Wednesday, September 17, 2014

በምድራችን ላይ በክፉ መንፈስ ተነድተው ሕዝብን ያሳሳቱ ሀሰተኛ ክርስቶሶች!

ክፍል ሁለት )

ዘመኑ የቀሳጥያን፤ የሀሰተኛ ትምህርትና የክህደት መፍለቂያ መሆኑን የበለጠ ለማስረዳት ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩትን ማሳየት ጠቃሚ ይመስለናል። የሰው ልጅ በወንጌል ላይ የተገለጠውን ክርስቶስን ሳይሆን በሰው ብልሃት የተቋቋመችውን ምድራዊ ተቋም፤ የሰዎች ድርጅት፤ የአስተምህሮ መንገድና ስብከት እየተከተሉ ከእውነት ሲያፈነግጡ ማሳየት ተገቢ እንደሆነም ይሰማናል። ዛሬም ቢሆን ሰዎች የድርጅት፤ የተቋምና የሰዎች ተከታዮች ሆነው ይታያሉ። እውነታው ግን ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ የመሠረተው አንድም የእምነት ድርጅት ወይም ተቋም  አለመኖሩ ነው። ጲላጦስ ከመሰቀሉ በፊት ኢየሱስን «እውነት ምንድር ነው?» ብሎ ስለሆነው ነገር ጠይቆት ነበር። ( ዮሐ 18፤38) እውነቱ ግን ሰዎች «እስኪ ራሱን ያድን» እያሉ እየተዘባበቱበት የሰቀሉትን ኢየሱስን ማመን ነበር። አይሁዳውያን ሰዎች ራሷን ማዳን የማትችል ምድራዊት የእምነት ተቋም ስለነበራቸው ከእምነት እንጂ ከተቋም ስላልሆነችው የኢየሱስ ስብከት ጆሮአቸውን አልሰጡም። ስለዚህም እውነቱ አመለጣቸው። ዛሬም ሰዎች ክርስቶስን እናምናለን ቢሉም ከተቋምና ከድርጅት ስብከት አልወጡም። በዓለም ላይ በተለያየ ስም የተከፋፈለው የእምነት ተቋም መሠረቱ በሰዎች አስተምህሮ ላይ የተንጠላጠለ ነገር ግን ክርስቶስ ያጠለቀ በሚመስል ድርጅት የሚጠራ መሆኑ ነው። እውነቱ ግን «እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም» ባለው ቃል ጸንቶ መገኘት ብቻ ነው። የምናምነውን ነገር በወንጌል መነጽር እንመርምረው። ወንጌል ካስተማረው ውጪ የሆነው ሁሉ ከሰይጣን የተገኘ ነው።

 
ሚዝራ ጉላም አህመድ (1835-1908)

 ይህ በሃይማኖቱ እስላም የሆነ ሕንዳዊ ዜግነት የነበረው ሰው በአንድ ወቅት ራሱን እንዲህ ሲል ገልጾ ነበር። እስላሞች በመጨረሻው ቀን ከሰማይ ይመጣል ብለው የሚጠብቁት «ማህዲ» የተባለውን ነብይና ክርስቲያኖች ለፍርድ ዳግም ይመጣል ብለው የሚጠባበቁት «ኢየሱስ»ን የምወክል ስሆን እነሆ ሁለቱም በእኔ ውስጥ በሥጋ ተገልጸዋልና ተከተሉኝ በማለት ሲለፍፍ ቆይቷል። ማሳሳት ጥንተ ግብሩ የሆነው ሰይጣን በህንዳዊው አህመድ ውስጥ አድሮ እሱን ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች መሳሳት ምክንያት ሆኖ ከእስልምና ሴክት/ክፍል/ አንዱ የሆነውን «አህመዲያ» የተባለው ቅርንጫፍ ፈጥሮ በማለፍ ዛሬም ድረስ ከ20 ሚሊዮን ያላነሱ አባላትን በዓለም ዙሪያ ማፍራት ችሏል።

ሎ ደ ፓሊንግቦኸር (1898- 1968)

በዜግነቱ ኔዘርላንዳዊ የሆነው ፓሊንግቦኸር በሙያው የተዋጣላት ዓሳ አጥማጅ ነበር። በዓሳ አጥማጅነት ሥራው ከሱ ዘንድ ዓሳ ለመግዛት ለሚመጡ ሸማቾች በትንሹ የጀመረውን ስብከት አሳድጎ በስህተት ሰው ወደ ማጥመድ ሥራ አሳደገው። ተከታዮችን ማፍራቱን እንዳረጋገጠ የዓሳ ጀልባውን በመሸጥ ስብከቱን የሙሉ ጊዜው ሥራው በማድረግ የቀጠለ ሲሆን ዓለም ከክፉ ነገር ሁሉ የምትድነው እኔን በማመን ነው እያለ በየጎዳናው ይለፈልፍ ነበር። ትምህርቱን እንደትክክለኛ አድርገው የተቀበሉ ተከታዮቹ ትልቅ የመኖሪያ ቤት ገዝተው የሰጡት ሲሆን በስተመጨረሻም እኔ «ኢየሱስ» ነኝ በማለት ስብከቱን ገፍቶበታል። አንዳንዶች ይህ ሰው ከሀዲ ነው ብለው ቢያወግዙትም ፓሊንግቦኸር «እግዚአብሔር» ወደመሆን ይለወጣል በማለት ይከራከሩለት የነበሩ ተከታዮችን ማፍራት ችሏል። ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ አግብቶ በመፍታት የሚታወቀው ይህ ቀሳጢ እንኳን ሌሎችን ሊያድን ይቅርና ራሱን ከሞት ማዳን ሳይችል ቀርቶ እስከወዲያኛው አሸልቧል።

ኃይለሥላሴ (1892-1975)

 የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት የነበሩት አፄ ኃይለ ሥላሴ ራሳቸውን እንደመሲህ አድርገው ባይቆጥሩም መሢህ ናቸው የሚሏቸው ወገኖች አሉ። ንጉሡ በአንድ ወቅት በሳቸው ዙሪያ ስለሚባለው ነገር ተጠይቀው «እኛ ሰው ነን እንጂ መሲህ አይደለንም» ብለው የመለሱ ቢሆንም ተከታዮቻቸው በንጉሡ ምላሽ ዙሪያ የሰጡት ማስተባበያ «የኛ መሲህ ያለውን ትህትና ተመልከቱ» በማለት የንጉሡን ምላሽ ከአትህቶ ርእስ ጋር በማያያዝ ለማሳመን ቢሞክሩም እውነታው ግን አፄው መሲህ አለመሆናቸው ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለውለታ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አፄ ኃይለ ሥላሴ ለመታሰቢያቸው አርኬ እና መልክእ በመድረስ በነግህና በሰርክ ጸሎት ታስባቸው ነበር። አንዳንዶች የዋሃን አፄው አይሞቱም የሚል ግምት የነበራቸው ቢሆንም ደርግ የገደላቸው መሆኑ ይታወቃል። ከጃማይካ ህዝብ 5% የሚሆነው የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታይ ሲሆን በአሜሪካም ብዙ አባላት አሉት።

ኤርነስት ኖርማን (1904-1971)


  አሜሪካዊ የኤሌክትሪካል ኢንጂነር ባለሙያ የነበረና (ዩራንየስ አካዳሚ ኦፍ ሳይንስ) መስራች የሆነ ሰው በአንድ ወቅት ከሙያው ውጪ እብደት መሰል ስብከት ጀምሮ ነበር። ከዚህ በፊት በዚህ ምድር ላይ የተገለጸው «ኢየሱስ» እኔ ነበርኩ። ወደሰማይ ባርግም በዚህ ምድር ላይ በሊቀ መልአክ ሩፋኤል አምሳል ነበርኩኝ እያለ ቢቀላምድም ተከታዮችን ከማፍራት የከለከለው ነገር አልነበረም። ይሁን እንጂ ይህ የዘመኑ ቀሳጢ እንኳን ለሌሎች ሊተርፍ ይቅርና ለራሱም መሆን ሳይችል ቀርቶ በጉሮሮ ህመም ሲሰቃይ ቆይቶ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

ክሪሽና ቬንታ (1911-1958)

 ቬንታ በሳንፍራንሲስኮ የተወለደው ሲሆን በሁለተኛው ዓለም ጦርነት የአሜሪካ ወታደር በመሆን አገልግሏል። ከተመለሰም በኋላ ቀደም ሲል አቋቁሞት የነበረውን ተቋም በማንቀሳቀስ 1948 ዓ/ም «የጥበብ፤ የእውቀት፤ የእምነትና የፍቅር ፏፏቴ» የተሰኘ የክህደት ድርጅት ሥራውን ጀምሯል። ቬንታ የክህደት ደረጃውን በማሳደግ «እኔ ኢየሱስ ነኝ» ከማለቱም ባሻገር የማኅበሩ አባል ለሚሆኑ ሰዎች «ያላችሁን ሀብትና ንብረት ለማኅበሩ ገቢ አድርጉና ሰማያዊ መዝገብ አከማቹ» በማለት ሀብታቸውን በመሰብሰብ ለበጎ አድራጎት ሥራ ለማዋል የሞከረ ቢሆንም ሀብታቸውን ተሞልጨው፤ ሚስቶቻቸውን በቬንታ የማማገጥ ተግባር የተፈጸመባቸው ሁለት ተከታዮቹ በቂም በቀል ተነሳስተው ቦንብ በማፈንዳት አብረው ሊሞቱ ችለዋል። የክሪንሽና ቬንታ የክህደት ተግባርም እስከወዲያኛው በዚያው አክትሟል።

አህን ሳንግ ሆንግ (1918- 1985)

 በደቡብ ኮሪያ የተወለደ ይህ ሰው  በ1964 ዓ/ም «የአዲስ ኪዳን ፋሲካ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን» የሚል የሃይማኖት ተቋም መስርቶ ነበር። በኋላ ላይ ደግሞ «ዓለም አቀፍ የተልእኮ ማኅበር የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን»  የሚል ሁለተኛውን ድርጅት አቋቁሟል። ሳንግ ሆንግ እሱ የኢየሱስ ዳግም ምጽአት ምልክት መሆኑን ይሰብክ ነበር። በአዲስ ኪዳን ፋሲካ ቤተ ክርስቲያኑ እንደመምህር ሲቆጠር በዓለም አቀፍ የተልእኮ ቤተክርስቲያኑ ደግሞ እንደእግዚአብሔር ይቆጠራል።  የቤተክርስቲያኒቱ ዋና አመራር የሆነችው ዛንግ ጊልጃህ የተባለችው ሴት በገላትያ 4፤26 ላይ የተመለከተውን ትንቢት የምታሟላ እሷ ናት ስለሆነች «የኢየሩሳሌም እናት» ወይም «የእግዚአብሔር እናት» ተብላ ትጠራለች።
የቤተ ክርስቲያኑ መሥራች ሳንግ ሆንግ ደግሞ «እግዚአብሔር አብ» ተብሎ ይጠራል።


ሱን ሚዩንግ ሙን (1920- 2012)


 በሰሜን ኮሪያ ተወልዶ በደቡብ ኮሪያ ያደገው ሙን «የውህደት ቤተ ክርስቲያን» መሥራች ሲሆን ራሱን ሁለተኛው ኢየሱስ እንደሆነና  ከዚህ ቀደም ኢየሱስ በሥጋ ተገልጦ ሳለ ሳይጨርሳቸው የሄደውን ጉዳይ የሱ መገለጽ ማስፈለጉን በአደባባይ የሚናገር ሰው ነበር። ሚስተር ሙን ባለቤቱን « ሃክ ጃን ሃን»ን የሚጠራት አዳምና ሔዋን ያበላሹትን ዓለም በማጽዳት መልካም ቤተሰብን በዓለም ላይ ለመመሥረት የተፈጠረች ናት በማለት ያሞካሻት ነበር። ሙን «የተባረከ የኅብረት ጋብቻ» በሚል ዘመቻ በአንድ ቀን እስከ 30 ሺህ የሚቆጠሩ ጥንዶችን  አሜሪካ ባለችው በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ጋብቻ በማስፈጸም ዝናው ይታወቃል። ሙን በአሜሪካን ሀገር ሳለ በፈጸመው የታክስ ማጭበርበር ወንጀል ተከሶ 18 ወራት ተወስኖበት፤ ከዚህ ውስጥ የ13 ወራት እስራቱን ቅሞ በአመክሮ ሊለቀቅ ችሏል። ሱን ሙን  ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ሃብት ያለው ሲሆን የተለያዩ ኮርፖሬሽኖችንና የአክሲዮን ማኅበራት አሉት። ሃሳዊው ሙን በተወለደ በ92 ዓመቱ በኒሞንያ በሽታ ሞቶ እስከወዲያኛው ተቀብሯል። እሱ ቢሞትም በሱ የሀሰት ትምህርት የተታለሉ 4 ሚሊዮን አባላት በተለያዩ የዓለም ሀገራትን ለማፍራት ችሏል።

ይቀጥላል%

Wednesday, September 10, 2014

በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ!



እኛ ነን ወደአዲሱ ዓመት የደረስነው ወይስ ዘመኑም እንደእኛው እየሄደ ነው? 

  ቆሞ የሚጠብቅ ዘመን የለም። ዘመኑም እኛም በዘመኑ ውስጥ እየሄድን ነው። እግዚአብሔር በዓመት፤ በዓመቱ የሚሰራው አዲስ ዘመን የለም። እግዚአብሔር ዘመናትን የሠራው አንድ ጊዜ ነው።  በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተሠራው ዘመን በራሳችን እድሜ ላይ ሲቆጠር «አዲስ ዘመን» ከማለታችን በስተቀር ዘመኑም ለማለቅ ራሱ ወደእርጅና እየተጓዘ ነው።  ሰውም ዘመናትም የማለቂያ እድሜ አላቸው። ዘመናት የተሠሩት፤ ለሰው ልጆች አገልግሎትና የእግዚአብሔርን ፈቃድ አውቀው መልካሙን ሁሉ ይሠሩባቸው ዘንድ ነው። እንኳን «ለአዲሱ ዘመን አደረሰን!» ስንል እኛ በዘመን ውስጥ መታደሳችንንና መለወጣችንን መናገራችን ነው። እንደዚያ ካልሆነማ ዘመናት የተሠጣቸውን ግዳጅ እየፈጸሙ ወደተሰጣቸው እርጅና እየሄዱ እንጂ መቼ ቆመው ይጠብቁናል? ክረምትና በጋ፤ ብርሃንና ጨለማ፣ ዘርና ማዕረርን ዘመናት ከመስጠት አለማቆማቸውና በዘመን ስሌት መፈራረቃቸው እስከጊዜው የተሰጣቸውን ግዳጅ እየተወጡ መሆናቸውን ልብ ልንል ይገባል። እድሜአቸው አልቆ እስኪጠቀለሉም ይህንኑ ግዳጃቸውን ይወጣሉ። 

  መዝ 102፤25-26 «አቤቱ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል»

ሐዋርያው ጴጥሮስም በመልዕክቱ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደምንጠባበቅ መናገሩ አሁን ያለን ሰማይና የምንኖርባት ምድር አርጅተው እንደሚለወጡ በግልጽ ያስረዳናል።

2ኛ ጴጥ 3፥13 «ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን»

 ስለዚህ በዘመን ውስጥ በእድሜ ጣሪያ የምንጓዝ እኛ የሰው ልጆች ምን ማድረግ ይገባናል?
በጎ መመኘት በጎ ነው። በጎ መመኘት ብቻውን በጎ ነገር አያመጣም። የተመኘነውን በጎ ነገር ለመሥራት በጎ ጥረት ያስፈልገናል። አዲስነት ከእኛነታችን ውጪ የሚገኝ አይደለም። ዘመን በተቆጠረ ቁጥር «እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ» መባባሉ ጥሩ ቢሆንም ባልተለወጠ ማንነታችን ውስጥ ምን አዲስ ለውጥ አይመጣም። መታደስ፤ መለወጥ ለሰው ልጆች ማንነት ልዩ ግኝት ስለሆነ መለወጥ ያለብን እኛ ነን።

 ቁጡና ቂመኛ ሆነን ስለአዲሱ ዘመን ማውራት ምን ይጠቅማል? በውሸትና በቅድስና ጉድለት እየኖርን ከጉዞው ጨብጠን ልናስቀረው ስለማንችለው አዲስ ዘመን መልካምነት መመኘት በራሱ የሚጨምርልን አንዳች ነገር የለም።
ይልቁንስ ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረውንና ሁልጊዜ እያነበብን ለመተግበር የተቸገርነውን በጎ ነገር እየፈጸምን ስለአዲስ ዘመን በጎ ምኞት እናስብ። 

 «በእርግጥ ሰምታችሁታልና፥ እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል፤ ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ። ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፥ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም። ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ»  ኤፌ 4፤21-32

አለበለዚያ ዘመን ካልሰራንበት «እንኳን አደረሳችሁ ሲባባሉብኝ ጊዜያቸውን በከንቱ ፈጸሙ\ ብሎ በኋለኛው ቀን እንዳልሰራንበት ይመሰክራል።
«ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል» ስለዚህ ንስሐ እንግባ፤ በልባችንም መታደስ እንለወጥ! ለዚህም እግዚአብሔር ይርዳን! አሜን!

Saturday, September 6, 2014

በምድራችን ላይ በክፉ መንፈስ ተነድተው ሕዝብን ያሳሳቱ ሀሰተኛ ክርስቶሶችና ነብያት!


አን ኤልዛቤጥ  ሊ (1736-1784)
በእንግሊዝ አገር የተነሳችና «ተንቀጥቃጮች» የተሰኘ ሃይማኖት የፈለሰፈች፤ ተከታዮቿም «እናታችን» እያሉ የሚጠሯት ሀሳዊ ክርስቶስ ሆና ተነስታ ነበር። ስታስተምርም ራሷን የምትገልጸው እኔ በሴት መልክ የተገለጥኩ ሁለተኛው ኢየሱስ ነኝ እያለች ብትሰብክም እንኳን ለሌላው ልትተርፍ ይቅርና እራሷን ማዳን ሳትችል ቀርታ እስከምጽአት የመጨረሻውን ፍርድ ድረስ ላትነሳ ሞታ በድንጋይ ታትማለች።


        **************************************************


ጆን ኒኮላስ ቶም (1799-1838)
በእንግሊዝ ሀገር ኮርንዎል ተወልዶ ያደገና  የወይን ነጋዴ ሆኖ ሲሰራ የቆየ ሰው ነው። በሥራውም ላይ በታክስ ማጭበርበር ተከሶ እንደነበር የህይወት ታሪኩን የመዘገበው የኮርንዎል ቤተ መዛግብት ፋይል ያስረዳል። ቶም ሽቅርቅርና መዓዛው በሚያውድ ሽቶ ልብሱን ነክሮ፤ ጢሙን አሳድጎ የሚዞር ሰው ሲሆን የብዙዎችንም ቀልብ መሳብ የቻለ ነበር። ቶም ከወይን ነጋዴነት፤ ከጋዜጣ አዘጋጅነትና ገበሬዎችን ከአነስተኛ ንግድ ባለቤቶች ጋር በጥምረት የዐመጽ መሪነት ድረስ ሲ,ሰራ ቆይቷል። የሕይወት ስኬት ሲጎድለው ከእለታት አንድ ቀን ድንገት ተነስቶ «ሁለተኛው ኢየሱስ ሆኜ በሥጋ ተገልጫለሁ» በማለት ወደስብከት የገባ ሲሆን ተከታዮችን ካፈራ በኋላ በ1834 ዓ/ም ጀምሮ ወደቅዱስ መንፈስ ተቀይሬአለሁ ቢልም ባልተላቀቀው የዐመጽ መሪነቱ ተግባሩ ቀጥሎ በግንቦት 31/1838 ኬንት ከተማ ላይ በጥይት ተገድሎ እስከወዲያኛው ላይነሳ ያሸለበ ሰው ነው።

**************************************************


አርኖልድ ፖተር (1804-1872)
«የኋለኛው ቀን ቅዱሳን» የተባለው የክርስትና ክፍል መሪ የነበረ ሰው ነው። ፖተር በኒውዮርክ ተወልዶ፤ በኢንዲያና ውስጥ በኋለኛው ቀን ቅዱሳን በተባለ ቤተ ክርስቲያን የተጠመቀ ሲሆን በኢሊኖይስ ላይ ደግሞ የሞርሞን ቤተ ክርስቲያን መሥራች በሆነው በጆሴፍ ስሚዝ «ካህን፤ ሽማግሌና የቡራኬ አበው» ተብሎ ደረጃ በደረጃ የተሾመ ሰው ነበር። እስከአውስትራሊያ ድረስ ለስብከት የተጓዘው ፖተር «የኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ በኔ ውስጥ በመግባቱ ከዛሬ ጀምሮ እኔ ሌላው ኢየሱስ ነኝ» እያለ ሲያስተምርና ተከታዮችን ሲያፈራ ቆይቷል። በኋላ ላይ ወደካሊፎርኒያ ተመልሶ በ1872 ዓ/ም ወደሰማይ የማርግበት ሰዓት ደርሷል በማለት የአህያ ውርንጫ ተቀምጦ ከገደል አፋፍ ላይ በደመና ለማረግ ሲጋልብ ወደላይ መውጣቱ ቀርቶ ቁልቁል እስከነ አህያዋ በመምዘግዘግ  ፖተር ዳግም ላይመለስ እስከወዲያኛው አሸልቧል።

         **************************************************

ጆንስ ቬሪ 1813-1880
 ፀሐፊ ተውኔት፤ ገጣሚና በሐርቫርድ የግሪክ ቋንቋ መምህር የነበረ ሰው ነው። ቬሪ እጅግ የጠለቀ እውቀትና ሙያ ያለው ሰው ቢሆንም ከእለታት አንድ ቀን  ለተማሪዎቹ «በማቴዎስ 24 ላይ ዳግም ይመለሳል የተባለው ኢየሱስ እኔ ነኝ» በማለት የተናገረ ሲሆን ይህንኑ ስብከቱን ቀጥሎበት ቀይቷል። በኋላ ላይ  በአእምሮ በሽታ ክፉኛ በመጠቃቱ ለከፍተኛ ጭንቀት ህመም ተጋልጦ  እህቱ እሱን የማስታመም ኃላፊነት ወድቆባት ነበር።  ቬሪ «ኢየሱስ ነኝ» እያለ ቢሰብክና ብዙዎችንም ቢያታልል ከአእምሮው በሽታ ሳይድን  በ1880 ዓ/ም በተወለደበት በማሳቹሴትስ ሞቶ በትልቅ ሃውልት መቃብሩ ተደፍኖ ዛሬ ድረስ ይታያል።




******************************************



ባሃ ኡላህ (1817-1892)
የእስልምናው አንዱ ክንፍ ከሆነውና በዛሬይቱ ኢራን ያለው የሺአይት እስላም ቤተ ሰብ የተወለደው ባሃኡላህ በዚሁ እምነት ስር ያደገ ሲሆን ሃይማኖታዊ ፍልስፍናው በፈጠረበት ስሜት ተነሳስቶ ዓለም በአንድ እምነትና መተሳሰብ ስር መጠቃለል አለባት ብሎ በመነሳት ራሱን «የባቢ እምነት» ፍጻሜ ነብይ አድርጎ በመቁጠር ከሺአት ተገንጥሎ በስሙ የባሃኡላህ እምነትን የመሠረተ ሰው ነው። ትምህርቱንም በባግዳድ ጀምሮ በእስልምና ህግ ተይዞ በሃይፋ/ እስራኤል/ እስከተሰቀለበት ቀን ድረስ እኔ የመጨረሻው የእግዚአብሔር ነብይ ነኝ፤ በኋለኛውም ቀን ለፍርድ እመጣለሁ ሲል የነበረ ሰው ነው። ይህ የሃይፋው ዋናው የባሃኢ እምነት ማእከል በዓለም ላይ ላሉ የእምነቱ ተከታዮች ቅዱስ ስፍራ ሲሆን አጠቃላይ መመሪያው የሚመነጨው ከዚሁ ከሃይፋው ማእከል ነው። 
 እግዚአብሔር ራሱን በሰው አምሳል ከገለጸባቸው መንገዶች አንዱ ባሃኡላህ ሲሆን የሰዎችን ነፍስ በማጥራት ምድርን ወደገነት የመቀየር ተልዕኮ ያነገበ እሱ ብቻ መሆኑን ሲሰብክ ቆይቷል። ባሃኢዎች እንደመንፈስ አባታቸው ሲዖልና ገነት ተብለው በሰዎች አእምሮ የተሳሉ ግምቶች እንጂ በእውን ሰዎችን ለመቅጫ በእግዚአብሔር የተፈጠሩ አይደለም ይላሉ። ባሃኡላህ የሞተው በ1892 በስቅላት ነው።
ሃይፋ/እስራኤል የባሃኢ ዋና ማእከል


*******************************************


ዊሊያም  ዳቪየስ (1833-1906)
የሞርሞን ቤተ ክርስቲያን ቅርንጫፍ በሆነውና የኋለኛው ቀን ቅዱሳን በተባለው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሪ የነበረ ሰው ነው። በደቡብ የዋሽንግተን ስቴት ዋላዋላ ከተማ ላይ «የእግዚአብሔር መንግሥት» ማኅበርን መስርቷል። ተከታዮቹንም «እኔ ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሚካኤል ነኝ» በማለት ያስተማረ ሲሆን «አዳም፤ አብርሃም፣ ዳዊት» ሆኖ ከዚህ በፊት በምድር ላይ የመጣውም እሱ ራሱ መሆኑንም በድፍረት ይናገር ነበር። በኋላ ላይ ሚስት አግብቶ በየካቲት 11/1868  «አርተር» የተባለ ልጁን እንደወለደ  ልጁን «በሥጋ የተገለጠ የእግዚአብሔር ልጅ» ነው በማለት ሲናገር «ዴቪድ» የተባለ ሁለተኛ ልጁን ሲወልድ ደግሞ እኔ ወደ «እግዚአብሔር አብነት» ተቀይሬአለሁ እያለ ይሰብክ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ሁለቱም ልጆቹ በጉሮሮ በሽታ ሲሞቱ ተከታዮቹ ባቀረቡበት ክስ የቤተ ክርስቲያኑን ንብረት ሸጦ በመክፈልና ከተማውን ለቆ ወደካሊፎርንያ በመሰደድ መልሶ ለመደራጀት ሞክሮ ሳይሳካለት ልጆቹን እንደቀበረ ሁሉ እሱም ሞቶ ድንጋይ ተጭኖት ይገኛል።



 ይቀጥላል%