" ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ፥" (ሮሜ 1:22)

my finger to you? (blogger)


                                ፍቅር ፍቅር ነው” ኦባማ

" እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ።" " እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው"
ሮሜ1፣27-28

ወንድ ከወንድ፤ ሴትም ከሴት ጋር ጋብቻ መፈጸም ይችላሉ፤ ለእነርሱ የጋብቻ ሠርቲፊኬት መከልከል ሕገመንግሥቱን ይጥሳል በማለት የአሜሪካው ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተመሳሳይ ጾታ ያላቸው መጋባት እንደሚችሉ ወሰነ፡፡ ለጋብቻ ቅድስናና ክቡርነት የሚከራከሩ “የእግዚአብሔርን ሕግ ምድራዊ ፍርድ ቤት ይህን መለወጥ አይችልም” በማለት ውሳኔውን አጥብቀው ተቃውመዋል፡፡ በምንም መልኩ ይገለጽ ፍቅር ፍቅር ነው በማለት ፕሬዚዳንት ኦባማ ውሳኔውን ደግፈዋል፡፡

 ዋናውን (ዓቃቤ ፍትህ) ጨምሮ ዘጠኝ የፍትህ ዳኞች የያዘው የአሜሪካው ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዚህ የሰዶማውያን ጋብቻ ላይ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ጉዳዩ ከቀረበለት ጊዜያት ተቆጥረዋል፡፡ በአሜሪካ የፍትሕ ሥርዓት ምዕራፍ ከፋች የተባለለት ውሳኔ አርብ ዕለት ሲተላለፍ የፍትሕ ዳኞቹ በአምስት ለአራት በመወሰን ነው ያጸደቁት፡፡ ይህ ጠባብ ልዩነት የታየበት ውሳኔ ሲተላለፍ አምስቱን ደጋፊዎች ወክለው አስተያየታቸውን የጻፉት የፍትሕ ዳኛ አንቶኒ ኬኔዲ ናቸው፡፡ እርሳቸውም ሲጽፉ “ከጋብቻ አንድነት የሚበልጥ የለም፤ ምክንያቱምታላቅ የሆነ ፍቅር፣ ታማኝነት፣ መስዋዕትነትና ቤተሰብን ያካተተ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለት ከመሆን ይልቅ አንድ በመሆን የሚገኘው ኅብረት ይበልጣል በማለት ሰዎች የጋብቻ ኅብረት ይፈጥራሉ” ብለዋል፡፡ ሲቀጥሉም “ይህንን ጉዳይ በተመለከተ አቤቱታቸውን ያቀረቡት እንዳሳዩት ጋብቻ ማለት ሞትን አልፎ የሚሄድ ፍቅር መሆኑን ነው፤ … እነዚህ ሰዎች የጋብቻን ክቡርነት ያቃልላሉ ማለት እነርሱን አለመረዳት ነው፤ እንዲያውን እነርሱ ጋብቻን እንደሚያከብሩ ነው በመማጸን የሚናገሩት፤ ጋብቻን በጣም ስለሚያከብሩ ነው ተፈጻሚነቱን በእነርሱ ህይወት ማየት የሚፈልጉት፤ ጥንታዊ ከሆኑ ተቋማት አንዱ ከሆነው ጋብቻ ተገልለውና በብቸኝነት ተኮንነው ላለመኖር ነው ተስፋቸው” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

 ውሳኔውን ከተቃወሙት የአራቱን በመወከል አስተያየት የጻፉት ዓቃቤ የፍትሕ ዳኛው ዮሐንስ ሮበርትስ ናቸው፡፡ እርሳቸው ውሳኔው በርካታዎች ሊያስደስት ይችላል ካሉ በኋላ ሲጽፉ “አብላጫውን ድምጽ የሰጡት ውሳኔ በጥልቅ ልብን የሚነካና ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው፤ ጋብቻ በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መካከል የሚፈጸም ኅብረት ነው የሚለው ዓለምአቀፋዊ ትርጉም በምንም ዓይነት መልኩ ታሪካዊ አጋጣሚ አይደለም፤ ጋብቻ በፖለቲካ ትግል፣ በግኝት መልክ፣ በበሽታ፣ በጦርነት፣ በሃይማኖታዊ ሥርዓተ ሕግ ወይም አንዳች የዓለምን ታሪክ ባናወጠ ኃይል የተከሰተ አይደለም፤ እንዲሁም ወንድና ወንድ ወይም ሴትና ሴት ተጋቢዎችን ለማግለል ተብሎ የተደረገ የቅድመታሪካዊ ውሳኔ ውጤትም አይደለም” ብለዋል፡፡ ሲቀጥሉም “ጋብቻ የተከሰተው ወሳኝ የሆነን ፍላጎት ለማሟላት ነው፤ ይህም ደግሞ ከእናትና አባት ልጆችን በመውለድ እነርሱን በተረጋጋ ሁኔታ ለማሳደግ ራስን አሣልፎ በመስጠት የህይወት ሙሉ ውሳኔ በማድረግ ነው” ብለዋል፡፡

የውሳኔው እንደምታ

የጋብቻን ክቡርነት የሚሰብኩና ጋብቻ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል መወሰን አለበት የሚሉ ወገኖች በዚህ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ክፉኛ ሃዘን ገብቷቸዋል፤ የወደፊቱም ሁኔታ አስግቷቸዋል፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ የሚከሰቱት ነገሮች ማኅበረሰቡን በእጅጉ የሚበጠብጡ እንደሚሆኑም ካሁኑ እየተነገረ ነው፡፡
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ሲያሳልፍ የጋብቻን ሃይማኖታዊ ገጽታ አልተመለከተም የሚሉ ወገኖች በተለይ መጽሐፍ ቅዱስ ሰዶማውያንን በተመለከተ የሚናገረውን ከሮሜ መጽሐፍ አንደኛው ምዕራፍ ላይ ያለውን ይጠቅሳሉ፡፡ “እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ። … ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵስነት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ … ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ (ከወንድ ጋር መገናኘት ትተው) ለባሕርያቸው በማይገባው (እርስ በርሳቸው በማድረግ) ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ። እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤ … ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ”፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን በዚህ ውሳኔ ምክንያት በርካታ ግለሰቦችና ተቋማትም አደጋ ላይ እንደሚወድቁ እየተነገረ ነው፡፡ ለምሳሌ በጋብቻ ሥርዓት ላይ አገልግሎት የሚሰጡ የሠርግ ኬክ ጋጋሪዎች፣ አበባ አዘጋጆች፣ የሠርግ ዕቅድ አውጪዎች፣ ፎቶግራፍ አንሺዎች፣ ወዘተ በእምነታቸው ምክንያት ለሰዶማውያን ጋብቻ አገልግሎት አንሰጥም በሚሉበት ጊዜ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ቅጣት የሚቀበሉ ይሆናሉ፡፡ በኮሎራዶ ጠቅላይ ግዛት አንድ ኬክ ጋጋሪ እንዲሁም በኒውዮርክ ግዛት የገጠር ቤታቸውን ለሠርገኞች የሚያከራዩ ለሰዶማውያን አገልግሎት አንሰጥም በማለታቸውና ግዛቶቹ የሰዶማውያንን ጋብቻ ያጸደቁ በመሆናቸው ፍርድቤት ቀጥቷቸዋል፡፡ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ ግን በየትኛውም ግዛት ቅጣቱ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ከአምሳዎቹ የአሜሪካ ግዛቶች 14ቱ በሰዶማውያን ጋብቻ ላይ ዕገዳ ያደረጉት ከአርቡ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ ዕገዳቸውን ማንሳት አለባቸው፡፡


“ተመሳሳይ ጾታ” ብሎ “ጋብቻ” የሚለው ቃል አብሮ አይሄድም በማለት የሚከራከሩ ወገኖች ጋብቻ የሚለው ቃል የሚውለው ለተቃራኒ ጾታ ብቻ ነው ይላሉ፡፡ ከዚህም ሲያልፍ የተቃራኒ ጾታዎች ግንኙነት ብቻ ነው ልጆችን ማፍራት የሚችለው ይላሉ፡፡ ሰዶማውያን ወይም ተመሳሳይ ጾታ ያላቸው ሲጋቡ የሚያፈሩት ልጅ የለም፡፡ ሴቶቹ ተጋቢዎች የወንድ ዘር ከዘር ባንክ በመግዛትና ውስጣቸው በህክምና በማስጨመር ቢወልዱም ወንድ ተጋቢዎች ግን በጉዲፈቻነት ሌሎች በተቃራኒ ጾታ ግንኙነት የፈጠሩትን ልጅ ወስደው ነው የሚያሳድጉት፡፡ ስለሆነም ሁለቱ ተጋቢዎች በተፈጥሮ ለመውለድ የማይችሉ በመሆናቸው በጥቅሉ ከሚታወቀው ጋብቻ እኩል ተደርጎ መወሰድ የለበትም ይላሉ፡፡ እንዲያውም የሰዶማውያን ጋብቻ የሰው ዘር እንደ ብርቅዬ እንስሳ እንዲጠፋ ድጋፍ የሚሰጥ ነው እስከማለት አጥብቀው ይከራከራሉ፡፡

ይህንን ውሳኔ ተከትሎ ካሁን በኋላ ሰዶማውያን የፈለጉትን ልጅ በጉዲፈቻነት ለማሳደግ ልክ እንደ አንድ ባልና ሚስት ፈቃድ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ይህ ፈቃድ በሰዶማውያን “ወላጆች” አድጎ በነርሱ መስመር የሚቀጥል ልጅ ለማሳደግና ሰዶማዊነት እንደ መደበኛ ተግባር እንዲቆጠር ለማድረግ በር ከፋች ይሆናል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ከሃይማኖታቸው አንጻር የሰዶማዊነትን ትክክለኛ አለመሆን የሚሰብኩ ካህናት በሰብዓዊ መብት ረገጣ እስር ቤት የሚጣሉበት ቀን ሩቅ አይሆንም፡፡ በየአምልኮ ቦታው የሚሄዱ ሰዶማውያን ልጆችን ከማስተማር ጀምሮ በአምልኮ ቤቶቹ አገልግሎት እንዳይሳተፉ መከልከል አይቻልም፡፡ በመሆኑም መጪው ትውልድ ከሥነምግባር አኳያ በትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን በአምልኮ ሥፍራዎችም የሰዶማውያን ጋብቻ ትክክል ነው በማለት እያመነ እንዲያድግ ይቀረጻል፡፡

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንደተሰማ ተቃውሟቸውን ያሰሙት የሉዊዚያናው አገረ ገዥ ቦቢ ጂንዳል ሲሆኑ እርሳቸውም ዘለግ ያለ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ ለመጪው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚወዳደሩት ጂንዳል “ውሳኔው ሰዶማዊነትን በመቃወም ሰዎች የሃይማኖት ነጻነታቸውን በገሃድ እንዳይለማመዱ ጥቃት የሚሰነዝር ነው” ብለውታል፡፡ ሲቀጥሉም “ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው የሕዝብ አስተያየትን በመከተል መሆኑ የሚያስደንቅ አይደለም፤ ሆኖም ውሳኔው ጠቅላይ ግዛቶች በሚያስተዳድሯቸው ግዛቶች ላይ የሚፈልጉት ሕግ እንዳያወጡ ወይም እንዳይቃወሙ መብታቸውን የሚረግጥ ነው፤ በመሠረቱ በአንድ ሰውና በአንዲት ሴት መካከል ጋብቻ እንዲሆን የመሠረተው እግዚአብሔር ነው፤ ማንኛውም ምድራዊ ፍርድ ቤት ይህን መለወጥ አይችልም” ብለዋል፡፡


የጠቅላይ ፍርድቤቱ ውሳኔ እንደተሰማ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በሰጡት መግለጫ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ “ፍቅር ፍቅር ነው” በማለት የተናገሩት ኦባማ የግብረሰዶማውያን ጋብቻ ሕጋዊ እንዲሆን በተለይ በሁለተኛው የአስተዳደር ዘመናቸው ጥረዋል፡፡ ውሳኔው “ለአሜሪካ ድል ነው” በማለት በወጣትነት ዘመናቸው ሰዶማዊ ነበሩ ተብለው በአንዳንዶች የሚታሙት ኦባማ በካሜራ ፊት አውድሰውታል፡፡


ኦባማ የሰዶማውያን መብት በአገራቸው ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም እንዲከበር አበርትተው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ባለፈው ምዕራብ አፍሪካን በጎበኙበት ወቅት ይህንኑ ጉዳይ አንስተው ያደረጉት ንግግር በአፍሪካውያን ዘንድ ተደማጭነት ያጣ ብቻ ሳይሆን የከረረ ተቃውሞም ገጥሞት ነበር፡፡ ሆኖም ግን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የአሜሪካ ሸሪክ በመሆን የአሜሪካንን ጥቅም ጎረቤት አገርን በመውረርም ሆነ ወታደራዊ ቤዝ በመስጠት የሚያስከብሩ የአፍሪካ አገራት በዚህ የሰዶማውያን መብት ጥበቃ ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ የሚለው አስተያየት ሲሰማ ይደመጣል፡፡ አሜሪካ የበጀት ድጎማ የምታደርገውም ሆነ አምባገነኖችን በጭፍን የምትደግፈው በምላሹ የምታገኘውን በማሰብ እንደሆነ የሚናገሩ ወገኖች አሜሪካ ገንዘቧ ሰጥታ ይፈጸምልኝ የምትለውን ሳታገኝ የምትቀርበት ምንም ምክንያት አይኖርም ይላሉ፡፡
ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያ ውስጥ እየተስፋፋ በመጣው የወሲብ ልቅነትና የሰዶማውያን ሁኔታ ሳይንሳዊ መረጃ ማቅረብ የሚያዳግትበት ቢሆንም ከውጭ ድጋፍና ተጽዕኖ ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ፓትሪሽያ ሃስላክ የሹመት ጥያቄያቸውን ለአሜሪካው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በማቅረብ በውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ፊት ቀርበው ሲመሰክሩ እንዲህ ብለው ነበር፤ “(የአምባሳደርነት ሹመቴ) ከጸደቀ በጾታ ላይ የሚደረግን ጥቃት እንዲሁም በግብረሰዶማዊያን ኅብረተሰብ ላይ የሚፈጸመውን መድልዖ አስመልክቶ እኛ (አሜሪካውያን) የምንከተለው የፖሊሲ አቅጣጫና ጥረት (በኢትዮጵያም እንዲሆን) የሚቻለኝን ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኔን እገልጻለሁ”፡፡


በሐምሌ ወር ማገባደጃ አካባቢ ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ ባለፈው ሰሞን መነገሩ ይታወሳል፡፡


(Golgul web news)

Share this article :

+ የተሰጡ አስተያየቶች + 1 የተሰጡ አስተያየቶች

Anonymous
July 11, 2015 at 2:00 AM

ደሰታ ላይ ነሃ::

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger