በአባ ሰላማ ድረ ገጽ ላይ «ፍቅር ለይኩን» የተባለ ሰው ስለየትኞቹ ስም አጥፊ ብሎጎች ለመናገር እንደፈለገ ስማቸውን ባይገልጽም እሱን ደስ ያላሰኘውን ነጥብ በማመልከት፤ የሰዎችንም ኃጢአት መዘርዘር
ጥሩ እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶችን በማስረጃ አቅርቦ ምክርና
ተግሳጽ ለመስጠት ሲሞክር ተመልክተናል።
ይህ በአባ ሰላማ ድረ ገጽ ላይ ጽሁፉን ያቀረበው «ፍቅር ለይኩን» የተባለው ሰው ፤ በፖለቲካው ዓለም ደከመን፤ ሰለቸን
ሳይሉ የኢሕአዴግን መንግሥት በማጥላላትና በመቃወም ሌሊትና ቀን በሚደክሙት
ድረ ገጾች ላይ የተለያዩ ፖለቲካዊ መጣጥፎችንና አንዳንዴም መንፈሳዊ መሰል የነቀፋ ጽሁፎችን የሚያቀርበው የደቡብ አፍሪካው «ፍቅር ለይኩን» መሆኑን የምናውቀው ከስሙ ባሻገር «ሻሎም፤ ሰላም» በሚለው የጽሁፉ ማሰረጊያ
ቃል የተነሳ እሱነቱን ብንገምት ከእውታው የራቅን አይመስለንም።
ከዚህ ተነስተን ስለአቶ ፍቅር ለይኩን ጽሁፍ ጥቂት ለማለት
እንወዳለን።
አቶ ፍቅር ስለአባቶች መዋረድና አለመከበር ተገቢ መሞገቻ
ይሆነው ለመከራከሪያነት የተጠቀመበትን ዐውደ ጥቅስ በማስቀደም እንጀምር።
‹‹ደፋሮችና ኩሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም፣ ዳሩ ግን መላእክት በኃይልና በብርታት
ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡ በጌታ ፊት በእነርሱ ዘንድ የስድብን ፍርድ አያመጡም…፡፡›› ፪ጴጥ ፪፣፲፩፡፡
ይህን ጥቅስ አቶ ፍቅር ለይኩን ያቀረበው ምንም ይስሩ ምንም፤ ምንም ያድርጉ፤ የቱንም ያህል ይበድሉ፤ ስለ ጳጳሳት አትናገሩ፤ ምክንያቱም ወንጌል አትናገሩ ብሏልና ሲል የአፍ መዝጊያ
ጥቅስ በማቅረብ ሊሞግተን ይፈልጋል። ጥቅሱ ስለማን እና ስለምን እየተናገረ እንደሆነ ግን አያብራራም። መቼም ምግባረ ብልሹና የጥፋት
ኃይል ለሆኑ ሹመኞች ሁሉ እንድንገዛ የተነገረ ነው እንደማይለን ተስፋ
እናደርጋለን። እንደዚያማ ከሆነ አቶ ፍቅር የኢህአዴግ መንግሥት ክፉና መሰሪ ነው፤ የአባ ጳውሎስ አስተዳደር አጥፊና ከፋፋይ ነው
እያሉ ለኢህአዴግ ውድቀት በሚሰሩ ድረ ገጾች ላይ ጽሁፎቹን ሲለቀልቅ ባልዋለም ነበር። ምክንያቱም ወንጌል እንደዚህ ሲል ያስጠነቅቀዋልና።
ስለ ጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙ፤ ለንጉሥም ቢሆን፥ ከሁሉ በላይ ነውና፤
ለመኳንንትም ቢሆን፥ ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና ተገዙ። 1ኛ ጴጥ 2፤13-14
ኢህአዴግን መቃወምም ሆነ መደገፍ መብት በመሆኑ ጸረ ኢህአዴግ ድረ ገጾች
አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል። የማያሻማ ሆኖ «ለንጉሥም ቢሆን ተገዙ፤ ክፉ የሚያደርጉም ቢሆኑ መኳንንቱ ከላይ ተልከዋልና» የሚለውን የወንጌል
ቃል ጨቋኞች፤ አምባገነኖችንና አላውያን መሪዎችን ሁሉ አሜን ብለን እንድንሸከም የሚናገር ቃል አይደለም ከሚል ጽንሰ ሃሳብ የተነሳ እየታገሉ ይገኛሉ። አቶ ፍቅር ደግሞ በነዚያው ድረ ገጾች ስሜቱን በጽሁፍ እየገለጸ ሲያበቃ ከወንጌል ቃል ጠቅሶ ለምግባረ ብልሹዎችና ለሥርዓት አፍራሾችም ቢሆን ተገዙ በማለት ሊያስተምረን ይፈልጋል። ምነው ጽሁፎቹን ለሚያቀርብባቸው ድረ ገጾች የእናንተ ተቃውሞ ቃለ እግዚአብሔርን የተጻረረና ሕገ እግዚአብሔርን ያፈረሰ ስለሆነ አርፋችሁ ተቀመጡ፤ ዝም ብላችሁም ለኢህአዴግ ተገዙ! የሚል ምክርና ጽሁፍ ያላቀረበላቸው? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ እኔና መሰሎቼ የምንጠላው ሲጻፍበት እንጂ የምናወዳቸው ሲነኩብን ያመናል የሚል ቃና ይሰጠናል።