Thursday, January 5, 2012

የአባታችሁን ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ!



ደጀሰላምና አንድ አድርገን የተባሉ ብሎጎችን እንጠይቃለን
 

                              ወንጌል ደግሞ«የአባታችሁን ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ» ይላችኋል።ዮሐ ፰፣፵፬

(by dejebirhan)ይህንን ቃል የተናገረው የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ለፈሪሳውያን ካህናት ነበር። ጌታ የመጣው የታሰሩትን እንዲፈቱ፣ በሞት ጥላ ስር ያሉ ወደሕይወት እንዲመጡ ነበርና የመንግሥቱን ወንጌል በቃል እያስተማረ፣ ኃይሉንም በግብር እየገለጠ የመጣ የይቅርታና የምህረት ባለ ቤት መሆኑን አሳይቷል። ከዚህም ውስጥ አንዱ የሆነው ጉዳይ ፈሪሳውያን በዝሙት የተያዘችውን ሴት በክስ ወንበር አቁመዋት እንደሕጋቸው በድንጋይ ተወግራ የምትገደል መሆኑን ቢያውቁም ጌታችንን ሊፈትኑትና የሚከሱበትን ምክንያት ሲሹ ፈታኝ በሆነው መንፈስ እየተነዱ ዘማዊቷን ከፊቱ አቅርበው የሙሴ ሕግ ተወግራ ትገደል ይላል፣ አንተስ በሕግህ ምን ትላለህ? ብለው ሲጠይቁት «መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ። ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው» ዮሐ ፰፣፯
ኃጢአት ያልሰራ ማንም ፈሪሳዊ ካህን አልነበረምና ውልቅ ፣ውልቅ እያሉ እሱና ሴትየዋ በመቅረታቸው ፣ ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? ሲላት «አንድም» ብላ መለሰች፣ እሱም «ሂጂ፣ ከአሁን ጀምሮ ኃጢአት ደግመሽ አትስሪ» ብሎ በፈውስና በሰላም እንዳሰናበታት እናነባለን።
ጌታ ብርሃን በመሆኑ በጨለማ ላሉ ሊያበራ እንጂ በአንድም ስንኳ ሊፈርድ እንዳልመጣ፣ የሚፈርድበት በልጁ ባላመኑ ሁሉ ላይ አብ መሆኑን፣ ኢየሱስ ቢፈርድም እንኳን ፍርዱ እውነት እንጂ በዘማዊቷ ላይ ህግ ጠቅሰው ለመፍረድ እንደሚሹ ፈሪሳውያን እንዳይደለ፣ ለራሱ የሚመሰክር አባቱ መሆኑንና ራሱም ቢመሰክር ምስክሩ እውነት መሆኑን የሚገልጸው የወንጌል ቃል በሰፊው ተጽፎልን እናገኛለን።
ስለራስህ ራስህ እንዴት ትመሰክራለህ? እውነት አርነት ያወጣኋችል እንዴት ትለናለህ? አንተ አባቴ ብትል እኛስ አብርሃምን የሚያክል አባት አለን ብለው ሲሞግቱ በየዘመናቱ እንደተነሱት ፈሪሳውያን በዘመናችንም በተነገረው ዘላለማዊ ቃል ትንቢት ሆኖ የሚመሳሰሉበትን አንድነት  እንረዳለን። ይኸውም፣
1/ ስለኢየሱስ የሚመሰክረው አብ ነው። ራሱ ቢመሰክርም ምስክሩ እውነት ነው። ፈሪሳውያኑ ራሳቸው ህግ ጠቃሽ፣ ራሳቸው ፈራጅ፣ ራሳቸው ፈታኝ ሆነው ከሚታዩ በስተቀር አንድም የእውነት ምስክር የሌላቸው የኃጢአት ባሪያዎች ናቸው። ዮሐ ፰፣፴፬
2/ኢየሱስ በኃጢአት ላሉ መፈታትንና በሞት ጥላ ስር ላሉ መዳንን ሊሰጥ መጥቷል። ዘማዊቷን «ሂጂ፣ ደግመሽ ኃጢአት አትስሪ »ሲላትና በነጻ ከእስራት ሲያወጣት የያኔው ፈሪሳውያንም ይሁኑ የዘመኑ፣ በጨለማ የኃጢአት ዓለም ሳሉ አንድ ዘማዊ፣ ወይም በስጋ ድካም የሚሰራውን ብዙ ብዙ ኃጢአት እየጻፉ የሚከሱ፣ በድንጋይ ወግረው ለመግደል አደባባይ የሚቆሙ ናቸው። ምክንያቱም እነሱ «እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና» ዮሐ፰፣፵፬ በማለት ማንነታቸውን ገልጿል። ይባስ ብለውም ራሳቸው የሰይጣንን ስራ እየሰሩ ሳለ በተቃራኒው የራሳቸውን ግብር ለኢየሱስ ሰጥተው «አንተ ሳምራዊ እንደሆንክና ጋኔን እንዳለብህ እናያለን» ሲሉ ሰድበውታል። በእነሱ ዘንድ ሳምራዊ የሆነ ሰው ሁሉ ጋኔን አለበት፣ ከእነሱ ውጪ የተለየ ሃሳብም ያለው ጋኔን የያዘው ነው ማለት ነው። ዛሬም የዘር ውርስ ፈሪሳዊነትን የተረከቡት የሚጠሉትን አንተ ርኩስ ሳምራዊ ብለው ጎራ ይለዩበታል፣ ያለ የሌለ ኃይላቸውን ይዘው ይዘምቱበታል።
ከዚህ በላይ ያየነው የእግዚአብሔር ምርጦች ነን፣ የአብርሃም ልጆች ነን፣ የሙሴን ሕግ የምንጠብቅ ጥንቁቆች ነን እያሉ ነገር ግን እገሌ ተሃድሶ፣ እገሌ ሳምራዊ፣ እገሌ ሰዱቃዊ፣ እገሌ ደግሞ ኦርቶዶክሳዊ ነው በማለት እራሳቸው መርምረው፣ እራሳቸው መጽሐፍ ገልጠው፣ እራሳቸው በፍርድ ወንበር ተቀምጠው ከፈረዱ በኋላ አንደኛውን ወገን በድንጋይ ወግረው ለመግደል፣ የራሳችን የሚሉትን ወገን ደግሞ ከፍ ከፍ ሲያደርጉ ይታያሉ።
ያዕቆብ ፬፣፲፬«ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ነው፤ እርሱም ሊያድን ሊያጠፋም የሚችል ነው፤ በሌላው ግን የምትፈርድ አንተ ማን ነህ? »የሚለው ቃል እነርሱ ዘንድ አይሰራም።
ዛሬም በዚህ ዘመን ክርስቶስ የሞተለትን አንድ ደካማ ወይም ኃጢአት ያሸነፈውን ወይም እነሱ ላቆሙት ህግ አልገዛም ያለውን ሰው ክስ መስርተውበት በሕጋቸው ወግረው ለመግደል፣ ራሳቸው ለኃጢአት ባሪያ ሆነው ሳሉ፣ ሌላውን ጋኔን አለብህ የሚሉ፣ የአብርሃምን ስራ ሳይሰሩ አብርሃም አባት አለን የሚሉ፣ የአባታቸውን የዲያብሎስን ስራ እየፈጸሙ በክስ አደባባይ የሚያቆሙ፣ ስም የሚያጠፉ፣ የሚደበድቡ፣ የሚወነጅሉ፣ የሀሰት አባት ልጆች መሆናቸውን የሚመሰክሩ ፈሪሳውያን በዚህ ዘመንም ሞልተዋል። ከእነዚህም ውስጥ ግንባር ቀደሞቹ ማኅበረ ቅዱሳን፣ እንደዚሁም ዓይንና ጆሮ ሆነውለት የሚሰሩ ደጀሰላምና አንድ አድርገን የተባሉ በስም ስለሰላምና አንድ መሆን የሚመስሉ፣ በግብር ግን ሰላምና አንድነት እንዳይመጣ ሌሊትና ቀን የሚደክሙት ተጠቃሾች ናቸው። ይህም በማስረጃ ይረጋገጣል።ውድ አንባቢያን አስተዋይ ልቦና ኖሮን እንደእግዚአብሔር ቃል እውነቱን በማወቅ ለወንጌሉ ምስክር ልንሆን እንደሚገባን በአጽንዖት አሳስባለሁ!!
ከታች ያለውን አስረጂዎች ይመልከቱ።


አባ ፋኑኤል በቀድሞ ስማቸው አባ መልአኩ የሚባሉ ጳጳስ ስለመኖራቸው ብዙዎች በአካል ያውቋቸዋል። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ግን ከስማቸው ባለፈ ስለተባሉት ጳጳስ ቅርበት የሌለው ሆኖ የሚወረወርባቸው ድንጋይ ቢገርመው ብቻ እንደእግዚአብሔር ቃል ለመመልከት ተገዷል። እኚህ ሰው ጻድቅ ይሁኑ ኃጥእ መፍረድ የሰው ልጅ ድርሻ ባለመሆኑ ምስክርነቱ እውነት ለሆነው ለክርስቶስ መተው ወይም የክርስቶስ መንፈስ ለዳኝነት አስቀምጧቸዋል ለሚሏቸው ሲኖዶሳቸው ማቅረብ ሲገባ ወይም እነርሱን (እነደጀሰላም) ለዳኝነት የሾማቸው አካል ካለ በዚያ ሥልጣናቸው ተቀምጠው ከሙሴ መጽሐፍ እየገለጡ በድንጋይ ይውገሩ ወይም የመርገምን ስቅላት መበየንና ጉዳዩን እንደሕጋቸው መቋጨት ሲገባቸው፣ ሰውዬውን ከመሄዳቸው በፊትና ከሄዱም በኋላ ተከትለው የሚያሳድዷቸው ለምን ይሆን? ሲኖዶሳቸው ሲሰበሰብ ረብሻና ሁካታ የተቀላቀለበት ዘገባ፣ አንዱን አበሻቅጠውና ኮንነው፣ ሌላኛውን ክበውና አሞግሰው ታውከው የሚያውኩት ለምን ይሆን? ድረገጾቻቸው የሰላምና የአንድነት የሕይወት ቃል የሆነውን ወንጌል ከማስተማር ይልቅ የማይጨው ዘመቻ ማእከል የሚሆኑት ለምንድነው? የሚል እሳቤ ጽሁፎቻቸውን እንደወረደ በማስቀመጥ ሕዝቡ እንዲረዳ፣ እነሱም ልቡና ካላቸው የጻፉትን አይተው እንዲያፍሩና ንስሐ እንዲገቡ አቅርበነዋል። «ደጀሰላም» እና «አንድ አድርገን» የሚባሉት ድረገጾች አዲስ አበባና አሜሪካ ካሉ ቃል አቀባዮቻቸው ጋር በመተባበር እያደረጉ ያለውን የክስ ዘመቻ ከፈሪሳውያኑ ጋር የሚያመሳስላቸውን ነጥብ በነጥብ እንመልከት።
ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት ወር ሰብሰባ ተቀምጦ ነበር። በዚህም ስብሰባ ላይ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ብዙም መስማማት የማይታይባቸው አቡነ ፋኑኤል ማኅበረ ቅዱሳን በሌለበት ቦታ መድቡኝ እስከማለት መድረሳቸው ቀደም ሲል የተሰማ ነገር ነው። ከአዋሳ የተነሱትና ወደሰዋስወ ብርሃን የተዛወሩት፣ አሁን ደግሞ ወደምድረ አሜሪካ የሄዱት በሲኖዶሱ ውሳኔ ቢሆንም በማኅበረ ቅዱሳን እግር በእግር የሚከታተል ክስ እንደሆነ ሰምተናል። የሰማነው ግን እውነት ስለመሆኑ ደጀሰላምና አንድ አድርገን እየተቀባበሉ ሲዘግቡ መታየታቸው አረጋጋጭ ነው። ሃዋሳ ላይ በ400 ቴኳንዶዎች ይጠበቃሉ በማለት ለልዕለ ሀገራት አሜሪካ ፕሪዚደንት«ባራክ ኦባማ» ያልተደረገውን ሲጽፉ ሀፍረት የላቸውም። እንኳን ለአባ ፋኑኤል ለብቻቸው ይቅርና በጠቅላላው ቢቆጠር በደቡብ ክልል 400 ቴኳንዶ ይኖር ይሆን? ደጀሰላም ግን ቆጥሮ ይነግረናል።




ሲኖዶሱ አቡነ ፋኑኤልን ወደአሜሪካ እንደመደበ ሲሰማ ደግሞ ምድረ አሜሪካ የሰፈሩት ክርስቲያኖች ያሰሙት ነው የተባለውን ዘገባ እነዚህ ሁለት ብሎጎች ይዘው ብቅ አሉ። እኚህ ጳጳስ ምንም ይሁኑ ምንም ሲኖዶስ ጳጳስ ብሎአቸዋል፣ ጳጳስም ብሎ ሀገረ ስብከት ሰጥቶ መድቧቸዋል፣ አጥፍተዋል ብሎ ሲኖዶሳዊ እርምጃ ለመውሰድ ስልጣን ያለው ይኸው ሲኖዶስ የሚባለው አካል ነው። ከሃዋሳ ተዘመተባቸው፣ ሲኖዶሱ ወደሌላ ቦታ አዛወረ፣ ገና ከመድረሳቸው ቅድመ ወረራ ዜና ይሰራ ጀመር። እንዲህ ያለ ነገር የየት ሀገር ክርስትና ነው? እስኪ ይህንን ዘገባቸውን ተመልከቱት!!


>
በአንድ በኩል ሲኖዶስ የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ ነው የሚሉ፣ በሌላ መልኩ ደግሞ ሲኖዶስ ያለመንፈስ ቅዱስ እንደሚንቀሳቀስ በማመን ውሳኔአችሁን እንደገና በደንብ አጢኑ ማለት ከየት የተገኘ እውቀት ነው? የሲኖዶሱ ውሳኔ የሌላ አካል ማሳሰቢያ የሚገባው በራሱ በቂ ባለመሆኑ ነው? በደብዳቤ ይኸው መገለጹ ሳያንስ እኛ የቤተክርስርቲያኒቱ ዋና ተቆርቋሪዎች ነን የሚሉቱ ደጀሰላምና አንድ አድርገን ሲኖዶስ የተሳሳተ ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት ማጤን ያለበት እንደሆነ አምነው ደብዳቤውን በየብሎጋቸው ከጥሩ ማብራሪያ ጋር መዘገባቸው ምን ይባላል? አባ ፋኑኤልን እየተከታተሉ የክስና የስድብ ናዳ ሲወረውሩባቸው የሥልጣን አቻ ለሆኑት ሌሎች ጳጳሳት ደግሞ የድጋፍ ዘመቻ በተቃራኒው ጮኸው ሲያስጮሁ ይታያሉ። ይህን ይመልከቱ!


የሚገርመው ደግሞ ምድረ አሜሪካዎች የእንዳይመደቡ ጥያቄ በሲኖዶሱ ውድቅ ሆኖ አባ ፋኑኤል በእርግጠኝነት መመደባቸው ሲታወቅ ወደአሜሪካ እንዳይገቡ ደግሞ ዘመቻው ቀጣይ ሆኖ በሁሉም ወገን ሲሰራ ማየቱ አስገራሚ ነው። አባ ፋኑኤል ኃጢአተኛ ስለሆኑ ነው? ኃጢአተኛን የሚከስ ፈሪሳዊ እንጂ በክርስቶስ ክርስቲያን የሆነ አይደለም። አባ ፋኑኤል ማስተዳደር ካልቻሉ መወቀስ ያለበት ሲኖዶሱ አይደለምን? ተሃድሶ ሆነዋል ካሉ ምነው በደጋፊ ጳጳሶቻቸው በኩል ምንፍቅናቸውን አያስመረምሩም? ዘማቾቹ መዝመት ያለባቸው መንፈስ ቅዱስ ይመራዋል በሚሉትና ለመመደብ ስልጣን ባለው ሲኖዶስ ላይ እንጂ ሲኖዶሱ በላካቸው አባ ፋኑኤል ላይ መሆን አልነበረበትም። እነዚህ ሰዎች «እናንተ ሥጋዊ ፍርድን ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በአንድ ሰው ስንኳ አልፈርድም» ዮሐ 8፣15 ያለውን ቃል እየተገበሩት ይሆናል። ኃጢአተኛን የሚከስ ሁሉ ኃጢአተኛ ነው። «ኢየሱስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው» ዮሐ 8፣34
ይሄ የዘመቻና ኃጢአተኛን የመከታተል ማእበል ሰውዬውን ካላጠፋ እንደማይቆም እያከታተሉ ሲናግሩን እናገኛቸዋለን።




ጠንካራው አባታቸው አባ አብርሃም ያለቪዛ ተሰቃይተዋል፣ የመኖሪያ ፈቃድ እንዳያገኙ ተጉላልተዋል ስለሆነም እጄን አልሰጥም ብለዋል ብለው አግንነው ዜና እንዳልሰሩላቸው ያህል ቆይተው እጃቸውን ሰጥተው ሲኖዶስ ያለኝን አከብራለሁ ማለታቸውን አስነበቡን። ግሪን ካርድ ሳያገኙ ወይም ቪዛው ሳይታደስላቸው ምነው እጃቸውን ሰጡ? እንዴት ነው ነገሩ? ችግራቸው ተፈትቶ ነው እጃቸውን የሰጡት ወይስ ድሮም እሳቸው ያላሉትን እነደጀሰላም ኃይለኛ አባት እንዳላቸውና እንደማይደፈሩ ሊነግሩን ፈልገው ይሆን? የሆኖ ሆኖ ዘመቻው ከፋፍለህ ምታ ከመሆን ያለፈ አይደለም። ክሱ ዒላማውን ይምታም፣ አይምታም፣ መተኮስ የነዚህ ሰዎች እቅድ መሆኑን ከማሳየት የሚችሉትንና የሚመኙትን ሁሉ አድርገዋል። እጅ የማይሰጡት አባታችን እንዳላሉ ይኸው እጃቸውን ሲሰጡ ደግሞ የእጅ መስጠትን ዜና አለሳልሰው አቀረቡልን።


ሌላው የማኅበረ ቅዱሳን፣ ደጀሰላምም ሆነ አንድ አድርገን የውሸት ዘመቻ ማእበል ይጠብቃቸዋል፣ ሲኖዶስ ያጢን፣ ቀውጢ ይፈጠራል፣ መሬት ይቀደዳል እንዳላሉ ሁሉ አሜሪካ የሕግ አገር እና የማኅበረ ቅዱሳን ሲኖዶስ መብት እንደሌለው ስለሚታወቅ የአባ ፋኑኤልን መመደብ መስክረው እንዲህ ሲሉ ጽፈው ነበር። የዚህ ጽሁፍ አንባቢያን የተሰመረባቸውን የታችኛውን ሁለት ደብዳቤዎች ልብ ብለው እንዲመለከቱ እጠይቃለሁ።



በመጀመሪያ የዲሲና የካሊፎርንያ አኅጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ሆነው በሲኖዶስ መመደባቸውን በታህሳስ 6/2004 ዓ/ም ጽሁፋቸው ራሳቸው መስክረዋል። እንደገና ይህንኑ መራር ምላሳቸውን ክደው ለዲሲና ለአካባቢው በማለት... በታህሳስ 24/2004 ዓ/ም የአሜሪካውን ቡድናቸውን ደግፈው የተመደቡት ለካሊፎርንያና ለዲሲ አካባቢ ሳይሆን ለዲሲና ለአካባቢው ነውና ይባረሩልን ሲሉ ይገኛሉ። በአንድ አፍ ሁለት ምላስ ለምን? የሚያሳዝነው ሰውዬው ሁሉንም የድንጋይ ናዳ ተቋቁመው አሜሪካ ሲገቡ እንዲህ ሲሉ በገቡ ጊዜም እነዚህ ቤተክርስቲያናቸው ለሾመችው ሰው ክብር የሌላቸው ጳጳሱ ያላሉት እራሳቸው ፈጥረው ለማበሻቀጥና ለማዋረድ ምድረ አሜሪካ አጎዛ ለምንጣፍ እንደማይውል እየታወቀ አጐዛ አንጥፉልኝ እያሉ ነው ሲሉ ሲያዋርዱ ይታያሉ።


የአሳዛኝ ዘመቻው ጥቅል መጠይቅ፣

1/ ሃዋሳ ላይ እንደተዘመተባቸው መዘገቡን አይተዋል ? አራት መቶ የቴኳንዶ ዘብ እንዳላቸው መናገሩንስ አንብበዋል?

2/ አሜሪካ ያለው የደጀሰላም ክፍል አባ ፋኑኤል ወደ አሜሪካ አንዳይመደቡ ሲኖዶስ ያጤን ዘንድ ደብዳቤ መጻፉን ልብ ይሏል? ሲኖዶሱ ከመደባቸውስ በኋላ ወደአሜሪካ ካቀኑ ቀውጢ ይፈጠራል፣ ማለቱን ያስታውሷል?

3/ አባ አብርሃም እጅ እንደማይሰጡና እንደማይመለሱ አንብበዋል? ኋላስ ፓትርያርኩ ላቀረቡት የዝውውር ጥያቄ፤ ሲኖዶሱ ሲወስን እጅ ሰጥተዋል?

ይህ ሁሉ ዜናና ሽብር ለምን ይሆን?

ስናጠቃልል እነዚህ ሰዎች ምን እያደረጉና ምን እየሰሩ እንደሆነ አያውቁም። ምክንያቱም የሚያደርጉትን ሁሉ እንደጽድቅ ስራ ስለሚቆጥሩት የሚያስተውል ኅሊና የላቸውም። አንባቢም ይሁን አድማጭ ግን በዘመቻ ስማበለው ሆ እያለ የዘመቻውን ዓላማና ግብ ሳያጤን ከፈሪሳውያን ዘመቻ ቢቀላቀል፣

1/ የራስን ኃጢአት በመመልከት ንስሀ ከመግባት ይልቅ የሌላውን ኃጢአት እንደሚቆጣጠር ፈሪሳዊ መሆን ነው።

2/ እኛ የቤተክርስቲያን ፍሬዎችና የአብርሃም ልጆች ነን እያሉ ነገር ግን የአብርሃምን ስራ እንደማይሰሩ በስም ብቻ እንደሚመኩ ፈሪሳውያን መሆን ነው።

3/ሰውን መክሰስ፣ መወንጀል፣ኃጢአትና ጋኔን አለበህ ማለት የዲያብሎስ ልጆች እንደተባሉት ፈሪሳውያን መሆን ነው።

ስለሆነም እናስተውል፣ አስተዋይ ልቡና ይሰጠን ዘንድ እንጸልይ!

                                                               ወስብሐት ለእግዚአብሔር