Tuesday, March 20, 2012

አንድ ጥያቄ አለኝ!

እ/ር ለሳኦል ያልመለሰበት ምክንያቱ ምንድነው?ማነው ትክክል?-
-1ኛ ሳሙ. 14፤ 37 በሚገኘው ክፍል እ/ር ለሳኦል ያልመለሰበት ዮናታን ከወለላው ስለ በላ ነው?የሳኦልስ ዉሳኔ ትክክል ነበር?1ኛ ሳሙ. 14፤24 ሳኦል ጾምን አወጀ ቁጥር 27 ላይ ዮናታን ስላልሰማ ከወለላው በላ አይኑም በራ ቁ.30 ህዝቡም ሁሉ ቢበሉ ይበረቱ ነበር ነገርግን ለሳኦል መልስ ማጣት ምክንያት ሆኖ የተገኘው ዮናታን ሆነ እጣ ስለወደቀበት ግን በህዝቡ ድምጽ ዮናታን ከመሞት ዳነ.
ትክክል ያደረገው ሳኦል ነው ወይስ ዮናታን ወይስ ህዝቡ? የተጠቀሱትን ጥቅስ በማስታረቅ ብታብራራው። እ/ር ይባርክህ።
yoni Tibesso

መልስ በደጀብርሃን


ይህ ጥያቄ ሰፊ ነገሮችን ወደመዳሰስ ይወስደናል። ስለሆነም ወደጥያቄህ ጭብጥ ከማምራታችን በፊት እስኪ ሕዝቡን፣ ሳኦልንና ዮናታንን ለየብቻቸው እንመልከታቸው።

ሕዝቡ፣

1/ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር አልገዛም በማለቱ ታቦተ ጽዮን ተማርካ ነበር። በኋላም ተመልሳ አቢዳራ ቤት ተቀምጣ ሳለ ሕዝቡ ከጣዖት አምልኮ እንዲወጣ ሳሙኤል አስጠንቅቋቸዋል።

«ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ። በሙሉ ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር ከተመለሳችሁ እንግዶችን አማልክትና አስታሮትን ከመካከላችሁ አርቁ፥ ልባችሁንም ወደ እግዚአብሔር አቅኑ፥ እርሱንም ብቻ አምልኩ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ያድናችኋል ብሎ ተናገራቸው» 1ኛ ሳሙ 7፣3
ሕዝቡም ያለ ንጉሥ በሳሙኤል ነብይነትና ፈራጅነት ይተዳደሩ ነበር።


2/ የእስራኤል ሕዝብ ነብይና ፈራጅ ሆኖ ሳሙኤል ለብዙ ዓመታት ቆይቷል። ሳሙኤል እርጅና እየተጫጫነው በመሄዱ በእርሱ ምትክ ልጆቹን ኢዮኤልና አብያን ሾሞላቸዋል። ይሁን እንጂ የነብዩ ሳሙኤል ልጆች ጉቦ እየተቀበሉ ፍርድን እያጣመሙ ሕዝቡን አስመረሩ እንጂ በአባታቸው መንገድ አልሄዱም።(1ኛ ሳሙ8፣2-3)
በዚህም የተነሳ ሕዝቡ ሳሙኤልን ንጉሥ በላያቸው ላይ እንዲሾምላቸው ግድ ብለው ያዙት።
«እነሆ፥ አንተ ሸምግለሃል፥ ልጆችህም በመንገድህ አይሄዱም አሁንም እንደ አሕዛብ ሁሉ የሚፈርድልን ንጉሥ አድርግልን አሉት» (ቁ፣5)

3/ እግዚአብሔርም ለሳሙኤል ተናገረው። እኔን አላከበሩኝም እንጂ የአንተን ነብይነት ስላልዘነጉ እንደጥያቄያቸው ሹምላቸው አለው።

«እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው። በእነርሱ ላይ እንዳልነግሥ እኔን እንጂ አንተን አልናቁምና በሚሉህ ነገር ሁሉ የሕዝቡን ቃል ስማ» 1ኛ ሳሙ 8፣7
እንደሕዝቡ ጥያቄ ሳኦል በነሱ ላይ በሳሙኤል ተቀብቶ ነገሰ።

«ሳሙኤልም የዘይቱን ብርሌ ወስዶ በራሱ ላይ አፈሰሰው፥ ሳመውም፥ እንዲህም አለው፦ በርስቱ ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶሃል የእግዚአብሔርንም ሕዝብ ትገዛለህ፥ በዙሪያውም ካሉ ጠላቶቻቸው እጅ ታድናቸዋለህ» 1ኛ ሳሙ 10፣1

ከዚህ ቃል የምንማረው ሳኦል የተሾመው በሕዝቡ ጥያቄ እንጂ እግዚአብሔር ለተገዛለት ሕዝብ ራሱ የመረጠው ንጉሥ አይደለም። ሕዝቡ እግዚአብሔር በላያቸው ላይ የነገሰ አምላክ መሆኑን ከመቀበል ይልቅ ከፍልስጤማውያን የሚታደጋቸውን ንጉሥ ፈለጉ።

የአሞንም ልጆች ንጉሥ ናዖስ እንደ መጣባችሁ ባያችሁ ጊዜ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ንጉሣችሁ ሳለ። እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ ይንገሥልን አላችሁኝ» 1ኛ ሳሙ 12፣12

ነብዩ ሳሙኤልን ግን የእግዚአብሔር ነብይ አድርገው በመቀበላቸው ምክንያት ብቻ የንጉሥ አንግሱልን ጥያቄ ምላሽ አገኘ። ሐዋርያው ጳውሎስም ይህንኑ አረጋግጧል።
«ከዚያም ወዲያ ንጉሥን ያነግሥላቸው ዘንድ ለመኑ፥ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሚሆን ሰው የቂስን ልጅ ሳኦልን አርባ ዓመት ሰጣቸው» የሐዋ 13፣21
የሕዝቡ ልብ ወደሳኦል፣ የሳኦልም ልብ ወደሕዝቡ እንጂ ወደእግዚአብሔር ሊሆን ባለመቻሉ ለውድቀትና ለሞት መብቃታቸውን በቀጣዮቹ የሳሙኤል መጻሕፍት ውስጥ እናነባለን።

ሳኦል

ሳኦል የእግዚአብሔርን ንጉሥነት ባልተቀበለ ሕዝብ ላይ የተሾመ ንጉሥ ነበር። ስለዚህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ንጉሥ ሳይሆን የእስራኤል ሕዝብ ንጉሥ ነው። በዚህም የተነሳ ሕዝቡን ከጠላት የሚታደግ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡንም የሚያስጨንቅ ገዢ እንዲሆን ተደርጓል።

«ሎሌዎቻችሁንና ገረዶቻችሁን፥ ከከብቶቻችሁና ከአህዮቻችሁም መልካም መልካሞቹን ወስዶ ያሠራቸዋል። ከበጎቻችሁና ከፍየሎቻችሁ አሥራት ይወስዳል እናንተም ባሪያዎች ትሆኑታላችሁ። በዚያም ቀን ለእናንተ ከመረጣችሁት ከንጉሣችሁ የተነሣ ትጮኻላችሁ በዚያም ቀን እግዚአብሔር አይሰማችሁም» 1ኛ ሳሙ 8፣14-20

እግዚአብሔር እንደልቡ የሆነ ሰው እስኪመርጥ ድረስ ሳኦል ለእግዚአብሔር ፈቃድ ያልተገዛ የሕዝቡ ንጉሥ ሆኖ ነበር።

«አሁንም መንግሥትህ አይጸናም እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሆነ ሰው መርጦአል እግዚአብሔርም ያዘዘህን አልጠበቅህምና እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አዝዞታል አለው» 1ኛ ሳሙ 13፣14

ዮናታን

ዮናታን የሳኦል ልጅ ነው። ከአባቱ የተሰጠው 1000 ጦር ነበረው። 1ኛ ሳሙ 13፣2
ዮናታን ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠይቆ በፍልስጤማውያን ላይ ከጋሻ ጃግሬው ጋር ሁለት ሆነው በመዝመት ገድለዋቸዋል፣ ከስፍራቸውም አባረዋቸዋል። 1ኛ ሳሙ 14፣12-13

ዮናታን አባቱን አገልግሏል። ዮናታን የእግዚአብሔር የልቡ ሰው ከሆነውና ለሕዝቡ ንጉሥ ይሆን ዘንድ ከታጨው ከዳዊት ጋር ተማምሏል፣ ምስጢርም ሲያካፍለው ቆይቷል። 1ኛ ሳሙ 20፣13

ሳኦል በሕዝቡ ላይ ስለሰጠው የመሃላ ቃል

«የእስራኤልም ሰዎች በዚያ ቀን ተጨነቁ ሳኦል፦ ጠላቶቼን እስክበቀል እስከ ማታ ድረስ መብል የሚበላ ሰው ርጉም ይሁን ብሎ ሕዝቡን አምሎአቸው ነበርና። ሕዝቡም ሁሉ መብል አልቀመሱም»

ሳኦል ይህን መሃላ ያማለው ፍልስጤማውያንን እስኪያጠፋ ድረስ ማንም ሰው እስከማታ ምንም እንዳይቀምስ ነበር።
ሳኦል የራሱን ሃሳብ እንጂ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አይከተልም። ፍልስጤማውያንን በእጁ አሳልፎ እንደሚሰጥ ከእግዚአብሔር መልስ ከመጠየቅ ይልቅ ራሱ እንደሚያጠፋቸው አምኖ ተግባሩን በመሃላ አጸና። በመሃላው ራሱም ይሁን መሃላውን የጣሰ መያዙ አይቀርም። ምክንያቱም መሃላው የተፈጸመው በእግዚአብሔር ስም ስለሆነ ነው።
ሳኦል ፍልስጤማውያንን ለመውጋት ከመማሉ በፊት ፍልስጤማውያን በልጁ በዮናታን ተወግተዋል፣የቀሩትም ሸሽተዋል። ዮናታን ወደውጊያው ከመግባቱ በፊት አሳልፎ እንደሚሰጠው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ምልክቶች ጠይቋል።

«እርሱም፦ ወደ እናንተ እስክንመጣ ድረስ ቆዩ ቢሉን በስፍራችን እንቆማለን፥ ወደ እነርሱም አንወጣም፣ነገር ግን፦ ወደ እኛ ውጡ ቢሉን እግዚአብሔር በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና እንወጣለን ምልክታችንም ይህ ይሆናል» 1ኛ ሳሙ 14፣9-11 ይሁን እንጂ ዮናታን ምንም እንኳን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ምልክቶች አግኝቶ ወደውጊያው የገባ ቢሆንም ከመግባቱ በፊት ለንጉሡ መንገር ሲገባው ይህንን ባለማድረጉ በንጉስ ማሃላ ስር እንዲወድቅ ሆኗል። መክብብ በመጽሐፉ እንዲህ ሲል ስለንጉስ ቃል ከባድነት ይናገራል።

«እኔ፣በእግዚአብሔር መሐላ ምክንያት የንጉሥን ትእዛዝ ጠብቅ እልሃለሁ» መክ 8፣2

ሳኦልም የተሳሳተው ፍልስጤማውያን በእግዚአብሔር ፈቃድ በልጁ በዮናታን በኩል ድል መደረጋቸውን ባለማወቁና ጫጫታቸውን ሰምቶ ሊዘምቱበት የተነሱ መስሎት የአምላኩን ፈቃድ ሳይጠይቅ ወደመሃላ መግባቱ ቀዳሚው ስህተት ነበር።
ሁለተኛው ስህተት በመሃላው የተያዘውን ልጁን እንደመሃላው መግደል ሲገባው እርሱን ንጉሥ እንዲሾምላቸው በጠየቁት በሕዝቡ ፈቃድ ስር አድሮ የእግዚአብሔር ስም የተጠራበትን መሃላውን ማፍረሱ ነበር።
የሕዝቡም ትልቁ ስህተት ደግሞ እነርሱ የጠበቁት የንጉሥ መሃላ በእግዚአብሔር ሥም መሆኑን ረስተው ለዮናታን አድልተው የመሃላውን ቃል ማፍረሳቸው ነው።
ስለዚህ ከመጀመሪያው አንስቶ ሕዝቡ ወደእግዚአብሔር ፈቃድ ሳይሆን ወደልባቸው ፈቃድ፣ ንጉሡም ወደአምላክ ፈቃድ ሳይሆን ወደልቡ ፈቃድ በመሆኑ እግዚአብሔር የልቡን ፈቃድ የሚፈጽምለት ሰው አዘጋጅቷል። ይህ ከመሆኑ በፊት ፈቃዳቸውን በራሳቸው ላይ ያደረጉና መሃላቸውን ያላከበሩ ሁሉ በራሳቸው ላይ ቁጣን ማምጣታቸው የግድ ሆኗል።
በመጨረሻቸው ሁሉም ዋጋቸውን ተቀበሉ።

«ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ተዋጉ የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፥ ተወግተውም በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወደቁ፣ፍልስጥኤማውያንም ሳኦልንና ልጆቹን በእግር በእግራቸው ተከትለው አባረሩአቸው ፍልስጥኤማውያንም የሳኦልን ልጆች ዮናታንንና አሚናዳብን ሜልኪሳንም ገደሉ፣ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን፦ እነዚህ ቈላፋን መጥተው እንዳይወጉኝና እንዳይሳለቁብኝ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋኝ አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ነበርና እንቢ አለ። ሳኦልም ሰይፉን ወስዶ በላዩ ወደቀ» 1ኛ ሳሙ 31፣1-5
ለእግዚአብሔር ያልተገዙና በቃላቸው መሃላ የተያዙ ሁሉ የመጨረሻቸውን ዋጋ በራሳቸው ላይ ተቀበሉ። የጥፋታቸውም ፋይል በሞት ተዘጋ።