Saturday, March 17, 2012

ያኔ ሲኦልም ቢሆን የመረጡ ዛሬ ደግሞ ጳውሎስ ነን ይላሉ!

 
(ከደጀብርሃን) ዘመድኩን ከሐዋርያው ጳውሎስና ከሲላስ ጋር አይመሳሰልም!
«ለራስ ሲቆርሱ፣ አያሳንሱ» ማንም ወዳጁን ወይም ራሱን ሲክብና ሲያሞካሽ ይህ ቃል ይነገራል። ደጀ ሰላም የተባለው መካነ ጦማር ግን እሱ የጠላውን ሲያክፋፋና ስሙን ጥላሸት ሲቀባው ወዳጆቹን ደግሞ በማሞካሸት ጳውሎሳዊና ሲላሳዊ ዓይነት የወንጌል ተጋዳይ አድርጎ ሲያቀርብ እንኳን እንደሃይማኖት ሠራተኛነት፣ እንደሥጋውያን ሰዎች ይህንን ለማለት የሚያስችለውን አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ አለመቻሉ አስገራሚ ይሆንብናል።
ደጀ ሰላም እንዲህ ሲል ስለነዘመድኩን ጽፎልናል።
«ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ ከግንድ ተጠርቀው በታሰሩበት ወኅኒ ቤት የወኅኒውን መሠረት ያናወጠውን፣ ምድርን ያንቀጠቀጠውን፣ ወህኒ አዛዡንና ቤተ ሰዎቹን ካለማመን ወደ ማመን የመለሰውን መዝሙራቸውንና ትምህርታቸውን፤ ቅዱስ ጳውሎስ በእስራቱ ዓመታት የከተባቸውን መልእክታት፤ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በግዞቱ ሓላፊያትን፣ ማእከላውያንን፣ መፃዕያትን ያየበትን ራእዩን ያስታውሷል»
እንግዲህ ዘመድኩንን ከሲላስና ከጳውሎስ ጋር ለማመሳሰል የሚያስችለው መነሻ ምንድነው? ብለን ለመጠየቅ የምንገደድ ሲሆን ደጀ ሰላም የወደደውን እንኳን ጳውሎስና ሲላስ ከፈለገም ከሰማይ የወረደ መልአክ ከማድረግና የጠላውን ደግሞ ቤተክርስቲያን እንደተገኘች ውሻ እንደሚያሳድድ ስለምናውቅ እኛው ራሳችን አባባሉን «ለራስ ሰው ሲቆርሱ አያሳንሱ» ብለን ሀሰተኛነቱን ለማሳየት እንሞክራለን።
 በቅድሚያ ከሳሽና ተከሳሽ ወደፍርድ ቤት መሄዳቸውን አጥብቀን የምንቃወመው ጉዳይ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን። በወንጌል አለሁ የሚል ማንም ቢኖር ወደዓለማዊ ፍርድ ቤት ዳኝነትን ፍለጋ ወይም ሙግትና ክርክርን በመሻት የሁለት ወገን ጠላት ሆኖ ከሳሽና ተከሳሽና መሄድ አልነበረባቸውም።
«ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል፥ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋልን?» 1ኛ ቆሮ6፣6
ደጀ ሰላም ብሎግ በዘመድኩን ላይ የፈረደው እስላም ዳኛ ነው፣ በሃይማኖት ስለማይመስለን በግፍ ነው የፈረደበት የሚል ዘገባ አውጥቶ ነበር። ቀድሞውኑ እናንተ መቼ ክርስትና ኖሯችሁ ነው? ወንጌል በማያምኑ ሰዎች ፊት ክስ ሊደረግ እንደማይገባ እየተናገረ ይህንን ጥሳችሁ አይደለም እንዴ ወደሙግት የገባችሁት? ማንም ወደ ሩጫ ሜዳ የሚገባ ተወዳዳሪ በኋላ ሲሸነፍ «ሱሪዬ ነው የጠለፈኝ፤ ቀሚሴ ነው ያደናቀፈኝ »የሚል ተልካሻ ምክንያት ቢደረድር የሩጫውን ውጤት አይቀይረውም። አስቀድሞ ነው እንጂ የማያደናቅፍ ሱሪ ወይም ቀሚስ መልበስ የነበረበት!
ከወደቁ በኋላ መንፈራገጥ፣ አጉል ለመላላጥ እንለዋለን ይህንን ተልካሻ ምክንያት።
በጋሻው ወደክርክሩ ከመገባቱ በፊት ጉዳዩን በእርቅ ለመጨረስ መፈለጉን የነገረን በጋሻው ሳይሆን ይኸው ዛሬ «የቀሚሴን ጠለፈኝ» ዘፈን አቀንቃኝ የሆነውን ደጀ ሰላም ብሎግ ነበር። እንዲያውም አለን እንጂ! …. «እንዲያውም ዘመድኩን ከበጋሻው ጋር ከምታረቅ ሲኦልም ቢሆን መውረድ ይሻለኛል ብሏል» በማለት ከእርቅ ይልቅ ሲኦል እንደሚሻል መፈለጉን ያበሰረን ደጀ ሰላም ራሱ ነበር።
እናስ ታዲያ? በመጀመሪያውኑ ጉዳዩን በእርቅ በመጨረስ የወንጌል ቃል አስተምህሮን በማሳየት መፈጸም እየተቻለ፣ ይህንን የሰላም ገበታ ደፍቶ በመገልበጥ «ትንቢትሰ ይቀድሞ ለነገር» እንዲሉ የተመኙትን ከርቸሌ ከተረከቡ በኋላ እስላም ዳኛ ነው የፈረደብን ማለት ምን ማለት ይሆን?
ዳሩ ግን ደጀ ሰላምም ሆነ የደጀ ሰላም ባለቤት ከኋላ ሆኖ በብር ኃይል ሁሉን መደፍጠጥ የሚቻል እየመሰላቸው ከእርቅ ይልቅ ወደክሱ ገብተው የተመኙትን አገኙ። ምክንያቱም ወንጌልን ለእምነት ሳይሆን ለሸቀጥ አገልግሎት የሚጠቀሙበት ቢጽ ሃሳውያን ካልሆኑ እርቅን ባልጠሉ ነበር። እኛ ግን ይህንን ቃል ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ እናቀርብባቸዋለን።
«ከባላጋራህ ጋር ወደ ሹም ብትሄድ፥ ወደ ዳኛ እንዳይጐትትህ ዳኛውም ለሎሌው አሳልፎ እንዳይሰጥህ ሎሌውም በወኅኒ እንዳይጥልህ፥ ገና በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ እንድትታረቅ ትጋ»ሉቃ 12፣58
ከባለጋራህ ጋር ታረቅ እያለ እነርሱ ግን ከከርቸሌም በላይ ሲኦልን የመረጡበት ምክንያት ምን ይሆን? በእልከኝነት፣ በትእቢት፣ ፍቅረ ቢጽን በመጥላት፣ በትምክህትና በማን አህሎኝነት የሰከሩ ስለሆነ ብቻ ነው። ከዚህ በፊት በዚህ ርእስ ላይ በዚሁ ጉዳይ ጽፈን የሰማን የለም።« የምትጠፋ ከተማ፣ ብትነገር አትሰማ» ሆኖ ነው እንጂ ነግረናቸዋል። ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ
እንግዲህ ይታያችሁ! አንድም የወንጌል መንገድ ያልተከተሉ ፣ እንዲያውም ከወንጌል ቃል ይልቅ ሲኦል እንደሚሻል ያወጁ ሰዎች ዛሬ ደግሞ ተመልሰው ወንጌላውያን መሆናቸውን ሊነግሩንና አብረናቸው የከርቸሌ ዝማሬ እንድንዘምር ይፈልጋሉ። ያውም ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር እራሳቸውን አመሳስለው ዛሬም ይሉኝታና ማስተዋል የተነፈገ ኅሊናቸውን እውነት አድርገን እንቀበል ዘንድ ያግባቡናል።
ዘመድኩን፣ ደጀ ሰላምም ሆነ የደጀ ሰላም ባለቤት በየትኛውም መስፈርት ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር መመሳሰል ቀርቶ ለአተያይ የሚቀርብ ክርስቲያናዊ ምግባር የሌላቸው መሆናቸውን የምንመሰክረው ከልባችን አፍልቀን ሳይሆን የእነሱኑ አፍ ምስክር ቆጥረን ነው። ማስረጃዎቻችን፣
1/ ከወንጌል ቃል እርቅ ይልቅ ሲኦል ይሻላል ማለታቸውን እራሳቸው ነግረውናል።
2/ ሲኖዶስ ወይም ሥልጣን ያለው ማንም የቤተክርስቲያኒቱ አካል እነበጋሻውን ተሀድሶ ወይም መናፍቃን ብሎ በጉባኤ ያላወገዛቸው ሆኖ ሳለ እነደጀ ሰላም ይህንን እያስተጋቡ መገኘታቸው እለት እለት የምናነበው ሐቅ ነው።
3/ የማንንም ሰው መብትና ክብር ለመንካት ወይም ስም እየጠሩ፣ በቪዲዮ፣ በመጽሔት ወይም በሌላ የሚዲያ መንገድ ለማውገዝ ወይም ለማባረር የሚያስችል ሥልጣን ሳይሰጣቸው ይህንን ማድረጋቸውን ሲናገሩ ቤተክርስቲያንን ከመናፍቃን ለመጠበቅ ይሉናል። ማን ላካቸው?  ማን ምን እንደሆነ ተንታኝና ፈራጅ አድርጎ የሾማቸው ማነው? እስኪ ይህንን የገዛ ጽሁፋቸውን ተመልከቱ።

(አርማጌዶንን፣ እንቁ መጽሔትን ልብ ይሏል) የተክልዬ ልጆች በመርካቶ ተ/ሃይማኖት ለፈጸሙት ድብደባ እንዲህ ነው እንጂ ብሎ ያሞካሸው ደጀ ሰላምንም አይዘንጉ!
4/ሐዋርያው ጳውሎስ በማንም ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ አልሰራም፣ የተከሰሰው ኢየሱስን ይሰብካል ተብሎ ሲሆን ዘመድኩን ግን የተከሰሰው የበጋሻውን  ስም አጥፍተሃል ተብሎ ነው።
5/ጳውሎስ ከመታሰሩ በፊት እውር አብርቷል፣ ድውይ ፈውሷል፣ ሙት አስነስቷል፣ አጋንንትን ከሰዎች አስወጥቷል።በማንም ላይ ክፉ ነገር አልፈጸመም፣ አላሰበምም። ዘመድኩን ግን እንኳን ይህንን ሊያደርግ ቀርቶ «በእምነት የደከመ ሆኖ ቢሆን እንኳን በየውሃት መንፈስ ማቅናት ሲገባው ከሰው ልብ አወጣሃለሁ ሲል በበጋሻው ድክመት ላይ ዜናና ፊልም ሰርቶበታል። ከዚህ የወንጌል ቃል ጋር በተጻራሪ ቆሟል አያሰኝም?
ሮሜ 141 በእምነት የደከመውንም ተቀበሉት፥ በአሳቡም ላይ አትፍረዱ።
6/ ጳውሎስ ሲታሰር እጁን ጎትተው ወደወኅኒ ወረወሩት እንጂ ችሎት ቆሞ ተከራክሮ፣ ጠበቃ ቀጥሮ፤ ማስረጃና ምስክር አቅርቦ አይደለም። ዘመድኩን ግን ወራትን ባስቆጠረ ክርክር ጠበቃ አቁሞ፣ ደጋፊዎቹ በርታ ልጃችን፣ ጀግናችን እያሉ ወደሲኦል ሃሳቡ እየገፉት፣ ሰነድና ምስክር አቅርቦ ከጨረሰ በኋላ በሀገሪቱ ሕግ ሊያስቀጣው እንደሚችል የሕግ አግባብ ተጠቅሶበት እንደተፈረደበት  ይታወቃል። ይህም ሆኖ ይግባኝ እንዲጠይቅ ተፈቅዶለት መብቱ የተጠበቀለትን ሰው ከጳውሎስ ጋር ማመሳሰል በጳውሎስ እስር ላይ ከማሾፍ የተለየ አይደለም።
እንደጌታ ቃል የዘመድኩን እስራት ያሳዝነናል። ለራሱም፣ለቤተሰቦቹም ቢሆን ባይታሰርና ሰላማዊ ኑሮውን ቢኖር የተሻለ ነበር። ከታሰረም በኋላ የምንመኝለት እንዲጽናና፣ ተስፋ እንዳይቆጥርና ወደፊት መልካም ኅሊናን ይዞ እንዲወጣ ነው። ከዚያ ባለፈ ግን ደጀ ሰላም እንደሚቀባጥረው ታሳሪው እንዳይታረምና እንዳይማር የሚያሰክር የትእቢት መርዝ አናቀርብለትም። የእሱ እስራት ከሐዋርያው ጳውሎስ እስራት ጋር እንኳን መመሳሰል በምንም መለኪያ የሚነጻጸር አይደለም። ሂደቱ፣ ዓላማና ግቡ የሰማይና የምድር ያህል ይርቃልና ያኔ «ሲኦልም ቢሆን ወርዳለሁ» ብሏል እያሉ እንዳሳሳቱት ዛሬም ደግሞ «እኔ እንደሐዋርያው ነኝ» እንዲል ሌላ የጥፋት ዜና ሲሰሩበት ልንሰማ አይገባም። ታረቁ ስንል ሳትሰሙ የቀራችሁትን ዛሬ ደግሞ ሐዋርያው ነህ እያላችሁ አታሳስቱ እንላለን። ችግሩን ማስቀረት ባንችል ብለን የሚሰማን አላገኘንም እንላለን።
ስለሆነም ዘመድኩን ከሐዋርያው ጳውሎስና ከሲላስ ጋር አይመሳሰልም!