Saturday, June 29, 2013

ከሰዓሊና ገጣሚ ገ/ክርስቶስ ደስታ የግጥም ስብስቦች


The painter-poet, was born in 1932 in the Eastern province of Harar, Ethiopia, to father Aleka Desta, a clergyman, and mother W/o Atsede Mariam Wondimagegnehu. Gebre Kristos completed his elementary education in his native town of Harar, and attended the Haile Sellassie 1st School and General Wingate High School. He later joined the Science Department at Haile Sellassie 1st University, presently Addis Ababa University. Gebre Kristos did not pursue a career in his field of study, scientific agriculture, but instead studied art and painted in his spare time. Initially, Gebre Kristos was a self-taught artist, but in his sophomore year, his predilection for art won out, and Gebre Kristos abandoned his studies in hope of becoming a full-time artist.

Sunday, June 23, 2013

በሰማንያ ወአሀዱ ሽፋን የተፈጸመው የጠላት ሴራ ሲገለጥ (ክፍል ሦስት )



ከባለፈው ክፍላችን የቀጠለውን በሰማንያ ወአሀዱ ሽፋን ጠላት አስርጎ ያስገባውን የስህተት መንፈሱን አሰራር በቀጣይነት እንመረምራለን። ጥንተ ጠላታችን በእግዚአብሔር ዋና ቃል ውስጥ ጥቂት የስህተት ቃላትን ሰንቅሮ ማስገባት መቻሉ ጠቅላላ የአምልኮ ሥርዓታችንን እንደፈለገ ለማናጋት በር ስለሚያገኝ በዚህ ዙሪያ አጥብቆ ይሰራል። ይህንን እስትንፋሰ እግዚአብሔር የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ከአበው ሲወርድ እዚህ ዘመን የደረሰውን ጠብቆና ጠንቅቆ በማቆየት፤ ስህተት ሲገኝ በማቃናት፤ የጎደለውን በማረም፤ የሁል ጊዜ አዲስነቱን እንደያዘ፤ ትውልዱን እያደሰ መቀጠል እንዲችል የማድረግ ኃላፊነቱ የቅዱስ ሲኖዶስና የሊቃውንት ጉባዔው ሥልጣን ቢሆንም ምሁራኑ በዐረፍተ ዘመን በሞት ጥላ ሥር አርፈው ቦታቸውን በመልቀቅ ለጊዜው ጥሬ ትርጉሙን እንኳን ለመረዳት አቅሙ በሌላቸውና «ከተንስኡ ለጸሎት» በዘለለ ቃለ እግዚአብሔርን ለመመርመር ድክመት ቤቱን የሰራባቸው ወንበሩ ላይ ያለአቅማቸው በመቀመጣቸው ቅዱሱ መጽሐፍ ሊበረዝ ችሏል። ሊቃውንቱ ወደዳር ተገፍተው በደጀ ጠኝነት ያንጋጥጣሉ።፤ ገሚሱም በጋዜጣ አዟሪነት ያለቦታቸው ተሰማርተዋል። እነ «በአፍ ጤፍ ይቆሉ»  በሊቃውንት ስም የቤተክህነትን ገበያ ያደራሉ። መጋቤ ብሉይ ሠይፈ ሥላሴን የመሳሰሉ ሊቃውንት የደረሱበትን እውቀትና እውነት እንዳይተነፍሱ በድንቁርና መዶሻ ተመትተው እስከወዲያኛው አሸለቡ። ድኩማነ አእምሮዎች ሲያዋክቧቸው የቆዩት ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ እንኳን በዚህ በጎጋ ጉባዔያተኛ መካከል ባገኙት መንገድ ሁሉ ያካፈሉት ቃለ እውነት ብዙ ዘር ያፈራ ቢሆንም የተመኙትን ያህል ሳይሰሩ ያንን ሁሉ እውቀት ይዘውት የሄዱት ለቤተክርስቲያን ትልቅ ጉዳት መሆኑን እያየነው ነው። 
   እንደው ለመሆኑ ከእሳቸው ወዲያ በነገረ መጻሕፍትና ትርጉም አዋቂነት የሚጠራ ጳጳስ ማን ይሆን? ከተረትና ከእንቆቅልሽ በዘለለ ቃለ እግዚአብሔርን በምልዓትና በስፋት ማስተማር፤ ማረቅ፣ ማቃናት የሚችል አንድም ጳጳስ በዚህ ዘመን አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን የሚቆጨውም ሰው አለመገኘቱ በጣም አሳሳቢ ነው። ሊቃውንት ጉባዔ የተባለው የእነ ክንፈገብርኤል አልታዬና የሊቀ ሥዩማን  ራደ መሥሪያ ቤት ሊቅነቱን ሳናይለት ዘመኑን ፈጠመ።  የሚብሰው ደግሞ ትልቁንና ዋናውን ቃለ እግዚአብሔር/መጽሐፍ ቅዱስ/ ጥንታዊውን የአበው ትርጉምና ሕግጋት ጠብቆ እንደንጹህ የምንጭ ውሃ ኮለል ብሎ የምእመናን የልቡና ጥማት እንዲያረካ ማድረግ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን የነበረውን መጽሐፍ አደፍርሰው፤ በጥብጠውና ከመርዝ ጋር ደበላልቀው በማቅረብ ሊቃውንት የሚባለውን ክብር ትቢያ ላይ ወድቆ እንዲቀር ማድረጋቸው ሌላው አሳዛኙ ገጽታቸው ነው። 
የሊቃውንት ጉባዔነትን ሥልጣን ተሸክመው የራሳቸውን ግዙፍ ድክመትና ስህተት በማየት ከማረም ይልቅ  የመንደር ላይ ጽሁፎችንና በራሪ ወረቀቶችን እየለቀሙ  አብረዋቸው የሌሉ ሰዎችን በማውገዝ መጠመዳቸው የሊቅነት ስያሜ  አቅጣጫው የጠፋ ይመስለናል። በየተአምሩ፤ በየድርሳኑ፤ በየገድላቱ፤ በየመጽሐፍ ቅዱሱ የተሰነቀረውንና ማን እንዳስገባው የማይታወቀውን ከእግዚአብሔር ቃል ሃሳብና ትርጉም የማይስማማውን እየመረመሩ ማስተካከል ሲገባ ሊቃውንት ጉባዔው የተኛበትን ሥራ በፈቃዳቸው ተረክበው «ይህ፤ ይህ ግድፈት ነው፤ ሊታረም ይገባል፤ የቀደምት አበው አስተምህሮ ሥፍራውን ይያዝ » በማለት በማስረጃ አስደግፈው የጠቆሙ ሰዎችን ጽሁፍ እየለቀሙ አውግዘናል ማለቱ ሊቃውንት ጉባዔው ኮምፓስ እንደሌለው መርከብ ውቅያኖስ ላይ መንሳፈፉን ራሱ አረጋግጧል። ሰዎቹ ይታረም ያሉት የተጻፈውን ስህተት አንስተው እንደ ወንጌል ቃልና እንደአበው አስተምህሮ ይታረም ማለታቸው ወንጀል ሆኖ ሊያስወግዝ ቀርቶ እኛ መሥራት ያቃተንን ስለሰራችሁልን እናመሰግናለን ሊባሉ ይገባ ነበር።
እኛም አቅማችንና ችሎቻን የፈቀደውን ያህል በመረጃና በማስረጃ አስደግፈን  ሁሉም እንዲያውቀው በሰማንያ ወአሀዱ ሽፋን ጠላት አስርጎ ያስገባውን የስህተት ቃል ለማሳየት እንሞክራለን። 

1/ የብቻችን መጽሐፍ እንዴት?

በባለፈው ክፍል ሁለት ጽሁፋችን ለመጠቆም እንደሞከርነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፊት እንደትርፍ የቀኖና መጻሕፍት ትቆጥራቸው የነበሩትና ከ2000 ዓ/ም መጽሐፍ ቅዱስ ህትመት በኋላ ግን እንደዋና  የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የደመረችው የመቃብያን መጻሕፍት ሦስት ክፍሎች ከአይሁዳውያን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ቁጥር ውስጥ የሌለ መሆኑን ለማሳየት ሞክረናል። በ3ኛውና በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበሩት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ትንቢተ ሚልክያስ ያሉትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በ39 ክፍል መድበው ትክክለኛ የእግዚአብሔር ቃል የሆኑ የአይሁዳውያን መጻሕፍትን ሙሉ በሙሉ መቀበላቸውም ታሪክ ያስተምረናል። ከዚህ ውጪ የአይሁዳውያን መጻሕፍት ያልነበሩትን የኦሪት መጻሕፍት እንደብሉይ ኪዳን ለመቀበል የሚያስችል ሌላ ምክንያት የለም። ለእስራኤል ዘሥጋ የተሰጡ የእግዚአብሔር ቃል መጻሕፍት ሙሉ በሙሉ በአዲስ ኪዳን ዘመን ተቀባይነት አግኝተዋል። እነዚህንም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ብለን እንጠራቸዋለን። ነገር ግን ለሕዝበ እስራኤል ያልተሰጡና በብሉይ ኪዳን መጻሕፍትነት ያልተመዘገቡ መጻሕፍት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከየት አምጥታ እንደብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ቆጠረቻቸው? ምንጫቸው ከየት ነው?  እነዚህንም በትርፍነት የያዘቻቸው በእርግጥ ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሰጥ የለም። ስማቸውን ዘወትር የምታነሳቸው ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን/ እነአትናቴዎስ/ የማያውቋቸውና ዛሬም ድረስ እናቴ የምንላት የኮፕት ቤተ ክርስቲያን የማታውቃቸውን መቀበላችን ለምን? ብለን መጠየቅ አግባብነት አለው። ደግሞም በዓለማችን ላይ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት በአንዱም ውስጥ የሌለ መጽሐፈ መቃብያን ለኢትዮጵያ ብቻ የተሰጠው ከሰማይ ነው ወይስ ከምድር? መቼና እንዴት? ለሚሉት ጥያቄዎች በእርግጥ በቂ መልስ የሚሰጥ የለም።

2/ዲያብሎስ ከክብሩ የወደቀው ለአዳም ስገድ ተብሎ አልሰግድም በማለቱ ነው። 

መጽሐፈ መቃብያን ምንጩ ያለመታወቁ አንዱ ምክንያት የያዘው ሃሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለመሆኑ ነው። ዲያብሎስ ከክብሩ የወረደው እግዚአብሔር ለአዳም ስገድ ባለው ጊዜ ለሚዋረድልኝ ለአዳምስ አልሰግድም ብሎ እምቢተኛ በመሆኑ ነው ይለናል። ዲያብሎስ ራሱ ይህንን ቃል ሲናገር ያዳመጠው ሰው ማን እንደሆነ ለጊዜው ባይገለጽም መቃብያን ግን የዲያብሎስን ንግግር የሰማ ያህል እንዲህ ሲል አስፍሮታል።
«የሚጠፉ በኔም የሚስቱ ሰዎች ፈጽመው ይበዙ ዘንድ የአዳምም ልጆች ይጠፉ ዘንድ ይህንን በተናገሩ ጊዜ እኔ ደስ ይለኛል። ለሚዋረድልኝ ለአዳም አልሰግድም በማለቴ እግዚአብሔር ስለአባታቸው ስለአዳም ከማዕረጌ አዋርዶኛልና« 3ኛ መቃ 1፤15

ዲያብሎስ ራሱን ከፍ ከፍ ስላደረገና አምላክነትን ስለፈለገ ከማዕረጉ እንደተዋረደ የምታስተምር ቤተ ክርስቲያን፤ የለም ዲያብሎስ የወደቀው ለአዳም ስገድ በተባለ ጊዜ አልሰግድም በማለቱ ነው የሚለውን የመቃብያን መጽሐፍ፤ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ያለበት የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ነው በማለት ከ 81 ዱ ጋር አዳብላ ልትቆጥረው እንዴት ቻለች? ጥያቄአችን ነው። አይሁዶቹም እንደብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ያልቆጠሩት፤ ኮፕቶችና ሌሎቹም አብያተ ክርስቲያናት የማያውቁትን ይህንን መቃብያንን ከብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ጋር እንድንደምረው የሚያስገድደን መንፈሳዊ ይዘቱ ምንድነው? ስለ ሰማንያ ወአሀዱ መጽሐፍ ቅዱስ ስንናገር አሰሱንና ገሠሡን ሁሉ በመቆጠር ሊሆን አይገባውም። የአንድ መንፈሳዊ መጽሐፍ ልኬታ ምንጩ፤ መንፈሳዊነቱ፤ ተቀባይነቱና አገልግሎቱ ካልተመዘነ የጠላት አሰራር መግባቱ አይቀሬ ይሆናል። 

3/ ሳምራውያን ትንሣዔ ሙታን የለም ብለው ያምኑ ነበር ወይ?

ስለሰዱቃውያንና ስለፈሪሳውያን ትምህርተ ሃይማኖት የምናገኘው ማስረጃ ያለው በአዲስ ኪዳን ውስጥ ብቻ ነው። ሁለቱም የካህናተ ኦሪት ወገን ቢሆኑም  ሰዱቃውያን ከሞት በኋላ ስላለው ትንሣዔም ሆነ ዘላለማዊነት በፍጹም እምነት የላቸውም። ትንሣዔም፤ መላዕክትም የለም ባዮች ናቸው። ፈሪሳውያን ግን መላእክትም፤ ትንሣዔ ሙታንም መኖሩን  ቢያምኑም ይህ የሚሆነው ለአይሁዳውያን ብቻ ነው የሚል የትምክህት አስተምህሮ ስለነበራቸው ኢየሱስ ለክርስቲያኖች እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል።
«ኢየሱስም፦ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ አላቸው። ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ እንድትጠበቁ ብዬ ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉምን? እነርሱም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዲጠበቁ እንዳላላቸው ያን ጊዜ አስተዋሉ» ማቴ 16፤6-12 የአዲስ ኪዳን የትንሣዔ አዋጅ ለተወሰነ ሕዝብ ስላይደለ የፈሪሳውያንን አስተምህሮ ክርስቲያኖች መቀበል ስለሌለባቸው ከዚህ ክፉ እርሾ እንዲጠበቁ አሳስቧል። እንደሰዱቃውያንም ትንሣዔ የለም ከሚል ትምህርትም ራሳቸውን እንዲጠብቁ ጳውሎስ  ሲያስረዳ የስንዴ ቅንጣት እንዴት ፈርሳና በስብሳ  ፍሬ እንደምታፈራ ትንሣዔውን በምሳሌ ሲያስተምር «አንተ ሞኝ፥ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም» 1ኛ ቆሮ 15፤36 ይለናል።
እዚህ ላይ ስለሰዱቃውያንና ስለፈሪሳውያን የትንሣዔ ሙታን እምነት ማንሳት ያስፈለገው ከላይ በቁጥር 3 ላይ ላመለከትነው የጥያቄ ኃይለ ቃል መንደርደሪያ እንዲሆነን ነው። ሰዱቃውያንና ፈሪሳውያን ስለትንሣዔ ሙታን ያላቸው እምነት ከላይ እንደገለጽነው የአዲስ ኪዳን አስረጂ ከሆነ ሳምራውያን የሚባሉት ሕዝቦች ትንሣዔ ሙታን የለም ያሉት መቼ ነው? ብለን እንጠይቃለን። ምክንያቱም መጽሐፈ መቃብያን ሳምራውያን ትንሣዔ ሙታን የለም ብለዋል ይለናልና። 

አጭር ታሪክ፤

ሴኬም የያዕቆብ ምንጭ ያለባት የዐሥሩ ነገድ ሰሜናዊው እስራኤል መቀመጫ ከተማ ነበረች። የሰሎሞን መንግሥት በልጁ በሮብዓም/ ሁለት ነገድ/ በኢየሩሳሌም እና በአገልጋዩ በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም /ዐሥር ነገድ/ በሴኬም ከተከፈለ ( 1ኛ ነገ 12፤20) በኋላ ቆይቶ የሰማርያ ታሪክ ይጀምራል። እሱም የአክአብ አባት ዘንበሪ ሳምር ከሚባለው ሰው ላይ ከሴኬም ከተማ በስተቀኝ ያለውን ተራራ በሁለት መክሊት ከገዛ በኋላ በባለቤቱ በሳምር ስም ተራራ ላይ ቤት ሰርቶ ቦታውን ሰማርያ ማሰኘቱን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። 1ኛ ነገ 16፤24 ከተማው እያደገ፤ ሀገሩም እየሰፋ ሰማርያ ስያሜውን ይዛ ዛሬም ድረስ አለች። ሰማርያ ገሪዛንና ጌባል የሚባሉ የአምልኮ ኮረብታዎቿን ይዛ በመገኘቷ ከሁለቱ ነገድ መዲና ከሆነችው ከኢየሩሳሌም ጋር ኅብረት ያልነበራቸው ከዚያን ጊዜ አንስቶ ነበር። ስለዚህም ጌታችን ከኢየሩሳሌም ወደሰሜናዊ የገሊላ አውራጃ ለመሄድ አማራጭ መንገዱ ሩቅ ስለሆነና የመጣበትም ዓላማ ስለነበረው በዚህች ከይሁዳውያን ጋር ኅብረት ባልነበራት በሰማርያ ማለፉን እናነባለን። (ዮሐ 4፤4)

ሰማርያውያን የእግዚአብሔር የክብሩ መገለጫ ስፍራ ገሪዛን ተራራ እንጂ ኢየሩሳሌም አይደለችም ከማለታቸው በስተቀር፤ የትንሣዔ ሙታንና የገነትንም መኖር ያምናሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፈ መቃብያን የተባለው የአዲስ ኪዳኑን ታሪክ እንደብሉይ ኪዳን ዘመን ትረካ ወደኋላ ጎትቶ የሌለውን ነገር ያስነብበናል።
«ሳምራውያን ግን ሥጋችን ትቢያ ይሆናል፣ አይነሳም ይላሉ» (2ኛ መቃ 14፤1-3) እዚህ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳው መቃብያን የተባለው መጽሐፍ በአዲስ ኪዳን የተጻፈውንና ጌታችን ያስተማረውን ታሪክ ስለሰዱቃውያንና ፈሪሳውያን ይዞ መገኘቱ አንዱ ነጥብ ሲሆን ትንሣዔ ሙታን የለም ያላሉትንና የማይሉትን ሳምራውያንን ከሰዱቃውያን ጋር አብሮ መጨፍለቁ ታሪኩን አስገራሚ ያደርገዋል። ምክንያቱም ሰዱቃውያንና ፈሪሳውያን ስለትንሣዔ በጠየቁት ጊዜ ሳምራውያን ያልነበሩ ሆነው ሳለ መቃብያን ግን ልክ እንዳሉ ቆጥሮ፤ ያልተናገሩትን ስለመናገራቸው መዘገቡ ምን ይባላል? ሳምራውያን የብሉይ ኪዳን እምነት ተከታዮች ስለትንሣዔ ሙታን ያላቸው እምነት ግልጥ ነው። መቃብያን ግን የትም ያልተጻፈውን አንስቶ ይለጥፍባቸዋል።
ዛሬ በቁጥር ከ 800 የማይበልጡ ሳምራውያን በትንሣዔ ሙታንም በመላእክትም መኖር የማመን ጥንታዊ እምነታቸውን ያልተዉ የ10ሩ ነገድ ዘሮች በሰማርያ ይኖራሉ። መቃብያን ግን ይዋሽባቸዋል። ለምን?
(ይቀጥላል)

Sunday, June 16, 2013

«መድኃኒት መልካም ነው፤ መድኃኒትን አላግባብ መጠቀም ግን አደጋ አለው»



(በ2002 ዓ/ም በሳይበር ኢትዮጵያ ድረ ገጽ አባ /ትንሣዔ ላደረጉት ሃይማኖታዊ ክርክር፤ ተሳታፊ ከሰጣቸው መልስ ተስተካክሎ የተወሰደ)
 «የሞኝ ለቅሶ መልሶ፤ መልሶ» እንዲሉ ስንት ያውቃሉ ተብሎ የሚነገርላቸው ትልቅ ሰው የባልቴት ወሬ ሲያንስነብቡን ይገርማል። በመሰረቱ ቅድስት ማርያም እሙ ለእግዚእነ፤ በኅቱም ድንግልና ወለደችው ብሎ ማመን ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኘ እንጂ ከመጽሀፈ ባልቴት የተወረሰ አይደለም። እናትህና «አባትህን አክብር»ያለው መጽሀፍ ቅዱስ የኢየሱስ ክርስቶስን እናት ክብር ዝቅ ማድረግ ጤናማነት አይደለም። ችግሩ ግን ያለው ማርያም ክርስቶስን በሥጋ ስለወለደችውና ይህንን የመመረጥ ጸጋ ለማጉላትና በጣም የሚወዷት አድርጎ ለመሳል የተሞከረበት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነና ይህንኑም «ትንሽ ዱቄት ይዘህ ወዳለው »ተጠጋ እንዲሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነውን እና እሱን የሚያፈርሰውን ሃይለ ቃል ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እየለቀሙ ይሄ ይደግፈናል፤ ይሄ ይረዳናል የሚል ለራስ ማሳመኛና ሌላውን በራስ ትርጉም መከራከሪያ አድርጎ ማቅረብ ምን ይሉታል? እስኪ አባ ከላይ የሰጡበትን የሞገት ሂደቶች እንቃኝ። ተዓምረ ማርያም አባ ገብርኤል አባ ሚካኤል በተባሉ የግብጽ ጳጳስት ዘመን፤ ቆስጠንጢኖስ ብሎ ራሱን በሰየመው ዘርዓ ያዕቆብ በነገሰ በ7ኛው ዐመት ከዓረብኛ ወደ ግዕዝ ተተረጎመ ይላል የተዓምር መቅድም። እውነቱ ይሄ ሆኖ ሳለ አባ ወ/ትንሳዔ ተዓምረ ማርያም ከዘርዓ ያዕቆብ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደነበረ አድርጎ ማቅረብን ምን ይሉታል? አባ በእርግጥ እውነቱን ያውቁታል፤ ችግሩ ግን በስብከተ ወንጌል የካቡት ስምና ክብር ተዓምር በሚሉት መጽሐፍ ልቡ የተሰረቀው ወገን ባንድ ሌሊት ዓይናቸውን ላፈር እንደሚላቸው ስለሚያውቁ ይህንኑ ጠብቆ ለመኖር ስሉ ብቻ ነው ብሎ መገመት ይቻላል። እናም አባ ተዓምር ተብዬው መጽሐፍ ኢትዮጵያ የገባው በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ንግስና መሆኑን ከተዓምር መቅድም አንብበው ይመኑ እንልዎታለን። የሚገርመው ግን ተዓምር ተብዬው መጽሀፍ ከግብጽ መጣሁ ብሎ መቅድሙ ላይ ይቀባጥር እንጂ ይህንን የተዓምር መጽሐፍ የግብጽ (ኮፕቲክ) ቤተክርስቲያን የማታውቀው መሆኑ ነው። ግብጽ የራስዋ የሆኑ  መጻሕፍቶችዋንም እንደዚህ እንደእኛ በማውገዝና በማስፈራራት በ «አሌ ለከ» በወየውልህ ማስፈራሪያ  የማያውቀውን ንባብ እንዲሰማ በማይፈታ ሥልጣን በጽኑ አወገዝን እያሉ የፍርሃት ቀንበር በግድ አይጭኑም። በየትኛውም የግብጽ ቤተክርስቲን ከሰሜን አሌክሳንድሪያ እስከ ደቡባዊ ለክሰር ከተሞች ብንሄድ የኢትዮጵያው ተአምር ተመሳሳዩ በግብጽ የለም። ካይሮ በሚገኘው የኮፕቲክ ቤተመጽሃፍት ውስጥ ከኢትዮጽያ የመጣ ተብሎ በግዕዝ እንደተጻፈ ተቀምጦ ይገኛል። በለንደን ብሪቲሽ ሙዚየም ከግዕዝ በስተቀር የሌላ የማንም ምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት አይገኝም። ታዲያ ዘርዓ ያዕቆብ ከየት አመጣው? ምንአልባት ለእግዚአብሔር እኛ ልዩ ህዝቦች ስለሆንን ከሰማይ ወርዶልን ይሆን? ምን አለበት የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት ለእኛ እንደሚስማማን አድርገን እየተረጎምን አዎ! ወርዶልናል ብንል!! አባ ሌላው መከራከሪያ ነጥባቸው «በክርስቶስ ያመኑቱ ኃይል ይከተላቸዋል» የሚለው የወንጌል ቃል ነው። ስለሆነም የተደረገውን ተዓምራት ሁሉ ልንቀበል እንዲገባን ይመክሩን ዘንድ መሻታቸው ነው። በእርግጥ በክርስቶስ ያሉ ቅዱሳን ድንቅ ተዓምርን ሰርተዋል፤ዛሬም ይሰራሉ። ሌላው ይቅርና አባ እርስዎም የእግዚአብሔር መንፈስ ካደረብዎ ብዙ ተአምራትን ሊሰሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ማንኛውም ተአምር በስመ ክርስቲያን ስለተሰራ እንዳለ ለመቀበል የማንችለው፤
1/በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሲመዘን የሚጋጭ ሆኖ መገኘት የለበትም።
2/በተደረገው ተዓምር ክብሩ ሁሉ ኃይልን ለሰጠ ለክርስቶስ መሆን አለበት። (የሐ/ሥራ14፤15)
3/ ተዓምር ሁሉ እውነት ስላይደለ የእምነትና የምግባር ሚዛኑ መለካት አለበት።(1ኛ ዮሐ4፤1)
ሀ/ ከዚህ አንጻር አጼ ዘርዓ ያዕቆብ የተዓምር መጽሐፍ ሲመዘን በቅድሚያ ጠላቶችችሁን ውደዱ፤ የሚሰድቧችሁን መርቁ የሚለውን የወንጌል ቃል ሽሮ አናምንም፤ አንቀበልም ያሉትን አባ እስጢፋኖስንና ደቀመዛሙርቱን አፍንጫቸውን ፎንነው(ቆርጠው) ጉድጓድ ቆፍረው እስከአንገታቸው በመቅበር ከብት እንደነዱባቸው፤ አስቃይተው ስለገደሏቸው ይህም ታላቅ የጽድቅ ስራ እንደሆነ ተቆጥሮ የዚህን በረከት አሳድርብን ብሎ ሰው ሁሉ እንዲቀበል በውግዘት ያስገድዳል። ይህ እንግዲህ የዘርዓ ያዕቆብን የመግደልና የማሰቃየት ተዓምር፤ ተዓምረ ማርያም በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ማርያም ደስ መሰኘቷን ተጽፎ ይገኛል።  በቅዱስ ወንጌላችን ውስጥ ክርስቲያኖች ስለእምነታቸው መገደላቸውን እንጂ ለማሳመን ሰው ገደሉ የሚል አንድም ቦታ ተጽፎ አናገኝም። ስለዚህ ተዓምረ ማርያም መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም ብሎ መደምደም ይቻላል። ሰውን መግደል ለእውነተኛ ክርስቲያኖች እንደክርስናትያናዊ ተአምር አይቆጠርም። ድንግል ማርያምም ሰው የገደለውን ሰው ቅዱስ ትለዋለች ብለን አናምንም። አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ግን ቅዱስ ተብሎ ቤተክርስቲያን ታንጾለት፤ ስም አጠራሩ ጳጉሜን 3 ቀን ይከበራል።
ለ/ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ጅግራ ናት ብለው ይከራከራሉ እንዲሉ አምልኮ ስዕልን ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ የኦሪቱን የሚናተፍ አውራ ዶሮ አስመስሎ ሙሴ ሁለቱን ኪሩብ እንዲቀረጽ የተነገረውን ቃል ሁሉም ኦርቶዶክሳዊያን መምህራን ሳይጠቅሷት እንደማያልፏት ሁሉ አባም ያቺኑ ጭምብል ብቅ አድርገዋታል። ሙሴ አስመስለህ ቅረጽ የተባለው ለምንድነው? አስመስሎ መቅረጽን የታዘዘው ሙሴ ብቻ ነው ወይስ ሕዝቡ ሁሉ? አስመስሎ የተቀረጸው ምስል የሚቀመጠው በየሰዉ ቤት ወይስ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ብቻ? አስመስሎ የሚቀረጸው ምስል ዓይነት ኪሩብ ወይስ የሰው ምስል? በቁጥርስ ስንት? አጠቃላይ የብሉይ ኪዳን ሕግ ለም? እንዴት? ለማንና መቼ?  የሚለውን አመክንዮአዊ ሕግ ባለማየት የራስን የልብ መሻት ከልብ ለማድረስ መጠቃቀሱ ተገቢ አይደለም እንልዎታለን። በአዲስ ኪዳን ስለምስል የተነገረን ሳይኖር እናድርግ ብንል እንኳን የሙሴ የቅድስተቅዱሳን ኪሩብ ሳይሆን ልባችን ያፈለቀውንና በጭብጥ አልባ ምትሀት(illusion) የምንስላቸውና የምንቀርጻቸውን ሁሉ በህዝበ እስራኤል ዘንድ እንደተደረገ አድርጎ መቁጠር ዋሾ ቀጣፊ ያሰኛል።
     ሙሴ እንዳደረገው እናድርግ ብንል እንኳን  ሙሴ በሚናተፍ አውራ ዶሮ ዓይነት የቀረጸው ኪሩብ የተቀመጠው በመንበሩ ላይ በቅድስተ ቅዱሳን እንጂ በሕዝበ አስራኤል ድንኳን ሁሉ አይደለም። አንድም ቦታ ሕዝቡ የሙሴን ኪሩብ ምስል ሰርቶ በየቤቱ አስቀመጠ የሚል ጽህፉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም። ስለዚህ ሙሴን እንደምሳሌ ማቅረብዎ ከጠላት የተገኘ ምክር እንጂ የመንፈስ ቅዱስ አይደለም። ለሀገር ለመንደሩ፤ለደጅ ለሰፈሩ በመፍቀድ ምንጭና ባለቤት የሌላቸውን ሰዓሊ፤ ጠራቢ ያልሕግ የሰውን ልብ ሊያማልል፤ ዋጋ ገበያ እንዲያወጣለት የሚያጓጓ አድርጎ የሳለውን ሁሉ ሰው እየገዛ እንዲያመልክ እንዲሰግድ ማስተማር የጤንነት አይደለም። ሙሴም ይህንን አላደረገም፤ አላስተማረምም። የስዕልና የምስል አምልኮ መቼ እንደተጀመረ? ማን እንደጀመረ? ሊቃውንቱን ስንት እንዳከራከረ ተጽፎ ይገኛል። ወደኢትዮጵያም ቤተክርስቲያን መቼ እንደገባ ይታወቃል።
        ስዕል መሳልና ለስዕል መስገድ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ስለዚህ የዛሬዎቹ ሰዎች ስለምስል ሙሴን አግዘን ብለው ኪሩብን ከመጥቀሳቸው በፊት ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ምስልና ስዕል በስግደት የማይታወቅበት ጊዜ ነበር። በዚህ ጉዳይ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። የሚገርመው ደግሞ ስዕልና ምስል በሙሴ ተፈቅዷል ባዮች ህዝብ እንዲሳሳት ማድረጋቸውን አለማወቃቸው የሚያሳየው በዛሬዋ ቤተክርስቲያን መቅደስ ውስጥ የሚናተፉ አውራ ዶሮ የሚመስሉ ሁለቱ የሙሴ ኪሩብ አለመኖራቸው ነው። ምነው የሙሴን የኪሩብ ምስል ከቤተመቅደሱ አስወገዳችሁት? ሙሴን እንደአጋዥ ምክንያት ስታቀርቡ ሙሴ ያደረገውን መተዋችሁ ለምነው? ወይስ ሙሴ አሻሽሉት የሚል ሕግ ትቶላችሁ ነበር?
      ለህዝቡ በምክንያትነት ኪሩቦቹን ስትጠቅሱ እናንተ የሱን አርአያና ምሳሌ ተከትላችሁ ቤተመቅደሱ ውስጥ እንደሚናተፍ አውራ ዶሮ ግራና ቀኝ አለማስቀመጣችሁ የናንተ ሥራ ከሙሴ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ምስክር ነው። ስዕልም ይሁን ምስል ለታሪክ አስረጂ፤ ለመረጃ፤ ለትምህርት አስረጂና ጠቃሚ ሊሆን ከሚችል በላይ በየቤታችን ወይም በየመቅደሱ እጣን እንድናጥን፤ እንድንሰግድ፤ ከፊት ለፊታችን አስቀምጠን እንድንጸልይባቸው አንድም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት የለንም። እግዚአብሔር የሚገለጥበትን መንገድ ለሙሴ በብሉይ ኪዳን ተናግሯል። በአዲስ ኪዳንም በጾም፤ በጸሎት፤ በምጽዋትና በክርስቲያናዊ ምግባር ከተጋን የእግዚአብሔርን መልስ ለማግኘት፤ መልዕክት ለመቀበል፤ የሚገለጥበት መንገድ ያለራሱ ማንም አያውቀውም። እግዚአብሔርን ለመለመን በቅዱስ ሚካኤል ስም ካቶሊካዊው ጉይዶ ሬኒ በ1636 ዓ/ም በልቡ አቅንቶ፤ ችሎታውን ተጠቅሞ የሳለውን ስዕል ከገበያ ገዝቶ በመስገድ ወይም በእጣን ማጠን በዚያ በኩል እግዚአብሔርን መፈለግ እብደት ነው። ጉዶ ሬኒ ዛሬ ላይ ይህንን ቢያይ ኖሮ ምን ይል ይሆን?

                                 (www.artcyclopedia.com)
ሐ/ ሌላው ችግራችሁ የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት አለቦታው በመጠቀም የልባችሁን መሻት ሁሉ በእሱ ቻይነት ካባ ለመሸፈን መሞከር ነው። ተአምር ሁሉ እውነት አይደለም ያልኩበት 3ኛው ነጥቤ ወንጌል፤ አባት አባ ያለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማይ የሚገባ አይደለም እንዳለው ሁሉ ተዓምር ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው ብለን አንቀበልም። በዚህ ዓለም ብዙ መናፍስት ገብተዋልና። ሲሞን መሰርይ የሰማርያ ከተማ ድንቅ ተዓምር ሰሪ ነበር። ግን ተዓምሩ ከእግዚአብሔር መንፈስ አልነበረም። ታዲያ እነዚህ የኛ ሰዎች እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ስለሆነ በኛ ተጽፈው የተገኙትን ተአምራት ሁሉ ድንቅ ስራ እያላችሁ ተቀበሉ ይሉናል። እስኪ አንዱን እንመልከት፤ በገድለ ተ/ ሃይማኖት የተሰራ ተዓምር ነው። አባ ተ/ ሃይማኖት «ባህር አልቅም» የተባለ ሰይጣን በመስቀል ምልክት አማትበው ከያዙት በኋላ አሳምነው፤ አስተምረው፤ አጥምቀው፤ እግዚእ ኀረዮ ብለው ስመ ክርስትና ሰጥተው ካበቁ በኋላ አመነኮሱት የሚል አስነብበበውናል። በእነሱ እንዴት ብሎ መጠየቅ አይቻልም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ነዋ!!! ጥሩ የበደል መሸፈኛ ምክንያት!!
እኛ የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት ብናምንም ከሃሌ ኵሉነቱን አለአግባብ ሲጠቀሙበት ማየት ስለማንፈልግ እንዲህ እንጠይቃቸዋለን።
1/ ሰይጣን ስጋና ደም አለው ወይ? ሲገርዝስ ደም ይፈሰዋል? ግርዛትስ ክርስቲያን ለመሆን መመዘኛ ነው? «በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና» ገላ 5፤6
2/ ሰይጣን ንስሃ ይገባል ወይ? በወንጌልስ ሊያምን ይችላል?
3/ የክርስቶስ ሞትና ትንሳዔ (ሎቱ ስብሐት) ሰይጣናትን ያካትታል ወይ? ሰይጣን ዘላለማዊ ህይወትን ወርሶ ገነት ገባ የሚሉ ሰዎችን አባ፤ ምን ይሏቸዋል?
መቼም በዚህ ላይም ጉድ እንዲያስነብቡን እንጠብቃለን። በበኩሌ የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት አለቦታው መጠቀም በእግዚአብሔር ላይ ከማሾፍ የተለየ አድርጌ አላየውም። መጠያየቅና እውነቱን ከመረዳዳት ባሽገር ጴንጤ፤ተሃድሶ፤ካቶሊክ፤መናፍቅ ወዘተ መባባል የትም አያደርስም። መድኃኒት መልካም ነው፤ መድኃኒትን አለቦታው መጠቀም ግን አደጋ አለው፤ የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት ለልባችን መሻት ሁሉ ማዋላችን ይብቃ። ከእውነቱ እንታረቅ። አስተዋይ ልቦና ይስጠን።