«ዴር ሡልጣንን በዐሥር ዓመት ውስጥ ልናጣው እንችላለን» ዳንኤል ክብረት ለአዲስ ጉዳይ መጽሔት እንደተናገረው
በመለኮታዊ ተአምራት ኢየሩሳሌም ካልተገለባበጠች ወይም
ሰማይና ምድር ካላለፈ በስተቀር ዴር ሡልጣንን የሚያሳጣን ምንም የሚታይ ክስተት የለም!(ደጀ ብርሃን)
የዴር ሡልጣን ገዳም አሁን ያለበት ይዞታ በ21ኛው ክ/ዘመን ላይ ሊሆን ይገባው በነበረበት ሁኔታ ላይ እንዳይደለ ማንም
ቦታውን ያየ ሊያረጋግጠው የሚችለው ሐቅ ነው። ይሁን እንጂ የዴር ሱልጣን ይዞታ ተገቢውን እድሳት አለማግኘቱና ለኑሮ ምቹ አለመሆኑ
ብቻውን የርስቱን ባለቤትነትና በኢትዮጵያውን እጅ የመቆየቱን ሀብትነቱን ሊለውጠው የሚችል ምንም ነገር አልተከሰተም። ይህንን
የርስቱን ባለሀብትነት በሚቀጥሉት ዐሥር ዓመታት ውስጥ ከኢትዮጵያውያን እጅ ሊያወጣ የሚችልና የሚታይ ነባራዊ ክስተት በሌለበት ሁኔታ
ውስጥ ያለውን ችግር ለማግዘፍና ንግግር ለማሳመር ሲባል ብቻ በሚቀጥሉት ዐሥር ዓመታት ውስጥ ዴር ሡልጣንን ልናጣው እንችላለን በማለት
መደስኮር ሰማያዊ ቁጣ የመጣ አስመስሎ መዓት መጥራት ካልሆነ በስተቀር ከዐሥር ዓመት በኋላ ኢትዮጵያውያንን ከርስት ባለመብትነት
የሚያሳጣቸው ምንም ነገር አልታየም። ምቹ አይደለም፤ እድሳት ያስፈልገዋል
ማለትና አሳማኝ የመረጃ ጥናት በሌለበት ሁኔታ ከዐሥር ዓመት በኋላ እናጣዋለን ማለት ተገቢ ትንበያም፤ ግምትም ሆነ የተዋጣለት ጥንቆላ
አይደለም። ከዐሥር ዓመት በኋላ ይህ ግምታዊ ትንበያ ካልተፈጸመ ነብዩን ዋሾ ያሰኘዋል፤ የነብዩ አራጋቢዎችንም ተላውያነ ሀሰት ያስብላቸዋል።
ስለዴር ሡልጣን ቅርሳችን ትኩረት እንዲያገኝ ወይም ምን ያህል ችግር ላይ እንዳለ ለማስረዳት ከተጨባጭ እውነታው ያፈነገጠ
ዜና መስራት ለምን እንዳስፈለገ አይገባንም። አሳቢ መስሎ በመታየት የሆነ ቀዳዳ ለመክፈት ተፈልጎ ካልሆነ በስተቀር ከዐሥር ዓመት
በኋላ አሁን ባለው ይዞታ የመፍረስም ሆነ የኢትዮጵያ ቅርስ ከመሆን የሚያወጣው ተጨባጭና በጥናት የተደገፈ ማስረጃ የለም። ስለዚህ በጣም በተለጠጠ ዲስኩር
እናጣለን የሚያሰኝ ዘገባ እስከማውጣት መድረስ አግባብነት ይጎድለዋል። እስራኤላውያን ቦታው እንዳይፈርስ የሚፈልጉት ለባለቤቶቹ አዝነው ሳይሆን ሁሉንም
ሃይማኖቶች በማስተናገድ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት መሆኗን ለዓለም በማሳየት ለመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ ትኩሳት ድጋፍ ለማግኘት ጭምር
መሆኑ መጤን አለበት። ያልተጠናና ያልታወቀ ሕንጻ በእስራኤሎች ዘንድ ስለሌለ እንዲያውም ፈርሶ አደጋ የሚያደርስ ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል
ካወቁ አስቀድመው ራሳቸው ይከላከላሉ ወይም ቦታውን በአደጋ ክልልነት ፈርጀው ያሽጋሉ እንጂ ዝም ብለው የሚተውት ጉዳይ አይደለም። እስራኤሎች
የኢትዮጵያውያኑ ቤቶች በቅርብ ዓመታት ውስጥ እንደማይፈርሱ አሳምረው ያውቃሉ። ይሁን እንጂ ለኑሮ ተስማሚ አድርጎ ለመለወጥ ግን ያለመፈለጋቸው ዋናው ምክንያት ቤቶቹ እስኪፈርሱ ዝም ብለው ለማየት ስለፈለጉ ሳይሆን ይታደስ ዘንድ ለኢትዮጵያውያኑ የሚጮህላቸው ቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥት እንደሌላቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁ
ነው። ምንም የኋላ ግፊት በሌለበት ሁኔታ በእድሳት ሰበብ ከግብጽ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ራሷን ለማስገባት ስለማትፈልግ ጉዳዩን
እያለሳለሰች መያዙን መርጣለች። የኮፕቶችንም የይገባኛል ጥያቄ ተቀብላ ርስታችሁ ነው ብላ ባለመስጠት ለጩኸታቸው ዝምታን የመረጠችው
በታሪክም፤ በባህልና በፈላሽ ሞራ ትስስር በምትመሳሰላት በኢትዮጵያ ላይ ደባ በመፈጸም ታሪክን ለመሰረዝ ስለማትፈልግ ብቻ ነው።
እንዲያውም የኢትዮጵያ ነገሥታት አፄ ኃ/ሥላሴ ለዛሬዋ ወጭት ሰባሪ ኤርትራ ሲሉ ለእስራኤል ነጻነት በድምጸ ተዐቅቦ በተባበሩት ነገሥታት
ጉባዔ ላይ ድምጽ በመንፈጋቸው እስራኤሎች መቀየማቸው እርግጥ ነው። ደርግም በቀጥታ የፍልስጥኤሙ ፋታህ ቀንደኛ ደጋፊና ጸረ ምዕራባውያን
ስለነበር ያተረፈው ወዳጅነት ምንም አልነበረም። ኢህአዴግስ? ብንል ከእስራኤሎች ጋር ያዝ ለቀቅ ያለ ወዳጅነት እንጂ ይህንን ያህል
በተጋነነ ደረጃ የሚወራለት ወዳጅነት እንዳለው አይታይም። እንዲያውም
በሰፋፊ ኢንቨስትመንት ላይ ዐረቦቹ የተሻለ ግንኙነት አላቸው። እንደምናስበው እስራኤሎች በምሥራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ በፖለቲካ፤ በኢኮኖሚና
በወታደራዊ ኃይል ያደገች ሆና ማየት እንጂ መዳከም ይፈልጋሉ ተብሎ አይገመትም። ከታሪካዊነትና ከህዝቦች ትስስር ባሻገር መካከለኛው
ምሥራቅና ሰሜን አፍሪካ በዐረብ እስላማዊ ሰፊ ግዛት የተያዘ ሲሆን ቀይባህርን ተከትሎ ከዐረቡ ክልል ጋር ቅርብ የሆነችው ኢትዮጵያ
መዳከም ወይም መውደቅ ቢጎዳቸው እንጂ የሚጠቅማቸው ስላይደለ በብዙ መልኩ የምትመሳሰላቸው ኢትዮጵያን ማጣት አይፈልጉም። ይሁን እንጂ
የእንዳለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያውያን መሪዎች ከእስራኤል ወዳጅነት ማትረፍ የሚችሉበትን ትብብር ሲጠቀሙበት ባለመታየቱ እስራኤሎቹም
የኢትዮጵያውያንን ሁኔታ በጥንቃቄ ሲመለከቱት ቆይተዋል ብሎ መውሰድ
ይቻላል። ከዚህ አንዱ ማሳያ የዴር ሡልጣን ገዳም እድሳት ጉዳይ ነው። እንደታሪካዊ ትስስራችን ርስቱን ከግብጾች እጅ ወስዳ ለኢትዮጵያውያን
ስትሰጥ የራሷ መለኪያ ሚዛን ስለነበራት እንጂ ኢትዮጵያውያን ፖለቲካዊ ድጋፍ ስላደረጉላት አልነበረም። እንደፖለቲካዊ ርቀታችን ደግሞ
ኢትዮጵያውያንን አስደስታ ግብጾችን ማስቀየም ስለማትፈልግ በኢትዮጵያውያን መኖሪያ አካባቢ አንድ ሚስማር ሲመታ ሥራውን በማስቆም
ለግብጾች የይገባኛል ጥያቄ የቆመች መስላ በመታየት የኢትዮጵያውያኑን መብት ችላ ትላለች። ያለው ጫወታ ይህ ነው።
ለእድሳቱ መጓተትና ፍጻሜ አለማግኘት ዋናው ምክንያት ፖለቲካዊ እንጂ ሃይማኖታዊ ወይም የባለቤትነት ጉዳይ እንዳልሆነ
መረዳት ይቻላል። በመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ ትኩሳት ውስጥ ግብጾች የግብጽን ተሰሚነት ለማስጠበቅ ሲሉ ዜጋዎቻቸው የሆኑትን የኮፕቶችን
መብት በማንሳት እስራኤልን ሰንጎ በመያዣነት ይጠቀሙበታል። ምንም እንኳን ከአጠቃላይ የአካባቢው ፖለቲካ የማርገቢያ ስልት
ውስጥ ዴር ሡልጣን እንደዋናው ሆኖ ባይቆጠርም እንደ አንድ ጫፍ ሆኖ
ስለሚያገለግል እስራኤልም ኮፕቶቹን ባለመግፋት ወይም ባለማስኮረፍ ሽፋን እንደመብት ጠባቂ ሆነው በመታየት የግብጽን መንግሥት ዝምታ ለመግዛትና ግፊት ማብረጃ ስልት አድርገው ከሌሎች ስልቶች ጋር ደርበው ይገለገሉበታል ብሎ መገመት ይቻላል። ኮፕቶቹ
ክርስቲያኖችም ይህንን ስልት ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ርስቱን እንደክርስቲያን ቅርስ ሳይሆን እንደግብጽ መንግሥት የመካከለኛው ምሥራቅ
ሀብት አድርገው ስለሚያቀርቡ የመንግሥታቸው ድጋፍ ተለይቷቸው አያውቅም። በዚህ የተነሳ በኢየሩሳሌም ያሉ የኢትዮጵያውያን መነኮሳት
አኗኗርና ህንጻ እድሳት ጉዳይ የመንግሥታቸውም ሆነ የቤተ ክህነታቸው ድጋፍ ምንም ስለሌለ ድምጻቸው ለዘመናት ሰሚ አልባ ሆኖ ቀይቷል።
የርስቱ ባለቤት ነኝ የምትለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ጉዳይ ለመፍታት አንድም ጊዜ ጫና አድርጋ
አታውቅም። ርስቱ በመካከለኛው ምሥራቅ የኢትዮጵያን መንግሥት የሚወክል ሀብት ሆኖ ሳለ ይህንን ሀብት እንደሀገራዊ ሀብት ለማስከበር መንግሥትም አለመሞከሩ ያስገርማል። በቅርበት በመገኘት የግብጽን
የፖለቲካ ድምጽና ኃይል ማስተንፈሻ መንገድ አድርጎ ከመጠቀም ባሻገር ልማታዊ መንግሥት ነኝ የሚለውንም ቲዎሪ እንደማስተዋወቂያ መንገድ
ሊጠቀምበት በቻለ ነበር። ምክንያቱም ቅርሱ ኢትዮጵያን እንጂ ቤተ
ክርስቲያኗን ብቻ አይወክልምና ነው። መንግሥት አምባሳደር እያለ የሚያሞካሻት፤
ኢትዮጵያውያን ቀዳሚዎቹ ዝንጀሮዎች እንደሆንና የዝንጀሮነታችን አስረጂ መሆኗን እንድታረጋግጥልን ወደምድረ አሜሪካ ከተላከችው አጥንት
ይልቅ ዴር ሡልጣን ለመንግሥት ትልቅ ሥፍራ በኖረው ነበር። በምድረ እስራኤል የተተከለና የማይነቃነቅ ሰፊ ሀብትና ቅርስ በበለጠ
መንግሥታችንንም፤ ሕዝባችንንም መግለጽ በቻለ ነበር። መጠቀም አለመቻላችን ያሳዝናል ብቻ ሳይሆን የሚዛቀውን የታሪክና የክብር
ማንነት ገላጭ የሆነውን ቅርስ ለማየት አለመቻል ዓይን ያላቸው አመራሮች አለመኖራቸው ያሳያል። የኢትዮጵያን ስምና ክብር ለመተክል ብዙ ከሰሩ ቀደምት ነገሥታት ውስጥ እንደ
አፄ ዮሐንስ ለቦታው የደከመ ማንም የለም። አፄ ዮሐንስ ለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ገንዘባቸው፤ አንገታቸውን ደግሞ ለሀገራቸው ሰጥተዋል።
ሌሎቹም አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ማድረጋቸው ሳይዘነጋ መሆኑም ከግንዛቤ ይግባ። መሣፍንቱና መኳንንቱ እንዲሁም እቴጌ ጣይቱ በተለይ
ብዙ መስራታቸው መረጃዎች ያረጋግጣሉ። ከየትኞቹም መንግሥታት በተሻለ
ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ሊኖረው በቻለው በዘመነ ኢህአዴግ ግን ይህንን
ሀገራዊ ቅርስ ለመጠበቅና እንዲታደስ ለማድረግ የተደረገ መንግሥታዊ ትኩረት አንዳች ነገር አለመኖሩ ለምን ይሆን?
ቦታው ታድሶ ለሰው ልጅ ኑሮ እንዲስማማ የማድረጉ ሥራ ፖለቲካዊ መልክና ግፊት ካልያዘ በስተቀር በኢትዮጵያውያኑ ማኅበረሰብ
የሚቻል አይደለም። የኮፕት ቤተ ክርስቲያን ከነ መንግሥታቸው በእጃቸው የሌለውን ርስት ለመውሰድ ጫና ሲፈጥሩ የኛዎቹ ቤተ ክህነትና
ቤተ መንግሥት ግን ገዳማውያኑ በገዛ ቤታቸው ምስማር ለመምታት የግብጾች ፈቃድ የግድ አስፈላጊ ከሆነበት አስገራሚ ኑሮ ለማዳን ምንም ነገር አለማድረጋቸው ምን ዓይነት አዚም ቢዞርባቸው ነው ያሰኛል።
ቤተ ክህነት ከግብጽ ሲኖዶስ ጋር እወያያለሁ ብላለች የሚባለው ዜና ለውሃ ወቀጣ ራስን ከማዘጋጀት የተለየ አይደለም።
ግብጽ ይገባኛል የምትለው ይህ ይዞታ አሁን ያለው በኢትዮጵያውያን እጅ ነው። በእጃችን ባለው ርስት ላይ ኮፕት ሆይ ርስቱ ያንቺ ነው ወይስ የእኛ ? ወይም እንድናድሰው ፍቀጂልኝ፤
ወይም ጥያቄሽን ተይልኝ ለማለት ካልሆነ ለ200 ዓመታት ከኢትዮጵያውያን እጅ ለመቀማት አንዴም ሳይሰለቹ የታገሉትን ለማስተው የሚቻለው በምን ዓይነት ጥበብ እንደሆነ ለጊዜው አልገባንም። ኮፕቶች
የሚሉት ኢትዮጵያውያንን አስጠግቼ አልወጣም በማለት ቀሙኝ ነው። አዎ ቀምተንሻል ነው? ወይስ አለመቀማታችንን
እመኝልን ነው ማለት የሚፈለገው? በእኛ እምነት ከግብጾች ጋር ስለዴር ሡልጣን ገዳም ይዞታ ቤተ ክህነትን የሚያነጋግራት ምንም ምክንያት
የላትም። ርስቱ ያለው በኢትዮጵያውያን እጅ ነው፤ የሚፈለገው የእስራኤል
መንግሥት እንዲያድሰው መጠየቅ ብቻ ነው። ኮፕቶች እስከዕለተ ምጽአት
የኛ ነው ከማለት የሚያርፉ ሰዎች አይደሉም። በአንድ ጽሁፋቸውም እንዲህ ብለዋል። In the 17th century, the
Ethiopians couldn’t pay the taxes of their properties in Jerusalem, and lost
them all to the Greek Orthodox and the Armenians. As the Ethiopians lost their
properties, they came to the Coptic Metropolitan who accommodated them in Deir
El Sultan, replacing the poor Coptic families. They then lived in Deir El
Sultan as temporary guests until 1820, when the restoration of the Monastery
required them to leave the rooms
በ17ኛው ክ/ዘ ገደማ ለመንግሥት ይከፈል የነበረውን ቀረጥ ኢትዮጵያውያኑ መክፈል ስላልቻሉ በኢየሩሳሌም ያሉ ንብረቶቻቸውን
ሁሉ በአርመኖችና በግሪኮች ተቀሙ። የግብጹ ጳጳስ ግን ኢትዮጵያውያኑን እንደ እንግዳ በመቁጠር ኮፕቶችን እያስለቀቀ ቤት ሰጥቶ እስከ 1820 ድረስ ተቀብሎ ሲያስተናግዳቸው
የቆየ ሲሆን በቤቶች እድሳት ምክንያት ኢትዮጵያውኑ እንዲለቁ ቢጠየቁ ፈቃደኞች ሳይሆኑ በመቅረት ቁልፍ ቀምተው ባለርስት እኛ ነን
በማለት ቀምተውናል» በማለት ግብጾቹ ኢትዮጵያውያኑን እንደቀማኛ ይከሳሉ። በዝርዝር ለማንበብ ይህን ሊንክ ይመልከቱ!
መንግሥትንና ቤተ ክህነትን የምንመክረው አሮጌው እንዲታደስ፤
ሰው የሚኖርበት እንዲመስል በጋራ የእስራኤልን መንግሥት ወጥረው እንዲይዙ ብቻ እንጂ ከግብጾች ጋር እንዲወያዩ አይደለም። ከዚያ ባሻገር የኢትዮጵያውያኑ የከፋ አኗኗር ከጀርባቸው ላይ ለዘለዓለሙ አይወርድም።