Saturday, August 22, 2015

ዘማሪት ዘርፌ ከበደ በማኅበረ ቅዱሳን ከተጠመደባት ወጥመድ በእግዚአብሔር ርዳታ ዳነች!


ባለፈው እሁድ ማለትም 10/12/2007 ዓ/ም በአዳማ ከተማ፣ በሥላሴ ቤተክርስቲያን፣ በተካሄደው ታላቅ ጉባኤ ዘማሪት ዘርፌ ከበደን በሕዝብ ሁሉ ፊት ‹‹በድንጋይ ወግሮ ማስወገርን›› ዓላማ አድርጎ ወደ ጉባኤው በነጎደው ማህበር ቅዱሳን ወጥመድ፤ እግዚአብር በችሎቱ ያዳናት፡፡ ይህ የጥፋት ማኅበር በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ጠብንና ሁከትን በምዕመናኑ መካከል የመፍጠር አጀንዳ ከመሸከሙ የተነሳ እንዲህ ዓይነት የወረደ አህዛባዊ ወጥመድ አጥምዶ በእግዚአብሔር ጉባኤው ውስጥ መግባቱ ለብዙዎች ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳን ያነገበ ጽንፈኛ ማህበር መሆኑን ፍንትው አድርጎ ያሳየ ሆኖል፡፡

    ዘማሪት ዘርፌ ከበደ በቤተክርስቲያናችን ደንብና ስርዓት በመዘመር በሕዝብ ሁሉ ፊት በአንድ ልብ በአንድ መንፈስ እግዚአብሔርን እያከበረች ባለበት ወቅት ነው፤ ባለ-ጊዜ በሆነ አንድ የማህበሩን ራዕይ በሚያራምድ ግለሰብ፤ መድረክ ላይ በእጇ የጨበጠችውን ማይክ በመንጠቅ፣ በግብዝነት በነሆለለ አዕምሮ ቢስነት በጥፊ ለመምታት ሙከራ ያደረገው፡፡ በሰዓቱ በሺዎች የሚቆጠር ምእመናን በመንፈስ መቃኘት ተወስኖ፣ በቅድስት ቤተክርስቲያን ዐውደ ምህረት ተሰባስቦ፣ የአንድነት የምስጋና ድምጽ ወደ ክቡር ዙፋን፣ ወደ ጸባኦት እንዲህ ሲል ይዘምር ነበር፡-

‹‹የማልደራደርበት የማልቀብረው እውነት፣ አንገት የማያስደፋ የማላፍርበት፣ ኢየሱስ የሚለው ስም እስትንፋሴ ነው፣ እውነቱ ይሄ ነው››፡፡ አስከትሎም ደግሞ በዚሁ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ኢየሱስን በሚያከበረው መንፈስ በመቀጣጠል ይሄው ሕዝብ፡- ‹‹የኔ ናርዶስ የኔ ቤዛ፣ በመዓዛው ልቤን ገዛ፣ ያንን መዳፍ ተመልክቼ፣ ተከተልኩት ሁሉን ትቼ"

 እያለ በአንድ ልብ እያመሰገነ ባለበት ቅጽበት ነው እግዚአብሔር ሲከብር በአንዳች ቁጣ የሚሞላው፣ በአንዳችም ሽንፈት ወራዳ ሥራን ሲሰራ የሚታወቀው፣ የጨለማው ዓለም ገዥ ዲያብሎስ በአደራጃቸው ጋሻ ጃግሬዎቹ በማኅበረ ቅዱሳን በኩል በስጋ አካል መዋጋት የጀመረው፡፡ በዚህ ሽብር መሐል ነው መጋቢ ምስጢር ቀሲስ ገብረሚካኤል የማነ በመነሳት ከወጋሪዎቿ እጅ ባላቸው የቤተክርስቲያኒቱ ስልጣንና አክብሮት በመንጠቅ ሥራ ተጠምደው ሳሉ፤ የአዳማ ከተማ ፖሊስ በስፍራው ደርሶ ዘማሪት ዘርፌን ከጽንፈኛው ማህበር ወጥመድ ያያዳኗት፡፡ መጽሐፍ እንደሚል፡- ‹‹ነፍሳችን እንደ ወፍ ከአዳኞች ወጥመድ አመለጠች። ወጥመድ ተሰበረ እኛም አመለጥን።›› መዝ 124፡-7፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የተመለከቱ፣ በዚህ አንካሳ ማኅበር ሽብር ክፉኛ ልባቸው የተሰበረ ምዕመናን ‹‹በጉባኤው ውስጥ በሐዘን እንባ ፊታቸው›› ሲታጠብ ተስተውሏል፡፡ ማህበረ ቅዱሳን የቤተክርስቲያን የወቅቱ ፈተናና መከፋፈል ምክንያት መሆኑ አሁን አሁን በግላጭ መታየት ጀምሯል፡፡

    እንዲህ ዓይነት የወረደ ግብር በማኅበረ ቅዱሳን ሁከት ፈጣሪነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናንና ብርቅዬ አገልጋዮቿ ላይ መፈጸሙ እንግዳ እንዳልሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ ለዛም ነው ብዙዎች የደብር አለቆችና ካህናት በአንድ ድምጽ ማኅበሩ ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳውን በቤተክርስቲያኒቱ ስም እየፈጸመ እንዳለ የመሰከሩትን በማስረጃነት በመጥቀስ ሆነ ብሎ ‹‹ቤተክርስቲያኒቱን በሽብር ለማናጥ እየሰራ›› ነው ሲሉ የሚከሱት፡:

    ከዚህ በፊትም ይሄው ማህበር ባሰለፋቸው ጨካኝ ወንቤዴዎቹ በመታገዝ፤ ግንቦት 8 ቀን 2005 ዓ/ም በቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን፣ የቀሲስ ሊቀ መዘምራን ትዝታው ሳሙኤልን ደም ማፍሰሳቸውንና በአምቡላንስም ለፈጣን ህክምና ሆስፒታል ድረስ ለመሄድ ተገዶ እንደነበር የምናስታውሰው ነው፡፡ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ቀሲስ ትዝታው ሳሙኤል በማኅበረ ቅዱሳን በኩል በቅድስት ቤተክርስቲናችን ላይ እየደረሰ ስላለው እኩይ ተግባር ለአባ ሰረቀ ብርሃን ያቀረበውን ግልጽ ጥያቄ  ማየት ይችላሉ፡-

    በቅርቡ አፍሪካ ሕብረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን፣ በሴኔ ወር 12 ቀን 2007 ዓ/ም እንዲሁ በደቀመዝሙር ዘማሪ ዲያቆን ከፍያለው ቱፋ ላይ ከፍተኛ ድብደባ መፈጸሙና ለቀናት ያክል በህክምና ሲረዳ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ ድብደባቸው ሳይሆን የሚገርመው ቅድስት ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ በማን አለብኝነት መፈንጨታቸና አገልጋዮችን እየደበደቡ ሞባይል ቀፎና ገንዘብ የመዝረፋቸው ነገር ነው የሚደንቀው፡፡

ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ዲያቆን ከፍያለው ቱፋን ደብድበው ከጣሉት በኋላ የ4500 ብር ስማርት ፎንና ገንዘብ ሰርቀው ሲያበቁ ‹‹አንተ ተሐድሶ፣ አንተ ጴንጤ፣ ደበደብንህ፣ ምንትሆን እንግዲህ›› እያሉ መንፈሳዊ መስለው መቆማቸው ነው፡፡ እግዚአብሔር ከዚህ ዓይነቱ አዕምሮ ቢስነትና ድንዛዜ የቅድስት ቤተክርስቲያንን ምዕመን ይጠብቅልን!
ይህን መረጃ ያቀበላችሁኝ የአዳማ ሥላሴ ቤተክርስቲያን መዘምራንን እግዚአብሔር አምላክ ይባርካችሁ! የጨለማውን ሥራ እንዲህ በብርሃን ጸዳል መግለጡ ተገቢ ነውና!
ከውስጥ አዋቂ ምንጭ