Wednesday, February 29, 2012

ዳንኤል ክብረት፣ ዘበነ ለማና ምህረተአብ ሃዋሳ ላይ ለመስበክ መመሪያ አይፈቅድላቸውም!

 የአቡነ ገብርኤል የገጽታ ግንባታ ተግባር!

የተሰደዱት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ጉባዔውን ለማደናቀፍ ምንም ዓይነት ዕቅድ እንደሌላቸው አስታወቁ

በሀዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ከመጪው የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ መንፈሳዊ ጉባዔ ሊዘጋጅ እንደሆነ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅና የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ስምዓ ጽድቅ ተከፋይ ዐምደኛ መልአከ ብርሃን ይትባረክ ታጠቅ ድምፅ ማጉያ ይዘው በሹሽሹክታ ለሕዝብ መናገራቸውን መግለጻችን ይታወሳል፡፡  በሀዋሳ ዳቶ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ለእመቤታችን በዓለ ንግሥ ለተሰበሰበው ሕዝብ ዳንኤል ክብረት፣ ዘመድኩን በቀለና ዘማሪ ቴዎድሮስ ዮሴፍ ሄደው እንደሚያስተምሩ መናገራቸውን ጭምር መግለጻችን አይዘነጋም፡፡ ሆኖም አሁን በደረሰን መረጃ ሄደው የሚያስተምሩት መ/ር ዘበነ ለማ ከአሜሪካ፣ ዳንኤል ክብረት፣ መ/ር ምሕረተአብ አሰፋ፣ ዘማሪ ቴዎድሮስ ዮሴፍና ሌሎችም ስማቸው ያልተገለጹ ሰዎች እንደሆኑ ታውቋል፡፡

ይሁን እንጂ የመ/ር ዘበነ ባይታወቅም ዳንኤል ክብረት ከፍተኛ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" አመራር፣ እንዲሁም መ/ር ምሕረተ አብ አሰፋ የ"ማኅበሩ" አባልና ደጋፊ በመሆናቸው ሄደው ለማስተማር ቀደም ሲል የተላለፉ መመሪያዎች እንደማይፈቅዱላቸው ታውቋል፡፡ እነዚህም:-
  1. ክቡራን የመንግሥት ሚኒስትሮች በታዛቢነት በተገኙበት አቡነ ገብርኤል ራሳቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ሆነው መስከረም 12 ቀን 2002 ዓ.ም በተካሄደው የሠላም ጉባዔ የወሰኑትና የፈረሙበት "ማኅበረ ቅዱሳን" በማናቸውም የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅሮች ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ ጥቅምት 6 ቀን 2002 ዓ.ም በቁጥር 44/70/2002 መመሪያ ወጥቷል፡፡
  2. የሀዋሳን ግጭት ለማብረድ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የተመራው አጣሪ ቡድን ያቀረበው ሪፖርት ግጭቱ የተከሰተው ተስፋ ኪዳነ ምሕረትና ፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ ማኅበር እና "ማኅበረ ቅዱሳን" ባስነሱት ሁከት መሆኑን ይገልጽና ተስፋ ኪዳነ ምሕረት ማኅበርን ጨምሮ "ማኅበረ ቅዱሳን" እንደማንኛውም ተቋምና ግለሰብ አስቀድሶና ተገልግሎ ከመውጣት በስተቀር በቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡና በዐውደ ምሕረት ላይ እንዳያስተምሩ፣ የካቲት 2 ቀን 2003 ዓ.ም በቁጥር 92/54/2003  ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት መመሪያ ተላልፏል፡፡

Monday, February 27, 2012

በክብረ መንግሥት የማኅበረ ቅዱሳን ግጭት

በጉጂ ቦረና ሀገረ ስብከት በክብረ መንግሥት (አዶላ ወዩ) ከተማ ዓርብ የካቲት 16 ቀን 2004 ዓ.ም "ማኅበረ ቅዱሳን" በቀሰቀሰው ግጭት የእመቤታችን የቅድስት ኪዳነ ምሕረት በዓለ ንግሥ ሳይከበር መዋሉን ከሥፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ በክብረ መንግሥት (አዶላ ወዩ) ከተማ በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ዓመታዊ በዓለ ንግሷ የሚከበረው የእናታችን የኪዳነ ምሕረት መታሰቢያ በዓለ ንግሥ ሳይከበር የዋለው በአካባቢው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፣ የቅዳሴ ሥርዓቱም ሳይካሄድ ቤተመቅደሱ ተቆልፎበት መዋልና ማደሩን አረጋግጠናል፡፡ የግጭቱ መነሻ የሆነው "ማኅበረ ቅዱሳን" በመላው ዓለም ከጠረፍ እስከ ጠረፍ እንደሚያደርገው ሁሉ በክብረ መንግሥትም እኔ ያልፈቀድኩት ሥርዓት አይካሄድም፤ እኔ ያልፈቀድኩለት አገልጋይ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ አይደርስም በሚል ትዕቢት ተነሳስቶ የቀሰቀሰው ሁከት ነው፡፡ የሁከቱ ቀንደኛ መሪ ሲያምር ተክለ ማርያም የተባለ የቀድሞው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ የነበረ ሰው መሆኑ ታውቋል፡፡ ይኸው ግለሰብ በሀገረ ስብከቱ መኪና ኮትሮባንድና ሌላም ሌላም የንግድ ሥራ ሲሠራበትና "ማኅበረ ቅዱሳን"ን ሲያገለግልበት ቆይቶ፣ በዚሁ የሙስና ሥራውና የመልካም አስተዳደር ብልሹነቱ የተማረረው ሕዝብ እንዲነሳለት ለጠቅላይ ቤተክህነት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ካለፉት ስድስት ወራት በፊት ከቦታው ተነስቶ አዲስ አበባ ወደሚገኘው ትንሣኤ ዘጉባዔ ማተሚያ ቤት የተዛወረ ሰው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ግለሰቡ፣ የጠቅላይ ቤተክህነቱን ሕጋዊ አሠራር ተቀብሎና አክብሮ በማተሚያ ቤቱ መደበኛ ሥራው ላይ ተገኝቶ መሥራት ሲገባው የሀገረ ስብከቱን ተሽከርካሪ መኪና ይዞ በመሰወር የግል ጥቅሙን ሲያሳድድበት መክረሙን በዚሁ ብሎጋችን መዘገቡ አይዘነጋም፡፡ የቦረና ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ የጽ/ቤቱን መኪና ይዘው ተሰወሩ በሚል ርዕስ ያቀረብነውን ዘገባ እዚህ እዚህይመልከቱ ሰውዬው የሚደረግበትን የፖሊስና የኅብረተሰቡን ክትትል በመፍራት ባልተጠበቀ ሰዓት መኪናዋን ሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አቁሟት የጠፋ ሲሆን፣ ከጊዜ በኋላ ደግሞ አረሳስቶ ብቅ ማለቱንና ጽ/ቤቱን እንደገና መውረሱን የአካባቢው ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ ይህ ግለሰብ፣ የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤትና በእጁ የሚገኘውን ንብረት አላስረክብም ብሎ ሙጭጭ ከማለቱም በላይ የ"ማኅበረ ቅዱሳን"ን ጭፍሮች በዙሪያው በመኮልኮል፣ በምትኩ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተመደቡትን ሊቀ ትጉሃን ተሾመ ኃ/ማርያምን አላሰገባም በማለት ከስድስት ወራት በላይ ሲያንከራትቷቸው መቆየታቸው ታውቋል፡፡

Friday, February 24, 2012

ለእንዳለ ገብሬ 200ሺህ ተዋጣ!


ቀሪውን 250 ሺህ ብር ሰፋ ባለ መርሐ ግብር ለማሟላት ዕቅድ ተይዟል
በከፍተኛ የልብ ሕመም በመሰቃየት ላይ ላለው ወጣት እንዳለ ገብሬ መታከሚያ በአንድ ቀን መንፈሳዊ አገልግሎት 200 ሺህ ብር ያህል ማሰባሰብ መቻሉን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ (ታሪኩን በይበልጥ ለመረዳት፣ ከዚህ ቀደም ሲል ስለ ወጣቱ ችግር ካወጣናቸው ዘገባዎች ጋር ያስተያዩት) ይህንን ያህል ገቢ ሊሰባሰብ የቻለው በአሁኑ ወቅት "ማኅበረ ቅዱሳን" በሚያሳድዳቸው ውድ የሆኑት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የስብከተ ወንጌልና የመዝሙር አገልጋዮች ባዘጋጁት መንፈሳዊ ጉባዔ ነው፡፡
የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ.ም ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በሻላ 17 17 መናፈሻ አዳራሽ በተካሄደው በዚህ መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ በግል በአድራሻ ጥሪ የተደረገላቸው ሦስት መቶ ያህል ሰዎች ተገኝተው ግማሽ ያህሉን ገንዘብ የለገሡ ሲሆን ቀሪውን ግማሽ መጠን በቃል መግቢያ ሠነድ እንደሚሰጡ ማረጋገጣቸው ታውቋል፡፡ የዕለቱን መርሐ ግብር የመራው መምህር ተረፈ አበራ ሲሆን፣  መምህር ታሪኩ አበራም በበኩሉ የወደቀውን ስላነሳው የደጉን ሣምራዊ ታሪክ ከወንጌል ጋር በማጣቀስ፣ ችግር ላይ የወደቁትን ወገኖች መርዳት ክርስቲያናዊ ግዴታችን መሆኑን ሰፋ ባለ ሁኔታ ትምህርት ሰጥቷል፡፡