Saturday, November 9, 2024
ስለሸኮናው ድፍንና ቅድ ክርክር መነሻው ከኦርቶዶክስ አጠቃላይ የወንጌል እውቀት ችግር የሚመነጭ ነው!
አባ በርናባስ የተባሉ ሊቀጳጳስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስተምህሮና በምእመናኖቹም ቅቡል የሆኑና እንደጽዩፍ የሚቆጠሩ የአህያና ተመሳሳይ እንስሳትን ጉዳይ አንስተው በሐዲስ ኪዳን ትምህርት ክልክል እንዳይደሉ ለማብራራት ሞከረዋል። ምሁርና ሊቅ ነኝ ባይ መንጋው የአቡኑን ትምህርት ለመቃወም ከዳር ዳር ለመጮህ አንካሳ ዶሮ አልቀደመውም። ከአፉ ለሚወጣው መራር ቃላት ግድ የሌለው መንጋ ስለአህያ ሥጋ ርኩሰት ለመናገር የቸኮለው የጽድቅ ጉዳይ አንገብግቦት ሳይሆን እንደፈሪሳውያን ሕጋችን ተነካ ከሚል አጉል ተመጻዳቂነት የመነጨ ነው። ሀገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ችግርና ኦርቶዶክስ እንደቤተ ክርስቲያን በውስጧ ሌባና ማጅራት መቺ አመራር፣ በውጪ ደግሞ በሰሜን የትግራይ፣ በመሐል የኦሮሚያ፣ በጎጃም የቅባት ወዘተ ሲኖዶስ እየተባለ ሊበታትናት ጎራ የለየበትን ችግር ከመፍታት ይልቅ የአህያ ሥጋ ይጣፍጣል! ወይስ ይመራል! ብሎ ለመከራከር መራኮቱ የሚያሳየን ቤተ ክርስቲያኒቱ በአዚም፣ በድንዛዜ ውስጥ እንዳለች አመላካች ይመስለኛል። ከዚህ ድንዛዜ የሚያወጣ ያልተጠበቀ መለኮታዊ ኃይል ካልደረሰላት በስተቀር ቤተክርስቲያኒቱ እንደሥጋ ደዌ በሽታ እየፈራረሰች ማለቋን የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ያየ ያስተውላል። የዚህ ታሪክ ጸሐፊ ከ10 ዓመት በፊት ስለቤተ ክርስቲያኒቱ አደጋ በሰፊው ጽፎ ነበር። ይህንን ሊንክ ከፍተው ያንብቡ!
1/ለውጥ አንድ
2/ለውጥ ሁለት
3/ለውጥ ሦስት
4/ለውጥ ዐራት
5/ለውጥ አምሥት
ወደተነሳንበት ርዕስ እንመለስ!
ለመሆኑ አህያ፣ ፈረስ ወይም አሳማ፣ ሸኮናው ድፍን፣ሸኮናው ቅድ፣ የሚያመሰኳ፣ የማያመሰኳ ይበላል፣ አይበላም ያለው ማነው? ኢትዮጵያ በሲና ተራራ ላይ ኪዳን የተገባላት የኪዳን ሀገር ናት ወይ? ብለን እንጠይቅ። መልሳችን አይደለችም ይሆናል። ኢትዮጵያ ከግብፅ፣ ከሱዳን፣ ከየመን ወይም ከሶሪያ የተለየች የኪዳን ሀገር አልነበረችም፣ አይደለችምም። ሙሴ የሕጉን ኪዳን በሲና ተራራ ላይ ከተቀበለበት አንስቶ በሰሎሞን ቤተመቅደሱ እስከታነፀበት ድረስ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ለ500 አመታት ያህል በጣኦትና በፀሐይ አምልኮ ስር እንደነበረች ታሪክ ይነግረናል። ታዲያ ባልኖረችበትና በሌለችበት ረጅም የእንቅልፏ ዘመን ውስጥ ልክ የብሉይ ኪዳንን ሕግ ተቀብላ ስትተዳደርበት የነበረች አድርጋ ስለሸኮና ድፍንና ቅድ የኦሪት ሕግ ለማውራት የሚጠይቃት የተለመደ ድፍረቷን እንጂ እውቀቷን አይደለም። ሲጀመር ከእግዚአብሔር ለኢትዮጵያ የተሰጠ የኪዳን ሕግ የለም። ሕግ ሁሉ ለእስራኤል ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን እውነት ይህንኑ ነው።
“ነገር ግን እናንተን፦ ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ ትወርሱአትም ዘንድ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር እሰጣችኋለሁ አልኋችሁ። እኔ ከአሕዛብ የለየኋችሁ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ።”
— ዘሌዋውያን 20፥24
ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር በዚህ ኪዳን ውስጥ ነበረች? ኧረ በጭራሽ! በተረትና እንቆቅልሽ PHD ሲኖርህ እንደዘቤ ደፋሩ የሌለህን እውቀትና ማስረጃ በ"ተረቴን መልሱ፣ አፌን በዳቦ አብሱ" ዘዴ ይሆንን ጎጋ ምእመን ታስጨበጭባለህ። ከየት እንደተማረው ባይነግረንም ከዘበነ ለማ በስተቀር የኦሪት ሕግ ለኢትዮጵያ መሰጠቱን ታሪክ አያውቀውም።
ንጉሡ ዳዊትም በመዝሙር እስራኤልን ለርስቱ የተመረጠ ሕዝብ እንደነበረ እንዲህ እያለ ሲዘምር እናገኘዋለን። ዳዊት የኢትዮጵያ ንጉሥ ሆኖ ያውቃል እንዴ? ዳዊት ለርስቱ እግዚአብሔር የመረጠው ሕዝብ ንጉሥ እንጂ የአህዛብ ንጉሥ አልነበረም። አህዛብ ግን ከእግሩ በታች ተቀጥቅጠው የተገዙ ባሪያዎች ነበሩ። መዝ 47፣3-4
አሕዛብን ከእኛ በታች፥ ወገኖችንም ከእግራችን በታች አስገዛልን። ለርስቱ እኛን መረጠን፥ የወደደውን የያዕቆብን ውበት።
ኦርቶዶክስ ወንጌል ገና አልገባትም ስንል በማስረጃ ነው። እሷ ግን 2000 አመቴ ነው ብላ እድሜዋን በመቁጠር የእውቀት ሁሉ ጫፍ እንደደረሰች ልትነግረን ትፈልጋለች። እኛ ደግሞ ድንጋይ ውሃ ውስጥ ለሺህ አመታት ስለኖረ ዋና ይችላል ማለት አይደለም እንላታለን። እድሜ ጥሩ ቢሆንም በራሱ ምሉዕና ባለእውቀት ያደርጋል ማለት አይደለም። የግእዝን ብሂል ስላጠኑ ብቻ የእውቀት ጫፍ የደረሱ የሚመስላቸው የተረት አባቶች ከእውነት እንደተፋቱ ዛሬም አሉ።
የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ አህያም። አሳማም፣ አንበጣም አይበላም። የማይበላው የተጠቀሱት ፍጥረታት እንደብሉይ ኪዳን ሕግ አትብሉ ስለተባለ ወይም በሐዲስ ኪዳን አስተምህሮ ርኩሳን እንደሆነ እንደተቆጠሩ ስለተማረ ሳይሆን የመብላቱ ባህልና ልምድ ስለሌለው ነው። እኔ አልበላም ማለት የሚበላ ሰው ቢኖር ረክሷል በሚል ኢ-ክርስቲያናዊ አስተምህሮ ከማነወር ነጻ ሰው ስለሆነ ነው።
ወንጌል እንደሚነግረን “የሚበላ የማይበላውን አይናቀው የማይበላውም በሚበላው አይፍረድ፥ እግዚአብሔር ተቀብሎታልና።”
ሮሜ 14፥3
የኦርቶዶክስ መምህራን ነን ባይ ከእውቀት የተፋቱ የተረት አባቶች በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተምታታ መልስ ሲሰጡ ተዉ እንጂ ብሎ የሚከለክላቸው የለም። ተሳስታችኋል ብሎ የሚያርማቸው ስለሌለ እንደፈለጉት እየተረጎሙ ስለ ሸኮና ቅድ፣ ሸኮና ድፍን፣ የሚያመሰኳ፣ የማያመሰኳ እያሉ ያልተሰጣቸውን ሕግ እየጠቀሱ የረከሰና ያልረከሰ ሕዝብ እያሉ ራሳቸውን ከጻድቃን ጎራ፣ የሚበላውን እንደኃጢአተኛ ፈርጀው ፍርድ ሲሰጡ ድንቁርናቸው አይሰቀጥጣቸውም። በሐዲስ ኪዳን ከልማድና ከወግ ካልሆነ በስተቀር የማይበላ ነገር የለም።
1ኛ ጢሞ 4:4-5
እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነውና፥ ከምስጋናም ጋር ቢቀበሉት የሚጣል ምንም የለም፤ በእግዚአብሔር ቃልና በጸሎት የተቀደሰ ነውና።
በዘንዶና በፀሐይ ታመልክ የነበረችው የአህዛብ ሀገር ኢትዮጵያ ያልተሰጣትን ሕግ እየጠቀሰች ቅድና ድፍን የምትለው ተረት ተረት ለእስራኤል የተነገረውን ቃል ወደራሷ እየተረጎመች ካልሆነ በስተቀር በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ውስጥ አህዛብ ማነው? ሕዝብስ? ብለን እንጠይቃታለን።
“አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤”
— ዘጸአት 19፥5
ከእስራኤል ውጪ ያለው ሁሉ አህዛብ ይባላል። አህዛብ ደግሞ የኦሪቱ ሕግ የኪዳን ሕዝብ አካል አይደለም። ስለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በሌላት የኪዳን ሕግ የሚበላና የማይበላ እያለች ስለኮሼር kosher” (כָּשֵׁר) ሕግ መናገር አትችልም። ከተናገረችም ከድንቁርና የተነሳ ነው። ከእስራኤል ውጪ የነበረው አህዛብ ይባላል። የአህዛብ ሀገር ኢትዮጵያ ስለሕግ ማውራት አትችልም።
ከሕጉ ውጪ የነበርነውን እኛን አህዛቦችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕጉን ትእዛዛት ሁሉ ፈፅሞ በሐዲስ ኪዳን ሕግ እንደአዲስ ወለደን።
ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ፣
“እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና፥ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና፤”
— ሮሜ 9፥4 ካለ በኋላ ከሕግ መሰጠት ውጪ የነበርነውን እኛ አህዛብን ወደአዲሱ የድነት ሕግ እንዴት እንደገባን እንዲህ እያለ ይነግረናል። "የምሕረቱ ዕቃዎችም ከአይሁድ ብቻ አይደሉም፥ ነገር ግን ከአሕዛብ ደግሞ የጠራን እኛ ነን። እንዲሁ ደግሞ በሆሴዕ፦ ሕዝቤ ያልሆነውን ሕዝቤ ብዬ፥ ያልተወደደችውንም የተወደደችው ብዬ እጠራለሁ፤ እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም በተባለላቸውም ስፍራ በዚያ የሕያው እግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉ ይላል። (ሮሜ9፣24-26)
ሕግን የተከተሉ እስራኤሎች ሕግን በመከተላቸው በእምነት ከሚገኘው ጽድቅ ጎደሉ። እኛ አህዛብ ደግሞ በሕግ ከነበረው ሥርዓት ውጪ ስለነበርን በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በማመን ከሚገኘው ጽድቅ የእምነት ተካፋይ ሆንን።
"እንግዲህ ምን እንላለን? ጽድቅን ያልተከተሉት አሕዛብ ጽድቅን አገኙ፥ እርሱ ግን ከእምነት የሆነ ጽድቅ ነው፤ እስራኤል ግን የጽድቅን ሕግ እየተከተሉ ወደ ሕግ አልደረሱም።" ሮሜ9፣30-31
ማጠቃለያ፣
ስለሕግ አፈጻጸም ዛሬ ማንም የመናገር መብት የለውም። ፊተኛውን አስረጅቶ ዛሬ በአዲስ ኪዳን ሕግ ውስጥ ነን። የቀደመችቱ ሕግ፣ ሕጉን ያፈረሰ ምን ይሁን ትላለች? በድንጋይ ተወግሮ ይገደል! ኦርቶዶክስ የቀድሞውን ሕግ በግድ እየተገብራለሁ ካለች ስንት ሰው ደብድባ ልትገድል ነው? አባ ባርናባስ ያስተማሩት እንደወንጌል ሕግ ስህተት ባይኖርባቸውም እንደኦሪት ሕግ አስፈጻሚዋ ኦርቶዶክስ አንድ ቀን የማደር መብት ሊያገኙ አይገባም ነበር። ሕጉ ይገደሉ ስለሚል። ዘቤ ለማ ምትክ አልባው የተረት አባት phd በተረት holder፣ ሄኖክ ኃይሌ በተረቱ ብዛት ምእመናን በባዶ ሜዳ ያሰከሩት ዲያቆን፣ መምህራነ ኮኑ በበደወሉ፣ ፊደላተ ዘኈለቁ ኵሉ የተባለላቸው ተረት ጠምጣሚ ሁሉ በማይመለከታቸውና በማያውቁት የኦሪት ሕግ በግድ ነው የሚጮሁት እውነቱን ስለሚያውቁ ሳይሆን ድንቁርናቸውን እንደባለእውቀት ትውልዱ ስላጸደቀላቸው ነው።
የእግዚአብሔር መንግስት አሳማ በመብላት አትጠፋም፣ ባለመብላትም አትገኝም። “የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና።”
— ሮሜ 14፥17
እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነውና፥ ከምስጋናም ጋር ቢቀበሉት የሚጣል ምንም የለም፤ በእግዚአብሔር ቃልና በጸሎት የተቀደሰ ነውና።
1ኛ ጢሞ4፣4-5 ስለዚህ በመብላትና ባለመብላት ራሷን ጻድቅ የምታስመስለው ኦርቶዶክስ ከ2000 ዓመት በኋላም ወንጌል ገና አልገባትም። በግሌ አሳማም፣ አህያም አልበላም። አልበላም አልኩ እንጂ የሚበሉት ተኮንነዋል፣ ረክሰዋልም ማለቴ አይደለም። የሚበሉትን አናረክስም፣ የማይበሉትንም ብሉ ብለን አንሰብክም። ወንጌል ስለመብልና መጠጥ አይደለችምና። አባ በርናባስ ያስተማሩት ምንም ስህተት ባይኖርበትም በመንጋ ለሚነዳ ምእመን ይህንን ማስተማር እንደወንጀል ስለሚቆጠር ስለመብልና መጠጡ ትተው መጀመሪያ ስለወንጌል የመዳን ቃል ይስበኩ። ኦርቶዶክሶች ወንጌልን በግእዝም፣በአማርኛም በልዩ ልዩ ቋንቋ ያነቧታል እንጂ አልተረዷትም! የዘሌዋውያን ሕግ እንኳን በኢትዮጵያ በዛሬይቱ እስራኤል የለም። የሌለውን ሕግ እንዴት አድርጋ ነው ኦርቶዶክስ የምትተገብረው? ዘቤ መልስልኝ። ሕጉ ካልተፈጸመ መውገሪያ ድንጋይህን ይዘሃል ወይ? ለነገሩ አንተ ራስህ የቤተክርስቲያኒቱ መርግ ነህ።
Subscribe to:
Posts (Atom)