ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎቷን እንድታድስ የተቋቋመ ትምህርት ቤት

                          ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ 
  ከተመሠረተበት እስከ አሁን
  (ክፍል አንድ) www.tehadeso.com
  ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በቀድሞ መጠሪያው “ከፍተኛ የትምህርት ማዕከል”፣ አሁን ወዳለበት ቦታ ከመዘዋወሩና ደረጃውም ወደ ኮሌጅነት ከፍ ከማለቱ በፊት ትምህርት ማስተማር የጀመረው በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ውስጥ ነበር፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጣልያን ወረራ ምክንያት ሕገ ወጥ የሆነውን ወረራ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስረዳትና አቤቱታን ለማቅረብ ከሀገር ውጭ ተጉዘው ነበር፡፡  በውጪው ዓለም በስደት በቆዩበት ዓመታት እርሳቸውና አብረዋቸው የተሰደዱ ባለስልጣናት ከጎበኟቸው ልዩ ልዩ ተቋማት መካከል የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን አንዷ በመሆኗ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጥንካሬ ምክንያት ደግሞ መንፈሳዊ የትምህርት ተቋማቶቿ አገልጋዮችን በብቃትና በጥራት እያስተማሩና እያዘጋጁ ለቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ አገልግሎት በማሰማራቷ መሆኑን በመገንዘባቸው ይህንንም ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ጋር አገናዝበው ቤተ ክርስቲያን ልትታደስ ይገባታል ብለው በማመናቸው ከስደት እንደተመለሡ ቤተ ክርስቲያን ለምእመናን የምትሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንዲሆንና ሰባክያንና መምህራን በትምህርተ ወንጌል ዘመኑንና ትውልዱን መዋጀት የሚችሉ እንዲሆኑ፣ እውቀት የበለጠ እንዲስፋፋ ትኩረት በመስጠታቸው፣ በተለይም ካህናት በሕዝቡ ዘንድ ተሰሚነት ስላላቸው እውቀታቸው ከተሻሻለ ለሕዝቡ የተሻለ አገልግሎት ይሰጣሉ ብለው በማሰብ፣ ትምህርት ቤት እስኪዘጋጅ ድረስ እንኳ ሳይጠብቁ ቤተ መንግሥታቸውን (አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ) ትምህርት ቤት አድርገው ተማሪዎችን በመቀበል፣ በቶሎ ደርሰው ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን በበለጠ ያገለግላሉ ተብለው የተገመቱትን ሊቃውንት ሰብስበው መምህር መድበው የእንግሊዝኛ ቋንቋ እንዲማሩ አደረጉ፡፡ የዚህን ቋንቋ ትምህርት ቤት ጀምረው እስከ መጨረሻው ከተከታተሉት ሊቃውንት መካከል መምህር መልእክቱ (በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ.አቡነ.ቴዎፍሎስ) ይጠቀሳሉ፡፡

       ከዚህ በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በ1935 ዓ.ም. የቅድስት ሥላሴን መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ሕንጻ የመሠረት ድንጋይ አስቀመጡ፤ በ1937 ዓ.ም. በይፋ ተመርቆ ተከፈተ፡፡ በዚያ ወቅት የአስተዳደር ኃላፊነት የተሰጣቸው የሚከተሉት ነበሩ፡-
1.     ሊቀ ሥልጣናት መልእክቱ (በኋላ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ)- ሊቀ መንበር
2.    ሚስተር ሃፍዝ ዳውድ ግብጻዊ- ዳይሬክተር
3.    ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ-  አባል
4.    አለቃ ሐረገ ወይን- አባል
5.    ባላንባራስ ወልደ ሰማዕት- አባል
6.    መ/ር ፌላታያስ ሰማዕት- አባል
7.    መጋቤ ሐዲስ ወ/ሚካኤል- አባል
የትምህርት ቤቱ መምህራንም፡- ሃፍዝ ዳውድ፣ መ/ር ፌላታዎስ፣ አለቃ መኩሪያ፣ አለቃ ወልደየስ፣ አባ ፍስሐ፣ አባ አሥራት ዘገየ፣ ሊቀ ጠበብት አክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስ ይባሉ ነበር፡፡ ለትህምርት ቤቱ በአመራር ደረጃ እና በመምህርነት የተመደቡ በወቅቱ ሀገሪቱ ላይ ዕውቅ ሊቃውንትና ባለ ሥልጣናት መሆናቸው ተቋሙ የታለመለትን ዓላማ ከግብ እንዲያደርስ ከልብ የታሰበበት እንደነበረ በግልጽ ያስረዳል፡፡


ኮሌጁ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ አካል መሆኑ፡-
     በመንፈሳዊው ኮሌጅ ገብተው በዩኒቨርስቲ ደረጃ የሚሰጠውን የ4 ዓመት ጥናት በሚገባ በማጠናቀቅ በ1956 ዓ.ም. የጨረሱት ተማሪዎች የመጀመሪያዎቹ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ተመራቂዎች ነበሩ፡፡ በ1956 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ 6 ወጣቶች ቢ.ቴ.ኤች ዲግሪያቸውን በቴዮሎጂ ተቀበሉ፤ እነዚህም፡-
1.     አበራ በቀለ
2.    አዕምሮ ወንድም አገኘሁ
3.    እጅጉ ደሳለኝ
4.    ገ/ክርስቶስ መኮንን
5.    ሐጎስ ገ/ማርያም
6.    ጸጋዬ ሐብቴ ይባላሉ፡፡
እነዚህ የመጀመሪያዎቹ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቃን ነበሩ፡፡
   ኮሌጁ ለቤተ ክርስቲያን ተሐድሶን ያመጣል ተብሎ ታምኖበት የተከፈተ እንደመሆኑ መጠን የተማሪዎች ምልመላ ላይም ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል፡፡ ከዚህ መንፈሳዊ ተቋም ተምረው የወጡ ሁሉ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለንተናዊ ተሐድሶ የበኩላቸውን ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክተዋል፡፡ ከኮሌጁ ፍሬዎች መካከል በተራ ቁጥር 1 ላይ የተጠቀሱት ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ ተሐድሶ የሚያውጅ መጽሐፍ ‹‹ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት…›› በሚል ርዕስ በ1996 አዘጋጅተው ማኅበረ ቅዱሳን ማሳተሙ ይታወሳል፡፡ በተራ ቁጥር 4 የጠቀስናቸው ገ/ክርስቶስ መኮንን ደግሞ በ1996 ዓ.ም. የዚሁ ኮሌጅ ዲን ሆነው ማገልገላቸው ይታወቃል፡፡
     በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ኮሌጁ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው እንደ ነበረ ለመረዳት የሚቻለው በአስተዳደር ኮሚቴ ውስጥ የሚመረጡ ሰዎች ሀገሪቱ አለኝ ከምትላቸው ምሁራን የተውጣጡ መሆናቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ በ1945 ዓ.ም. የህንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባል የነበሩት ዶክተር ሳይመን የዳሬክተርነቱን ሥልጣን ከአባ ማርቆስ ዳውድ ሲረከሉ በአስተዳደር ሓላፊነት ላይ፡-
-    ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ- ሊቀ መንበር
-    ዶ/ር ሳይመን - ጸሐፊ (አርመናዊ)
-    ደጃዝማች ዘውዴ ገ/ሥላሴ- አባል
-    አቶ አበበ ረታ
-    ብላታ መርስኤ ኀዘን ወ/ቂርቆስ
-    ሊቀ ሊቃውንት መሀሪ ትርፌ (አቡነ ጴጥሮስ የቅ/ጳውሎስ መልእክት የተረጎሙ)
-    ደጃዝማች አምሀ አበራ
-    ልጅ እንዳልካቸው መኮንን (በኋላ ጠ/ሚኒስቴር)
-    አቶ ከበደ ሚካኤል (ት/ሚኒስቴር)
-    አቶ ሚሊዮን ነቅንቅ
-    አቶ አዲስ አለማየሁ የተካተቱበት ነበር፡፡
  ይህ ታላቅ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከተመሠረተበት እስከተዘጋበት ድረስ (1935-1970)፣ ሐፍዝ ዳውስ ግብፃዊ፤ ዶ/ር ሣይመን ሕንዳዊ፣ ቴሬንግፓላዲ አርመናዊ ጳጳስ በዲንነት ኮሌጁን ያስተዳደሩት ሲሆን፣ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ትምህርት ቤቱ ካፈራቸው መካከል ሥራቸው ጎልቶ የወጣ ታዋቂ የነበሩትን እንደ ማሳያ ብንመለከት እንኳ፡-
-    አባ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ
-    ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ
-    አባ ጳውሎስ ፓትርያርክ
-    ፕሮፌሰር ሉሌ መላኩ (በሕይወት ያሉ)
-    ዶ/ር ስርግው ኃብለ ሥላሴ
-    ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገ/አማኑኤል (በሕይወት ያሉ)
-    ዶ/ር ሐዲስ የሻነው (በሕይወት ያሉ)
-    ሊቀ ሥልጣናት አባ ኃብተማርያም (አባ መልከ ጼዴቅ)(በሕይወት ያሉ)
-    ገብረ ክርስቶስ መኮንን (ዲን የነበሩ) ተጠቃሾች ናቸው፡፡
እነዚህ የዚህ ተቋም ፍሬዎች ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የሚተርፍ የተሐድሶ ሥራ በመሥራት ባለ ውለታ ናቸውና ሲዘከሩ ይናራሉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ሥራቸውን በስፋትና በጥልቀት ባናቀርብም አቋማቸውን ለመግለጥ ያህል ስለ አንዳንዶቹ እናንሣ፡-
    ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ
        ሁለተኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሁለንተናዊ እድገት ያፋጠኑ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ለቤተ ክርስቱያኒቱ ተሐድሶ እንደሚያስፈልጋት አስረግጠው የመሰከሩም ናቸው፡፡
-    የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ማቋቋም
-    የሰ/ት/ቤት ማዕከል ማቋቋም
-    የኢኪውሙኒካል ግንኙነትን መጀመራቸውና ማጠናከራቸው
-    ቤተ ክርስቲያን የራሷን ፓትርያርክ እንድትሾም በመታገል ራሷን ማስቻል
    የእኚህ የሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ፍሬ የሆኑት አባት የአቡነ ቴዎፍሎስ ዋናዎቹ የተሐድሶ የሥራ ውጤቶች ናቸው፡፡ ተሐድሶ ማለት ምን ማለት እንደሆነም ፓትርያርክ ሆነው በተሾሙ ዕለት ያስተላለፉት መልእክት ይህ ነበር፡-
‹‹የሰው ልጅ ዳግም ልደት ያገኘበት መንፈሱ ህሊናው ሁለንተናው የታደሰበት ሁልጊዜ በየቀኑ የሚታደስበት የዘላለም ፍስሐ መገኛ የሚሆን የእግዚአብሔር ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን... ሐዲስነት ያለማቋረጥ ሁልጊዜ በክርስቶስ መታደስ መሆኑን ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ ያለማቋረጥ የሚያስተጋባበት ብርቱ ድምፅ ደጋግሞ አሰምቷል (2ቆሮ. 4፥16፤ 5፥17፤ ዕብ. 10፥20፤ ራእ. 21፥5 ሮሜ 6፥4 ፤ ኤፌ. 4፥24 በዚህ ትምህርት ተሐድሶ ጽድቅ፣ ርትዕ፣ ንጽሕ፣ ለሰው ሁሉ መንፈሳዊ ሕይወት ጉዞ (አቅጣጫ) መሪዎች ናቸው…››
                             (ሐዲስ ሕይወት ቁ. 1 ግንቦት 1ቀን 1964)
ይህ የቅዱስነታቸው መልእክት የተሐድሶን ጽንሰ አሳብ በሚገርም ቋንቋ በዘመናቸው አስተላልፈዋል የኮሌጁ ዓላማ ምን እንደሆነም አንጸባርቀዋል፡፡ ተሐድሶ አዲስ መጤ አሳብ እንዳልሆነ መስክረዋል፡፡
 ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ
አምስተኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አባ ጳውሎስ የዚህ ኮሌጅ ፍሬ ሲሆኑ፣ ዳግም ኮሌጁ ተከፍቶ ነፍስ እንዲዘራ ያደረጉ፤ አጠገባቸው ያሉ ባይረዷቸውም የአባ ቴዎፍሎስን ፈለግ በመከተል ቤተ ክርስቲያኒቱ ተሐድሶን እንደሚያመጡላት የታመነባቸው፣ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር በደርግ አማካኝነት የተቋረጠውን የኢኪውሙኒካል ግንኙነት በሚገባ ተጠቅመውበት ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ ዓለም መድረክ ብቅ ያደረጓት አባት ናቸው፡፡ ተሐድሶን በተመለከተ በፓትርያርክነት በዓለ ሲመታቸው የወጣው መጽሔት ርእሰ አንቀጽ እንዲህ ይላል፡-
‹‹ዶ/ር ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የቤተ ክርስቲያኒቱን የተሐድሶ መሠረት በጣሉበት ወቅት የመጀመሪያው ተመራጭ አባትና የተሐድሶውን መሠረት የመጣሉን ተግባር ከቅዱስነታቸው ጋር አብረው ያከናወኑ ስለ ነበር የቤተ ክርስቲያኒቱን የተሐድሶ ተግባርም በብፁዕነታቸው ዘመነ ሲመት እንደሚቀጥል ይታመናል…››
                          (5ኛው ፓትርያርክ ሐምሌ 5 ቀን 1984 ዓ.ም.)
ብፁዕነታቸው ምንም እንኳ በብዙ ጫና 20 ዓመታት ቢያሳልፉም
-    የኮሌጁ ዳግም መከፈት
-    የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ መስፋፋት
-    ቤተ ክርስቲያን በዓለም መድረክ ያላትን ተሰሚነት ማሳደግ
-    ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያላት ግንኙነት እንደ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን እንዲቀበሉን እኛም እንድንቀበላቸው ያደረጉት ጥረት
-    በቤተ ክህነት ግቢ ውስጥ የሚመጥኑ ሕንጻዎች መገንባት
-    የከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ መከፈት
በእነዚህና መሰል ሥራዎቻቸው የቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ ጭራሽ ሳይደበዝዝ አስቀጥለውታል፡፡
    ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ
        አባ አበራ በቀለ የቅድስት ሥላሴ የመጀመሪያው የቴዮሎጂ ምሩቅ መሆናቸውን ተመልክተናል፡፡ ኮሌጁ ምን ያህል ሰውን ቀርጾ ወደ እውነተኛው የክርስቶስ መንገድ እንደሚመራ የተመለከትነው እኚህ ሰው ባዘጋጁት መጽሐፍ የገለጹትን በመመልከት ነው ይህም፡-
-    በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ብቻ ወደ አብ መቅረብ እንደሚገባ ይህን አስፍረዋል፡፡
‹‹ተስፋ የምናደርገውም የመጨረሻው ነገር ገነት መንግሥተ ሰማያት እንደሆነ የእምነታችንና የተስፋችን ባለቤት እራሱ ክርስቶስ አስረድቶናል፡፡ በክርስቶስ ላሉ ሁሉ የሚሰጣቸው የዘላለም ሕይወት ይኸው ነው፡፡ የምንሄድበት ሀገር ይኸው ብቻ ነው፡፡ መሄጃ መንገዱ መድረሻው ሀገሩ በክርስቶስ በኩል እንጂ በሌላ በኩል አይገኝም››
       (ትምህርት ሃይማኖት ክርስቲያናዊ ሕይወት ገጽ 216)
   - ጸሎትን በክርስቶስ በኩል ብቻ ማቅረብ እንደሚገባ ደግሞ፡-
‹‹በክርስቶስ ስም መጸለይ ማለት እሱ ለሰው ሲል ሰው ሆኖ በእግዚአብሔርና ለሰው መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሶ ያስታረቀንና ያቀረበን እርሱ በመሆኑ በእሱ መንፈስ እግዚአብሔር ‹‹አባታችን›› ብለን ለመጥራት ለመጸለይ መቻላችንን ያመለክታል መዳናችንና መታረቃችን በእርሱ በኩል ብቻ ስለሆነ ያለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ አንችልም. . . ››
          (ትምህርት ሃይማኖት ክርስቲያናዊ ሕይወት ገጽ 322)
እነዚህን እና ሌሎች መሠረታዊ ክርስቲያናዊ ትምህርት በጽሑፍ ያሠፈሩት ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ ኮሌጁ የተመሠረተበትን መሠረታዊ ዓላማ ምን እንደሆነ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረታዊ እምነት ምን እንደሚመስል በመጽሐፋቸው ገልጸው አልፈዋል፡፡
   ዶ/ር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ
ዶ.ር ሥርግው ታላቅ ታሪካዊ ተመራማሪ ከመሆናቸውም በላይ የማይክሮፊልም ፕሮጀክት (የብራና መጻሕፍት ፊልም ማንሻ) ለመጀመሪያ ጊዜ በአቡነ ቴዎፍሎስ አማካኝነት ከአሜሪካ በእርዳታ ሲመጣ ዳይሬክተሩ ዶ/ር ሥርግው ነበሩ፡፡
    በግል የሠሯቸው በተለይ 13 ቅጽ (Volume) ‹‹አማርኛ የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት›› የተሰኘው ሥራቸው ተወዳዳሪ የለውም፡፡ በውስጡም የአባ እስጢፋኖስ ደቀ መዛሙርት ገድላቸው፣ ገዳማቸው፣ የትውልድ ቦታቸው ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ እስከ አሁን በሁሉም ዘንድ በቂ የታሪክ ማስረጃ ሆኖ የሚጠቀሰው (የጥንትና የመካከለኛ የኢትዮጵያ ታሪክ) የተሰኘው የእንግሊዝኛ መጽሐፋቸው ነው፡፡ እነዚህን ስናስብ ኮሌጁ ምን ያህል ታላቅ እንደነበር መገመት አያዳግትም፡፡
  ፕሮፌሰር ሉሎ መላኩ
እኝህ አንጋፋ ምሁር እዚህ ኮሌጅ የተማሩና አሁን በማስተማር ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የታሪክ ምሁር ናቸው፡፡ በተለይ ‹‹ጠቅላላ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ›› በሚል ርእስ ባዘጋጁት መጽሐፋቸው ላይ «የቤተ ክርስቲያኒቱ ዘመን አመጣሽ፣ ወፍ ዘራሾች የሆኑቱ ጽንፈኛ ቡድኖች ሌሎችን የዓለም አብያተ ክርስቲያናትን እንደ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን›› የማይቀጥሩ ቢሆኑም ፕሮፌሰር ሉሌ በዓለም ያለች ቤተ ክርስቲያን አንድ መሆኗን እና የሁሉንም ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከነአመሠራረታቸው፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረትም አመሠራረትንና ዓላማን… መዝግበዋል፡፡
 ዶ/ር ሐዲስ የሻነው
ዶ/ር ሐዲስ እዚሁ ኮሌጅ ተምረው አሁን ዶግማና ቀኖና በማስተማር የሚገኙ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን ማረም ያለባትን በግልጽ መናገር ብቻ ሳይሆን የጻፉም ናቸው ለምሳሌ ‹‹ፍንጭ ፍተሻ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ገጽ 28 ላይ የገድላት መጻሕፍትን በተመለከተ፡-
‹‹የገድላት መጻሕፍት ከአወንታዊ ጎኑ ይልቅ አሉታዊ ይዘት በጉልህ ይታያል፡፡  አሉታዊ ይዘቱን የጎላ ያደርገዋል ሲባል አዎንታዊ ጎኑን ከመጠን በላይ በማጋነን (ድራማታይዝ በማድረግ) ከእውነተኛው እምነት በማውጣት ወደ ባዕድ አምልኮ ደረጃ ስለሚያመራው ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም አንዱን ክፍለ ሀገር ከሌላው በማሳነስ አንዱን ዘርና ጎሳ ከሌላው በማኮሰስ በማቆሸሽና በማጥላላት ተዘግቦ ይገኛል፡፡ ይህ የሚሆነው ቅዱስ የሚል ስያሜ ባለው ጻድቅ ዜና ሕይወት (ገድል) ውስጥ ሲሆን ይህን የመሰለ ግለኛ አስተሳሰብ ሊስተካከል የሚችለው በቅዱስ ሲኖዶስ ነበር…›› በማለት ጽፈዋል፡፡
(ፍንጭ ፍተሻ 1998 ገጽ 28-29)
  ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገ/አማኑኤል
ዶ/ር ምክረ እንደ ፕ/ር ሉሌ መላኩ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ታሪክን ‹‹የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ በምድር ላይ›› በተሰኘው በ2 ክፍል ባዘጋጁት መጽሐፍ ላይም ቤተ ክርስቲያኒቱን ማረም የሚገባትን እንድታርም ስለ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በጻፉት ክፍል ላይ ‹‹አፈወርቅ›› የተባለበትን ምክንያት የእኛን ቤተ ክርስቲያን በተለይ ማህሌተ ጽጌ ላይ የሠፈረውን የተሳሳተ አስተሳሰብ እንዲታረም ጽፈዋል፡፡
    ከብዙ በጥቂቱ ለማሳያ የሆኑትን የዚህ ኮሌጅ ፍሬዎች የእንታረም ጥያቄያቸውን ስንመረምር፣ መንፈሳዊ ኮሌጁ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የነበረው የመማር ማስተማር ሂደት ምን ያህል  የተማሪን ህሊና በሚገባ ማርኮ ለተሐድሶአዊ ጉዞ ያመቻች እንደነበር እንረዳለን፡፡ እነዚህንና ሌሎችን በርካታ ምሁራንን ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን ያፈራ፣ የንጉሠ ነገሥቱና የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የቅርብ ክትትል ያልተለየው መንፈሳዊ ኮሌጅ ነበር፡፡  ትምህርት ቤቱ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት እንደመጀመሩ መጠን በ1945 ዓ.ም. ወደ ሁለተኛ ደረጃ፣ በ1953 ወደ ኮሌጅ ደረጃ አደገ፡፡ በ1954 ብሔራዊ ዩኒቨርስቲ ሲከፈት እንደ ሌሎች ኮሌጆች ሁሉ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅም ቻርተሩ እንደተጠበቀ ሆኖ የዩኒቨርስቲው አካል ሆነ፣ ትምህርት ቤቱ ሲመሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ 20 ተማሪዎች ብቻ ነበሩ፤ ወደ ኮሌጅ ደረጃ ከፍ ሲል 15 ተማሪዎች ብቻ ነበሩ፡፡ እስከ ንጉሡ መውደቅ ድረስ ሲያገለግል ቆይቶ በአገሪቱ በ1966 ዓ.ም የተከሰተው የመንግሥትን ለውጥ ተከትሎ ወታደራዊው መንግሥት እንደ ሌሎቹ የቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረቶች ይህንንም ኮሌጅ ዘግቶ ወረሰው፡፡

ይቀጥላል…
Share this article :

+ የተሰጡ አስተያየቶች + 3 የተሰጡ አስተያየቶች

Anonymous
August 22, 2013 at 6:54 PM

እኔን ያልገባኝ ፡ አብ መንፈስ ቅዱስ አይደለም ብሎ ማለት ምን ማለት ነዉ። እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። ዮሐንስ 4/14 መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ አድርጎ ስለ እግዚአብሔር አንድነት እየተናገረ እንዴት ሶስት ነዉ እንላለን

Anonymous
August 22, 2013 at 6:55 PM

እኔን ያልገባኝ ፡ አብ መንፈስ ቅዱስ አይደለም ብሎ ማለት ምን ማለት ነዉ። እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። ዮሐንስ 4/14 መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ አድርጎ ስለ እግዚአብሔር አንድነት እየተናገረ እንዴት ሶስት ነዉ እንላለን

Anonymous
February 5, 2014 at 6:29 PM

do not expect to understand the doctrine of Trinity. You just accept it with out questioning because no one can answer your question unless you believe as a believer.

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger