Friday, January 27, 2012

ሕሙም እንዳይረዳ የተቃውሞ ዘመቻ!


የአቶ እንዳለ ገብሬን ሕይወት ለመታደግ የገቢ ማሰባሰቢያ መንፈሳዊ ጉባዔ ሊካሄድ ነው
"ማኅበረ ቅዱሳን" ጉባዔው እንዲካሄድ በመፍቀዳቸው ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስን ስም አጠራራቸው እስኪረሳ እንዲያልፉ እርግማን አወረደባቸው
ባደረበት የልብ ሕመም ምክንያት ውጭ ሀገር ሄዶ ካልታከመ በስተቀር የመዳን ተስፋው የመነመነው የአቶ እንዳለ ገብሬን ሕይወት ለመታደግ ከ450 ሺህ በላይ ወጪ የተጠየቀ ሲሆን፣ ቤተክርስቲያንን በማገልገል ላይ ያሉት መምህራንና ዘማርያን፣ በጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት አዳራሽ ጥር 20 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ ሰባት ሰዓት የሚጀምርና ገቢው ለዚሁ ወንድም መታከሚያ የሚውል መንፈሳዊ ጉባዔ አዘጋጅተዋል፡፡
ይህንን የተቀደሰና ሁሉም ወገን ሊረባረብበት የሚገባ ዕርዳታ በወንጌሉ ቃል መታጀቡና መመራቱ በዘልማድ ማኅበረ ሰይጣን የሚባለውና ራሱን "ማኅበረ ቅዱሳን" እያለ የሚጠራው ፈሪሳዊ ማኅበርን በማስኮረፉ ጉባዔውን ለማደናቀፍ በመውተርተር ላይ ይገኛል፡፡ ካለ እኔ በስተቀር ቤተክርስቲያን ልጅ የላትም የሚለው ይኸው ማኅበር፣ ልዩ ልዩ አቃቂሮችን በማውጣት ራሱ ፈራጅ፣ ራሱ ፈጻሚ በመሆን በምዕመናንና በቤተክርስቲያን መካከል እንደ ግድግዳ ቆሞ ማወክ ከጀመረ ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፣ ይህንኑ ጉባዔ ያዘጋጁት ለእርሱ ዓላማ አንገዛም ያሉ ሰባክያነ ወንጌልና መዘምራን በመሆናቸው፣ እንደተለመደው የተሃድሶ ታፔላውን ከፍ አድርጎ በማንሳት ያዙኝ ልቀቁኝ እያለ ነው፡፡(ዘመቻውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ)
ዘወትር ስድብና ዕርግማን ከአፉ የማይጠፋው "ማኅበረ ቅዱሳን" የወንድማችንን ሕይወት ለመታደግ ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ዕርዳታ እንዲያደርግለት በመማጸን ፈንታ በሲኖዶስ ያልታገዱትና ያልተከለከሉት ሰባክያንና ዘማርያን እንደታገዱና እንደተወገዙ አስመስሎ በማውራት ጠቅላይ ቤተክህነት አዳራሽ ለምን ተፈቀደላቸው ብሎ በመጮህ ላይ ነው፡፡ ይባስ ብሎም፣ "አንድ አድርገን" በተባለው ብሎጉ፣ ". . . ፈቃጆች ነገ ስም አጠራራቸው እስኪረሳ ድረስ ያልፋሉ. . ." በማለት ሆን ብሎ በስም ባይጠራቸውም ጉባዔው እንዲካሄድ የፈቀዱትን እነአቡነ ፊሊጶስን ወርፏል፡፡



"ጅብን ሊወጉ፣ በአህያ ይጠጉ" እንዲሉ፣ ማኅበሩ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስን የረገመው ቀደም ሲል የመምህር ዘመድኩን በቀለ ክስ ጉዳይ እንዲዘጋ የፈረሙትን ደብዳቤ "አልፈረምኩም፤ ክሱ ሊቀጥል ይችላል" ብለው በመካዳቸው የቋጠረውን ቂም የረሳ ለመምሰልና ጉባዔውን የፈቀዱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እንደሆኑ አድርጎ ለማሳመን ነው፡፡ ማኅበሩ በዚሁ የርግማን እሩምታው ". . . አቡነ ጳውሎስን እና መሰሎቻቸውን እግዚያብሔር ሀሳብ ድርጊታቸውን የሚያስታግስበት ጊዜ ሩቅ ነው ብለን አናስብም . . ." በማለት ራሱን ከቤተክርስቲያን በላይ አድርጎ በማስቀመጥ የስድብ አፉን ከፍቷል፡፡ የቤተክህነት አገልጋዮችን ማዕረግ በራሱ ሥልጣን በመግፈፍ መጋቤ ሀዲስ መባል ያለበትን አቶ ወይም በነጠላ ብቻ ስሙን በመጥራት፣ ብፁዕ ወቅዱስ መባል የሚገባቸውን አቡነ እያለ ተራ እና የመንደር ወሬውን ይዘራል-ለቃላቱ እንኳን ምርጫ የለውም፡፡
ከጠቅላይ ቤተክህነት አካባቢ ያገኘነው ማስረጃ እንደሚያሳየው ታማሚው ዕርዳታ እንዲደረግለት ባቀረበው ማመልከቻ ላይ ዕርዳታ እንዲደረግለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለበጎ አድራጎትና ዕርዳታ ሰጪ ክፍሎች የመሩለት ከወራት በፊት ሲሆን በመሩት ማመልከቻ ላይ የሚሰጠው ዕርዳታ መጠንና ዓይነት፣ እንዴት፣ ማን፣ የትና መቼ መሰጠት እንዳለበት ባልወሰኑበት ሁኔታ ያለሥራቸው ሲኮንናቸው፣ ". . . ለዚህ ሁሉ ስራቸው የጀርባ አጥንት ሁነው ስራቸውን የሚደግፉትን አቡነ ጳውሎስን እና መሰሎቻቸውን. . ." በማለት ረጅም ምላሱን አወናጭፏል፡፡
"ማኅበረ ቅዱሳን"፣ እንዲህ የሚወተውተው የሃይማኖት ጉዳይ ሆኖበት ሳይሆን የመድረክ ዕድሉን ላለማጣትና እግረ መንገዱንም የትርፍራፊ ሳንቲም ጥማቱን ለማርካት መሆኑን እንዲህ ሲል በ"አንድ አድርገን" ብሎጉ ፍንጭ ሰጥቶናል:- ". . . በፊት በወር 30 ቀን ሙሉ በውሎ አበል እየዞሩ እንዳይጨፍሩ ማድረግ መቻላችን ጥሩ ሆኖ ሳለ. . ."
ምንም እንኳ የጽሑፋችን ዋነኛ አጀንዳ አይደለም እንጂ ነገሩ ከተነሳ እንኳን 30 ቀን ለምን 365ቱም ቀናት ውሎ አበል አይበሉም? ደግሞም እኮ "የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሠር" ተበሎ ተጽፏል፡፡ አገልጋዮች የራሳቸው ኑሮ፣ የራሳቸው ሕይወት የላቸውም ያለው ማነው? ያለ እህል ውኃ መኖርስ ይችላሉ? መጓጓዣ ትራንስፖርት፣ ሰውነታቸውን በንፅሕና መያዝ አያስፈልጋቸውም ብሎ የሚደመድም ማነው? በቤቱ አስጠግቶ የሚያኖርስ ማነው? ይህንን ወጪያቸውን በግሉ ለመሸፈን የተዘጋጀ አለ? ወይንስ እነዚህ አገልጋዮች ሰዎች አይደሉም፤ ምንም አያስፈልጋቸውም? በከንቱ ለምን እንፈርዳለን? ለዚህም ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማኅበረ ቅዱሳን አስተሳሰብ የሚጓዙትን ፈሪሳዉያንን ሲገልጽ እንዲህ ያለው ". . . ከባድና ፅኑ ሸክም አሥረው ሰውን በትከሻው ያሸክሙታል፡፡እነርሱ በጣታቸው ስንኳ አይነኩትም. . . " (ማቴ. ምዕ.23፡4)፡፡ ድሮ አገልጋዮች የሚጓዙት በእግር ነበር፤ ለነፍሱ ያደረ በቤቱ አስገብቶ እህል ውኃ ያቀምሳቸዋል፡፡ መብራት አያስፈልጋቸውም፤ ለገላቸውና ለልብሳቸው ሳሙና አያስፈልጋቸውም፣ የኅብረተሰቡ ኑሮ እምብዛም የማይበላለጥ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ባለው ነገር ይረካል፡፡ የጥንቱን ወደዛሬ ገልብጠን እናምጣው ብንል አንችልም፡፡ ወንጌልን ያለ ወጪ ልናሠራጨው አንችልም፡፡ ሌላው ቀርቶ የወንጌል መርሐ ግብር መዘርጋቱን ማስታወቂያ እንንገር ብንል እንኳን ስንት ወጪ አለው? በቅንነት ካየነው የምናገኘው ትምሕርትና የነፍስ ድኅነት በ30 ቀን አበል ልንለካው አንችልም፤ ሞራላዊም አይደለም፡፡
ማኅበሩ ይህም ብቻ ሳይሆን በሚታወቅበት ፈሪሳዊ ክሱ አገልጋዮችን በስም ጠርቶ ተሃድሶዎች ካለ በኋላ በእነርሱና በጠቅላይ ቤተክህነት ግቢ ለምን ዕርዳታ ይደረጋል ሲል ቁጭቱን ገልጿል፡፡ የእንደነዚህ ዓይነቶቹን ሰዎች ልብ ክፋት ጠንቅቆ የሚያውቀው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ". . . ከመሥዋዕት ይልቅ ምፅዋትን እመርጣለሁ፡፡ ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኖሮ ያልበደሉትን ባልፈረዳችሁባቸውም ነበር . . . " ብሏቸዋል፡፡ ጌታ ይህንን ያለው ደቀመዛሙርቱ ሲርባቸው ከእርሻ መካከል እሸት ስለበሉ በሰንበት ለምን እሸት ቆርጠው ይበላሉ ብለው ፈሪሳውያን ስለከሰሱ ነበር፡፡ (ማቴ. 14፡1-7) ክርስቲያንን የሚያስደስተው ጾሞ፣ ነጭ ነጠላ ለብሶ ቤተመቅደስ ገብቶ ስላስቀደሰና መሥዋዕት ስላቀረበ ሳይሆን፣ የታመሙትንና የተቸገሩትን በመርዳት ነው-አራት ነጥብ፡፡
ጌታችን ስለ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን በማቴዎስ ምዕ.23 ላይ ያብራራው በትክክል "ማኅበረ ቅዱሳን"ን ይገልጻል፡፡ ". . . ከባድና ፅኑ ሸክም አሥረው ሰውን በትከሻው ያሸክሙታል፡፡እነርሱ በጣታቸው ስንኳ አይነኩትም. . . የሚሠሩት ሥራቸውን ሁሉ ለሰው ይምሰል ይሠሩታል፤ ክታባቸውን ይዘረጋሉ፤ የልብሶቻቸውንም ዘርፎች ያንዘረፍፋሉ፤ በግብዣም ጊዜ የራሰጌውን ወንበር ይመርጣሉ፤ በአደባባዮችም ፊት ለፊት መቀመጥን ይወዳሉ፡፡ ግብዞች፣ ጻፎችና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ትዘጉበታላችሁና እናንተም አትገቡም፤ የሚገቡትንም ከመግባት ትከለክላችኋላችሁ፡፡ ግብዞች፣ ጻፎችና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! አንድ መጻተኛን ለማጥመቅ ባህሩንና የብሱን ትዞራላችሁ፤ ከተጠመቀም በኋላ የናንተ ድርብ የገሃነም ልጅ ታደርጉታላችሁ . . . "
"ማኅበረ ቅዱሳን" በሰንበት ቀን ላሚቱ ወድቃ ብትሰበርበት ላለማንሳት ካለው ልዩ ባህርዩ የተነሳ የልጅ አባት ለሆነው አቶ እንዳለ ገብሬ ዕርዳታ እንዳይደረግ እና ምዕመናንም በዚህ እንዳይሳተፉ ለማድረግ የማያንኳኳው በር የለም፡፡ አሥራ ሰባት የሚሆኑ አባላቱም ወደ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ ቢሮ በመሄድ ጉባዔውን እንዲያስቆሙ፣ ይህ ሳይፈጸም ከቀረም በጥቅምቱ ሲኖዶስ ጉባዔ መጀመሪያ ዋዜማ ዕለት በቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን እንዳካሄዱት ረብሻ እንደሚያውኩ ዝተዋል፡፡
የሆነው ሆኖ፣ "ዶሮ በተነች ተብሎ ጾም አይታደረምና" ዝግጅቱ በሰፊው እንደቀጠለ ነው፡፡ በ"ማኅበረ ቅዱሳን" ድርጊት የተበሳጩ የአዲስ አበባ ምዕመናንም በማኅበሩ እየተካሄደ ያለውን እኩይ እንቅስቃሴ አውግዘው፣ ለታማሚው አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ ናቸው፡፡ በሞባይል ስልኮች በቁጥር 8512 የሚደረገው የብር 1.50 ገቢ ማሰባሰብ ጥረትም አመርቂ ውጤት እያስገኘ ነው፡፡ አዘጋጆቹ ሰፊ ሕዝባዊ መሠረትና የቤተክርስቲያን ድጋፍ ያላቸው በመሆኑም ከክልል እና ከአቅራቢያ ከተሞች በብዛት ወደጉባዔው ሄደው ያላቸውን ልግሥና እንደሚያደርጉ ይታመናል፡፡
የዚህ ብሎግ ዝግጅት ክፍልም ምዕመናን የጉባዔውን የተቀደሰ ዓላማ በመገንዘብ እጃቸውን በሰፊው እንዲዘረጉና ለታማሚው እንዲደርሱለት ወገናዊ ጥሪውን እያስተላለፈ፣ ወንድማችን እንዳለ ገብሬም ከሕመሙ ተፈውሶ በእግዚአብሔር የተደረገለትን ምሕረትና ፈውስ በዐውደ ምሕረት ላይ ለመመስከር ያበቃው ዘንድ ልባዊ ምኞቱን ይገልጻል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
ወለወላዲቱ ድንግል!!!
ወለመስቀሉ ክቡር!!!
ይቆየን
Posted by Dejeselaam at 5:24 AM dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com