እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? (ክፍል ፩)
የያዝነው
አርባ ጾም ዐቢይ (ታላቅ) ጾም እንደመሆኑ መጠን በመጽሐፍ ቅዱሳችን በምዕራፉ ሙሉ ስለጾም የሚናገረውን ትንቢተ
ኢሳይያስ ም. ፶፰ ከሕይወታችን ጋር በማያያዝ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረንን እናያለን።
ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ ፶፰፡-
ቁ .፩ በኃይልህ ጩኽ፥ አትቈጥብ፥ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፥ ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን ንገር።
ኃጢአት
ሰዎችን ከእግዚአብሔርን የሚለይ ሲሆን ንስሐ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ የሚያደርግ ተግባር ነው። ሰዎች ወደ
እግዚአብሔር እንዲመለሱ ኃጢአታቸው ሊነገራቸው፡ እነርሱም ኃጢአታቸውን በመናገር ንስሐ ሊገቡ ይገባል። በዚህ ክፍል
እግዚአብሔር ነቢዩ ኢሳይያስን ለአይሁድ ኃጢአታቸውን እንዲነግራቸው ያዘዋል። አይሁድ እግዚአብሔርን የሚያውቁና
የሚያምኑ ሕዝቦች ቢሆኑም ጥፋታቸው ሊነገራቸው ይገባ ነበርና ነቢዩን ላከላቸው።
ዛሬ እግዚአብሔርን የሚያውቁና፡ በቤቱ ስለሚኖሩ ክርስቲያኖች ጥፋት ምን እያደረግን ነው? ጥፋታቸው ለራሳቸው ተነግሮአቸው ንስሐ እንዲገቡ ወይስ ለሌላው ተነግሮባቸው እንዲበረግጉ? ወንድሞቻችን ምንም ዓይነት ጥፋት ያጥፉ ቁም ነገሩ ለምን አጠፉ? ሳይሆን እንዴት ይመለሱ? መሆን አለበት። አንድ ወንድም «ከጥፋቴ በፊት መጥፋቴ ያሳስባችሁ» ብሎአል። ብዙ ጊዜ ስለ ጥፋታቸው እንጂ ስለመጥፋታቸው አናስብም። እግዚአብሔር ግን ሁሉም በጥፋታቸው ተጸጽተው በንስሐ ይመለሱ ዘንድ ጥሪ እንድናደርግ በኃይልህ ጩኽ፥ ዝም እንዳንልም አትቈጥብ ይለናል። በአንድምታውም ጩኽህ አስተምር፡ ማስተማሩን ቸል አትበል ይላል።
ከዚህ
ሌላ ብዙዎቻችን በዓለም ያሉ ሰዎችን ኃጢአት በግልጽ መቃወም እንወዳለን። በቤቱ ላሉት ግን ጥፋታቸውን መናገር
እንፈራለን። ሰባኪም ይሁን ተማሪ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚታየው (ምናልባት ለራሳቸው የማይታያቸው) ጥፋታቸው
ሊነገራቸው ይገባል። ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ንገር ይላል። ለሌላው ተናገር ሳይሆን ለራሳቸው ንገር።
ቁ.፪ . ነገር ግን ዕለት ዕለት ይሹኛል መንገዴንም ያውቁ ዘንድ ይወድዳሉ ጽድቅን እንዳደረጉ የአምላካቸውንም ፍርድ እንዳልተዉ ሕዝብ እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወድዳሉ።
አይሁድ
የእግዚአብሔርን ሥርዓቱንና ሕጉን በመጠበቅ እግዚአብሔርን ማምለክ ይወዳሉ። እርሱን ለማስደሰት ሁሉንም ውጫዊ
ሥርዓት ለመፈጸም አጥብቀው ይጠነቀቃሉ፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ፍትህን እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ። በአንድምታው በጎ ሥራ እንደሚሠራ ሰው ሁሉ ሕጌን ልታውቁ ትወዳላችሁ፡ ይላል፤ በጎ ሥራ የላቸውም ማለት ነው።
ዛሬም
ብዙዎቻችን በምንፈጽማቸው ዕለታዊ የሃይማኖት ሥራዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን በመመላለስ፡ እንደ ጸሎት፡ ጾም፡
ስግደት…ያሉ የአምልኮ ሥርዓቶችን በመፈጸም እግዚአብሔርን ለመቅረብና ደስ ለማሰኘት እንጥራለን። ይህ ጥሩ መነሻ
ሊሆን ይችላል። ያለ በጎ ሥራ ይህ ትጋታችን ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ይህ ክፍል ያስተምረናል።
ቁ ፫. ስለ ምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም? ይላሉ። እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ
አይሁድ ስለፈጸሙት የአምልኮ ሥርዓት እግዚአብሔር መልስ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ። ሕዝቡም ካላየኸን ለምን ጾምን ይላሉ። ካላወቅኸነ ሰውነታችን በመከራ ለምን አሳዘነ። ይሄው ጾምን፡ ጸለይን አንተ ግን አልተመለከትክም ይሉታል። እግዚአብሔር ያልመለሰላቸው ለምንድን ነው? የሰጣቸው መልስ ግልጽ ነው። በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ። ይህም ማለት እንደፈለጋችሁ ትሆናላችሁ፣ትዝናናላችሁ፡ ትደሰታላችሁ። ሠራተኞቻችሁን ታስጨንቃለችሁ።
አይሁድ ስለፈጸሙት የአምልኮ ሥርዓት እግዚአብሔር መልስ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ። ሕዝቡም ካላየኸን ለምን ጾምን ይላሉ። ካላወቅኸነ ሰውነታችን በመከራ ለምን አሳዘነ። ይሄው ጾምን፡ ጸለይን አንተ ግን አልተመለከትክም ይሉታል። እግዚአብሔር ያልመለሰላቸው ለምንድን ነው? የሰጣቸው መልስ ግልጽ ነው። በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ። ይህም ማለት እንደፈለጋችሁ ትሆናላችሁ፣ትዝናናላችሁ፡ ትደሰታላችሁ። ሠራተኞቻችሁን ታስጨንቃለችሁ።
ዛሬስ
የእኛ ጾም ምን ዓይነት ነው? ፈቃዳችንን እያደረግን በመዝናናት ከሆነ፡ ሠራተኞቻችን፡ ባልደረቦቻችን አስጨንቀን፡
ወንድሞቻችን አስቀይመን ነገር ግን በጾማችን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት የምንሄድ ከሆነ ምንም ዋጋ አይኖረንም።
ጌታም በወንጌል፡-
እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፥ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፥ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፥ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ። ማቴ ፭፡፳፫-፳፬።
እንደ ጾም፡ ጸሎት፡ አምሀ… ያሉ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡ ነገሮችን ከመፈጸም በፊት ከወንድሜ ጋር እንዴት ነኝ? ብለን ራሳችን መጠየቅ አለብን። ይህንንም ሃሳብ የሚቀጥለው ክፍል ይበልጥ ያብራራልናል።
ቁ ፬፡ እነሆ፥ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም።
ይህ
ማለት ትካሰሳላችሁ፡ ትጣላላችሁ፡ ትከራከራላችሁ ነው። አይሁድ በጾማቸው ወቅት ጥልና ክርክር ያበዛሉ። ዛሬም ለኛ
ወደላይ ለሚሄደው አምልኮአችን (ጾምና ጸሎታችን) ማነቆ በመካከላችን ያለው ጥልና ክርክር የተባለው ፍቅር ማጣት፡
በሌሎች ላይ የምናደርሰው ግፍና በደል ነው። ጾም ለእግዚአብሔር ያለንን መገዛት የምንገልጽበት ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ጉዳይ ቢሆንም እርስ በርስ በሚኖረን ግንኙነት በፍቅር ካልሆነ ተቀባይነት እንደማይኖረው ያስጠነቅቀናል።
ቁ. ፭. እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነውን? ሰውስ
ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነውን? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ያደርግ ዘንድ ማቅንና አመድንም
በበታቹ ያነጥፍ ዘንድ ነውን? በውኑ ይህን ጾም፥ በእግዚአብሔርም ዘንድ የተወደደ ቀን ትለዋለህን?
እንግጫ፣-
ሸምበቆ ወይም ደንገል ነው። ትሕትናን ያመለክታል። አይሁድ ጾማቸው ከትሕትና ጋር እንዲያውም ማቅ ለብሰው፡ አመድ
ነስንሰው ራሳቸውን አዋርደው ይጾሙ ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ከፍተኛ የጾም ደረጃ ያስወቀሰው ፍቅር የለሽ ፣
በጥልና በክርክር የተሞላ መሆኑ ነው።
ጾማችን ተቀባይነት የሚያስገኘው ከሱባዔ ጋር ማቅ በመልበስ፡ አመድ በመነስነስ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጋር የሚኖረን ግንኙነት በፍቅር የመሆኑ ያለመሆኑ ጉዳይ ጭምር ነው። በአገራችንሞ ቂም ይዞ ጸሎት፡ ሳል ይዞ ስርቆት ይባላል። የማይሄድ ነገር ነው።
ጾማችን ምን መምሰል እንደሌለበት ከገለጸ በኋላ ምን መምሰል እንዳለበት ደግሞ ይናገራል።
ቁ ፮ና፯. እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን?
አይሁድ
ከእግዚአብሔር ጋር ጥሩ የሆነ የአምልኮ ግንኙነት ቢኖራቸውም ከሠራተኞቻቸው ጋር እና እርስ በርሳቸው ግን በሠላምና
በፍቅር አልነበሩም። ጭቆናና ብዝበዛ ያበዛሉ። በሙግትና በቃላት ጦርነት ብዙ ጊዜያቸውን ያጠፋሉ። ስለዚህ
እግዚአብሔር ይህንን የበደል እስራት (ቂም) እንዲተው፡ ግፍን እንዲያቆሙ ቀንበር ተብሎ የተገለጸውን ጭቆና
እንዲያነሱ ይገስጻቸዋል።
ከክፉ
ሥራቸው መከልከል ብቻ ሳይሆን በመልካም ሥራም መትጋት እንዳለባቸው ሲናገርም የተራበን እንዲያበሉ፡ እንግዳን
እንዲቀበሉ፡ የታረዘውን እንዲያለብሱ አብሮ ያዛቸዋል። ይህም ጌታ በመጨረሻ ሲመጣ ከሚጠይቃቸው የእምነት ሥራዎች ጋር
ይመሳሰላል።
ጾማችን ከጠብና ከሙግት በመራቅ ብቻ ሳይሆን መልካም በማድረግ የታጀበ መሆን አለበት። በዕለተ ምጽአትም ጌታ የሚጠይቀን ስለጾማችን ሳይሆን ስለመልካም ሥራችን መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል።
ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና። ማቴ ፳፭፡፴፭።
ይህ
መልካም ሥራ ከእምነትና ከአምልኮ ጋር ሁልጊዜ ልንፈጽመው የሚገባ የዘወትር ጉዳይ እንጂ በጾም ቀን ብቻ
የምናደርገው እንዳልሆነ ማስተዋል አለብን። ድሆችን እና የተራቡትን በጾማችን በምንተወው ቁርስ ብቻ ማሰብ ዋጋ
አያሰጥም። በጾም ወቅትም ሆነ ከጾም ወቅት ውጪ ድሆች የዘወትር አጀንዳችን ሊሆኑ ይገባል። ክርስቶስ የሚጠይቀንና
ዋጋ የምናገኝባቸው አነርሱ ናቸውና።
እንግዲህ
እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው በጾም ላይ ማተኮራችን ብቻ ሳይሆን በአኗኗራችን ከሰዎች ጋር የሚኖረን ግንኙነት
እንዲሁም ወንድሞቻችንን ጥፋታቸውን ለራሳቸው በመንገር ንስሐ እንዲገቡ ማድረግ፡ ከጥልና ከሙግት በመራቅ እርስ በርስ
በፍቅር ሆነን እንድንጾም ያዘናል። በጾማችን ወቅት ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜም ድሆችን ማሰብና መልካም ማድረግ እንደሚገባ መጽሐፉ ያስተምረናል።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለጾም በሚያስተምረን በዚህ ምዕራፍ የመጀመሪያ ክፍል ጾማችን ምን መምሰል እንደሌለበትና ምን መምሰል እንዳለበት ተመልክተናል።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም በቀሪው ክፍል በጾማችን የምናገኘውን በረከት በቀጣይ እናያለን።
ይቆየን።
http://www.bible27.blogspot.com/2012/02/blog-post_29.html#more