«ክብሬን
ለሌላ አልሰጥም»
በ15ኛ ው ክ/ዘመን የግራኝ ሰይፍ፣ በ16ኛው ክ/ዘመን የጎንደር ሱስንዮስ ሰይፍ፣ ማዕከላዊ መንግሥት እየተዳከመ የተፋጀበትና እስከ18ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ድረስ የዘመነ መሳፍንት የእርስ በእርስ ሰይፍ፣ በ19ኛው ክ/ዘመን የግብጾችና ድርቡሾች ሰይፍ፣ የጣሊያን ሰይፍ፣ እንደገና በ20ኛው ክ/ዘመን የጣሊያን ሰይፍ ሀገሪቱን ጎብኝቷታል። ይህ ሁሉ ሰይፍ እንግዲህ በድርቅና በወረርሽኝ መልክ እየተከሰተ የተፈጀውን ሳይጨምር መሆኑን ልብ ይሏል። በዘመን ቀመር ስንዘረዝረው
ደግሞ ይህንን እናገኛለን።
(by dejebirhan) to read in PDF (Click here)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ድርሻ አላት። በቀደሙት ዘመናት ውስጥ ሃይማኖታዊ መንግሥት የሀገሪቱ አስተዳደር ሥርዓት ስለነበረ ቦታዋና ወሳኝነቷ አሌ ሊባል የማይችል እውነት ነው። ቤተክርስቲያኒቱ ያልፈቀደችው ሰው ዙፋን ላይ ሊወጣ አይታሰብም ነበር። በጉልበትም ይሁን በዘዴ አንዱ አንዱን አጥፍቶ ሥልጣን ላይ ቢወጣ እንኳን የቤተክርስቲያኒቱን እውቅና ለመጠየቅ መገደዱ አይቀርም። የንጉሠ ነገሥትነቱ ክብር እሷ ካላጸደቀችው የጸና ስለማይሆን ይህንኑ ለመስጠትና ለመፍቀድ ድርሻዋ ትልቅ ነው። በእርግጥም «እምነ መንግሥት የዐቢ ክህነት» እንደሚለው ቃሉ ቢያንሳት እንጂ ይህ ድርሻዋ የሚበዛባት አይደለም። ከተወሰነኑ ወቅቶች ማለትም ከወለተ ጌዴዎን ዮዲት 40 ዘመንና ከኢብን ኢብራሂም አልጋዚ (ግራኝ) የ15 ዓመታት ወረራ ጊዜያት በስተቀር የቤተክርስቲያኒቱ ሥፍራ ላለፉት 1600 ዓመታት ከቤተመንግሥቱ የራቀ አልነበረም። በዚህም የተነሳ ቤተክህነቱ ከቤተመንግሥቱ አልራቀም ወይም ቤተመንግሥቱ ከቤተክህነቱ አልወጣም ማለት ይቻላል።
በነዚህ ዘመናት ሀገርን በማስከበር፣ በተለይም ዛሬ ኢትዮጵያ የምንላትን ሀገር ከመገንባትና ከመጠበቅ አንጻር፣ ፊደላትንና ስነ ጽሁፋትን በማስፋት፣ ቅርስን እንዲሁም ትውልዱን ከታሪክ፣ ታሪኩን ከሀገር ጋር በማስተሳሰር ረገድም ሚናዋ የጎላ ነው። ብዙ ብዙ ሊባልላት እንደሚቻል የሚታወቅ እውነታ ነው።
ከዚሁ ጋር በተነጻጻሪ ነገሥታቱ በዘመናቸው በሰሯቸው መልካምም ይሁን መጥፎ ስራቸው ድርሻዋ አብሮ የሚታይ መሆኑንም መካድ አይገባንም። ለምሳሌ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ደቂቀ እስጢፋኖስ የተባሉ ክፍሎችን አንድ በአንድ እየለቀሙ ጆሮ እየቆረጡና አፍንጫ እየፎነኑ ሲያሰቃይዋቸው መናፍቃንንና ጸረ ማርያሞችን ማስወገድ ነው በማለት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ትብብሯን አሳይታለች። እነዚህን መናፍቃን አሰቃይቶ መግደል ተገቢ እንደነበር በማመንና በማሳመን በየተአምራት መጻሕፍቱና በየታሪክ ድርሳናቱ ጽፋ አቆይታለች። ዛሬም በነዚሁ ታሪክ የጸሎት ቡራኬ ይደርስባቸዋል።
ጉዳዩን አስቸጋሪ የሚያደርገው መናፍቃንንና ጸረ ማርያም የተባሉትን (ለዚያውም ሆነው ከተገኙ) እየለቀማችሁ አጥፏቸው የሚል አስተምህሮ አለ ወይ ብለን ብንጠይቅ የእውነቱን ጽዋ ለመጠጣት ካላስቸገረን በስተቀር በወንጌል አለሁ የሚል ማንም ቢኖር ይህንን በፍጹም ሊቀበል የሚችለው አይደለም።
«እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና» ማቴ 5፣44
ብላ የምታስተምር ቤተክርስቲያን የነገሥታቱን የግድያ ተግባር ደግፋ ብቻ ሳይሆን አሞካሽታ ስታበቃ ግድያቸውን የጽድቅ ተግባር አድርጋ መጻፏ ወንጌል አልተሰበከም ወይም ሃይማኖቱ የቆመው ሠይፍ በታጠቀው ንጉሠ ነገሥት ብርታት ነው ለማለት እንደፍራለን።
መቼም እንደዚህ ዓይነት ጠጠር ያለ ግን እውነተኛ ጽሁፍ በአክራሪዎች የሚታየው ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት እንደሚነገር እንጂ በሰራነው መልካም ነገር መሞገስን እንደምንሻው ሁሉ ባጠፋው ነገር ደግሞ ልናዝን እንደሚገባን ለማሰብ በማይችሉ ሰዎች ዘንድ ይሆናል። «በሽታችንን ደብቀን መድኃኒት እናገኛለን ማለት ዘበት ነው»
ምንም ይሁን ምንም ነገሥታቱ በፈጸሙት ግድያና ትውልድን ለቅሞ የማጥፋት ዘመቻ አብራ በተሰለፈችው ቤተክርስቲያናችን ላይ አመልከዋለሁ የምትለው ኢየሱስ ክርስቶስ «እሰይ አበጀሽ፣ ለእኔ ስትይ ልቅምቅም አድርገሽ ስለፈጀሻቸው ደስ ብሎኛል» የሚል የምስራች ይነገራታል የሚል ቢኖር እሱ ክርስቶስን የማያውቅ ሰው መሆን አለበት ብለን እውነቱን አስረግጠን እንናገራለን።
ምክንያቱም ለሰቀሉት ይቅርታ የጠየቀ፣ ለሚገድሉ ክብርንና ጸጋን ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅምና ነው።
«ኢየሱስም፦ አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ። ልብሱንም ተካፍለው ዕጣ ተጣጣሉበት» ሉቃ 23፣34
ስለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመልካምነትዋና በጥሩ ስራዋ በሀገራችን ታሪክ ከፍ አድርገን እንደምናያት ሁሉ በመጥፎ ነገሯና ይህንን መጥፎ ነገሯንም እንደጀብድ የምትቆርበትን የሚያሳዝን ተአምራዊ ድርሰቷን አንብበን ልናፍርብ ይገባል። ወደድንም ጠላንም የእነዚያን የእግዚአብሔር ፍጡራን ደም ከሰማይ ይጮሃል! እግዚአብሔርም ደማቸውን ከእጃችን ይፈልጋል።
እስኪ ከእነ አባ እስጢፋኖስ ፍጅት በኋላ የሆንነው እንይ!
1/ ግራኝ ሀገሪቱን በወረረበት ዘመን ከሠራዊቱ አንዱ ቢያንስ ዘጠኝና ከዚያም በላይ በቅሎዎችን ጭኖ ትግራይ ውስጥ ገብቷል፣ ከዓመታት በኋላ ግን ከድርቅ ኃያልነት የተነሳ አንድም እንኳን እስከማይቀር ድረስ አልቀዋል። የግራኝ ወንድ ልጅ አህመድ አል ነጋሲ የሞተውም ያኔ ነበር። አብዛኛው የትግራይ ሰው በድርቁ አልቋል። (Futuh Al Habasha)የአረብ ታሪክ ጽሁፍ እና (The Conquest
of Abyssinia; by Pual Lester stenhouse) page 367 & 373
2/ ከ1543 እስከ 1567 ዓ/ም ገደማ ታላቁ የሐረር የድርቅ እልቂት ተብሎ የሚታወቀው ሲሆን ይህም (Islam In
Ethiopia by J. Spencer Trimingham; p.94) ተዘግቧል።
3/ ከ1633- 1635 ዓ/ም ድረስ በትግራይ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ሰብል አውድሞ አልፏል። በዚሁ ዘመን ከጎንደር ደምቢያ ተነስቶ እስከትግራይ የዘለቀው «ከንትር» ወይም «ፈንግል» የተሰኘው የኰሌራ በሽታ ሺዎችን ገድሎ አልፏል።
4/ በ1678 የጋማ ከብቶች በሽታና በ1700 ሰብስቴዎስ ገዢ በነበረበት ዘመን በሸዋ የተከሰተው ረሃብ ብዙ ሕዝብ ፈጅቷል። (by Donald
Lavine; Wax and Gold, P. 32)
5/1796 This
famine was particularly serious at Gondar, and blamed on an infestation of
locusts. 1797 From the Royal Chronicle 1800 Soldiers died on campaign due to
famine. 1829 Famine in Shewa, followed by a cholera outbreak 1830-1. 1835 Rains
failed, leading to famine and "great mortality" throughout Shewa.
1880–1881 Cattle plague (1879) spreads from Adal region, causing famine as far
west as Begemder. (by Dr Richard pankhurst)\
6/ ከ1888-1892 ድረስ በመላ ሀገሪቱ ኰሌራ፤ ፈንጣጣና ድርቅ ብዙ ሕዝብ ፈጅቷል።
7/ መጠኑ ይለያይ እንጂ ከ1900 እስከ1929 ድረስ ድርቅና በሽታ ብዙ እልቂት ማስከተሉ አልቀረም። ከዚህ ውስጥ የከፋው ደግሞ በ1950 ዓ/ም በትግራይ ብቻ ከ100 ሺህ ሰው በላይ የገደለው ድርቅ የሚጠቀስ ነው።
(Baharu
Zewdie; History of Modern Ethiopia, P.196)
8/ በ1966 የተከሰተውና በተለምዶ የወሎ ድርቅ የተባለው ከወሎ ብቻ ከ80 ሺህ በላይ ሰው ቀጥፏል።
9/ በ1977 ዓ/ም በደርጉ በተከሰተው ድርቅ ከ2 ሚሊየን በላይ የተጎዳ ሲሆን ከዚህ ውስጥም ከ400 ሺህ በላይ ሰው ገድሎ ማለፉም የሚዘነጋ አይደለም።
እንግዲህ ይህ ሁሉ ሲሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከመንግሥት ጋር መሆን ብቻ ሳይሆን ከመንግሥት ድርሻ ሲሶው የእርሷው ሆኖ ከምእመናኖቿ ድርሻዋን ስትቀበል መቆየቷ ሳይዘነጋ ነው። የሰላሌ ገበሬ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ላይ ያነሳው የሲሶ ገፈፋና የሰፋፊ መሬት ጥያቄዎች የደርግ መንግሥትን ማራገብ ያስታውሷል። ታሪክ እንደሳየን «ደርግ» የተባለ ድርቅን፣ ሰይፍን የተሸከመ ኃይል ከዚህ መጣ ሳይባል ኢትዮጵያን አዙሪትና እልቂት ውስጥ መክተቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ይህ ሁሉ ቁጣ በሀገሪቱ ሕዝብ ላይ የወረደው « ሀገራችን ሀገረ እግዚአብሔር እና ሕዝቡን ሕዝበ እግዚአብሔር ነው» እየተባለ ዝማሬ ሳያቋርጥ ነው። ነገሩ ግን እንደምንለው ሳይሆን እንዳላሰብነው መሆናችን የተደበቀ ችግር እንዳለ አመላካች ነው። የጎንደር ነገሥታት አነሳስና አሟሟት፣ የአፄ ቴዎድሮስ አነሳስ፣ጭካኔያቸውና የቤተክርስቲያን ድርሻ፤ አሟሟታቸው፣ የበዝብዝ ካሳ ፍጻሜና የምንሊክ አነሳስ፣ የኢያሱ አወዳደቅና የተፈሪ እንደራሴነት ኋላም ንግሥና ሁሉም ጋር ቤተክርስቲያን አለች። ቋንቋ አልባ ጳጳሳትና እጨጌዎች፣አብረው ነበሩ። ከራሶች፤ ከፊታውራሪዎችና ከደጅ አዝማቾች ጀርባ ቤተክርስቲያን አለች።
ደርግ የተባለው ዱላ ተቆርጦ ከወደቀብን ጊዜ አንስቶ ከድርቁና ከጦርነቱ ውጪ በቀይ ሽብር ብቻ ከ500 ሺህ በላይ ወጣት እንደወጣ መቅረቱንም ታሪክ ዘግቧል። ቤተክርስቲያኒቱም ፓትርያርኳን ገብራለች። ከቤተክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ ግድያ ጀርባ እኔ የለሁም፤ ከደሙ
ንጹህ ነኝ ብላ እንደጲላጦስ እጇን ልትታጠብ አትችልም። አስረጂዎች
አባቶች የምትላቸው ላይ ጣታቸውን ይቀስራሉ። በዚህም ንስሐ አልገባችም። ይህም መራራ እውነት ነው። ዛሬም እንደዚያው ዘመን ከወጪውና ገቢው ዶሴ ጀርባ መኖሯ ሀቅ ነው። በዚህም በዚያም ወገን በጎራ ተከፍላ እየተተጋተገች መኖሯን የሚክድ የለም። ደርግ መሪዋን ገድሎና ሀብቷን ቀምቶ፤ንብረቷን ዘርፎ፣ ልጆቼ ናቸው የምትላቸውን
ሺዎች አፍላ ወጣት ሲሰለቅጥ ዝምታዋ ከጴጥሮስ ወዲያ ምን ተዳዬ አለማለቷን አያሳይ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስን ሲያስጥል ፈቃደኝነቷን ከማሳየት በስተቀር ለምን አለማለቷ የ17
ዓመት ቅጣቷን አላሳየንም? ይህ ሁሉ ሲሆን «ሀገረ እግዚአብሔር ነን» ማለቷን ግን አላቋረችም። የኛው አጥፊነት እንጂ ጥፋት ያመጣብን እግዚአብሔር ግን ከየትኛውም ግድያና ጥፋት ጋር አብሮ እንዳልነበረ ጥርጣሬ የለብንም። እውን ሀገረ እግዚአብሔር ስለሆንን ነው? ለ500 ዓመታት ሳያቋርጥ ረሃቡ፤ድርቁ፤ጦርነቱ፣እርስ በእርሱ ፍጅቱ ያላቆመው? ብለን ልንጠይቅ እንገዳደለን። ሀገሪቷ ይህንን ሁሉ እልቂት ማሳለፏ ሳያንስ የሀገር ድርቅ መትቷት መበጣጠስስ የጀመረችው፣ እውን እግዚአብሔር ፍቅሩን ለመግለጹ ምልክት ይሆን? ይህ እራስን ለመሸንገልና በከንቱ ተስፋ ከመከራው ለመደበቅ የፈጠርነው መሸሸጊያ እንጂ የእግዚአብሔርን ማንነትና ፍቅር የሚያንጸባርቅ አባባል አይደለም። ይህንን ለማለት የሚያስችለን የእግዚአብሔርን ባህርይ እውነትን እንጂ እንደእኛ ምኞት የማይናገረው መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያረጋግጥልን ከቃሉ ጥቂት እንመዛለን።
ለዚህ ነገር ምሥክር ነህምያ የተባለው የእስራኤል ሰው ነው። በአንድ ወቅት እስራኤሎች ለእግዚአብሔር ባለመገዛት ዐመጽ የእልቂት ዱላ ወርዶባቸው ባቢሎን ወርደዋል። ከዚያም እንባን የሚያብስ አምላክ ወደቀደመው ተስፋቸው ይመለሱ ዘንድ ከተላከው አንዱ ነህምያ ስለደረሰባቸው ነገር ሁሉ እንዲህ ሲል ጸሎቱን አሰምቷል።
«ወደ ሕግህም ትመልሳቸው ዘንድ አስመሰከርህባቸው ነገር ግን ታበዩ፥ ትእዛዝህንም አልሰሙም፥ ሰውም ባደረገው ጊዜ በሕይወት የሚኖርበትን ፍርድህን ተላለፉ ትከሻቸውንም ሰጡ፥ አንገታቸውን አደነደኑ፥ አልሰሙምም።ነገር ግን ብዙ ዓመታት ታገሥሃቸው፥ በነቢያትህም እጅ በመንፈስህ መሰከርህባቸው አላደመጡም፥ ስለዚህም በምድር አሕዛብ እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው፤ነገር ግን አንተ ቸርና መሐሪ አምላክ ነህና በምሕረትህ ብዛት ፈጽመህ አላጠፋሃቸውም፥ አልተውሃቸውምም፣አሁንም አምላካችን ሆይ፥ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና ኃያል የተፈራኸውም አምላክ ሆይ፥ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛና በነገሥታቶቻችን በአለቆቻችንም በካህናቶቻችንም በነቢያቶቻችንም በአባቶቻችንም በሕዝብህ ሁሉ ላይ የደረሰው መከራ ሁሉ በፊትህ ጥቂት መስሎ አይታይህ፣በደረሰብንም ነገር ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፥ አንተ እውነት አድርገሃልና፥ እኛም ኃጢአት አድርገናል፣ነገሥታቶቻችንም አለቆቻችንም ካህናቶቻችንም አባቶቻችንም ሕግህን አልጠበቁም፥ የመሰከርህባቸውንም ትእዛዝህንና ምስክርህን አልሰሙህም» ነህ 9፣29-34 እንዳለው የሆነብንና እየሆነብን ያለው ከእኛ ኃጢአት የተነሳ ብቻ ነው።
በእርግጥ ግን እየተቀጣን ያለነው ስለሚጠላን ሊያጠፋን ፈልጎ ሳይሆን ስለሚወደን ወደእሱ እንድንመለስ፣ ኃጢአታችንን በፊቱ እንድንናዘዝ፣ ምሕረቱንና ቸርነቱን እንድንጠይቅለት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። «እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ እቀጣቸውማለሁ፤ እንግዲህ ቅና ንስሐም ግባ» ራእ 3፣19
ከዚህ ውጪ እግዚአብሔር ሲቀጣም ምክንያት እንዳለውና ሲምረውም ምክንያት እንደሚጠይቅ ካለመረዳት የተነሳ ዝም ብለን በደፈናው «እኛ የእግዚአብሔር ሰዎች ነን» የሚለው ማታለያ ቃል መከራችንን ከሚያበዛና የእግዚአብሔርን የረጅም ዘመናት ትዕግስት ጨርሶ ከሚያርቀው በስተቀር መፍትሄ አይሆንም።
ለ500 ዓመታት የወረደው መከራ ሳያበቃና ሀገሪቱ መቆራረጧ ሳይፈጸም፤ ዛሬ ደግሞ ቤተክርስቲያኒቱ ራሷ ወደ መቆራረጥ መውረዷ ምንን ያመለክታል? እርስ በእርሳችን ከመከፋፈላችን በላይ ውስጣችን ጥርጣሬና ግለኝነት ነግሶ ፍጭትና ቡድናዊ ስሜት ከወዲያ ወዲህ መስተጋባቱ እውን የኃጢአት ውጤት አይደለም? ገሚሱ ይነግዳል፣ ገሚሱም ያምሳል።
አሰቦት ተቃጠለ፣ ዝቋላ ነደደ፣ ዋልድባ ታረሰ ጩኸት የኃጢአት ውጤት እንጂ የእግዚአብሔር በረከትን መብዛት አያመለክትም። የሚጮሁት ራሳቸው ኃጢአት የፈጠራቸው ከመሆን ውጪ ወደእግዚአብሔር እውነተኛው መመለስ የተላኩ ነብያት አይደሉም።
መፍትሄ የሚገኘው የኃጢአታችንን ስር ስናውቅ ብቻ ነው። ለእስራኤላውያን ይህን ተነግሯቸው አልሰሙም።
ኢሳ 1----
14 መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች ሸክም ሆነውብኛል፥ ልታገሣቸውም ደክሜያለሁ።
15 እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፥ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል።
16 ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንጹ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ ክፉ ማድረግን ተዉ፥
17 መልካም መሥራትን ተማሩ፥ ፍርድን ፈልጉ፥ የተገፋውን አድኑ፥ ለድሀ አደጉ ፍረዱለት ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ።
18 ኑና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች።
19 እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ
20 እምቢ ብትሉ ግን ብታምፁም፥ ሰይፍ ይበላችኋል የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።
ዛሬስ እየሆነብን ያለው ምንድነው? ቤተክርስቲያንን የሚጠብቁ እረኞች አሉን? ለንስሐ እንድንጮህ የሚማልዱን የት ናቸው? ነጣቂ ጩልሌዎች አልሰለጠኑብንም? ዝማሬ የሚያሰሙ ግን በላተኞች አልከበቡንም? በሽታው፤ድርቁ፤ ስደቱ፣ ልዩነቱ፣ ክፍፍሉ አልነገሰብንም? ሰርቶ መና፣ ለፍቶ ባካና፣ ደክሞ ባዶ አልሆንምን? አንድ ሀገር ሳለን ድምጻችን፣ ለችግሮቻችን ጩኸታችን መተባበር አቅቶት እንደሰናዖር ሰዎች ተደበላልቆ እየተሰማማን መደማመጥ ያቃተን ለምን ይሆን? የ2000 ዘመን እድሜ ይዘን 45 ሚሊዮን አባላት አሉን እያልን ስንኩራራ 50 ዓመት ያልሞላቸው ይልቁንም ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ወንጌላውያኑ ወደ 16 ሚሊየን ማደጋቸው ለምን ይሆን? ሰው በፋብሪካ እያመረቱ ነው? እውነታው ያ አይደለም። በተሰጠን የንስሐ ዘመናት መጠቀምን ስላልቻልን አሁን ከመቅጣት ይልቅ ወደማስቀናት እግዚአብሔር እየሄደ መሆኑን ነው።
«ዳሩ ግን። ባይሰሙ ነው ወይ? እላለሁ። በእውነት። ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ
ነገር ግን። እስራኤል ባያውቁ ነው ወይ? እላለሁ። ሙሴ አስቀድሞ። እኔ ሕዝብ በማይሆነው አስቀናችኋለሁ በማያስተውልም ሕዝብ አስቆጣችኋለሁ» ሮሜ 10፣19
እንዳለው ቀድመው የታወቁት እስራኤላውያን ቀድመው በተገለጠው የወንጌል እውነት መኖር ሲገባቸው ገሸሽ ስላደረጉት ያልተጠበቁና ያልታወቁ ወገኖች የወንጌል ሰው መሆናቸውን ይነግረናል። ስለሆነም ወንጌላውያኑን እኛ እንደምንለው የማይጸድቁ ናቸው ብለን ብንናገርም እግዚአብሔር ሳይፈቅድ ግን ከምንም ተነስተው በ20 ዓመት ውስጥ የኛን ግማሽ ለማደራጀት መቻላቸውን መካድ ለማወቅ ካለመፈለግ የሚመነጭ ሃሳብ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምን ይባላል?
ግብረ ሰዶምና ውርጃ የኃጢአቱ የመጨረሻ ጫፍ መሆኑም ልንክድ አይገባም። ዝምታችንስ ለእግዚአብሔር ቃል ያለመገዛት እምቢታችን አንዱ መገለጫ አይደለንምን?
ሲጠቃለል ለ100 ዓመታት ሳያቋርጥ ከያሉበት እየታደኑ የተፈጁት (ከሃዲዎች ይሁኑ መናፍቃን እግዚአብሔር እውነታውን ያውቃል) በእኛ ውሳኔ የተገደሉት የእነ አባ እስጢፋኖስ ደም በመፍሰሱ ያበራልን ደብረ ብርሃንን ሳይሆን የቁጣ መብረቅ ነውና እስካሁን ላጠፋነው ሁሉ ወደእግዚአብሔር ንስሐ እንግባ፣ እንጩህ፣ እንደቃሉ ለመኖርም ቃሉን የሚያጣምም የጥፋትና ከአምላክ የሚያጣላንን ግሳንግስ ለእግዚአብሔር ክብር ስንል እናስወግድ! በውስጣችንም ሆነ በጸሎት ቤታችን የእግዚአብሔርን ዙፋን ብቻ እንትከል! ደባል ወይም ማጋራት በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው።
«ስለ ስሜ ቍጣዬን አዘገያለሁ፥ እንዳላጠፋህም ስለ ምስጋናዬ እታገሣለሁ፤እነሆ፥ አንጥሬሃለሁ ነገር ግን እንደ ብር አይደለም በመከራም እቶን ፈትኜሃለሁ፣ስለ እኔ፥ ስለ ራሴ አደርገዋለሁ ስሜ ተነቅፎአልና ክብሬንም ለሌላ አልሰጥም፤ያዕቆብ ሆይ፥ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማኝ እኔ ነኝ እኔ ፊተኛው ነኝ እኔም ኋለኛው ነኝ»ኢሳ 48፣9-12
የነጻ ወጪና የነጻ አውጪ ትግልና ድምጽ የፈየደው ነገር አለመኖሩ ሳያንስ በሳበው ጉተተው ፍትጊያ ዛሬም ብዙዎች ይሞታሉ፣
ይሰደዳሉ፣ እረኛና ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በበረሃ ይንከራተታሉ። ቤተክርስቲያኒቱ ደግሞ እንኳን እረኝነቷን ልታሳይ ይቅርና ራሷም
እረኛ የሌላት ሆና ከወዲህም በገንዘብና በባእድ የዲሞክራሲ ኃይል በወዲያም በጡንቻና በበትር ኃይል ተጠብቀው እግዚአብሔር ምን ያደርግልናል
ከተባለ ዓመታት ተቆጥረዋል። እውነታው መራራ ቢሆንም ቤተክርስቲያን ስጋውን የሚንከባከብና የሚወድ መሪ እንጂ ስለበጎቹ ራሱን አሳልፎ
የሚሰጥ የእግዚአብሔር ሹመኛ እንደሌላት ምንም ጥርጥር የለውም።
በአጭሩ «በመስኮት ተገባ፣ በመስኰት ተወጣ» ሌላ ሀተታ ማስከተል ስለበጎቹ የሚገደውን እረኛ ማንነት ከወንጌሉ የምናነብ
ስለሆነ ጉንጭ አልፋ ከመሆን አያልፍም። ቤተክርስቲያኒቱ ለዘመናት ተከትሏት የመጣውና እሷም ከዚያው ታዛ ሳትወጣ የቆየችበት የቤተመንግሥቱ
ሲሶ መንግሥትነት ሃብቱ ቢቀር እንጂ ጡንቻው ግን ዛሬም አልተለያትም። ፍጥጥ ያለው ሀቅ ይህ ነው። ከመሪዎች ጥሩነትና መጥፎነት
ጋርም አለች። «ሀገረ እግዚአብሔር፣ ሕዝበ እግዚአብሔር» የሚለው ቃል ከድምጸት ባለፈ እውነታውን በምድር ላይ አያሳይም። ይልቁንም
ይህ ይስማማን ይሆናል።
«የእግዚአብሔር መቅደስ፥ የእግዚአብሔር መቅደስ፥ የእግዚአብሔር መቅደስ ይህ ነው እያላችሁ በሐሰት ቃል አትታመኑ፣መንገዳችሁንና
ሥራችሁን ፈጽማችሁ ብታሳምሩ፥ በሰውና በጎረቤቱ መካከል ቅን ፍርድ ብትፈርዱ፣መጻተኛውንና ድሀ አደጉን መበለቲቱንም ባትገፉ፥ በዚህም
ስፍራ ንጹሕ ደምን ባታፈስሱ፥ ክፉም ሊሆንባችሁ እንግዶችን አማልክት ባትከተሉ፣ከዘላለም እስከ ዘላለም ለአባቶቻችሁ በሰጠኋቸው ምድር
በዚህ ስፍራ አሳድራችኋለሁ፣እነሆ፥ በማትረቡበት በሐሰት ቃል ታምናችኋል።ትሰርቃላችሁ፥ ትገድላላችሁ፥ ታመነዝራላችሁ፥ በሐሰትም ትምላላችሁ፥
ለበኣልም ታጥናላችሁ፥ የማታውቋቸውንም እንግዶች አማልክት ትከተላላችሁ፤መጣችሁም፥ ስሜም በተጠራበት በዚህ ቤት በፊቴ ቆማችሁ። ይህን
አስጸያፊ የሆነ ነገርን ሁሉ አላደረግንም አላችሁ።ይህስ ስሜ የተጠራበት ቤት በዓይናችሁ የሌቦች ዋሻ ሆኖአልን? እነሆ፥ እኔ አይቻለሁ፥
ይላል እግዚአብሔር» ኤር 7፣ 4-11
እኛ ዘንድ የሆነው ይህ ነው።ከሆነብንና ከሆንነው ለመውጣት ስለዚህ ምን እናድርግ? መልሱ ያለምንም ማቅማማት በደላችንን እንመን! በዝምታችን ለፈሰሰው ደም ሁሉ
ከእጃችን የደሙን ዋጋ እግዚአብሔር ይፈልጋልና ንስሐ እንግባ! የክርስቶስ ጠበቃ ሆና የተወከለች ቤተክርስቲያን ለእውነት ብቻ መሞት
ሲገባት በውሸት አእላፍ ሲሞቱ ዝም ብላለች። በእነእስጢፋኖስ ደም የእሷም እጅ ተነክሯል። አንዱ ወድቆ፣አንዱ ሲወጣ በነገሥታቱ ስጋዊ
ፍትጊያና የሥልጣን ሽኩቻ ጀርባም አለች። ይህም ታሪክ ያኖረው እውነት ነው። ስለአጥፍቶ ጠፊና ተጠፋፊ ልጆቿ ሁሉ ልታዝንና ልታለቅስ
ይገባት ነበር ግን አልሆነም። እነሆ ለ500 ዓመት እዳውን እየከፈለች መጨረሻው ላይ እራሷ ለመጥፋት መስዋእት ሆና እየታየች ሳለ
ዛሬም አለሁ ትላለች። እውነታው ግን ዛሬ አባት የለም፤ ሲኖዶስ የለም፤ ቅዱስ ማኅበር የለም፤ካህን የለም፣ ዲያቆን የለም፤ መሪ
የለም፤ ያለው ነገር ነጋዴ፣ ገንዘብ፤ ጡንቻና የማጭበርበር ሕግ ብቻ ናቸው።
የተነገራቸውን ያልሰሙ የዮሐንስ ራእይ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የጠፉት «ከአፌ ልተፋህ ነው» የተባለውን ባለመስማት
የተነሳ ነው።
ስለሆነም የእግዚአብሔርን ክብር እንመልስ፣ ከኃጢአታችንንና በእጃችን ካለው ደም እንጽዳ፣ ንስሐ እንግባ! ቅድስና ቦታው ይመለስ፣ ወርቅና ርግብ ለዋጮች ተጠርገው ይውጡ! በአንዱ
መንጋ ውስጥ የተሸሸጉ ሽኰኰዎች ይጠረጉ! እግዚአብሔርን የሚያስቀናና ክብሩን የሚቀማ ምናምንቴ ነገር ይወገድ! ያለበለዚያ ግን መቅረዙን ያለጥርጥር ከቦታው የሚያነሳበት ዘመን ደርሷል!!
ክብሩን እንመልስ፤ እጃችንንም እንታጠብ!!