Thursday, March 22, 2012

አንድ ጥያቄ አለኝ!

 ሰላም ለእናንተ ይሁን
በብሉይ ዘመንና በአዲስ ኪዳን ዘመን ስላሉት ነብያት ልዩነት ላኩልኝ በአዲስ ኪዳን ያሉት ነብያት በበለጠ አገልግሎታቸው እንዴት መሆኑን እንዳለበት ላኩልኝ ተባረኩ! (ስሙን ያልገለጸ ጠያቂ)
ከደጀብርሃን መልስ፣
 በአዲስ ኪዳን ውስጥ ነቢይነት ጨርሶ የሚረሳና የማይሰራ ጸጋ ነው እንዴ?
ስለ ነብይ ምንነት፣ማንነትና አገልግሎት በዚህ በአዲስ ኪዳን ዘመን ብዙ እያከራከረ ይገኛል። አንዳንዶች አብያተ ክርስቲያናት እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ያሉት በአዲስ ኪዳን ስላለ ነብይነት ምንም ሲናገሩ አይሰማም። አዲስ ኪዳን ግን ብዙ ቦታ ላይ ከጸጋ ስጦታዎች አንዱ የነብይነት አገልግሎት እንደሆነ ጽፎ ይገኛል። ስለየትኛውና ስለምን ነብይነት አዲስ ኪዳን እየተናገረ እንደሆነ አንድም ሰው ትንፍሽ ሲል አይሰማም። ለምን?  የተጻፈውን መተንተን ወይም መካድ ወይም መናገር እየተገባ ዝምታ ለምን? ኢየሱስ ነብይ ነው ከሚል ጥቅል ሃሳብ ውጪ ስለጸጋ ስጦታው ምንነት ግን ምንም አለመባሉ ያሳዝናል። ሌሎች ደግሞ እኛ ለነብይነት የተላኩና የተመረጡ ሰዎች ያሉባቸው አብያተክርስቲያናት ነን ይላሉ። እንዴትና ለምን? ብለን እነዚህኞቹንም ብንጠይቅ አጥጋቢ መልስ ከሚሰጡን ይልቅ ለራሳቸው እንደሚመቻቸው አድርገው ይተነትናሉ። ስለአዲስ ኪዳኑ ነብይነት ጨርሶ የረሱና እንደራሳቸው ምርጫ የሚጠቀሙበት ክፍሎች ቢኖሩም ስለብሉይ ኪዳን ዘመን ነብይነት ግን ሁሉም ብዙ አይከራከሩም። አለመከራከራቸውም የሚገለጸው ሁሉንም የብሉይ ኪዳን ነብያት በጋራ ይቀበሏቸዋልና ነው። በሁሉም ዘንድ ማለት በሚቻልበት ደረጃ ሃሳቡና ትርጉሙ የጋራ ተቀባይነት አለው። ከሥነ መለኰት ምሁራንና ሚዛናዊ አስተምህሮ ካላቸው ሊቃውንት ያገኘነውን ትምህርትና መረጃ መሠረት አድርገን ስለነብይነትና የነቢያት እንዴትነት ጥቂት ለማለት እንፈልጋለን።
  ነቢይ ማለት ምን ማለት ነው?
የግሪኩ «ፕሮፌሚ» ቃል ሲሆን ትርጉሙም «አስቀድሞ መናገር» ማለት ነው። ይህም ትንቢቱ ከመፈጸሙ በፊት ትንቢቱ ለተነገረለት ሕዝብ የትንቢቱን ምንነትና የፍጻሜ ሂደት አስቀድሞ ማሳወቅ ወይም ማስተላለፍ ነው።


ብሉይ ኪዳን፣
 

ነብይነት ለምን አስፈለገ?
የነብይነት አገልግሎት የተፈለገው የመጀመሪያው ሰው አዳም ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት ከተቋረጠ በኋላ ነው። እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት የተቋረጠ ስለነበር እግዚአብሔር መልእክቱን «አስቀድሞ መናገር» ፕሮፌማ ሰው ስለፈለገ ለዚህ አገልግሎት ከሰው መካከል በመምረጥ ነው ነብይነት የተፈገለው።
መልእክቱ የሚተላለፍበት መንገድ፣
በራእይ፣ በህልም፤ በድምጽና በምልክት ሊሆን ይችላል።
«እርሱም፦ ቃሌን ስሙ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፥ እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ፥ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ» ዘኁ 12፤6
«እግዚአብሔር ሳሙኤልን ጠራው እርሱም፦ እነሆኝ አለ»1ኛ ሳሙ3፣4
«እርሱም፦ በአንተ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁ፥ የምትናገረኝም አንተ እንደ ሆንህ ምልክት አሳየኝ»መሳ 6፣17
ኢሳይያስ ራእይ አይቶ፣ ኤርምያስ ቃል ሰምቶ፣ሕዝቅኤልም ዳንኤልም ራእይ አይተው ነብይነታቸውን ፈጽመዋል። ሌሎቹም እንዲሁ!
እንግዲህ የብሉይ ኪዳን ነብያት ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ሸክም ወደሕዝቡ በማድረስና የሕዝቡንም ጩኸት ወደእግዚአብሔር በማድረስ የነብይነት አገልግሎታቸውን መካከለኛ ሆነው ፈጽመዋል።
አዲስ ኪዳን፣

እንግዲህ ነብይ ማለት ምን እንደሆነ፣ ነብያትም ምን እንደሚሰሩና መልእክት እንዴት ተቀብለው ያስተላልፉ እንደነበር ከላይ ካየነው አንጻር ስለአዲስ ኪዳን ዘመንም ጥቂት ልንል የተገባ ነው።
የአዲስ ኪዳን ነብይ ማነው? ነብይ ሆኖ የተመረጠው በማነው? የሚናገረው መልእክት ምንድነው? ብለን እንጠይቃለን። የአዲስ ኪዳን ነብይነት ችግር የሚከሰተው እዚህ ላይ ነው። በአዲስ ኪዳን ነብይ ስለመኖሩ የተጻፈ ቢኖርም አጠቃቀሙና አገልግሎቱ በሰፊው የተብራራ ስላልሆነ እኔ ነብይ ነኝ፣ በኛ ዘንድ ነብይነት አለ፣ የተመረጥኩት ለነብይነት አገልግሎት ነው ወዘተ የሚሉ ድምጾች ከዚህም ከዚያም ይሰማል። ለምሳሌ The later Day Saints ወይም «የኋለኛው ቀን ቅዱሳን» የእምነት ተቋማት የጆሴፍ ስሚዝን ነብይ መሆን ለዚያውም ብቸኛው ነብይ እንደሆነ ከተከታዮቹ ውጪ ለዚህ አገልግሎት የተመረጠ እንደሌለ ሲናገሩ እንሰማለን። በጽሁፎቻቸውም ይህንኑ ይናገራሉ።
ነብይ ማለት«ፕሮፌሚ» ወይም አስቀድሞ የሚናገር ከሆነ ስለምን አስቀድሞ ለመናገር? ለማን ለመናገር? የቀረ ነገር ምን ስለነበረ? ብለን ብንጠይቅ ምላሽ የላቸውም።
የኢየሱስ ክርስቶስን የነብይነት ቦታ ለመቀበል ራሳቸውን በመሾምና በስህተት ቦታ ለማስቀመጥ የመጡ ከመሆን አያልፉም።
 

*ኢየሱስ ራሱ ነብይ መሆኑን ተናግሯል። 
 «ነቢይ በገዛ አገሩ እንዳይከበር ኢየሱስ ራሱ መስክሮአልና» ዮሐ 4፣44
 

*የኢየሱስ ነብይነት፣ራሱ የእግዚአብሔር መልእክት ነበር።
«ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ»ዮሐ 16፣28 


*መልእክቱ የመጣው ለተወሰነ ሕዝብ ሳይሆን ለዓለም ሁሉ ነው
«የጌታን ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል»የሐዋ 2፣21
 

*መልእክቱ ማዳን ነው። 
«ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና» ሉቃ2፣11
 

ከዚህ ተነስተን ኢየሱስ የአዲስ ኪዳን ነብይ መባል የተገባው ከመሆኑም በላይ መካከለኛነቱ እንደኦሪቱ ነብያት በመናገር ላይ የተመሰረተ ሳይሆን ማዳንንም በመፈጸም ጥልን አፍርሶ በአባቱና በእኛ መካከል እርቅን የመሰረተ በመሆኑም ጭምር ነው።
 

*በቤቱ ላይ እንደሙሴ ታማኝ ሎሌ ሳይሆን የታመነ ልጅ ሆኖ ያገለገለው ኢየሱስ ነው።
በአዲስ ኪዳን ነብይ ሙሴስ በኋላ ስለሚነገረው ነገር ምስክር ሊሆን በቤቱ ሁሉ እንደ ሎሌ የታመነ ነበረ፥ ክርስቶስ ግን እንደ ልጅ በቤቱ ላይ የታመነ ነው» ዕብ 3፣5
  
በዚህ ዘመን ነቢይ ነኝ የሚል ካለ ነብይነቱ ለቤተክርስቲያን መታነጽ እንጂ  ለሌላ እንዳልሆነ ከጳውሎስ ቃል እንረዳለን።             1/ነቢይ የሆነ እሱ ነቢይ እንጂ አስተማሪ አይደለም።የተቀላቀለ አገልግሎት የለም። አገልግሎቱ የተለየ ስለመሆኑ ተቀምጧል።
«እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛም ነቢያትን፥ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፥ ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን፥ ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ፥ እርዳታንም፥ አገዛዝንም፥ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጎአል» 1ኛ ቆሮ 12፣28
«እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፤ ትንቢት ቢሆን እንደ እምነታችን መጠን ትንቢት እንናገር፣ አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ፤ የሚያስተምርም ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ» ሮሜ 12፣6
 

2/ የነብይነቱ መልእክት በሌሎች የተመረመረ መሆን አለበት።
ነቢያትም ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ ሌሎችም ደግሞ የተነገረውን በጥንቃቄ ይመርምሩ 1ኛ ቆሮ14፣29 

ተመርምሮ ትክክለኛ ስለመሆኑ ያልተረጋገጠ ትንቢት ከስህተት መንፈስ ሊሆን ይችላል።
 

3/ በልሳን መናገርና ትንቢት መናገር በተለያየ ሁኔታ ውስጥ መፈጸም ያለባቸው ስጦታዎች ናቸው። 1ኛ ቆሮ 14፣22-25
ባላመኑ ሰዎች መካከል በልሳን መናገር እብድ ያሰኛል እንጂ ያላመኑትን አያንጽም። ስለዚህ በልሳን መናገር ያመኑ ሰዎች ባለበት ብቻ መሆን አለበት፣ እንደዚያም ሆኖ የተነገረው መተርጎም አለበት። በልሳን የተነገረው በጉባዔ መካከል ካልተተረጎመ ምን ይጠቅማል?

«በልሳን የሚናገር ቢኖር ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት ሆነው በተራቸው ይናገሩ አንዱም ይተርጉም» 1ኛ ቆሮ 14፣27
 
እንደዚሁ ሁሉ ትንቢት መናገር ባላመኑ ሰዎች መካከል ከሆነ የልባቸውን ሃሳብ በመመርመርና በመግለጥ ስለሚገለጽ ያላመኑትን ሰዎች ያንጻል። ስለዚህ ትንቢት ባላመኑ ሰዎች መካከል ይፈጸም፣ ባመኑ ሰዎች መካከል ከሆነ ትንቢቱ ለጉባዔው ሊገለጥ ይገባል።
ስለዚህ ይህንን ያላሟላ ትንቢት፣ ትንቢት አይደለም።
 

4/ትንቢት እጅን በመጫን የሚሰጥ ጸጋ እንደሆነ ጳውሎስ ተናግሯል። 1ኛ ጢሞ 1፣14
 

5/ ትንቢት የሚናገር እንዳለ ሁሉ የትንቢቱን መንፈስ የሚለይ መኖር አለበት።
«ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል» 1ኛ ቆሮ 12፣10
 ትንቢቱና ትንቢቱን ያናገረ መንፈስ ከእግዚአብሔር እንደሆነ ካልተረጋገጠ በስተቀር ነቢያት ነን የሚሉ በበዙበት ዘመን ማመን አስቸጋሪ ነው።


6/ በኢየሱስ ስም ትንቢት የተናገሩ ሁሉ እውነተኞች ናቸው ማለት አይቻልም።
«በዚያ ቀን ብዙዎች። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል» ማቴ 7፣22
በአጠቃላይ ለቤተክርስቲያን የዚህ ዘመን ነቢይና ትንቢት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በእግዚአብሔር አብና በሰው ልጆች መካከል የነበረችውን ጥል አፍርሶ የመሰረተልንን የልጅነት ተስፋ የሚተካ ወይም የሚወክል አይደለም። በተመሠረተው  ላይ ሕንጻውን ለማሳደግ የሚጠቅም ስጦታ ነው እንጂ ሌላ ተልእኰ የለውም።  የነብይነት አገልግሎት በአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ውስጥ ስለመኖሩ ጳውሎስ የተናገረውን የማይቀበሉ እንዳሉ ሁሉ ስለመኖሩ አምነው አገልግሎቱን ግን እንደልባቸው መሻት የሚጠቀሙ በመኖራቸው ይህ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በአግባቡ እየተገለጸ አይደለም። ግድፈቶቹ ነቢይ በዚህ ዘመን የለም የሚሉና አለ ብለው በአጠቃቀሙ ላይ ግን በሚታዩ ግድፈቶች የተነሳ መንፈስ ቅዱስ ለቤተክርስቲያን ያለውን ጸጋ ሰዎች እንዳይረዱት አድርጓል። ነቢይ በዚህ ዘመን ሊኖር እንደሚችል  አለመቀበል በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተቀመጡትን እውነታዎች  እንዲካዱ የሚገፋፋ ክፉ መንፈስ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ላይ ሰፍኗል ማለት ይቻላል። መኖሩን ተቀብለው አሰራሩን የሚያጣምሙትም ቢሆኑ በነቢይነት ስጦታ መንፈስ ቅዱስ የፈቀደውን እንዳያደርግበት  እንቅፋት የሚያኖር መንፈስ አስቸጋሪ አድርጎታል እንላለን። እኛም ነቢይነት የለም የሚለውን መንፈስና አለ  ብሎ ግን የሚያጣምመውን መንፈስ ሁሉ መቀበልና ማመን የለብንም። ሕያው ማስረጃችን መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ሁሉንም በአገባብና በሥርዓት ጽፎልናልና።

 «ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና» ዮሐ 4፣1