Tuesday, March 13, 2012

የሚያረክሰው የትኛው ነው?

አሜሪካ በሚገኘው የማኅበረ ቅዱሳን ንዑስ ክፍል፣ በነዲ/ን አሐዱ አስረስ፣ በዲ/ን ዳንኤል ክብረት፣ በነቀሲስ በላቸው፣ በነሊቀ ኅሩያን ከፈለኝ ወዘተ ሰዎች የሚመራ ጉባዔ አካሂዶ ነበር። ጉባዔው በዋናነት የሚያጠነጥነው ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አውግዛቸዋለች በሚሏቸው ተሃድሶአውያን ላይ እና በአሜሪካ ስደተኛው ሲኖዶስ የሚባለው አካል የምንፍቅና ደረጃው ምን እንደሚመስል ለማጋለጥ የተካሄደ ነበር።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ አባ ወ/ትንሣዔ የተባሉትን አባት መናፍቅና ተሀድሶ ናቸው የሚል ዘመቻም አብሮ ተሰርቷል። ለተሃድሶነታቸው በምክንያትነት የቀረበው አባ ወ/ትንሳዔ በአዲስ ኪዳን ዘመን ሰውን የሚያረክሰው አሳማ መብላት፤ አህያ መብላት ወይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የልምድ አስተምህሮ ሸኮናው ድፍን ወይም የማያመሰኳ ርኩስ ነው የሚለው ሳይሆን «ከሰው አፍ የሚወጣ ነው የሚያረክሰው» ብለው ስላስተማሩ ተሃድሶና መናፍቅ  ተብለው ተፈርጀዋል።
እስኪ ይህንን ቪዲዮ ያዳምጡ።  በጥራት ለማዳመጥ ድምጹን ይቀንሱ!




እነዚህ ሰዎች የጠሉትን ለመምታት እንዲህ ዓይነት የተቀናጀ ዘመቻ ሲሰሩ ለሚያቀርቧቸው ዘመቻዎች አስረጂ የሚሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጭብጣቸው ምንድነው? ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን። በዲያቆን በጋሻው ላይ ዘመቻ የሰሩ ሰዎች ሁሉ ማኅበሩ ከጀርባ ሆኖ ግፋ በለው! ውረድ በለው! በሚል ጦረኝነት ቢነዳቸውም ከወረዱበት ዘብጥያ ሊታደጋቸው ግን አልቻለም። እንደዚሁ ሁሉ አባ ወ/ትንሳዔ መናፍቅና ተሃድሶ ናቸው ብሎ በጉባዔ ዘመቻ በመስራትና ቪዲዮ በማጠናቀር «በዩቱብ» የለቀቀባቸው እውን አሳማ ወይም አህያ የሚበላ ቢኖር የሚኮነን ሆኖ ነው? ረክሷል ማለት ነው?

እውነታው ግን እነዚህ እንስሳት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ የማይበሉት በአዲስ ኪዳን ርኩስ ናቸው የሚል ትምህርት ስላለ ያንን ለመፈጸም ሳይሆን የኦሪትን ሥርዓት ስትከተል የቆየችና በኦሪቱ የተከለከሉትን እንስሳት ሳትበላ የቆየች ስለሆነ ወደአዲሱ ኪዳን ስትገባ የቀደመው ሥርዓቷን ይዛ በመቀጠሏ ብቻ ነው።
ያልተለመደውን ነገር እንዲለመድ ለማድረግ ማስተማር የወንጌል ወግ አይደለምና ቤተክርስቲያኗ ምእመናኗን እንዲለማመድ አለማድረጓ የሚያስነቅፋት አይደለም። ደግሞም እየበሉ የቆዩ ወይም መብላት የፈለጉትን ትረክሳላችሁ ወይም ትኰነናላችሁ አትልም።
ጽድቅ በመብላት ወይም ባለመብላት አይደለምና።
የሸዋ ሀ/ስብከት ሊቀጳጳስ የነበሩት ሊቁ አቡነ ጎርጐርዮስ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ገጽ 180 እና 181 ላይ ከጻፉት ጽሁፍ ይህንን ለአስረጂነት አቅርበናል።


እናስ ታዲያ! አባ ወ/ትንሳዔ  አሳማ ወይም ሌላ እንስሳ የሚበላ አይረክስም፤ የሚያረክሰው ይህንን የሚባለውን ሰው አሳማ ውሻ ብለን ስንሰድበው ነው ማለታቸውን ነቅፎ ተሃድሶና መናፍቅ ናቸው የሚለው የአሜሪካው የማኅበረ ቅዱሳን ክንፍ በምን እውቀት ላይ ተመስርቶ ነው? ተሃድሶ ናቸው ተብለው ከታወጀባቸው ጋር አባ ወ/ትንሳዔ ደባልቀው  እንዲህ ዓይነት የስም ማጥፋት ዘመቻ ለምን? ማነው? ማኅበረ ቅዱሳንን ከእውቀት ባዶ በሆነ  ዘመቻ እንዲሰማራ የላከው? መናፍቁ ማነው? የወንጌል ቃልን የሚቃወም ወይስ የወንጌል ቃልን የሚያስተምር?
ሊቁ አቡነ ጎርጐርዮስ ግን የቆየውን የቤተክርስቲያን ሕግ በማጣቀስ እንዲህ ሲሉ ያስተምሩናል።

 ማኅበረ ቅዱሳኖችና ተባባሪዎቻቸው ነጠላ ከመልበስ፤ ከበሮ ከመደለቅና ገንዘብ ከማግበስበስ በፊት ወንጌል ተማሩ!!
በአንድ በኩል ብጹእ አቡነ ጎርጎሪዎስ አባታችን ናቸው ትላላችሁ፣ በሌላ መልኩ ደግሞ ከእሳቸው የወንጌል ቃል አስተምህሮ በተጻራሪ ትቆማላችሁ። ከቶ እናንተ ምንድናችሁ?
ቻይና ሀገር የማይበላ የእንስሳ ዝርያ የለም። ታዲያ የቻይና ክርስቲያን የሰማይ ፍርዱ በሲኦል ነው ማለት ነው? ያለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ይልቁንም ከማኅበረ ቅዱሳን አባላት በስተቀር በዚህ ዓለም ላይ እግዚአብሔር ለጽድቅ ያኖረው ፍጥረት የለም ማለት ነው?
 ምን ዓይነት ተመጻዳቂ የተረት ኃይል በኢትዮጵያ ላይ ዘመተባት? ዝምታህስ እስከመቼ ይሆን?

Monday, March 12, 2012

አቡነ ገብርኤል "የተሰደደ የለም" ያሉት የሀዋሳ ሕዝብ፣ ታላቅና ደማቅ መንፈሳዊ ጉባዔ አካሄደ

ራሳቸውን ከአቡነ ገብርኤል አስተዳደር የለዩት ምዕመናን አሁንም ከአሳዳጆቻቸው ጋር ተፋጠዋል

በአቡነ ገብርኤል የመልካም አስተዳደር ብልሹነት ተማረውና ተቀጥቅጠው በዱላ ኃይል ከሀዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም፣  ከደብረ ሠላም ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን እና ከደብረ ታቦር ቅዱስ ሩፋኤል ቅጥር ግቢ የተባረሩት ምዕመናን የራሳቸውን ታላቅ መንፈሳዊ ጉባዔ ማካሄዳቸው ዘጋቢዎቻችን አስታወቁ፡፡
 ዘጋቢዎቻችን በሥፍራው ተገኝተው እንዳረጋገጡት እነዚህ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናንና ምዕመናት፣ ልዩ ልዩ ሥልጣነ ክህነት ያላቸው አገልጋዮችና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች አቡነ ገብርኤል ከ"ማኅበረ ቅዱሳን"ና አሥር ከማይሞሉ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎች እና ኃላፊነታቸውን ከዘነጉ ፖሊሶች ጋር በመተባበር ተከታታይና ኢሰብዓዊ ድብደባ፣ እሥራትና እንግልት ስላበዙባቸው ተማረው መውጣታቸው ታውቋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ የተሰደደው ሕዝብ ተበታትኖ ወደየቤቱ ከመግባት ይልቅ እየተሰባሰበ በግለሰቦች መኖሪያ ቅጥር ግቢ ውስጥ ወንጌል በመከታተል ላይ ሲሆን በአደረጃጀት እየጠነከረ በመምጣቱ እነ አቡነ ገብርኤል እንደስጋት እንደሚያዩት ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከዚህም የተነሳ በእነ አቡነ ገብርኤል ወገን ያለው አሳዳጅ ኃይል ግፉአኑን "ተሀድሶዎች" ናቸው፣ "መናፍቃን" ናቸው በማለት፣ ዐውደ ምሕረት ላይ የሐሰት ወሬ በማስተላለፍ ላይ ሲሆን፣ ከዚሁ ጎን ለጎን አሳዳጆቹ ወደ ፍትሕና ፀጥታ አካላት እንዲሁም ወደ ክልል መስተዳድር እና ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ዘወትር እግራቸው እስኪቀጥን ድረስ በመመላለስ እንዲያዙላቸው፣ እንዲታገዱላቸውና እንዲታሠሩላቸው በመወተወት ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Friday, March 9, 2012

የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እንዲከላከሉ ተወሰነባቸው!

 ሊቀ ትጉሃን ተሾመ ኃይለ ማርያም በ"ማኅበረ ቅዱሳን" ሤራ በፖሊስ ተይዘው ወደ ነጌሌ ቦረና ተወሰዱ

በቆሞስ መልአከ ገነት አባ ሙሉጌታ ታዬ የክብረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ ከሸፈ

የካቲት 16 ቀን 2004 ዓ.ም በክብረ መንግሥት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ የሚከበረውን የቅድስት ኪዳነ ምሕረት በዓለ ንግስ በመረበሽ ያስተጓጎሉት ሃያ አምስት የማኅበረ ቅዱሳን አባላትና አፍቃሬ ማኅበረ ቅዱሳን ተከሳሾች ለመጋቢት 19 ቀን 2004 ዓ.ም ቀነ ቀጠሮ ቀርበው እንዲከላከሉ ተበይኖባቸዋል፡፡ ዐቃቤ ሕግ አሥራ ሦስት ምሥክሮችን ያሰማ ሲሆን ክሱን በጽሑፍ፣ በሰውና በምስል ማስረጃ አጠናቅሮ አስረድቷል፡፡ በተጨማሪም ሰባት ምሥክሮች ቃለ መሐላ ከፈጸሙ በኋላ ዐቃቤ ሕጉ በቃኝ ሳይሉ ምክንያቱ በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት ዳኛው አቶ ጉዩ እንዳይመሠክሩ አስቁመዋል ተብሏል፡፡  
በዚህም ሳቢያ ስምንት ቀንደኛ በጥባጮች በዚያው ዕለት 29/6/2004 ዓ.ም በነፃ አሰናብተዋቸዋል ተብሏል፡፡ ከነዚህ ስምንት ቀንደኛ መሪዎች ውስጥ መሪጌታ መዝገቡ ጌታነህ፣ ቄስ መኮንን ጉቴሳ (የአንድ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የታሪክ መምህር)፣ ወ/ሮ ሃይማኖት ጥላሁን፣ ወ/ሮ መቅደስ፣ ዲ/ን እንዳሻው፣ ዲ/ን ብንያም፣ ዮናስና ጌትነት የተባሉት መሆናቸው ታውቋል፡፡ በተለይም የእነዚህ ቀንደኛ በጥባጮች መለቀቅ፣ የከተማውን ኅብረተሰብ፣ የፍትሕና የፀጥታ አካላትን ማስቆጣቱ ተመልክቷል፡፡

Thursday, March 8, 2012

ትንቅንቅ!

 በእውነተኛ ራእይ ላይ የተመሠረተ፣

ርእስ- የመጨረሻው ትንቅንቅ
            ደራሲ- ሪክ ጆይነር
          ተርጓሚ ሰሎሞን አሰፋ
                                                            ናዝሬት፣ 2004 /
                          ክፍል ፩

የሲኦል ኃይላት እየተመሙ ናቸው

አጋንንታዊ ሠራዊቱ በዓይኔ ማየት እስኪሳነኝ ድረስ እጅግ ብዙ ሲሆኑ እያንዳንዳቸውም የተለያዩ ሰንደቅ ዓላማዎችን ተሸክሞ በተሰለፈ ክፍለ ጦር ስር ተከፋፍለው ተሰልፈው ነበር። ትላልቆቹ ክፍለ ጦሮች ትዕቢት፣ራስን ማጽደቅ፣ ስምን ማስጠራት፣ ራስ ወዳድነት፣ በጭፍን መፍረድና ቅናት የሚሉ ሰንደቅ ዓላማዎችን በያዘ ጦር ስር ተሰልፈው ነበር። በዓይኔ ማየት ከምችላቸው ከእነዚህም ሌላ እጅግ በርካታ ሌሎች ክፍለ ጦሮችም ተሰልፈው ነበር። ይሁንና ከገሃነም እየወጣ ከመጣው ከዚህ አስፈሪ መንጋ ፊት በግንባር ቀደምትነት የተሰለፉት ግን እጅግ ኃያላን ይመስሉ ነበር። የዚህ ሠራዊት መሪ ደግሞ የወንድሞች ከሳሽ የሆነው ራሱ ሰይጣን ነበር።
ይህ መንጋ ሠራዊት የታጠቃቸው የጦር መሣሪያዎች በላያቸው ላይ ስሞቻቸው ተጽፎባቸው ነበር። ሰይፎቹም ዛቻ፣ ጦሮቹ ክህደት፣ ቀስቶቹ ሀሰት፣ ክስና ስም ማጥፋት ይባሉ ነበር። መራርነት፣ አለመቀባበል፣ ትዕግስት ማጣት፣ ይቅር አለማለት የተባሉ ስሞች ያሏቸው ጥቂት የአጋንንቱ ቡድን አባላትም ለዋናው ውጊያ ከዚህ ሠራዊት ፊት ቀድመው እንዲጓዙ ተልከው ነበር።

እነዚህ የአጋንንቱ ቡድን አባላት ቁጥራቸው አናሳ ቢሆንም ኃይላቸው ግን ከኋላቸው ተሰልፎ ከሚገሰግሰው በርካታ ክፍለ ጦር የሚተናነስ አልነበረም። ቁጥራቸው አናሳ የሆነው ደግሞ ለስልታዊ ምክንያት ብቻ ነበር። እነዚህ ጥቂት አጋንንታዊ ቡድኖች ልክ ዮሐንስ መጥምቁ ሕዝቡን በጥምቀት ለጌታ ለማዘጋጀት ብቻውን የተለየ ቅባት እንደተሰጠው ዓይነት እነዚህም ህዝቡን ለጥፋት ለማዘጋጀት «ብዙሃኑን ሕዝብ ለማጥመቅ» ልዩ አጋንንታዊ ኃይልን የለበሱ ነበሩ። አንዱ የመራርነት አጋንንት በሕዝብ ወገን ሁሉ ወይም ባህሎች ላይ እንኳን ሳይቀር መርዙን መርጨት ይችል ነበር። የርኩሰት አጋንንቱ ደግሞ ከአንድ የቴአትር፣ የፊልም ወይም የንግድ ምርት አስተዋዋቂ ተዋንያን ጋር ራሱን በማቆራኘት ቁጥሩ እጅግ በርካታ የሆነውን ሕዝብ እንደኤሌክትሪክ ያለ ኃይል እየላከ በመምታት ያፈዛቸውና ያደነዝዛቸው ነበር። ይሄ ሁሉ ደግሞ ቀጥሎ ለሚመጣው ለታላቁ የክፋት መንጋ መንገድ ጠርጎ ለማዘጋጀት ነበር።

Tuesday, March 6, 2012

ሰበር ዜና! «ዘመድኩን በቀለ የ5 ወራት እስር ተፈረደበት»

ለቀበጠች አማት ሲሦ በትር አላት


ሕገ ቤተክርስቲያንንና ሕገመንግሥትን በጫማው ረግጦ፣ ከሕግ በላይ ሆኖ በሕዝብና በቤተክርስቲያን ተወዳጅ የሆኑ ሰባክያነ ወንጌልና ዘማሪያንን አፉ እንዳመጣለት ተሃድሶና መናፍቅ እያለ ሲሳደብና ሲወራጭ የነበረው ዘመድኩን የ5 ወራት የእሥር ዋራንት ተቆረጠለት፡፡

ዛሬ የካቲት 27 ቀን 2004 ዓ.ም በአራዳ ምድብ ችሎት የዋለው ፍርድ ቤት ግራ ቀኙን ካየ በኋላ ዘመድኩን ሕግን በመጣስ በተለይም በመጋቤ ሀዲስ በጋሻው ደሳለኝ ላይ ባደረሰው የሞራልና የስም ማጥፋት፣ እንዲሁም የዛቻ ወንጀል ፍርዱ ሊወሰንበት መቻሉ ታውቋል፡፡ ዐቃቤ ሕግ ፍርዱ አንሷል ቢልም፣ የዘመድኩን ጠበቃ የልጆች አባት፣ የብዙ ቤተሰብ አስተዳዳሪና ወላጅ እናቱ በቅርብ የሞቱበት መሆኑን አስረድቶ የፍርድ ማቅለያ ሃሣብ በማቅረቡ ሊቃለልለት እንደቻለ እማኞቻችን ገልጸዋል፡፡

ይሁ እንጂ 5 ወሩም ቢሆን እንደማይፈረድበት የገመተው ዘመድኩን፣ እጅግ መደንገጡንና ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ የነበሩ ተባባሪ የውንብድና ጓደኞቹ ሲያለቅሱ እንደነበር ተስተውሏል፡፡ የዝግጅት ክፍላችን ዘመድኩንን እግዚአብሔር ያውጣህ እያለ፣ የ5 ወራት የእሥር ቤት ቆይታህ የትምህርት፣ የንስሐ እና የመስተካከል ቆይታ ያድርግልህ በማለት ለማኅበረ ቅዱሳን ጓደኞቹ "የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም" በሚል ተረት ይሰናበታቸዋል፡፡
እግዚአብሔር ለሁላችንም ማስተዋልን ያድለን!!!
አሜን!!!
ምንጭ ፣http://dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com/2012/03/blog-post_06.html

Saturday, March 3, 2012

«እኔ የመረጥኩት ጾም»

እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? (ክፍል ፩)

የያዝነው አርባ ጾም ዐቢይ (ታላቅ) ጾም እንደመሆኑ መጠን በመጽሐፍ ቅዱሳችን በምዕራፉ ሙሉ ስለጾም የሚናገረውን ትንቢተ ኢሳይያስ ም. ፶፰ ከሕይወታችን ጋር በማያያዝ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረንን እናያለን።
ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ ፶፰፡-
ቁ .፩  በኃይልህ ጩኽ፥ አትቈጥብ፥ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፥ ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን ንገር።
ኃጢአት ሰዎችን ከእግዚአብሔርን የሚለይ ሲሆን ንስሐ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ የሚያደርግ ተግባር ነው። ሰዎች ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ኃጢአታቸው ሊነገራቸው፡ እነርሱም ኃጢአታቸውን በመናገር ንስሐ ሊገቡ ይገባል። በዚህ ክፍል እግዚአብሔር ነቢዩ ኢሳይያስን ለአይሁድ ኃጢአታቸውን እንዲነግራቸው ያዘዋል። አይሁድ እግዚአብሔርን የሚያውቁና የሚያምኑ ሕዝቦች ቢሆኑም ጥፋታቸው ሊነገራቸው ይገባ ነበርና ነቢዩን ላከላቸው።
ዛሬ እግዚአብሔርን የሚያውቁና፡ በቤቱ ስለሚኖሩ ክርስቲያኖች ጥፋት ምን እያደረግን ነው? ጥፋታቸው ለራሳቸው ተነግሮአቸው ንስሐ እንዲገቡ ወይስ ለሌላው ተነግሮባቸው እንዲበረግጉ?  ወንድሞቻችን ምንም ዓይነት ጥፋት ያጥፉ ቁም ነገሩ ለምን አጠፉ? ሳይሆን እንዴት ይመለሱ? መሆን አለበት። አንድ ወንድም «ከጥፋቴ በፊት መጥፋቴ ያሳስባችሁ» ብሎአል። ብዙ ጊዜ ስለ ጥፋታቸው እንጂ ስለመጥፋታቸው አናስብም። እግዚአብሔር ግን ሁሉም በጥፋታቸው ተጸጽተው በንስሐ ይመለሱ ዘንድ ጥሪ እንድናደርግ በኃይልህ ጩኽ፥  ዝም እንዳንልም አትቈጥብ  ይለናል። በአንድምታውም ጩኽህ አስተምር፡ ማስተማሩን ቸል አትበል ይላል።