Saturday, October 10, 2015

ስለአንዳንድ በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ላይ…ከአንዳንድ የኦሮሞ ጸሐፍት የተሰነዘሩ…ያስቀየሙኝ ክታቦች!!


 ከበአማን ነጸረ (ክፍል ሁለት)


5-- ክስ-አምስት፡- በኦርቶዶክስ እልህ ወለጋ ጰነጠጠ፤ወሎ-አርሲ-ጅማ-ሐረር ሰለሙ!!
መኩሪያ ቡልቻ ‹‹...In Wollo in the North, in Arsi in Bale and Hararghe in the South and Sout-East, and in Jimma in the South-West Islam was adopted to avoid the often forced mass conversion by the clergy of the Abyssinian Orthodox Church.In Wallaga, in the West many Oromos including most of the traditional elites became protestants>>ይለናል (Being and Becoming Oromo:p.55)፡፡እስኪ ይቺን የመኩሪያ ጽሑፍ ገላልጠን እንያት--አንድ በአንድ!!
(5.1) ወሎ እነ መኩሪያ ቡልቻ ‹‹አቢሲኒያ›› ብለው ከሚጠሩት ግዛት ራሱን ገንጥሎ የኖረ ሳይሆን በግዛቱ ውስጥ ተዋናይ ነበር፡፡‹‹ወሎ በእልህ እስልምናን ተቀበለ›› የሚል ታሪክ ምናልባት ከካቶሊካዊው አቶ አጽሜ አግኝተው እነ መኩሪያ ቡልቻ ‹የአዋቂ አጥፊ› እንሁን ካላሉ በቀር ታሪኩ በራሳቸው በሙስሊም አማንያንና በውጭ ሀገር ጸሐፊዎች ተተርኳል--ወደ ወሎ እስልምና የገባበት ጊዜ፡፡ለማሳያ ያሕል ታቦር ዋሚ ሙስሊም ጸሐፍትንና ፖርቱጋላዊው አልፋሬዝ በ1520ዎቹ ስለሙስሊምና ክርስቲያን ወለየዎች ተፋቅሮ የከተበውን ማስታወሻ ዋቢ አድርጎ የግራኝ አህመድ ጦር በአካባቢው ከመድረሱ በፊት ወሎዬ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እንደነበሩና ሕዝቡ [የወሎ] በሃይማኖት ሳይለያይ በሰላም አብሮ ይኖር እንደነበር አትቷል (ታቦር ዋሚ፡ገ.306)፡፡ከዚህ አንጻር ‹ወሎ በኦርቶዶክስ እልህ ሰለመ› ብሎ መጻፍ የኦርቶዶክስን ብቻ ሳይሆን የእስልምናንም ሆነ የወሎን ሕዝብ ታሪክ ያገናዘበ አይመስለም፡፡
(5.2) የአርሲን እስልምና በሚመለከት በአካባቢው ታሪክ ላይ ወረቀቶች የሠራው አባስ ሐጂ ሲገልጽ <<....among the Arsi and the Oromos of Harar where there was an old Islamic presence, Christianity failed to get foot hold>>በማለት (Abas Haji: p.107) አካባቢው የሰለመው ቀደም ብሎ ማለትም ከክርስቲያኑ ኃይል ማንሰራራት በፊት መሆኑን ያመለክታል፡፡አቶ አጽሜ ‹‹ኦሮሞ ዐማራን ስለጠላ ሰለመ›› እያሉ በካቶሊካዊ ሚሽነሪ ወገንተኛነት የጻፉትን አባስ ሐጂ ሲተችም <<This [Atsme’s] explanation is however, not adequate because Islam entered the region long before Imperial conquest...>> እያለ በአርሲ ነዋሪ ነባሪ የእስልምና እርሾ መኖሩን ይነግረናል፡፡የአባስ ትችት ለሀቅ ሳይሆን ለእስልምና ከመቆርቆር ነው ብዬ ለመጠርጠር እገደዳለሁ፤ቢሆንም ለእውነታው ከመኩሪያ እና ከአቶ አጽሜ ጽሑፍ የእሱ ይቀርባልና ተጠቀምኩት!
(5.3) የሐረር እና ጅማ ኦሮሞዎችን ቀደም ብሎ መስለምና የሸዋን ኦሮሞ ኦርቶዶክሳዊነት በሚመለከት ዶናልድ ሌቪን ሲገልጹ ‹‹ሐረር የፖለቲካ ማዕከል መሆኗ ቀርቶ የእስልምና ባህል ማስፋፊያና መስበኪያ ስለሆነች ፣ኦሮሞዎች ለሐረር ቅርብ በመሆናቸው እንዲሁም ደግሞ ምናልባት የሱማሌዎችንና የአፋሮችን ምሳሌ በመከተል ተነሳስተው አብዛኞቹ ኦሮሞዎች የእስልምና ተከታይ ሆነዋል፡፡......በላይኛው ጊቤ የሠፈሩት የኦሮሞ ጎሣዎች....በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ-ዘመን የራሳቸውን ነገሥታት አቋቁሙ፡፡የአቋቋሙት የዘውድ ሥርዓት የእስልምና ሃይማኖትን ተቀብሏል፡፡በአጭሩ በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ከምኒልክ ድሎች በፊት፡፡...በሣሕለሥላሴ ዘመን (1813-1847 ዓ.ም)...አብዛኛው የሸዋ ኦሮሞ ክርስቲያን ሆነና በዐማራና ኦሮሞ መካከል የሚፈጸመው ጋብቻ የዘወትር ክስተት ሆነ፡፡››(ሌቪን፡ገ.73-75)፡፡የኢናርያውን ንጉሥ የአባ ባጊቦን አስቀድሞ መስለም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መጽሐፍ ጸሐፊው አባ አንጦንዮስም ገልጧል (አባ አንጦንዮስ፡ገ.83)፡፡
(5.4) ዶ/ር ላጵሶ ጌ.ድሌቦ በ‹‹የኢትዮጵያ ረጅም ሕዝብና ታሪክ፣አንደኛ መጽሐፍ›› ሁኔታውን ሲገልጹ ‹‹...በ1840 እና 1870 መካከል ከሸዋና ከሰሜን ኢትዮጵያ እስላማዊ የወርጅ-ጀበርቲ ነጋዴዎች በአምስቱ የጊቤ ማለትም የጉንጋ ኦሮሞ መንግሥታት ከንግድ ጋር እስልምና አስፋፉ፡፡›› በማለት የጊቤ መንግሥታትን ወደ እስልምና መግባት ከሙስሊም ሲራራ ነጋዴዎች ስብከት ጋር አያይዘውታል፡፡ትረካቸውን ሲቀጥሉም ‹‹....በተጨማሪም በደቡብ ምስራቅ ጥንት የባሊ የአዳልና የሀዲያ እስላም አገሮች የሰፈሩ የኦሮሞ ማኅበረሰቦች ከገዳ ሥርዓት ወጥተው በአጭር ጊዜ ውስጥ እስላሞች ሆኑ፡፡›› በማለት የእስልምናን መስፋፋት እንደ መኩሪያ እና አቶ አጽሜ አበባል ‹‹ከዐማራ ቄሶች እልህ ጋር›› ሳይሆን ከንግድ መነቃቃት ጋር አያይዘው ተአማኒ በሆነ መንገድ አቅርበውታል (ዶ/ር ላጵሶ ጌ.ድሌቦ፡ገ.252)፡፡የዶ/ር ላጵሶን አተራረክ ተአማኒ የሚያደርገው በአጠቃላይ በ19ኛው ክፍለዘመን እስልምና በንግድና በግብጻውያን መሪዎች የተጠናከረ ኢስላማዊ ስብከት በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም በኤርትራ ቆላማ አካባቢ የነበሩ የትግረ፣የቢለን፣የማሪያ (የሀባብ፣የመነሳ፣የሳሆ) ጥንተ-ክርስቲያን ማኅበረሰቦች ወደ እስልምና መግባታቸው ነው (ዝኒ ከማሁ፡ገ፣258)፡፡የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ፀሐፊው ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ (M.A) ከዚህ የዶ/ር ላጵሶ ትረካ ጋር በሚመሳል መልኩ የኤርትራ ቆላማ አካባቢ ቀደምት ኦርቶዶክሳውያን ‹‹መሐመድ አሚን እልሚርጋኒ›› በተባለ ከግብጹ ገዥ ‹‹አህመድ ኢብን ኢድሪስ›› የተላከ ሙስሊም ሰባኪ ተሰብከው ስለመስለማቸው ጆን ስፔንሰርን ዋቢ አድርገው ጽፈዋል (አቡነ ጎርጎርዮስ፡ገ.69-71)፡፡ስለሆነም ይሕን በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በውጫዊ ኃይል ተልእኮና በውስጣዊ የሲራራ ነጋዴ ሙስሊም ሰባክያን የተገኘ የእስልምና መነቃቃት በኢኢተቤክ እልህ ብቻ ያውም በኦሮሚያ ብቻ እንደታየ እንግድ እንቅስቃሴ አድርጎ መተረክ አድማስን ማጥበብ ይመስለኛል፡፡
(5.5) የወለጋን በፕሮቴስታንት ተጽእኖ ስር መውደቅ በሚመለከት ድርጊቱ የተከናወነው በኦርቶዶክስ ጥላቻ ነው ብሎ መደምደም አስቸጋሪ ነው፡፡የቀ.ኃ.ሥ መንግሥት ከጣሊያን መውጣት በኋላ በነበረበት የኢኮኖሚ ድቀት የተነሳ ሚሲዮናውያን ወደ ሀገሪቱ ገብተው ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲያበረክቱ ፈቀዱ፡፡በዚህ አጋጣሚ የኦርቶዶክስና የእስልምና ተጽእኖ ወዳልበረታበት ወለጋ ሄዶ በመስበክ የአውሮፓ ሚሽነሪዎች (ኋላ ግንባር ፈጥረው መካነ ኢየሱስን የመሰረቱት) እና የአሜሪካ ሚሽነሪዎች (ኋላ ቃለሕይወትን ያቋቋሙት) እድሉን ተጠቀሙበት፡፡ሚሽኖቹ ተደብቀው ሳይሆን በሕግ ማስታወቂያ ቁጥር 3/1937(?) (decree No.3/1944) በአካባቢው በይፋ እንዲሰብኩ ንጉሡ ፈቅደው ነው የተሰማሩት፡፡ወለጋ ፕሮቴስታንት እንዳይሆን ኃይለሥላሴ አልተከላከሉም፤ይልቅስ ፈቅደዋል ቢባል ይሻላል፡፡ይሕን ደግሞ <<...CMF [Chiristean Missionary Fellowship] ....choose Ethiopia because of Haile Selassie’s friendly policy towards Missionary groups.>> በማለት (Eric Gilchist:p.63) ያብራራልናል፡፡በአጠቃላይ የወለጋ በፕሮቴስታንት ተጽእኖ ስር መውደቅ መኩሪያ ቡልቻ እንደሚለው በኦርቶዶክስ የግዳጅ ክርስትና ሽሽት ሳይሆን ለወትሮውም በአካባቢው ስር የሰደደ የእስልምና እና የክርስትና ዘውጎች ተጽእኖ ስላልነበረ፣ስለ ኦርቶዶክስ ስላልተሰበከ፣በአንጻሩ የሃይማኖት ስብከታቸውን ከማኅበራዊ አገልግሎት (ትምህርትና ጤና) ጋር አቀናጅተው የሚሰሩ ፕሮቴስታንት ሚሽነሪዎች በመንግሥት እውቅና እና ፈቃድ በአካባቢው እንዲንቀሳቀሱ ከ1930ዎቹ ጀምሮ በሕግ ስለተፈቀደ ነዋሪው በብዛት ፕሮቴስታንት ሆነ ቢባል የተሻለ ይሆናል፡፡እንደሚታወቀው ከጣሊያን መውጣት በኋላ ለሚሽኖች በወጣው ሕግ ወለጋ እና ደቡብ ኢትዮጵያ የመሳሰሉት አካባቢዎች open area ተብለው ለሚሽኖች ሲፈቀዱላቸው ማዕከላዊና ሰሜን ኢትዮጵያ ግን closed area ተብሎ ሚሽኖች ወደዚያ ሄደው ለመስበክ ፈቃድ አልነበራቸውም፡፡የሚያሳዝነው mis-ነሪዎቹ ስላላዩትና ስላልሰበኩበት የሰሜን ሕዝብ (በእነሱ አጠራር ‹‹አቢሲኒያ››) እና ስለሚከተለው እምነት በነሲብ (በጨበጣ) እየጻፉ በእንግሊዝኛ የተጻፈን ሁሉ እንደወረደ ለመቀበል የሚያሰፈስፈውን ሐገራዊ ምሑር ስተው ያሳስቱታል፡፡‹እግዜር ይይላቸው› ከማለት በቀር ምን ይባላል!!
6-- ክስ-ስድስት፡- ኦርቶዶክስ የኦሮሞ ባሕል ጸር!!
‹‹ኦሮሙማ›› የሚለውን ቃል ከእምነት (belief)፣ከዘውግ (ethinicity) እና ከማንነት (identity) ጋራ አስተሳስሮ የሚሰብከው ባህል-ተኮሩ ገመቹ መገርሳ <<An Oromo person does not become a member of a beiliving community through a formal rite of incorporation such as baptism.An Oromo is born with Orommuma>> ካለ በኋላ የተለመደውን ‹‹አቢሲኒያ››ን እና ኦርቶዶክስን ሆን ብሎ አመሳስሎ የመጥራት ዘዴ ተጠቅሞ ሲተርክ <<…Borrowing their faith from the Judo-Chiristian tradition, Abyssinians came to revere a white God and reduced the Oromo belifs in Waqqa Guraacha to a form of Devil Worship>>ይለናል (Bieng and Becoming Oromo:p.97)፡፡ንባቡ አጭር ቢሆንም ስንሰነጣጥቀው ትርጉሙ ይበዛል፡፡እናብዛው!!
(6.1) ይቺ ትረካ በራሷ ‹‹አቢሲኒያ›› በሚል በሚገለጸው አካባቢ በውስጡ ከኦርቶዶክ የተለዩ ባሕላዊ እምነቶችና እስልምና መኖራቸውን ትዘነጋለች፡፡አዎ!ይቺ ተደጋግማ የምትነገር ‹‹የአቢሲኒያ ቤ/ክ›› የምትል ቃል ተግሳጽ ያሻታል፡፡የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ራሷን ‹‹የአቢሲኒያ ቤ/ክ›› ብላ ጠርታ አታውቅም፡፡አማንያኗም እንዲያ አይሏትም፡፡እንኳንስ እሷ የሺህ ዘመናት ታሪክ የምትቆጥረው የቅርቦቹ መካነ ኢየሱስ እና ወንጌላውያንም ራሳቸውን ሲጠሩ ‹‹የኢትዮጵያ›› የሚል ቅጽል አስቀድመው ነው፡፡ስለዚህ የኢኦተቤክ ራሷን በማትጠራበት ‹‹አቢሲኒያዊት›› የሚል ስያሜ መጥራት ‹‹ነገር ፍለጋ›› እንጂ ሌላ ስም የለውም፡፡ቤተክርስቲያኒቱን ራሷን በምትጠራበት ሳይሆን ፈረንጅ አኮላትፎ እና አጣሞ በሚጠራት ስያሜ ነው የምንጠራት ማለት የቅንነት አይመስልም፡፡ያስተዛዝባል፡፡
(6.2) በዚህ በነገመቹ መገርሳ እና የሚሽነሪ ማጠቀሻዎቻቸው ለዐማራ-ትግራይ ብቻ በመጠሪያነት በተሰጠው ስመ - ‹‹አቢሲኒያ›› ከሄድን እንደ አገው፣ቅማንት፣ነገደ-ወይጦ፣ኢሮብ፣የወሎና የትግራይ (ራያ-አዘቦ-አሸንጌ) ክርስቲያን ጥንተ-ኦሮሞዎች በትረካው ምክንያት ታሪካቸው ይጨፈለቃል፡፡ከኦሮሚያ ሕዝብ 30.5% የሚሆነው ነዋሪ የሚከተለውን ሃይማኖት እንደዋዛ በባሕላዊ ማንነት ሽፋን ምሑራዊ ቅሰጣ ተጠቅሞ ጥምቀተ-ክርስትናውን ሕሳዌ (የውሸት) ማስመሰልም ደስ አይልም፡፡ምሑራዊ አምባገነንት ይመስላል፡፡ከማንነትም አንጻር ዐማራ እና ትግራይ ራሳቸውን በዜግነታቸው (በብሔር አላልኩም) የሚገልጹት ‹‹ኢትዮጵያዊ›› ብለው እንጅ ‹‹አቢሲኒያ›› ብለው አይደለም፡፡‹‹ኦሮሞ ራሱን በሚጠራበት ስም ነው ሌሎችም ሊጠሩት የሚገባ›› ተብሎ ሁላችንም ከልባችን አምነን ተቀብለን ከተስማማን በኋላ ዐማራና ትግራይ ዐረቦችና ሚሺነሪዎች ባወጡላቸው ስም ‹‹አቢሲኒያ›› ተብለው መጠራት አለባቸው ብሎ የሌላውን ማንነት በይኖ መከራከርና የሃይማኖት ተቋሙንም በዚያ መንገድ ሰይሞ ለማክፋፋት መሞከር ተገቢ አይመስለኝም፡፡ቅር ያሰኛል፡፡አንድ ሰው/ተቋም ራሱን በይፋ የሚጠራበትን የመዝገብ ስም ለውጦ በዚህ እነ እከሌ ባወጡልህ ነው የምጠራህ ማለት ለመደማመጥና ስንጠራራ ለመሰማማትም ያውካል፡፡ራሴን በማልጠራበት ቢጠሩኝ ‹‹አቤት›› አልልም፡፡በአምልኮ ደረጃም ‹‹እ/ሔር ሰውን በአምሳሉና በአርአያው ፈጠረ›› እንላለን እንጅ ‹‹ነጩን በአምሳሉ አንጽቶ፤ጥቁሩን በጥላው አጥቁሮ ፈጠረው›› አንልም፡፡‹‹ሁሉም ሰው በአምሳለ-ፈጣሪ ተፈጥሯል›› ተብሎ ነው በይሁዲውም ሆነ በክርስትናው የሚሰበከው፡፡ከዚህ ውጭ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ‹‹እ/ሔር ጥቁር ነው፤ነጭ ነው›› ብላ ለፈጣሪዋ ቅርጽና ቀለም የማውጣት ትውፊት የላትም፡፡እንዲያውም አብዛኞቹ በየአብያተ-ክርስቲያናቱ ያሉ ጥንታውያን ቅዱሳት ስእላት በቆዳቸው ነጭ ናቸው ተብለው የሚታመኑትን እመቤታችንን፣ጌታን፣ሐዋርያትንና ሰማእታትን ጠይም አድርገው በማቅረብ ትውፊታቸው የሚታወቁት፡፡የሐዲስ ኪዳን መርህኣችን ይኽ ነው፡- ‹‹አይሁዳዊ፡ወይም፡የግሪክ፡ሰው፡የለም፥ባሪያ፡ወይም፡ጨዋ፡ሰው፡የለም፥ወንድም፡ሴትም፡የለም፤ዅላችኹ፡በክርስቶስ፡ኢየሱስ፡አንድ፡ሰው፡ናችኹና››(ገላትያ ምዕራፍ 3 ቁጥር 28)፡፡
(6.3) ገመቹ መገርሳ ግን እንኳንስ ይሕን ሀቅ ወደመሬት ወርዶ ሊጽፍልን የሁሉም ክርስቲያኖች ሆነ ይሑዲዎች ወይም የሙስሊሞች የሃይማኖት መርህ ሐጋጊዎች (ደንጋጊዎች) የመካከለኛው ምስራቅ የፈካ ገጽታ ያላቸው (ነጮች?) ነቢያት/ሐዋርያት መሆናቸውን ሳያስተውል ክርስትናን እና ይሁዲን ከእስልምና ነጥሎ ስለ ‹ዋቃ ጉራቻ› ክብር ሲል ይሰዋቸዋል፡፡አናሲሞስ ወደ ኦሮሚፋ የተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ ከይሑዲ-ክርስቲያን ባሕል ውጭ ይመስል ጃሌ ገመቹ አቃቂር ይነቃቅሳል፡፡ምስጢሩ ዞሮ-ዞሮ የፈረደባትን ኦርቶዶክስ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ነጥሎ ማነወር ነው!የዋቃ ጉራቻን የጠየመ ምስል ለማጉላት ክርስቶስን (ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና) እና አምላኪዎቹን ማሳነስ ነው!!ለነገሩማ ጥቁሩ አምላክ(Waqqa Guraacha) በጥቁረቱ ከተወደሰ፣ነጩ አምላከ-ሙሴ (እ/ሔር ወይም ኢየሱስ) በንጣቱ ከተወቀሰ ዘረኝነቱ አልሸሹም ዞር አሉ ነው፡፡ማን ነው የጥቁርን ዘረኝነት ቅድስና የሰጠው?!Is it not counter-racism? Is racism of black people against white brothers justifiable?
(6.4) የኦርቶዶክሳዊነት-እና-ኦሮሞነት ውኅደት በተግባር ይታይ ከተባለ የኢኦተቤክ በኦሮሞ ባሕላዊ ጭፈራዎች ታጅባ የታቦት ንግሦችንና ጥምቀትን ማክበሯን ጃንሜዳ፣ፉሪ ሃና፣የካ ሚካኤል እንዲሁም በአጠቃላይ ኦሮሞ ኦርቶዶክሳውያን ባሉባቸው አድባራት ሄዶ መታዘብ ይቻላል፡፡በተለይ በሸዋ ኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳትን በማበረታታት፣በኦሮሚፋ መዝሙራት ባሕላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎችን ብቻ በመጠቀም፣ጨፌ በየገዳማትና አድባራቱ በመጎዝጎዝ፣ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእሬቻን ጤናማ ትርጉም በማጤንና በማጉላት ኦርቶዶክሳውያን የኦሮሞ ካሕናትም በአከባበሩ ተገኝተው በማክበር፣በኦሮሚያ በሚገኙ አብያተ-ክርስቲያናት (ደ/ሊባኖስ፣ቁልቢ፣ዝቋላ፣ወንጪ ቂርቆስ፣ደብረ-ፅጌ፣ዝዋይ ገዳማት፣ወዘተ…) መንፈሳዊ ጉዞዎችን በማካሄድ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ሲደረግ ኖሯል፤አሁንም የበለጠ ለማዳበር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡እነዚህ ድርጊቶች እንዴትም ቢተረጎሙ በኦሮሙማ ላይ አሉታዊ ጎን አላቸው ማለት አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡ኦሮሙማ እና ኦርቶዶክስ እንዳይጋጩ አድርጎ ማስቀጠል እንደሚቻል ኦርቶዶክሳውያን የቱለማ ኦሮሞዎች በበረከቱበት የሸዋ ምድር በድምቀት የሚከበሩት 2ቱ የፀደይና የበልግ እሬቻዎች ምስክሮች ናቸው፡፡
(6.5) ኦሮሙማን በማስተናገድ አቅሙ ኦርቶዶክስ በጥንታዊው የኦሮሞ እምነት ዋቄፋና እና በእምነቱ መሪ በአባ ሙዳ ዐይን ይገምገም ከተባለም ሌሎች የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎቻቸው ስለ እሬቻ፣ቃሉ፣ቃሊቻ፣ጂላ፣ጨሌ፣ቦረንትቻ፣ዋቃ ጉራቻ፣ሀማቺሳ፣ወዘተ ያላቸው አተያይ፣እንዲሁም ለኦሮሞ አለባበስ፣ባሕል፣ሙዚቃ፣ሥነ-ልቦና ያበረከቷቸው አስተዋጽኦዎች በዝርዝር ተገምግመው ደረጃ ቢሰጠን ሸጋ ነው፡፡አሁን እየተደረገ ያለው በሕግ ተፈቅዶላቸው በኦሮሚያና በደቡባዊ ሀገሪቱ ክፍል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሚሽነሪዎች ሀገሪቱን በፈለግነው መጠን ፕሮቴስታንትና ካቶሊክ እንዳናደርጋት ተከላክላናለች የሚሏትን የኢኦተቤክ እያነወሩ የጻፉትን እንደወረደ እየገለበጡ በዋቄፋና ከለላነት ተጠልሎ ምሑራዊ ጥላቻ መዝራት ነው፡፡በውጤቱም ኦርቶዶክሳውያን ኦሮሞዎችን ሆድ እያስባሱ ወደ ፕሮቴስታንቲዝም ከማስኮብለል በቀር በኦሮሚያ የዋቄፋና ተከታዮች ቁጥር 4% እንኳ ሲደርስ አላየንም!

To be continued.......