Tuesday, May 17, 2016

"ኢየሱስ ክርስቶስ የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ"



Part One (www.chorra.net)

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት ላይ በዚህ ዐምድ በተከታታይ የወጡትን ጽሑፎች አስመልክተው፣ የተለያዩ አንባብያን የስልክ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ለዝግጅት ክፍሉ አቅርበዋል። ከአንባብያኑ መካከል አንዳንዶቹ የክርስቶስን መካከለኛነት ላለመቀበልና ለሌሎች ቅዱሳን ለመስጠት አለን ያሉትን ማስረጃ በማቅረብ ጭምር ለመከራከር ሞክረዋል። ለክርክራቸው እንዲረዳቸውም፣ “ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም” (2ቆሮ. 5፥16) የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል የጠቀሱ ሲሆን፣ በመጨረሻም፣ “አሁን እርሱ መካከለኛ መሆኑ ቀርቷል፤ አሁን አምላክ ነው” ሲሉ ደምድመዋል። ክርስቶስን ከመካከለኛነቱ ስፍራ አንሥተውም፣ “አሁን መካከለኛው ሥጋ ወደሙ ነው” ሲሉም አክለዋል። ስለ ሥጋ ወደሙ የተባለውን ለቀጣዩ ዕትም እናቈየውና በጥቅሱ ላይ የተላለፈውንና ክርስቶስ አሁን አምላክ እንጂ ሰው አይደለም የሚለውን አውጣኪያዊ ትምህርት በመመርመር የክርስቶስን መካከለኛነት መጽሐፍ ቅዱስንና የአበውን ምስክርነት በመጥቀስ ወደ ማሳየት እንለፍ።
‘ክርስቶስ በዚህ ምድር ሳለ ብቻ ነበረ እንጂ አሁን ወደ ክብሩ ከገባ በኋላ መካከለኛ አይደለም’ የሚሉት በትምህርተ ሥጋዌ ላይ በቂ ዕውቀት የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ ተምረዋል የሚባሉትም ጭምር እንደ ሆኑ ይታወቃል። በተለይም የተማሩት ክፍሎች እንዳልተማሩቱ አፋቸውን ሞልተው አሁን አምላክ ብቻ ነው እንጂ ሰውም አይደለም አይሉም፤ ክርስቶስ ዛሬም ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑን እናምናለን ይላሉ። ክርስቶስ አሁን በአብ ቀኝ ተቀምጦ ባለበት ሁኔታ ግብረ አምላክን (የአምላክን ሥራ) እንጂ ግብረ ትስብእትን (የሰውነትን ሥራ) አይፈጽምም ስለሚሉ ግን በክብር የሆነውን ግብረ ትስብእትን ያስተባብላሉ። ለምሳሌ፣ “… ነቢረ የማን (በአብ ቀኝ መቀመጥ) ክርስቶስ ግብረ ትስብእት ከፈጸመ በኋላ እንደ ገና የሰውነትን ሥራ የማይሠራ፥ ነገር ግን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በክብር መለኮታዊ ሥራውን እየሠራ የሚኖር መሆኑን የሚያስረዳ ቃል ነው”[1] ያሉ ይገኛሉ። አባባሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በአብ ቀኝ እስኪቀመጥ ድረስ መለኮት ሥራውን ለትስብእት ትቶ ትስብእት ብቻ ይሠራ ነበር፤ ትስብእት ደግሞ አሁን በተራው የሥራ ጊዜውን ስለ ፈጸመ ሥራውን ለመለኮት ተወ ያሰኛል። እንዲህ ከሆነም ክርስቶስ በዚህ ምድር ሳለ ግብረ ትስብእትን ብቻ እንጂ ግብረ መለኮትን አይፈጽምም ነበር የሚል አንድምታ ያለው ይመስላል። ቅዱሳት መጻሕፍትና በእነርሱ ላይ የተመሠረቱ የአበው ምስክርነቶች ግን የሚነግሩን ከዚህ የተለየ እውነት ነው።

“አንሶሰወ ከመ ሰብእ እንዘ ይገብር ከመ እግዚአብሔር። ርኅበ በፈቃዱ ከመ እጓለ እመ ሕያው ወአጽገቦሙ ለርኁባን ብዙኃን አሕዛብ እም ኅዳጥ ኅብስት ከመ ከሃሊ። ጸምአ ከመ ዘይመውት ወረሰዮ ለማይ ወይነ ከመ ማሕየዌ ኵሉ። ኖመ ከመ ውሉድ ዘሥጋ ነቅሐ ወገሠጾሙ ለነፋሳት ከመ ፈጣሪ። ደክመ ወአዕረፈ ከመ ትሑት ወሖረ ዲበ ማይ ከመ ልዑል። ወኰርዕዎ ርእሶ ከመ ገብር ወአግዐዘነ እም አርዑተ ኀጢአት ከመ እግዚአ ኵሉ።”
ትርጓሜ፥ “እንደ እግዚአብሔር እየሠራ እንደ ሰው ተመላለሰ። ሰው እንደ መሆኑ በፈቃዱ ተራበ፤ ከሃሊ እንደ መሆኑ የተራቡ ብዙ አሕዛብን ከጥቂት እንጀራ አጠገባቸው። የሚሞት እንደ መሆኑ ተጠማ፤ ሁሉን የሚያድን እንደ መሆኑ ውሃውን ወይን አደረገው። እንደ ሥጋ ልጆች ተኛ፤ ፈጣሪ እንደ መሆኑ ነቅቶ ነፋሳትን ገሠጻቸው። ትሑት እንደ መሆኑ ደክሞ ዐረፈ፤ ልዑል እንደ መሆኑ በባሕር ላይ ሄደ። እንደ ተገዢ ራሱን መቱት፤ የሁሉ ጌታ እንደ መሆኑ ከኀጢአት ቀንበር ነጻ አደረገን።”[2]
በዚህ ቃለ ቅዳሴ ውስጥ አንዱ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ ይመላለስ በነበረ ጊዜ በሰውነቱ የተከናወነውንና ያከናወነውን ግብረ ትስብእትን፣ በአምላክነቱም የሠራውን ሥራ (ግብረ መለኮትን) በንጽጽር እንመለከታለን።
· መራብ የሰውነት ግብር ነው (ማቴ. 4፥2፤ 21፥18)፤ - በጥቂት እንጀራ ብዙዎችን ማጥገብና ዐሥራ ሁለት መሶብ ተረፍ ማስነሣት ደግሞ ግብረ መለኮት ነው (ዮሐ. 6፥10-13)።
· መጠማት የሰውነት ግብር ነው (ዮሐ. 4፥7፤ 19፥28)፤ - ውሃውን ወደ ወይን መለወጥ ደግሞ ግብረ መለኮት ነው (ዮሐ. 2፥7-11)።
· ማንቀላፋት የሰውነት ግብር ነው (ማቴ. 8፥24፤ ሉቃ. 8፥23)፤ - ነፋሱንና ባሕሩን መገሠጽና ጸጥ ማድረግ ደግሞ ግብረ መለኮት ነው (ማቴ. 8፥26-27፤ ሉቃ. 8፥24-25)።
· መድከምና ማረፍ ግብረ ትስብእት ነው (ዮሐ. 4፥6)፤ - በባሕር ላይ መሄድ ደግሞ ግብረ መለኮት ነው (ማቴ. 14፥25-26)።
· ተኰርዖተ ርእስ (ራስን በዘንግ መመታት) ግብረ ትስብእት ነው (ማቴ. 27፥29-30)። - ሰውን ከኀጢአት ማዳን ደግሞ ግብረ መለኮት ነው (1ጢሞ. 1፥15፤ ዕብ. 2፥14-15)።
ክርስቶስ አሁን ያለው በክብር እንጂ በዚህ ምድር በነበረበት ሁኔታ አይደለምና በዚህ ምድር በሰውነቱ የተቀበለው ግብረ ትስብእት ማለትም፦ መራብ፣ መጠማት፣ መድከም፣ ማረፍ፣ ማንቀላፋት፣ ወዘተ. አሁን የለበትም። ይሁን እንጂ ክርስቶስ በዚህ ምድር ሳለ አንድ ጊዜ በፈጸመውና ለዘላለም በሚያገለግለው የአድኅኖት ሥራው አሁን በክብር ባለበት ሁኔታ፣ በእርሱ በኩል አምነው ለሚመጡትና ከመጡም በኋላ ጠላት የሆነው ሰይጣንና ኀጢአት ለሚከሷቸው ሁሉ ዋስትናቸውና መታረቂያቸው ሆኖ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለ መሆኑን መካድ አይቻልም። የሚከተሉት መጽሐፍ ቅዱሳውያን ጥቅሶች ይህን ያስረዳሉ፤
· “እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” (ሮሜ 8፥33-34)።
· “ልጆቼ ሆይ፥ ኀጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኀጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፥ ለኀጢአታችንም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኀጢአት እንጂ” (1ዮሐ. 2፥1-2)።
በክብር የሆነውና ክርስቶስ በአብ ቀኝ ተቀምጦ ባለበት ሁኔታ የሚያከናውነው ግብረ ትስብእት ከሊቀ ካህናትነቱ ጋር የሚያያዝ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማያት ያለፈ በድካማችንም ሊራራልን የሚችል ታላቅ ሊቀ ካህናት ነው (ዕብ. 4፥14-15)። “ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኀጢአት መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ጌታ ሊቀ ካህናት የሆነው በሰውነቱ ነው (ዕብ. 5፥1)። ስለዚህም በሰማያዊቱ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ የሚከናወነው የሊቀ ካህናትነቱ ተልእኮ ግብረ ትስብእት ነው። እርሱ “በሥጋው ወራት (በዚህ ምድር ሳለ) ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፤ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ … ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው” (ዕብ. 5፥7፡9-10)። በዚህ ጥቅስ ውስጥ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር በነበረበት ጊዜ ጸሎትንና ምልጃን እንዳቀረበና እንደ ተሰማለትም ተገልጿል። ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ ደግሞ በሊቀ ካህናትነቱ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆኖ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአድኅኖት ሥራውን ፈጽሞ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጧል (ማር. 16፥19፤ ሐ.ሥ. 2፥33፤ 7፥55-56፤ ሮሜ 8፥34፤ ቈላ. 3፥1፤ ዕብ. 10፥12፤ 1ጴጥ. 3፥22)። በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠውም በዚህ ምድር ሳለ ይፈጽም የነበረውን ግብረ ትስብእትን የማይፈጽም ሆኖ፣ ነገር ግን በክብር የሆነውን ግብረ ትስብእት እየፈጸመ ነው። የዕብራውያኑ ጸሓፊ ይህን ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፤ “ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛዪቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፤ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት” (ዕብ. 8፥1-2)። ልብ እንበል! በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠው ሊቀ ካህናት፣ በዚያው ሁኔታ በሰማይ ያለችውና በእግዚአብሔር የተተከለችው የእውነተኛዪቱ ድንኳን አገልጋይ ነው። ወደዚያች የገባውም፣ ስለ እኛ ቀዳሚ ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት አሁን ይታይልን ዘንድ ነው (ዕብ. 6፥20፤ 9፥24፡28)። ይህም በክብሩ ሆኖ ግብረ ትስብእትን እንደሚፈጽም ያመለክታል።
ከዚህ ቀደም በተከታታይ ለማስገንዘብ እንደ ሞከርነው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ እንድ ጊዜ ባቀረበው ምልጃ (ዮሐ. 17፥9፡20-21) እና አንድ ጊዜ ባቀረበው መሥዋዕት (ዕብ. 10፥12፡14) ለዘላለም መካከለኛችን ነው። ይህም ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም በሰማይ ምልጃና መሥዋዕት ያቀርባል ማለት ሳይሆን፣ አንድ ጊዜ ባቀረበው ምልጃና መሥዋዕት ዛሬም አስታራቂያችንና መታረቂያችን እርሱው ብቻ ነው ማለት ነው። ዛሬ አንድ ኀጢአተኛ ሰው የወንጌልን ቃል ሰምቶ፣ በክርስቶስ አዳኝነት ቢያምንና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ቢጸልይ ከእግዚአብሔር ጋር የሚታረቀውና የኀጢአቱን ስርየት የሚቀበለው፣ ክርስቶስ አንድ ጊዜ ባቀረበው ምልጃና መሥዋዕት (በደሙ) አማካይነት ነው። በክርስቶስ ያመነውና በልዩ ልዩ ምክንያት በኀጢአት የወደቀ ክርስቲያንም ንስሓ ሲገባ ስርየተ ኀጢአትን የሚቀበለው በዚሁ መንገድ ነው። በእርሱ በኩል አምነው ለሚመጡት ለዘላለም የመዳን ምክንያት ሆነላቸው ተብሎ የተነገረውም ስለዚህ ነው (ዕብ. 5፥9-10፤ 7፥25)።
ክርስቶስን አሁን አምላክ እንጂ ሰው አይደለም፤ ወይም የአምላክነቱ ግብር እንጂ የሰውነቱ ግብር ቀርቷል ማለት ያስፈለገው ታዲያ ለምን ይሆን? ብለን መጠየቅ ይገባናል። የምናገኘው ምላሽም ከሁለቱ ውጪ እንደማይሆን እንገምታለን። የመጀመሪያው ‘ክርስቶስ አሁንም መካከለኛ ነው ካልን የሰውነቱን ግብር መግለጻችን ነውና እርሱን ዝቅ ማድረግ ይሆናል’ ከሚል ሥጋት ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ ‘ክርስቶስን አሁንም መካከለኛ ካደረግነው እኛ መካከለኛ ያደረግናቸው ቅዱሳን ምን ሊሆኑ ነው?’ የሚል ይመስላል።