Wednesday, January 17, 2024

“መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።” ሐዋ 4፥12

አዳም ከአምላኩ ትዕዛዝ በወጣ ጊዜ፣ ከሔዋን ጋር ከገነት ተባሮ አሜከላና እሾህ ወደምታበቅለው ምድር መጣሉን መጽሐፍ ቅዱሳችን ይነግረናል። ዘፍ 3:1—24 ይህ የአዳም በደል ከእሱ በተወለዱ ዘሮቹ በሙሉ በውርስ ሲተላለፍ ኖሯል። ከሰማይ ከወረደው ሁለተኛው አዳም/ ኢየሱስ/ በቀር ያለ ውርስ ኃጢአት የኖረ ማንም አልነበረም። የኢየሱስም ከሰማይ ወርዶ ሰው የመሆን ምስጢሩም የሚነሳው፣ የአዳም ዘር በሙሉ በሞት ፍርድ ሥር ያለ በመሆኑ ከሥጋ ለባሽ አንድም ሰው ዘሩን ነጻ ማድረግ ስለማይችል ነበር። ይህንንም ሐዋርያው ጳውሎስ አስረግጦ ሲያስረዳ ወደ ሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ እንደዚህ ብሎታል። “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤” ሮሜ 5፥12 ስለዚህም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል "ወልድ" በሥጋ ሰብእ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፣ ከኃጢአት ብቻ በቀር አዳማዊ ባህርይን ተዋሕዶ ሰው ሆነ። አዳምንና ልጆቹን ከዘላለም ሞት ማዳን የሚችለው ከኃጢአት ነጻ መሆን የቻለ ብቻ ስለነበር ኢየሱስም የእግዚአብሔር በግ ሆኖ ለኃጢአተኞች ነጻ መውጣት የአብ መስዋእት ሆኖ ቀረበ። “በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።”ዮሐ 1፥29 ይህ የዓለምን ኃጢአትን የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ (ካልቪኒስቶች ለዓለሙ ሁሉ አልሞተም ይላሉ) መስቀል ላይ ውሎ የኃጢአት ሥርየት እርሱ መሆኑን አምነው፣ በስሙ ለተጠመቁና እስከመጨረሻው እምነታቸውን አጽንተው ለተጠበቁ በሙሉ እንጂ ለተወሰነ ዘር፣ ነገድ፣ ጎሣ፣ ብሔር ወይም ለተወሰነ ወገን የተፈፀመ ማዳን አልነበረም። ሐዋርያው ጳውሎስ ሞት ወደዓለም በአንዱ አዳም በኩል ለሁሉ እንደደረሰ ሕይወት ደግሞ በአንዱ በኢየሱስ በኩል ለተቀበሉት ሁሉ ሆነ በማለት ያስረዳናል። “በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ።” ሮሜ 5፥17 እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደዓለም የላከውና ለመስቀል ሞት የታዘዘው የአዳም ዘር በሙሉ በእርሱ አምነው እንዲድኑበት እንጂ የተወሰነ ቡድን ወይም በምርጫ ለተለየ ወገን ለይቶ ለማዳን አይደለም። በዚህ ዘመን ጆን ካልቪን የተባለ የ17ኛው ክ/ዘመን የተነሳ የአዲስ ሃይማኖት አስተማሪ ደቀመዛሙርት ነን የሚሉ በዚህ ዘመንም ኢትዮጵያ ውስጥ ሃይማኖታዊ ክሂዶትን አጠናክረው በመቀጠል ኢየሱስ የሞተልን ለእኛ ለተመረጥን፣ አስቀድሞ ለተለየንና ለተጠራን ብቻ እንጂ ለአዳም ልጆች ሁሉ ኃጢአት አይደለም እያሉ በታላቅ ድፍረት ሲናገሩ ይደመጣሉ። ብዙዎችንም እያሳቱ ይገኛሉ። በመጥምቁ ዮሐንስ የተመሰከረልንና "የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ" ዮሐ 1:29 የሚለው ቃል በካልቪኒስቶች አስተምህሮ "ለኛ ለተመረጥነው እንጂ ለዓለሙ ሁሉ አይደለም" በሚለው መቀየር አለበት እንደማለት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በአዳም አለመታዘዝ ሞት ለሁሉ እንደደረሰ፣ በአንዱ በኢየሱስ መታዘዝ ሕይወት ለሁሉ እንደበዛ እንዲህ በማለት ይነግረናል። “በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።” ሮሜ 5፥19 ከእኛ ከኃጢአተኞቹ የሚጠበቀው እግዚአብሔር በልጁ ሞት እንዳዳነን፣ ሕይወትም እንደሰጠን ማመንና መቀበል ብቻ እንጂ ከእኛ በሆነ ሥራ አይደለም። "ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም" ኤፌ 2:8—9 ነገር ግን ካልቪኒስቶች ሥራም፣ እምነትም፣ ማወቅም፣ መረዳትም፣ ማመንም ሳይጠበቅብን አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተመረጥነውና የተለየነው እኛ ብቻ /predestination/ የተሰጠን ስንድን ለሲኦል የተዘጋጁት ደግሞ ያልተመረጡና አስቀድሞ የተፈረደባቸው ናቸው በማለት አምላካዊ ምህረቱን ለግላቸው በመውሰድ በሌሎች ላይ የፍርድ ቃል በድፍረት ሲናገሩ አይሰቀጥጣቸውም። ይህ አባባላቸው ኢየሱስ የተሰቀለው አስቀድሞ ለተመረጡና ለተወሰኑ ሰዎች እንጂ በእርሱ አምነው ለሚመጡ ለዓለሙ ሁሉ አይደለም ለማለት የሚረዳቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ ቦጭቀው ሲጠቀሙ ይህንን ይጠቅሳሉ። “አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው።” ሮሜ 8፥30 ይሄንን ቃል ሲያብራሩ እኛ /ካልቪኒስቶቹ/ ራሳቸውን ማለታቸው ነው። አስቀድሞ እንድንድን የተወሰነልን ነን። ከእንግዲህ የትኛውንም ኃጢአት ብንሰራ አንጠፋም። አስቀድሞ በተሰወነልን መሠረት የጠራን አንዴ ልጆቹ አደረገን። አፅደቆም በሰማይ አከበረን ይላሉ። ከዚህ ከእግዚአብሔር ቃል እውነት ፍፁም ተቃራኒ በሆነ ክህደት ውስጥ እንዲዘፈቁ ያደረጋቸው ሰይጣናዊ ትርጉም ሁለት መሰረታዊ ነገርን ከመሳት የመጣ ነው። እሱም፣ 1/ የእግዚአብሔር ሁሉን አዋቂነት ወደሰውኛ እውቀት ማውረድና 2/ የእግዚአብሔርን ምሕረትና የይቅርታ ሚዛን አለመረዳት ናቸው። እግዚአብሔር አምላክ የማያውቀውና የተሰወረበት ምን ምስጢር አለ? እግዚአብሔር ፍጥረትን ከፈጠረበትና ዓለማትን ከሚያሳልፍበት ሁሉን ቻይነቱ፣ የሉዓላዊነት ሥልጣን ውጪ የሆነና መሆን የሚቻለው አንዳችም ፍጥረት የለም። ይህም የእግዚአብሔር የሁሉን አዋቂነቱ /Omniscient/ እና የከሃሌ ኩሉነት /Omnipotent/ በራሱ አምላካዊ ባህርይው የሚገኝ ነው። ከዚህ ተነስተው እነዚህን ጥያቄዎች ብናነሳ የምናገኛቸው ትክክለኛ መልሶች ያሉት በእርሱ ዘንድ ብቻ ናቸው። የሰው ልጅ ከተፈጠረ ጀምሮ ስንት ሰው ተወልዷል፣ በፆታ ስንቱ ወንድ ስንቱስ ሴት ነው? ስንትስ ሰው ሞቷል፣ ስንት ሰውስ በሕይወት አለ? ስንቱ ገነት ገባ? ስንቱስ ሲዖል ወረደ? የሚሉትን ጥያቄዎች ብንጠይቅ ይህንን በትክክል የማወቅ ኃይሉ ያለው በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው። በዚህም እግዚአብሔርን ሁሉን አዋቂ አምላክ እንለዋለን። “ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ፥ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ።” መዝ 103፥14 “የጠለቀውንና የተሠወረውን ይገልጣል፤ በጨለማ ያለውን ያውቃል፥ ብርሃንም ከእርሱ ጋር ነው።”ዳን 2፥22 የእግዚአብሔርን ሁሉን አዋቂነት ካልቪኒስቶቹ ራሳቸውን ከፀደቁት ጎራ ጨምረው እግዚአብሔር ዓለም ሳይፈጠር የፈረደባቸውንና በሰማይ ያፀደቃቸውን ስለሚያውቅ እኛን ከፀደቁት አድርጎ አስቀድሞ ወደፅድቁ ስለጨመረን ኩነኔ የሚባለው ነገር አይመለከተንም እያሉ በአስቀድሞ መወሰን/Predestination/ ውስጥ ራሳቸውን ያስቀምጣሉ። እግዚአብሔር ሁሉንም አዋቂ ነው ማለት ጄምስን ኮንኜዋለሁ፣ ገብረማርያምን ደግሞ አፅድቄዋለሁ ብሎ አስቀድሞ ውሳኔ የሰጠበት ሰው የለም። እንደዚያ አስቀድሞ ከተወሰነ የኢየሱስ ሰው መሆን ለምን አስፈለገ? ለምንስ ተሰቀለ? እምነትስ ምን ሊጠቅመን? እምነትንስ በሥራ መግለፅ ምን ሊጨምር? አስቀድሞ ለፅድቅ የተወሰነ ሰው ስለኃጢአት የሚከፈል ዋጋስ ለምን አስፈለገው?ቢከፈልለትም ሆነ ባይከፈልለት አስቀድሞ የተወሰነለትን ከመቀበል የሚያግደው ነገር ምን አለ?የሚሉ ጥያቄዎችን ብናነሳ መሆን የሚገባቸው ትእይንቶች/ ትርኢቶች/ እንጂ በመሰረታዊ የሰው ልጆች የመዳን መንገድ ላይ ትርጉም የሌላቸው ሆኖ እንዲታዩ የሚያደርግ ነው። ውሳኔው ቀድሞ ስለተሰጠ መዳኑ አይቀርበትም። ቀራንዮ ላይ የተፈፀመው ስቅለት አስቀድሞ የተነገረለትን ለማሳየት የተደረገ ትርኢት ነው ማለት ነው። ይህ የጆን ካልቪን ትምህርት አደገኛና የእግዚአብሔርን ፍፁም የሆነ ፍቅር በመሻር ሰው የሚፈረድበት በራሱ ምርጫ ሳይሆን ለሲዖል እሳት እንደማገዶ እንጨት አስቀድሞ አዘጋጅቶት የነበረውን ሰው ወደእሳት በመወርወር የሚደረግ ድምዳሜ እንጂ በማመኑ ወይም ባለማመኑ የሚደረግ ፍፃሜ አይደለም የሚል ክህደት ነው። ይህም እግዚአብሔር ሰው በምርጫው እንዲወስን ነባቢት፣ ለባዊትና ሕያዊት ነፍስ አልሰጠውም የሚል አምላክን እንደጨካኝ ገዢ የሚስል ሰይጣናዊ ትምህርት ነው። ዮሐንስ በራእዩ የጻፈልን ቃል፣ "ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ። እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ"ራእይ 22:11—13 የሚለው ቃል አስቀድሞ በተወሰነ ነገር ላይ ዝም ብሎ የተጻፈ እንጂ ፅድቅም፣ ርኩሰትም በማድረግ እንደሥራው የሚባል ክፍያ የለም እያሉን ነው ካልቪኒስቶቹ። የጆን ካልቪን ክሂዶተ እምነትና አስቀድሞ የመወሰን /predestination/ ስህተቶች በ5 ነጥቦች የተመደቡ ናቸው። 1/ Total Depravity/ የሰው ልጅ ከውድቀት በኋላ በጭራሽ ጻድቅ መሆን አይችልም የሚል ነው። ይህ የስህተት ትምህርት በአዳም ስህተት የተላለፈው ውድቀት የሰውን ልጅ ከነአካቴው የክፋት ሁሉ ባለቤት ነው ብሎ በሰው ጆሮ የሚያንቃጭል የሰይጣን ውንጀላ ሲሆን ሰው ሁሉ እኔን መስሏል የሚል ሰይጣናዊ ድምፀት ያለበት ክስ ነው። ከውድቀት በኋላ ለአዳም ልጆች ሁሉ የተላለፈውን ሞት የሚያስቀር የጽድቅ ሥራና ወደወጣበት ገነት የሚመልስ ማንነት በሥራው አያገኝም ማለት፣ ሰው በጎነት፣ ደግነት፣ በፈሪሃ እግዚአብሔር መኖር፣ የጽድቅ ሥራ መፈፀም አይችልም ማለት አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱሳችን በዚህ ተግባር የተመሰከረላቸው ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ ሄኖክ፣ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሎጥ፣ ሳሙኤል፣ ኤልያስ፣ ኤልሳዕ፣ ዳንኤል፣ ሠለስቱ ደቂቅ ወዘተን መጥቀስ ይቻላል። ከዚህም የተነሳ የካልቪኒስቶች ስሁት ትምህርት በምድር ላይ የጽድቅ ስራን መሥራት በመቻልና በሥራ በመጽደቅ መካከል ያለውን ልዩነት አቅላቅለው እውነትን ደፍጥጠው ይክዳሉ። 2/ Unconditional Election /አስቀድሞ መመረጥ/ እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚድኑትን አስቀድሞ መርጧቸዋል። ሲመርጣቸውም ምንም ዓይነት መስፈርትና መለኪያ አላደረገም። በቃ! ጻድቅ እንዲሆኑ ተፈጠሩ የሚል ነው። ኃጢአት፣ ሥርየት፣ እምነት፣ የሚባል ነገር ለፎርማሊቲ እንጂ ከተመረጡበት አያስቀራቸውም፣ አይጨምርላቸውም። የትኛውም ኃጢአት ከምርጫው አያስቀራቸውም የሚል ሲሆን እግዚአብሔር ለሲዖል መርጦ ያስቀራቸው አሉ በማለት ፍፁም ፍቅር የሆነውን የእግዚአብሔር ፍቅር ከሰው ልብ አውጥቶ የሚጥል ሰይጣናዊ ትምህርት ነው። ሲጀመር ሲዖል ለሰይጣንና ለመላእክቱ እንጂ ለሰው ልጅ አልተፈጠረም። ማቴ 25:41 3/ Limited Atonement የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት የተከናወነው ለእኛ አስቀድሞ ለተመረጥነው ብቻ ነው የሚል አስተምህሮ ነው። ለዚህም እንዲረዳቸው ይህንን ጥቅስ ይጠቅሳሉ። “መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።”ዮሐ 10፥11 ኢየሱስ ነፍሱን የሰጠው ለእኛ ለተመረጥነው በጎቹ ብቻ ነው የሚል ነው። ሲጀመር ካልቪኒስቶች በ/Limited Atonement/ /ለበጎቹ ብቻ/ በሚለው አስተምህሮአቸው ውስጥ ሁለት ነገር ይስታሉ። አንደኛው በማይቀየር ማዳኑ ውስጥ አስቀድሞ በጎቹ ከተመረጡ ኢየሱስ ለምን መሰቀል አስፈለገው? ዝም ብሎ እነሱን እየለየ ወደገነት ማስገባት ተገቢ በሆነ ነበር። ሲቀጥል ካልቪኒስቶች የስህተት ትምህርታቸውን ተርጉመው የኢየሱስ በጎች እኛ ነን ያሉት ራሳቸው እንጂ ካልቪኒስቶች ብቻ የተመረጡ ናቸው የሚል ማረጋገጫ በመጽሐፍም፣ በመላእክትም የተመሰከረ አይደለም። ደግሞ የተነገረን እውነት የተለየ ወንጌል የሰበከ የተረገመ ይሁን የሚል ነው። ገላ 1:8 እኛ ግን እንዲህ ብለን እናምናለን። “በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤” ገላ 3፥26 በኢየሱስ አዳኝነት ያመነ፣ የተጠመቀና እምነቱን በሥራ የገለፀ አማኝ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኗል ብለን እንናገራለን እንጂ ኢየሱስ የዓለም መድኃኒት የተባለበትን ሞትና ትንሣኤውን የካልቪኒስቶች ብቻ መድኃኒት ብለን ስለሁሉ የሞተበትን ምስጢር አንክድም። 4/ Irresistible Grace/ የካልቪኒስቶች ሌላው ስሁት አስተምሮአቸው አስቀድሞ በፀጋው የተጠሩት መቼም እንዳይጠፉ ሆነው የሚል ነው። ለዚህም ደጋፊ እንዲሆናቸው ዮሐንስ በወንጌሉ የጻፈውን የራሳቸው ብቸኛ ማረጋገጫቸው አድርገው ያቀርባሉ። “አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም” ዮሐ 6፥37 የሚገርመው ነገር በ30 ጠገራ ብር ኢየሱስን የሸጠው ይሁዳ ከተጠሩት ሐዋርያት መካከል አልነበረም ወይ? ሲባሉ ከሐዋርያነት የተደመረው ሽያጩን እስኪፈፅም እንጂ በዘላለማዊ ጥሪ ውስጥ አልነበረም ይላሉ። ለያህዌ ስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ካልቪኒስቶች እግዚአብሔር በሰው ሕይወት ላይ ቁማር ይጫወታል፣ ያለምርጫህ ብትጠፋም ላንተ መጥፋት ግድ አይሰጠውም ወደሚል የአምላክን ባህርያዊ ፍቅር ወደማስካድ ይወርዳሉ። እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ስለሆነ የሚጠፉትንና የሚድኑትን ያውቃል ማለት የሚጠፉትና የሚድኑት እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለወሰነባቸው ሳይሆን ሰዎች በሚያደርጉት የራሳቸው ውሳኔ የተነሳ መሆኑን አይቀበሉም። አዳም ከገነት ከመባረሩ በፊት ፍጻሜውን እግዚአብሔር ያውቅ ነበር ማለት አትብላ ያለውን እፀ በለስ በግድ እንዲበላ ስለወሰነበት ነበር ብሎ ማቅረብ አደገኛ ክህደት ነው። ይህም የሰው ልጅ በራሱ ማሰብና መወሰን የማይችልና አስቀድሞ በተገጠመለት የውሳኔ ሶፍትዌር የሚንቀሳቀስ ቁስ ነው እንደማለት ነው። የተወሰነብህን ትኖራለህ እንጂ በእውቀትም፣ በእምነትም የምትጨምረውና የምትቀንሰው ነገር የለም ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱሳችን የሚነግረን አንዴ በተሰጠ ምርጫ የለሽ ውሳኔ ሳይሆን የምናምነው አምላክ አውቀን በዚሁ በእምነታችን ፀንተን ስንቆይ እንደሆነ በግልፅ ይነግረናል። “የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ፥ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና፤” ዕብ 3፥14 እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ከወጡ በኋላ ወተትና ማር ወደምታፈሰው ምድር ሳይገቡ በምድረ በዳ የቀሩት እግዚአብሔር በረሃ በልቷቸው እንዲቀሩ አስቀድሞ በወሰነባቸው ውሳኔ ሳይሆን ድንቅና ተአምራትን አድርጎ ከሰማይ መና፣ ቀን በደመና፣ ሌሊት በብርሃን ዓምድ እየመራቸው በነበረው አምላካቸው ላይ በማመፃቸው ነበር። " ዛሬ ድምጹን ብትሰሙት፥ በማስመረር እንደሆነ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ። ሰምተው ያስመረሩት እነማን ነበሩ? በሙሴ ተመርተው ከግብጽ የወጡ ሁሉ አይደሉምን? አርባ አመትም የተቆጣባቸው እነማን ነበሩ? ሬሳቸው በምድረ በዳ የወደቀ፥ ኃጢአትን ያደረጉት እነርሱ አይደሉምን? ካልታዘዙትም በቀር ወደ እረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ? ባለማመናቸውም ጠንቅ ሊገቡ እንዳልተቻላቸው እናያለን" ዕብ3: 15—19 5/ PERSEVERANCE OF THE SAINTS ይህ ማለት አንዴ ከዳንክ ለዘላለም ድነሃል። በየትኛውም ኃጢአት ወይም በዓመጻ የሚጎድልህ ማንነት አይኖርህም ማለት ነው። Once saved, always saved ይሉሃል። በካልቪኒስቶቹ ዘንድ በዕብራውያን 10:36 ላይ የተመለከተው በእምነት ፀንቶ፣ ፈቃዱን እያደረጉ መኖር ነገር እርባና የለውም። “የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና።” ዕብ 10፥36 አንዴ የዳነ፣ ለዘላለም የማይጠፋ ስለሆነ በካልቪኒስቶች ዘንድ የሐዋርያው ጴጥሮስ ምክር ምንም አያስቀርበትም። “ስለዚህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፥” 2ኛ ጴጥ 3፥14 የእግዚአብሔር ፈቃድ ብታደርግም፣ባታደርግም አንዴ ድነሃልና አትጠፋም፣ አትጨነቅ። ዮሐንስ በመልእክቱ የፃፈው ካልቪኒስቶችን አይመለከትም። ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው የሚለው ቃል ቢኖርም አንዴ ስለዳንክ ችግር የለውም ይሉሃል። “ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና።”1ኛ ዮሐ 3፥8 አንዴ ስለዳንክ በኃጢአት የተነሳ ከዲያብሎስ ብትሆንም አትጨነቅ፣ አትጠፋም እያሉ ለድፍረት ኃጢአት ያበረታቱሃል። ኃጢአት መስራት፣ አለመስራትህ የሚቀንስብህ ወይም የሚጨምርልህ ነገር የለም ይሉሃል። “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።”1ኛ ዮሐ 2፥17 ፈቃዱን ብታደርግ ጥሩ ነው። ሳትፈፅመው ብትቀርም ችግር አያስከትልብህም፣ አትጨናነቅ፣ አንተ ለዘላለም የተመረጥህ ነህና። ዮሐንስ በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዓላማ ውስጥ ለመኖር ፈቃዱን መፈፀም ተገቢ ነው ያለው የራሱ ግምት በመሆኑ ካልቪን ያሻሻለውንና አንዴ የዳነ፣ ለዘላለም ዳነ የሚለውን ትምህርት ተከተል ይሉሃል ከሃዲዎቹ! ማጠቃለያ፣ ካልቪኒስቶቹ የሳቱት እውነት፣ የምሥራቹ ቃል የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል እንጂ የጆን ካልቪን ትርጉም፣ አባባል፣ አገላለፅ ወይም የአስተምህሮ አቋም አለመሆኑን አለማወቃቸው ነው። ካልቪን በአንድ ወቅት የተለየ የወንጌል አስተምህሮ ተገልጾልኛል ብሎ የራሱን ትርጉም ይዞ የመጣ ሰው እንጂ የምሥራቹ ቃል ምንጭ ስላልሆነ ካልቪኒስት ነኝ ብሎ እሱን መከተል አደገኛ ስህተት ነው። ማንም አማኝ የወንጌልን ትምህርት በብዙ መንገድ፣ ከብዙ ሰዎች ሊሰማ ወይም ሊያገኝ ይችላል። ያ ማለት ግን የወንጌል እውነት እሱ ከሰማበት ቦታ ብቻ ይገኛል ማለት አይደለም። የየትኛውም ትምህርት ማረጋገጫና መመዘኛ መንፈስ ቅዱስና የምሥራቹ ቃል እውነት መሆኑን አለማወቃቸው ነው። ሉተር፣ ካልቪን፣ ዝዊንግሊ፣ ኤራስመስ፣ ኖክ፣ ዊክሊፍ፣ ኸስ፣ ሜላንክቶን ወይም ቲንዳል የእውነት ቃል ምንጭ ወይም የመጨረሻው የእውነት ማረጋገጫ ሊሆኑ እንደማይችሉ አለመረዳታቸው ነው። ከኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ይልቅ ግለሰቦቹ በሰጡት ትንታኔ ላይ በመመስረት ለማመን መሞከራቸው ነው ካልቪኒስት ሆነው ለመኖር የወሰኑት። እኛ ግን የተሰቀለልንና ከሞት ያዳነን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይና ደቀመዛሙርት እንጂ የአጵሎስ ወይም የጳውሎስ አይደለንም። ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የተሰጠን ስም ማነው? ከሰማይ በታች ሊድኑበት ለወደዱና ወደእርሱ ለመጡ በሙሉ የሚያድነው ስም ኢየሱስ ብቻ ነው። ከሰማይ በታች የተሰጠ የካልቪን አስተምህሮ፣ ለካልቪኒስቶች ሊኖር ይችላል። እኛን ክርስቶሳውያንን አይመለከትም። የካልቪን የሚባል አስተምህሮም፣ መምህርም የለንም።

Saturday, January 13, 2024

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዋና ችግር ጳጳሳት ናቸው!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዋና ችግር ራሳቸው ጳጳሳቱ ናቸው። ምክንያቶቹ፣ 1/ አንድ ወጥ የሆነ የቀደምት አበው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ የለውም። ተረት፣ ተረት፣ እንቆቅልሽና እንቶ ፈንቶውን ስህተት አርሞ በትክክለኛው የወንጌል ጎዳና ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትሄድ ማድረግ አልቻለም። ዳንኤል 5፣ 24—28 ስለዚህም እነዚህ የእጅ ጣቶች ከእርሱ ዘንድ ተልከዋል፤ ይህም ጽሕፈት ተጽፎአል። የተጻፈውም ጽሕፈት፦ ማኔ ቴቄል ፋሬስ ይላል። የነገሩም ፍቺ ይህ ነው፤ ማኔ ማለት፥ እግዚአብሔር መንግሥትህን ቈጠረው ፈጸመውም ማለት ነው። ፋሬስ ማለት፥ መንግሥትህ ተከፈለ፥ ለሜዶንና ለፋርስ ሰዎችም ተሰጠ ማለት ነው። ከዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል አንፃር ቤተክርስቲያኒቱ መፈረካከሷ ገና ይቀጥላል። 2/የጳጳሳቱ ጉባዔ በቤተ ክርስቲያኒቱ ትልቁ የሥልጣን ማዕከል ነው። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኒቱን በመንፈሳዊ ምሳሌነት፣ በእውቀት፣ በዘመናዊ አስተዳደርና መዋቅር መምራት አልቻለም። በዚህም የተነሳ ዘረኝነት፣ ሌብነት፣ ዘረፋ፣ ጉቦ፣ የፍትህ መጓደል፣ ጥንቆላና አስማተኝነት ከጳጳሳቱ ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ የዕለት ከዕለት ተግባር ነው። ከዚህ የተነሳ የሚከናወነው አምልኮተ እግዚአብሔር ከምእመናኑ የሚገኘውን ገንዘብ ለመሰብሰብና ጥቅም ማስገኛ ምንጭ ከማድረግ ባለፈ እግዚአብሔርን ከመፍራትና ለቃሉ ለመገዛት ካለ መንፈሳዊ ብቃት የተነሳ አይደለም። 3/ ቤተ ክርስቲያኒቱ የታሪክ፣ የቅርስ፣ የሥነ ፅሑፍ፣ የሰነድ ባለቤት ሆና ሳለ ይህንን ሁሉ አራግፋ በመጣል የገዢዎች ባለሟል፣ ትዕዛዝ ፈጻሚ እና የመከራ ጽዋ የምትጎነጭ እርስ በእርሷ የምትባላ ሆና እያየናት ነው። ሲጠቃለል፣ ቤተክርስቲያኒቱ ጥቋቁር ጨርቅ በተሸፋፈኑ ጳጳሳት ከመፍረስ አትድንም። ወደቀደመ ክብሯ አትመለስም። ከተረት፣ ተረት እና ከፈጠራ የስህተት አስተምህሮ ወጥታ ወደእውነተኛ የወንጌል መንገድ ልትገባ አትችልም። ቢመርም እውነቱ እሱ ነው።

Tuesday, August 8, 2023

የጾመ ፍልሰታ: የማርያም ትንሣኤና እርገት መንፈሳዊ መሰል ኢ—መጽሐፍ ቅዱሳዊታሪክ!

የዚህ ፅሑፍ ዓላማ የጌታን እናት ቅድስት ማርያምን የማሳነስ ወይም የመተቸት ዓላማ ግብ የሌለውና ሰዎች በማርያም ሽፋን የሚሰሩትን ኢ—መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሀሰት ትረካ ለአንባቢው ማሳየት ነው። ቅድስት ማርያም ቅድስትና ብጽዕት ናት። ጥንተ ጠላታችን በተንኮሉ "አምላኬና መድኃኒቴ" ካለችለት ውድ ልጇ ይልቅ ወደእርሷ እንዲመለከቱ አዚም ማድረጉን በማወቅ እውነቱን መግለፅ ግድ ስለሚለን ነው። ቅድስት ማርያም ዓለም ሁሉ እንዲድን እኔ ልሙት አላለችም። መድኃኒቷ መሆኑን የመሰከረችለት ልጇን ተክታ በእኔ ሞትና ትንሣኤ ሕይወት ይሆንላችኋል አትልም። ታዲያ ጾመ ፍልሰታ ምንድነው? በጾመ ፍልሰታ የሚገኝ ዘላለማዊ ሕይወት አለ ወይ? ብለን ስንጠይቅ መልሱን ለማግኘት ፅሑፉን በትዕግስት እንዲያነቡ ይመከራሉ። ሲወጣ እንዳየነው ሲመጣም የምንጠብቀው እሱን ነው።
ቅዱሳንን ስለማክበር ምንም ጥያቄ የለንም። መታሰቢያ ማድረግም የነገሮችን ሁሉ ባለቤት እስካልተካ ድረስ የሚደገፍ ነው። ነገር ግን «ጥቂት አሻሮ ይዞ፤ ዱቄት ወዳለው መጠጋት» የሚለውን ብሂል ለመተግበር መሞከር ግን ተቀባይነት አይኖረውም። በተለይም በሃይማኖታዊ አስተምህሮ ወቅት ወንጌል እንደዚህ ስለሚል፤ እኔም እንደዚህ ብል ችግር የለውም የሚለውን ራስን መሸሸጊያ ምክንያት በማቅረብ ለመከለል መሞከር አያዋጣም። ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሱትና እነዚህ የመሳሰሉ የስህተት ችካሎች አልነቀል ያሉት በምክንያት ስር በመወሸቃቸው ነው። ራሱን የማርያምን እረፍትና ትንሣዔ ሳይሆን በማርያም እረፍት፤ ቀብር፤ ትንሣዔና እርገት ላይ ያሉ አስተምህሮዎችን ለመቃኘት እንሞክራለን። ስለማርያም እረፍት፤ ትንሣዔና እርገት አብያተ ክርስቲያናት አንድ ዓይነት የእምነት አቋም የላቸውም። እንዲያውም ስለማርያም ሞትና የእርገት ዕለት በግልጽ የሚታወቅ ማስረጃ እንደሌለ በ5ኛው ክ/ዘመን የኖረው የሳላሚሱ ኤጴፋንዮስ ተናግሯል። ዕረፍቷና እርገቷ በኢየሩሳሌም እንደሆነ የሚናገሩ ቢኖሩም ይህንን አባባል የማይቀበሉ አብያተ ክርስቲያናትና የቴኦሎጂ ምሁራን ሞልተዋል። በኢየሩሳሌም አርፋለች የሚለውን አባባል የማይቀበሉበትን ማስረጃ ሲያቀርቡም ዮሐንስ በወንጌሉ ላይ እንደተናገረው «እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት» ዮሐ19፤27 ባለው መሠረት ማርያም እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ ድረስ ከዮሐንስ ጋር ስለኖረችና ወንጌላዊው ዮሐንስም ከጌታ ሞት በኋላ በኢየሩሳሌም ጥቂት ዓመታትን ከቆየ በኋላ በ37 ዓ/ም ገደማ ወደ ቤዛንታይን ከተማ ኤፌሶን ሄዶ ወገኖቹን ወንጌል እያስተማረ መቆየቱንና ማርያም በሞት እስከተለየችው ድረስ ከ48-52 ዓ/ም እዚያው እንደነበር ብዙ ተጽፏል። ከማርያም ክፍል ትይዩ ያለው የዮሐንስ መኖሪያ ቤት ፎቶ፤
በኋላም በቅርብ ርቀት ባለችው ደሴተ ፍጥሞም በግዞት መኖሩ ይነገራል ። አንዳንዶች ከዶሚኒሽን አገዛዝ ቀደም ብሎ የራእይ መጽሐፉን ከ55-65 ዓም ገደማ እንደጻፈም ይናገራሉ። ዋናው ነገር ማርያም በኤፌሶን ከዮሐንስ ጋር ኖራለች ወይስ አልኖረችም ነው ጥያቄው። በኢየሩሳሌም አርፋለች የሚሉ ሰዎች አንድም ጊዜ ከዮሐንስ ጋር በኤፌሶን ኖራለች ሲሉ አይደመጥም። ለምን? ዮሐንስ ማርያምን እንደእናት ሊይዛት አደራ ተሰጥቶታል የሚባል ከሆነ ከዮሐንስ ጋር ኤፌሶን ስለመቀመጧ የማይነገረው ለምንድነው? ዮሐንስ እስከ 96 ዓመቱ ድረስ ከኤፌሶንና ከደሴተ ፍጥሞ ውጪ ስለመኖሩ የተነገረ ነገር የለም። ማርያም ከዮሐንስ ጋር በኤፌሶን አልኖረችም ብሎ በመከራከርና በኢየሩሳሌም ኖራ፤ እዚያው ማረፏን በግልጽ በመናገር መካከል ልዩነት አለ። «እነኋት እናትህ» ባለው መሰረት አብረው ኤፌሶን ኖረው እዚያው ማረፏን የማይቀበሉና ኢየሩሳሌም ኖራ አርፋለች የሚሉ ሰዎች እንደልጅና እናት አብረው የመኖራቸውን የወንጌል ቃል መካድ ሊሆንባቸው የግድ ነው። ያ ደግሞ እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ በኢየሩሳሌም ኖራ እረፍቷም፤ ቀብሯና እርገቷ ሆነ ከሚለው አስተምህሮአቸው ጋር «እነኋት እናትህ» የሚለው የወንጌል ቃል ስለሚጋጭባቸው ለዚህ ዓይነት ያፈጠጠ እውነት ምን እንደሚሉ አይታወቅም። ወይ ደግሞ ኤፌሶን ላይ እድሜውን ሙሉ የኖረው ዮሐንስና ኢየሩሳሌም ማርያምን ይዞ የኖረው ዮሐንስ የተለያዩ ናቸው ሊሉ ይገባል። ሮበርት ክሬው የተባለ የነገረ መለኮትና የታሪክ ጸሐፊ ዮሐንስ ወንጌላዊ ዘመኑን ሁሉ በኖረበት ከኤፌሶን ከተማ 8 ኪሎ ሜትር ወጣ ብላ ባለች ኰረብታ ላይ በተሰራ ቤት ውስጥ እንደኖረና ማርያምም እዚያ ማረፏን ጽፏል። ይህንን በኤፌሶን ያለውን የማርያምን መቃብር የዓለም ክርስቲያኖች እንዲሆም ሙስሊሞች ሳይቀሩ ይጎበኙታል፤ ይሳለሙታል። በቱርክ ግዛት ያለው ይህ ስፍራ በቱርካውያን ሙስሊሞች ዘንድ «ሜሪዬማና» ተብሎ ይጠራል። ቅድስት ድንግል ማርያም ከዚህ ዓለም የተለየችው መቼ ነው? ለሚለው ጥያቄ ጥንታዊያን አብያተ ክርስቲያናት የሚባሉት የምሥራቁና የምዕራቡ ጎራዎች የተለያየ አመለካከት አላቸው። በተወለደች በ58 ዓመቷ ዐርፋለች የሚሉ አሉ። በ72 እና 63 እድሜዋም አርፋለች የሚሉ መረጃዎች አሉ። እንደ ግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ግን የሚታመነው በ64 ዓመት እድሜዋ ማረፏ ነው። ኖረችበት ተብሎ ከሚገመተውና አርፋለች ከሚባለው ቦታ ያለው ልዩነት እንዳለሆኖ በጥር ወር ከዚህ ዓለም ተለይታ በ40ኛው ቀን ማረጓን የሚናገሩ አሉ። በነሐሴ ወር አርፋ ከተቀበረች በኋላ ትንሣዔዋን ሳያዩ መቃብሯ ባዶ ሆኖ ስላገኙት ሐዋርያት ሱባዔ ይዘውበሦስተኛው ቀን ተገለጸችላቸው የሚሉም አሉ። እንደኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ደግሞ በጥር ሞታ፤ በነሀሴ ተቀበረች የሚል ትምህርት አለ። በጥር ወር አርፋ፤ በነሀሴ ተቀብራለች የሚሉ ሰዎች ሥጋዋ በገነት ዛፍ ስር ለስምንት ወራት መቀመጡንና በሱባዔ ጸሎት በተደረገው ልመና የተነሳ ለመቀበር መቻሏን አስፋፍተው ይነግሩናል። በጥር ወር እንዳረፈች፤ ለመቀበር ያልቻለችውም ታውፋንያ የሚባል ሽፍታ፤ ጎራዴ ሲመዝባቸው ወደ ቀብር ሥጋዋን ተሸክመው ይሄዱ የነበሩት ሐዋርያት በመፍራት ጥለዋት በመሸሻቸውና ዮሐንስ ብቻውን ቀርቶ ወደ መቃብር ሳትገባ ወደ ገነት ዛፍ ስር በመወሰዷ እንደሆነ ይነገራል። ዮሐንስም ወደቤቱ ማምራቱንና ሸሽተው የነበሩትም ሐዋርያት ሥጋዋስ የታለ? ብለው ቢጠይቁት በገነት ዛፍ ስር መቀመጧን ስለነገራቸው ዮሐንስን ገነት ዛፍ ስር ሬሳዋ መቀመጡን አይቶ ለምን እኛስ ይቀርብናል በማለት ነሐሴ 1/ ቀን የጾም የጸሎት ሱባዔ ጀምረው በ15ኛው ቀን ትኩስ ሬሳ ከገነት ዛፍ ስር እንደመጣላቸውና እንደቀበሯት ይናገራሉ። ይህ እንግዲህ በ49 ዓ/ም ገደማ መሆኑ ነው። ዮሐንስ ግን ኤፌሶን መኖር ከጀመረ 10 ዓመት አልፎታል። ሌላው ጥያቄ የሚያስነሳው ነገር በጥር ወር አርፋ ከቀብር በፊት ወደገነት ዛፍ ስር ስለመወሰዷና ዮሐንስ ወደ ቤት ገብቶ ለሐዋርያት ከነገራቸው በኋላ እሱ ያየውን እነርሱም ለማየት ሐዋርያቱ ለስምንት ወር ያህል የቆዩበት ምክንያት ግልጽ አለመሆኑ ነው። ሐዋርያቱ የልባቸውን ተምኔት ለማሳካት ሱባዔ ባያደርጉ ኖሮ የማርያም ሥጋ ከገነት ዛፍ ስር አይንቀሳቀስም ነበር ማለት ነው? ሌላው ደግሞ ይህ የማርያም ሥጋ አርፎበታል የሚባለው የገነት ዛፍ ምንነትና የሙት ሥጋ ማረፊያ ተብሎ የሚመረጥ የገነት ዛፍ ስለመኖሩ እግዚአብሔር እንደዚህ ዓይነት አሰራር እንዳለው ለሰው ልጆች በመጽሐፍ ቅዱስ ያላሰፈረ አዲስ ግኝት የመሆኑ ጉዳይ ነው። በሌላ መልኩም የማርያም ሥጋ ለመቀበር የግድ የሐዋርያቱን ሱባዔ በተስፋ እየጠበቀ የመቆየቱ ነገር አስገራሚ ይሆናል። እንደሰዎቹ አባባል በጥር ወር አርፋ ሳይቀበር የቀረውን የማርያምን ሥጋ በስምንተኛው ወር ከገነት ወጥቶ ከተሰጣቸውና ከቀበሯትም በኋላ ቢሆን ሐዋርያቱ እርግቷን ለማየት አልቻሉም። ሐዋርያቱ ቀብረዋት ወደ ቤታቸው ከገቡ በኋላ ቶማስ ሐዋርያው በደመና ተጭኖ ከህንድ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ ማርያምን ሐዋርያት በቀበሯት በሦስተኛው ቀን ወደ ሰማይ ስታርግ የዳመናው ጎዳና ላይ ያገኛትና ቀድሞ የልጅሽን እርገት ሳላይ ቀረሁ አሁን ደግሞ ያንቺን ሳላይ ልቀር ነው? ብሎ ቢያዝን ትንሣዔዬን ያላንተ ማንም አላየም ካለችው በኋላ የተገነዘችበትን ጨርቅ እና ሰበን ለምልክት ሰጥታው እንዳረገች ሰፊ ታሪክ ይነገራል። ሰዎቹ ነገሩን ሁሉ ለማጣፈጥ የሚጠቀሙበት ነገር አስገራሚ ነው። የሰው ልጅ ከትንሣዔው በኋላ የዚህን ዓለም ጨርቅና ልብስ እንደተሸከመ ወደ ሰማይ ይገባል ማለት ክርስቲያናዊ አስተምህሮ ነው ወይ? የሚል ጥያቄን ያስነሳልና ነው። ወንጌል ከትንሣዔ በኋላ ክርስቶስን ይመስል ዘንድ ሰው ይለወጣል ይላል እንጂ የመቃብሩን ልብስና ሰበን እየተሸከመ ያርጋል የሚል አስተምሮ የለውም። « 2ኛ ቆሮ 3፤18 እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን» ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን በመቃብሩ የተገነዘበትን ጨርቅ ትቶ መነሳቱን እንጂ ያንኑ ለብሶ መነሳቱን አላነበብንም። ዮሐ 20፤6-8 «ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ደግሞም በራሱ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ» የሁላችን አማኞች ትንሣዔ የክርስቶስን ትንሣዔ መምሰል ካለበት በቀብር ወቅት ከዚህ ዓለም ጉድጓድ የገባ ጨርቅ ወደ ሰማይ አብሮን የሚያርግበት ምንም መንገድ የለውም። ስለዚህ ተጠራጣሪ እንደሆነ ሁል ጊዜ የሚነገርበት ቶማስን በማርያም ትንሣዔ ላይ ግን የተለየ ተጠቃሚ እንደሆነ አድርጎ ለማቅረብ ሲባል ማርያም ወደ ሰማይ ስታርግ የመቃብሯን ከፈን ተሸክማ የሄደች በማስመሰልና ለምልክት ይሆን ዘንድ ከፍላ ሰጠችው የሚለው አባባል በአንዳችም ነገር ከወንጌል እውነት የተጠጋ አይደለም። ሌላው ነገር በመንፈስ ቅዱስ በመነጠቅ፤ በሌላ ስፍራ ወዲያውኑ መገኘት ስለመቻል ለሐዋርያው ፊልጶስ ከተነገረው የወንጌል ቃል በተለየ በዳመና ላይ ተቀምጦ ስለመሄድ ግልጽ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ባይኖርም የቶማስን ከህንድ ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ እንደፊልጶስ መነጠቅ አድርገን ብንቆጥረው እንኳን የቶማስ ሰብአዊነትና የማርያም የእርገት ማንነት የተለያየና ፈጽሞ የማይገናኝን ነገር ለማቀራረብ መሞከር ነው። የቶማስን የዳመና ላይ ውይይትን ከረቂቅ ክርስቶሳዊ አዲስ ፍጥረት ጋር ለማገናኘት መሞከር የጥንቶቹን የግሪክ ወጎች/fable story/ እንድናስታውስ ያደርገናል። በሞትና በትንሣዔ እንዲሁም በእርገት መካከል እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን እግዚአብሔር በሰውኛ ትረካ ይጫወታል ማለት እግዚአብሔር ስለሞትና ትንሣዔ በተናገረው መቀለድ ይሆናል። ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ ማርያምን በጥር ሞታለች ያሉ ሰዎች፤ በመጀመሪያው ሞት ዮሐንስ ብቻ እድለኛ ሆኖ በገነት ዛፍ ስር ለማየት በመቻሉ፤ በኋለኛውም ቀብር ቶማስ ብቻ ተጠቃሚ የሆነበትን የእርገት እድል፤ ሌሎቹ ሐዋርያት ለማግኘት ባለመቻላቸው በቀጣይ ዓመት ነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ሱባዔ ለመያዝ መገደዳቸውንና በ16ኛው ቀን ሁለተኛ ትንሣዔና እርገትን ለማየት የመቻላቸው ነገር ነው። ቀብር ሳይኖር ትንሣዔዋንና እርገቷን እንዴት ማየት እንደቻሉ ግልጽ አይደለም። በምሳሌ ይሁን በምትሃት እርግጠኝነቱን ያብራራ ማንም የለም። ሁለት ጊዜ ትንሣዔና እርገትስ ማለት ምን ማለት ነው? ሌላው ደግሞ ማርያምን መንበር፤ ጴጥሮስን ንፍቅ ቄስ፤ እስጢፋኖስን ገባሬ ዲያቆን አድርጎ በመቀደስ አቁርቧቸዋል የሚለው ትረካ እርገቷን ተከትሎ የመጣ አባባል ነው። የማርያም ነፍስ እንዴት መንበር መሆን እንደሚችል? ምን የሚባለው ቅዳሴ እንደተቀደሰ? ለማወቅ የምናቀርባቸው ጥያቄዎችን ለጊዜው እንተዋቸውና፤ ሰራዔ ካህኑ ክርስቶስ የማንን ሥጋ እንደቆረበ? እንዲነግሩን ግን እንጠይቃቸዋለን። ለየትኛው ድኅነት/መዳን/ እሱ ይቆርባል? ክርስቶስ ቀደሰ እንጂ አልቆረበም አንድ ነገር ነው። ቆርቧል የሚባል ከሆነም ምክንያትና ውጤቱን የሚተነትን ትምህርት አያይዞ ማቅረብ የግድ ይላል። እሱማ የሕይወት ምግብ ሰጪ እንጂ ተቀባይ አይደለም የሚባል ከሆነም ሰራዔ ካህናት በዚህ ምድር መቅደስ ውስጥ ከመቀደስ ባሻገር መቁረብ አይጠበቅባቸውም በማለት አብነታዊ የክህነት አስተምህሮን አያይዞ ማቅረብ የተገባ ይሆናል። እንግዲህ ማርያምን መንበር አደረጋት፤ ክርስቶስ ሰራዔ ካህን ሆኖ ያልታወቀ ቅዳሴ ቀደሰ ማለት ስለማርያም ትንሣዔና እርገት ማጠናከሪያ በማቅረብ ትዕይንቱን ተአማኒ ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር አንድም እውነትነት የለውም። / እንደተለመደው አባባል ቅዳሴ እግዚእ ነው የተቀደሰው የሚል ካለም ክርስቶስ ራሱን በሁለተኛ መደብ አስቀምጦ « ነአኩተከ አምላክ ቅዱስ፤ ፈጻሜ ነፍስነ፤ ወሀቤ ሕይወትነ ዘኢይማስን» ሲል አይገኝም። ራሱ ሕይወት ሰጪ ሆኖ ሳለ ሕይወት ይሰጠው ዘንድ አይለምንምና ነው። እንደዚህ ዓይነቱ አደገኛ ክህደት፤ ሰዎች ለማርያም ባላቸው ፍቅር ውስጥ ተደብቆ ለዘመናት ቆይቷል። በጉ መስዋእቱን ለህይወታችን ሰጥቷል። ከዚያ ውጪ እሱ በመንግሥቱ የፍርድ ሰዓት ዳግመኛ ሊመጣ ካልሆነ በስተቀር ከማእዱ አይካፈልም።«ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማዕድ ተቀመጠ። እርሱም፦ ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር፤ እላችኋለሁና፥ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ፥ ወደ ፊት ከዚህ አልበላም አላቸው። ጽዋንም ተቀበለ አመስግኖም። ይህን እንካችሁ በመካከላችሁም ተካፈሉት» ሉቃ 22፤14-17 በጉ መስዋዕቱን ሕይወት ይሆናቸው ዘንድ ለሰዎች ከሰጠ በኋላ፤ በፍርድ ቀን የደሙን ምልክት ለተቀበሉት ሁሉ ዋጋቸውን ይሰጣቸዋል እንጂ እሱ የመስዋእቱ ተካፋይ ስላልሆነ፤ ክርስቶስ በቀዳሽነት ቆርቦ፤ ማቁረብ የሚባል ታሪክ ከወንጌል ቃል ሊመጣ አይችልም። ይህም በማርያም ሞትና ትንሣዔ ላይ የተጨመረ ሌላ አሳዛኝ ትረካ ነው። በግ ለተራቡ ምግብ እንጂ እራሱን ተመጋቢ ሊሆን አይደለምና። ወደዋናው ሃሳባችን ስንመለስ ለመሆኑ በማርያም ላይ ስንት ቀብር፤ ስንት ትንሣዔና ስንት እርገት ተደረገ? ብለን ብንጠይቅ እንደሚነገረው ከሆነ ፤ 1/ዮሐንስ ያየውና አፈር ያልነካው እርገት በገነት ዛፍ ስር 2/ አፈር የነካው የሐዋርያቱ ቀብር በነሐሴ 14 ቀን /ከስምንት ወር በኋላ/ 3/ ቶማስ ያየው የትንሳዔ እርገት፤ ከቀብር በኋላ በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16 4/ ከአንድ ዓመት በኋላ ሐዋርያት ያዩት የነሐሴ 16 ትንሣዔና እርገት ናቸው። እንግዲህ በማርያም ሞትና እርገት መካከል አራት ትእይንት መከሰቱን ዛሬም ድረስ ከሚሰጡት የቃል አስተምህሮዎችና የተዘጋጁ ጽሁፎች ውስጥ በግልጽ እናገኛለን። ማርያምን መውደድ አንድ ነገር ነው። ማርያምን ግን እየቀበሩና እያነሱ ለማረጋገጥ መሞከር ደግሞ ሌላ አሳዛኝ ክስተት ይሆናል። እንዲያውም ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት መሆን ከቻልኩ ሰባት ጊዜም ቢሆን እሞታለሁ ብላ ለልጇ ተናግራለች የሚሉትም ተረት ተያይዞ ይነገራል። የእሷ መሞት የዓለሙ ሁሉ መድኃኒት መሆን ከቻለ የክርስቶስ ከእሷ መወለድ አስፈላጊ አይደለም የሚል ሃሳብን የሚያንጸባርቀው ይህ አባባል ከአሳሳች ትረካዎች ውስጥ የሚደመር ከመሆን አያልፍም። እኛ ማርያምን ብንወዳትና ብጽእት ብንላት «እናትህንና አባትህን አክብር» ያለውን የአምላክ ቃል መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ለእርሷ የተነገረ ቃል ስላለም ጭምር ነው። ነገር ግን የዘላለማዊ አምላክ የክርስቶስ ፤ እናቱ ስለሆነች በማዳላት ወይም አምላካዊ ባህርይውን በሰውኛ ጠባይ በመለወጥ ከፍርድ ሚዛኑ በማጉደል የእሷን ሞትና ትንሣዔ የተለየ ያደርጋል ብሎ ማሰብ የዋሕነት ይሆናል። የእሷ ሞትም የመድኃኒትነትን ውክልና ለሰው ልጆች የያዘ እንደሆነ ማሰብ ክህደት ነው። ብቸኛው መድኃኒት አንዱ በግ ኢየሱስ ብቻ ነው። ማርያምም ይህንን ስለምታውቅ « ነፍሴ በአምላኬና በመድኃኒቴ ተስፋ ታደርጋለች» ብላ ነግራናለች።የትንሣዔ በኩር የሆነው ሁላችንም በሞቱ እንድንመስለው እንጂ የተለየ አድሎአዊ ጥቅምን/ faver/ ለተለዩ ሰዎች በመስጠት አይደለም።ወንጌል የሚናገረው ይህንን ነውና። ሮሜ 6፥5 «ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን» ስለዚህ ደጋግሞ መሞት፤ መነሳትና ደጋግሞ ማረግ አለ ከተባለ ያ ነገር ከክርስቶስ ትንሣዔ ጋር ያልተባበረ ስለሆነ አንቀበለውም። እንዲያውን ይህ ኑፋቄና ወንጌልን መካድ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስም የተናገረው ስለክርስቶስ ወንጌል በሞቱም ክርስቶስን እንዲመስል ነበር። ፊልጵ 3፥10-11 «እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ» ማርያምን እንወዳለን እያሉ በጥር ሞተች፤ ገነት ዛፍ ስር ስምንት ወር በሬሳ ቆየች፤ በስንት ሱባዔ ስጋዋ መጥቶ ነሐሴ ተቀበረች፤ እስከነ ምድራዊ ልብሷ አረገች፤ በዳመናው ጎዳና ላይ ከቶማስ ጋር ጨርቅ ተለዋወጠች፤ እድል ላመለጣቸው ሐዋርያት ዳግመኛ በስንት ሱባዔ በሌላ ትንሳዔና እርገት ተረጋገጠች፤ መንበር ሆና ተነጠፈች ወዘተ በማለት እየገደሉና እያነሱ በማርያም ላይ መጫወት ተገቢ ነው ብለን አናምንም። የክርስቶስን ሞትና ትንሣዔንም ማፋለስና መካድ ይሆናል። የማርያም ሞትና ትንሣዔ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ካዘጋጀው የትንሣዔው በኩር አንድያ ልጁ የተለየ አያደርገውም። ከመግቢያችን ላይ ጀምሮ ለመግለጽ እንደሞከርነው የኤፌሶኑና የኢየሩሳሌሙ ታሪክ እንዳለ ሆኖ አብያተክርስቲያናት ሁሉ የተለያየ የሞትና የትንሣዔ አስተምህሮ ከመያዛቸው አንጻር ኤጲፋንዮስ እንዳለው ትክክለኛው ታሪክ ቀን አይታወቅም። [2 ] አሁን የሚደረገው ግን ልምድና ትውፊት ነው። ይሁን እንጂ የሆነውን ቀን ወስኖ መታሰቢያ ማድረጉ ባይከፋም እየገደሉና እያነሱ ከመጽሐፉ ቃል በተጻጻሪ የትንሣዔንና የእርገትን ነገር ዋጋ ማሳጣት ተገቢ አይደለም።