Thursday, September 13, 2012

«ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም!»

«እናንተ ብትገቡበት አያቅታችሁም፤በቤተ ክህነት አጽናኝም አሸባሪም መኖሩን የተናገሩት» አባ  ኤልሳዕ የደቡብ ጎንደር ሊቀ ጳጳስ

«ማኅበረ ቅዱሳን ቅዱስ ሲኖዶስን በዙሪያው ኾኖ የሚጠብቅ፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔዎች በማስፈጸም ረገድም ቋሚ ተጠሪ ነው»
አባ ማትያስ የካናዳ ሊቀ ጳጳስ
«የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዳይናጋ “በወርድም በቁመትም መሥራቱን” አጠናክሮ እንዲቀጥል» አባ ገብርኤል የሃዋሳ ሊቀ ጳጳስ
«ማኅበሩን መደገፍ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል እንደኾነ» ቄስ ኃ/ሥላሴ ዓለማየሁ
ከ40 ሚሊዮን ተከታዮች በላይ ያሏትን ቤተክርስቲያን ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ የገጠሪቱ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ድረስ የመምራትና የማስተዳደር ሥልጣን የተረከቡ ሊቃነ ጳጳሳት ከቤተክርስቲያኒቱ የምእመናን ማኅበር አንዱ አባል ለሆነው ለማኅበረ ቅዱሳን ይህን ያህል «ተቀመጥ በወንበሬ፤ ተናገር በከንፈሬ» ዲስኩር ለማሰማት መድረሳቸው በእርግጥም የቤተክርስቲያኒቱ መሪዎች እግዚአብሔርን ተስፋ ከማድረግ ወርደው፤ መንፈስ ቅዱስን አጋዥና መሪ ከማድረግ ወጥተው፤ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተክርስቲያኒቱ መንፈስ ቅዱስ ስለሆንክ አንተ ምራን ከሚሉበት ደረጃ መድረሳቸው አሳዛኝም ፤አሳፋሪም ነው።
አባ ኤልሳዕ የደቡብ ጎንደር ሊ ቀጳጳስ በሁለቱ ሲኖዶስ መካከል ያለውን ቅራኔ ለመፍታት ማኅበረ ቅዱሳን ቢገባበት ምንም የሚያቅተው እንደሌለ መናገራቸው ሲሰማ በእርግጥ እኒህ አባት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይመራሉ? ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን። የ21 ዓመቱ ክፍፍል ሊያበቃ ያልቻለው ለካ፤ በሥጋዊ መንፈስ እየተመሩና የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ታምነው እንዳልነበረ ከማሳየቱም በላይ ዛሬም ከዚያው ስህተታቸው ሳይላቀቁ ማኅበረ ቅዱሳንን ለማስቀደም መድፈራቸውን ስንመለከት ቤተክርስቲያኒቱ የምትመራው በእነማን እንደሆነ ቁልጭ ብሎ ይታየናል።  «እናንተ ብትገቡበት አያቅታችሁም» ማለታቸው የሚያሳየው እስከዛሬ የዘገውም ማኅበረ ቅዱሳን በእርቁ ውስጥ የማሸማገል ሚናውን ስላልተወጣ ነው ማለታቸው ነው። ሲኖዶሱ ደካማና ለእርቁ መፈጸም አቅም የሌለው በመሆኑ እስካሁን የመዘግየቱ ምክንያት እንዲህ ከተገለጸላቸው ታዲያ ለምን ማኅበረ ቅዱሳንን የሲኖዶሱ የእርቁ ቋሚ ተጠሪ አድርገው በመሾም ቶሎ እንዲፋጠን ያላደረጉ? በዚያውም ደግሞ በሲኖዶስ ጉባዔ ላይ እንደፓርላማ ደንብ በአጋር ድርጅትነት ወንበር የማይሰጡት?
ማኅበረ ቅዱሳን የራሱ የሆነ  የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ ያለው ድርጅት ነው። በዚህ ስውርና ግልጽ የዓላማዎቹ ጉዞ ላይ የሚቀበሉትን እስከነጉድፋቸው ተሸክሞ ለመጓዝ የማይጠየፍ፤ የማይቀበሉትን ደግሞ ምንም እንኳን ንጹሐን ቢሆኑ አራግፎ ለመጣል ጥቂት የማያቅማማ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን እነ አቡነ ኤልሳዕን የመሳሰሉ ታማኞች  «አንተ ስላልገባህ እኛ አቅቶናል» የሚል ድምጸት ያለውን ቃል ቢናገሩለት ማን መሆናቸውን ከሚያሳዩ በስተቀር ስለማኅበረ ቅዱሳን ሁሉን አዋቂነትና የመፍትሄ ቁልፍነት መናገራቸው ማንንም አያሳምንም።
ሌላው አባትም ገና ከወደ ካናዳ ብቅ ከማለታቸው «እስመ አልቦ ነገር ዘይሰዓኖ ለማኅበረ ቅዱሳን» የሚል ትርጉም ያለውን ቃል ሲናገሩ መስማት ለጆሮ ይቀፋል። እሳቸው የተናገሩት ነው ተብሎ በደጀ ሰላም የሠፈረውን ይህን ቃል መዝኑት።
«ማኅበረ ቅዱሳን ቅዱስ ሲኖዶስን በዙሪያው ኾኖ የሚጠብቅ፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔዎች በማስፈጸም ረገድም ቋሚ ተጠሪ ነው»
ማኅበረ ቅዱሳን እውነት የሚታዘዝ ሆኖ ከሆነ ይታዘዛል፤ ይላካል፤ የሲኖዶሱን ትእዛዝ ተግባራዊ ለማድረግ ሲጠሩት አቤት፤ ሲልኩት ወዴት ይላል ብሎ ታዛዥነቱን መግለጽ አንድ ነገር ነው። ነገር ግን ማኅበረ ቅዱሳን፤ ቅዱስ ሲኖዶስን በዙሪያው ኾኖ ይጠብቀዋል ማለት ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ኾኗል ማለት ነው።  ቅዱስ ሲኖዶስ ዙሪያውን ሆኖ የሚጠብቀው መንፈስ ቅዱስ ነው ወይስ ማኅበረ ቅዱሳን? የሲኖዶሱ አባል አባ ማትያስ ግን ሲኖዶሱ ዙሪያውን ሆኖ የሚጠብቀው ማኅበረ ቅዱሳን ነው ሲሉ በግልጽ መናገራቸው ማኅበረ ቅዱሳን ሁሉን ማድረግ እንደሚችል የማወጃቸው ነገር አስገራሚ ነው። ሲኖዶሱ በምን ዓይነት ሰዎች እንደተሞላ ከማሳየት አልፎ ፓትርያርክነቱን ለማግኘት ስለማኅበረ ቅዱሳን ታላቅነት መማል ፤ መገዘት የግድ ሆኗል ማለት ይቻላል።
አባ ማትያስ የሲኖዶሱ ጠባቂ ማኅበረ ቅዱሳንን ከማድረጋቸውም በላይ የሲኖዶሱን ውሳኔዎች ለማስፈጸም የሲኖዶስ ቋሚ ተጠሪ መሆኑንም አያይዘው አውጀውልናል። አሁን እንግዲህ ማኅበረ ቅዱሳን ከማኅበር ጣሪያ በላይ ወጥቷል። ከእንግዲህ ማኅበረ ቅዱሳን ድስት ያላጠለቀ ሲኖዶስ ነው ማለት ነው። በንግግር መሳት ካልቀረ እንደእነ አቡነ ማትያስ ጭልጥ ብሎ መንጎድ እግዚአብሔር ሲኖዶስን ይጠብቃል፤ ሥራውን ሁሉ ያከናውናል እስኪባል ድረስ የሲኖዶስ ጣዖት ሆኖ ማኅበረ ቅዱሳን ይቀጥላል ማለት ነው።
እነሱው በሰጡህ ፈቃድ መሠረት የሲኖዶስ ጠባቂ ማኅበረ ቅዱሳን ሆይ እነዚህን ጳጳሳት ጠብቅ፤ ከፍ ከፍም አድርጋቸው!!! እንላለን።
ሌላው ሊቀ ጳጳስ ደግሞ አባ ገብርኤል ናቸው። በመሠረቱ አባ ገብርኤል ከሲኖዶሱ ይልቅ በማኅበረ ቅዱሳን እንደሚታመኑና እንደሚመኩ ይታወቃል። አባ ገብርኤል ወደ ምድረ አሜሪካ ኰብልለው በመሄድ ኢህአዴግ ይውደም፤ አባ ጳውሎስ ይውረዱ በማለት የፖለቲካ ሰልፍ ሲመሩ እንደነበሩ መረጃዎቻችን ያሳያሉ። ከዚያም በድርድር ይሁን በእርቅ ለጊዜው በማይታወቀው ምክንያት ግሪን ካርዳቸውን ይዘው ወደ አዲስ አበባ በሁለት ዜግነት መግባታቸውን ደግሞ አየን። በእርግጥ ሰው ከስህተቱ ቢታረም አያስገርምም። አባ ገብርኤልን ስንመለከት ከስህተት የሚማሩ አይመስሉም። ዛሬ ደግሞ የዳቦ ስሙን ላወጡለት ማኅበር እንዲህ ሲሉ ይደመጣሉ።
«የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዳይናጋ “በወርድም በቁመትም መሥራቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል»  ማኅበረ ቅዱሳን ያስፈልጋል ይሉናል።ኧረ ለመሆኑ  የቤተክርስቲያኒቱ አንድነት እንዳይናጋ፤ በወርዷም፤ በቁመቷም ለመስራት አልነበረም እንዴ አባ ገብርኤል ጵጵስና የተሾሙት?  በተሰጣቸው ጵጵስና መስራት ካቃታቸው ለሰጠቻቸው ቤተክርስቲያን መመለስ እንጂ ቤተክርስቲያንን እንዲመራ ውክልና ለሌለው ማኅበር ከወርድ እስከቁመቷ እንዲያዝባት እነሱ ደግሞ በተራቸው አሳልፈው እንዴት ይሰጣሉ?
ሲኖዶሱ ከመንበረ ፓትርያርክ አንስቶ እስከ ገጠሪቱ የሳር ክዳን አጥቢያ ድረስ መዋቅሩን የዘረጋው በወርዷም፤ በቁመቷም ለመሥራት አይደለም እንዴ?   አባ ገብርኤል ግን ያቃተቸው ይመስላል። ይልቁንም እኛ ስራውን ሁሉ ለማኅበረ ቅዱሳን እናስረክብና በወርዷም፤ በቁመቷም እሱው ይዘዝባት እያሉ አዋጅ ማስነገር ይዘዋል። አባ ገብርኤልስ የሌላ ሀገር ዜግነት ስላላቸው ነገር ዓለሙ መበላሸቱን ሲያዩ እብስ ብለው ወደ ጥንት የሰልፍ ሀገራቸው አሜሪካ ሊሄዱ ይችላሉ! ማኅበረ ቅዱሳን እንኳን በወርድ በቁመቷ፤ አንዲት ጋት በቤተክርስቲያን ላይ የማዘዝ መብት የለውም የሚሉ የቤተክርስቲያን ልጆችንስ ጅቡ ማኅበር ይዋጣቸው ማለት ነው?
እስከሚገባን ድረስ የቤተክርስቲያኒቱ ራስ እግዚአብሔር ነው። አንዳንድ ጳጳሳት ጠባቂያችን ማኅበረ ቅዱሳን ቢሉም እስከሚገባን ድረስ የሲኖዶሱ ጠባቂ መንፈስ ቅዱስ ነው። እግዚአብሔርን ራስ አድርጎ ሲኖዶሱ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና መገለጥ ቤተክርስቲያንን በወርድና በቁመቷ ይመራታል እንላለን። ከእነ አባ ገብርኤል የተገኘው አዲስ ግኝት ግን በወርድና በቁመቷ ለመሥራት ሥልጣኑ የማኅበረ ቅዱሳን ሆኗል። አባ ገብርኤል ፓትርያርክነቷ ተወርውራ እኔ ጋር ትደርሳለች ብለው አስበው ይሆን?
አንድ ጊዜ ሥልጣናቸው ተገፎ አቶ ኢያሱ የተባሉ፤ ሌላ ጊዜ ደግመው ኮብልለው የፖለቲካ ሰልፍ ሲመሩ የነበረ፤ በኋላም ተመልሰው የወደዷቸውን ጸረ ኢህአዴጎችን ከአሜሪካ ከድተው ፤ የጠሉትን ኢህአዴግን ወደው፤ የጽዋውን ማኅበር ማኅበረ ቅዱሳንን አነግሳለሁ እያሉ በአደባባይ በማወጅ የተጠመዱና በአንድ ቦታ በአንድ ቃል የማይረጉ አባ፤  እንኳን ፓትርያርክ ሊመረጡ ለእጩነትም ሊቀርቡ ተገቢ አይደለም። መጽሐፍ  «በዲያብሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል» ይላልና። አባ ገብርኤል ለምንም ሹመት የሚበቁ አይደሉም እንላለን። « ሆያ ሆዬ ጉዴ ፤ብሯን ብሯን ይላል ሆዴ» እንደሚሉት የሆያ ሆዬ ጫወታ የእሳቸውም ሆድ ቁንጮዋን መጨበጥ ስለሆነ ሆዳቸውን እየቆረጠ እንዳይቸገሩ ቁርጣቸውን ማሳወቅ ተገቢ ነው።

Tuesday, September 11, 2012

በአዲሱ ዓመት አዲስ ሰው እንሁን!


ለነፍሳችን እረፍትን የሰጠን እግዚአብሔር የታመነ ነው። ይሁን እንጂ ይህንን የነፍስ እረፍት ባለማግኘታችን በረከትና የኃጢአት ሥርየት ፍለጋ ከቦታ ቦታ የምንዞር ኢትዮጵያውያን ስፍር ቁጥር የለንም። ዘመናቱን እያፈራረቀ መግቦቱን ያላቋረጠ እግዚአብሔር ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያለውን እነሆ ይመግባል። ነገር ግን ሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን የእለት እንጀራችንን ከእርዳታ ለጋሽ ሀገራት ምጽዋት በመጠበቅ የወፍ ጫጩት ከመሰልን ዓመታት አለፈን። ገሚሶቻችንም ምጽዋቱ ሲቀንስ፤ እድሜና ሆዳችን በማደጉ ረሃብና ጠኔ ከሚገለን የበረሃው ሃሩር ያቅልጠን፤ የባሕሩ ዓሳ ይብላን እያልን ዳቦ ፍለጋ መንጎዳችን ቀጥሏል።
እንግዲህ በነፍሳችን በረከት፤ ቃል ኪዳን፤ ሥርየት፤ ምሕረት፤ እረፍትና መድኃኒት መፈለግ ከጀመርን፤ ለሥጋችንም ዳቦ፤ ለእርዛታችን እራፊ መሻታችን ማብቂያ አለማግኘቱ የሚጠቁመን ነገር በእኛ በቃል ተቀባዮቹና በቃል ሰጪው በእግዚአብሔር መሃከል የሆነ ችግር አለ ማለት ይቻላል። እግዚአብሔር ለነፍስ እረፍትን ለሥጋ መግቦቱን ስለመስጠቱ ከተማመንን ከዚህ ስጦታ የኛው ድርሻ የጎደለው ለምንድነው? ብለን መጠየቁ ተገቢ ነው።
መጽሐፍ እንደሚለው በእርሱ የሚታመኑ ሁሉ ሕያው ቃሉን እየታመኑ ይህንን ለማለት ይደፍራሉ። «ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርገዋለች፥ ረዳታችንና መጠጊያችን እርሱ ነውና» መዝ 3320
ይሁን እንጂ ለነፍስ እረፍት የሚሰጠው እግዚአብሔር ያጎደለው ነገር ያለ ይመስል ኢትዮጵያውያን የነፍስ እረፍት ፍለጋ ሀገሪቱን ስናስስ እድሜአችንን ኖረናል። ዛሬም ፍለጋችን እነሆ አላቋረጠም። መሻታችንን ከምንፈልግበት ቦታ ደርሰን በማግኘት የረካነው ስንቶቻችን እንሆን? ብዙዎች ግን ዛሬም ተስፋው እንደሞላ ሰው ረክቶ ከመቀመጥ ይልቅ የተሻለ መተማመኛና እረፍት ፍለጋ ላይ ናቸው። በረከት፤ ምሕረት፤ ሥርየት፤ ቃል ኪዳን፤ አስተማማኝ ቃል ፍለጋ፤ ፍለጋ.........ግን መገኛው የት ይሆን?
እስካሁን አስተማማኝ ነገር ላለመገኘቱ እለታዊ ሕይወታችን ግን ይመሰክርብናል። እኛም አላረፍንም፤ ሀገራችንም ከችግር አላረፈችም።
መዝሙረኛው እንዳለው «ነፍሳችን በመሬት ላይ ተጐሳቍላለችና፥ ሆዳችንም ወደ ምድር ተጣብቃለች» መዝ 4425 እንዳለው እየሆነብን መሆኑ እርግጥ ነው።
ሚሊዮኖች በሀገራቸው ባለው ነገር ተስፋ በመቁረጣቸው ተሰደዋል። ወለተ ማርያም ከድጃ፤ አመተ ማርያም ፋጡማ ወዘተ እየተባሉ የማያውቁትን እምነት እምነታቸው አድርገው ለባርነትና ከሰው በታች ለሆነ ኑሮ እራሳቸውን በመሸጥ የሚኖሩትን ብዙ ሺዎችን ስናይ እግዚአብሔር ተስፋችን ባርኮታል ማለት እጅግ ይከብዳል። እኛ እንደምንለው፤ እውነት ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር ከሆነች የተሰጠው አጸፋ እንዲህ ዓይነት ፈተና ሊሆን ይገባው ነበር? ወይስ እግዚአብሔር ስለሚወደን እኛን ለመከራ አሳልፎ በመስጠት ሊፈትነን ስለፈለገ ይሆን?
ይህንን ቃል ለመቀበል ያስቸግራል። እየተራበ፤ ያስራበኝ እግዚአብሔር ስለሚወደኝ ነው የሚል ሰው እግዚአብሔርን አያውቀውም፤ አለበለዚያም እግዚአብሔር ቃሉን ለሚጠብቁ አጠግባችኋለሁ ካለው እኛን የሚበድልበትን ምክንያት ሊያሳየን የግድ ይሆናል።
እውነታው ግን እግዚአብሔር ቃሉን እንደሰው አይለዋውጥምና ለሚታዘዙት በረከትን፤ ለሚቃወሙት ቁጣን እንደሚሰድ ስለምናውቅ ራሳቸውን እየደለሉና ሕጉን ሳይጠብቁ እኛ ሀገረ እግዚአብሔር ነን የሚሉቱን አስመሳዮች አንቀበላቸውም።
ረሃብ፤ እርዛት፤ ህመምና ሞት ለሰው ልጆች ከእግዚአብሔር የተሰጡ ገጸ በረከቶች አይደሉም። ሰው ራሱ በራሱ ላይ ወዶና ፈቅዶ ያመጣቸውና የሚያመጣቸው ጉድለቶች ስለመሆናቸው ቃሉ ይናገራልና።
«ለስሜ ክብር ትሰጡ ዘንድ ባትሰሙ፥ በልባችሁም ባታደርጉት፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እርግማን እሰድድባችኋለሁ፥ በረከታችሁንም እረግማታለሁ አሁንም በልባችሁ አላደረጋችሁትምና እኔ ረግሜአታለሁ» ሚል 22


Saturday, September 8, 2012

እውነቱ የቱ ነው?

መነሻ ሃሳብ «ገመና ዘ81ዱ» መጽሐፍ

ርእስ፤  እውነቱ የቱ ነው?
    
 ሀተታ፤
በኦርቶዶክሳውያን  ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከታች ጀምሮ እስከላይኛው እርከን ድረስ ያለው ሰው ስህተት ይኖርብናል ወይም ልንሳሳት እንችላለን ብሎ የሚያስብ ማግኘት አዳጋች ነው። በክርስቶስ ደም የተመሰረተችው ቤተክርስቲያን ፍጽምትና ንጽሕት መሆኗን በመቀበል እንዳለ መሪውና ተመሪው ራሱንም በዚያው ዓይን እያየ እኛ ፍጹማንና ንጹሐን ነን በሚል ከለላ ስር ራሱን በማስጠለል፤ ስህተትን አምኖ ለመቀበል አይፈልግም። የስህተት አስተምህሮ አለ፤ በእግዚአብሔር ቃል ሲመረመር አደጋው የከፋ ነው፤ የክፉ መንፈስ አሰራር ወደማወቅ እንዳንደርስ ቃሉን በክሏል ሲባል የሚሰጠው ምላሽ፤ 2000 ሺህ ዘመን የኖረችን ቤተክርስቲያን ዛሬ የተነሱ አፍቃሬ ተሐድሶ መናፍቃን ሊያርሟትና ሊበርዟት ይፈልጋሉ በማለት ታፔላ መለጠፍ ይቀናቸዋል። የስም ታፔላ መለጠፍ ብቻ ሳይሆን ሽልማት የሚያሰጥ ቢሆን ኖሮ የተመረጡና ለመስማት የሚዘገንኑ ስድቦችና ዛቻዎች ይዥጎደጎዳሉ።
በእርግጥ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ፍጽምትና ንጽሕት መሆኗ አያጠራጥርም። ምክንያቱም የመሠረታት በዓለቱ ላይ በፈሰሰው ደሙ ነውና። ይህ እውነት ቢሆንም በክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ አባል ሆነው የሚኖሩት የአዳም ልጆች መሆናቸውንም በመዘንጋት የቤተክርስቲያኗን መንፈስና ባህርይ እንዳለ ወደሰዋዊ ማንነት በመውሰድ እኛ ፍጹማንና ንጹሐን ነን በማለት ከስህተት አልባነት የቤተክርስቲያን ማንነት ጋር ራስን መቁጠር ትኩረት የሚያሻው መሆኑን ልናሰምርበት ይገባል። በእርግጥም የተጠራነው ፍጽምት በሆነች ቤተክርስቲያን ውስጥ ፍጹማን እንድንሆን ነው። ነገር ግን ሰው ከተፈጠረበት ማንነት የተነሳ በፍጽምቷ ቤተክርስቲያን ውስጥ ፍጹም ሆኖ መኖር የሚችል ማንነት የለውም።
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑን የሚችሉት የገላትያ ሰዎች ማንነት ነው። የገላትያ ሰዎች በክርስቶስ አዳኝነት አምነው ወደ ሕይወት መንገድ የተመለሱ ሕዝቦች ነበሩ። ፍጽምትና ንጽሕት በሆነች የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ተጨምረው የቆዩ ሆነው ሳለ ሰብአዊ ማንነታቸው አሸንፎአቸው ወደስህተት መንገድ በመግባታቸው በሐዋርያው ጳውሎስ እጅግ የተወቀሱ ሕዝቦች ሆነዋል።
«የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?» ገላ 3፤1
ክርስቶስ ኢየሱስ በፊታቸው የተሰቀለ ሆኖ በእምነት ይታያቸው የነበሩት ሕዝቦች ከዚያ የቅድስና ማንነት ወርደውና እውነትን በመተው፤ የጠላት አዚም የወረደባቸው  ሕዝቦች እስከመሆን መድረሳቸውን ሲናገር እናያለን። ሥራቸውን ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የጀመሩ ሆነው ሳለ ቁልቁል ተመልሰው የሥጋን ሃሳብና እውቀት ወደማመን መመለሳቸው በእርግጥም አሳዛኝ የሰው ልጆች ማንነት ማሳያዎች እንደሆኑ የሚያስገነዝበን  ነገር ነው።
«እንዲህን የማታስተውሉ ናችሁ? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትፈጽማላችሁን?» ገላ 3፤3 ይላል።

 እንግዲህ ክርስቲያኖች ፍጽምትና ንጽሕት በሆነች ቤተክርስቲያን ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እምነታቸውን ሊጀምሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይህንን ፍጽምና ወደአለማወቅ መመለስም ሊታይባቸው ይችላል። ምን ጊዜም ቢሆን የስህተት መንፈስ አገልግሎቱ፤ የእውነቱን መንፈስ ከሰው ልቡና ላይ በመውሰድ ወደስህተት መንገድ መምራት ስለሆነ በቅድስት ቤተክርስቲያን ውስጥ ባሉ ሰዎች ውስጥ የስህተት አስተምህሮ እንደሚገባ እናረጋግጣለን።
ብዙዎች የአብያተ ክርስቲያናት አባላት በክርስቶስ ፍቅር ላይ ጸንተው ከመቆም ይልቅ ወደ ምድራውያንና ሰማያውያን ፍጥረቶች ፍቅራቸውን ስለለወጡ የሕይወት መንገድን ስተው መገኘታቸው እውነት ነው።
ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ልጁን ወደ ተሰሎንቄ የላከበት ዋናው ምክንያትም ተሰሎንቄዎች  ከእምነት ጽናታቸው ወደኋላ እንዳይመለሱ በመንፈስ ያበረታታቸው ዘንድ ነበር። ምክንያቱም ፈታኝ የምንጊዜም አዚሙን የሚያፈሰው  የአማኞችን ልቡና በማደንዘዝ ወደ አልሆነ አቅጣጫ መመለስ  ሥራው ስለሆነ ከዚህ ፈታኝ ይጠበቁ ዘንድ እንደላከላቸው ቅዱሱ ወንጌል ይነግረናል።
«ስለዚህ እኔ ደግሞ ወደ ፊት እታገሥ ዘንድ ባልተቻለኝ ጊዜ። ፈታኝ ምናልባት ፈትኖአቸዋል ድካማችንም ከንቱ ሆኖአል ብዬ እምነታችሁን ለማወቅ ላክሁ» 1ኛ ተሰ 3፤5
ከከሳቴ ብርሃን አባ ሰላማ ወዲህ ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል ተብለው የሚጠሩ መነኮሳት በዋሻና በፍርክታ ገዳም መስርተው ሰው ሁሉ ወደዚያው እንዲከትም ከማድረግ ውጪ ሀገር ላገር ዞረው፤ እንደሐዋርያቱ ወንጌል ላልበራለት ሕዝብ ወንጌልን ስለማስተማራቸው የሚታወቅ ነገር የለም። ወንጌል ለሕዝቡ የበራ ቢሆንማ ኖሮ እስከዛሬ በዛፍ ስር ቡና የሚደፉ፤ ደም የሚያፈሱ፤ቅቤ የሚቀቡ፤በጨሌ፤ ቆሌና የቤት ጣጣ አምልኮ ሰርጾባቸው የሚኖሩ ባልኖሩ ነበር።  እምነት አለን፤ አውቀናል የሚሉት እንኳን እስከፕሮቴስታንት መምጣት ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን አያውቁትም። ደረትን ነፍቶ ኦርቶዶክሳዊ ስለመሆን አረጋጋጭ ከሆኑት ከድርሳናት ውጪ መጽሐፍ ቅዱስን ይዞ መገኘት በራሱ ኮትልኳል ወይም ጰንጥጧል የሚያሰኝ በመሆኑ ይዞ መገኘት ያሳፍር ነበር። ይህ በእድሜአችን ያየነው እውነት ነው። አንዳንዶች «ሳያዩ የሚያምኑ ብጹአን ናቸው» የሚለውን ቃል ጠምዝዘው ራሳቸው ለመሸንገያነት በመጠቀም አንድም ሐዋርያ ሳይመጣ ያመንን ስለሆንን ቃሉ እኛን ኢትዮጵያውያንን ያመለከታል ለማለት ቢፈልጉም የሐዋርያ ወይም የሰባኪ አለመምጣት እንደ ጉዳት እንጂ እንደጠቃሚ ነገር መቁጠር አለማወቃችንን የሚያሳይ ነው። መጽሐፍ የሚለን እውነት ይህንን ነው።
«እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?» ሮሜ 10፤14
እንደዚሁ ሁሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እውነተኛ ወንጌል በማስተማርና ሕዝቡን ከክርስቶስ ወንጌል ጋር በማስማማት እንዲኖር ለማድረግ እስከሞት ድረስ ከታገለው ከአባ እስጢፋኖስ በቀር ግብጻውያንም ጳጳሳት የሰሩት የወንጌል አገልግሎት አልነበረም። ወንጌል ሥራው በግጻዌ ምድቡ በጥቅስ ደረጃ በየሥርዓተ ቅዳሴው ላይ ተመርጦ ከሚነበብ ውጪ ከተአምረ ማርያምና ከድርሳናት እኩል መድረክ አልነበረውም። አቡነ ቴዎፍሎስ የወንጌልን አስፈላጊነት በማመን አዳሪ ት/ቤቶችን በማጠናከር፤ ሰንበት ት/ቤቶች በማቋቋምና በቃለ ዓዋዲ እንዲደነገግ እስኪያደርጉ ድረስ አብያተ ክርስቲያናት በግእዝ ቀድሰው፤ በግእዝ አንብበው፤ ለዓለመ ዓለም ካሉ በኋላ እግዚኦ መኀረነ ክርስቶስ እንበል 12 ጊዜ ብለው ጣት ከማስቆጠር ባለፈ ህዝቡ ወንጌልን እንደማያውቅ ጠንቅቀን እናውቃለን።
 እንዲያውም ወንጌል እቃ ግምጃ ቤት ገብቶ የሸረሪት፤ የአቧራና የአይጥ ቀለብ ሲሆን በአንጻሩ ልፋፈ ጽድቅ በየአንገት ላይ የሚንጠለጠል ክቡር መጽሐፍ ሆኖ ለዘመናት ኖሯል። ዛሬም እስከመቃብር ድረስ አብሮ የሚወርድ፤ ክቡር አዳኝ መጽሐፍ ሆኖ መቆጠሩን አላቋረጠም። የዲቁናም ይሁን የቅስና ማእርግ የሚሰጠው ሥርዓተ ቅዳሴውንና ኩሳኩሱን ከመልክዓ መልክዑ ጋር መሸምደዱ እንጂ ወንጌልን ተንትኖ ሕይወት የሚገኝበትን ቃል ማስተማር ስለሚችል አይደለም።  
ከዚህ በታች የምናቀርባቸው መጽሐፍ ቅዱሳችን በምንለው መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ ስህተቶች፤ ነገር ግን እውነት እንደሆኑ ቆጥረን የምንከራከርላቸው ሲሆኑ ችግሩን እንደችግር ያለመቁጠራችን ዋና ምክንያት ከላይ በሀተታ እንደዘረዘርነው አንድም እኛ ፍጽምትና ንጽሕት በሆነች ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለን ስህተት አልባዎች ነን ከማለት የመነጨ ሰውኛ ማንነትን ካለመቀበል ችግር፤ አንድም- ክርስቶስ ከፊታቸው ተስሎ የነበሩት ገላትያውያን እንደሆኑት የሆነ አዚም አደንዝዞን እውነትን ለመቀበል ባለመፈለግ፤ አለያም ሳያዩ የሚያምኑ……በሚለው የሽንገላ ቃላት ተሸውደን እውነተኛውን የክርስቶስ ወንጌል የሚሰብክ እንዲኖረን ባለመፈለግ ራሳችንን ስናሞኝ በመኖራችን ይሆናል።

 የስህተት ትምህርት አስረጂዎች፤
ብዙውን ጊዜ «ከእውነተኛ የወንጌል አስተማሪዎች እጦት የተነሳ» /ከአስተማሪዎች እጦት የተነሳ አላልኩም/ ሕዝቡ እስካሁን ለወንጌል ቃል አዲስ በመሆኑ አሳማኝ መልስ መስጠት ስለማይችል እንደችግር መፍቻ መፍትሄ የሚጠቀምበት መንገድ በመሳደብ፤በማሳደድ፤በማሽሟጧጥ፤ በመደባደብ ብሎም በመግደል  ልዩ ለሆነ ሃሳብ ሁሉ ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል። አሁንም ይህ አድራጎት አላቋረጠም። ከዚህ በታች ለሚቀርቡ አስረጂዎች ምላሽ መስጠት የሚችል አንድም ሰው እንደሌለ እርግጠኞች ስንሆን የሚሳደብ ወይም የሚያንቋሽሽ ክርስቲያኖችን ግን በሺህዎች እንጠብቃለን። 
  • 1/ ስለታቦተ ጽዮን ትረካ፤
  • 1,1  ስለታቦተ ጽዮን አመጣጥ ታሪክ የሚናገረውን  «ክብረ ነገሥት» የተባለውን መጽሐፍ ማኅበረ ቅዱሳን ውሸታም ብሎታል።
ማኅበረ ቅዱሳን ትውፊትንና ባህልን፤ ልምድንና አምልኰትን ለይቶ የማያውቅ የጅምላ እምነት አራማጅ መሆኑ ሲታወቅ፤ ራሱ እገዛበታለሁ የሚለውን ትውፊት ሲሽር እንጂ ሌሎች ሲሽሩ ዓይኑ ደም የሚለብስ አስቸጋሪ ድርጅት ነው። እንደሚታወቀው ግራሃም ሐንኰክ የተባለ እንግሊዛዊ ምሁር /The sign of the seal/ በሚል ርእስ እ/ኤ/አ በ1992 ዓ/ም ያሳተመውን መጽሐፍ ይህ የትውፊት ጠበቃ ነኝ የሚለው የጅምላ እምነት አራማጅ ማኅበር፤ /ታቦተ ጽዮንን ፍለጋ/ በሚል ርእስ በጌታቸው ተስፋዬ አስተርጉሞ ያሳተመው መጽሐፍ  እንደሚተርከው ታቦተ ጽዮን በንጉሥ ሰሎሞን ዘመን በልጁ ኢትዮጵያዊ ንጉሥ በቀዳማዊ ምኒልክ እጅ ሳይሆን ወደኢትዮጵያ የመጣው በግብጽ ኤሌፋንታይን አቋርጦ ከዓመታት ቆይታ በኋላ የዓባይን ሸለቆ ተከትሎ ቀስ በቀስ በጣና አድርጎ ነው የገባው በማለት ይናገራል። ስለዚህ «ክብረ ነገሥት» ስለታቦተ ጽዮን አመጣጥ የሚተርከው የእነ ቀዳማዊ ምኒልክ ታሪክ በውሸታምነቱ ተመዝግቧል ማለት ነው። ማኅበረ ቅዱሳን የታቦተ ጽዮንን አመጣጥ በግራሃም ሃንኰክ አተራረክ መሰረት የሚያምን ከሆነ ክብረ ነገሥትን ትረካ ዋጋ ቢስ ያደርገዋል። የሚገርመው አንድም የሊቃውንት ጉባዔ ይሁን የጳጳሳቱ ዓለም የክብረ ነገሥትን ትረካ የሚቃወመውን የማኅበረ ቅዱሳን እትም መጽሐፍ ሲያወግዝ ወይም ታሪካችንን አፋልሷል ሲል አልተሰማም። ስለዚህ የክብረ ነገሥትን ውሸታምነት አጽድቆታል ወይም የማኅበረ ቅዱሳንን የትርጉም አተራረክ ለመከላከል አቅም አጥቷል። ከዚህ አንጻር ስለታቦተ ጽዮን አመጣጥ የሚናገር የተለያየ ሃሳብ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ስላለ እውነተኛው የትኛው እንደሆነ ለጊዜው አይታወቅም ማለት ነው። 

  • 1,2/ ታቦተ ጽዮን ወደኢትዮጵያ አልመጣችም በማለት መጽሐፈ እዝራ ካልዕ ይናገራል።
ከላይ እንዳስቀመጥነው ማኅበረ ቅዱሳን ክብረ ነገሥትን ውሸታም በማለት በግብጽ በረሃ አድርጋ ነው ታቦተ ጽዮን የመጣችው የሚለውን የግራሃም ሃንኰክን መጽሐፍ ለተከታዮቹ ሲያከፋፍል የምንረዳው ሁለት የተለያየ የአመጣጥ ትረካ መኖሩን ነበር። ይሁን እንጂ ሰማንያ አሀዱ በተባለው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመጽሐፈ እዝራ ካልዕ ምዕራፍ 1 ቁጥር 54 ላይ እንዲህ በማለት ከላይ የቀረቡትን ሃሳቦች ሁሉ ውድቅ በማድረግ ታቦተ ጽዮን ወደኢትዮጵያ እንደመጣች ሳይሆን ወደባቢሎን መሄዷን በግልጽ ይናገራል።
«እግዚአብሔርን የሚያገለግሉበትን ንዋየ ቅድሳቱንና ጥቃቅኑንና ታላላቁን ዕቃ ሁሉ የእግዚአብሔር ማደሪያ ታቦትንም፤ ከቤተመንግሥት ዕቃ ቤት ያለውን ሣጥኑንም ሁሉ ማርከው ወደ ባቢሎን ወሰዱ» እዝራ ካልዕ 1፤54
ናቡከደነጾር ከ634-562 ዓ/ዓ የነበረ የባቢሎን ንጉሥ ሲሆን እርስ በእርሳቸው ያልተስማሙት የክብረ ነገሥትና የታቦተ ጽዮንን ፍለጋ መጻሕፍት ትረካ ውድቅ በማድረግ ወደ ባቢሎን ማርኰ ስለመውሰዱ ሰማንያ ወአሀዱ የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ አፖክሪፋ መናገሩ ነገሩን ሁሉ መያዣ መጨበጪያ የሌለው አድርጎታል። አሁን እንግዲህ ሊነሳ የተገባው ጥያቄ፤
  • ·         ክብረ ነገሥት የተባለው መጽሐፍ ነው ትክክል?
  • ·         ታቦተ ጽዮንን ፍለጋ የተባለው መጽሐፍ ትረካ ነው ትክክል? ወይስ
  • ·         የለም! ሁለቱም የሚሉት ትክክል አይደለም፤ ታቦቱ ወደባቢሎን በምርኰ ተወስዷል የሚለው የመጽሐፈ እዝራ ካልዕ ቃል ነው ትክክል?