ክርስትናን አጋድመው ያረዱት..."


(ያሬድ ሹመቴ)

ከዚህ በታች የማስነብባችሁን ጽሁፍ ከዚህ ቀደም በጨርቆስ ተገኝቼ የሰማውትን በዚሁ መገናኛ መድረካችን ላይ አስነብቤያችሁ ነበር።
ከሰሞኑን በአሜሪካን ሀገር በግብረ ሰዶም ተግባር ላይ እጅግ አስነዋሪ የጋብቻ ህግ መጽደቁን ተከትሎ ልንነጋገርበትና መንፈሳዊ ምግብ እንሰንቅበት ዘንድ የመጋቢ ሀዲስ እሸቱን ስብከት ከመድረኩ የሰማውትን ለንባብ እንዲመች አድርጌ በማቀናበር በድጋሚ እነሆ ብያለው።
"ሰው ብቻ አትሁኑ" መ.ሀ.እሽቱ
"...ሰው ብቻ ማለት ምንድን ማለት ነው? ብዬ ሳስብ፤ የሚበላ፣ የሚጠጣ፣ በሚለብሰው ልብስ፣ በሚነዳው መኪና የኑሮን ስኬት የሚለካ ማለት ነው። እስከ ሞት የሚኖር ማለት ነው፦ እንደ እንስሳ።
"...ታላቁ ሊቅ ዮሀንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል 'ሰው እግዚአብሄር ሲለየው' ይላል። ሰው እግዚአብሄ ሲለየው፤ ጠባዩ እንደ አራዊት፤ አመጋገቡ እንደ እንስሳ፣ ሆኖ መልኩ ብቻ የእግዚአብሄር ሆኖ ይቀራል። በጣም ቀለል ባለ አገላለጽ ሲም ካርዱ የወጣ ሞባይል ማለት ነው። ጥሪ የማይቀበል። ለጉትቻ ማንጠልጠያ ብቻ የተሰራም ጆሮ አለ።"
"...እኔ በዕውነቱ ከተማው ፈርሶ እየተሰራ ነው እየተባለ አይናማዎቹ ሲያወሩም ሲያስወሩም እሰማለው። ፈርሶ መሰራት ያለበት የሰዉ አስተሳሰብ ነው።... የሰዉ አስተሳሰብ ፈርሶ ካልተሰራ፤ የተሰራ ከተማ ይፈርሳል። ጃፓንና ቻይና ሀገራቸውን ያለሙት መጀመሪያ አስተሳሰባቸውን አልምተው ነው። አስተሳሰቡ ያልለማ ህዝብ የለማውን ያወድማል።"
"...ምንድነው አሁን ያሳየሁዋቹ? (ትንሽ ጣታቸውን አውጥተው ወደላይ እያሳዮ) ይህች ጣት ብትታምም ሀኪም ቤት ብቻዋን ነው የምትሄው?... የማይመለከታቸው እነ ጉበት፣ እናፍንጫ፣ እነ እግር፣ አብረው ነው የሚሄዱት።"
"...ከረባት የሚታሰረው የት ላይ ነው?... አንገት ላይ የታሰረ ከረባት አካሄድን ይቀይራል። አሁን እግር ምን አገባው እውነት ለመናገር? (ከፍተኛ ሳቅ) ውድ መነጽር አይናቸው ላይ ያደረጉ ሰዋች አካሄዳቸውን ሁሉ ነው የሚቀየረው። አይን መነጽር ያደረገው መላ የሰውነት አካላትን ተክቶ ነው። ለዚህ ነው ታላቁ ሊቅ ዮሀንስ አፈወርቅ "እኛ የሰውነት ክፍሎች ነን ክርስቶስ ግን ራስ ነው" ያለው። ሰው እጁ ተቆርጦ ይኖራል፤ አይኑ ጠፍቶ ትኖራል። እራሱ ተቆርጦ ግን አይኖርም። እራስ ክርስቶስ ነው። እኛ ብንሞት (የሰማይ ህይወት) ይቀጥላል። የክርስትናው እራስ ክርስቶስ ስለሆነ።"
"ቤታችሁ ገብታችሁ እንድታጤኑት ነው። እነዛ... (ምንትስ) የምንላቸው ክርስቲያኖችን አርደዋል... ምዕራባውያኑ ደግሞ ክርስትናን እራሱን አርደውታል።....ወንድ ለወንድ፣ ሴት ለሴት፣ በቤተክርስቲያናቸው እያጋቡ፤ ክርስትናን አጋድመው ያረዱ ምዕራባውያን ናቸው። (ይህን ሁሉ ያመጣውም) የምዕራባውያን ልክ ያጣ ነጻነትና ገደብ ያለፈ ዝርክርክነት ነው።"
"እንደምታዩት እኔ አይነ ስውር ነኝ። ቀላል አይደለም.... እንክዋን ዘውትር ዓይን አጥቶ አንድ ቀን መብራት ሲሄድ ስንት እንደምታማሩ ታውቅታላችሁ። አንድ ቀን ግን አልቅሼ አላውቅም። ከሞት ወዲያ መብራት አለ። ከመቃብር በላይ መብራት አለ። ... ወደ መቃብር ሲወርድ ማንም ዓይነ ስውር ነው። ማንም አይኑ እያየ የተቀበረ የለም። ተስፋችን ግን ምንድን ነው? ከሞት ወዲያ ህይወት አለ። ከሞት ወዲያ ብርሀን አለ።"
"...አንድ አንድ ጊዜ እመኛለሁ። እማይረባ እማይረባ ነገር ስናይ (ዓይናችንን) የሚያጠፋ ቆጣሪ ቢኖር... መልካም ነገር እስክናይ ድረስ ለጊዜው የሚያጠፋ ቆጣሪ ቢኖር።
"አሁን እንደው ጆሮ በካርድ የሚሰራ ቢሆን ሀሜት እንሰማ ነበር?(ከፍተኛ ሳቅ)... የምንፈልገውን (ብቻ) አውርተን ስዊች ኦፍ እናደርገው ነበር። ስንት ዞማ ጸጉር ይዞ አስተሳሰቡ የከረደደ አለ።
"ጀርመን ሀገር ሄጄ ሲነግሩኝ፤ ባለ አምስት ኮከብ የውሻ ሆቴል አለ ተባለ። እኛ ሀገር አምስት ኮከብ ሆቴል ገብተው የበሉ ትንሽ ዝና (ሀብት) እና ትንሽ ስልጣን ያላቸው ናቸው። ማን ይገባል ከነሱ ውጪ። ግን ሰዋች ነን። የጀርመን ውሻ ዛሬም ውሻ ነው ለዘላለምም ውሻ ነው። እኛ ግን ሰው ነን።
እንደ ሰው አስቡ (ምዕመናን) በማርያም።"
" እስኪ እንደው ትዳራችሁን ገምግሙት ደስተኛ ናችሁ? እንደሰው እየኖራችሁ ነው? ሚስቶቻችሁን ታከብራላችሁ? ፖለቲከኞቹ የኪነጥበብ ሰዎቹ (እዚህ) አላቹ ሲባል ሰምቻለሁ። ቆም ብላችሁ ልታስቡ ይገባል።"
" እኛም የሀይማኖት ሰዎች ሰበክን ሰበክን፤ ስብከቱ የህዝቡን አመለካከት መቀየር ትቶ የኛን ኑሮ ቀየረ።(ከፍተኛ ሳቅ)... የሰበክነው ክርስቶስ ሳይታወቅ እኛ እንታወቃለን። ማስታወቂያ ሰርተው ዝነኛ የሆኑ ሰዎች አሉ። ምርቱ ተሽጠ? ወይስ አልተሸጠም?" (ከፍተኛ ሳቅ)
" ተርቦ ያበላን፣ በክራይ ቤት እየኖረ እኛን በቪላ ቤት ያኖረን፣ እሱ በግሩ እየሄደ ለኛ መኪና የገዛልንን፤ ዝነኛ ያደረገንን ህዝብ እኛ አመለካከቱን ልንቀይረው ይገባል። አለባበስን መቀየር ቀላል ነው አስተሳሰብን መቀየር ግን ዋጋ ያጠይቃል።"
"የግሪክ ፈላስፎች እነ ሶቅራጥስ የህዝቡን አመለካከር ለመቀየር ደከሙ። ዛሬ በኢኮኖሚ ውድቀት የምትንገላታ ግሪክ ናት፦ የነ ሶቅራጥስ ሀገር። 'ሀገር ሲያረጅ ጃርት ያፈራል' ይባላል። እኛ እንክዋን ይክበር ይመስገን ኢትዮጵያውያን ነን።"
"አሁንም ደግሜ እናገራለው። ይሄን ችግር ያደረሱብን ኢትዮጵያውያን አይደሉም። (እዚህ ያሉት) ጎረቤቶቻችንን እነ መሀመድ እነ ከድጃ... ስጋዎቻችን፣ ደሞቻችን፣ አካሎቻችን ናቸው።"
"ልብ ካለ ሊቢያ ሄዶ እናዛን መፋለም ነው። '... ቢያሸንፈው ወደ ሚስቱ ሮጠ' ይባላል። አንድ አንድ አባ ወራ አለ ቡና ቤት ሄዶ ከዚያ መልስ ቅዳ (ሂሳብ በኔ ነው) ይላል። (ሚስቱ) የወር ወጪ ስትጠይቀው፤ ጥጦ እንደተነጠቀ ህጻን የሚያለቅስ።"
"...ወቀሳ አበዛሁ?(የተሰበሰበው ህዝብ ከሳቅ ጋር አላበዙም አለ) ማርያምን?... ኮሶ የሚጠጣው ስለሚጣፍጥ አይደለም ስለሚያሽር(ስለሚያድን) ነው። ለመጣፈጥማ ስኩዋር ይሻል ነበር ግን ወስፋት ነው ትርፉ።" (ሳቅ)
"...የንጉሰ ነገስቱ የክርስቶስ አልጋ ወራሾች ነን... የደስታችሁ ልኬት የደስታችሁ ሚዛን ምግብና መጠጥ አይሁን፤ መኪናና ቤት ዝናንም አታርጉ። እኛ መለኪያችን ጽድቅ ነው። መከኪያችን መንግስተ ሰማያት ነው። ያ የምንገባበት ቤት ደግም የተዋበ፣ የደመቀ፣ መብራት ውሀ የማይሄድበት፤ 24 ሰኣት ክርስቶስ የሚያበራበት፤ 24 ሰኣት የህይወት ውሀ የሚጠጣበት፤ ሀብታም፤ ደሀ፣ተራሰው የማይባልበት፣ እገሌ ግባ እገሌ ውጣ የማይባልበት ቦታ ነው። ደህና እደሩ"
መጋቤ አዲስ እሸቱን ቃለ ህይወት ያሰማልን...
አሜን!
Share this article :

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger