Wednesday, August 1, 2012

ይድረስ ለፖሊስ !! "ማኅበረ ቅዱሳን"ም ያደረገው ይህንኑ ነው!


                         ምንጭ፤ http://dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com
የእሁድ ሐምሌ 22 ቀን 2004 የፖሊስና ኅብረተሰብ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፕሮግራም በሀገራችን ስለተከሰተው የአክራሪ ሙስሊሞች እንቅስቃሴ ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ አብራርቶታል፡፡ በዘገባው ክቡር ወርቅነህ ገበየሁ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ ሼህ አህመዲን ሼህ አብዱላሂ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚደንት እንዲሁም ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በተሰጠው ማብራሪያ አክራሪዎቹ በሥራ ላይ የነበሩትን ዑለማዎች ከየመስጊዱ በመደብደብና በማባረር፣ ጥበቃዎችን ከየሥራ ክፍሎች በማሰወገድ፣ የድምፅ ማጉያዎችን ከተቆለፈባቸው ቦታ ነቃቅሎ በመውሰድ የመብራት ሲስተሙን በማጥፋት፣ ለሶላት የሄዱትን ወገኖች በማገት፣ እኛ ያልፈቀድንለት ሰው አያስተምርም፣ በማለት እጅግ አሳፋሪ እና የአሸባሪነት ድርጊት መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው የጽንፈኝነት አካሄድ መሆኑ ጭምር ተብራርቷል፡፡
በእርግጥ አንድ ሕጋዊ ተቋም ባወጣው ድንጋጌ መሠረት ሊተዳደር የግድ ነው፡፡ በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት የሚወከሉ ባለሥልጣናቱ ሥራቸውን በአግባቡ መምራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ በኃይል የሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ ፀረ ሠላም መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል።
የፖሊስ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ክፍል ከወደ ሙስሊሞቹ በኩል ያጣራው ሐቅ እንደተጠበቀ ሆኖ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በኩልም የጽንፈኝነት አካሄድ ያለው ቡድን መኖሩ ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ ይኸው ቡድን ማለትም "ማኅበረ ቅዱሳን" አባላቶቹ በቤተክርስቲያን የተወከሉ አባቶችን ሥልጣን በመጋፋት፣ የማይተባበሯቸው ካህናቶችን በመስደብ፣ በመደብደብና በማሳደድ፣ ተመሳሳይ ጥፋት ፈጽመዋል፤ እየፈጸሙም ነው፡፡
በተለይም ሀዋሳ እና አዲስ አበባ ላይ የተፈጸመው እንደማሳያ ቢሆን በቅዳሴ ሰዓት የድምፅና የመብራት ሲስተሙን ቆርጠዋል፤ የጄኔሬተር ክፍሉን ቁልፍ በመስበር በራሳቸው ቁልፍ ከርችመዋል፡፡ በጥቅምት 2004 የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ዋዜማ ላይ የአባቶችን ሥርዓተ ፀሎት ደወል በመደወልና ከፍተኛ ድምፅ በማሰማት አውከዋል፡፡ በክብረ መንግሥት ከተማ የየካቲት ኪዳነ ምሕረት ዓመታዊ በዓለ ንግሥ እንዳይካሄድና ታቦት ከመንበሩ ወጥቶ ዑደት እንዳይደረግ የሁከት እንቅስቃሴ ፈጽመዋል፡፡
"ማኅበረ ቅዱሳን" ከመስከረም 12 ቀን 2002 . ከተካሄደው ሀገር አቀፍ የሠላም ጉባዔ ወዲህ እንኳን የፈጸማቸው ድርጊቶች ለቁጥር ይታክታሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ቤተክርስቲያን ላወጣችው ሕግና መመሪያ እንደማይገዛ በይፋ አሳይቷል፡፡ ፖሊስ በያዘ እጁ ከጠቅላይ ቤተክህነት እስከ አጥቢያ ቤተረክርስቲያናት እንዲሁም ሁከት በተካሄደባቸው ከውጭ ሀገር እስከ ሀገር ውስጥ በአዲስ አበባ፣ በደሴ፣ በኮምቦልቻ፣ በአርባ ምንጭ፣ በክብረ መንግሥት፣ በሞያሌ፣ በዲላ፣ በሐረር፣ በሀዋሳ፣ በአዲግራት፣ በሎስ አንጀለስ፣ በዳላስና በሌሎችም ሀገረ ስብከቶችና ከተሞች የፈጸማቸው የሁከትና የሽብር ድርጊቶች ኅብረተሰቡን ጭምር በማነጋገር ሰፊ ጥናት ቢያካሂድ ሕዝብና ሀገርን፣ መንግሥትንና ቤተክርስቲያንን ይታደጋል የሚል እምነት አለን፡፡ "ማኅበረ ቅዱሳን" አደረጃጀቱና አባላቱ ህቡዕ የሆኑ፣ የገንዘብ ዝውውሩ ሚስጥራዊ የሆነ፣ የንብረትና የገንዘብ አስተዳደሩን ኦዲት ለማስደረግ ፈቃደኛ ያልሆነ፣ በተፈጥሮው ምንም ዓይነት መንፈሳዊነት የሌለው እና ፖለቲካዊ ቅኝት የተቃኘ ሃይማኖት ለበስ ማፊያ ቡድን ነው፡፡
ለዚህም ነው "ማኅበረ ቅዱሳን" የሰለፊያ ግልባጭ ነው የሚባለው፡፡

Sunday, July 29, 2012

እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ!


እግዚአብሔር ይወድሃል! በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ እያለህ መግቦቱን ያልከለከለህ ስለሚወድህ ብቻ ነው። ሰዎች በኃጢአት ውስጥ ስንኳ እያለን ዝም የሚለን በሕይወት እንድንኖር ጊዜ የመስጠት ፍቅሩ ነው። ማንም እንዲጠፋ አይፈልግም።  ወይኑ የሚያፈራው መራራ መሆኑን እያወቀ እንኳን ወይኑን ቶሎ አይነቅለውም። ወይኑን ይንከባከባል። ጣፋጭ ፍሬ እንዲያፈራ ይጠብቀዋል። ነገር ግን ወይኑ በተደረገለትና በተሰጠው ነገር ሁሉ ፍሬያማ መሆን ካልቻለ «ለወይኔ ያላደረግሁለት፥ ከዚህ ሌላ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድር ነው? ወይንን ያፈራል ብዬ ስትማመን ስለ ምን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ?» ብሎ የወይኑ ባለቤት መራራውን ወይን ይነቅለዋል። የመራራው ወይን መጨረሻም እጣ ፈንታ መራራ ይሆናል።
   እናም ወንድሜ ሆይ! መግቦቱን፤ ፍቅሩንና ትእግስቱን እንድናውቅለት እግዚአብሔር ይፈልጋል። በፍቅርና በምሕረት እንጂ በኃይልና በማስገደድ የሚገዛን እንዳልሆነም እንድንረዳ ይሻል። «በሰው ገመድ በፍቅርም እስራት ሳብኋቸው፤ ለእነርሱም ቀምበርን ከጫንቃቸው ላይ እንደሚያነሣ ሆንሁ፥ ድርቆሽም ጣልሁላቸው» እንዳለው  የሚስበን በፍቅሩ እስራት፤ ከሸክምም ነጻ በማውጣት፤ መግቦቱን በፍቅር እንጂ በማስገደድ አይደለም። ሆሴዕ 11፤4
ወንድሜ ሆይ፤ በሰውነታችን የወይን ተክል፤ መንፈስ ቅዱስን ብናስመርረው ከበረሃ ላይ ወድቀው እንደቀሩት ዐመጸኞች፤ የዐመጻ ዋጋችንን መቀበላችን አይቀርም።  ዐመጽን እንድንጸየፍ፤ ጽድቅን እንድንወድቅ አማራጭ የለው ምርጫችን ነው። ዐመጽን ጠላሁ፤ ጽድቅንም ወደድሁ ብሎን የለ! ዐመጽን ልንጠላ፤ ጽድቅንም ልንወድ ይገባል።
ጥያቄው መቼ? የሚል ይሆናል። መልሱንም  በቃሉ ይናገራል።  «የመዳን ቀን አሁን ነው» ያለው ሐዋርያው ለመዳን ፈልገው፤ ጩኸታቸውን ለማሰማት ለተነሱ የመራራ ነፍስ ባለቤቶች ሁሉ ነው። «በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው» 2ኛ ቆሮ 2፤6
ከዐመጻ ለመውጣት በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደው ሰዓት፤ ኃጢአትን ለመተው ውሳኔ ባሳለፍንበት ቅጽበት ነው። በዚያም በመዳን ቀን ረዳሁህ የሚል አስተማማኝ ኃይል ይሰጠናል። ሰዓቱም አሁንና አሁን ብቻ ነው።
ምናልባት ተዘጋጅተንበትና ጊዜ ሰጥተን ሁኔዎችን  ካመቻቸን በኋላ ቢሆንስ? የሚል አስተሳሰብ ሊኖር ይችላል። ይሁን እንጂ «ቀን የሚያመጣውን ምን እንደ ሆነ አታውቅምና ነገ በሚሆነው አትመካ» እንደተባለው ነገ የእኛ ቀን ስለመሆኑ ቀናቶቹን በእጃችን የያዝናቸው ስላይደለ በሌለን ነገር ላይ ተስፋ እናደርግ ዘንድ የተገባ አይደለም። የእኛ ቀንና የተሰጠን ተስፋ አሁን ያለንባት የሕይወት ጊዜ ብቻ ናት። እሷም ብትሆን «ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፋሎት ናችሁና» ያዕ 4፤14  ተብሎ ስለተጻፈ እንኳን ለነገው ቀን ከጥቂት ጊዜ በኋላ በሕይወታችን ላይ ለሚመጣው ነገር የምናውቀው ምንም የለም። እናም መራራው ወይናችን የሚነቀለው ቀን ከመድረሱ በፊት በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሳለን ለመገበን አምላክ ጣፋጭ ለመሆን አሁኑኑ እንሠራ!!  «እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ»
ከኃጢአት በመውጣት መንፈሳዊ ቤት ለመሆን የምንሠራው በቁርጠኝነት እንጂ በጠባይ፤ በቀጠሮና በመለሳለስ አይደለም። ያልጀገነ ተዋጊ ጠላቱን ሊያሸንፍ እንደማይችል ሁሉ ጠላትም ድል ለማድረግና በኃጢአት ምርኰ ይዞ ለማቆየት አይለሳለስምና ኃጢአትን በመተውና በመዳን መካከል ድርድር የለም። ጠላታችን በጀግንነት ካልተዋጋነው በስተቀር ካለማመደን ኃጢአት ውስጥ በነጻና በፍላጎት አያሰናብተንም። ጠላት ምን ጊዜም ጠላት ነው። እናም ውጊያችን መራራና ጠንካራ መሆኑን አውቀን መግጠም ይገባናል። በእኛና በጠላታችን መካከል ያለው ልዩነት ጠላታችን ውሱን ማንነት ያለው፤ ከኃይል በቀር ሥልጣኑን  የተቀማ ሲሆን በእኛ ዘንድ ያለው ሰይፍ ግን ሁሉን በእጁ የያዘ የፈጣሪ ኃይል፤ የሁሉ ገዢና አስገኚ፤ የዘላለማዊ ሥልጣን ባለቤት በመሆኑ የውጊያው አሸናፊነታችን በምክንያትና በሁኔታ ላይ ያልተወሰነ፤ እርግጠኛና አስተማማኝ ነው። ግን ይህንን ኃይል እንዴት መታጠቅ እንደምንችል፤ መቼ መታጠቅ እንዲገባንና እንዴት መጠቀም እንዳለብን ብዙዎቻችን እውቀቱ የለንም። ይህ አስተማማኝ አሸናፊነት እያለው የሰው ልጅ ሁሉ በኃጢአት የሚሸነፈው ታዲያ ለምንድነው?
እንደ ጳውሎስ ቁርጠኛና አሁኑኑ ወደውጊያው ለመግባት የሚወስን ጀግና መሆን ባለመቻሉ የሰው ልጅ ለሚሸነፍለት ኃጢአት ተሸንፎ ይኖራል። ጳውሎስ ለእግዚአብሔር ቀንቶ ክርስቲያኖችን ለማሳደድና ወኅኒ ለመወርወር እንኳን ቅንጣት አላመነታም።  ከኢየሩሳሌም ተነስቶ 217 ኪሎ ሜትር በእግሩ ወደ ደማስቆ ለመጓዝ ቅሌን ጨርቄን አላለም።  የጳውሎስ ጉዞ የክርስቶስን ቤት ለማፍረስ ቢሆንም እንደቁርጠኛ ውሳኔውን ግን ለእግዚአብሔር ከታሰረለት ፍቅር የተነሳ ነበር። ለእግዚአብሔር ፍቅር ጠላትን የሚዋጋ ጊዜ መፍጀት እንደሌለበት  ያመላከተ ሆኗል። ጳውሎስ በመንገዱ ላይ ያጋጠመው ብርቱ ኃይል ከእርሱ የሚበልጥ በመሆኑም  «አንተ ማነህ?» ማለቱም የጀግንነቱ ልክ መገለጫ ነበር። እግዚአብሔርም ራሳቸውን ለእርሱ የሰጡትን እንደዚህ ዓይነቶቹን ሰዎች ይወዳል። ጀግናን ማን ይጠላል?

Saturday, July 28, 2012

የሃይማኖታችን ሊቀ ካህናት


የጽሁፉ ባለቤት ገ/እግዚአብሔር ኪደ ይባላል። በአፍቃሬ ማኅበረ ቅዱሳን ብሎጎች ላይ ጽሁፉን በማቅረብ ይታወቃል። በፌስ ቡክ ገጹ ከሰጠን መረጃ ተነስተን ብሎጉ ላይ ካሰፈራቸው ጽሁፎች ውስጥ ይህንን ጽሁፉን መርጠነዋል። ጽሁፉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው፤ በቀደምት አበው አስተምህሮ ላይ የቆመ፤ በዘመናችን ውስጥ የሚታዩትን ብዙ የመዳኛ መንገዶች ውድቅ ያደረገ፤ የኢየሱስ ሊቀ ካህንነት በሌሎች ድካም በሚያሸንፋቸው ያልተተካ መሆኑን፤ ማዳኑ ፍጹምና ወደእሱ ለሚመጡት ሁሉ እስከ ዓለም ፍጻሜ እንደሚሰራ፤ በመሃላ የተሾመው ሊቀ ካህን «እኔ የበጎች በር (ደጅ) ነኝ» ይላልና ወደዚህ በር እንግባ እያለ ይነግረናል። ከዚህ እውነተኛው በር ውጪ ሌላ በር የለም።  ወደዚህ በር መሿለኪያ ወይም ውስጥ ለውስጥ መንገድ የለም። በመሃላ የተሾመ ሌላ ሊቀ ካህን የለም። «አንኳኩ ይከፈትላችኋል» ወዳለው የሕይወት ቃል እንድንቀርብ የሚናገረውን ይህንን ጽሁፍ መርጠነዋልና ካካፈለን ነገር እኛም አካፍለናችኋል።

    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

 በክፍል ሁለት ትምህርታችን ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ እግዚአብሔር ሥርዓት ከሰዎች ተመርጠው ከሚሾሙት የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ፍጹም የሚለይባቸውን ነጥቦች ማሳየት ጀምረን ነበር፡፡ የሚምር ነው፤ የታመነ ነው፤ በሰማያት ያለፈ ነው፤ በድካማችን የሚራራልን ነው ብለን አራት ነጥቦችን አይተናል፡፡ ለዛሬም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ካቆምንበት እንቀጥላለን፡፡ ቢችሉ አስቀድመው ይጸልዩ!

1. በመሐላ የተሾመ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ 

 መሐላ የማይለወጥ ነገርን ያመለክታል፡፡ አንድ ሰው ይህን አላደርግም እንዲህም አላደርግም ብሎ ከማለ የነገሩን ሓቅነት ያመለክታል፡፡ሰዎች ከእነርሱ በሚበልጠው (ሎሌ በጌታው፣ ገረድ በእመቤቷ፣ ደቀ መዝሙር በመምህሩ፣ ልጅ በአባቱ) ይምላሉና ለማስረዳትም የሆነው መሓላ የሙግት (የክርክር የጸብ) ሁሉ ፍጻሜ ይሆናል፤ ስለዚህም እግዚአብሔር የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደማይለወጥ አብልጦ (አብዝቶ) ሊያሳያቸው ስለ ፈቀደ እግዚአብሔር ሊዋሽ (ሊፈርስ፣ ሊታበል) በማይቻል በሁለት  በማይለወጥ ነገር በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት ይሆንልን ዘንድ በመሐላ (በሥጋዌው) በመካከል ገባ፤ ይህም ተስፋ እንደ ነፍስ መልሕቅ አለን (ተስፋችንን አጽንተን ለያዝን ለእኛ ልቡናችን እንዳይነዋወጥ እንደ ወደብ የሚያጸናን ፍጹም ደስታ አለን) እርሱም እርግጥና ጽኑ የሆነ ወደ መጋረጃውም ውስጥ የገባ (እንደ መልከ ጼዴቅ ባለ ሹመት ተሹሞ ወደ ውሳጤ መንጦላዕት የገባ የዘላለም አስታራቅያችን ፊተውራርያችን ኢየሱስ ክርስቶስ) ነውእንዲል /ዕብ.616-19/፡፡ እንግዲያውስ ከሌዋውያን ክህነት በሚበልጥ ክህነት፣ እንደ መልከ ጼዴቅ ክህነት ዘላለማዊ በሆነ ክህነት የተሾመ ሊቀ ካህናት አለን፡፡ የዘመነ ብሉይ ሊቃነ ካህናት ምንም እንኳን በእግዚአብሔር ጥሪ የተመረጡ ቢሆኑም አገልግሎታቸው ጊዜአዊ ስለ ነበረ ያለ መሓላ የተሾሙ ነበሩና፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከኦሪት ለምትበልጥ ለወንጌል መምህር ለመንግሥተ ሰማይም አስታራቂ ሆኖአልና በመሓላ የተሾመ ዘላለማዊ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ ሐዋርያውም ስለዚሁ ሲናገር እንዲህ አለ፡- “እነርሱም ያለ መሓላ ካህናት ሆነዋልና፤ እርሱ ግን፡- ጌታ፡- አንተ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት ከመሓላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሓላ ካህን እንዳልሆነ መጠን እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል” /ዕብ.720-22/፡፡ በዚህም ኦሪት ሥርየተ ኃጢአትን ማሰጠት ስላልቻለች እንደተሻረች ወንጌል ግን ማዳን ስለቻለች፣ ሥርየተ ኃጢአትን ማሰጠት ስለቻለች ሕልፈት ሽረት እንደሌለባት አወቅን፤ ተረዳን፡፡ ካህኑም አገልግሎቱም እንደዚሁ፡፡ ለምን ቢሉ ያለ መሓላ ከተሾሙት የብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት ይልቅ በመሓላ የተሾመ ሊቀ ካህናት ወልደ አብ ወልደ ማርያም ኢየሱስ ይበልጣልና፡፡