናቸውን እልህና እንባ በተናነቀው ስሜት አብራርተዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ የተሰጣቸውን በትረ ሥልጣን በመናቅ፣ ቤተክርስቲያንን ከሁሉም አስበልጠው ማገልገል እና ሁሉንም የቤተክርስቲያን ልጆችን እኩል ማየት ሲገባቸው፣ ከ"ማኅበረ ቅዱሳን" ያውም በገዳሙ ቅጥር ግቢ ውስጥ መመሪያ ለመቀበል መሰብሰባቸው በምን ያህል ዝቅጠት ዓለም ውስጥ እንደተዘፈቁ ያሳያል ተብሏል፡፡

ሪፖርቱን ያዳመጡት የ"ማኅበረ ቅዱሳን" አመራር አባላት በሰጡት ምላሽ፣ ለሥራ አስኪያጁ ለመልአከ ብርሃን ይትባረክ ታጠቅ ያላቸውን ቁርጠኝነትና ድጋፍ ገልጸው፣ "አቡነ ገብርኤል ራሳቸው ይሄዳሉ እንጂ፣ እርስዎ እኛን ጥለው የትም አይሄዱም" ብለዋቸዋል፡፡ ይትባረክ ታጠቅ ሀገረ ስብከቱን ጥለው ከሄዱ እትብት እንደተቆረጠበት ጽንስ ሕይወት እንደሚያጣ ያወቀው "ማኅበረ ቅዱሳን" አቡነ ገብርኤልን በማስወገድና እርሳቸውን በሥራ አስኪያጅነት በማቆየት ሠላም ማምጣት እንደሚቻል ከስምምነት ላይ ደርሷል፡፡

በዚህ ሁኔታ የተበረታቱት አባ ይትባረክ ታጠቅ በአቡነ ገብርኤል ላይ ለሚሠነዘረው የማስነሳት ጥቃት ማናቸውንም ስልት መጠቀም እንደሚቻል ከሰብሳቢ አለቆቻቸው ጋር መክረዋል፡፡

ከዚህም መረዳት እንደሚቻለው፣ በመጪው የግንቦቱ ርክበ ካህናት የሲኖዶስ ጉባዔ የሀዋሳ፣ የዲላና የሌሎቹም በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ አጥቢያዎች የሠላም ዕጦት ጉዳይ መነሳቱ ስለማይቀር አቡነ ገብርኤል በዝውውር ይነሳሉ ብሎ የገመተው "ማኅበረ ቅዱሳን"፣ በምትካቸው እንደ አቡነ ሕዝቅኤል፣ አቡነ ሉቃስ (መኖሪያ ቤታቸውን ለ"ማኅበረ ቅዱሳን" በቢሮነት እንዲጠቀምበት የሰጡ)፣ አቡነ ቀውስጦስ፣ አቡነ አብርሃም፣ አቡነ ቀሌምንጦስና የመሳሰሉትን አስወስኖ በማምጣት ከሥራ አሰኪያጁ ጋር አዋህዶ ለመቀጠል ማቀዱ ታውቋል፡፡

ይህንን የማታውን ስብሰባ ፈጽሞ መካሄዱን የማያውቁትና ያልፈቀዱት አቡነ ገብርኤል ሀገር አማን ብለው  የራሳቸውን ዓለም በመቅጨት ላይ ሲሆኑ፣ እንደማፊያ ሰዎችን ከተጠቀመባቸው በኋላ እንደ ቆሻሻ ዕቃ የትም የሚጥለው "ማኅበረ ቅዱሳን" የደገሰላቸውን ድግስ አልተረዱትም ተብሏል፡፡

በመሠረቱ አቡነ ገብርኤል የሥራ አስኪያጁ ሁኔታ ካልጣማቸው በማስረጃ አስደግፈው ለቅዱስ ፓትርያርኩ አቅርበው ማስነሳት የሚችሉ ሲሆን፣ "ማኅበረ ቅዱሳን" አባ ይትባረክን ሊታደጋቸው አይችልም፡፡ ይሁን እንጂ፣ በ"ማኅበረ ቅዱሳን" ስሌት በዚህም ሆነ በዚያ አቡነ ገብርኤል መነሳታቸው ስለማይቀር፣ ሌላ አፍቃሬ "ማኅበረ ቅዱሳን" ሊቀጳጳስ አስመድቦ፣ ከአባ ይትባረክ ታጠቅ ጋር አስማምቶ ዕድሜውን ማራዘም እንደሚችል የራሱን ግምገማ አድርጎ ደምድሟል ማለት ነው፡፡

ነጭ ለባሹ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ሠራዊት በዚህ ብቻ ሳይወሰን የተሰደዱትን የሀዋሳ ምዕመናንንም ጉዳይ አንስቶ ተወያይቷል፡፡ በዚህም መሠረት የተሰደዱት ምዕመናን "የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሃይማኖት ተከታዮች ነን ካሉ ወደ ቅጥር ግቢው ተመልሰው ይግቡ፣ ካለበለዚያ በሃይማኖታችን ስም መነገድ አይችሉም፡፡ ለዚህም ማንኛውንም መስዋዕትነት ከፍለን እናስቆማቸዋለን" ብለው መማማላቸውን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡

ወደ ተሰደዱት የሀዋሳ ምዕመናን አባላትና ተወካዮች ደውለን፣ ለ"ማኅበረ ቅዱሳን" ዛቻ የሚሰጡት ምላሽ እንዳላቸው ስንጠይቃቸው፣ ስብሰባ መደረጉን እንደሚያውቁና የ"ማኅበረ ቅዱሳን" አባላት በገዳሙ ዘወትር ከሚያደርጉት የተለየ ስብሰባ አድርገው እንደማይወስዱት ገልጸው፣ አቡነ ገብርኤልን አስነሱ፣ አላሰነሱ፣ ጉዳዩ አይመለከተንም ብለዋል፡፡

"ማኅበረ ቅዱሳን" የሃይማኖትና እምነት ሥርዓት ደረጃ መዳቢ፣ ፈቃድ ሰጪም ከልካይም አይደለም፡፡ የሚሠለጥንባቸው አባቶች ካሉ እንዳስለመዱት እነርሱው ላይ ይሠልጥን፡፡ እኛ ግን ዜጎች በነፃነት የማምለክ ካላቸው ሕገ መንግሥታዊ መብት አንፃር ራሳችንን ለይተናል ብለዋል፡፡ ያም ሆኖ ሕንፃ ቤተክርስቲያናት በድሆች ድቃቂ ሣንቲምና ጉልበት ጭምር መገንባቱን ሳንረሳ ስለ ሠላም ብለን ትተንላቸው ወጥተናል ብለዋል፡፡

"እዚህ ላይ ግንዛቤ ሊወሰድልንና በሁሉም ወገኖቻችን ዘንድ ሊታወቅልን የሚገባው ሃይማኖታችን ምንጊዜም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲሆን፣ ይህች እምነታችን ጌታችን መድኃኒታችን በደሙ የዋጃት እንጂ፣ ማንም የሚሰጠን፣ የሚከለክለን እና የኮፒ ራይት ወይም የንግድ ምልክት ሕግ ጥሰት ጥያቄም ሊነሳበት የሚችል አይደለም" በማለት አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ ጋር አያይዘውም "እኛ ከአቡነ ገብርኤል ጋር የግል ጠብ የለንም፡፡ የጠላነው ብልሹ የመልካም አስተዳደር አያያዛቸውን ነው፡፡ ለእኛ ማንም ሄደ፣ ማንም መጣ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ጉዳይ አስፈጻሚ ሊቀጳጳስ እስከተመደበ ድረስ በቤተክርስቲያናችን እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተደርገን መቆጠርን ስለማንሻ፣ ስለወንጌልና ስለመልካም አስተዳደር ብለን ራሳችንን ለይተናል"፤ ብለዋል፡፡

"እንደ ስዩም ያሉ ድንጋይ ወርዋሪ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" አባላት የገዳሙ ሰበካ ጉባዔና ልዩ ልዩ መዋቅሮችን ተቆጣጥረው፣ እንደ አቡነ ገብርኤል፣ እንደ አባ ይትባረክ አሰፌ እና እንደ አባ ይትባረክ ታጠቅ ያሉ ቀንደኛ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" መሥራችና አመራር ያሉ ሰዎች ሀገረ ስብከቱን ቆንድደው ይዘው ባሉበት ሁኔታ፣ ነጭ ለባሽ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ሠራዊት መለያ ባጅ ተሰጥቷቸው ሕዝቡን በዱላና በቆመጥ እያሸማቀቁ፣ ምን ዓይነት ሥርዓተ አምልኮ ነው የሚፈፀመው በማለት ኀዘናቸውን በምሬት ገልጸዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን አጥርቶ የተመሠከረላቸው ገለልተኛ አባቶችና አገልጋዮች፣ ሕዝብ የሚያምንባቸው ገለልተኛ የሰበካ ጉባዔና የልዩ ልዩ ኮሚቴ አባላት ተመርጠው እንዲሠሩ ካልተደረገ፣ እስከ ወዲያኛውም ተመልሰን ወደ ገዳሙ ለባርነት የምንገባበት ሁኔታ አይኖርም" በማለት አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

ውድ የብሎጋችን ተከታታዮች "ማኅበረ ቅዱሳን" በቤተክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ እንደማንኛውም ግለሰብ ከመገልገል በስተቀር በማናቸውም የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ የወጡትን መመሪያዎች በተደጋጋሚ ከመጣሱም በላይ ሥራ አስኪያጅን በቦታው ላይ አቆይቶ፣ ሊቀጳጳስን እሰከ ማሰናበትና እርሱ የሚፈልጋቸውን ሊቃነጳጳሳት እስከማስመደብ በደረሰ ትዕቢት መወጠሩን እዚህ ላይ ልብ ይሏል፡፡

ይህ ብቻም አይደለም በወንጌልና በመልካም አስተዳደር ብልሹነት ከአቡነ ገብርኤል አምባገነናዊ አገዛዝ ራሳቸውን የለዩትን ሕፃናት፣ ወጣቶችና አዛውንት ምዕመናንና ምዕመናት እንዲሁም የሰንበት ት/ቤት አገልጋዮችን እንደግል ዕቃ "ውጡ፣ ግቡ" የሚባሉበት አሠራር በዲሞክራሲያዊ እና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት ውስጥ ለማስረጽ መሞከር "ማኅበረ ቅዱሳን" ምን ያህል በነፍጠኛ ርዕዮተ ዓለም አመለካከት ውስጥ እንደተዘፈቀ ያሳያል፡፡

ከዚህም በላይ ራሱን እንደ ፈቃድ (License) ሰጪ በመቁጠር እርሱ ያልፈቀደው ማንኛውም እንቅስቃሴ መፈጸም እንደሌለበት፣ እርሱ ያዘዘው ደግሞ መከናወን እንዳለበት ዓይኑን በጨው አጥቦ የቤተክርስቲያንን ሥልጣን በከፊል በመውሰድ በማዘዝ ላይ ይገኛል፡፡

ብታምኑም ባታምኑም፣ በሀዋሳ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት በተለይም በመንበረ ጵጵስናው የቅዱስ ገብርኤል ገዳም ከአቡነ ገብርኤል ጀምሮ ወሎዬዎች በአንድ ወገን ተክፈለው አመራሩን የያዙ ሲሆን፣ ጎጃምና ጎንደሬዎቹ በሌላ ወገን ተሰልፈው በዘረኝነትና በጠባብነት አስተሳሰብ ውስጥ በመዘፈቅ በኃይል ሚዛን አጠባበቅ ዙሪያ፣ ውስጥ ውስጡን በመወዛገብ ላይ መሆናቸው በይፋ እየታወቀ መጥቷል፡፡ 

በአብነት ት/ቤቶች ብዛት፣ በዋልድባና በዋሸራ ባለቤትነታቸው የሚመኩት ጎጃሜዎችና ጎንደሬዎቹ በቤተክርስቲያን አመራርም የበላይነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ያምናሉ፡፡ ይህ ብቻም አይደለም አብዛኛውን በጎጃሞችና በጎንደሬዎች የተሞላው "ማኅበረ ቅዱሳን" ራሱን እንደ ሃይማኖት "አስመጪና ላኪ" በመቁጠርና የሃይማኖትና የእምነት ሥርዓቱን እኔው ልምራው በማለት በሥልጣን ሽሚያው ውስጥ የተቻለውን ያህል ድርሻ ለመውሰድ በመተናነቅ ላይ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል ወሎዬዎቹ ይዞታቸውን በማጠናከር ሌሎቹን ኮስተር ባለ አመራር ለመቃኘት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በቅርቡ አንድ "ቢሻው" የሚባሉ ወሎዬ ሰው በሞቱበት ወቅትም፣ ወሎዬው አቡነ ቄርሎስ ለማስቀበር በመጡበት እግረ መንገዳቸውን በሌላው ሀገረ ስብከት ውስጥ ጣልቃ በመግባት በገዳሙ የክርስትና ማጥመቂያ አዳራሽ ውስጥ የተወሰኑ ካህናትን ሰብስበው ለወሎዬው አቡነ ገብርኤል በሙሉ ልባቸው እንዲታዘዙና እንዲያግዟቸው መመሪያ የሰጧቸው ሲሆን፣ ስለ ገዳሙ ስብሰባ ዓላማ ያልሰሙት የገዳሙ አስተዳዳሪ (ጎጃሜ ናቸው) አባ ፍቅር ማርያም ረፈደብኝ ብለው እየተሽቆጠቆጡ ወደ አዳራሹ ይገባሉ፡፡ ከዚያም አቡነ ቄርሎስ ቀበል አድርገው "በል ስማ አንተ! መልአከ ብርሃን ነህ? ወይስ መልአከ ጽልመት፣ መልአከ ሰይጣን"? በማለት አሸማቀው፣ "ስብሰባው አንተን አይመለከትም" ብለው እንዳባረሩአቸው ታውቋል፡፡

"እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ሰጥቶ ዓለምን ያዳነው ያለ ዘር ልዩነት ነው፡፡ ሌላው ሕዝብ ጠባብነትን አስወግዶ ያለ ዘር ልዩነት ተቃቅፎ እግዚአብሔርን በሚያመልክበትና በጋራ በሚረዳዳበት እንዲሁም ለሀገር በርትቶ በሚሠራበት ወቅት የእነርሱ በዘር መናቆር ምን ይሉታል"? ሲሉ አንድ ታዛቢ ከዚያው አካባቢ ገልጸውልናል፡፡

ቀጣዩ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" እርምጃ ምን ይሆን? እየተከታተልን መረጃውን እናደርስላችኋለን፡፡

የእግዚአብሔር ምሕረቱ፣ ቸርነቱና ጥበቃው!
የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃዋ!
የመላዕክት፣ የጻድቃን ሰማዕታት ፀጋና ረድኤታቸው ከእኛ ጋር ይሁን!!!
አሜን!!! source;http://dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com/2012/03/blog-post_13.html