Sunday, January 29, 2012

«ገና በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ እንድትታረቅ ትጋ»ሉቃ 12፣58

ከዚህ ቀደም ስለእርቅ ጉዳይ በተነሳ ሃሳብ ዘመድኩንን ኃያልና የማይንበረከክ ክንድ ባለቤት እንደሆነ አጋኖ ደጀሰላም ብሎግ ዘግቦ ነበር። ዘመድኩንም ሲኦል ብወርድ እንኳን ከበጋሻው ጋር እርቅ አይሞከርም በማለቱም ተገርመን አስተያየት ጽፈን በደጀሰላም ላይ አስነብበናል። ሰጥተን የነበረውም አስተያየት ከላይ የሰጠነውን ርእስ መሰረት ያደረገ ነው። በወቅቱ የሰጠነውን አስተያየት እንዳለ አቅርበነዋል፣
«Anonymous said... ከሳሽንም ተከሳሽንም በደንብ አውቃቸዋለሁ። ወደ ዝርዝር ብንገባ ከአምላክ የሚያጣላ ይሆናልና ተከድኖ ይብሰል። የሆኖ ሆኖ ፍርድ ቤት ስለምስጢረ ሥላሴ ሳይሆን ስለስመ ማጥፋት ወንጀል የቀረበ ክስን እያየ እንደሆነ ከክሱ ጭብጥ ስንረዳ ከሳሽና ተከሳሽ ክርክሩን በእርቅ ቢጨርሱት 1/ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉ ። 2/ሃይማኖተኞች ሃይማኖት በሌላቸው(ዓለማውያን) ፍርድ ቤቶች የሚያደርጉት ክርክር ሃይማኖቱን ያስነቅፋልና ይህንን ለማስቀረት 3/የበደሉንን ይቅር ማለት ስለሚገባን ዘመድኩን ዕርቅ አልቀበልም ማለቱ እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊ መሆኑን ሳይሆን የሚያመለክተው አለማወቁን፤ ግብዝነቱንና የታይታ ክርስቲያን መሆኑን እንጂ የክርስቶስ ልጅ መሆኑን አይደለም። ክርስቶስ ፍርድ ቤት ይለያችሁ ሳይሆን ያለው ከባላጋራህ ጋር አስቀድመህ ታረቅ ነው ያለው። እኔ ከአንድ እስላም ጋር ብጣላና ብታረቅ በሰውነቱ እንጂ የሱን ሃይማኖት ለመቀበል ስላልሆነ ዘመድኩን እሱ ከበጋሻው ጋር ታረቀ ማለት እሱ እንደሚለው ተሃድሶ ሆነ ማለት አይደለም። የሚያሳብቅ ውሸት መሆኑ ደግሞ ሲዖልም ቢሆን እወርዳለሁ በማለት አንድ ክርስቲያን በህይወት ዘመኑ ዕድል ፈንታውና የፍርድ ዕጣው በፍጹም ሊሆን ቀርቶ ሊመኝ የማይገባውን መናገሩ አሳዛኙ አባባል ነው። እውነተኛ ክርስቲያን ነኝ ለማለት ማረጋገጫና ሌላውን የማሰመኛ ቃል አድርገን ሲዖልም ቢሆን እወርዳለሁ ማለት ከየት የተገኘ ትምህርት ነው። እኛ እድል ፈንታችንና መንፈሳዊ ፍላጎታችን መቼም ቢሆን ከክርስቶስ ጋር መኖር ነው እንጂ ሲዖልም ቢሆን ወርደን የምናረጋግጠው እውነተኛነታችን ስለሌለ ይህንን ቃል ከመጠቀም(ሎቱ ስብሐት)እንላለን። ሳጠቃልል ዘመድኩን የምትረታ መሆንህን ብታውቅ እንኳን ከፍርድ ቤት ክርክርና ጭቅጭቅ በኋላ ከምታገኘው የረቺነት ኃላፊ ጠፊ ዝና ይልቅ ለክርስቶስ ብለህ ሁሉን ትተህ የምታደርቀው እርቅ ብዙ ኃጢአትህን ይሸፍናል፤ ሰማያዊ ክብርንም ያስገኝልሃልና ከልብህ መክረህ ታረቁ የሚሉ ሽማግሌዎች ካሉ ወደመጡበት አትመልስ ወንድማዊ ምክሬ ነው። September 10, 2011 12:37 PM የሚል አስተያየት ሰጥተን የሰማን የለም።
የያኔውን የደጀሰላም ብሎግ «ወደፊት በሉለት ይለይለት» ሙሉ ጽሁፍን ለማንበብ ከፈሉጉ (እዚህ ላይ ይጫኑ)
  አሁን ደግሞ «ደጀሰላአም» የተሰኘ ብሎግ በወቅቱ ብለነው የነበረውን አስተያየት የሚያጠናክርና የክሱ ሂደት የፈራነው ግምት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ከታች አስነብቦናል። መልካም ንባብ!


እንደገመትነውም ዘመድኩን በቀለ የመከላከያ ምስክሮቹ ሊያድኑት አልቻሉም።
ዳንኤል ክብረት ራሱን "የቤተክርስቲያን ተመራማሪ" ብሎ እንደሰየመ በይፋ አመነ በተከሳሹ ላይ የሚተላለፈው የመጨረሻ ውሳኔ ለየካቲት 27 ቀን 2004 ዓ.ም ተቀጠረ።
በመጋቤ ሀዲስ በጋሻው ደሳለኝ እና በዘመድኩን በቀለ መካከል ባለው ክርክር፣ ዘመድኩን ጥር 18 ቀን 2004 ዓ.ም የመከላከያ ምስክሮቹን አቅርቦ አሰምቷል፡፡ ተከሳሹ ዘመድኩን ቀደም ሲል ያቀረብንላችሁን ዘገባ ሌሎች አካላትም ስላማከሩት ይመስላል፤ ዲ/ን ደስታ ጌታሁንን እና ዘሪሁን ሙላቱን አያዋጡኝም ብሎ በመገመቱ በሌሎች ምስክሮች ተክቶ አቅርቦአል፡፡ በዚህ መሠረት አንደኛ የመከላከያ ምስክር ሆነው የቀረቡት መምህር ደጉ ዓለም የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሀዲስ ኪዳን መምህር ሲሆኑ፣ ለምን እንደመጡ ሲጠየቁ "አላውቅም" ብለዋል፡፡ "የመጡበትን ካላወቁ ለምን ፍርድ ቤት ድረስ ሊመጡ ቻሉ"? ተብለው ሲጠየቁ፣ "ዘመድኩን እንድመሰክርለት አምርሮ ስለተማፀነኝ ነው፤ ይሁን እንጂ የክሱ ጭብጥ ምን እንደሆነ አላወቅሁም" ብለዋል፡፡ ዘመድኩን አሳትሞ ያሠራጨውን አርማጌዶን ቪሲዲ ተመልክተውታል ወይ? ሲል ዐቃቤ ሕጉ ላቀረበላቸው ጥያቄ "አልተመለከትኩትም" ብለዋል፡፡ መጋቤ ሀዲስ በጋሻው ደሳለኝንስ ያውቁታል ወይ? "አዎን አውቀዋለሁ"፡፡ "የት ያውቁታል"? "በቤተክርስቲያን ሰፊ ተደማጭነት ያለው ሰባኪ መምህር መሆኑን አውቃለሁ"፡፡ "ዘመድኩንንስ ያውቁታል ወይ"? "አዎን"! "የት"? "ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የማታ ተማሪ ሳለ አውቀዋለሁ"፡፡ "በሁለቱ መካከል በስም ማጥፋት ወንጀል ስላለው ክስ ያውቃሉ"? "አላውቅም"፡፡ "ለመሆኑ አንድ ሰባኪ ሌላውን ሰባኪ ወይም አንድ አገልጋይ ሌላውን አገልጋይ በትምህርቱ እና በአገልግሎቱ በሕዝብ ፊት ለመተቸትና ለማጣጣል ይችላል ወይ"? "በፍጹም አይችልም፡፡ መተቸትና ማጣጣል ለማንም የተሰጠ መብት አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር ዘመድኩን መጋቤ ሀዲስ በጋሻውን ለመተቸትም ሆነ ለማጣጣል መብቱም ብቃቱም የለውም፡፡ አንድ አገልጋይ ስህተት ቢኖርበት የሚያርመውና እርምጃ ሊወስድ የሚችለው በሊቃውንት ጉባዔ በኩል ቅዱስ ሲኖዶሰ ብቻ ነው" በማለት መልሰዋል፡፡ ሁለተኛ የመከለከያ ምስክር ሆኖ የቀረበው ዳንኤል ክብረት መጋቤ ሀዲስ በጋሻው ደሳለኝን ከመቼ ጀምሮ እንደሚያውቀው ሲጠየቅ፣ ከሁለት ዓመት ወዲህ መሆኑን ገልጿል፡፡ "በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለ ቀርቶ ማንም ሰው ከሰባት ዓመታት ጀምሮ ያውቀዋል፡፡ አንተ እንዴት ከሁለት ዓመት በፊት አላውቀውም ትላለህ"? "በጭራሽ አላውቀውም"፡፡ "ዘመድኩን በመጋቤ ሀዲስ ላይ ባወጣው አርማጌዶን የዘለፋ ቪሲዲ አጥፍቷል ትላለህ? ወይንስ አላጠፋም"? "በፍጹም ጥፋት የለበትም"፡፡ "ከመንበረ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት ማንም ሰው ተነስቶ ሌላውን በአስተምህሮ ጉዳይ እንዳይተች ሐምሌ 25 ቀን ለየቤተክርስቲያኑ ሠርኩላር ተላልፏል፡፡ ከዚህ አንፃር ዘመድኩን መስከረም 21 ላይ ባወጣው ቪሲዲ መመሪያውን አልተላለፈም ትላለህ"? "ይህ መመሪያ ዘመድኩንን አይመለከትም፡፡ መመሪያው የወጣው እነ በጋሻው ማንንም እንዳይተቹ ለማገድ ነው"፡፡ "ስለ ሥራህ በፍርድ ቤቱ ስትጠየቅ "የቤተክርስቲያን ተመራማሪ ነኝ" ብለሃል፡፡ ለመሆኑ ይህንን ሥልጣን የሰጠህ ማነው"? "አአይ! እኔ በግሌ ነው የምመራመረው እንጂ ሌላ አካል ሥልጣኑን አልሠጠኝም"፡፡ "ቅድም ስንጠይቅህ መመሪያው ዘመድኩንን አይመለከተውም ብለሃል፡፡ ዘመድኩንን የማይመለከትበት ልዩ ምክንያት ለፍርድ ቤቱ ብታስረዳ"፤ ዳኒ ይሄኔ ፀጥ አለች፡፡ "መልስ እንጂ ጥያቄ እኮ ነው የቀረበልህ" አሉ ዳኛው፡፡ ዳኒ ፀጥ . . . ሦስተኛው ምስክር አባ ወልደ ጊዮርጊስ ሲሆኑ እርሳቸውም የወላይታ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በእርሳቸው የምሥክርነት ክፍለ ጊዜ መላው የችሎቱ ታዳሚ ሳቅ በሳቅ የሆነበትና የተዝናናበት ነበር፡፡ በተለይም አባ፣ አንዳንድ መስቀለኛ ጥያቄ ሲቀርብላቸው የተምታታ መልስ በመስጠት ጎል እንዳይቆጠርባቸው ለመጠንቀቅ፣ "ጥያቄው ይለፈኝ" በማለት ሲመልሱ "ይህ እኮ የቴሌቪዥን ጥያቄና መልስ ውድድር አይደለም፤ ለሚጠየቁት ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ይስጡ" የሚል ተግሳጽ ተሰጣቸው፡፡ "አባ! ለመሆኑ መጋቤ ሀዲስ በጋሻውን ከመቼ ጀምሮ ነው የሚያውቁት"? "ከአንድ ዓመት ወዲህ"፡፡ "ምነው በሀገረ ስብከትዎ እየተዘዋወረ የሚያስተምርን ሰው እንዴት ከአንድ ዓመት በፊት አያውቁትም"? "በቃ! አላውቀውም"፡፡ "ዘመድኩን ያሠራጨውን አርማጌዶን ቪሲዲን ተመልክተውታል"? "አዎን ተመልክቼዋለሁ"፡፡ "ታዲያ፣ ዘመድኩን መጋቤ ሀዲስ በጋሻውን 'አጉራ ዘለል' ብሎ ለመሳደብ ምን መብት አለው"? "ኧረ በጭራሽ! አጉራ ዘለል አላለውም፡፡ በቢሲዲው በጋሻውን በስም ጠቅሶ አጉራ ዘለል አላለውም"፡፡ "እንዴ! ዘመድኩን እኮ ብዬዋለሁ ብሎ አምኖአል እርሶ እንዴት ይክዳሉ? ቪሲዲውን አላዩትም እንዴ"? "አርማጌዶን የሚባል ቢሲዲ ወጣ ሲባል ሰማሁ እንጂ በእርግጥ አላየሁትም"፡፡ ይኸን ጊዜ ዳኛው ጣልቃ ገቡና "ለምንድነው የተምታታ መልስ የሚሰጡት? አንዴ አይቻለሁ ሌላ ጊዜ ደግሞ አላየሁትም ለምን ይላሉ? ካህን ባይሆኑ አሁኑኑ ወደ እሥር እንልክዎት ነበር፡፡ ሐሰተኛ ምሥክርነት በተከሳሽ ላይ እንደሚያከብድበት አያውቁም"? አባ ይሄኔ አቀረቀሩ፡፡ "የመጨረሻ ጥያቄ እንጠይቅዎት፡፡ ማንም ማንንም በስብከትና በአገልግሎት እንዳይተች የተላለፈው መመሪያ ዘመድኩንን ይመለከተዋል? ወይንስ አይመለከተውም"? "ኧረ ይመለከተዋል"፡፡ ዐቃቤ ሕጉ "ጥያቄዬን ጨርሻለሁ፤ አመሰግናለሁ"! ብለው አጠናቀቁ፡፡ የአራዳው ምድብ ችሎት በእንደዚህ ያለ ሂደት የተካሄደ ሲሆን፣ ለመጨረሻ ውሳኔ ለየካቲት 27 ቀን 2004 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ዘመድኩን ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባዔ መጀመሪያ ዋዜማ ሥርዓተ ፀሎት ላይ ይረብሹ ለነበሩ ወሮበሎች ገንዘብ ሲከፍል ታይቷል ተብሎ ለተሰጠበት ምሥክርነት ማስተባበያ ወደ ቲዎሎጂ ምሩቃን ማኅበር አባላት ሄዶ፣ "በረብሻው ወቅት በስብሰባችን ላይ ነበር" የሚል ምስክርነት ስጡልኝ ብሎ ቢለማመጥም፣ "አንተ በግልህ ሄደህ ለፈጸምከው ጥፋት ተባባሪ የምንሆንበት አንዳች ምክንያት የለም" ብለው ከፊታቸው ዞር እንዲልላቸው አባረውታል፡፡ ቁጥጥር የማይደረግበት የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ገንዘብ በጉቦ መልክ ተሠራጭቶ ካላዳነው በስተቀር የዘመድኩን የነፃነት ቀናት እየተቆጠሩ ናቸው፡፡ ለማንኛውም ጊዜው ደርሶ ለማየት ያብቃን፡፡ የእግዚአብሔር ሠላምና ጥበቃ ለሁላችን ይሁን!!! Posted by Dejeselaam at 10:25 AM