ስለማኅበረ
ቅዱሳን ማንነት ገና ብዙ እንጽፋለን። የተገኙ መረጃዎችን ሁሉ እናስነብባለን። ምክንያቱም ማኅበረ ቅዱሳን ያልሆነውን ሆኖ በመታየት
የዋሃንን የሚያሳስት፤ የተሳሳቱትን ወደእውነት ማወቅ እንዳይደርሱ በሩን የሚዘጋ የእውነት ሁሉ እንቅፋት ስለሆነ ነው። ከዚህ ቀደም
እንደምንለው ሁሉ በቅንነትና ለቤተክርስቲያን በመቆርቆር እየተከተሉ ያሉትን የዋሃንን ሳንጨምር ነው።
ብልጣብልጦቹና
መሰሪዎቹ ሲነግዱም ሆነ የሰው እውቀት ሲዘርፉ ራሳቸውን የሚደብቁት፤ ለቤተክርስቲያን የሚቆረቆሩ አፍላ የወጣቶች ማኅበር ተደርገው
እንዲታሰቡ ማታለያን በመጠቀም ሲሆን በግብር ግን ከዚህ በታች እንደቀረበው ጽሁፍ የሌላውን እውቀትና ሀብት ያለምስክር በመዝረፍ
እንደራሳቸው ፈጠራ ገበያ ላይ አውጥቶ በመቸብቸብ ነው።
የሙት ወቃሽና ከሳሽ የሆነው ማኅበረ ቅዱሳን እነ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ፤
እነ ነጋድራስ ባይከዳኝ፤ እነ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ሥላሴ አጽማቸው እንዳያርፍ ስማቸውን በማኩሰስ ከሙት ዓለም እየጠራ መወንጀሉ
ሳያንስ፤ እነዚህ ሊቃውንት አባቶች ካካፈሉን የእውቀት ማእድ እየሰረቀና በስሙ መጽሐፍ እያሳተመ ሲሸጥ ሃፍረት ያልፈጠረበት ኅሊና
ቢስ ማኅበር መሆኑ ከምንም በላይ አረጋጋጭ ነው።
ማኅበሩ ከእነዚህ መናፍቃንና ተሐድሶ በማለት ከሚከሳቸው ምሁራን መጻሕፍት ውስጥ
ለምን መስረቅ ፈለገ? ቃል በቃል ከሰረቀስ በኋላ ለምን ያገኘበትን ምንጭ ያልጠቀሰ? ብለን ብንጠይቅ፤ ድሮውን ሲፈጠር ጀምሮ ማኅበሩ
እውቀት በዞረበት ያልዞረ፤ በብልጣብልጥ ዘመንኛ ጥበብ የሚሸቅጥ፤ ግብረ እኩይ ማንነቱን በሚያጣፋው ነጠላ የሚሰውር፤ ከዚህም ቡጭቅ፤
ከዚያም ቡጭቅ አድርጎ የሚኖር የዋህ መሳይ አውደልዳዮች የተሰባሰቡበት ማኅበር ስለሆነ ብቻ ነው። በአንድ ወቅት ከፕሮቴስታንቱ ከዶ/ር መለሰ ወጉ መጽሐፍ ላይ ገልብጦ አቶ ማኅበረ ቅዱሳን ስለጻፈው ጽሁፍ
«አባ ሰላማ ብሎግ» በመረጃ አጣቅሶ አስነብቦን ነበር። አሁን ደግሞ ሙት ከሳሹ አቶ ማኅበረ ቅዱሳን፤ ተሐድሶ ናቸው ይወገዙልኝ ካላቸው ከብላቴን
ጌታ ኅሩይ መጽሐፍ ውስጥ እውቀት በመስረቅ ምንጩን ሳይጠቅስ ቃል በቃል በመገልበጥና ፊደላትን በማስተካከል ብቻ አሳትሞ የነገደበትን
መጽሐፍ በመንቀስ «ዓውደ ምሕረት» ብሎግ እነሆ ማኅበረ ቅዱሳን ማለት ይህ ነው ተዋወቁት ይለናል። በግብሩ የምትደግፉትም እፈሩ! ያፈራችሁበትም ተሸማቀቁ!
ግብሩን አይታችሁ የተለያችሁትም ጥሩ ውሳኔ አድርጋችኋል። ንስሐ ማለት ከክፉ መሸሽ ነውና።
መልካም ንባብ!!
ማኅበረ
ቅዱሳን ከሚታወቅበት የክፋት ሥራዎቹ መካከል አንዱ የሰውን ጽሑፍ በመስረቅ እና የራሱ ሀሳብና እቅድ አድርጐ በሚያሳትማቸው መጽሔቶቹ፣ ጋዜጦቹ መጽሐፍቶቹ ላይ በማውጣት ነው፡፡ አንባቢ ከኔ ወዲህ ላሳር ብሎ የሚያምነው ይህ ማኅበር አይታወቅብኝም ብሎ የሰው ሥራ እየመነተፈ ከሳተማቸው መጽሐፍት መሀል ለዛሬ አንዱን እናያለን።
ይህ
ሊቅ የማያስወድድ ባህሪው እያንደረደረ እና እያንቀዠቀዠ ወስዶ ይወገዙልኝ ካላቸው በርካታ ግለሠቦች መካከል የሀገራችንን የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ እድገት እዚህ ደረጃ ያደረሡ፣ 42 የሚደርሡ መጽሐፍቶችን የዳሰሱ ይልቁንም እንደነ ጎህ-ጽባሕ እና አዲስ ዓለም የተሠኙ መጻሕፍቶችን የደረሱ እና ባለ ትልቅ ራዕዩና ከዘመናቸው ቀድመው የተፈጠሩት ታላቅ ሰው ይጠቀሳሉ። እኚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊና ኦርቶዶክሳዊ (በማ.ቅ. አጠራር ፕሮቴስታንታዊ ተሀድሶ ተብለው የተፈረጁ) ክቡር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ይባላሉ፡፡ እኚህ ታላቅ አባት ከነ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ከነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ከነ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም እና ከነ ፕሮፌስር ጌታቸው ኃይሌ ጋር ፕሮቴስታንታዊ ተሀድሶ ተብለው የተፈረጁ ሲሆን ማኅበሩ ይህን ስም የሰጣቸው
ስራዎቻቸውን ሁሉ ካስወገዘ በኋላ በስሙ ለማሳተም ፈልጎ ነው ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል።
ማኅበሩ
በ1988 ዓ.ም ከእርሳቸው ገልብጦ ባሣተመው “ቤተ ክርስቲያንህን እወቅ” የሚለው መጽሐፍ በተለይ የቅ/ጳውሎስንና የቅ/ጴጥሮስን ታሪክ ከእነሙሉ ሥራቸው ብላቴን ጌታ ኅሩይ“ነቅዕ ንጹህ- ዜና ሐዋርያት” ብለው በ1923 ዓ.ም ካሣተሙት ወስዶ ተጠቀሞበታል። ለማሳያ ያህል የሚከተሉትን ታሪኮች እናቀርብላችኋለን፡-
1. ዜና ሐዋርያት ገፅ 324 (1923)
Ø ቅዱስ
ጴጥሮስ ፊቱ ሰፊ ሆኖ ሪዛም ነበር፣ ቁመቱም ካጭር የረዘመ ከረዥም ያጠረ መካከለኛ ነበር፡፡
v ቤተ ክርስቲያንህን እወቅ ገፅ 65 (1988)
Ø ቅዱስ ጴጥሮስ ፊቱ ሰፉ ያለ ሲሆን ረዥምና መካከለኛ ቁመት የነበረው ራሰ በራ ሰው ነው፡፡
2. ጥሩ ምንጭ ገፅ 330
Ø ቅዱስ
ጳውሎስ መልኩና ሠውነቱ የምሥራቅ ሊቃውንት ቃል ለቃል ተያይዞ እንደመጣላቸው ከጻፉት መጻሕፍት ያገኘነውን ከዚህ ቀጥለን እንጽፋለን፡- ጭንቅላቱ ትልቅ ሆኖ ራሡ በራ ነበር፡፡ የሁለቱም ሽፋሉ ጠጉር የተጋጠመ ያውም የረዛዘመ ነበር፡፡ ዓይኖዋ ሰማያዊ ቀለም የመሠሉ ብሩሀን ነበሩ፡፡ አፍንጫውም ትልቅና ቀጥ ብሎ የወረደ ጉንጭና ጉንጩ የሮማን ፍሬ የመሠሉ ነበር፡፡ ጽሕሙና ሪዙም ረጃጅም ነበር፡፡ ጽሕም ማለት ከአገጭ ላይ በቅሎ ወደ ታች የሚወርደው ነው፡፡ ሪዝ ማለት ግን ከላይ ከራስ ጠጉር ተያይዞ የበቀለና ወደ ታች በጉንጭ ላይ ወርዶ ከጽሕም ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ አንገቱ አጠር ያለው ሆኖ ትከሻው ክብና ጎባጣ ነበር፡፡ እግሮቹ ከጉልበቱ ላይ የተቃረቡ ሆነው ከቅልጥሙ በታች የተራራቁ ነበሩ (ወርኃ ነበር ማለት ነው)፡፡ ቁመቱ ግን ከረዥም አጠር ያለ ከድንክ ረዘም ያለ ለአኃውን አሳቻ ነበር፡፡