(የደጀብርሃን ልዩ ዘገባ) ፖፕ ሺኖዳ ሳልሳዊ አረፉ! ፎቷቸው ላይ ሀገሬ በሰማይ ነው የሚሉ ይመስላሉ!
የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ሆነው ከ1971(እ ኤ አ) ጀምሮ በማገልገል ላይ የነበሩት ፖፕ ሺኖዳ ሳልሳዊ
በፕሮስቴት ካንሰር፣ በጉበትና ሳንባ በሽታ ለዓመታት ሲሰቃዩ ቆይተው በተወለዱ በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ፖፕ ሲኖዳ በኮፕት ክርስቲያን ልጆቻቸው ዘንድ እጅግ በጣም ተወዳጅና ተፈቃሪ የነበሩ ሲሆን በበሽታ እየተሰቃዩ ከወንጌል
አስተምህሮ ሳይለዩ፣ ቅዳሴ ሳያቋርጡ፣ በሐዋርያው ጉብኝቶቻቸው፣ አድባራትና ገዳማቶቻቸውን በማጽናናት ሌሊትና ቀን ደክመው አገልግሎታቸውን
ለግብጽ ቤተክርስቲያን በትጋት ፈጽመው ያለፉ ታላቅ አባት ነበሩ። «ባባ ሹኑዳ» እያሉ የሚጠሯቸው ልጆቻቸው አስተምህሮአቸውን ለመስማት
ሲሽቀዳደሙ፣እግሮቻቸውን፣ እጆቻቸውን ለመሳለም ሲሰለፉ ማየት እንግዳ ነገር አይደለም። ይህ ሁሉ ለክርስቶስ ቤተክርስቲያን የተሰለፉበትን
አባታዊ ተልእኰ በመፈጸም እድሜአቸውን ሙሉ ባበረከቱት ትጋት የተነሳ የተሰጣቸው ትልቅ ክብር እንጂ ለውዳሴ ከንቱ እንዳልሆነ ሁላችንም
የምንመሰክረው ሐቅ ነው። በአንድ ወቅት በቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ ትምህርተ ወንጌል አስተምረው የተናገሩትና
እሳቸው አልቅሰው ምእመናኑን ሁሉ ያስለቀሱት መቼም አይረሳም።
እንዲህ አሉ! «ልጆቼ ካስተማርኳችሁ ሁሉ ያልነገርኳችሁ ብዙ ነገር በልቤ ውስጥ አለ፣ እሱን ለእናንተ አልነግርም ፣
የልቤን ለሚያውቅ ለኢየሱስ ለክርስቶስ ትቼዋለሁ» ሲሉ ቁጭ ባሉበት ስቅስቅ ብለው አለቀሱ።ቤተክርስቲያኑን የሞላው ሕዝብ ተከትሎ
አለቀሰ። ቅዳሴውን በቀጥታ ስርጭት ይከታተል የነበረው ሁሉ በየቤቱ አነባ። አዎ ፓትርያርኩ ብዙ ምስጢራቸውን፣ችግራቸውንና ስለቤተክርስቲያን
ያላቸውን ጭንቀት የመፍትሄ ባለቤት ለሆነው ለክርስቶስ ይነግሩ ነበር። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚያቀርቧቸው ሃሳቦቻቸው መካከል «ክርስቶስ
የሰጠን አንዲቱን ቤተክርስቲያን ሆኖ ሳለ እኛ ተለያይተን እንዴት ክርስቶስን በእውነት እናመልካለን፣ ክርስቶስን ይህን እያየ ዝም
የሚለው እስከመቼ ነው?» እያለ እለት እለት የሚያሳስባቸውን የቤተክርስቲያን ጉዳይ የሚያነሱ ባለትልቅ ራእይ አባት ነበሩ።
በሰሜን የኤልሳሄል፣ በምሥራቅ ከሻራቢያ፣ በምእራብ የኤልፋራግ ክፍለ ከተሞች በሚያዋስኗት የባቡር መንደር በሆነች ው
«ሹብራ» በካይሮ ከተማ ቅዱስ እንጦንስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ወጣቱ
ናዚር ጋየድ አገልግሎታቸውን ጀመሩ። ከዚያም የሰንበት ት/ቤቱ አስተማሪ ሆነው ተሾሙ። እንደገናም በማህሻማ ቅድስት ማርያም ቤክርስቲያን ውስጥም ተዛውረው አገልግለዋል።
የበለጠ እውቀት ለመገብየት ወደካይሮ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት በታሪክ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ከያዙ በኋላ እዚያው ካይሮ ከተማ ውስጥ በ2ኛ
ደረጃ ት/ቤት ውስጥ የእንግሊዝኛ ቋንቋና የማኅበራዊ ጥናት መምህር ሆነው ተቀጠሩ። በ2ኛ ደረጃ ት/ቤት መምህርነት እያገለገሉ ሳለ በማታው ክፍለ ጊዜ ደግሞ በኮፕቲክ
ቲኦሎጂካል ኮሌጅ በመማር የመጀመሪያ ድግሪያቸው በነገረ መለኰት ትምህርት በ1949 ዓ/ም አገኙ። ያን ጊዜ የ2ኛ ደረጃ መምህርነታቸውን
ትተው እዚያው በተመረቁበት ኮሌጅ የአዲስ ኪዳን መምህር ሆነው ተቀጠሩ። እስከ 1954 ዓ/ድረስ በመንፈሳዊ ኮሌጁ መምህርነት ሲያገለግሉ
ከቆዩ በኋላ ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው በመልቀቅ ሁሉ ነገር ይቅርብኝ ብለው ወደ ገዳም አመሩ። ነሐሴ 5 ቀን 1954 ዓ/ም በግብጽ
ከሚገኘው የሶሪያ ገዳም ከገቡ በኋላ ዓለማዊ ስማቸው ተቀይሮ «አንቶንዮስ ኤል ሲሪያኒ» ተብለው ተጠሩ። ትርጉሙም «ሶሪያዊው እንጦንስ»
ማለት ነው።
በገዳሙ ውስጥ ለሁለት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ገዳሙ ራሳቸውን ለክርስቶስ ሙሽራ አድርገው ያጩትን እኚህን አባት ምንኩስናና
ማእረገ ቅስና እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። ከማኅበር ኑሮ ይልቅ ለብቻቸው በመለየት ስለነገረ መስቀሉ ማሰላሰል እንደሚሻል በማሰብ ለሰባት ዓመታት በጾምና በጸሎት ተወስነው በበዓት
ውስጥ ቆይተዋል። በ1959 ዓ/ም የፓትርያርክ ምርጫ ሲደረግ የአሁኑ አባ ሺኖዳ የቀድሞው እንጦንዮስ ኤልሲሪያ ከዘጉበት ዋሻ በገዳሙ
ማኅበረ መነኰሳት ተጠርተው እንዲመጡ ከተደረገ በኋላ የግብጽ ገዳማት ሁሉ የየራሳቸውን እጩ ለፓትርያርክነት ከሚያቀርቧቸው መካከል እሳቸው ደግሞ ገዳማቸውን ወክለው እንዲወዳደሩ ተደርጎ በውድድሩ እሳቸው ሳያልፉ ቀሩ። አብረዋቸው ከተወዳደሩት መካከል «ቄርሎስ 6ኛ» ፓትርያርክ ሆነው ተመረጡ።
አባ እንጦንስ(ሺኖዳ) ወደገዳማቸው ተመልሰው ወደቀድሞ በዓታቸውና የብቸኝነት ጸሎታቸው ገቡ። ቀድሞውኑ አባ እንጦንስን ገዳሙ
ወክሏቸው እንጂ ሥራቸውንና የከተማ ደመወዛቸውን እርግፍ አድርገው የተዉት ፓትርያርክ ለመሆን በመመኘት አልነበረምና ወደበዓታቸው በመመለስ የክርስቶስን ፍቅር፣ ሞትና
ትንሳዔ እንዲሁም የቅዱሳት መጻሕፍትን ምስጢር በመመርመር ተጠመዱ። የሚገርመው ደግሞ አባ እንጦንስ ለውድድር ተልከው ከ5 ተወዳዳሪዎች
መካከል በውድድሩ እጣ አሸንፈው ፓትርያርክ የሆኑት ቄርሎስ 6ኛ በተሾሙ በ3ኛው ዓመት አባ እንጦንስ(ሺኖዳን) በአስቸኳይ እንዲመጡ
ለገዳማቸው ትእዛዝ አስተላለፉ። አባ እንጦንስም የፓትርያርኩን ትእዛዝ አክብረው በ1962 ዓ/ም ወደ ካይሮ አመሩ። ከዚያም በፓትርያርኩ
እጅ የጵጵስና ማእረግን አባ ሺኖዳ ተብለው ተቀበሉ።
ምንም ሳይታሰብ ጳጳስ ተብለው ከተሾሙ በኋላ በጵጵስና ማእረግ የኮፕት አብያተክርስቲያናት መንፈሳዊ ኮሌጆች የበላይ ኃላፊና
ዲን ሆነው ተመደቡ። አዲሱ ጳጳስ ሺኖዳም መንፈሳዊ ኰሌጆችን የሚመሩና የሚያስተምሩ መምህራንን በብቃትና በጥራት አደራጅተው በዓመት
ውስጥ ቀድሞ ከነበረው ሦስት እጥፍ ተማሪዎችንና ምሩቃንን ማፍራት ቻሉ። የተንዛዛውን የቢሮክራሲ አሰራር በማሻሻልና አስተምህሮው
ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን መሠረት ብቻ የተከተለ እንዲሆንና ታሪክ፣ባህልና ትውፊት ጠቃሚ ቢሆንም የወንጌል አገልግሎትን ስለማይወክል
ወጣቱ እንዲነቃቃ፣ ትውፊቱን እንደያዘ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነብ፣ እንዲመረምር፣ እንዲማር በማድረግ የኮፕት ቤተክርስቲያንን የአዲስ ኪዳንን ትምህርታዊ አብርሆት አሳይተዋል። በዚህም
የተነሳ ከቤተክርስቲያን እየራቀና በዓለማዊው ትምህርት እየተጠመደ የነበረውን ወጣት ስለቤተክርስቲያን እንዲመለከት፣ የነፍሱን ቤዛ
ክርስቶስን ችላ እንዳይል በማድረጋቸው የሚመጣ የወጣቱ ቁጥር በመጨመሩ መንፈሳዊ ኰሌጆች እንዲከፈቱ፣ በተጓዳኝም ዘመናዊ ት/ቤቶች
እንዲስፋፉ አድርገዋል።
በጳጳስ ሺኖዳ በኩል በግብጽ ቤተክርስቲያን ውስጥ መነቃቃትን
የፈጠረው አዲስ ትንሳዔ ብዙ ሺህ ወጣቶችን ለመሳብ፣ገዳማትና አድባራት በወንጌል መምህራንና ተማሪዎች እንዲስፋፋ አስችሏል። በዚህ
የተነሳ አባ ሺኖዳ ተከታዮቻቸው በመብዛታቸውና የወንጌል መምህራችን የሚለው ሰው ቁጥር በማየሉ የተነሳ ፖፕ ቄርሎስ 6ኛን ደስ አላሰኛቸውም።
እንዲያውም ይባስ ብለው ከነበሩበት የሥራ ኃላፊነት በማባረር አባ ሺኖዳ እጃቸውን አጣጥፈው እንዲቀመጡ አደረጓቸው።
የወጣቱን ልብ በወንጌል አገልግሎት መሳብ የቻሉት አባ ሺኖዳ ምንም ቅር ሳይሰኙ በፓትርያርኩ ትእዛዝ አርፈው ተቀምጠው
ሳሉ ወጣቱ ግን አድራጎቱን በመቃወም የቤተክርስቲያን አስተዳደር ተሐድሶ
ሊደረግበት ይገባል ሲል ተቃውሞውን አሰማ። ተቃውሞው ሰፊና ሁሉን ያዳረሰ በመሆኑ በ1967 ዓ/ም መጀመሪያ አካባቢ ውዝግቡ በስምምነት
ተፈጽሞ ፓትርያርኩ እግዳቸውን አንስተው አባ ሺኖዳ ወደቀደመ ሥራቸው እንዲመለሱ ተደረገ።
ከ4 ዓመታት በኋላ በ1971 ዓ/ ም ፓትርያርክ ቄርሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። የፓትርያርክ ቄርሎስን ሞት
ተከትሎ በ9ኛው ወር የሚተካቸው ፓትርያርክ ምርጫ ተደረገ። ለፓትርያርክ እጩነት ከቀረቡት መካከል አባ ሺኖዳ ቀድሞ የገዳም መነኩሴ
እንደነበሩ በተወዳደሩበት ሁኔታ እንደገና ጳጳስ ከሆኑ በኋላም ለሁለተኛ ጊዜ ለፓትርያርክነት ውድድር ቀረቡ። ለእጩነት ከቀረቡት
5 ተወዳዳሪዎች መካከል ስማቸው ተጽፎ ከተቀመጠበት ሳጥን ውስጥ ዓይኑን በጨርቅ የተሸፈነ ልጅ አንዱን እንዲያነሳ ተደርጎ ሲገለጥ
«አባ ሺኖዳ» የሚል ሆኖ ተገኘ። በዚህም ባሳደዷቸው በፓትርያርኩ ቦታ 117ኛው የኮፕት ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ሺኖዳ ሳልሳዊ
ተብለው ተሾሙ። እዚህ ላይ ሳንገልጽ የማናልፈው ድንቅ ነገር በኮፕት ቤተክርስቲያን የመጨረሻ አምስት እጩ ፓትርያርኮች ላይ የድምጽ ካርድ መስጠትና የድምጽ ቆጠራ ቆጠራ ብሎ ነገር የለም። በምእመናን፣ በመነኮሳት፣ በገዳማት፣ አድባራትና የሲኖዶስ አባላት 1000 ያህል ተወካዮች ከሚያቀርቧቸው ተጠቋሚዎች ውስጥ በድምጽ ብልጫ ያገኙ አምስት ጳጳሳት መካከል ስማቸው በወረቀት ላይ ተጽፎ በሳጥን ውስጥ ከገባ በኋላ እድሜው ከ7 ዓመት ያልበለጠ ልጅ ዓይኑን በጨርቅ ታስሮ ሲያበቃ ሳጥኑ ውስጥ ካለው እጣ አንዱን እንዲያወጣ ይደረጋል። የወጣለት እጩ ፓትርያርክ ይሆናል። ከዚያ ውጪ የምርጫ ካርድ ይዞ፤ ቡድንና ደጋፊ አስርጎ በማስገባት በሚደረግለት ፖለቲካዊ ድጋፍ እየታገዘ ፓትርያርክ ሆነ እንደሚባለው እንደሌሎቹ አብያተክርስቲያናት የማጭበርበሪያ ስልት ኮፕቶች የላቸውም።
ፖፕ ሺኖዳ ሳልሳዊ በሥራቸው ላይ ሳሉ ከፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት አስተዳደር ጋር ባለመስማማታቸው ሳዳት እሳቸውንና 8 ሌሎች ጳጳሳትን ከስልጣን አባሮ ጭው
ካለው በረሃ በሚገኘው አባ ብሶይ ገዳም ተዘግተው እንዲቀመጡ አደረገ። በምትካቸው 5 ጳጳሳት ያለው የፓትርያርክ ወኪል የጳጳሳትን
ቡድን እራሱ ሳዳት ለቤተክርስቲያኒቱ ሾመ። ቅዱስ ሲኖዶስ ድርጊቱን ተቃወመ፤ ጳጳሳቱም ሹመቱን አንቀበልም አሉ። ሲኖዶሱ የቤተክርስቲያኒቱን
ሥራ ተረክቦ እስከ1984 ዓ/ም ድረስ ቆየ። አንዋር ሳዳትም በነፍሰ ገዳዮች ጥይት ተገደለ። በምትኩም ሆስኒ ሙባረክ ፕሬዚዳንት
ሆኖ ሲሾም የአባ ሺኖዳም ስደት አከተመና ወደመንበራቸው በ1985 ዓ/ም ተመለሱ።
አባ ሺኖዳ ወደመንበራቸው ከተመለሱ በኋላ የወንጌል አባትነታቸውን ቀጥለዋል። በዚህም ከ100 መጻሕፍትን በላይ በአረቢኛና
በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽፈዋል። በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በመጽሔቶችና በጋዜጦች ሁሉ ወንጌልን ሰብከዋል። ነገረ ወንጌሉን አዳርሰዋል።
መዳን በማንም እንደሌለ አጥብቀው በአዳባባይ መስክረዋል። ባህሉንና ትውፊቱን እንዲጠብቅ ግን በዚያው ላይ ሙጭጭ ብሎ ወንጌልን ወደዳር የመግፋቱን ተግባር በጹኑ ተከላክለዋል። የዘመኑን ወጣት ልብ ለክርስቶስ እንዲገዛ በማድረግ ጥበብ የተሞላበትን
አስተምህሮ አስፋፍተዋል። ይህንን ሁሉ ተጋድሎ ፈጽመው በተወለዱ በ88 ዓመታቸው፣ በተሾሙ 41 ዓመታቸው ከዚህ ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም በመጋቢት 17/2012 ዓ/ም ሄደዋል። እኒህን የወንጌል መምህር፣ ዘመኑን የዋጁ፤ ራሳቸውን
በንጽህና የክርስቶስ ሙሽራ አድርገው ያቀረቡ አባት ነፍስ ከቅዱሳኖቹ እንዲደምርልን ለወንጌሉ አገልግሎት ዘመናቸውን ሁሉ በመስጠት የተጋደሉለት ክርስቶስን እንለምነዋለን። አሜን።
(ተጨማሪ፤ በአጽዋማት ጊዜ በበዓላት ቀን ሥርዓተ ቅዳሴ ጥዋት እንዲሆን ያደረጉት ፖፕ ሺኖዳ ናቸው። ለምሳሌ የእመቤታችን ወርሃዊው በዓል 21ኛው ቀን ከሰኞ እስከ ዓርብ ቢውል በጾመ አርብዓ ይሁን በጾመ ፍልሰታ ቅዳሴ የሚቀደሰው ጥዋት እንጂ እንደኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ውሎ ከሰዓት በኋላ አይደለም። ይህን ያደረጉት ይህ ቀኖና እንጂ ዶግማ ባለመሆኑ ሕዝቡ ከማስቀደስ እንዳይርቅ፣ ለኑሮው ደፋ ቀና የሚለው ምእመን በድካም የተነሳ በመሰላቸት ወጥቶ እንዳይቀር፤ ሙሉ ቀን ጾሙን፣ ሥራውንና ቅዳሴውን ለመተግበር ስለሚቸገር ያሻሻሉበት ዋና ምክንያት ነው። ሥርዓቱን ያሻሻሉ አባት ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ተሀድሶ ተብለው ይደበደቡ ነበር። ደግነቱ እሳቸው የኮፕት ፓትርያርክ ናቸው።)
(ተጨማሪ፤ በአጽዋማት ጊዜ በበዓላት ቀን ሥርዓተ ቅዳሴ ጥዋት እንዲሆን ያደረጉት ፖፕ ሺኖዳ ናቸው። ለምሳሌ የእመቤታችን ወርሃዊው በዓል 21ኛው ቀን ከሰኞ እስከ ዓርብ ቢውል በጾመ አርብዓ ይሁን በጾመ ፍልሰታ ቅዳሴ የሚቀደሰው ጥዋት እንጂ እንደኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ውሎ ከሰዓት በኋላ አይደለም። ይህን ያደረጉት ይህ ቀኖና እንጂ ዶግማ ባለመሆኑ ሕዝቡ ከማስቀደስ እንዳይርቅ፣ ለኑሮው ደፋ ቀና የሚለው ምእመን በድካም የተነሳ በመሰላቸት ወጥቶ እንዳይቀር፤ ሙሉ ቀን ጾሙን፣ ሥራውንና ቅዳሴውን ለመተግበር ስለሚቸገር ያሻሻሉበት ዋና ምክንያት ነው። ሥርዓቱን ያሻሻሉ አባት ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ተሀድሶ ተብለው ይደበደቡ ነበር። ደግነቱ እሳቸው የኮፕት ፓትርያርክ ናቸው።)
(በጽሁፋችን ውስጥ የተጠቀሱት ዓ/ምህረቶች ሁሉ እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር ነው)