የጽሁፉ ምንጭ፤ቤተ ጳውሎስ/.www.betepawlos.com/
/ ከደጀ ብርሃን፦ ቅዱሱን መጽሐፍ መሠረት አድርጎ ከወዲያም ይሁን ከወዲህ ያሉትንና ራሳቸውን የጽድቅ ሰራተኞች አድርገው የሚቆጥሩ ነገር ግን በዚያ ሥፍራ ተቀምጠው ያልተገኙትን ሁሉ የተመለከተበትን ይህንን ድንቅ ጽሑፍ እንድታነቡት አቅርበናል። /
/ ከደጀ ብርሃን፦ ቅዱሱን መጽሐፍ መሠረት አድርጎ ከወዲያም ይሁን ከወዲህ ያሉትንና ራሳቸውን የጽድቅ ሰራተኞች አድርገው የሚቆጥሩ ነገር ግን በዚያ ሥፍራ ተቀምጠው ያልተገኙትን ሁሉ የተመለከተበትን ይህንን ድንቅ ጽሑፍ እንድታነቡት አቅርበናል። /
ገና ሻዩን አዝዤ ወደ አፌ ላስጠጋው ስል ከወዲያ ማዶ ለመቆም የምትጣጣረውን መኪና እያየሁ ዓይኔ ተተክሎ ቀረ፡፡ መኪናዋን
አላወቅኋትም፡፡ ዓይኔ ግን በእርሷ ላይ ቀረ፡፡ የሾፌሩ በር ተከፍቶ የወጣው ሰው ግን የማውቀው ወንድም ነበረ፡፡ ወዲያው ግን ማወቄ
ወደ አለማወቅ ተለወጠ፡፡ እንኳን የእርሱን ህልውና የራሴን ህልውና ያጣሁት መሰለኝ፡፡ እውኑ ሕልም መሰለኝ፡፡ የጨበጥኩት የጉም
ስፍር ሆነብኝ፡፡ ሻዩን ሳልቀምሰው አፌ እሬት ሆነብኝ፡፡ አጠገቤ ያሉትን ሰዎች ሁሉ ሕልውናቸውን መቀበል ከበደኝ፡፡ ዓለም ለቅጽበት
ውሸት፣ የአሳብ ቤት ሆነችብኝ፡፡ ዓይኔ እዚያች መኪና ላይ የተተከለው የቀጠርኩት ሰው መጣ ብሎ አይደለም፡፡ ራሴን ቀጥሬ ራሴን
እየጋበዝኩ ነበር፡፡ ያም ሰው እንደሚያገኘኝ ፍጹም አላሰበም፤ ነገር ግን ቀጠሮው ሞላ፡፡ እንደዚህ ባንገናኝ እመርጥ ነበር፡፡ በዓለም
ግን የሆነው እንጂ የመረጡት አይታይም፡፡ ወዳጅ የሆነ ሰው ሊያየውም ላያየውም የሚገባ ሁኔታ ነበር፡፡ ማየቱ ለማጽናናት፣ አለማየቱ
ላለመሰበር ነው። የመጣው ትንሽ ኬክ ቢጤ ገዝቶ ሊበላ ነው፡፡
ወደ እኔ መጓዝ ጀመረ፣ ይበልጥ ልቤ ፈራ፡፡ ያላየኝን ሰው ቀድሜ ዓይቼ የአሳብ ፍልሚያ ውስጥ ገባሁ፡፡ ያየ ታጋይ ነው፣
ያላየ ምን አለበት! ይህ ወንድሜ ቁመናው ያማረ፣ አንገቱ የንጉሥ ሕለተ ወርቅ የመሰለ፣ መልኩ የብር እንኮይ፣ አለባበሱ የጥቅምት
አበባ፣ ቆፍጣናነቱ የድሮ ወታደር፣ አነጋገሩ በሥልጣን የተሞላ፣ ለሚረግጠው የሚጠነቀቅ፣ ለሚለብሰው የሚጨነቅ፣ በአጠገብ ሲያፍ ሽቶው
የሚያውድ ነበር፡፡ መኪናውን የያዘ እንደሆነ እንደ መኪና ሳይሆን ያለ አቅሟ እንደ ጀት ሁኚ እያለ ያስጨንቃታል። እንደ ንጉሥ ሞተረኛ
ለራሱ ድምጽ እያሰማ በመኪናው ጥሩምባ አድባሩን እያወከ ይነጉዳል። ብዙም አልናገረውም ነበር፡፡ ምክንያቱም ወደ መሬት ገና አልወረደም
ነበርና ስለማንደማመጥ ነው፡፡ ከመፈለጉ የተነሣ ኩሩ፣ ከመወደዱ የተነሣ ውድ ነበር፡፡ ወደ እግዚአብሔር እንዲቀርብ ብዙ ዘመን ነገርኩት፡፡
እኔን ላለማስቀየም ብቻ በትዕግሥት ይሰማኛል፡፡ ነገር ግን እሺታው የውሃ ሽታ ሆኖ ይቀራል፡፡ የአሁኗ ዓለም እንደ እርሱ ያታላለችው
ሰው አልነበረም፡፡ እኔም ሰው ነኝና ደክሞኝ ተውኩት። ዛሬ ያየሁት ከብዙ ወራቶች በኋላ ነው፡፡ ያቺ የቡልጋ አልቃሽ ያለችው በጆሮዬ
አቃጨለ፡-
‹‹ምን ቆንጆ ቢሆኑ
ቢረዝሙ እንዳክርማ
መጠቅለል አይቀርም በነጠላ ሸማ››