ለአቡነ ገብርኤል ጥሪ የሀዋሳ ምእመናንና የሰ/ት/ቤት ወጣቶች ምላሽ ሰጡ!

«እስከ ጥቁር ዉሃ ሄዶ የተቀበለ  ሕዝብ እስከ ጥቁር ውሃ ተሰደደ» (ደጀ ብርሃን)

 /ምንጭ፦dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com/
 በሀዋሳ በግፍ የተሰደዱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ብፁዕ አቡነ ገብርኤል "ኑ ልጆቼ ወደ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ተመለሱ" ሲሉ ላደረጉት ጥሪ ምላሽ መስጠታቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ምዕመናኑ ለአቡነ ገብርኤል በአድራሻ፣ ለ17 የቤተክርስቲያንና መንግሥታዊ ተቋማት ደግሞ በግልባጭ ያሠራጩትን ደብዳቤ በብሎጋችን ፖስት እንድናደርግላቸው ለዝግጅት ክፍላችን በኢሜይል ልከውልናል፡፡ የደብዳቤው ሙሉ ይዘት የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ነሐሴ 7 ቀን 2005 ዓ.ም
ለብፁዕ አቡነ ገብርኤል
የሲዳማ፣ ጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ
ሀዋሳ፣
ጉዳዩ: ̶  "ወደ ቤተክርስቲያን እንድትመለሱ" በማለት ለተጻፈልን ደብዳቤ ምላሽ ስለመስጠት
በቀን 25/1/171/2005 (ቀኑን ከደብዳቤው ላይ ማየት እንደሚቻለው) በቁጥር 1459/171/2005 የተጻፈ ደብዳቤ ሐምሌ 25 ቀን 2005 ዓ.ም ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት በሁለት ፖሊሶች እጅ ተልኮልን ወንጌል ከምንማርበት ሥፍራ ተጠርተን መተማመኛ ፈርመን በመቀበል በአንክሮ ተመልክተነዋል፡፡ ቀጥሎም ለምዕመናን ተነቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ የጋራ አቋም የተወሰደበት ሲሆን፣ ጥሪ ማድረግዎን በስምንቱም አጥቢያ ቤተክርስቲያናት ዐውደ ምሕረቶች እንዲነበብ እንዳደረጉት ሁሉ ይህንን የምላሽ ደብዳቤያችንንም  ለሰፊው ምዕመን በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲያስነብቡልን አደራ እንላለን፡፡ የሰጠነውም ምላሽ የሚከተለው ነው፡፡ 
አንደኛ፣ ደብዳቤውን እንደ ወንጀል ክስ መጥሪያ በፖሊስ እጅ መላኩ እና ከመደበኛ የሥራ ሰዓት ውጪ ከምሽቱ 1፡30 ከሆነ በኋላ መምጣቱ፣ እንዲሁም መተማመኛ ፈርመን እንድንቀበል መደረጉ ከሕግ አንፃር ተገቢ ካለመሆኑም በላይ የጥሪው አካሄድ የፍቅር እንዳልሆነ ተገንዝበናል፡፡ በተጨማሪም ደብዳቤው ቅንነትና እውነት ያለበት ሳይሆን ማስመሰልና ውሸት የተሞላበት ከመሆኑም በላይ እርቅ፣ ሠላምና አንድነትን ከማምጣት ይልቅ ራስን ከሕዝብ (ከታሪክ) ፍርድ ለመከላከልና ለገጽታ ግንባታ (ፕሮፖጋንዳ ፍጆታ) ሲባል ብቻ የተዘጋጀ መሆኑን ተረድተናል፡፡
በደብዳቤው ውስጥ "የተወደዳችሁ ልጆቻችን ምዕመናንና ወጣቶች" የሚል ሐረግ ተደጋግሞ ይታያል፡፡ ልጆቻችሁ እንደሆንን ሲነግሩን ከእርስዎ ሳይሆን ከሌላ አካል የሰማነው ያህል መስሎ ነው የተሰማን፡፡ ምክንያቱም እኛ ልጆችዎ እንደሆንን ባንክድም ከእርስዎ ዘንድ ግን የአባትነት ወግ ፈጽሞ አይተን ስለማናውቅ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የደብዳቤውን ይዘት ስንመረምረው የተረዳነው ነገር ቢኖር ̶ አንዳንዴ በግልጽ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በስውር በሀገረ ስብከታችን የሚካሄዱትን ሕገወጥ ሥራዎች ለመሸፋፈንና "ለምን አሳደዳችኋቸው? ለምን አትመልሷቸውም"? ብሎ ለሚጠይቃችሁ አካል "ይኸው፣ በደብዳቤ ጠርተናቸውም እምቢ ብለውናል" በማለት በብልጣብልጥ አካሄድ ሪከርድ ለማስያዝ እና ወደፊት ለምታደርጉት የተለመደ እንቅስቃሴ ምክንያት ለማመቻቸት መሆኑን ለማወቅ ልዩ ጥበብ አያስፈልገውም፡፡
ጥሪዎ ቅንነት ቢኖረው ኖሮና እኛን "ልጆቻችን" እንዳሉን ሁሉ እርስዎም አባትነትዎን አምነውበት ቢሆን በአባትና በልጅ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ልጅ ቤቱን ለቆ ቢኮበልልና አባትም በበኩሉ የኮበለለው ልጅ ወደ ቤቱ እንዲመለስ ቢፈልግ ደብዳቤ ጽፎ በፖሊስ በኩል መላክ ትክክለኛው መንገድ አለመሆኑን ለእርስዎ መንገር ለእናት ምጥ እንደማስተማር ይቆጠራል፡፡
በተጨማሪም፣ ከቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ተባርረን ከወጣን ሁለት ዓመታት እስኪቆጠሩ ድረስ ከሀገረ ስብከቱ ውጪ ያሉ ካህናትና አገልጋዮች መጥተው ሲባርኩንና ሲያፅናኑን እርስዎና ከእርስዎ ሥር ያሉ አባቶች ግን የጠፉትን በጎች ፍለጋ ሳትወጡ ኖራችሁ፣ ዛሬ ከረፈደና ከመሸ፣ ጉዳዩም ከእጃችሁ ወጥቶ በጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤትና በቅዱስ ሲኖዶስ ከተያዘ በኋላ ድንገት ይህንን ኦፊሴላዊ ጥሪ ለማድረግ የተገደዳችሁበትን ሚስጥር ስናሸተው ጠረኑ የሚነግረን ሌላ ጉዳይ መሆኑን ነው፡፡ ደብዳቤው ሆን ተብሎ እውነታውን ለማዛባት የተደረጉ ጥረቶች እንዳሉበት ከማሳየቱም በላይ "እንዳያማህ ጥራው፤ እንዳይበላ ግፋው" እንደሚባለው ለይተበሀል ያህል ብቻ የተጻፈ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ሁለተኛ፣ በደብዳቤው የመጀመሪያ መሥመር ላይ፣ "ከቤተክርስቲያን ተባረናል በሚል . . .  እየተሰባሰባችሁ የምትገኙ ልጆቻችን ምዕመናንና ወጣቶች . . . " የሚል ሐረግ ሰፍሯል፡፡ ይህ የሚያሳየን እኛ ተባረናል እንላለን እንጂ እናንተ ማባረራችሁን አምናችሁ ለመቀበል እንደማትፈልጉና ዛሬም እንኳን ፀፀት እንዳልተሰማችሁ ያመለክታል፡፡  ታዲያ ከእናት ቤተክርስቲያናችን ውጪ ለመገኘታችን ምክንያቱ እርስዎ፣ የእርስዎ አስተዳደር እና እርስዎ ያደራጁት ማኅበር ካልሆነ፣ ቤተክርስቲያንና ቅጥሯ አስጠልቶን አካባቢ ለመለወጥና ለሽርሽር የሄድን መስሎዎት ይሆንን? ይሁን እንጂ እንዳባረራችሁን መላው የሀዋሳ ምዕመናን ምሥክር ናቸው፡፡


በተጨማሪም የሰንበት ት/ቤቱን ቢሮ እና የመሰብሰቢያ አዳራሽ በኃይል በፖሊስ መጥተው ያሳሸጉት ራስዎ መሆንዎን ኅሊናዎ ያውቀዋል፡፡ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችም በዚህ በእርስዎ ድርጊት (ማኅበረ ቅዱሳንን ለመተካትና ለማስደሰት) ነው ከቤተክርስቲያናቸው ተጠርገው የወጡት፡፡ በዚህም ምክንያት አቤቱታ አቅርበው፣ ከጠቅላይ ቤትክህነት ጽ/ቤት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ቢሮና የመሰብሰቢያ አዳራሻቸው እንዳይታሸጉ ደብዳቤ ቢደርስዎትም እምቢ አሻፈረኝ ያሉትም እርስዎ ነዎት፡፡ ከዚህም በላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሰኔ 21 ቀን 2003 ዓ.ም ልዩ ባጅ በተለጠፈባቸው የማኅበረ ቅዱሳን አባላት አማካይነት በቅዱስ ገብርኤል ገዳም ውስጥ ጭፍጨፋ ከተካሄደብን በኋላ ከቅጥር ግቢው መባረራችን በይፋ የሚታወቅ ስለሆነ ሀገር የሚያውቀውን ሐቅ ለመሸፈን መሞከር ትዝብት ከማትረፍ በስተቀር እውነትን ቀብሮ ማስቀረት ስለማይቻል በከንቱ ባይለፉ ጥሩ ነው፡፡ ችግሩ በዚህ ብቻ ሳያበቃ "የእኛ ተባባሪ ለምን አልሆኑም" በሚል ስሜት መልአከ ኃይል ቆሞስ አባ ኃ/ጊዮርጊስ የሀዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ፣ መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ናትናኤል የደብረ ሠላም ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ እንዲሁም አባ ዘነአኩቶ ለአብ የደብረ መንክራት አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ያለ ጥፋታቸው በተደራጀ ቡድንዎ አባላት ጫጫታ ከሥራቸው ያባረሯቸው ሲሆን ከእናንተ ጋር ያልወገኑ ሌሎች አገልጋዮችንም በማዛወር፣ ከደረጃ ዝቅ በማድረግ እና በማባረርም ጭምር አስከፊ የበቀል እርምጃ መውሰድዎ አይዘነጋም፡፡
ሦስተኛ፣ በደብዳቤው የመጀመሪያ አንቀጽ መጨረሻ መሥመር ላይ፣ "በየአጥቢያ ቤተክርስቲያኑ እየገባችሁ ቤተክርስቲያኗ በምትሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት ተጠቃሚ እንድትሆኑ በተደጋጋሚ በየቤተክርስቲያኑ ዐውደምሕረትና በየበዓላቱ ሁሉ መልዕክት ስናስተላልፍ መቆየታችንን ታውቃላችሁ " የሚል ዐረፍተ ነገር አስቀምጠዋል፡፡ እውነታው የሚያሳየው ግን፣ ዐውደ ምሕረቱን የመርገሚያ፣ የመሳደቢያ፣ የመለያያ እና የመከፋፈያ ዘር መዝሪያ መድረክ እንዳደረጋችሁት እኛም ሕዝብም የሚያውቀው ሐቅ ነው፡፡ ለምሣሌ ያህል መጥቀስ ካስፈለገም፣ በ2005 የጥምቀት በዓል ላይ ለምዕመናን መልዕክት ሲያስተላልፉ "እነዚያ ክፉ መንፈስ የተጠናወታቸው ሰዎች ከመካከላችን ስለተለዩ እና ሠላማችንን ስላገኘን በዓላችንን በሠላም ማክበር በመቻላችን ዕልል በሉ" እያሉ ሲያስጨበጭቡ እንደነበር በይፋ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህንን ንግግርዎን አይረሱትም፤ ካስፈለገም በቴፕ የተቀረፀ ስለሆነ ማስረጃውን ልናቀርብልዎ እንችላለን፡፡ ከዚህ በተረፈም፣
̶    ድንጋይ ወርዋሪ ወሮበሎች፣
̶   የጋለሞታ ሴቶች ስብስብ ናቸው፤
̶   ከአምስት የማይበልጡ ድንጋይ ወርዋሪዎች፣
̶ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ሌቦች ናቸው፤ የቤተክርስቲያንን ንዋየ ቅድሳት ዘርፈውናል፤
̶   የእኔ የሆኑት በገዳሙ ቅጥር ግቢ ውስጥ ናቸው፤ እነዚያ የእኔ አይደሉም፡፡
̶  እነዚያ በየቅርጮ (ቀርከሃ) ቤቱ፣ የሚያመልኩ መናፍቃን ናቸው፣ እነርሱ ዘንድ አትሂዱ፤ ልጆቻችሁንም እንዳይሄዱ ከልክሉ፤
በማለት በእኛ ላይ ጥርጥር የመፍጠር እና ከኅብረተሰብ የመነጠል ተደጋጋሚ ንግግር በማድረግ የምናውቅዎ ሲሆን፣ እኛን በመኮነን በየዐውደ ምሕረቱና በየበዓላቱ ያላንቋሸሹበት፣ ያልተሳደቡበት ጊዜ አልነበረም፡፡ እርስዎ እንደዚያ ሲሰድቡንና ሲያንቋሽሹን ከፊት ለፊት ቆሞ ከሚያዳምጥዎት ሕዝብ መካከል አብዛኛዎቹ እኛና የእኛ ቤተሰቦች መሆናችንን አለማስታዋልዎ የሚገርም ነው፡፡
ከዚህም በላይ ሐምሌ 2003 ዓ.ም ለታተመው ዕንቁ መጽሔት ቁጥር 47 በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣  " . . . ከቡድንተኞቹ ክፍል አንደኛው ክፍል ዝም ያለ ሲሆን፣ ሌላኛው ክፍል ተሳዳቢ፣ ተወራዋሪ፣ የሚነቅፍና የሚሳደብ ነበር፡፡ ከፊታችን ድምፅ ማጉያ የሚነጥቁም ነበሩ፡፡ በሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ያየሁትን ሁሉ ብዘረዝረው ''እግዚኦ'' የሚያሰኝ ነው. . . እነርሱ የማይደግፉት ሰው ሲያስተምር እንደ ቀበሮ ተሰብስበው "ውው" ብለው ይጮኻሉ" ብለው ከመሠከሩት በላይ ስለእኛ ያለዎትን ጥላቻ በምን መልኩ ልንገልጽልዎ እንችላለን? ነገር ግን፣ ሥርዓተ ቁርባንን ደወል እየደወለ እንዲታወክና እንዲቋረጥ ያደረገ፣ የድምፅ ማስተላለፊያ መሥመሮችን እየቆረጠ፣ የጄኔሬተር ክፍል ቁልፍ እየሰበረ የአባቶች መልዕክትና ትምህርት ለምዕመናን እንዳይተላለፍ ያሰናከለ፣ እናቶችንና ሕፃናትን በዱላ እየቀረደደ ደም ያፈሰሰው ከእርስዎ ጋር ያለው ወገን እንደሆነ ድፍን የሀዋሳ ሕዝብ ይመሠክራል፡፡ በሌላ በኩል ምዕመናንንና አገልጋዮችን ከፋፋይና በታኝ የሆነውንና ቤተክርስቲያንን የሚያዳክም ቡድንዎን ከማሞካሸት ሌላ ሐቅን ተንፍሰው አያውቁም፡፡
አምስተኛ፣ በደብዳቤው ሁለተኛ አንቀጽ 5ኛ መስመር ላይ ". . . እያስቀደሳችሁና ትምሕርት እየተማራችሁ በቤተክርስቲያን ሕግና ሥርዓት እንድትመሩ በፊትም ሆነ አሁን ያልተከለከለ መሆኑን እንድታውቁት . . .  " የሚል ሐረግ ሰፍሯል፡፡ እርግጥ ነው ቤተክርስቲያናችን የሕግና የሥርዓት ምንጭና ባለቤት እንደሆነችና ለዘመናት በዚህ ስትተዳደርና ስትመራ እንደኖረች እናውቃለን፤ እናምናለን፡፡ ዛሬ ግን  ይህ ሕግና ሥርዓት ቀርቶ፣ ጥቂት ነጣቂ ግለሰቦችና ቡድኖች ተደራጅተው የቤተክርስቲያንን ሕግና ሥርዓት በመተው የራሳቸውን ዓለማዊ ፍላጎት በሚያሟላ ሕገ ልቦና በመተካት ቤተክርስቲያናችንን እያሽከረከሯት ይገኛሉ፡፡ እኛንም እስከመሰደድ ያደረሰንና ዋጋ ያስከፈለን ቤተክርስቲያናችን በራሷ ሕግና ሥርዓት መመራት አለባት ብለን በመጠየቃችን ነው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፣ ዛሬ ቤተክርስቲያናችን በራሷ ሕግና ሥርዓት ነው እየተመራች ያለችው?  እርስዎስ ቤተክርስቲያንን በሕጓና በሥርዓቷ ነው እየመሯት ያሉት? እርስዎ ተግባራዊ ያላደረጉትንና ያላሳዩንን ሕግና ሥርዓት እኛ ከየት አምጥተን እንመራበት? ሕግና ሥርዓት ጠፍቶ ቤተክርስቲያን የገነባውንና ከመቀነቱና ከኪሱ በሚያወጣው ገንዘብ የሚያስተዳድረው ሕዝብ መብት ተዘንግቶና ተረግጦ፣  በተቃራኒው ቤተክርስቲያንን እንደግል የንግድ ድርጅት መቆጠሩ ነው የችግሩ መሠረታዊ ምንጭ፡፡ ይህ ዘመን እንደ ፊውዳል ዘመን፣ ሕዝብ በገዛ ቤተክርስቲያኑ መብቱንና ክብሩን አስረግጦ፣ ያሉትንና ሁን የተባለውን ብቻ እየተቀበለና እያደረገ ለመኖር የማይችልበት ዘመን መሆኑን አለመገንዘብ ሌላው የአንዳንድ የቤተክርስቲያን አባቶች ችግር ነው፡፡
በሀዋሳና በዙሪያዋ የሚገኙ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት ቅድመ አያቶቻችን፣ አባቶቻችንና ቀጥሎም እኛ በዕውቀታችን፣ በጉልበታችንና በገንዘባችን ያነጽናቸው ናቸው፡፡ ከእርስዎ ጀምሮ እስከ ጥበቃ ሠራተኛ ድረስ ደመወዝ ከፍለን የምናሠራችሁ እኛ ነን፡፡ አብዛኛዎቻችሁ እነዚህ ሕንፃ ቤተክርስቲያናት ሲሠሩ በስፍራው አልነበራችሁም፡፡ አንዲት ጠጠር እንኳን አልጣላችሁም፡፡ ነገር ግን ምዕመናን ይህንን አሟልተን ኑና አገልግሉ ብለን ከመጣችሁ በኋላ እኛ ባለቤት እንዳልሆንን ሁሉ ባለቤቶቹና ባለመብተቶቹ እናንተ ብቻ የሆናችሁ ይመስል አባረራችሁን፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ተቀጣሪ ቀጣሪን አያባርርም፡፡ ቀጣሪ ግን ጥፋትና ድክመትን አይቶ ተቀጣሪን መሸኘት መብቱ ነው፡፡  ይህ ሐቅ እውን ሆኖ ሳለ የሀዋሳን ምዕመናን ወንድማማቾችንና እህትማማቾችን እርስ በእርስ ከፋፍሎ ሠላም እንዳይመጣ በማድረግ አንዱን የቤተክርስቲያን ልጅ ሌላውን በጥባጭ እና አጥፊ አድርጎ በመቁጠር ቤተሰብን ከቤተሰብ፣ ባል ከሚስት፣ ወላጅን ከልጅ በመለያየት በሕዝባችን መካከል የነበረውን አንድነትና ፍቅር ያበላሸብንና ያጠፋብን የእርስዎ አመራርና አስተዳደር ነው፡፡
". . . እያስቀደሳችሁና ትምሕርት እየተማራችሁ በቤተክርስቲያን ሕግና ሥርዓት እንድትመሩ በፊትም ሆነ አሁን ያልተከለከለ መሆኑን እንድታውቁት . . .  " ለሚለው ሐረግ የሚኖረን ተጨማሪ ምላሽ፣ ሐረጉ እውነታውን ለማያውቅ አካል አሳሳች መልዕክት ያዘለ መሆኑን ነው፡፡  ሐቁን ከዚህ ጋር አያይዘን ያቀረብነው ማስረጃ ማለትም መጋቢት 6 ቀን 2004 ዓ.ም "ጥብቅ ማስጠንቀቂያ"! በሚል ርዕስ ባወጣችሁት ማስታወቂያ፣
" . . . በአንዳንድ ምክንያት ቅር ተሰኝተናል በማለት እጅግ በጣም ውስን የሆናችሁ . . . በግለሰብ ቤት ውስጥ ማንነታቸው ካልታወቁ መምህራን ጉባዔ የምትሳተፉ መሆኑን በየጊዜው በተደጋጋሚ ሪፖርት ቀርቦልናል . . . ለሁለት ጌቶች መገዛት አትችሉም. . . ከዚህ ድርጊታችሁ ባትቆጠቡ ቤተክርስቲያን ከምትሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት ማግኘት የማትችሉ መሆኑን በቅድሚያ በጥብቅ እናስታውቃለን" በማለት፣ መንፈሳዊ አገልግሎት ማገዳችሁ በይፋ ይታወቃል፡፡ እኛ በአሥር ሺዎች የምንቆጠር እንጂ "እጅግ በጣም ውስን የሆናችሁ" የምንባል አይደለንም፤ አርስዎም ይህንን አሳምረው ያውቁታል፡፡ ማንነታቸው ካልታወቁ መምህራን ጉባዔ የምንሳተፍም አይደለንም፡፡ መምህራኖቻችን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቀኖና መሠረት የተቀቡና ፀጋው ያላቸው እንዲሁም ከመንፈሳዊ ኮሌጆች የሥነ መለኮት ምሩቃን ጭምር ናቸው፡፡ "ለሁለት ጌቶች መገዛት አትችሉም" የሚለውን መልዕክት በተመለከተም እኛ ምንም ዓይነት የሃይማኖት ጥርጥር የሌለብንና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ያልወጣን ነገር ግን ከመልካም አስተዳደር እጦት የተነሳ ከእናንተ የተለየን ስንሆን ይህ መለየታችን ለሁለት ጌቶች እንደተገዛን አያስቆጥረንም፡፡
በተጨማሪም፣ ዛሬ የንስሐ አባት በነፍስ ወከፍ እንድትይዙና እንድትመዘገቡ አዘዘናል እንደምትሉት ሳይሆን፣ " . . . በየግለሰቡ ቤተጉባዔ ለመሳተፍ የሚሰበሰቡት ግለሰቦች የንስሐ አባት የሆናችሁ ሁሉ የንስሐ ልጆቻችሁን በመምከርና በማስተማር እስከ መጋቢት 30/ 2004 ዓ.ም ድረስ ወደ ቤተክርስቲያኒቱ እንዲመለሱ እንድታደርጉና ስም ዝርዝራቸውንም ለገዳሙ አስተዳደር ሪፖርት እንድታቀርቡ እያሳሰብን ይህ ባይደረግ ግን በንስሐ አባቶች ላይ ጥያቄ የሚደረግ መሆኑን በጥብቅ እናስታውቃለን. . .  " ብላችሁ መዛታችሁን ከላይ የጠቀስነው ደብዳቤ ያስረዳል፡፡
ከላይ የገለጽነውን ማስታወቂያ ወደ ተግባር በማሸጋገርም የእርስዎ መንበረ ጵጵስና  በሆነው ገዳም ውስጥ ከምዕመኖቻችን መካከል ሥጋ ወደሙን እንዳይቀበሉ፣ ጋብቻቸውን በተክሊል እንዳይፈጽሙ የተደረገ ሲሆን፣ እነዚህ ምዕመናን ከክልሉ ውጪ ወደ ሆኑ ሌላ አጥቢያ ቤተክርስቲያናትና ሀገረ ስብከት በመሄድ መንፈሳዊ አገልግሎት ለማግኘት መገደዳቸውን ልንገልጽ እንወዳለን፡፡ ሌላው ቀርቶ በግርግሩ ወቅት አራት ንጹሐን ወንድሞቻችን ከሦስት የተለያዩ የጤና ተቋማት በቀረቡና በሦስት የተለያዩ የምርመራ ወጤቶች ባልፈጸሙት ወንጀል እሥር ተፈርዶባቸው ማረሚያ ቤት ሳሉ እነርሱን ለመበደል ሲባል ብቻ በቅደሴው ሰዓት ሆን ተብሎ "የታሠሩትን አስፈታልን" የሚለው የጸሎት ክፍል እንዲዘለል ማድረጋችሁን ያስተዋለ አስተውሎታል፡፡ የሆነው ሆኖ እነዚህ ወንድሞቻችን ከቤተክርስቲያን ይልቅ በመንግሥት መልካም ፈቃድ ከሁለት ዓመት የእሥራት ቆይታ በኋላ በምሕረት የተለቀቁ መሆናቸውን በዚህ አጋጣሚ ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡
ስለዚህ፣ "ብፁዕ አባታችን"! እርስዎ የላኩልን የ"ተመለሱ" ጥሪ ደብዳቤ ባጠቃላይ ሲታይ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት በሀገረ ስብከታችን በተለይም በሀዋሳ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት ስለነበረው ዋና እና ከእናንተ ስላለያየን ችግር ምንም የሚለው ነገር የለም፡፡ የይቅርታና የችግር ፈቺነት መንፈስ በውሰጡ አልያዘም፡፡ በቤተክርስቲያኒቱ አጠቃላይ አሠራር ውስጥ ችግር ነበረ ወይንስ አልነበረም? ችግሩ ከነበረ ተፈትቷል ወይንስ አልተፈታም? ካልተፈታስ ለምንድነው የማይፈታው? የሚፈታስ ከሆነ እንዴትና መቼ ነው የሚፈታው? ስለዚህ ነገር ምንም ያላለ በመሆኑ የጥሪ ደብዳቤያችሁ ዋጋ የለውም፡፡
በሀገረ ስብከትዎ ችግሮች ሞልተው ተርፈዋል፡፡ ይህንን ለማስተካከል ምንም ጥረት አላደረጉም፡፡ ጥረት ለማድረግም ቅንጣት ታህል ፍላጎተ የለዎትም፡፡ በደፈናው ተመለሱ ቢሉን ትርጉም የለውም፡፡ እርስዎ ባሻዎ ዘመን አባርረውናል፤ ባሻዎ ዘመን ደግሞ ተመለሱ የሚሉን እርስዎ ያረቡን በጎች ወይም ዶሮዎች አይደለንም፡፡ የመንጋው መበተን የሚቆጭዎ እረኛ ከሆኑ "ጥቂት፣ አምስት የማይሞሉ" እያሉ በሐሰት በቁጥር ሚዛን ፍርድዎን መስጠት አልነበረብዎትም፡፡
እኛን በተደጋጋሚ ድንጋይ ወርዋሪ እያሉ ማጥላላትዎንና ስም ማጥፋትዎንም ቢያቆሙ የሚሻል መሆኑን ልንጠቁምዎ እንወዳለን፡፡ አንዳችም የሚጠቅም ነገር የለውምና፡፡ ድንጋይ ወርዋሪው ማንና እነማን እንደሆኑ የእኛም የእርስዎም ልብ ያውቀዋል፡፡ በቅዱስ ገብርኤል ገዳም የእግዚአብሔር መንግሥት ወንጌል እንዳይሰበክ፣ የምሥጋናው ዝማሬ እንዳይደመጥ፣ ምዕመናንና አገልጋዮች ላይ የሽብር ጥቃት በመፈጸም ለወንጌል የታደመውን ሕዝብ ለመበተን ድንጋይ ሲወረውሩ የነበሩት የተደራጀ ቡድን አባላት በፀጥታ አስከባሪዎች እጅ ገብተው በሕግ ተጠያቂ እንዳይሆኑ ጥቃት እያደረሱ፣ የግቢ በር እየተከፈተ እየገቡ ይሸሸጉ የነበሩት እርስዎ መኖሪያ ግቢ (መንበረ ጵጵስና) ነበር፡፡ ስለሆነም እውነተኛዎቹ ድንጋይ ወርዋሪዎች የተደራጁትና ያሉት በእርስዎ በኩል እንጂ በእኛ በኩል አይደለም፡፡ በዚህ ኃላፊነትዎና ዕድሜዎ ይህንን የማያምኑ ከሆነ በተንቀሳቃሽ ባለቀለም ቪዲዮ ምስል እፊትዎ አቅርበን እናሳይዎታለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣
· አንዲት የ60 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን እናታችንን በድንጋይ እጃቸውን ሰብሮ አካላቸውን ያጎደለውን አንድ የማኅበረ ቅዱሳን አባል የቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሰንበት ት/ቤት አመራር አድርገው ማስቀመጥዎን፣
· ዩኒፎርም የለበሰች የቀድሞ የሰንበት ት/ቤት አባልን አገልግሎት ላይ ሳለች በቡጢ የተማታ አንድ ግለሰብ ለፈጸመው ጀብዱ ያለ አጥቢያው ሄዶ የቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን የሰበካ ጉባዔ እና የቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን የልማት ኮሚቴ አባል አድርገው በሹመት ማንበሽበሽዎን፣
·  አሁንም በአንዲት የቀድሞ የሰንበት ት/ቤት ወጣት ዓይን ውስጥ ሚጥሚጣ የጨመረች አንዲት ግለሰብ የቤተክርስቲያን የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል አድርገው መሰየምዎን፣ ሁሉም የሚያውቀው ሲሆን ስለተጠቀሱት ግለሰቦች ድርጊት የሰው፣ የቪዲዮና የጽሑፍ ማስረጃ ማቅረብ እንችላለን፡፡ ከዚህ አንፃር ድንጋይ ወርዋሪው እና ምዕመናንን የሚያሸብሩ የእርስዎ ወገን መሆናቸውን በይፋ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ አሠራርም ለእርስዎ ዓላማ ምን ዓይነት ሥነምግባር ያላቸው ሰዎች እንደሚስማሙዎትና የቤተክርስቲያኒቱንም መዋቅር በምን ዓይነት ሰዎች እንደሞሉት ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡
እርስዎ ስለሀዋሳ ችግር አንድም ነገር በቅጡ ሳይረዱ እና ሳይመረምሩ እኛን ማሳደድ የጀመሩት ገና ወደ ሀገረ ስብከታችን ሳይመጡ (አፈሩን ሳይረግጡ) በፊት አስቀድመው የመረጡትን ሥራ አስኪያጅ በመላክ ከዚያም "ሰንበት ት/ቤቱ ይታሸግልኝ" ብለው በማዘዝ እንደነበር ልናስታውስዎ እንወዳለን፡፡ ምንም እንኳን ከእርስዎ በፊት የሀገረ ስብከታችን ሊቀጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በሐሰት እንደተወነጀሉና ንጹሕ መሆናቸውን ብናውቅ እና የተዛወሩበትን ውሳኔ ማሻር ባንችልም፣
1ኛ. የእርሳቸውን (የብፁዕ አቡነ ፋኑኤልን) ንጽሕና ለመመስከር፣
2ኛ. ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ ከሀገረ ስብከታችን ተነስተው የነበሩትን ብፁዕ አቡነ በርተለሜዎስን በሕዝብ ስም ይቅርታ ለመጠየቅ፣
3ኛ. የሲኖዶስን ውሳኔ አክብረን እርስዎን ለመተዋወቅ እና ሦስታችሁም ሊቃነ ጳጳሳት ባላችሁበት በፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፊት ይህ ዓይነት ጳጳሳትን በኃይል የማስወገድ ባህል እንዳይደገም ለመመካከር ወደ አዲስ አበባ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት መጥተን ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ እርስዎን ለመተዋወቅና ቡራኬዎንም ለማግኘት ወደ እርስዎ ስንቀርብ የአማካሪዎችዎንና የአጃቢዎችዎን ምክርና ወሬ ሰምተው፣ "ይህ ሕዝብ እኔን ሊቃወመኝ እንጂ ከሀዋሳ ተነስቶ በጤናው እዚህ ድረስ አልመጣም" በማለት ሊያነጋግሩን ቀርቶ ሊያዩን በመጠየፍ መሸሽዎን አይረሱትም፡፡ ከላይ በጠቀስነው ዕንቁ መጽሔት ቁጥር 47 ላይም አንደኛው ቡድን ዝም ያለ ሌላኛው የሚነቅፍ፣ የሚሳደብ ብለው መግለጫ እስከ መስጠት ደርሰዋል፡፡ አዲስ አበባ ላይ ሆነው ይታሸግልኝ ያሉትን የሰንበት ት/ቤት አዳራሽና ጽ/ቤት በልመና ለጊዜው ቢከፍቱትም አንድ ጊዜ አስተያየትዎ የተዛባና ለአንድ ወገን ያደላ ነበርና ከአምስት ቀናት በኋላ እስከወዲያኛው በፖሊስ ኃይል ማሳሸግዎን እና ነባሮቹን የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን መበተንዎን ያስታውሱታል ብለን እናምናለን፡፡ ከዚያ በኋላ፣ እኛ እንድንታሠር፣ እንድንበተን ደጅ ያልጠኑበት፣ በር ያላንኳኩበት መሥሪያ ቤት ይኖራልን? ዛሬ የዜጎችን በነፃ እምነትን የማራመድ መብት የሚጠብቅ ሕገመንግሥትና መንግሥት ባይኖሩ ኖሮ ከሁሉም በላይ ደግሞ የምንመካበት ታላቁ እግዚአብሔር ባይታደገን ኖሮ እንደ አስተሳሰባችሁ ቢሆን ኖሮ ገና ድሮ ከምድረ ገጽ በጠፋን ነበር፡፡
የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ሺፈራው ሽጉጤ ከሁለታችንም ወገን ሃምሣ ሃምሣ ሰው ሰብስበው ባነጋገሩበት ወቅት እርስዎ ከአቶ ሺፈራው ጎን ተቀምጠው በገለልተኝነት "ልጆቼ አትለያዩብኝ፤ ታረቁልኝ" በማለት ፈንታ እንደ ተበዳይ ሆነው ከ49ኙ የእርስዎ ቡድን አባላት ጋር 50ኛ ሆነው ሚናዎን ለይተው ሲከራከሩን እንደነበር ማንም ያውቀዋል፡፡ ስለዚህ፣ ዛሬ "ልጆቼ ኑ ተመለሱ" ብለው የጥሪ ደብዳቤ ቢልኩልን ከትዝብት በስተቀር የሚያተርፉት የለም፡፡
የነበረውን የቤተክርስቲያን ችግር ለመፍታት የመንግሥት ታዛቢ ባለበት ከሁለቱም ወገን ሃያ አምስት ሃያ አምስት ሆነን በድርድር የፈታነውንና በዐውደ ምሕረት ላይ በሥርዓተ ጸሎት ጭምር የታወጀውን ሁሉ አቀፍ የዕርቅ ሠነድ ከአንድ ሳምንት በኋላ አንድ ባላምባራስ አልፈቀዱትምና (ቤተክርስቲያኗ የባላምባራስ የግል ድርጅት የሆነች ይመስል)ተግባራዊ አይሆንም በማለት እርስዎ ራስዎ መሰሠረዝዎን በደንብ ያስታውሱታል፡፡
"ብፁዕ አባታችን" በአሁኑ ሰዓት እርስዎ በሀገረ ስብከትዎ እግዚአብሔር ያመላከተዎትን ለመወሰንና ለመፈጸም ከማይችሉበት ደረጃ ላይ እንደደረሱ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ በአሁኑ ወቅት ሀገረስብከቱን እያሽከረከረ ያለውን ቡድን እርስዎም፣ እኛም እናውቀዋለን፡፡ ስለዚህ የአምላክን ጎዳና የሳተ እና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የሚጥስ ተግባር ሲፈጸም ስለእርስዎ እናዝናለን፤ እንጨነቃለን፡፡ እንዲያውም ዛሬ የቤተክርስቲያኗ መሪ እርስዎ ሳይሆኑ ከእርስዎ ጀርባ ሆነው የሚያስተዳድሩት ዋናዎቹ ሰዎች የሚያዙዎትን ለመፈጸም የተቀመጡ ይመስለናል፡፡
እርስዎ በሀገረ ስብከታችን እስከዛሬ ለዘለቀው ብርቱ ክፍፍልና አንድነት አለመምጣት ቀዳሚውን ሚና የተጫወቱ ሲሆን በእርስዎ ጥሪ እና ማግባቢያ የቤተክርስቲያኒቱ የቀድሞ ፍቅርና ሠላም ይመለሳል የሚል እምነት ጨርሶ የለንም፡፡ በመካከላችን ምንም ዓይነት የአባትነትና የልጅነት ግንኙነት የለም፤ በተከታታይ እንቅስቃሴዎና እርምጃዎ ይህንን ግንኙነት ዳግም ላይቀጠል ቆርጠው ጥለውታል፡፡ ስለዚህ፣ ወደየአጥቢያ ቤተክርስቲያናቶቻችን ቅጥር ግቢ ለመመለስና አንድነት ለመመሥረት የእርስዎ ከሀገረ ስብከታችን መነሳት እና በቦታዎ የገለልተኛ አባት መመደብ ዋና እና እጅግ በጣም አስፈላጊው ቀዳሚ ነገር መሆኑን ሊያሠምሩበት ይገባል፡፡
የ"ተመለሱ" ጥሪ ደብዳቤው ግልባጭ የተደረገላችሁ የቤተክርስቲያናችንና የመንግሥት ተቋማትም እውነታውን እንድትረዱት እና ከብፁዕ አቡነ ገብርኤል ጋር ስላለን ልዩነት ግልጽ እንዲሆንላችሁ ወደ ቤተክርስቲያናችን እንድንመለስ የሚፈለግ ከሆነ: ̶
1.  ለሀገረ ስብከታችን ብጥብጥ መስፋፋት ምክንያት የሆኑት፣ በኋላም ቅዱስ ሲኖዶስ በኮሚቴ አጣርቶ ቋሚ ሲኖዶሱ መጋቢት ቀን 2003 ዓ.ም በወሰነው መሠረት ከሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነታቸው የተነሱትና ከአንድ ዓመት በኋላ አቡነ ገብርኤል የሲኖዶሱን ውሳኔ ሽረው በግል ፍላጎታት መልሰው በድብቅ የመደቧቸው ሊቀ ህሩያን ዓለምሸት ገ/ፃድቅ በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት ከሀገረ ስብከቱ እንዲነሱልን፣
2.  ቅዱስ ሲኖዶስ መስከረም 12 ቀን 2002 ዓ.ም ባካሄደው የሠላም ጉባዔ ማኅበረ ቅዱሳን የተባለው ማኅበር በማናቸውም የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ የተላለፈው ውሳኔ ሊከበር ይገባል፡፡ ስለዚህ፣ አቡነ ገብርኤል በየአጥቢያ ቤተክርስቲያናት፣ በየወረዳ ቤተክህነት ጽ/ቤት፣ በሰበካ ጉባዔ፣ በስብከተ ወንጌል፣ በልማት ኮሚቴ እና በሰንበት ት/ቤት ስም ከላይ እስከ ታች ባለው የቤተክርስቲያን መዋቅር ሥር የሰገሰጓቸው የማኅበረ ቅዱሳንና የጥቂት ጥገኛ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴ ኃይሎች ወጥተው ለማንም የማይወግኑ ከማኅበራት ንክኪ ነፃ የሆኑ የምዕመናንን ወገን ፍትሐዊ እና ግልጽ በሆነ አኳኋን እንዲመደቡልን፣
3.  አጥቢያ ቤተክርስቲያናት በተለይም የሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ገዳምንና የደብረ ሠላም ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያናት የሚያካሄዱትን የልማት እንቅስቃሴ ማለትም የሁለገብ ሕንፃ ግንባታ፣ የቤተክህነት ት/ቤት አስተዳደርና የገቢ አሰባሰብ፣ የአውቶቡስ ሽያጭ ገንዘብ አጠቃቀም፣ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ግንባታ በነፃ ኦዲት እንዲመረመር፤ እንዲሁም የቤተክርስቲያን ገቢና ወጪ በሕጋዊ ኦዲተሮች ተመርምሮ ለምዕመናን ይፋ ሲደረግ እና ምዕመናን የቤተክርስቲያኒቱ ልጅና የሀብት ምንጭ በመሆናቸው የሀብቱ አድራሻና መጠን የማወቅ መብታቸው ሲረጋገጥ፣ እንዲሁም ለወደፊት ከእያንዳንዱ ምዕመን ኪስና መቀነት በወጣ ሳንቲም የተገነቡ የቤተክርስቲያን የሀብት ማመንጫ ተቋማት ባለቤት የሆነው ሕዝብ ሳያውቀውና ሳይመክርበት ወደ ግለሰብ ነጋዴ ይዞታነት የማስተላለፍ አሠራር እንዲቆም፤
4.  አንድ ግለሰብ በቅዱስ ገብርኤል ገዳም የልማት ኮሚቴ አባልነት ያገለገለ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ከሚኖርበት የገብርኤል አጥቢያ ተንቀሳቅሶ እስከ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን በመላክ የልማት ኮሚቴ ቁጥጥር አባል ተደርጓልል፡፡ ይኸው ግለሰብ በኮሚቴነቱ ሳያፍር ሥልጣኑን ተገን በማድረግ የቅድስት ሥላሴን 6ሺህ ካ.ሜ. መሬት ቆርሶ ለአምስት ዓመታት ያለጨረታ በመከራየት አስነዋሪ ድርጊት ፈጽሟል፡፡ ስለዚህ ሳይውል ሳያድር ይህ ግድፈት ተወግዶ ይዞታው ለቤተክርስቲያን እና ለምዕመኖቿ እንዲመለስ፣
5. አንድ ምዕመን በቃለዐዋዲው የተዘረዘሩትን የምርጫ መስፈርቶች እስካሟላ ድረስ ማገልገል ያለበት በተመዘገበበትና የአባልነት መታወቂያ በወሰደበት አጥቢያ ብቻ ነው፡፡ እየሆነ ያለው ግን ከገብርኤል አጥቢያ ሰዎችን በመላክ በሌሎቹ ሰባት አጥቢያ ቤተክርስቲያናት ሰበካ ጉባዔዎችና በሌሎች ኮሚቴዎች ውስጥ በመሰግሰግ የቤተክርስቲያኒቱን ሀብትና የአሠራር ነፃነት በአንድ ማዕከል ጨምድዶ በመያዝ ሕግን ያልተከተለ አሠራር ማስፈን ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በቅድስት ሥላሴ ልማት ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለገሉት ሰዎች ከገብርኤል አጥቢያ የተላኩና ያለ አጥቢያቸው፣ ያለሰበካ ጉባዔያቸው የተመደቡ ናቸው፡፡ በዳቶ ኪዳነምሕረት፣ በመድኃኔዓለም፣ በቅዱስ ሩፋኤል፣ በባለወልድ እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያናት የተመደቡት ሰዎች ያለአጥቢያቸው፣ ሕዝብም ያልመረጣቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ፣ ሁሉም በየራሱ አጥቢያ ብቻ ተወስኖ እንዲያገለግል፣
6. በሕንፃ ግንባታ ውስጥ የተሰገሰጉ የልማት ኮሚቴ ተብዬዎች ራሳቸው የሕንፃ ዕቃ አቅራቢ፣ ሻጭ፣ ገዥ፣ ከፋይ፣ አጽዳቂ የሚሆኑበትን የአሠራር ግድፈት እንዲወገድ እና ግልጸኝነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የሂሣብ አሠራር እንዲዘረጋ፣
7.     የተባረሩት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ወደ እናት ቤተክርስቲያን ተመልሰው የሰንበት ት/ቤት አባልነታቸው ተጠብቆ እነርሱም ባሉበት ከማኅበረ ቅዱሳን ንክኪ ነፃ የሆነ አዲስ አመራር በጋራ እንዲመረጥ፣
8.  አሁን በቅርቡ ሐምሌ 24 ቀን 2005 ዓ.ም የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ለሀዋሳ ከንቲባ ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ የአገልጋዮችን ስም በመጥቀስ ለማገልገል ፈቃድ የሌላቸው ናቸው በማለት ከንቲባ ጽ/ቤቱ የጉባዔ ማካሄጃ ቦታ እንዳይፈቀድላቸው መጠየቁን መረጃ ደርሶናል፡፡ በሌላ በኩል ከሀገረ ስብከታቸው ያልተፈቀደላቸው እና ቅጥር ሠራተኛ ያልሆኑትን እነ መምህር ዘበነ ለማን፣ ዳንኤል ክብረትን፣ ዘሪሁን ሙላቱን እና ሌሎችንም ዘማርያን ነን ባዮችን እያስመጣ ዐውደ ምሕረት ላይ እንዲወጡና ያሻቸውን እንዲናገሩ እንደሚፈቅድላቸው እናውቃለን፡፡ ሌላውን የቤተክርስቲያን አገልጋይ ደግሞ ፈቃድ የሌለው አጉራ ዘለል እያሉ ስብከተ ወንጌል እንዳይካሄድ ያግዳሉ፡፡ ይህ በራሱ የአንድ እናት ቤተክርስቲያን ልጆችን መለያየትና ግልጽ ማዳላት ነው፡፡ ይህን የመሰለ መድልዖ የተሞላበት ኢፍትሐዊ አስተዳደር በቤተክርስቲያን አገልግሎት ወደፊት ችግርና መከፋፈል የሚያስከትል ነው፡፡ ስለዚህ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ለይቶ ካላወገዘው በስተቀር ቤተክርስቲያን የቀባቻቸው ሰባክያነ ወንጌል እና መዘምራን ያለ ልዩነት ማገልገል እንዲችሉ፤ ከተደረገ ልዩነታችን ተወግዶ ነገ ተነገ ወዲያ ሳንል ወደ እናት ቤተክርስቲያናችን ቅጥር ግቢ ተመልሰን እንገባለን፡፡
ስለዚህ "ብፁዕ አባታችን"፣ ስለ ደብዳቤዎ እያመሰገንን፣ ዘወትር ጥይት እየተተኮሰ፣ ኡኡታና ሁከት በዝቶባት ችግር ላይ ወድቃ የነበረችው እናት ቤተክርስቲያናችን ሠላሟ እንዲጠበቅ እና የቀደመው ፍቅር እንዲመለስ የልብዎ ፈቃደ ከሆነ ሀገረ ስብከታችንን ለቀው ይሂዱልን፡፡ ቀሪዎቹ ችግሮች በጠቅላይ ቤተክህነት እና አዲስ በሚመደቡ ገለልተኛ አባት የሚፈቱ ይሆናሉ፡፡ በመግቢያው ላይ እንደጠቀስነው ጥሪያችሁ የለበጣ ከሆነ እና እግረ መንገዳችሁን ለገጽታ ግንባታ (ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ) ብቻ  ከሆነ በከንቱ አይልፉ፤ ፍትሕን ከቅዱስ ሲኖዶስ እየጠበቅን ነው፡፡ ምናልባት በጠላት አሠራር ፍትሕን ከሲኖዶስ ባናገኝ እንኳን አባታችን እግዚአብሔር ስለማይጥለን ሕገ መንግሥቱ በሰጠን መብት ተጠቅመን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነታችንን በልባችን ይዘን የፍትሕ ፀሐይ የምትወጣበትን ቀን ካለንበት ሆነን እንጠባበቃለን፡፡
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት እና ከጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት የምንጠብቀው ዐቢይ ጉዳይ፣ ከላይ የዘረዘርናቸው ችግሮች አንድ በአንድ እንዲፈቱልንና ወደ እናት ቤተክርስቲያናችን እንድንጠቃለል ነው፡፡ ነገር ግን እንዳለፉት ሦስት ዓመታት ችላ የሚባልና ተሸፋፍኖ የሚቀር ከሆነ ምናልባትም በቤተክርስቲያናችን ተጨማሪ መሰንጠቅ እንዳይከሰትና ለምዕመናን መከፋፈል እንዳይሆን እንድናስብበት በአባታችን በእግዚአብሔር ስም አደራ እንላለን፡፡
የእግዚአብሔር ሠላም ከሁላችን ጋር ይሁን!!
ጥላሁን አመጆ
በሀዋሳ በግፍ የተሰደዱት ምዕመናን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ሕብረት ተወካይ

ግልባጭ
·  ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
·  ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት
·  ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት
·  ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር
አዲስ አበባ

·  ለሲዳማ፣ ጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት
·  ለደ/ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት
·  ለደ/ሠላም ቅ/ሥላሴ ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት
·  ለደ/ጽ/ቅ/ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት
· ለደ/ታ/ቅ/ሩፋኤል ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት
·  ለኆህተ ሰማይ ቅ/እግዚአብሔር ወልድ ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት
· ለደ/መንክራት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት
· ለሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት
· ለሀዋሳ ከተማ ፍትሕ እና ፀጥታ አስተዳደር መምሪያ
· ለመሀል ከተማ ክ/ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት
· ለአዲስ አበባ ቀበሌ አስተዳደር ጽ/ቤት
· በደቡብ ክልል ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ለሃይማኖት መቻቻልና መከባበር ዋና የሥራ ሂደት
· በየአጥቢያ ቤተክርስቲያኑ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክስቲያን ምዕመናን በሙሉ
ሀዋሳ
Share this article :

+ የተሰጡ አስተያየቶች + 1 የተሰጡ አስተያየቶች

Anonymous
August 16, 2013 at 11:44 AM

Yediabilos Lijoj Nachihu/////////////////

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger