እሳትና ውሃ አጥፊና ጠፊ ቢሆኑም አስፈላጊዎች ናቸው!

(ከኪሩቤል ሮሪሳ ጽሑፍ ተሻሽሎ የተወሰደ)
ነገሥታቶች በሪፐብሊካዊ መንገድ ሥልጣንን በእጃቸው ካስገቡ መሪዎች የበለጠ ቅቡል ነበሩ። የሥልጣን መሠረታቸው መለኮታዊ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ሕዝብ በፈቃዱ ይገዛላቸው ነበር። እነርሱም ሕዝባቸውን ይወዳሉ... ሕዝብም ይወዳቸዋል። በንጉሣዊ አገዛዝ ንጉሡ አባወራ.., ንግሥቲቱ እማወራ... ሕዝብ ደግሞ ልጆች ናቸው። አዋጅ ሲነገር "የምንወድህና የምትወደን ህዝብ ሆይ" ብለው ንግግር ይጀምራሉ። ይኼ ጭምብል ያለው ማታለያ አይደለም። እውነት ነው። በእነዚህ አካላት መካከል እውነተኛ ፍቅር ነበር። ምክንያቱም በታዛዥ ልጅና አባት መካከል ፀብ አይኖርም። ፀቡ የሚጀምረው ልጅ እምቢ ሲል ነው።
ሕዝብ ሁሉንም ነገር እሺ ብሎ በሚቀበልባቸውና ንጉሣዊ አስተዳደር ባለባቸው አገሮች የተሻለ ሰላም አለ። ሕዝብ ጠግቦ ሊበላ ይችላል። ባይበላም ከላይ ከሰማይ የተሰጠን የ40 ቀን እድል ነው ስለሚባልና የመብት ጥያቄዎች ስለማይኖሩ የአገርም አንድነት አይናጋም። እዚህም እዚያም የቦምብ ፍንዳታና ግድያ አይኖርም። የትልቅ አገር (በተለየ አተያይ) ባለቤት የመሆን እድልም ሰፊ ነው። በኛም አገር ከነበሩት የንጉሣዊ አስተዳደር ጥቅሞች መካከል ከላይ የተጠቀሱት ይገኙበታል። ስለዚህ እነኚህን የንጉሣዊ አስተዳደር ጥቅሞችን የቀመሰም ሆነ የሰማ ሰው... ዛሬ ላይ የድሮ ሥርዓት ናፋቂ ነኝ ቢል ላይገርም ይችላል።
ሥልጣንን የመጋራትም ሆነ ሌሎች የዴሞክራሲ ጥያቄዎች መነሳት የሚጀምርባቸው አገሮች ላይ ሰላም አይኖርም። ስደትና እንግልቶች ይኖራሉ። የረጋና ጸጥታ የሰፈነበትን ንጉሣዊ አስተዳደር ወደ ሌላ ሥርዓት የሚቀይረው እምቢታ ነው።
እምቢታ የለውጥ መጀመሪያ ነው። የዓለምን ቅርጽ የቀየረው እምቢታ ነው። የእምቢታ መሠረቱ ደግሞ እውቀት ነው። የንጉሣዊ አስተዳደሮች አገዛዝ ማዕበል አልባ ሐይቅ ነው። የማይንቀሳቀስ ውሃ ከሩቅ ሲታይ ፀጥታው ቢያስጎመዥም ውስጡ ላሉ አሣዎች ግን መራር ነው። ማዕበል ሲቆም አሣዎች መሞት ይጀምራሉ። እንቅስቃሴ አልባ የሆነ ነገር መልካም ቢመስልም ቆይቶ ግን ይገማል... ይሞታልም። ስለዚህ ንጉሣዊ አስተዳደሮች ለለውጥ የማይጋብዙ ስለነበሩ በኃይል መቀየራቸው ግድ ነበር። ሕዝብ በፀጥታው ውስጥ ተኝቶ ነበር። ሕይወት በድግግሞሽ የተሞላች አሰልቺ ነበረች።
በንጉሣዊ የአስተዳደር ሕግ ገዢው ግለሰብ እንጂ ሃሳብ አይደለም። ንጉሣዊ ባልሆነው ዓለም ደግሞ ገዢ የሚሆነው ሃሳብ ነው። የግለሰብ መኖር አስፈላጊ ላይሆንም ይችላል። ፓርቲዎች ሃሳቦችን ሲያመነጩ ሕዝቦች ደግሞ "ገዢ" ለሆነው ሃሳብ ድምፅ ይሰጣሉ። በዚህ የሥርዓት ሂደት... ሕይወት በምርጫ ውሳኔ ውስጥ ትወድቃለች። ለመምረጥ ሁለቱም መኖር አለባቸው። ሁለቱ ነገሮች ተነፃፃሪ እንጂ ተጻራሪ አይደሉም። መጻረር የሚባል ነገር የለም። ሁለቱም ትክክል ናቸው። የተሳሳተ የሚባል ነገርም የለም። አንዱ ከሌለ ምርጫ የሚባል ነገር ይጠፋል። አንዱ ፓርቲ ወንበር ይዞ ይቀርባል። አንዱ ደግሞ ሶፋ። ሕዝብ የፈለገውን መርጦ ያስቀመጥበታል። በዚህ መሃል ፓርቲዎች "ሶፋ ለእንቅልፍ ይጋብዛል" ወይም "ደረቅ ወንበር ለኪንታሮት ሕመም ይዳርጋል" ተባብለው ልዩነቱን ማጦዝ ይችላሉ። ነገር ግን ወንበር፣ ወንበር መሆኑ ሶፋም፣ ሶፋ መሆኑ እሙን ነው። ሁለቱም ይጠቅማሉ። ይህ ዓይነት የፖለቲካ ሥርዓት ፈጠራን አበረታቶ ለለውጥ ይጋብዛል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ባለ የፖለቲካ አረዳድ ሶፋ ካለ ወንበር አያስፈልግም። ወንበርና ሶፋ ተጻራሪ እንጂ ተነጻጻሪ አይደሉም። ሁለቱም ጎራዎች ውስጥ በውስጣቸው የተቀበረ ንጉሳዊ መለዮ አለ። እኔ ብቻ ነኝ፣ የሥልጣን ምንጭ የሚል። ልዩነትን እንደጠላት የማየትና የእኔ ብቻ ትክክል የማለት አባዜ አገራችንን ጠፍንጎ ይዟታል። ከንጉሣዊ አስተዳደር ተላቀን ከለውጡ ልናገኝ የነበረውን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እነዚህ ሁለት ጎራዎች መና አስቀርተውታል። የለውጡ ችቦ ከተለኮሰ ከ40 በላይ ዓመታት ቢቆጠሩም ዛሬም ፖለቲካችን አዙሪት ውስጥ ነው። የአዙሪቱ ምክንያት አንድ ነው። የመቀያየር ሳይሆን የመጠፋፋት አባዜ። ገዢው የተቃዋሚው.... ተቃዋሚው ደግሞ የገዢው ጠላቶች ናቸው። አንዱ በአንዱ መቃብር ላይ መንገሥ ይፈልጋል።
ይህ በሽታ ወደ አዲሱ ትውልድም እየተዛመተ ነው። ወጣቱ ልዩነትን ባየ ቁጥር፣ ስም መለጠፍ ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል። ፍላጎቱ አይታወቅም።
የንጉሣዊ አስተዳደርን ባሕርያት በጥልቀት በማጥናት ለውጡ አስፈላጊ እንደነበረ መረዳትና ወደኋላ ተመልሰን እሱን የምንናፍቅበት መሠረት እንደሌለ ማመን ላይ ገና ብዙ ክፍተት አለ። በዚህ ዘመን ወደኋላ ተመልሶ ንጉሥ መናፈቅ ምን ይባላል?
መነሻው ባለው ላይ በትንሽ ነገር ተስፋ መቁረጥ... እልህና አጉል ጀብደኝነት ነው። የታሰረ ሁላ ጀግና.... ተቃዋሚ ሁላ ሽብርተኛ በማለት ፈርጆ ለመጠፋፋት ምሏል። ለዚህ ሁላ ምስቅልቅል የፖለቲካ ባህል ተጠያቂው ስንፍናና ድንቁርና ነው። በየጊዜው ዓላማችን ሥርዓት ለመቀየር እንጂ እኛ ለመቀየር ፍላጎት የለንም። ያልተቀየረ አስተሳሰብ ደግሞ የተቀየረ ሕብረተሰብ ሊፈጥር አይችልም። መለወጥ ያለበት አተያያችን ነው። እሳትና ውሃን አለቦታው ለመጠቀም መፈለግ የፈጣሪ ስህተት ሳይሆን የኛ ጉድለት ነው።
ውሃን እሳት ውስጥ ብንጨምር ወይም እሳትን ውሃ ውስጥ ብናስገባ ለመጠፋፋታቸው ስህተቱ የማነው? የበረደው ሰው እሳትን በብብቱ ይይዝ ዘንድ አይጠበቅም።
ነገር ግን ውሃንና እሳትን መጥነን በመደጋገፍ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እንችላለን። ይህ የአስተሳብ ብስለት ነው። ፖለቲካችንን ግን ለምንኖርባት ቤታችን እንደሚመጥን አድርገን አስማምተን መጠቀም አልቻልንም። አጥፊና ጠፊ መሆኑ እስካላከተመ ድረስ አዙሪቱ ደግሞ አይለቀንም። ስለዚህ መለወጥ ያለበት ወንበሩ ሳይሆን ወንበሩን የሚፈልጉ ጭንቅላቶች ናቸው።
መጽሐፍ ቅዱሳችን እንደሚነግረን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ከቀረቡ ክሶች መካከል አንዱ "ንጉሥ ነኝ ይላል" የሚል ነበር። ይኽ ንግግር ደግሞ በወቅቱ በሕዝቡ ላይ ተሹሞ ለነበረው ሰው ትልቅ ራስ ምታት ነው። ምክንያቱም ሥልጣን የሚቀናቀን ሰው ቶሎ መጥፋት አለበት። ከሳሾቹም ይኽንን ያውቃሉ። በአደባባይም የተጠየቀው "አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህን?" የሚለው መቅደሙ መልሱን ለማወቅ ነው። የሚቀናቀን ከሆነ ቶሎ የማጥፋት አስተሳሰብ እስካልተቀየረ ድረስ መጠፋፋት አያቆምም። እርግጥ ነው፣ እንደሥርዓት ዛሬ አፄ የለም። በወንበር ላይ ግን መንግሥትም፣ ተቃዋሚም ሁሉም የአስተሳሰብ አፄ ነው። ትውልድ ከዚህ አስተሳሰብ መውጣት አለበት። እሳትና ውሃ አጥፊና ጠፊ ቢሆኑም በወሰን፣ በክልል፣ በመጠንና በልክ ከተጠቀምንባቸው ሁለቱም የግድ አስፈላጊዎቻችን ናቸው።

Share this article :

+ የተሰጡ አስተያየቶች + 1 የተሰጡ አስተያየቶች

Anonymous
July 15, 2016 at 6:00 PM

ድንቅ ፅሁፍ ነው። አልየሳሳትክም።

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger