(Part two) www.chorra.net
ትምህርተ ተዋሕዶ ምን ይላል?[3]
“ክርስቶስ አሁን መካከለኛ አይደለም” የሚለው ኑፋቄ ምንጩ የአውጣኪ ትምህርት መሆኑ ይታወቃል። አውጣኪ በአንዱ በክርስቶስ የቃልና ሥጋ መደባለቅ (ቱስሕት)፣ የሰውነት ወደ አምላክነት መለወጥ (ውላጤ) ወይም መለዋወጥ (ሚጠት) ተከናውኗል ብሎ የተነሣ መናፍቅ ሲሆን፣ እርሱም ትምህርቱም ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተወግዘው ከተለዩ ብዙ ምእት ዓመታት ተቈጥረዋል። በእርሱ የኑፋቄ ትምህርት አንጻር ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ትምህርተ ተዋሕዶን አምልተውና አስፍተው አስተምረዋል።
የተዋሕዶ ትምህርት “አንቀጸ ተዋሕዶ” እንደሚባል ሊቃውንቱ ያስረዳሉ። ተዋሕዶ ሊገኝ የቻለውም አንቀጸ ተከፍሎን መነሻ በማድረግ ነው ሲሉ ያክላሉ። እንደ ሊቃውንቱ ማብራሪያ የአንቀጸ ተከፍሎ ትምህርት የሚያመለክተው ከተዋሕዶ በፊት የነበረውን የሥግው ቃልን ባሕርያውያን ምንጮችን ነው። ይኸውም ከሁለት ባሕርያተ ልደታት፣ ማለትም ቃል እም ቅድመ ዓለም ከአብ መገኘቱን፣ ትስብእትም ድኅረ ዓለም ከድንግል ማርያም አብራክ መገኘቱን (መከፈሉን) ነው። በጥቅሉ የሁለቱም ምንጭና ተረክቦ (መገኘት) የሚታሰበብትን ጊዜ ያሳያል። አንቀጸ ተከፍሎን ፊልክስ ሰማዕት እንደሚከተለው አብራርቷል፤ “ወካዕበ ይቤ ንጠይቅ ክፍላተ ፪ቱ ህላዌያት ወስመ ፪ቱሂ ክፉል በኵሉ ጊዜ በምግባር ወበነገር ዘውእቶሙ መለኮት ወትስብእት። ወሶበ ንቤ ከመዝ ኢይምሰልክሙ ዘንከፍሎ እም ድኅረ ፩ዱ ከዊን ወዳእሙ ናጤይቅ ህላዌ መለኮት ወህላዌ ትስብእት ወዓዲ ነአምር እስመ ቃል አኮ ዘተመይጠ እም ህላዌ መለኮቱ ለከዊነ ትስብእት ሶበ ኀደረ ላዕሌነ። - ዳግመኛ [ቅድመ ተዋሕዶ የነበረ] የሁለቱን ባሕርያት (የመለኮትንና የትስብእትን) ልዩነት፣ የሁለቱም ስም በጊዜው ሁሉ በሥራ በአነጋገር ልዩ እንደ ነበረ እንወቅ፤ እነዚህም መለኮትና ትስብእት ናቸው። እንደዚህም ባልን ጊዜ ከተዋሕዶ በኋላ የምንለየው አይምሰላችሁ፤ የመለኮትን ባሕርይ የትስብእትን ባሕርይ እናስረዳለን እንጂ፤ ዳግመኛም ቃል ባሕርያችንን በተዋሐደ ጊዜ ከመለኮቱ ባሕርይ ሥጋ ወደ መሆን እንዳልተለወጠ እናውቃለን።” (ሃይማኖተ አበው 1986፣ ገጽ 131)።
“በዚህ መሠረት የአንቀጸ ተዋሕዶ ትምህርት በአንቀጸ ተከፍሎ መሠረት ከጥንት ተለያይተው ከኖሩ ከሁለቱ … የአንዱን የዐማኑኤልን ህላዌ ቅውም አድርጎ የሚያሳይ የምስጢረ ተሠግዎ ወይም የምስጢረ ተዋሕዶ ትምህርት ነው።”[4] ስለዚህ በተከፍሎ የነበሩት ከተወሐዱ በኋላ አንዱን ከሌላው መለየትና እየብቻቸው ማድረግ አይቻልም። ቄርሎስ ይህን ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፤ “ኢትፍልጥ ሊተ እም ድኅረ ትድምርት እስመ ዘፈለጠ እንተ ባሕቲቶ ብእሴ ወእንተ ባሕቲቶ አምላከ ቃለ ክልኤተ ይሬስዮ ለዐማኑኤል። - ከተዋሕዶ በኋላ አትለይብኝ፤ ከተዋሕዶ በኋላ ብቻውን ሰው፥ ብቻውን አምላክ ቃል የሚል ሰው ቢኖር ዐማኑኤልን ሁለት ያደርገዋል።”[5]
የአንጾኪያው ባስልዮስም፣ “አይትከፈል ኀበ ክልኤቱ ህላዌያት እም ድኅረ ተዋሕዶ እስመ ለምንታዌ አእተታ ተዋሕዶ፤ ወተዋሕዶኒ ያግሕሥ ኵነኔሁ ለምንታዌ እስመ ውእቱ ተዋሕዶ አካላዊ ዘኢይትከፈል። - ከተዋሕዶ በኋላ ወደ ሁለት ህላዌያት አይከፈልም፤ ተዋሕዶ መንታነትን አስወግዷልና፤ የመንታነትንም ፍርድ አርቋል። እርሱ የማይከፈል አካላዊ ተዋሕዶ ሆኖአል” ብሏል (ሃይማኖተ አበው 1986፣ ገጽ 422)።
ከእነዚህ ምስክርነቶች ስለ ወልድ ከትስብእትና ከተዋሕዶ በፊት ስለ ነበረው አቋም በአንቀጸ ተከፍሎ ሊነገር እንደሚገባና ከተዋሕዶ ወዲህ ስላለው አቋሙ ደግሞ በአንቀጸ ተዋሕዶ ሊነገር እንደሚገባ እንረዳለን። ምስጢረ ተዋሕዶ የተከናወነው በተለመደውና በሚታወቀው የውሕደት ሕግ ሳይሆን በሕገ ተዐቅቦ ነው። “ተዐቅቦ ማለት በቀላል አገላለጽ መጠበቂያ ማለት ነው። ለምሳሌ መጠበቂያ ያለው ነገር ከተፈለገ፣ ለጊዜው የጠመንጃ ሁኔታ ሊታወስ ይቻላል። ጠመንጃው ጥይት ጐርሶአል እንበል። ነገር ግን በአስፈላጊው ሁኔታና ጊዜ ምላጩ ተስቦ እስኪተኰስበት ድረስ መጠበቂያ ይደረግበታል። መጠበቂያም ስላለው፣ ምላጩን ወይም ቃታውን ሲስቡ፣ ጥይቱ አይተኰስም፤ አይባርቅም። ለዚያውም (ለተኳሹም) ለሌላውም ሰው ጕዳት አያስከትልበትም። መጠበቂያው እንዳይተኰስ ጠብቆታልና። እንግዲህ የመጠበቂያው መኖር በአስፈላጊነቱ መጠን ጠቀመ ማለት ነው።”[6] በምስጢረ ተዋሕዶ ላይ ሕገ ተዐቅቦ ያስፈለገውም ቃልና ሥጋ እንዲጠባበቁ ለማድረግ ነው። “ተዐቅቦ ተራርቀው ይኖሩ የነበሩትን ባዕል፣ ምሉእና ፍጹም የሆነ አካለ ቃልን እና ድኻ፣ ውሱንና ትሑት የሆነ አዳማዊ ትስብእትን አገናዝቦ የሚገኝ” የምስጢረ ተዋሕዶ መጠበቂያ ነው።
ምስጢረ ተዋሕዶ የተመሠረተው “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ ዐደረ” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ነው (ዮሐ. 1፥14)። እንደ ሊቃውንቱ ማብራሪያ በጥቅሱ ውስጥ የምናገኛቸው “ኮነ” እና “ኀደረ” (ሆነ እና ዐደረ) የሚሉት ቃላት ተዋሕዶንና ተዐቅቦን በኅብረት ይዘዋቸዋል። አንዱ ለብቻው ተነጥሎ ማለትም “ኮነ” ለብቻው “ኀደረ”ም ለብቻው የተዋሕዶን ምስጢር ለመጠበቅ አያስችሉም። ስለዚህ ኮነ እና ኀደረ በአንድነት ምስጢረ ተዋሕዶን የሚጠብቁ ቍልፍ ቃላት ናቸው ማለት ነው። ቃላቱ ለተዐቅቦ ሕግ የተወሰኑት ሁለቱን ነጣጥለው በመጠቀም የተዋሕዶን ምስጢር ያፋለሱትን የንስጥሮስንና የአውጣኪን የተሳሳተ ትምህርት ለማረም መሆኑን ከሊቃውንቱ ማብራሪያ እንገነዘባለን።
ንስጥሮስ ምስጢረ ተዋሕዶን ለመግለጽ ኮነን ትቶ ኀደረን ነው የወሰደው። ስለዚህ “ ‘በአንዱ ክርስቶስ ሁለት ህላዌያት አሉ’ እስከ ማለት ደረሰና ውስጣዊ መለያየትን (ቡዓዴን) እና መከፋፈልን (ፍልጠትን) በምስጢረ ተዋሕዶ ላይ አመጣ። ለዚህም የኮነን እውነተኛ ትርጕም ወይም ፍቺ የያዘና ከኀደረ ጋር የሚያገናኝ መጠበቂያ እንዲኖር አስፈለገ። እነሆም ‘ዘእንበለ ቡዓዴ (ያለመለያየት)፣ ዘእንበለ ፍልጠት (ያለመፈራረቅ/ያለመከፈል)፣ በኢተላፅቆ (ያለመነባበር)’ የሚሉ መጠበቂያዎች፣ የኮነን ምስጢር ይዘው “ኀደረ” ያለውን እንዲጠብቁ ተደረገና የሥግው ቃል ተዋሕዶ ተጠነቀቀ። ለዚህ ለንስጥሮስ ንጥል ሐሳብ ተዐቅቦ ባይደረግበት ለተዋሕዶ ትምህርት አደገኛ ይሆናል። የመጻሕፍት አተረጓጐምም ይጥበረበርበታል።”[7]
ከንስጥሮስ በተቃራኒ አውጣኪም እንዲሁ ምስጢረ ተዋሕዶን የሚያጠፋ ትምህርት አስተማረ። “በአንዱ ክርስቶስ ቱስሕት (መደበላለቅ)፣ ውላጤ (የሰውነት መለወጥ)፣ ሚጠት (መለዋወጥ) እንዳለበት፣ ሰውነቱ ወደ አምላክነቱ እንደ ተለወጠ ተናገረ። አውጣኪ ኀደረን በመተው የኮነን ፍቺ በተሳሳተ አተረጓጐም ተመለከተና ኮነን ‘ተለወጠ’ በሚል ቃል ተርጕሞ ተሳሳተበት። እንደርሱ ዐሳብ ቢሆን የተዋሕዶን ምስጢር ተዋሕዶንም ደመሰሰበት። ለዚህም መጠበቂያ ልጓም አስፈለገ። እነሆም ‘ዘእንበለ ቱስሕት (ያለመደበላለቅ)፣ ዘእንበለ ውላጤ (ያለመለወጥ)፣ ዘእንበለ ሚጠት ያለመለዋወጥ/ያለመመላለስ)’ የሚሉ ቃላት የኀደረን ምስጢር ይዘው የኮነን ፍቺ ወደ ሌላ እንዳይሄድ፣ ይኸውም በመለወጥ እንዳይተረጐም ይጠብቁ ዘንድ ተደረገ። በዚህም ተዐቅቦ የሥግው ቃል ተዋሕዶ ተጠነቀቀ፤ ታወቀ። ይህ ተዐቅቦ ባይኖር የአውጣኪን ግንጥል ዐሳብ ለተከተለ ሰው የተዋሕዶ እምነቱንና በቅዱሳት መጻሕፍት ያለው የአተረጓጐሙን መንገድ ያቃውስበታል።”[8]
በአጠቃላይ ምስጢረ ተዋሕዶን “የምንጠብቀው በእነዚህ ሕጋውያን የውሳኔ ቃላት መጠበቂያዎች /ሕገ ተዐቅቦ/ ነው። ተዋሕዶ ባለበት ሁሉ ተዐቅቦም ዐብሮት ይገኛል።” ስለዚህ በተዐቅቦ በሆነው ተዋሕዶ አንዱ ክርስቶስ ያለመለያየት፣ ያለመፈራረቅ/ ያለመከፈል፣ ያለመነባበር፣ ያለመደበላለቅ፣ ያለመለወጥ፣ ያለመለዋወጥ ወይም ያለመመላለስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑ ከትምህርተ ንስጥሮስና ከትምህርተ አውጣኪ የተለየ የተዋሕዶ ትምህርት ነው።
ምስጢረ ተዐቅቦን በተመለከተ ቄርሎስ፣ “ኢይደልወነ ንፍልጦ ለ፩ዱ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ ውእቱ ብእሲ በዐቅሙ ወለእመኒ ነአምሮሙ ለ፪ቱ ህላዌያት በዘዘዚኣሆሙ ወነዐቅቦሙ ዘእንበለ ቱስሕት በበይናቲሆሙ ንብል እንከ ፩ዱ ውእቱ ክመ ኢየሱስ ክርስቶስ። - በዐቅሙ እንደ ዕሩቅ ብእሲ አድርገን አንዱን ኢየሱስ ክርስቶስ ልንለየው አይገባንም፤ ሁለቱን ባሕርያት በየገንዘባቸው ብናውቃቸውም ያለመቀላቀል በየራሳቸው ብንጠብቃቸው ኢየሱስ ክርስቶስ መቸም መች አንድ ነው እንላለን” (ሃይማኖተ አበው 1986፣ ገጽ 338)።