ለአዳም ካሣ በመክፈልና የእግዚአብሔርን ትክክለኛ ፍትሕ በመጠበቅ ሞትን ለመሻር የተደረገ መገለጥ
* * *
የተወለደ ከአዳም፣
መሬት ያልገዛ የለም፡፡
ግብሩን መገበር አቅቷቸው፣
ገና ብዙ ዕዳ አለባቸው፡፡[1]
* * *
ለክርስቶስ በስብዕና መገለፅ ዋና ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው በአዳም መሳሳት የተነሳ በሰው ልጆች ላይ ያረፈውን የሞት ፍርድ በመሻር ለማስቀረት ሲኾን በሞት መሻርም የእግዚአበውሔር ትክክልኛ ፍርድ ሳይዛባ እንዲፈፀም ለማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም አዳምና ሔዋን በገነት በነበሩ ጊዜ እግዚአብሔር እንዳይበሉ ያስጠነቀቃቸውን ዕፀ በለስ በመብላት ትዕዛዙን በመሻራቸው ሞት የሚባል ዕዳ በሰው ልጆች ኹሉ እንደመጣባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ የኦሪት ዘፍጥረት ታሪክ ተገልፆ ይገኛል፡፡ ምናልባት እዚህ ላይ ‹የተሳሳቱት አዳምና ሔዋን ለምን ልጆቻቸው የሞት ቅጣት ተቋዳሽ ይሆናሉ?› የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ገለፃ ከኾነ ግን አዳምና ሔዋን የተሳሳቱ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ናቸው፤ኹሉም በዓለም ላይ በመዋለድ የተራባው የሰው ዘር ደግሞ ከእነሱ የመጣ ነው፡፡ ይህም የኾነው ስህተት ፈፅመው የሞት ፍርድ ከተላለፈባቸው በኋላ ስለኾነ ማንም ከእነሱ የተወለደ ዘር ኹሉ የእነሱን ሀብትና ማንነት ይወርሳል፡፡ ከእነሱ የተገኘው ሀብትም በስህተት ላይ የተመሠረተ የስብዕና ማንነት ሲኾን የእሱም መቋጫም ሞት ነው፡፡ ስለዚህ ልጆቻቸው ወይም ዘሮቻቸው በሙሉ በስህተት የመጣ የሞት ፍርድ ተካፋይ ናቸው፡፡ ያለበለዚያ በእነሱ ላይ የተፈረደውን የሞት ፍርድ ልጆቻቸው መውረስ የለባቸውም ከተባለ የእነሱን የስብዕና ማንነትም ልጆቻቸው መውረስ የለባቸውም፡፡ እንዲሁም በአዳምና ሔዋን የተወከለው የሰው ዘር በሙሉ ነው እንጂ የሁለት ሰዎች የመሳሳት ጉዳይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አዳምና ሔዋን ልጆቻቸውን በአብራካቸው ውስጥ በመያዝ ወክለው ትዕዛዙንና ፍረዱን ተቀብለዋል፤ ፍርዱም የተላለፈው ለሰው ልጅ ኹሉ ነው፡፡ ልጆቻቸው የእነሱ ዝርዝር ማንነቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ የሞት ፍርድ የተላለፈው በአዳምና በሔዋን ከእነ ልጅ ልጆቻቸው ነው፡፡
የሞት ፍርድ የተላለፈው ደግሞ አዳምና ሔዋን ክፉና ደጉን ከምታሳወቀው ዕፀ በለስ በመብላታቸው በመኾኑ ሞት የመጣባቸው በማወቃቸው ነው ማለት ነው፡፡ ‹ምን በማወቃቸው?› ‹ክፉና ደጉን ነዋ!› መልሱ ነው፡፡ ይህን በቀጥታ ሲወስዱት አደናጋሪ ይመስላል፤ አዳምና ሔዋን ከመሣሣታቸው በፊት ዕውቀት አልነበራቸውም፣ ስለዚህ የበሉትም ባለማወቃቸው ነው በማለት፤ ዕወቀት ስላልነበራቸው ተጠያቂ መኾን የለባቸውም የሚል አንድምታን ያሰማል፡፡ በዚህ አተያይ ላለመኾኑ ግን ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው እናገኛለን፡፡ ትዕዛዝ የተሰጣቸው በማወቃቸውና የሚያገናዝቡ በመሆናቸው ነው እንጂ ለማያውቅ አካል ጠብቅ ተብሎ ትዕዛዝ አይሰጠውም፡፡ ስለዚህ አዳምና ሔዋን ምንም ሳያውቁ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው ካጠፉ በኋላ ማወቅ ቻሉ ማለት ስህተት ነው፡፡
እና መጽሐፍ ቅዱስ ‹አዳም ክፉና ደጉን በማወቅ ከእኛ እንዳንዱ ኾነ› በማለት ዕፀ በለሰን ከበሉ በኋላ አዳምና ሔዋን ክፉና ደጉን ለይቶ የማወቅ ሀብትን ገንዘብ ማድረጋቸውን ይናገር የለም ውይ? ተብሎ ይጠየቅም ይሆናል፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ ለማያውቅ አካል ጠብቅ ተብሎ ትዕዛዝ አይሰጥም ብለናል፡፡ ሁለቱ እንዴት ይስማማሉ? የሚል ጥያቄንም ያስነሳል፡፡
ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፡፡ ትክክለኛው መልስም አዳምና ሔዋን ዕፀ በለስን ከመብላታቸው በፊት የነበራቸው ዕወቀት ክፉና ደጉን አመዛዝኖ በማወቅ ላይ የተመሠረተ ሳይኾን ትክክለኛውንና መልካሙን ነገር በማወቅ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነበር፡- የማገናዘብና የማመዛዘን ዕውቀታቸውም በክፉና በደግ፣ በመጥፎና በጥሩ፣… መካከል ሳይኾን በአንድ በኩል ብቻ ደግ ደጉን፣ ጥሩ ጥሩውን፣ ፍቅር ፍቅሩን፣… ማወቅ ነበር፡፡ ዕፀ በለሰን ከበሉ በኋላ ግን የክፉን፣ የመጥፎንና መሰል እኩይ ተግባራትንና የእነሱ ውጤት የኾነውን ህልውናን ማጣት (ሞትን) ጭምር ማወቅ ቻሉ፡፡ ምክንያቱም የክፉ ነገር መጨረሻ የኾነውን ህልውና ማጣትን ማለፍ የሚችል የደግነት ማንነትና ዕወቀት ስለሌላቸው ይህንን የክፋትና የመጥፎ ነገሮች ኹሉ ጉልላት የኾነውን ሞትን በዕውቀትም በግብርም ሲያውቁ በዚያው ካምላካቸው እየተለዩ ለመቅረት ተገደዱ፡፡ ስለኾነም አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔር ትዕዛዝን በመተላለፍ ዕፀ በለስን ሲበሉ ገንዘብ ያደረጉት ዕውቀት ክፉውንና መጥፎውን የዕውቀት በኩል ነው እንጂ በትክክልና በጥሩ በኩል ያለውን ጭምር አይደለም፡፡ የትዕዛዙም አንድምታ ‹በክፉነትና በመጥፎነት የሚታወቅ ዕውቀት አለ፤ የእሱም ውጤቱና መቋጫው ሞት ነው፤ ይህ ዕውቀትም በዚህች ዕፅ ላይ ይገኛል፤ ስለዚህ ኹሉንም ስትበሉ ይች ዕፅ ግን ትቅርባችሁ፤ ለእናንተም አይጠቅማችሁም፤ ሞትን ታሳውቃችኋለችና፡፡› የሚል ነው፡፡ ይህ የክፉው ክፍል ዕውቀት ደግሞ አዲስ የተጨመረ በመኾኑ ከደጉና ከትክክለኛው ዕውቀት ጋር ማነጻጸሪያ ሊኾናቸው ችሏል፤ ከስህተት በኋላ ያለቸው ዕውቀት በዚህ መልክ የተቃኘ ስለኾነም ‹ክፉና ደጉን የሚያሳውቅ› ዕውቀት መኾኑ ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ክርክሩ የሚኾነው ክፉን ማወቃቸው አስፈላጊና ጣቃሚ ነው ወይስ አይደለም? የሚል ነው፡፡
ልብ ብለን ካስተዋልነው የተለያየ ልምድና ባህልና ተፅእኖ ስላበት እንጂ የሰው ልጆች ተፈጥሯቸው ክፉ ነገርን አይመርጥም፤ የትኛውም ሰው ልጅ ሲወለድለት ደስ ይለዋል፤ ሲሞትበት ግን ያዝናል፡፡ ሞት የክፋት ኹሉ መጨረሻ (ህልውናን ማጣት) ሲኾን መወለድ ደግሞ ህልውናን ማግኘት መኾኑ ግልፅ ነው፡፡ ከሞት ያነሱትን ስቃዮችና መከራዎችም ቢኾን የሰው ልጅ ይቃወማቸዋል እንጂ ፈልጎ በመምረጥ አይጠቀምባቸውም፡፡ ፈልጎና መርጦ ቢተገብራቸው እንኳን በጫናዎች የተነሣ ነው የሚኾነው፡፡ ይህም የሰው ልጅ ከክፋት ተፈጥሮ ጋር ተፈጥሮው አብሮ የማይሔድለት ፍጡር መኾኑን ይመሰክራል፡፡ ይህ የማይፈለግና ከተፈጥሯችን ጋር አብሮ የማይሔድ ዕውቀት ክፍል ነው በአዳምና በሔዋን ታውቆ የሰው ልጆችን ሊስማማን ያልቻለው፡፡
[1] ኅሩይ ወ/ሥላሴ፤ ወዳጀ ልቤና ሌሎችም፣ ገጽ 36
ምንጭ፦kassahunalemu.wordpress.com