Wednesday, August 26, 2015

በአመልካች ጣትህ ሌላው ላይ ስትጠቁም፤ ሦስቱ ጣቶችህ ይመሰክሩብሃል!





  አንዳንድ ሰዎች የራሳቸውን ግፍ፤ ዐመጻና ኃጢአት ለመሸፈን የአቻቸውን በደልና ዐመጻ በማቅረብ ለመደበቅ ይሞክራሉ። ነገር ግን የሌላው ሰው ዐመጻና በደል መቁጠር የራስን የኃጢአት ደብዳቤ አይፍቀውም። በየትኛውም ማእዘን የሚገኙ ዐመጸኞች ከዐመጻቸው እስካልተመለሱ ድረስ ዐመጻቸው ሰላማዊውን ሊያጠፋ ይችላል።  ከኋላ ይሁኑ ከፊት ዐመጸኞች የቆሙበት ሥፍራ ብቻውን ንጹሐን አያደርጋቸውም። ይልቁንም ሰላማዊው ላይ በሽታቸው እንዳይጋባ ቢቻል ሸክማቸውን በንስሐ እንዲያራግፉ ሊነገራቸው፤ ሸክሙ ተስማምቶናል ካሉም ራሳቸው ተሸክመው ገለል እንዲሉ ሊደረግ ይገባል።  ተፈጥሮ የሰጣትን ሁለት መልክ በመጠቀም ለማሳሳት ሞክራለች ተብሎ በምሳሌ እንደሚነገርላት የሌሊት ወፍ ከአይጦች ዘንድ ሄዳ ጥርሷን በማሳየት «እኔ የእናንተ ወገን ነኝ» ካለች በኋላ ከወፎችም ማኅበር ተቀላቅላ ክንፏን እያራገበች «የተከበራችሁ ወገኖቼ እንደምን አላችሁ!» እንዳለችው እንስሳ በሁለት ገጽ ለማታለል የሚሞክሩ የዘመኑ ተለዋዋጮች ራሳቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሸክም ሆነው ሳሉ የችግሯ ደራሽ ለመምሰል መሞከራቸው በዚህ ዘመን እንደማይቻል በግልጽ ሊያውቁት ይገባል።

   ሰሞኑን የምንመለከተው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደአዞ ሐረግ በጎን በቅሎ በዋናው ግንድ ላይ የተጠመጠመው በቅዱሳን ስም የሚጠራው ማኅበር ተራራ የሚያክል የራሱን ኃጢአትና ዐመጻ ላይደበቅ ሸሽጎ የሙስና ተዋጊና የቤተ ክርስቲያኒቱ አዳኝ ለመሆን ሲታትር እያየን ሲሆን በሞት የሚፈላለጋቸውንም ፓትርያርክ በማወዳደስ ላይ መጠመዱ «ቁርበት አንጥፉልኝ» የተባለውን ብሂል እንድናስታውስ አድርጎናል።

  እኛም ነገሩ ቢገርመን «አመልካች ጣትህን ስትጠቁም፤ ሦስቱ ጣቶችህ በራስህ ላይ ይመሰክሩብሃል» ልንለው ወደድን። ሙሰኞቹም፤ ማኅበሩም የቤተ ክርስቲያኒቱ ጠንቅ ከመሆን ባለፈ አንዳቸው የአንዳቸው አጣሪ፤ ጠቋሚና አባራሪ ሊሆኑ በፍጹም አይችሉም። ከዚህ በፊት በማኅበሩም ላይ ሆነ በነፍሰ በላ ሙሰኞቹ ላይ ተከታታይ ጽሁፍ በማቅረብ ሁሉ አጥፊዎች  መሆናቸውን በግልጽ ተናግረናል። አሁንም የምንናገረው ያንኑ በመድገም ነው። የምናሰምርበትም እውነት «ከማኅበሩና ከሙሰኞቹ የትኛው በመወገድ ሊቀድም ይገባል? የሚለው ካልሆነ በስተቀር በሁለቱም አላስፈላጊነት ላይ አንዳችም ብዥታ የለንም»

   ስለሆነም በማኅበሩ ላይ ከዚህ በፊት በፓትርያርኩ የተያዙ አቋሞች በሙሰኞች ማጥራት ሽፋን የሚታለፍ ወይም የሚቀየር ከሆነ ከሁለት ጅቦች መካከል አንዱን ጅብ ምርጫ የመውሰድ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመታደግ የሚደረግ እንቅስቃሴ አይደለም እንላለን። በመካከላቸው የመጠንና የዓይነት ካልሆነ በስተቀር ቤተ ክርስቲያኒቱን በሚግጡ ጅቦች መካከል የተግባር ልዩነት ስለሌለ ሁሉም ቦታቸውን ሊይዙ የሚገባቸው የጥፋት ኃይሎች መሆናቸው አያጠያይቅም። እንደምንመለከተው ያለው መገፋፋት በሦስት የሚከፈል ይመስለናል።

  1ኛው- ጫንቃው የደነደነ ማኅበር ከቦታው ሊወገድ የተገባው ቢሆንም  የተወሰኑ አስተዳዳሪዎችና ከታች ያሉ ዘራፊዎች፤ ቅዱስ ነኝ የሚለውን ማኅበር የሚጠሉት ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ስላደረሰው በደልና ግፍ በመቆርቆር ብቻ ሳይሆን በስለላ መረቡ ስለተጠለፉና እዳ በደላቸው ስለተጻፈባቸው፤ ከሚከተላቸው ፍርሃትና ድንጋጤ ለመገላገል ሲሉ በሐቅ ከሚታገሉት ጋር በኅብረት የሚጮኹ አንድ ቡድን ናቸው።

 2/ ማኅበሩ ቤተ ክርስቲያኒቱን መስሎና አኅሎ በላይዋ ላይ ነግሶ በስሟ መነገዱ የታያቸው፤ በመንገድ ላይ ቆሞ እንቅፋት የሆናቸው፤ ለስውር ዓላማው የስለላ ቡድኑን ያወቁ፤ የቤተክርስቲያኒቱን ልጆች ለራሱ መመልመሉ የቆጫቸው፤የገቢ አቅሙን እያደለበ፤ ሀብቷን ለራሱ ዓላማ ሲጠቀም የተመለከቱ፤ የኃጢአት በደል ጸሐፊ፤ ለሲኖዶስ ክፍፍል ረጅም እጅ ያለው መሆኑን የተረዱ በትክክል አምነው የሚታገሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች በሁለተኛ ረድፍ አሉ። ይህ ረድፍ ድምጹን የሚሰማና የሚያስተባብረው የበላይ አመራር ቢኖር ኖሮ ውጤታማ ሥራ ለመስራት የሚችልና በሙሰኛ አስተዳዳሪዎችም ይሁን በማኅበሩ ተግባር የመረረው ቡድን ነው ።

  3/ ራሱን ቅዱስ፤ ጻድቅና የቤተ ክርስቲያኒቱ መድኅን አድርጎ የተነሳ፤ በገንዘቡ፤ በኃይሉ፤ በአስተዳደሩ፤ በሴራ መዋቅሩና በእንቅስቃሴው አደገኛ የሆነ፤ የራሱን የሲኖዶስ አባላት ያደረጃ፤ ስለቤተክርስቲያኒቱ ሳይሆን ከጥቅሙ ጋር ለቆመ ሰይጣንም ቢሆን የሚተባበር፤ ሰዎችን በማጥመድ አገልጋይ ለማድረግ የሚተጋ፤ የሰዎች የእዳ በደል መዝጋቢ፤ ሰላይ፤ በዝሙት የረከሰ፤ ነጋዴ፤ አስመሳይና አታላይ ነገር ግን በሩቅ ሲያዩት ቆዳው ከእባብ የለሰለሰ ማኅበር፤ ማኅበረ ቅዱሳን የሚባለው በሦስተኛ ረድፍ አለ።
በዚህ መካከል ከወዲህም ከወዲያም የሚዘምቱ፤ ነገር የሚያማቱ፤ የሚያወሻክቱ፤ የአስመሳዮች ቡድን እንደወቅቱ ሁኔታ፤ ኃይል ወዳጋደለበት የሚያጋድሉ የአስተሳሰብ ድሆች ከሲኖዶስ ጀምሮ በየደረጃው ቢኖሩም ተጽእኖ ፈጣሪ ሆነው ለእክል የሚበቃ አቅም የላቸውም።

 በሦስቱ ረድፎች ያለውን የኃይል አሰላለፍ ተመልክቶ ተገቢ ከሆነው ወገናዊ ኃይል ጋር በመቆም እንቅስቃሴ መውሰድ የተገባ ቢሆንም እስካሁን ከወሬ ባለፈ የሚታይ እርምጃ ብዙም ሲወሰድ አይታይም።
ወቅቱ በፈጠረው የቤተክርስቲያኒቱ ተግዳሮትና የችግር እሳት መካከል የተገኙትት ፓትርያርክ ማትያስ ምን ዓይነት እርምጃ፤ መቼና ከማን ጋር ሆነው መውሰድ ይችላሉ? የሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚያሻው ወቅታዊ ጉዳይ ይመስለናል። አካሄዱን በሳተ፤ ውጤቱም ምን ሊሆን እንደሚችል ባልተጠና ውሳኔ የሚወሰድ እርምጃ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። ስለሆነም በገበያ ግርግር መካከል የሚዘለው ማኅበር የራሱን የቤት ሥራ ሳይጨርስ «ከፓትርያርኩ ጋር አለሁ፤ አለሁ» የሚለው ጉዳይ አሳሳቢ ነው።
ስለማኅበሩም ይሁን ማኅበሩን በሚደግፉ ነገር ግን ብዙ ችግር ባለባቸው ሰዎች ዙሪያ ትንፍሽ የማይለው «ሐራ» የተባለው ብሎግ የማኅበሩ ቀኝ እጅ ስለሆኑት አባ ማቴዎስ ለሙስና ውጊያ የመዘጋጀታቸውን ዜና መስራቱ እንዲሁም የፓትርያርኩን ፈቃደኝነት አደበላልቆ ማቅረቡ ችግሩን ለመቅረፍ ሳይሆን የማኅበሩን ጉዳይ ለመሸፈን አጋጣሚ ማግኘቱን የሚያመለክት ነው።
 ስለሆነም ለፓትርያርኩ የመፍትሄ ሃሳብ ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦችን ለመጠቆም እንወዳለን።

  1/ በቅድሚያ ፓትርያርኩ ብቻቸውን ተንቀሳቅሰው፤ ብቻቸውን ጮኸው፤ ብቻቸውን ታግለው የሚያመጡት ውጤት እንደሌለ በመረዳት የተሻለ ግንዛቤ፤ እውቀትና የአስተዳደር ክህሎት ያላቸውን የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር ግድ የሚላቸውን ሰዎች በሥራ አጋርነት በዙሪያቸው ማሰባሰብ ያስፈልጋቸዋል። ከጳጳሳቱም ብዙዎቹ በማኅበሩ የተጠለፉ ወይም ከሙስናና ከዘረኝነት ጋር የተሳሰሩ ስለሆነ ከጳጳሳቱም ሆነ ከበታች ሹማምንት መካከል ጥንቃቄ የታከለበት ምርጫ መደረግ አለበት። የፓትርያርኩ ልዩ ፀሐፊ፤ የፕሮቶኮል ሹም፤ የውጪ ግንኙነት ክፍል፤ የፓትርያርኩ ቢሮ ኃላፊ እና ሌሎች ተጨማሪ ክፍሎችን ማደራጀት ያስፈልጋል። የፓርትያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት በሆነው አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ ሥራ አስኪያጅ፤ የሀገረ ስብከቱ ፀሐፊ፤ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ወዘተ ክፍሎች ፓትርያርኩ ለሚያደርጓቸው ቀጣይ እርምጃዎች ወሳኝ ስለሆኑ ይህንን በተጠናና መልኩ እንደገና ማዋቀር የግድ ይላል። የፓትርያርኩ ጽ/ቤት የየዕለት የሥራ ውሎ ከበታች ክፍሎች ሪፖርት በመቀበልና ለፓትርያርኩ በማቅረብ ተከታታይ የሥራ መመሪያና ትእዛዝ በማስተላለፍ ያልተቋረጠ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል።

2/ እንደአጭር ጊዜ የማስተካከያ እርምጃ  ከላይ በተራ ቁጥር 1 በተመለከተው ነጥብ ውስጥ ያሉ አካሎችና ሌሎች አጋዦች ያሉበት አጣሪ ኮሚሽን በማዋቀር በሚያደርጉት ምርመራ በሙስና የከበሩ፤ ከሌላቸው ደመወዝና ልዩ ገቢ ውጪ ሃብት ያከማቹ፤ አላግባብ የበለለጸጉ፤ የገንዘብ ብክነትን ያስከተሉ አሰራሮች ሁሉ ዝርዝር መረጃቸውና ከነመፍትሄ ሃሳቦቻቸው በማቅረብ ማስተካከያና የሕግ እርምጃ በማስወሰድ በፍጥነት መግታት ተገቢ ወቅታዊ እንቅስቃሴ መሆን አለበት እንላለን። ነገር ግን እንደረጅም ግብ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ በፓትርያርኩ የሚመራ የመዋቅር ጥናትና ማሻሻያ መምሪያ በማቋቋም ከዘመናዊ አስተዳደር ጋር ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማዘመን የመዋቅር ማሻሻያ ጥናት መደረግ ይገባል። 

ከዚያ ባሻገር በማኅበሩ ግፊት፤ በአስፈጻሚ ጳጳሳቱ በኩል ሙስናን እናጣራለን ማለቱ «በቆሻሻ መጥረጊያ ቤት መወልወል ይሆናል»

3/ ማኅበረ ቅዱሳን ከዚህ በፊት እንደተወሰነው ሀብትና ንብረቱን እንዲያስመዘግብ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሞዴላ ሞዴሎች እንዲጠቀም፤ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ያለውን ሂሳብ በቤተ ክርስቲያኒቱ ኦዲት እንዲያስመረምር፤ ለወደፊትም በቤተ ክርስቲያኒቱ ተወስኖ በሚሰጠው ደንብ እንዲመራ የተላለፈውን ውሳኔ ያለምንም ማመንታት ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል። በዚህ ዙሪያ ፓትርያርኩ የገቡትን ቃል በመጠበቅ ማስፈጸም እንዳለባቸው እናምናለን።
ስለሆነም ስለሙስናና ስለገንዘብ ብክነት ለመናገር በዘረኝነትና በእከከኝ ልከክህ የተሳሰሩ የጥቅም ተጋሪ ጳጳሳቱና ከኋላ በሚገፋቸው ማኅበር ሳይሆን እጃቸው ንጹህ የሆነ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን የጣሪያ ሳር ያልመዘዙ ልጆችዋ በኩል በመሆኑ ፓትርያርኩ ቆም ብለው በአስተውሎት እንዲመለከቱት ልናሳስብ እንወዳለን። እርግጥ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ችግር ላይ ነች። ነገር ግን ችግሯን ተተግነው ደረስንላት የሚሉ ሁሉ የየራሳቸውን ስውር ዓላማ ደብቀው የተነሱ ስለሆነ ጥንቃቄ መወሰድ ይገባዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ 

በቅንነት የምንገልጽልዎ ነገር የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር የሚያንገበግባቸው፤ በታማኝነት፤ በፈሪሃ እግዚአብሔር ለማገልገል መንፈሳዊነቱም ፈቃደኝነቱም ያላቸው የተማሩ ልጆች ስላሉአት በጥንቃቄ አጥንተው ለቀጣይ እርምጃ እንዲበራቱ እንጠይቃለን። ማኅበሩም አጋጣሚዎችን ለራሱ በሚመቸው መልኩ እየተጠቀመ፤ የተወሰነበትን ውሳኔዎች ለማስቀልበስ የሚሄድበትን መንገድ ሊዘነጉ አይገባም። ቁርጠነቱ ካለ ሙሰኞችንም፤ ማኅበሩንም ቦታ ቦታቸውን ለማስያዝ ሰውም፤ ጊዜም፤ ኃይልም አለ!!