Saturday, September 21, 2013

የማይቀረው ለውጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መጎብኘቱ አይቀርም!


ባልተዘጋጀችበትና በማትፈልገው ለውጥ ሳቢያ የሚደርስባት ጉዳት ከባድ ነው።

(ክፍል አራት)

በክፍል ሦስት ጽሁፋችን በአውሮፓ ሀገራት የእምነት መላሸቅ ስላስከተለውና በለውጡ ገፊ ምክንያትነት በቁጥር አንድ ስለተመዘገበው ነጥብ  ጥቂት ለማለት ሞክረናል። በሥራ ውጥረትና በጊዜ ማጣት የተነሳ የሰው አእምሮ በመባከኑ ሳቢያ በማኅበራዊ ኑሮው ያለውን ግንኙነት አላልቷል። ቤተሰባዊ ፍቅሩን የሚያሳልፍበትን ሰዓት አጣቧል። ከፍላጎት ማደግና ከወጪ ዓይነት ንረት ጋር ለመታገል በሚያደርገው ሩጫ የተነሳ ማንነቱን ለዚህ ዓለም ኑሮ አሳልፎ በመስጠቱ ለሰማያዊ እሱነቱ የሚገባውን እሳቤ ሸርሽሮታል። በዚህም የተዳከመ የእምነት ሰው አለያም እምነት ማለት ሰርቶ ኑሮን ማሸነፍ ብቻ ነው ወደሚል እሳቤ ወስዶታል። ከመላው አውሮፓ የክርስቲያን ቁጥር ውስጥ 45% ክርስትናውን ትቶታል ወይም ክዶታል። በፈረንሳይ ብቻ 40% እምነት የለሽ ወደመሆን የወረደው በክፍል ሦስት ያየነው ለለውጡ ገፊ ምክንያት በሆነው አንዱ ነጥብ የተነሳ ነው። ያንንም ምክንያት ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ተነስተን የት ነበርን? የት ደረስን? አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ እንገኛለን? አሉታዊ ጎኑን ለማስወገድ የወስድናቸው ርምጃዎች ካሉም ያንን በማንሳት ጥቂት ለመዳሰስ ሞክረን ነበር። በዚህ ጽሁፋችን ደግሞ ሁለተኛውን ምክንያት በማንሳት ጥቂት እንላለን።

2/ ኢንዱስትሪው በየጊዜው በሚፈጥረው ትንግርታዊ እድገትና ጥበብ የሰው ልብ መማረኩ፤ ያልነበሩና የማይታወቁ ልምዶችን፤ ባህሎችንና ሥነ ምግባርን የሚያላሽቁ ክስተቶች መምጣታቸው፤

ኢንዱስትሪው ረጅም የሥራ ጊዜና ኃይል እንደመውሰዱ አእምሮን ሁሉ ለእውቀትና  ለእድገት ሽግግር ጋብዞታል። በዚህም የተነሳ ቴክኖሎጂው መጥቆ ትንግርት እስኪሆን ድረስ ፈጠራና ክሂሎት ተመንድጓል። የመረጃ መረብ መዘርጋት፤ በመረጃ መረብ ላይ የሚተላለፉ የድምጽ፤ የምስል፤ የጽሁፍና የፈጠራ ውጤቶች ሉላዊውን ዓለም እንደማቀራረቡ መጠን የሰውን ሁሉ ልብ ሰርቆታል። ይህ ሰፊና ቁጥጥር የለሽ መረጃ መረብ የሚያስተናግደው ቁም ነገር ብቻ ሳይሆን ጸያፍና ጋጠ ወጥ የሆነው ሁሉ የሚለቀቅበት በመሆኑ የሰው ልብ በሚታይ ነገር እንዲማረክ፤ የማያውቀውን ልምምድ እንዲለማመድ፤ የነበረውን ባህል እንዲያራግፍ፤ ሥነ ምግባሩ እንዲላሽቅና የሥራ ውጥረቱን በሚያባብስ የክዋኔ ሂደት ውስጥ በማስገባቱ የተነሳ መንፈሳዊውን ዓለም በገሃዳዊው ዓለም የደስታም ይሆን የኅሊና ስካር እንዲለውጥ አስገድዶታል። ለልቅ ወሲብ/Pornography/፤ ለግብረ ሰዶም፤ ለአደንቋሪ ዘፈንና ጫጫታ፤ በስፖርት ሽፋን መንፈሳዊ ልብን ለሚሰርቅ የዓይን ጫወታ ስሱዕ መሆን፤ ለዕጽ ተጠቃሚነት፤ ለአስገድዶ መድፈር፤ ለሰው ጉልበት ሽያጭ ወዘተ ድርጊቶች በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ተገዢ እንዲሆን አድርጎታል።

ቅድመ ጋብቻ የወሲብ ልምምድ መበራከት፤ ለጋብቻ የተሰራውን የእግዚአብሔር ፈቃድ የሚፈጽመው ቁጥር እንዲመናመን አድርጎታል። ላልተፈለገ እርግዝናና ለውርጃ/abortion/ የወጣቱን ስነ ልቦና ሰልቦታል። ባልተፈለገ እርግዝናና ለውርጃ፤ በግብረ ሰዶምና በልቅ ወሲብ ውስጥ ተዘፍቆ የሚገኘው አብዛኛው ሕብረተሰብ ክርስቲያን የነበረ ወይም በክርስትና ስም የሚጠራው ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ በአውሮፓ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ። ከሀገር ሀገር የሚደረግ የወሲብ ንግድ መበራከት፤ የአደንዛዥ ዕጽ መስፋፋት፤የወንጀሎች ቁጥር ማደግ ፤ ተዛማጅ በሽታዎች /HIV/ የመሳሰሉት ሥርጭት አሳሳቢ መሆን ኢንዱስትሪውና ተከትለውት የመጡ መዘዞች ማሻቀብ ያስከተሉት አሉታዊ ጎኖች መሆናቸው አይካድም።  ይኸው ችግር በኢትዮጵያችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንወስደው ከዓመት ዓመት አስከፊ ገጽታው እየጨመረ መጥቶ የግብረሰዶማውያኑ የመብታችን ይከበር ድምጽ መሰማት መጀመሩ የሥነ ምግባር ልሽቀት ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የሚያመላክት ጉዳይ ነው። በእርግጥ አስደሳቹ ዜና «ፔው ዐለም አቀፍ የአስተሳሰብ ጥናት ማዕከል» በ2007 ዓ/ም ባደረገው ጥናት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ 97% ግብረ ሰዶም በምንም ዓይነት መልኩ በኢትዮጵያ ውስጥ እውቅና እንዳይኖረው እንደሚፈልግ መረጃው ቢያሳይም አሳፋሪው ድርጊት ግን ከዓመት ዓመት እየጨመረ መሄዱ አልቀረም። ይህ የማኅበራዊ ቀውስ አንዱ ክፍል መንስዔው በሥነ አእምሮ መላሸቅ የሚመጣና በአስነዋሪው ድርጊት በመለከፍ የሚስፋፋ እንደመሆኑ መጠን ኢንዱስትሪው የሚያስከትላቸውን ተመሳሳይ ጉዳቶች ለመከላከል ቤተ ክርስቲያን ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባት ያመላከተ ጉዳይ ነው። ማውገዝና በእምቢታ መጮህ ብቻውን የድርጊቱን መስፋፋት ስለማይከላከል ተግባሩን ከመኮነን ባለፈ በወጣቱ ሥነ ልቦናና መንፈሳዊ አእምሮ ላይ ብዙ መሥራት የግድ ከሚላት ደረጃ ላይ ደርሳለች። ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያኗ ለዚህ ዓይነቱ ተግዳሮት ከምኞት ባለፈ የስራ እንቅስቃሴ ለማሳየት እንኳን ተግባሩ ሃሳቡም ያላት አትመስልም። በዓመት ሁለት ጊዜ በአዋጅ ተሰብስባ የምታስተላልፈው መልእክት የእንቶኔ ሀገረ ስብከት ይህንን ያህል ፐርሰንት አስገባ፤ እንቶኔ አንደኛ ወጣ ከማለት በዘለለ ወጣት ተከታዮቿን እየመታው ካለው የዘመን ልክፍት ለመታደግ መደረግ ስለሚገባው የጥበቃና የክትትል ሥራ ትልምም፤ ዕቅድም፤ መርሃ ግብርም የላትም። ይሁን እንጂ ያልተፈለገው ለውጥ ቤተ ክርስቲያኒቱን ቀስ በቀስ እየመታትና እንኳን ተከታዮቿ መሪዎቿም ሳይቀሩ በዚህ ክስተት ተጠቂ ከመሆን አያመልጡም። የአውሮፓ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች በሥነ ምግባር ልሽቀት መመታታቸውን ስናይ ይህ ችግር ተሻግሮ እንዳይመጣ አሁን ካልተሰራ እውን መሆኑ አይቀሬ ነው። በየአብያተ ክርስቲያናቱ በየቦታው የሚታዩ የሥነ ምግባር ጉድለቶችም የመጻዒውን የምች በሽታ ስፋት አመላካች ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

አውሮፓውያኑን ከኢንዱስትሪው እድገትና ከአእምሮ መባከኑ ጋር ተጎዳኝቶ ስላበላሸው የማኅበራዊው ቀውስ ጉዳይ የኢትዮጵያ  ቤተ ክርስቲያን ቆም ብላ ተከታዮቿን በማስተማር፤ በእምነት ጸንተው እንዲገኙ በማድረግና ከዚያም ባለፈ የሥነ አእምሮ ህክምናና የምክር አገልግሎት በመስጠት ተጠቂዎችን ከማዳን አንጻር የሰራችው ምንም ነገር የለም። የት እንደሚውሉ የማታውቃቸውን ልጆቿን በጥቅል ቁጥር ሃምሳና ስልሳ ሚሊዮን ገደማ አሉኝ ከምትላቸው በስተቀር ለማይረባ አእምሮ ተላልፎ እንዳይሰጥ በመከላከልና የጠፋውን በግ ፈልጎ በማዳን ረገድ መሥራቱ ብዙ ይቀራል። በዚህ ረገድ በየአብያተ ክርስቲያናቱ መድረክ ላይ ከሚጮሁ ቅጥረኞች ባሻገር በሚዲያ ልጆቿን ተደራሽ የምታደርግበት ህልም ስለሌላት ከእናት ከአባቱ ክርስቲያን የሚለውን ስም ተረክቦ ከመኖር ባለፈ ክርስትናን የሕይወቱ ዋና ክፍል አድርጎ የሚመለከት ትውልድ እያጣች ትገኛለች። አንድ ለእናቱ በሆነው «ዜና ቤተ ክርስቲያን» ጋዜጣ ስለአቡነ እገሌ ታታሪነት ከመናገር በዘለለ የለውጥ አምጪ ክስተቶች መነሻና ውጤቱን በመገምገም መንፈሳዊ ትጥቅን በማስጨበጥ ረገድ የተላለፈ መልእክት ምን ያህል ይሆን? ስንቱንስ አዳርሷል? አጠያያቂ ነው። በመንፈሳዊ የሬዲዮ ሞገዶች፤ በምስል ወድምጽ ማስተላለፊያዎች /በቴሌቪዥን፤ በበይነ መረብ ወዘተ መንገዶች ምን ያህል ተሰርቷል? ምንም!!! ቤተ ክርስቲያኒቱ ከዘመኑ ጋር እንዴት እየሄደች ይሆን?

ዛሬ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የህጻናት ወይም የአሮጊቶች መድረሻ ሥፍራ ወደመሆን ተቀይሯል። ወጣቱ ትውልድ በየበዓላት ቀን እየተገኘ ወዝ ባለው በያሬዳዊ ዝማሬ ከበሮ በመምታት ድምቀት መስጠቱ ባይከፋም ክርስትና በሚያሳዩት ድምቀት የሚለካ ትርዒት ባለመሆኑ መንፈሳዊ ማንነቱን ገላጭና በሥነ ምግባር የታነጸ ምስጉን ትውልድ ሆኖ በቤተሰቡ፤ በማኅበረሰቡና በአካባቢው መልካም እኔነት እንዲኖረው በማስቻል ረገድ አልተሰራም ማለት ይቻላል። በየሰንበት ትምህርት ሽፋን ስንቱ የሥነ ምግባር ጉድለት እየተፈጸመ እንደሚገኝ በቅርብ ይታወቃልና ነው። በአእምሮ ላይ ተጽዕኖ ማሳረፍ የሚችል መንፈሳዊ ሥራ መስራት አለመቻል ሰው ስለድኅነት/ መዳን/ ያለውን እውቀት ከማነብነብ ባለፈ የእምነቱ ህልውና ዋና ክፍል አድርጎ ከመመልከትና በተግባር ከማዋል የራቀ ይሆናል።  ጴንጤ ተብለው በተሳልቆ የሚነሱት ክፍሎች ለስድብና ለሽሙጥ ምላሽ ሳይሰጡ አቀርቅረው እንደሚሄዱ ሲነገር ኦርቶዶክሳዊ የሆነ ግን ለቡጢ ቡጢ፤ ለስድብም ቡጢ እንደሚመልስ ገላጭ ሆኖ መታየቱ በመንፈሳዊ የአእምሮ ለውጥ ላይ ብዙ አለመሰራቱን አመላካች ነው። በመድረክ ላይ ከሚነገረው የወንጌል እውነት ውስጥ ቀኙን ሲመቱት ግራውን የሚሰጥ ከተገኘ በእውነት እድል ነው።

በአጠቃላይ ሉላዊው ዓለም በሚያደርሰው የእድገት ውርርስና የለውጥ አስገዳጅ ሁኔታ የተነሳ ሀገራችን ኢትዮጵያም በዚያው የአዲስ ክስተት አዙሪት ውስጥ መግባትዋ ባለመቅረቱ ከዚህ አዙሪት ለመውጣትም ይሁን ላለመግባት አሉታዊ ጎኑን ገምግሞ ቅድመ ዝግጅት አለማድረግ ውጤቱ አደገኛ ይሆናል። ቤተ ክርስቲያን ተከታዮቿን በፈሪሃ እግዚአብሔርና በሥነ ምግባር የታነጸ ሆኖ ራሱንና ትውልዱን የሚቀርጽ ተረካቢ እንዲኖር ለማድረግ በርትታ ካልሰራች አስቸጋሪ ሁኔታ ሊያጋጥማት ይችላል። መሪውም ተመሪውም መንፈሳዊ ካባውን ካወለቀ የአውሮፓ ዝቅጠት የሀገራችንም ዝቅጠት የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም። ከማይቀረው ለውጥ ውስጥ አሉታዊውን ለማስቀረት መሥራት የሚገባን ዛሬ ነው። ቤተ ክርስቲያን ባልተዘጋጀችበትና በማትፈልገው ለውጥ ሳቢያ የሚደርስባት ጉዳት ከባድ ይሆናል። እግዚአብሔር ያውቅልናል ብሎ መቀመጥ አውቀን እንድንሰራ ለተሰጠን ኃላፊነት መከላከያ ምክንያት ሊሆን አይችልም።  ኖኅን ያዳነው መሥራት የሚጠበቅበትን  መርከብ በመሥራቱ እንጂ እግዚአብሔር ኖኅን ያለመርከብ ማዳን ስለማይችል አይደለም።

//ይቀጥላል