Showing posts with label ትምህርት. Show all posts
Showing posts with label ትምህርት. Show all posts

Wednesday, July 22, 2015

" እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች"

ፕሮቴስታንት፣ ካቶሊክ፣ ኦርቶዶክስ ብንባልም የእምነታችን ጀማሪና ፈፃሚ ግን ያው አንዱ ክርስቶስ ነው። በዚህ ዘመን ይቅርና በሐዋሪያት ዘመን እንኳ ክርስቲያኖች እርስ በእርስ በመከፋፈልና በመገፋፋት ያስቸግሩ ነበር። ጴጥሮስ (ኬፋ) ያስተማራቸው፣ ጳውሎስ ያስተማራቸው እንዲሁም ሌሎች ያስተማሩዋቸው ክርስቲያኖች ለየብቻቸው መደራጀታቸውና መራራቃቸው ሐዋሪያው ጳውሎስን አስመርሮት እንዲህ ብሎ ፅፎላቸው ነበር፦ 1ኛ ቆሮንቶስ 1፥ 10 "ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ። ወንድሞቼ ሆይ፥ በመካከላችሁ ክርክር እንዳለ ስለ እናንተ የቀሎዔ ቤተ ሰዎች አስታውቀውኛልና። ይህንም እላለሁ። እያንዳንዳችሁ። እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ እኔስ የአጵሎስ ነኝ፥ እኔ ግን የኬፋ ነኝ፥ እኔስ የክርስቶስ ነኝ ትላላችሁ። ክርስቶስ ተከፍሎአልን? ጳውሎስስ ስለ እናንተ ተሰቀለን? ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን?"

በእኛ ዘመንም ቢሆን ክርስቶስ አልተከፈለም። በመካከላችንም ወይ በፕሮቴስታንት ወይ በኦርቶዶክስ ወይ በካቶሊክ ስም የተጠመቀ የለም። የተሰቀለውም አንድ ሲሆን፣ በታዘዝነው መሰረት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሁላችን ተጠምቀናል። ክርስትና አንድ ሲሆን አብያተክርስቲያናት ግን እንዳመለካከታችን መጠን ብዙ ናቸው። ልዩነት ችግር የሚሆነው እኛ ስናደርገው ነው፣ ካወቅንበት ግን ዉበት ነው።

============================
አለም ላይ እንዳለው ብዛት እና ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም የትና የት መድረስ ይችል የነበረው የተከበረው ሐይማኖታችን፣ በኋላቀር አስተሳሰባችንና እኔ ብቻ ልደመጥ ባይነታችን እርስ በእርሱ ተጠላልፎ ወደ ፊት ዳዴ እንኳን ማለት ተስኖታል። ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ እኛው ነን። ጥፋታችንን ሳንቀበል መፍትሄ ማምጣት አይቻልም። ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች በየቦታው ተበታትነናል። ለአንድ ዓላማ ልንቆምለት የምንችለው ትልቅ ሐይማኖት እና እውነት ይዘን፣ ነገር ግን እንደ ህፃናት በተገኘችው ጥቃቅን ቀዳዳ ሁሉ መበጣበጥ በጣም አሳዛኝ ነገር ነው። ተልኮአችንን ረስተነዋል። ውጪ ያሉትን ለክርስትና መማረክ ሲገባን የራሳችንን ወንድም በመታገል ጉልበታችንን እዛው ቤት ውስጥ እያፈሰስነው ነው። የራሳችንን ቤት እኛው እያፈረስነው ነው። ወደ ፍቅር እንመለስ!!

==========================
ማቴዎስ 12፥ 25 " እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፥ እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም።"

===========================
መዝሙረ ዳዊት 133 ፥ 1 "ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው።"

===========================
ዮሐንስ 17፥ 20-23 "ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፥ አንተ፥ አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ። እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል።"

===========================
ስለ ክርስቲያኖች አንድነት ብዙ የተባለ ቢኖርም ለዛሬ እነዚህን አይተናል። ስህተትን ማረም ከሁሉም ይጠበቃል። በየአብያተክርስቲያናቱ ያሉ መሪዎችም ራሳቸውን መፈተሽ እና ከሚከፋፍል እና ከጥላቻ የራቀ ትምህርት ማስተማር ይኖርባቸዋል። እንዲያ ካልሆነ ግን እግዚአብሔርን ማገልገልም ሆነ መከተል ከንቱ ነው። የፍቅርና የአንድነት አምላክ እንጂ የጥላቻ እና የመከፋፈል አይደለምና። ወንድሙን ጠልቶ እግዚአብሔርን እወዳለሁ የሚል እራሱን ያታልላል።

እያልኩ ያለሁት ያሉንን አብያተክርስቲያናት አፍርሰን አንድ ቤተክርስቲያን እናቋቁም ሳይሆን፣ በያለንበት ህብረት ማድረግ ይቻላል። ከልዩነቶቻችን በላይ አንድነታችንን እናጉላው የሚል ነው።

እንግዲህ በመካከላችን ያለውን አላስፈላጊ ርቀት እናጥብብ፣ ህብረት እናድርግ፣ እንፈላለግ፣ ይቅር እንባባል። አንድነት ውስጥ ያሉ የአመለካከት ልዩነቶች ውበት ናቸው እንጂ በራሳቸው ችግር አይደሉም። መንገዳችንንም እናስተካክል፣ እግዚአብሔርንም በአንድነት እንፈልግ።

===========================
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 7፥ 14 "በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው ቢጸልዩ፥ ፊቴንም ቢፈልጉ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፥ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፥ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ።"
===========================

በዚህ መልእክት የምትስማሙ መልእክቱን ለሌሎች ወንድሞችና እህቶች ሃሳቡን ለሌሎች አካፍሉ። እንዲህ ባለው ሀሳብ ደስተኛ የማይሆኑ አንዳንድ ግለሰቦች በየአብያተክርስቲያናቱ ቢኖሩ ለጊዜው ነው ተዋቸው፣ እግዚአብሔርን በሚገባ እስኪያውቁት ነው።


Lewi Ephrem's

Sunday, June 28, 2015

" ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ፥" (ሮሜ 1:22)

my finger to you? (blogger)


                                ፍቅር ፍቅር ነው” ኦባማ

" እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ።" " እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው"
ሮሜ1፣27-28

ወንድ ከወንድ፤ ሴትም ከሴት ጋር ጋብቻ መፈጸም ይችላሉ፤ ለእነርሱ የጋብቻ ሠርቲፊኬት መከልከል ሕገመንግሥቱን ይጥሳል በማለት የአሜሪካው ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተመሳሳይ ጾታ ያላቸው መጋባት እንደሚችሉ ወሰነ፡፡ ለጋብቻ ቅድስናና ክቡርነት የሚከራከሩ “የእግዚአብሔርን ሕግ ምድራዊ ፍርድ ቤት ይህን መለወጥ አይችልም” በማለት ውሳኔውን አጥብቀው ተቃውመዋል፡፡ በምንም መልኩ ይገለጽ ፍቅር ፍቅር ነው በማለት ፕሬዚዳንት ኦባማ ውሳኔውን ደግፈዋል፡፡

 ዋናውን (ዓቃቤ ፍትህ) ጨምሮ ዘጠኝ የፍትህ ዳኞች የያዘው የአሜሪካው ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዚህ የሰዶማውያን ጋብቻ ላይ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ጉዳዩ ከቀረበለት ጊዜያት ተቆጥረዋል፡፡ በአሜሪካ የፍትሕ ሥርዓት ምዕራፍ ከፋች የተባለለት ውሳኔ አርብ ዕለት ሲተላለፍ የፍትሕ ዳኞቹ በአምስት ለአራት በመወሰን ነው ያጸደቁት፡፡ ይህ ጠባብ ልዩነት የታየበት ውሳኔ ሲተላለፍ አምስቱን ደጋፊዎች ወክለው አስተያየታቸውን የጻፉት የፍትሕ ዳኛ አንቶኒ ኬኔዲ ናቸው፡፡ እርሳቸውም ሲጽፉ “ከጋብቻ አንድነት የሚበልጥ የለም፤ ምክንያቱምታላቅ የሆነ ፍቅር፣ ታማኝነት፣ መስዋዕትነትና ቤተሰብን ያካተተ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለት ከመሆን ይልቅ አንድ በመሆን የሚገኘው ኅብረት ይበልጣል በማለት ሰዎች የጋብቻ ኅብረት ይፈጥራሉ” ብለዋል፡፡ ሲቀጥሉም “ይህንን ጉዳይ በተመለከተ አቤቱታቸውን ያቀረቡት እንዳሳዩት ጋብቻ ማለት ሞትን አልፎ የሚሄድ ፍቅር መሆኑን ነው፤ … እነዚህ ሰዎች የጋብቻን ክቡርነት ያቃልላሉ ማለት እነርሱን አለመረዳት ነው፤ እንዲያውን እነርሱ ጋብቻን እንደሚያከብሩ ነው በመማጸን የሚናገሩት፤ ጋብቻን በጣም ስለሚያከብሩ ነው ተፈጻሚነቱን በእነርሱ ህይወት ማየት የሚፈልጉት፤ ጥንታዊ ከሆኑ ተቋማት አንዱ ከሆነው ጋብቻ ተገልለውና በብቸኝነት ተኮንነው ላለመኖር ነው ተስፋቸው” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

 ውሳኔውን ከተቃወሙት የአራቱን በመወከል አስተያየት የጻፉት ዓቃቤ የፍትሕ ዳኛው ዮሐንስ ሮበርትስ ናቸው፡፡ እርሳቸው ውሳኔው በርካታዎች ሊያስደስት ይችላል ካሉ በኋላ ሲጽፉ “አብላጫውን ድምጽ የሰጡት ውሳኔ በጥልቅ ልብን የሚነካና ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው፤ ጋብቻ በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መካከል የሚፈጸም ኅብረት ነው የሚለው ዓለምአቀፋዊ ትርጉም በምንም ዓይነት መልኩ ታሪካዊ አጋጣሚ አይደለም፤ ጋብቻ በፖለቲካ ትግል፣ በግኝት መልክ፣ በበሽታ፣ በጦርነት፣ በሃይማኖታዊ ሥርዓተ ሕግ ወይም አንዳች የዓለምን ታሪክ ባናወጠ ኃይል የተከሰተ አይደለም፤ እንዲሁም ወንድና ወንድ ወይም ሴትና ሴት ተጋቢዎችን ለማግለል ተብሎ የተደረገ የቅድመታሪካዊ ውሳኔ ውጤትም አይደለም” ብለዋል፡፡ ሲቀጥሉም “ጋብቻ የተከሰተው ወሳኝ የሆነን ፍላጎት ለማሟላት ነው፤ ይህም ደግሞ ከእናትና አባት ልጆችን በመውለድ እነርሱን በተረጋጋ ሁኔታ ለማሳደግ ራስን አሣልፎ በመስጠት የህይወት ሙሉ ውሳኔ በማድረግ ነው” ብለዋል፡፡

የውሳኔው እንደምታ

የጋብቻን ክቡርነት የሚሰብኩና ጋብቻ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል መወሰን አለበት የሚሉ ወገኖች በዚህ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ክፉኛ ሃዘን ገብቷቸዋል፤ የወደፊቱም ሁኔታ አስግቷቸዋል፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ የሚከሰቱት ነገሮች ማኅበረሰቡን በእጅጉ የሚበጠብጡ እንደሚሆኑም ካሁኑ እየተነገረ ነው፡፡
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ሲያሳልፍ የጋብቻን ሃይማኖታዊ ገጽታ አልተመለከተም የሚሉ ወገኖች በተለይ መጽሐፍ ቅዱስ ሰዶማውያንን በተመለከተ የሚናገረውን ከሮሜ መጽሐፍ አንደኛው ምዕራፍ ላይ ያለውን ይጠቅሳሉ፡፡ “እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ። … ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵስነት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ … ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ (ከወንድ ጋር መገናኘት ትተው) ለባሕርያቸው በማይገባው (እርስ በርሳቸው በማድረግ) ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ። እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤ … ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ”፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን በዚህ ውሳኔ ምክንያት በርካታ ግለሰቦችና ተቋማትም አደጋ ላይ እንደሚወድቁ እየተነገረ ነው፡፡ ለምሳሌ በጋብቻ ሥርዓት ላይ አገልግሎት የሚሰጡ የሠርግ ኬክ ጋጋሪዎች፣ አበባ አዘጋጆች፣ የሠርግ ዕቅድ አውጪዎች፣ ፎቶግራፍ አንሺዎች፣ ወዘተ በእምነታቸው ምክንያት ለሰዶማውያን ጋብቻ አገልግሎት አንሰጥም በሚሉበት ጊዜ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ቅጣት የሚቀበሉ ይሆናሉ፡፡ በኮሎራዶ ጠቅላይ ግዛት አንድ ኬክ ጋጋሪ እንዲሁም በኒውዮርክ ግዛት የገጠር ቤታቸውን ለሠርገኞች የሚያከራዩ ለሰዶማውያን አገልግሎት አንሰጥም በማለታቸውና ግዛቶቹ የሰዶማውያንን ጋብቻ ያጸደቁ በመሆናቸው ፍርድቤት ቀጥቷቸዋል፡፡ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ ግን በየትኛውም ግዛት ቅጣቱ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ከአምሳዎቹ የአሜሪካ ግዛቶች 14ቱ በሰዶማውያን ጋብቻ ላይ ዕገዳ ያደረጉት ከአርቡ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ ዕገዳቸውን ማንሳት አለባቸው፡፡


“ተመሳሳይ ጾታ” ብሎ “ጋብቻ” የሚለው ቃል አብሮ አይሄድም በማለት የሚከራከሩ ወገኖች ጋብቻ የሚለው ቃል የሚውለው ለተቃራኒ ጾታ ብቻ ነው ይላሉ፡፡ ከዚህም ሲያልፍ የተቃራኒ ጾታዎች ግንኙነት ብቻ ነው ልጆችን ማፍራት የሚችለው ይላሉ፡፡ ሰዶማውያን ወይም ተመሳሳይ ጾታ ያላቸው ሲጋቡ የሚያፈሩት ልጅ የለም፡፡ ሴቶቹ ተጋቢዎች የወንድ ዘር ከዘር ባንክ በመግዛትና ውስጣቸው በህክምና በማስጨመር ቢወልዱም ወንድ ተጋቢዎች ግን በጉዲፈቻነት ሌሎች በተቃራኒ ጾታ ግንኙነት የፈጠሩትን ልጅ ወስደው ነው የሚያሳድጉት፡፡ ስለሆነም ሁለቱ ተጋቢዎች በተፈጥሮ ለመውለድ የማይችሉ በመሆናቸው በጥቅሉ ከሚታወቀው ጋብቻ እኩል ተደርጎ መወሰድ የለበትም ይላሉ፡፡ እንዲያውም የሰዶማውያን ጋብቻ የሰው ዘር እንደ ብርቅዬ እንስሳ እንዲጠፋ ድጋፍ የሚሰጥ ነው እስከማለት አጥብቀው ይከራከራሉ፡፡

ይህንን ውሳኔ ተከትሎ ካሁን በኋላ ሰዶማውያን የፈለጉትን ልጅ በጉዲፈቻነት ለማሳደግ ልክ እንደ አንድ ባልና ሚስት ፈቃድ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ይህ ፈቃድ በሰዶማውያን “ወላጆች” አድጎ በነርሱ መስመር የሚቀጥል ልጅ ለማሳደግና ሰዶማዊነት እንደ መደበኛ ተግባር እንዲቆጠር ለማድረግ በር ከፋች ይሆናል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ከሃይማኖታቸው አንጻር የሰዶማዊነትን ትክክለኛ አለመሆን የሚሰብኩ ካህናት በሰብዓዊ መብት ረገጣ እስር ቤት የሚጣሉበት ቀን ሩቅ አይሆንም፡፡ በየአምልኮ ቦታው የሚሄዱ ሰዶማውያን ልጆችን ከማስተማር ጀምሮ በአምልኮ ቤቶቹ አገልግሎት እንዳይሳተፉ መከልከል አይቻልም፡፡ በመሆኑም መጪው ትውልድ ከሥነምግባር አኳያ በትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን በአምልኮ ሥፍራዎችም የሰዶማውያን ጋብቻ ትክክል ነው በማለት እያመነ እንዲያድግ ይቀረጻል፡፡

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንደተሰማ ተቃውሟቸውን ያሰሙት የሉዊዚያናው አገረ ገዥ ቦቢ ጂንዳል ሲሆኑ እርሳቸውም ዘለግ ያለ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ ለመጪው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚወዳደሩት ጂንዳል “ውሳኔው ሰዶማዊነትን በመቃወም ሰዎች የሃይማኖት ነጻነታቸውን በገሃድ እንዳይለማመዱ ጥቃት የሚሰነዝር ነው” ብለውታል፡፡ ሲቀጥሉም “ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው የሕዝብ አስተያየትን በመከተል መሆኑ የሚያስደንቅ አይደለም፤ ሆኖም ውሳኔው ጠቅላይ ግዛቶች በሚያስተዳድሯቸው ግዛቶች ላይ የሚፈልጉት ሕግ እንዳያወጡ ወይም እንዳይቃወሙ መብታቸውን የሚረግጥ ነው፤ በመሠረቱ በአንድ ሰውና በአንዲት ሴት መካከል ጋብቻ እንዲሆን የመሠረተው እግዚአብሔር ነው፤ ማንኛውም ምድራዊ ፍርድ ቤት ይህን መለወጥ አይችልም” ብለዋል፡፡


የጠቅላይ ፍርድቤቱ ውሳኔ እንደተሰማ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በሰጡት መግለጫ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ “ፍቅር ፍቅር ነው” በማለት የተናገሩት ኦባማ የግብረሰዶማውያን ጋብቻ ሕጋዊ እንዲሆን በተለይ በሁለተኛው የአስተዳደር ዘመናቸው ጥረዋል፡፡ ውሳኔው “ለአሜሪካ ድል ነው” በማለት በወጣትነት ዘመናቸው ሰዶማዊ ነበሩ ተብለው በአንዳንዶች የሚታሙት ኦባማ በካሜራ ፊት አውድሰውታል፡፡


ኦባማ የሰዶማውያን መብት በአገራቸው ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም እንዲከበር አበርትተው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ባለፈው ምዕራብ አፍሪካን በጎበኙበት ወቅት ይህንኑ ጉዳይ አንስተው ያደረጉት ንግግር በአፍሪካውያን ዘንድ ተደማጭነት ያጣ ብቻ ሳይሆን የከረረ ተቃውሞም ገጥሞት ነበር፡፡ ሆኖም ግን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የአሜሪካ ሸሪክ በመሆን የአሜሪካንን ጥቅም ጎረቤት አገርን በመውረርም ሆነ ወታደራዊ ቤዝ በመስጠት የሚያስከብሩ የአፍሪካ አገራት በዚህ የሰዶማውያን መብት ጥበቃ ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ የሚለው አስተያየት ሲሰማ ይደመጣል፡፡ አሜሪካ የበጀት ድጎማ የምታደርገውም ሆነ አምባገነኖችን በጭፍን የምትደግፈው በምላሹ የምታገኘውን በማሰብ እንደሆነ የሚናገሩ ወገኖች አሜሪካ ገንዘቧ ሰጥታ ይፈጸምልኝ የምትለውን ሳታገኝ የምትቀርበት ምንም ምክንያት አይኖርም ይላሉ፡፡
ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያ ውስጥ እየተስፋፋ በመጣው የወሲብ ልቅነትና የሰዶማውያን ሁኔታ ሳይንሳዊ መረጃ ማቅረብ የሚያዳግትበት ቢሆንም ከውጭ ድጋፍና ተጽዕኖ ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ፓትሪሽያ ሃስላክ የሹመት ጥያቄያቸውን ለአሜሪካው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በማቅረብ በውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ፊት ቀርበው ሲመሰክሩ እንዲህ ብለው ነበር፤ “(የአምባሳደርነት ሹመቴ) ከጸደቀ በጾታ ላይ የሚደረግን ጥቃት እንዲሁም በግብረሰዶማዊያን ኅብረተሰብ ላይ የሚፈጸመውን መድልዖ አስመልክቶ እኛ (አሜሪካውያን) የምንከተለው የፖሊሲ አቅጣጫና ጥረት (በኢትዮጵያም እንዲሆን) የሚቻለኝን ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኔን እገልጻለሁ”፡፡


በሐምሌ ወር ማገባደጃ አካባቢ ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ ባለፈው ሰሞን መነገሩ ይታወሳል፡፡


(Golgul web news)

Friday, April 10, 2015

"ሰላማችን ክርስቶስ ነው"



"ሰላማችን ክርስቶስ ነው"
ዓለም ዛሬ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት በታላቅ ሥጋት ላይ ወድቃ ትሸበራለች። ድርቅና በረሃማነት የዓለምን ሕዝብ ለረሃብና ለበሽታ አጋልጦታል። ከዓለም ሕዝብ ከፊሉ ያህል በጎርፍ: በረሃብ: በበሽታ: በመሬት መንቀጥቀጥና በዐውሎ ንፋስ ሕይወቱንና ንብረቱን እያጣ ነው።
  ይህም ብቻ አይደለም: አንዱ መንግሥት ከሌላው በፖለቲካ: በድንበር: እየተናቆረ: በንግድ ውድድር እየተጎናተለ ጉልበተኛው መንግሥት ደካማውን እያጠቃ ነው። እንዲያውም የአንዳንድ አገር ሕዝብ እርስ በእርሱ በጦርነት ሲተላለቅ ይታያል። ስለዚህም ነው "ሰላም:ሰላም!" የሚል ድምፅ በዓለማችን ዙሪያ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስተጋባው።
    የርግቧ ሥዕል ከነወይሯ ቀንበጧ በየጋዜጣው: በየመጽሔቱና በየቅ'ስቱ በሠፊው ተሥላ ትታያለች።
የተባበሩት መንግሥታት መልእክተኞችም በየቦታው በአስታራቂነት ይሯሯጣሉ። ይህ በዚህና በዚያ የሚሰማው ጩኸት: የሚደረገው ሩጫና ግርግር የተከሠተውን ውጥረት በመጠኑ ለማርገብ እንጂ እውነተኛውን መሠረታዊ ሰላም ለማስፈን አልቻለም።

እውነተኛው ሰላምስ? መቼ: እንዴት ይገኝ ይሆን? የእግዚአብሔር ቃል ለዚህ መልስ አለው።

  " እርሱ ሰላማችን ነውና: ሁለቱን ያዋሃደ: በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ: ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ: ሰላምንም ያደርግ ዘንድ: ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምሥራች ብሎ ሰበከ። በእርሱም ሥራ በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና።" ይላል።
 (ኤፌ 2:21-30)
 ሰው ራሱን: መሰሎቹንና ተፈጥሮንም ጭምር መጥላቱንና መጒዳቱ : ከእግዚአብሔር ጋር የመጣላቱ ውጤት ነው። አሁንም ከእግዚአብሔር ጋር እንድንስማማና ሰላም እንዲኖረን የእግዚአብሔር ቃል ይመሰክርልናል።
  ስለሆነም ሰው ሁሉ እግዚአብሔር ባዘጋጀለት የዕርቅ መንገድ ከአምላኩ ጋር ለመታረቅ እሺ ባይነት ቢኖረው ኖሮ " ሰላም በምድር" ይሆን ነበር።
ከክርስቶስ ጋር ያልታረቀች ዓለም ሰላም ይኖራታል ተብሎ አይታሰብም። ስለሆነም የትንሣዔን በዓል ስናከብር በልማዳዊ ሥርዓት " እንኳን አደረሰህ: አደረሳችሁ" ከመባባል ባለፈ በዕለታዊ ኑሮአችን ሁሉ የተለወጠ: ከክርስቶስ ጋር የታረቀ ሰላማዊ የሕይወት መገለጥ ልናሳይ ይገባል። ካልተለወጥን በስተቀር ሰላም በአካባቢያችንና በዐለማችን ሊኖር አይችልም።
አሁንም ነገም "ሰላም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ" ይሁን! እንል ዘንድ ከክርስቶስ ጋር እንታረቅ።
መልካም ትንሳዔ!!
(በ1984 ዓ/ም ከታተመው ጮራ መጽሔት ቁጥር 3 ተሻሽሎ የተወሰደ)

Wednesday, January 14, 2015

«ሳይኖረኝ አኖርከኝ»

አሌክስ ሎዶቅያ፤ ኦስሎ/ ኖርዌይ ( 6/5/ 2007 )

   የሰው አስጨናቂ አገዛዝ ክብደት፣ የመከራ ስጋት፣ የኑሮ ውድነት ጭንቀትና የወዳጅ ክዳት ለሚያስጨንቁን መፍትሔው የሚያኖረንን ማወቅ ነው፡፡ በዘላለም ክንዶቹ ደግፎ፣ አእምሮን ሁሉ በሚያልፍ ሰላሙ አሳርፎ፣ ሳይዘነጋ አስቦ፣ ቸል ሳይል እንደ ዐይኑ ብሌን ጠብቆ፣ ሳይሰስት ሰጥቶ እና ሳይደክም ተሸክሞ የሚያኖረን እግዚአብሔር ነው፡፡ ለሚታየው ኑሮአችን መሰረቱ የማይታየው እምነታችን ነውና በእግዚአብሔር እንመን፤ በእግዚአብሔርም እንተማመን፡፡

   ከኮሌጅ ተመርቄ እንደወጣሁ በሲኦል ፊት የተጣልኩ ያህል እጅግ ከፍቶኝ ነበር፡፡ ተስፋ ያደረኳቸው ሁሉ አነሱብኝ፡፡ የያዝኩት ዲግሪ ሰርተፊኬት የሌላቸው ሰዎች የሚበሉትን እንጀራ እንኳ ሊሰጠኝ አልቻለም፡፡ በቤቴ እንደ እንግዳ በእናቴ ጓዳ እንደ ባእድ በመሆኔ ልቤን ሀዘን ወጋው፡፡ አንድ ወዳጄ ጋር ሻይ ቡና እያልን የወዳጄ ወዳጅ ድንገት ተቀላቀለን፡፡ “ሕይወት ከምርቃት በኋላ እንዴት ነው?” አለኝ “እንዳሰብኩት መኖር አልቻልኩም” አልኩት፡፡ እርሱም የፍቅር መንፈስ በለበሰ ተግሳጽ “ወዳጄ እንደተፈቀደልህ እንጂ እንዳሰብከው አትኖርም” አለኝ፡፡ ይህ ቃል በልቤ ቀረ፡፡ እንዳሰብነው ለመኖር ብዙ ደክመን ይሆናል፤ መኖር የምንችለው ግን የሚያኖረን አምላክ እንደፈቀደልን ነው፡፡
   ተስፋ ካደረኳቸው ሁሉ አይኔን አንስቼ የሁሉ ዐይን ተስፋ ወደሚያደርገው የዘላለም አምላክ አንጋጠጥኩ፡፡ ያላሰብኩት በረከት ከበበኝ፡፡ ከምኞቴ በላይ በሆነ ከፍታ እግዚአብሔር አኖረኝ፡፡ ከወራት በኋላ በእልፍኜ ብቻዬን ሳለሁ የምድረበዳውን ጉዞ ከጀመርኩ በኋላ የሆነውን አሰብኩ ዐይኖቼ በእንባ ተሞሉ አንደበቴም ለምስጋና ተከፈተ “ሳይኖረኝ አኖርከኝ አምላኬ ተመስገንልኝ” አልኩት፡፡ ዲያሪዬም ላይ የሆነውን ሁሉ መዘገብኩት፡፡ እግዚአብሔር የሚኖር የሚያኖር አምላክ ነው፡፡ ምንም ሳይኖረን እግዚአብሔር እንደሚያኖር የእስራኤል ታሪክ ማሳያ ነው፤ ማንም በማይቀመጥበትና በማያልፍበት ምድረበዳ መርቷቸዋልና፡፡
 ዘዳ. 32፡11፣ ኤር. 2፡5፡፡
   የአንዲት እህት የሰላምታ ቃል “ኖሮ ያኖረኛል” በሚል ምስክርነት የተቃኘ እንደሆነ ሰምቼ ራሴን በሚያኖረኝ ውስጥ ስላገኘሁት ልቤ ሀሴት አደረገ፡፡ እግዚአብሔር ኖሮ የሚያኖር አምላክ ነው፡፡ መኖሩ የሚያኖረን ህልውናው ያቆመን ከእንግዲህ አንታወክም፡፡ ሕይወታችን ለምን በስጋት ታጠረ? የሚያኖረን እግዚአብሔር አይሞትም፤ አይሻርም፤ አያረጅም፤ አይደክምም፤ አይሰለችም፡፡ በአስፈሪ ሁኔታዎች ብንከበብም መኖር እንደምንችል የሚገባን እግዚአብሔር እንደሚያኖረን ስናውቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር እንደሚያኖራት የገባት ነፍስ የአራዊት መንጋጋ፤ የክፉዎች መንጋ አይነካትም፡፡
ዳዊት “በክንፎችህ ጥላ ደስ ይለኛል፡፡ ነፍሴ በኋላህ ተከታተለች፡፡ እኔንም ቀኝህ ተቀበለችኝ፡፡” አለ መዝ. 62፡9፡፡ እረኛችንን በደስታ እንከተል በሚያስተማምን እረፍት፣ በማይነጠቅ ደስታና አይምሮን ሁሉን በሚያልፍ ሰላም እንኖራለን፤ በለምለም መስክ እንሰማራለን፤ በእረፍት ውሃ በፍቅሩም ጥላ እናድራለን፤ በጥበቃው አጥር እንከበባለን፤ እረኛችን ሆኗልና የሚያሳጣን የለም፡፡ መዝ. 22፡1
ሙሴ ምድረ ርስትን በናባው ተራራ በሩቅ ከተሳለመ በኋላ ስለማይወርሳት አዘነ፡፡ እግዚአብሔር ግን መኖሪያህ እኔ ነኝ አለው፡፡ ሙሴም ለሕዝቡ “ይሹሩን ሆይ መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፡፡ የዘላለም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፡፡” አለ፡፡ ዘዳ. 33፡26-29፡፡ የዘላለም አምላክ እግዚአብሔር የዘላለም መኖሪያችን ነው፡፡ እኛም የእርሱ መኖሪያ ዐለማት ነን፡፡
ለመኖር ከመሠረታዊ ጥያቄዎች ባሻገር ለዛሬ ጥበቃ ለነገም ተስፋ ያስፈልገናል፡፡ እግዚአብሔር ለዘላለም መግባትና መውጣታችንን ሳያንቀላፋ የሚጠብቅ መልካም እረኛ ነው፡፡ የትውልድ መጠጊያ የሁላችን ተስፋ እርሱ ነው፡፡ ችግረኛና ምስኪኑን ይረዳዋል፡፡ መዝ. 71፡12፤ 120፡1-8፤ 144፡15፡፡
ስለዚህ ልቤ ከዘማሪው ጋር አብሮ ዘመረ “የሚያኖረኝ ጌታ ነው፤ ምን ያስጨንቀኛል፡፡ የሚያስፈልገኝንም ያዘጋጅልኛል፡፡ አይሻግትም አይጎልም ሞሰቤ፤ ከሰማይ ነው ቀን በቀን ቀለቤ” እንደ እኔ ምንም ሳይኖራችሁ የሚኖረው እግዚአብሔር የሚያኖራችሁ፤ ሀብት፣ እውቀትና ስልጣን ያላስመካችሁ ኖሮ የሚያኖረንን ባርኩ፡፡ ከፍ ስንል ከፍ ያደረገንን አምላክ በምስጋና ቃል ከፍ ማድረግን አንርሳ፡፡
// ካነበብኩት//

Monday, November 17, 2014

«ጌታ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን» (ዮሐ. 12፥21)

“ንፈቅድ ንርአዮ ለእግዚእ ኢየሱስ - ጌታ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን”
 (ዮሐ. 12፥21)
( ከጮራ ድረ ገጽ የተወሰደ)
ከግሪክ ወደ ኢየሩሳሌም ለፋሲካ በዓል መጥተው የነበሩ የግሪክ ሰዎች ለሐዋርያው ፊልጶስ ያቀረቡት ሐሳብ ነው። ፊልጶስም ለእንድርያስ ነግሮት ኹለቱም ለኢየሱስ መጥተው የሰዎቹን መሻት አወሩለት። ጌታም፥ “የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች” አለ። በዚህ መስተጋብር ውስጥ በተለይ ኢየሱስን ማየት የሚፈልጉ ሰዎችንና ለእነርሱ ኢየሱስን ማሳየት የቻሉ አገልጋዮችን መመልከት እንችላለን።
ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኢየሱስን የሚፈልጉና ኢየሱስን ከፈላጊዎቹ ጋር የሚያገናኙ ምን ያኽል ናቸው? የሚለውን ጥያቄ ማንሣት ይኖርብናል። በዚህ ዘመን በቤተ ክርስቲያን እየታየ ያለው አንዱ ችግር፥ ጌታ ኢየሱስን የሚፈልግ ምእመንና እርሱን የሚያሳይ አገልጋይ ቍጥር እየተመናመነ መምጣቱ ነው። ርግጥ የምእመናን የልባቸው መሻትና የነፍሳቸው ጥያቄ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ብዙዎቹ አገልጋዮች ግን ዕረፍተ ነፍስ ወደ ኾነው ጌታ ምእመናኑን ማድረስ ሲገባቸው ወደ ራሳቸው ይስቧቸዋል። በዚህ ምክንያት ምእመናን የክርስቶስ ተከታዮች ሳይኾኑ የእነርሱ ተከታይና አድናቂ እንዲኾኑ፥ ክርስቶስን ሳይኾን እነርሱን እንዲመለከቱ፥ የሕይወታቸው ዋና ምሳሌም ክርስቶስ ሳይኾን አገልጋዮቹ እንዲኾኑ በማድረግ፥ ኢየሱስን ፈልገው የመጡትን ምእመናን ወደ ኢየሱስ ሳያደርሷቸው እነርሱ ዘንድ በማስቀረት የእነርሱ ሎሌ ያደረጓቸው አገልጋዮች ጥቂቶች አይደሉም። 

እንጠብቀዋልን ብለው ከጌታ በዐደራ የተቀበሉትን መንጋ የራሳቸው የግል ንብረት በማድረግ በተሳሳተ መንገድ ስለ መሩት፥ ብዙው ምእመን ወደ ቤተ ክርስቲያንም ኾነ ወደ መንፈሳውያን ጉባኤዎች የሚኼደው ክርስቶስን ለማየት ሳይኾን ተከታዮቻቸው ያደረጓቸውን አገልጋዮች ለማየትና ለእነርሱ ለመገበር ይመስላል። ይህ ለምእመናን ትልቅ ኪሳራ ለአገልጋዮቹም ከባድ ቅጣትን የሚያስከትል ዐደራ በልነት ነው።
ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ብቻ ሙሽራ ናት። ዘወትር ልትፈልግና ልትሻ የሚገባት ውዷን ኢየሱስን ብቻ መኾን አለበት። ጌታ ለሙሽራው ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን የሰጠው ለቤተ ክርስቲያኑ እንጂ ለአገልጋዮቹ ጥቅም እንዳልኾነም ሊታወቅ ይገባል። አገልጋዮቹ በቤተ ክርስቲያን ላይ እንዲሠለጥኑባት፥ ትልቅ ስምና ዝናን እንዲያገኙ፥ እንዲበለጽጉና የመሳሰለውን ምድራዊ ትርፍ እንዲያተርፉ አይደለም። ቃሉ እንደሚመሰክረው፥ ጌታ አገልጋዮችን ለቤተ ክርስቲያን የሰጠው፥ “ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መኾን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚኾን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይኾኑ ዘንድ” ነው (ኤፌ. 4፥12-13)። ስለዚህ አገልጋዮች ይህን ተረድተው ለተሰጣቸው ተልእኮ መፋጠንና ኀላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት አለባቸው።
ምእመናንም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የእነርሱ መጋቢዎች እንጂ አምላኮቻቸው እንዳልሆኑ ዐውቀው እንደ እግዚአብሔር ቃል የሆነውን ትምህርታቸውን ሊቀበሉ፥ የሕይወታቸውን መልካም ምሳሌነት ሊከተሉ፥ የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከቱ በእምነታቸው ሊመስሏቸው ይገባል። ከዚህ ዐልፈው እነርሱን በማክበር ስም ከማምለክ ያልተናነሰ ተግባር በመፈጸም የመጥፎ ሥራቸው ተባባሪ መኾን የለባቸውም። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኢየሱስን የሚሹ ምእመናን ኢየሱስን የሚያሳዩ አገልጋዮች በእጅጉ ያስፈልጋሉ።

ዐዲሱ ዓመት ጌታን የምንፈልግበት ጌታን የምናሳይበት ዓመት ይሁንልን
(በጮራ ቍጥር 46 ላይ የቀረበ)