(ከዙፋን ዮሐንስ)
የሆነ ጊዜ ፷፬ ሰው በሚይዝ አገር አቋራጭ አውቶቡስ ተሣፍረን ወደክልል የሁለት ቀን መንገድ ተጓዝን። ቁርስ፣ ምሳ፣ አብሮ ከመብላት፣ አብሮ ከመቀመጥ፣ የተነሳ ሁሉ ዘመድ ቤተሰብ ሆነ። የሆድ የሆዱን ተጫወተ። ስልክ ተቀያየረ፣ እጮኛም ያገኘ አይጠፋም። ያልተነሳ ርእስ አልነበረም። ፖለቲካ፣ የኑሮ ውድነት፣ ስለሳይንስ፣ ሃይማኖት፣ ስለታዋቂ ደራሲያን፣ ዘፋኝ፣ ፈላስፋ፣ ስለሃይማኖት አባት፣ ብዙ ብዙ….ብቻ ያልተወራ አልነበረም። አንዳንዶቹም ወሲብ ቀስቃሽ ቀልዶችን ግጥሞችን አውርተው መኪናው ውስጥ ከጫፍ እስከጫፍ አነቃቅተዋል። የወሲብ ነገር ሲወራ ጆሮውን ቀስሮ ያዳምጣል። የሚያስቅ ከሆነ ይስቃል፣ የሚያሳፍር ከሆነም መስማት ያልፈለገ ይመስል የኮረኮሩት ያህል ግንባሩ ጥርስ በጥርስ ይሆናል። የአለቃ ገ/ሐና ነገር ሲነሳማ የአለቃን ወሲብ ወዳጅነትና ይጠቀሙ የነበረበትን የማማለል ዘዴ እያደነቀ ከልምዳቸው ብዙ የቀሰመው ነገር ያለ ይመስል ተሳፋሪው ይስቃል፣ ያውካካል።
ይህ ሁሉ ሲሆን አንድ ሰው ከዚህ ሁሉ ሳቅና ፍንደቃ ራሱን አግልሎ ከመስኮት ጥግ ተቀምጦ ያነብ ነበር። ድንገት ብድግ ብሎ “ኢየሱስ“ የሚለውን ስም አንስቶ ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሰ አዳኝነቱን፣ ተስፋነቱን፣ አጽናኝነቱን መናገር ሲጀምር ብዙ ፊቶች ተቀያየሩ። አንዳንድ ፊቶች ቲማቲም መስለው ቀሉ። የባሰባቸው አንዳንዶች ደግሞ እንደበርበሬ ቀልተው የቁጣ ብናኛቸው በሰውየው ላይ በተኑ። ስለዝሙት ቀልድ ቦታ ሳይመርጡ ሲያውካኩ የነበረውን ረስተው ስለኢየሱስ ለመስማት ቦታ አጡና “ሰብከት ቦታ አለው“ አሉና ደነፉ። ጫወታችንን አታበላሽ አሉና አጉረመረሙ። ስለፌዝ፣ እርባና ስለሌለው ቀልድና ስለዝሙት ማውራት እንደጥሩ ጫወታ ተቆጥሮ ስለኢየሱስ መስማት ግን ጫወታን እንደማበላሸት ሆኖ ተቆጠረ።
እርግጥ ነው። የሥጋን ነገር መከተል ከእግዚአብሔር የመለየት ጉዳይ ስለሆነ ማበሳጨቱ የሚጠበቅ ነበር።
ሮሜ 8፣7
“ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል” እንዳለው ሐዋርያው።
በየትኛውም መመዘኛ “ኢየሱስ” የሚለው ሃይለኛ ስም ሲጠራ ለመቀበል ወይም ላለመቀበል የሰዎች አስተሳሰብ ከሁለት ነገር ውጭ አይሆንም።
አንድም የኢየሱስን ጌትነትና አዳኝነት የሕይወቷ ቤዛ ላደረገችው ነፍስ ሃሴትን ያመጣልና በስሙ መጠራት ይኽች ነፍስ አታፍርም፣ አትቆጣም።
ሁለትም የኢየሱስ አዳኝነት፣ ጌትነትና አምላክነት ብቸኛ ቤዛዋ ያላደረገችውን ነፍስ ያበሰጫታል፣ ያናድዳታል።
ምክንያቱም ፪ቆሮ ፪፣፲፮ “ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ፣ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን“ እንደሚል ይኽ ስም ለዘላለማዊ ሕይወት ለተመረጡት የፕሮቴስታንት ይሁኑ የኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ አማኞች ሕይወት፣ ሕይወት የሚሸት ሰላምና እረፍት የሚያመጣ ሲሆን ለጥፋት ለተመረጡት ግን የሚያስቆጣ፣ የሚያነጫንጭ ጥርስ የሚያፋጭ ይሆናል። ዘፈንና ቀልዱ፣ ቧልትና ፌዙ ሲነገር ሁሉ ያለምንም ልዩነት አንድ ሆነው ሲስቁና ሲፈነድቁ እንዳልነበር “ኢየሱስ” የሚለው ስም ሲጠራ የሚያበሳጭበት ምክንያት ለምንድነው? እነዚህ ጴንጤዎች ቦታ የላቸውም እንዴ ማሰኘቱስ ለምን ይሆን? የራሱ የሆነውን ኢየሱስ ያዘጋጀ ሃይማኖት የለም።
ቢያንስ አዳምጦ ከወንጌል ቃል ውጪ የሆነውንና ያልሆነውን መለየት ሲቻል መቃወም ተገቢ አይደለም። ደደግሞም ፌዝና ሥጋዊ ነገርን ከማውራት ስለኢየሱስ መስማት በብዙ መልኩ ይሻላል። ለሁሉ ስለሞተው ስለኢየሱስ መናገር የተወሰኑ ሰዎች ስጦታ ሆኖ ሲያስወቅስ፣ ስለዝሙት መናገር ግን ለሁሉ የተፈቀደ መልካም ተግባር ሆኖ የሚቆጠርበት ምክንያት መኖር አልነበረበትም። ነገር ግን ይኽ ስም ሲጠራ ያስፈራቸውና ሐዋርያቱን፣ “ጀመሩ ደግሞ እነዚህ የተረገሙ!” ያስብል እንደነበር ወንጌል ያስታውሰናል።
1. ስሙን ሲጠራ ለተቀበሉ የሕይወት ሽታ የሆነላቸው። ሐዋ ፰
ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ፊልጶስ ስለኢየሱስ ሲሰብክለት ልቡ ደስ ተሰኘ። አጥምቀኝ አለው እንጂ “የእናትና አባት ሃይማኖቴን ተከትዬ ከኢትዮጵያ ኢየሩሳሌም ድረስ ያስመጣኝና ተራራ የወጣሁበትን ታላቅ የበረከት ጉዞ አድርጌ ከመመለስ ባለፈ ያንተን ኢየሱስ ለመስማት አልመጣሁም“…ብሎ አልተቆጣም።
በሉቃ ፳፯-፳ ላይም የኤማሁስ መንገደኞች ስለኢየሱስ በመጽሐፍ የተጻፈውን ሲሰሙ ልባቸው ይቃጠልባቸው ነበር። በዚያ በነበርንበት አውቶቡስ ላይ ግን ለብዙዎች ልባቸው የተቃጠለው ለምን ይኄንን ስም ትጠራላችሁ? ብለው በመናደድ ነበር።
ሐዋ ፲-፳፬ ላይ መቶአለቃ ቆርኔሌዎስም ጭራሽ ዘመዶቹንና ወዳጆቹን ጠርቶ ስለኢየሱስ ስበኩኝ ብሎአል። ስለኢየሱስ መስማት ደስ የሚያሰኝ ሆኖ ሳለ ጆሮ የሚያሳክክበት ምክንያት አይኖርም። ቢያንስ ስለአለቃ ገ/ሐና የዝሙት ጥበብና ሴቶችን እንዴት እንደሚያጠምዱ ከመስማት ይልቅ አምነው ባይቀበሉት እንኳን ስለኢየሱስ የሚነገረውን የወንጌል ቃል ማዳመጥ ለዝሙት ልብን ከማነሳሳት ከንቱ ወሬ ሳይሻል አይቀርም።
በበዓለ ሃምሳ የተሰበሰቡት አይሁድ ስለኢየሱስ ሲወራ ልባቸው ተነክቶ ሐዋርያትን “ምን እናድርግ ?? “ብለው እርዳታ ጠየቁ እንጂ “በየመንገዱ በየአደባባዩ በየባሱ እየሰበካችሁ፣ አታስቸገሩ “ብለው በተቆርቋሪነት ሰበብ የአጋንንትን ቁጣ አልተቆጡም። እነዚህ ስሙን የሰሙና ያልተቃወሙ ሁሉ መጨረሻቸው ያመረ ክርስቲያኖች ሆነው በሰማይ የዘላለም ሕይወትን በምድርም በረከትን አግኝተው ወደጌታ ሄደዋል።
2. የሞት ሽታ የሆነባቸውና ስሙ ሲጠራ የሚያበሳጫቸው የሚያስቆጣቸው ሰዎች እንዲህ የሚሆኑት እነሱ ሳይሆኑ በውስጣቸው የተቀመጠው ክፉ የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ነው። ይኽ ስም ሰዎችን ከሥጋዊና መንፈሳዊ ደዌ ስለሚፈታ ሰይጣን ይጠላዋል። መድኃኒትን ለመቀበል ዝግጁ ያልሆነ ሰውነት መድኃኒት ለሞት እንደሚሆንበት ሁሉ ኢየሱስ የሚለውም ስም ለሞት ይኾንባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከመለወጡ በፊት የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብን አምላክ እንደሚያመልክ ስለሚያምን “ኢየሱስ” የሚባለው ስም ያበሳጨው ነበር። ይኽንን ስም የሚጠሩትን ያስርና ያስገድል ነበር። ሐዋ ፬:፲፰ “በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዙአቸው” “ በማለት ፈሪሳዊያን ስሙ የሞት ሽታ እንደሆነባቸው ያሳያል። “ገረፉአቸው፥ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው።“ በማለት ስሙ እንዳስገረፈ አንብበናል።
ወንድሞቼና እህቶቼ ዛሬም ይህንን ስም መጥራት ያስደነግጣል/ያስፈራል/ኤሌክትሪክ ያስጨብጣል። በስካር መንፈስ ናውዞ ውሃ መውረጃ ቱቦ ስር የሚያድረው ብረቱ፣ አንበሳው ሲባል ዘማዊውና አለሌው ቀምጫዩ እየተባለ ሲሞካሽ፣ ሌባው ቢዝነሳሙ፣ እሳቱ ሲሉት የኢየሱስ ስብከት ሲነሳ ግን ሃይማኖተኛ ሆኖ ሲያፈጥ ማየት በጣም ያሳዝናል። ጫትና ሲጋራ፣ ሀሺሽና ሺሻ የሚያናውዘው ሱሰኛው ሰው ለጥምቀትና ትንሣኤ በአጭር ታጥቆ መንገድ ከሚጠርግ፣ ቄጠማ ከሚጎዘጉዝ፣ ምንጣፍ ከሚያነጥፍ ውስጡ ተጎዝጎዞ ከተቀመጠው ክፉ መንፈስ ኢየሱስን ንጉሡ አድርጎ ቢያኖር ኖሮ ከዐመጻ ተግባራቱ ነጻ በወጣ ነበር። የሕይወቴ መሪ ነው ያለ ሰው ንሰሃ ገብቶ ኢየሱስ ሰው አደረገኝ ይላል እንጂ “ኢየሱስ” ብሎ የሚሰብክን ሰው “መግደል ነበር“ አይልም። እህቴና ወንድሜ ዛሬ ኢየሱስ አንተና አንች ጋር የሞት ሽታ ወይስ የሕይወት ሽታ ነው? ሁላችን ራሳችንን እንመርምር።
ክብርና ምስጋና ነፍስ ሥጋና መንፈስን ነጻ ለሚያወጣው ሰው ለሚያደርገው ትልቅ ስም፣ ለኢየሱስ ክብር ይሁን! አሜን