ራሳቸውን ከአቡነ ገብርኤል አስተዳደር የለዩት ምዕመናን አሁንም ከአሳዳጆቻቸው ጋር ተፋጠዋል
በአቡነ
ገብርኤል የመልካም አስተዳደር ብልሹነት ተማረውና ተቀጥቅጠው በዱላ ኃይል ከሀዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል
ገዳም፣ ከደብረ ሠላም ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን እና ከደብረ ታቦር ቅዱስ ሩፋኤል ቅጥር ግቢ የተባረሩት
ምዕመናን የራሳቸውን ታላቅ መንፈሳዊ ጉባዔ ማካሄዳቸው ዘጋቢዎቻችን አስታወቁ፡፡
ዘጋቢዎቻችን በሥፍራው ተገኝተው እንዳረጋገጡት እነዚህ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናንና ምዕመናት፣ ልዩ ልዩ ሥልጣነ ክህነት ያላቸው አገልጋዮችና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች አቡነ ገብርኤል ከ"ማኅበረ ቅዱሳን"ና አሥር ከማይሞሉ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎች እና ኃላፊነታቸውን ከዘነጉ ፖሊሶች ጋር በመተባበር ተከታታይና ኢሰብዓዊ ድብደባ፣ እሥራትና እንግልት ስላበዙባቸው ተማረው መውጣታቸው ታውቋል፡፡
ይሁን
እንጂ ይህ የተሰደደው ሕዝብ ተበታትኖ ወደየቤቱ ከመግባት ይልቅ እየተሰባሰበ በግለሰቦች መኖሪያ ቅጥር ግቢ ውስጥ
ወንጌል በመከታተል ላይ ሲሆን በአደረጃጀት እየጠነከረ በመምጣቱ እነ አቡነ ገብርኤል እንደስጋት እንደሚያዩት
ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከዚህም የተነሳ በእነ አቡነ ገብርኤል ወገን ያለው አሳዳጅ ኃይል ግፉአኑን "ተሀድሶዎች" ናቸው፣ "መናፍቃን"
ናቸው በማለት፣ ዐውደ ምሕረት ላይ የሐሰት ወሬ በማስተላለፍ ላይ ሲሆን፣ ከዚሁ ጎን ለጎን አሳዳጆቹ ወደ ፍትሕና
ፀጥታ አካላት እንዲሁም ወደ ክልል መስተዳድር እና ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ዘወትር እግራቸው እስኪቀጥን ድረስ
በመመላለስ እንዲያዙላቸው፣ እንዲታገዱላቸውና እንዲታሠሩላቸው በመወተወት ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላ
በኩል ምዕመናኑ ከአሥራ ሦስት ጊዜያት በላይ ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት ተመላልሰው ያቀረቡት አቤቱታ እጅግ የተጓተተ
ምላሽና ሥር ነቀል መፍትሔ ያልተሰጠው በመሆኑ ራሳቸውን ከአቡነ ገብርኤል አስተዳደር ለይተው የሚንቀሳቀሱ ሲሆን
ዜጎች ካላቸው በነፃ እምነትን ከማራመድና ከመደራጀት አንፃር ጠንክረው በመጓዝ ላይ መሆናቸውን ተረድተናል፡፡ ግፉአኑ
ከእነአቡነ ገብርኤል ለሚሰነዘርባቸው የተሀድሶና መናፍቅነት የፕሮፖጋንዳ ጦርነት ምላሽ ሲሰጡም በአቡነ ገብርኤል
ዕዝ ሥር አለመተዳደር ቤተክርስቲያንን መካድ ማለት አይደለም፡፡ ትላንት፣ ዛሬ፣ ነገም ከእናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ
ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሃይማኖት የሚለየን የለም፡፡ መከራ፣ ችግር፣ ስቃይ ቢበዛብንም በሃይማኖታችን ጽኑ ነን
ብለዋል፡፡
የምዕመናን ተወካዮች በጉባዔው ማጠናቀቂያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ "ስለወንጌል ተሰድበናል፣ ተደብድበናል፣ ታሥረናል፣ ተሰደናል፡፡ 'እነርሱን ብናሥር ሌላው ተሸማቆ ይቀራል' በሚል የተሳሳተ ቀመር፣ በሦስት የተለያዩ የሕክምና ማስረጃዎች (የመንግሥት
ሆስፒታሎች የሆኑት የሀዋሳ አዳሬ ሆስፒታል እና ሪፈራል ሆስፒታሎች ትክክለኛ ማስረጃ ሰጥተው እያለ፣ ዶን ዴንታል
ክሊኒክ የተባለው የግል የሕክምና ተቋም በሰጠው የተሳሳተ ማስረጃ ላይ በተመሰረተ ክስ)፣
በተጭበረበረ መንገድ አራት ወንድሞቻችን ወደ ወህኒ ገብተውብናል፡፡ በተቃራኒው እግዚአብሔር ሕዝቡን በይበልጥ አበዛ
እንጂ ተሸማቆ አልቀረም፡፡ ይህን ታላቅ መንፈሳዊ ጉባዔም እነዚህን አራት ወንድሞቻችንና ቤተሰቦቻቸውን በማሰብ
እግዚአብሔርን ያመሰገንበትና ያከበርንበት በመሆኑ እንጽናናለን"ብለዋል፡፡
ስለ ወንጌል አገልግሎትና እምነታቸው ሲያብራሩም "ይህ
የተሰደደው የእግዚአብሔር መንጋ መላውን የሀዋሳ አጥቢያዎች ያካለለ ነው፡፡ ጠላት ዲያብሎስ እንደሚያስወራው እኛ
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት የወጣ እምነትም፣ ሥርዓትም የለንም፣ ለወደፊትም አይኖረንም፡፡ ወንጌል
በየዐውደ ምሕረቱ፣ በየእሥር ቤቱ፣ በየሠርግ ቤቱ፣ በየለቅሶ ቤቱ፣ በየአደባባዩ በዓለም በሁሉም ሥፍራ መሰበክ
እንዳለበት ሥርዓት የደነገጉልን የቀድሞ አባቶች ናቸው፡፡ ሥርዓተ ቤተክርስቲያናችንም ይህንኑ ትከተላለች፡፡ ነገር
ግን አንዳንዶች ይህንን አጣመው ወንጌል ከቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውጪ መሰበክ የለበትም በማለት ያሳስታሉ፡፡
ይህንንም ሥርዓት ከሌሎች ቤተእምነቶች ልምድ ጋር በማያያዝ ሲነቅፉ ይታያሉ፡፡ ይህንን የተዛባ አስተሳሰባቸውን
አባታችን ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ-ዳግማዊ በአካላዊ ሕይወት ሳሉ ስለስብከት ሥርዓት የጻፉትን መጽሐፍ አንብበው እንዲያስተካክሉ እንመክራቸዋለን" በማለት፣ አስገንዝበዋል፡
ስለ አቋማቸው እንዲታወቅላቸው የሚፈልጉትን ነጥብ ሲያስረዱም፣ "
ከእነ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ያለን ልዩነት የወንጌልና የመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑን ሁሉም ወገን ሊያውቀው
ይገባል፡፡ ቤተክርስቲያናችን የምትሰብከው ወንጌል ያለገደብና ያለልዩነት በሁሉም አገልጋዮቿ ከተሰበከ የማንስማማበት
ምክንያት የለም፡፡ የቤተክርስቲያኗ ሀብት በግልጸኝነት፣ በተጠያቂነት እና በኃላፊነት መንገድ ከተመራ እኛ በሰዎች
ላይ የመንጠላጠል ፍላጎት የለንም፡፡ የምሽት ዳንስ ቤቱን ማስተዳደር ትቶ ማንም እየተነሳ ሕገ ቤተክርስቲያንን ጥሶ
የሊቃውንት ጉባዔና የቅዱስ ሲኖዶስን ሥልጣን ወስዶ የቤተክርስቲያንን ካህናት እየተሳደበ፣ እከሌ 'ተሃድሶ' ነው፤ እከሌ 'መናፍቅ'
ነው እያለ የሚያውክ እስከሆነ ድረስ ልዩነት አለን፤ አንተባበርም፡፡ የተቀጠቀጥነው፣ የታሠርነው፣ የተሰደድነው
በዚህ ምክንያት እንጂ የሃይማኖት ልዩነት ኖሮን አይደለም፡፡ ይህንን የማያውቁ ቢኖሩ እንዳላወቁ ሊቀመጡ መብታቸው
ነው፡፡ እግዚአብሔር ካወቀልን በቂያችን ነው" በማለት አስገንዝበዋል፡፡
ስለሚኖራቸው ራዕይ ሲገልጹም፣ "እኛ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች የሆንንና በእግዚአብሔር የታመንን ወላጆች፣ የወንጌልን አገልግሎት
ከማስፋፋት ጎን ለጎን፣ ልጆቻችን በሥነምግባር የታነፁ እንዲሆኑ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተሰጠን መመሪያም
ለመንግሥትና ለባለሥልጣናት ሥርዓት ባለው መንገድ እየታዘዝን፣ በሚነደፉ የልማት ዕቅዶች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ
በማድረግ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ያላት ሥፍራ ከፍ እንዲል፣ ዜጎቿ በድህነቷ የሚያፍሩባት ሳትሆን በብልፅግናዋና
በሠላማዊነቷ የሚኮሩባት እንድትሆን የበኩላችንን አስተዋፅዖ ለማድረግ እንሻለን፡፡ ስለዚህ ይህንን ራዕይ የሚጋሩ
መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ከጎናችን እንዲቆሙ በዚህ አጋጣሚ መንፈሳዊ ጥሪያችንን በእግዚአብሔር
ስም እናቀርባለን"ብለዋል፡፡
በመጨረሻም፣"የተሰደዱትን ምዕመናን ዕንባ በማበስ ላጽናኑትና ለጉባዔው መስፋት አስተዋፅዖ ላደረጉት፣በመኖሪያ ቤታቸው ቅጥር ግቢ ሲያስጠልሉን ለነበሩት ወገኖቻችንን፣ ይህንን ጉባዔ በጉልበታቸው፣ በገንዘባቸውና በቁሳቁስ በመተባበር በተጠያቂነትና በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ያዘጋጁትን ክፍሎች፣ የጠላት ዲያብሎስ ወሬ ሳይበግራቸው፣ ስለአቋማችንና ስለዓላማችን እውነቱን በመረዳት፣ ዜጎች እምነታቸውን በነፃ የማራመድ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን በማስከበር መንግሥታዊና ሕዝባዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለተወጡት የመንግሥት አካላት ከልብ እናመሰግናለን"በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ይህ
በእንዲህ እንዳለ፣ ራሳቸውን ከአቡነ ገብርኤል አስተዳደር የለዩት እነዚህ ምዕመናን አሁንም ከአሳዳጆቻቸው ጋር
ተፋጠው ሕልውናቸውን በማስከበር የትግል ሂደት ላይ መሆናቸውን ውስጥ ዐዋቂ ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡ አቡነ ገብርኤል
ያባረሩትን ሕዝብ በክህደት ስም ከመሳደባቸውም በላይ ባገኙት አጋጣሚ ለቅዳሴና ለቀብር ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ
ለሚገኘው ሕዝብ "ወደእነርሱ ጉባዔ አትሂዱ፣ ተሀድሶ፣ መናፍቅ ናቸው"
በማለት ቢገዝቱም፣ ሕዝቡ እውነታውን በግልጽ ስለሚያውቅ፣ ግዝታቸውን ከመጤፍ ባለመቁጠር ራሳቸው በሠሩት ማስታወቂያ
ተቀስቅሶ የስደተኞችን ጉባዔ የተቀላቀለው ምዕመናንና ምዕመናት ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡
እግዚአብሔር ቸር ወሬ ያሰማን!!!
በምሕረቱና በቸርነቱ ይጠብቀን!!!
አሜን!!!http://dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com/2012/03/blog-post_11.html