Sunday, June 16, 2013

«መድኃኒት መልካም ነው፤ መድኃኒትን አላግባብ መጠቀም ግን አደጋ አለው»



(በ2002 ዓ/ም በሳይበር ኢትዮጵያ ድረ ገጽ አባ /ትንሣዔ ላደረጉት ሃይማኖታዊ ክርክር፤ ተሳታፊ ከሰጣቸው መልስ ተስተካክሎ የተወሰደ)
 «የሞኝ ለቅሶ መልሶ፤ መልሶ» እንዲሉ ስንት ያውቃሉ ተብሎ የሚነገርላቸው ትልቅ ሰው የባልቴት ወሬ ሲያንስነብቡን ይገርማል። በመሰረቱ ቅድስት ማርያም እሙ ለእግዚእነ፤ በኅቱም ድንግልና ወለደችው ብሎ ማመን ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኘ እንጂ ከመጽሀፈ ባልቴት የተወረሰ አይደለም። እናትህና «አባትህን አክብር»ያለው መጽሀፍ ቅዱስ የኢየሱስ ክርስቶስን እናት ክብር ዝቅ ማድረግ ጤናማነት አይደለም። ችግሩ ግን ያለው ማርያም ክርስቶስን በሥጋ ስለወለደችውና ይህንን የመመረጥ ጸጋ ለማጉላትና በጣም የሚወዷት አድርጎ ለመሳል የተሞከረበት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነና ይህንኑም «ትንሽ ዱቄት ይዘህ ወዳለው »ተጠጋ እንዲሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነውን እና እሱን የሚያፈርሰውን ሃይለ ቃል ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እየለቀሙ ይሄ ይደግፈናል፤ ይሄ ይረዳናል የሚል ለራስ ማሳመኛና ሌላውን በራስ ትርጉም መከራከሪያ አድርጎ ማቅረብ ምን ይሉታል? እስኪ አባ ከላይ የሰጡበትን የሞገት ሂደቶች እንቃኝ። ተዓምረ ማርያም አባ ገብርኤል አባ ሚካኤል በተባሉ የግብጽ ጳጳስት ዘመን፤ ቆስጠንጢኖስ ብሎ ራሱን በሰየመው ዘርዓ ያዕቆብ በነገሰ በ7ኛው ዐመት ከዓረብኛ ወደ ግዕዝ ተተረጎመ ይላል የተዓምር መቅድም። እውነቱ ይሄ ሆኖ ሳለ አባ ወ/ትንሳዔ ተዓምረ ማርያም ከዘርዓ ያዕቆብ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደነበረ አድርጎ ማቅረብን ምን ይሉታል? አባ በእርግጥ እውነቱን ያውቁታል፤ ችግሩ ግን በስብከተ ወንጌል የካቡት ስምና ክብር ተዓምር በሚሉት መጽሐፍ ልቡ የተሰረቀው ወገን ባንድ ሌሊት ዓይናቸውን ላፈር እንደሚላቸው ስለሚያውቁ ይህንኑ ጠብቆ ለመኖር ስሉ ብቻ ነው ብሎ መገመት ይቻላል። እናም አባ ተዓምር ተብዬው መጽሐፍ ኢትዮጵያ የገባው በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ንግስና መሆኑን ከተዓምር መቅድም አንብበው ይመኑ እንልዎታለን። የሚገርመው ግን ተዓምር ተብዬው መጽሀፍ ከግብጽ መጣሁ ብሎ መቅድሙ ላይ ይቀባጥር እንጂ ይህንን የተዓምር መጽሐፍ የግብጽ (ኮፕቲክ) ቤተክርስቲያን የማታውቀው መሆኑ ነው። ግብጽ የራስዋ የሆኑ  መጻሕፍቶችዋንም እንደዚህ እንደእኛ በማውገዝና በማስፈራራት በ «አሌ ለከ» በወየውልህ ማስፈራሪያ  የማያውቀውን ንባብ እንዲሰማ በማይፈታ ሥልጣን በጽኑ አወገዝን እያሉ የፍርሃት ቀንበር በግድ አይጭኑም። በየትኛውም የግብጽ ቤተክርስቲን ከሰሜን አሌክሳንድሪያ እስከ ደቡባዊ ለክሰር ከተሞች ብንሄድ የኢትዮጵያው ተአምር ተመሳሳዩ በግብጽ የለም። ካይሮ በሚገኘው የኮፕቲክ ቤተመጽሃፍት ውስጥ ከኢትዮጽያ የመጣ ተብሎ በግዕዝ እንደተጻፈ ተቀምጦ ይገኛል። በለንደን ብሪቲሽ ሙዚየም ከግዕዝ በስተቀር የሌላ የማንም ምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት አይገኝም። ታዲያ ዘርዓ ያዕቆብ ከየት አመጣው? ምንአልባት ለእግዚአብሔር እኛ ልዩ ህዝቦች ስለሆንን ከሰማይ ወርዶልን ይሆን? ምን አለበት የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት ለእኛ እንደሚስማማን አድርገን እየተረጎምን አዎ! ወርዶልናል ብንል!! አባ ሌላው መከራከሪያ ነጥባቸው «በክርስቶስ ያመኑቱ ኃይል ይከተላቸዋል» የሚለው የወንጌል ቃል ነው። ስለሆነም የተደረገውን ተዓምራት ሁሉ ልንቀበል እንዲገባን ይመክሩን ዘንድ መሻታቸው ነው። በእርግጥ በክርስቶስ ያሉ ቅዱሳን ድንቅ ተዓምርን ሰርተዋል፤ዛሬም ይሰራሉ። ሌላው ይቅርና አባ እርስዎም የእግዚአብሔር መንፈስ ካደረብዎ ብዙ ተአምራትን ሊሰሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ማንኛውም ተአምር በስመ ክርስቲያን ስለተሰራ እንዳለ ለመቀበል የማንችለው፤
1/በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሲመዘን የሚጋጭ ሆኖ መገኘት የለበትም።
2/በተደረገው ተዓምር ክብሩ ሁሉ ኃይልን ለሰጠ ለክርስቶስ መሆን አለበት። (የሐ/ሥራ14፤15)
3/ ተዓምር ሁሉ እውነት ስላይደለ የእምነትና የምግባር ሚዛኑ መለካት አለበት።(1ኛ ዮሐ4፤1)
ሀ/ ከዚህ አንጻር አጼ ዘርዓ ያዕቆብ የተዓምር መጽሐፍ ሲመዘን በቅድሚያ ጠላቶችችሁን ውደዱ፤ የሚሰድቧችሁን መርቁ የሚለውን የወንጌል ቃል ሽሮ አናምንም፤ አንቀበልም ያሉትን አባ እስጢፋኖስንና ደቀመዛሙርቱን አፍንጫቸውን ፎንነው(ቆርጠው) ጉድጓድ ቆፍረው እስከአንገታቸው በመቅበር ከብት እንደነዱባቸው፤ አስቃይተው ስለገደሏቸው ይህም ታላቅ የጽድቅ ስራ እንደሆነ ተቆጥሮ የዚህን በረከት አሳድርብን ብሎ ሰው ሁሉ እንዲቀበል በውግዘት ያስገድዳል። ይህ እንግዲህ የዘርዓ ያዕቆብን የመግደልና የማሰቃየት ተዓምር፤ ተዓምረ ማርያም በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ማርያም ደስ መሰኘቷን ተጽፎ ይገኛል።  በቅዱስ ወንጌላችን ውስጥ ክርስቲያኖች ስለእምነታቸው መገደላቸውን እንጂ ለማሳመን ሰው ገደሉ የሚል አንድም ቦታ ተጽፎ አናገኝም። ስለዚህ ተዓምረ ማርያም መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም ብሎ መደምደም ይቻላል። ሰውን መግደል ለእውነተኛ ክርስቲያኖች እንደክርስናትያናዊ ተአምር አይቆጠርም። ድንግል ማርያምም ሰው የገደለውን ሰው ቅዱስ ትለዋለች ብለን አናምንም። አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ግን ቅዱስ ተብሎ ቤተክርስቲያን ታንጾለት፤ ስም አጠራሩ ጳጉሜን 3 ቀን ይከበራል።
ለ/ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ጅግራ ናት ብለው ይከራከራሉ እንዲሉ አምልኮ ስዕልን ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ የኦሪቱን የሚናተፍ አውራ ዶሮ አስመስሎ ሙሴ ሁለቱን ኪሩብ እንዲቀረጽ የተነገረውን ቃል ሁሉም ኦርቶዶክሳዊያን መምህራን ሳይጠቅሷት እንደማያልፏት ሁሉ አባም ያቺኑ ጭምብል ብቅ አድርገዋታል። ሙሴ አስመስለህ ቅረጽ የተባለው ለምንድነው? አስመስሎ መቅረጽን የታዘዘው ሙሴ ብቻ ነው ወይስ ሕዝቡ ሁሉ? አስመስሎ የተቀረጸው ምስል የሚቀመጠው በየሰዉ ቤት ወይስ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ብቻ? አስመስሎ የሚቀረጸው ምስል ዓይነት ኪሩብ ወይስ የሰው ምስል? በቁጥርስ ስንት? አጠቃላይ የብሉይ ኪዳን ሕግ ለም? እንዴት? ለማንና መቼ?  የሚለውን አመክንዮአዊ ሕግ ባለማየት የራስን የልብ መሻት ከልብ ለማድረስ መጠቃቀሱ ተገቢ አይደለም እንልዎታለን። በአዲስ ኪዳን ስለምስል የተነገረን ሳይኖር እናድርግ ብንል እንኳን የሙሴ የቅድስተቅዱሳን ኪሩብ ሳይሆን ልባችን ያፈለቀውንና በጭብጥ አልባ ምትሀት(illusion) የምንስላቸውና የምንቀርጻቸውን ሁሉ በህዝበ እስራኤል ዘንድ እንደተደረገ አድርጎ መቁጠር ዋሾ ቀጣፊ ያሰኛል።
     ሙሴ እንዳደረገው እናድርግ ብንል እንኳን  ሙሴ በሚናተፍ አውራ ዶሮ ዓይነት የቀረጸው ኪሩብ የተቀመጠው በመንበሩ ላይ በቅድስተ ቅዱሳን እንጂ በሕዝበ አስራኤል ድንኳን ሁሉ አይደለም። አንድም ቦታ ሕዝቡ የሙሴን ኪሩብ ምስል ሰርቶ በየቤቱ አስቀመጠ የሚል ጽህፉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም። ስለዚህ ሙሴን እንደምሳሌ ማቅረብዎ ከጠላት የተገኘ ምክር እንጂ የመንፈስ ቅዱስ አይደለም። ለሀገር ለመንደሩ፤ለደጅ ለሰፈሩ በመፍቀድ ምንጭና ባለቤት የሌላቸውን ሰዓሊ፤ ጠራቢ ያልሕግ የሰውን ልብ ሊያማልል፤ ዋጋ ገበያ እንዲያወጣለት የሚያጓጓ አድርጎ የሳለውን ሁሉ ሰው እየገዛ እንዲያመልክ እንዲሰግድ ማስተማር የጤንነት አይደለም። ሙሴም ይህንን አላደረገም፤ አላስተማረምም። የስዕልና የምስል አምልኮ መቼ እንደተጀመረ? ማን እንደጀመረ? ሊቃውንቱን ስንት እንዳከራከረ ተጽፎ ይገኛል። ወደኢትዮጵያም ቤተክርስቲያን መቼ እንደገባ ይታወቃል።
        ስዕል መሳልና ለስዕል መስገድ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ስለዚህ የዛሬዎቹ ሰዎች ስለምስል ሙሴን አግዘን ብለው ኪሩብን ከመጥቀሳቸው በፊት ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ምስልና ስዕል በስግደት የማይታወቅበት ጊዜ ነበር። በዚህ ጉዳይ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። የሚገርመው ደግሞ ስዕልና ምስል በሙሴ ተፈቅዷል ባዮች ህዝብ እንዲሳሳት ማድረጋቸውን አለማወቃቸው የሚያሳየው በዛሬዋ ቤተክርስቲያን መቅደስ ውስጥ የሚናተፉ አውራ ዶሮ የሚመስሉ ሁለቱ የሙሴ ኪሩብ አለመኖራቸው ነው። ምነው የሙሴን የኪሩብ ምስል ከቤተመቅደሱ አስወገዳችሁት? ሙሴን እንደአጋዥ ምክንያት ስታቀርቡ ሙሴ ያደረገውን መተዋችሁ ለምነው? ወይስ ሙሴ አሻሽሉት የሚል ሕግ ትቶላችሁ ነበር?
      ለህዝቡ በምክንያትነት ኪሩቦቹን ስትጠቅሱ እናንተ የሱን አርአያና ምሳሌ ተከትላችሁ ቤተመቅደሱ ውስጥ እንደሚናተፍ አውራ ዶሮ ግራና ቀኝ አለማስቀመጣችሁ የናንተ ሥራ ከሙሴ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ምስክር ነው። ስዕልም ይሁን ምስል ለታሪክ አስረጂ፤ ለመረጃ፤ ለትምህርት አስረጂና ጠቃሚ ሊሆን ከሚችል በላይ በየቤታችን ወይም በየመቅደሱ እጣን እንድናጥን፤ እንድንሰግድ፤ ከፊት ለፊታችን አስቀምጠን እንድንጸልይባቸው አንድም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት የለንም። እግዚአብሔር የሚገለጥበትን መንገድ ለሙሴ በብሉይ ኪዳን ተናግሯል። በአዲስ ኪዳንም በጾም፤ በጸሎት፤ በምጽዋትና በክርስቲያናዊ ምግባር ከተጋን የእግዚአብሔርን መልስ ለማግኘት፤ መልዕክት ለመቀበል፤ የሚገለጥበት መንገድ ያለራሱ ማንም አያውቀውም። እግዚአብሔርን ለመለመን በቅዱስ ሚካኤል ስም ካቶሊካዊው ጉይዶ ሬኒ በ1636 ዓ/ም በልቡ አቅንቶ፤ ችሎታውን ተጠቅሞ የሳለውን ስዕል ከገበያ ገዝቶ በመስገድ ወይም በእጣን ማጠን በዚያ በኩል እግዚአብሔርን መፈለግ እብደት ነው። ጉዶ ሬኒ ዛሬ ላይ ይህንን ቢያይ ኖሮ ምን ይል ይሆን?

                                 (www.artcyclopedia.com)
ሐ/ ሌላው ችግራችሁ የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት አለቦታው በመጠቀም የልባችሁን መሻት ሁሉ በእሱ ቻይነት ካባ ለመሸፈን መሞከር ነው። ተአምር ሁሉ እውነት አይደለም ያልኩበት 3ኛው ነጥቤ ወንጌል፤ አባት አባ ያለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማይ የሚገባ አይደለም እንዳለው ሁሉ ተዓምር ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው ብለን አንቀበልም። በዚህ ዓለም ብዙ መናፍስት ገብተዋልና። ሲሞን መሰርይ የሰማርያ ከተማ ድንቅ ተዓምር ሰሪ ነበር። ግን ተዓምሩ ከእግዚአብሔር መንፈስ አልነበረም። ታዲያ እነዚህ የኛ ሰዎች እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ስለሆነ በኛ ተጽፈው የተገኙትን ተአምራት ሁሉ ድንቅ ስራ እያላችሁ ተቀበሉ ይሉናል። እስኪ አንዱን እንመልከት፤ በገድለ ተ/ ሃይማኖት የተሰራ ተዓምር ነው። አባ ተ/ ሃይማኖት «ባህር አልቅም» የተባለ ሰይጣን በመስቀል ምልክት አማትበው ከያዙት በኋላ አሳምነው፤ አስተምረው፤ አጥምቀው፤ እግዚእ ኀረዮ ብለው ስመ ክርስትና ሰጥተው ካበቁ በኋላ አመነኮሱት የሚል አስነብበበውናል። በእነሱ እንዴት ብሎ መጠየቅ አይቻልም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ነዋ!!! ጥሩ የበደል መሸፈኛ ምክንያት!!
እኛ የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት ብናምንም ከሃሌ ኵሉነቱን አለአግባብ ሲጠቀሙበት ማየት ስለማንፈልግ እንዲህ እንጠይቃቸዋለን።
1/ ሰይጣን ስጋና ደም አለው ወይ? ሲገርዝስ ደም ይፈሰዋል? ግርዛትስ ክርስቲያን ለመሆን መመዘኛ ነው? «በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና» ገላ 5፤6
2/ ሰይጣን ንስሃ ይገባል ወይ? በወንጌልስ ሊያምን ይችላል?
3/ የክርስቶስ ሞትና ትንሳዔ (ሎቱ ስብሐት) ሰይጣናትን ያካትታል ወይ? ሰይጣን ዘላለማዊ ህይወትን ወርሶ ገነት ገባ የሚሉ ሰዎችን አባ፤ ምን ይሏቸዋል?
መቼም በዚህ ላይም ጉድ እንዲያስነብቡን እንጠብቃለን። በበኩሌ የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት አለቦታው መጠቀም በእግዚአብሔር ላይ ከማሾፍ የተለየ አድርጌ አላየውም። መጠያየቅና እውነቱን ከመረዳዳት ባሽገር ጴንጤ፤ተሃድሶ፤ካቶሊክ፤መናፍቅ ወዘተ መባባል የትም አያደርስም። መድኃኒት መልካም ነው፤ መድኃኒትን አለቦታው መጠቀም ግን አደጋ አለው፤ የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት ለልባችን መሻት ሁሉ ማዋላችን ይብቃ። ከእውነቱ እንታረቅ። አስተዋይ ልቦና ይስጠን።