Monday, May 6, 2013

ፓትርያርኩ የህዳሴው ግድብ ያለጥርጥር እንደሚሳካ ተናገሩ


(Reporter) መጋቢት 24 ቀን 2003 .. የተጀመረውና በአሁኑ ጊዜ ስምንት ከመቶ ማደጉ የተነገረለት የህዳሴውን ግድብ ጨምሮ፣ ሁሉም የተጀመሩ ትላልቅ ሥራዎችን ያለምንም ጥርጥር ማሳካት እንደሚቻል፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አስታወቁ፡፡
ፓትርያርኩ የተናገሩት ሚያዝያ 27 ቀን 2005 .. የሚከበረውን የፋሲካ በዓል አስመልክተው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ባስተላለፉት የቡራኬ ቃል ላይ ነው፡፡

‹‹የእውነትና የሕይወት መንገድ አድሶልናልና የሚለውን የፋሲካ ትምህርተ ሃይማኖት፣ የህዳሴውን ልማት በማፋጠንና በማሳካት ልንገልጸው ይገባል፤›› ያሉት ፓርትያርኩ፣ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ እንደሚታየው፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃያ አራት ሰዓታት በትጋት ከሠራ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሌሎች የበለፀጉ አገሮች ከደረሰቡት የዕድገት ደረጃ የማይደረስበት ምክንያት እንደሌለ ገልጸዋል፡፡
ከክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ በሚመነጨው መርህ መሠረት በሥራ መትጋትና በፍፁም ፍቅር መኖር፣ ሕይወትን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባና ከሁሉም በፊት ሰው የተፈጠረው ለሥራና ለክብር መሆኑን መዘንጋት እንደማይገባ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ወደ መጣህበት መሬት እስከምትመለስ ድረስ ጥረህ፣ ግረህና ላብህን አንጠፍጥፈህ ብላ፤›› የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በማስታወስ፣ ሰው ለአንዲት ደቂቃ እንኳ እጅ እግሩን አጣጥፎ ያለሥራ እንዲቀመጥ እግዚአብሔርም እንደማይፈቅድ ተናግረዋል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በኅብረት፣ በአንድነት፣ በስምምነት፣ በመተማመንና በመቻቻል ለሥራና ለሥራ ብቻ መነሳት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ፣ ለሰው ልጆች ብሎ በሰው ልጆች ፈንታ መስዋዕት በመሆን የዘለዓለም ሕይወትን ካጐናፀፈው ጌታ ጋር ማክበር እንዳለባቸው፣ የተራቡትን በመመገብ፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የታመሙትንና የታሰሩትን በመጠየቅ፣ እንግዶችን በመቀበልና በማስተናገድ መሆን እንዳለበት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አሳስበዋል፡፡