የዛሬ ታቦትና ጽላት ከሙሴ ዘመን ጋር በጭራሽ አይገናኝም!

አንዳንዶች ከአበው የተረከብነው አስተምሕሮና ሕግ በማለት ሁሉን ነገር እንደወረደ እንድንቀበለው ይፈልጋሉ። አዎ፣ አበው ብዙ ነገር አስተላልፈውልናል። ነገር ግን የተላለፈልን ነገር ሁሉ ጠቃሚ ነው ማለት አይደለም። ለእግዚአብሔር ይቀርብ የነበረ የቤተመቅደሱ መስዋእት በመቅደሱ ሚዛን ይለካ እንደነበረው ሁሉ የተላለፈልን የአበው አስተምሕሮ ሁሉ በእግዚአብሔር ቃል ሚዛን መሰፈር አለበት። ምክንያቱም ከኛ በፊት ያለፉ ሁሉ በእድሜ አበው ቢሆኑም በአስተምሕሮ ግን በአበው ከለላ የስሕተት አስተምህሮ በስማቸው ሊገባ ይችላልና ነው። ስለሆነም በጅምላ አባቶቻችን ማለት ብቻውን ከስሕተት አያድንም። የአባቶች ትምሕርት ከመጻሕፍት ውጪ እንዳይኾኑ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በአንድ ወቅት አይሁዳውያን የኢየሱስ ክርስቶስን ትምሕርት እንዲኽ እንደዛሬው የተቃወሙት እኛስ ከአባታችን ከአብርሃም ነን እያሉ ነበር። አብርሃም አባታቸው መሆኑን ቢናገሩም በአብርሃም ስም ከመነገድ በስተቀር የአብርሃምን ስራ የማይከተሉ ነበሩ ተግባራቸው ይመሰክር ነበር።

ዮሐንስ 8፣39
መልሰውም፦ አባታችንስ አብርሃም ነው፡ አሉት። ኢየሱስም፦ የአብርሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ ነበር፣ ብሏቸዋል።
ዛሬም ከሙሴ የተቀበልነው የታቦት ሕግ አለን የሚሉ አሉ። ነገር ግን ለሙሴ የተሰጠውንና ያደረገውን ሥራ አያደርጉም። ግን በሙሴ ስም ይነግዳሉ፣ ያታልላሉ፣ ይዋሻሉ። ሙሴን አውቀውትማ ቢኾን ኖሮ ሙሴ ያደረገውን ባደረጉ ነበር። ሙሴ የታዘዘውና ያደረገውን ይኽንን ነበርና።

ዘጸአት 25፣10
ከግራር እንጨትም ታቦትን ይሥሩ፤ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን።
ሙሴ ለጽላቱ ማኅደር ይሆን ዘንድ እንዲሰራ የታዘዘውና የሰራውም ታቦት ልኩ ይኼው የተጠቀሰው ሆኖ ቤተመቅደሱ ፈርሶ አገልግሎቱ እስከተቋረጠበት እስከ 70 ዓ/ም ድረስ ለ 2000 ዘመን ይህ ልኬታ ተሻሽሎና ተቀይሮ ስለመገኘቱ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ላይ አልተጻፈም። ነገር ግን ዛሬ የጽላቱ ማደሪያ የሆነው ታቦት አለን የሚሉ ወገኖች በሙሴ ሽፋን የሚሰሩት ታቦት ርዝመቱም፣ ቁመቱም፣ ወርዱም እንደጠራቢው ችሎታና እንደአስጠራቢው ፍላጎት እንጂ የተወሰነ መጠን በሌለው ልቅ ፍላጎት ሲጠቀሙ ይታያሉ። የእግዚአብሔርን የመሥፈሪያ ሚዛን ሊጠቀሙ ይቅርና ለሚሰሩት የስሕተት ሥራ እንኳን አንድ ወጥ የሕግ ሚዛን ለራሳቸው የላቸውም። ጠራቢዎቹም የእግዚአብሔር መንፈስ እንደሞላባቸው በሙሴ እንደተመረጡት አልያብና ባስልኤል ሳይሆን ቤተክርስቲያን አነውራ የምትጠራቸው፣ ቆብና ቀሚስ የጣሉ መነኮሳት፣ ያፈረሱ ቄሶችና ደጋሚ ደብተራዎች፣ የሚያስገኘውን ገቢ የቀመሱ አወዳሾች መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።   በመኖሪያ ቤቱ የእንጨት ማሽን ተክሎ፣ ከጣውላ አቅራቢዎች ምንነቱ ያልታወቀ ጥርብ እየገዛ በሚቀርቡለት የፈላጊዎች ትእዛዝ መሠረት ጽላት የሚባለውን የዘመኑን የሰዎች መሻት እየቀረጸ የሚያከፋፍል ሰው የዚኽ ጽሑፍ አቅራቢ ያውቃል። ከሥራዎቹም የተወሰነውን ለማየት ችሏል። ከታች በገብርኤል ስም ከጣውላው የተቀረጸ ምስል ለአብነት ይመለከቷል።   እግዚአብሔር በሚሰራውና ጥንት ባደረገው ነገር ሁሉ ከመረጣቸው ሰዎች ማንነት ጀምሮ የተለዩና በሚሰሩትም ሥራ ጥንቃቄና ትእዛዙን የጠበቀ ስለመሆኑ ለአፍታ የሚዘነጋ ጉዳይ አይደለም።  ዛሬስ? በ 0% የቀደመ ሥርዓት ላይ ሆነው በሙሴ ሕግ ሥር የመደበቅ ዘመን አብቅቷል። በትውልዱም የተሸፈነው መገለጡ አይቀርም። በስተመጨረሻም የእግዚአብሔርም ትእግስት ሲሞላ ውርደት መከተሉ ሳይታለም የተፈታ ነው። በዋጋ መሸጪያ ተመን ገበያ ወጥቶለት በገንዘብ የሚገዛ ጽላት በጭራሽ ሊኖር አይችልም።
እንደእውነቱ ከሆነ በዚህ ዘመን በአባቶች እያሳበቡ የእግዚአብሔርን ቃል በመቀየር በትውልድ ላይ ለመጫን መሞከር ማብቃት አለበት።
 ሙሴ የዕንቁውን ጽላት አሮን ባሰራው የጥጃው ጣኦት ላይ ከሰበረ በኋላ አስመስለኽ ቅረፅና አምጣ ተብሎ በእግዚአብሔር ሲነገረው ለጽላቱ ማደሪያ ተብሎ አስቀድሞ የተሰጠው የታቦቱ ርዝመት፣ ቁመትና ወርድ ላይ የተሰጠ የለውጥ ትእዛዝ አልነበረም። ምክንያቱም የተሰበረው ጽላቱ እንጂ ታቦቱ አይደለምና።  ስለዚህ "ቀር ከመ ቀዳሚ"  የተባለው ጽላቱን እንጂ ማደሪያውን ታቦት ካልሆነ ሙሴ ያላሻሻለውን ታቦት ዛሬ ያሻሻሉት ከየት ባገኙት አምላካዊ ትእዛዝ ነው?  ውሸታቸውን ለማጽደቅ የፈረደበት የሙሴን ስም አቅርበው ሊሞግቱን ይዳዳሉ።
ስለማኅደሩ መሻሻል የተነገረ ካልነበረ እነዚህኞቹ በራሳችን ሥልጣን አሻሽለናል ይበሉን እንጂ ሙሴን ለሐሰት ምስክርነት አይጥሩብን።
ከዚያም ሌላ ሙሴ የፊተኞቹን ጽላቶች አስመስሎ ከቀረጸ በኋላ ይዞ የሄደው ወደሲና ተራራ ነው። በዚያም እግዚአብሔር በጣቶቹ 10ቱን ትእዛዛት ጻፈባቸው እንጂ ሙሴ በጭራሽ አልጻፈም።

ዘዳግም 10፣3-4
ከግራርም እንጨት ታቦትን ሠራሁ፥ እንደ ፊተኞችም ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠረብሁ፤ ሁለቱንም ጽላቶች በእጄ ይዤ ወደ ተራራው ወጣሁ።
ስብሰባ ተደርጎ በነበረበትም ቀን እግዚአብሔር በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ የተናገራችሁን አሠርቱን ቃላት ቀድሞ ተጽፈው እንደ ነበረ በጽላቶቹ ላይ ጻፈ፤ እግዚአብሔርም እነርሱን ለእኔ ሰጠኝ።
ይለናል መጽሐፍ ቅዱሳችን።

እዚህ ላይ እንደምናነበው ጽላቶቹ ላይ የጻፈባቸው እግዚአብሔር ራሱ ሆኖ ሳለ ሙሴ እንደጻፈ አድርጎ በሙሴ ላይ መዋሸት ለምን አስፈለገ?  አስመስለኽ ቅረጽና አምጣ መባሉን ልክ እራስኽ እየጻፍክባቸው አባዛ የተባለ ማስመሰል በእግዚአብሔር ላይ መዋሸት አይደለምን? ያልተባለውን እንደተባለ፣ ያልተነገረውን እንደተነገረ አድርጎ በማቅረብ የራስኽንም ስሕተት እንደማጽደቂያ መሳሪያ አድርጎ መጠቀም የከፋ ክሕደትና ሕዝቡን በስሕተት መንገድ መንዳት ነው።  ሙሴን ያላደረገው ነገር አድርገኻል ማለት መሳደብ ነው፣ እግዚአብሔርንም ለሙሴ አንተው ጻፍባቸው ያላለውን እንዳለ ማስመሰልስ ዋሾ ማድረግ አይደለምን?
 ጽላቶቹ ላይ የተጻፈባቸውና ሙሴ የተቀበላቸው 10ቱን ትእዛዛት ሆኖ ሳለ የሰው ስም ወይም የሰው ምስል ያለበት አድርጎ በማቅረብ በዚህ ዘመን እኛ የምንፈልገውን የልባችን ፈቃድ ለማሳካት ማጭበርበርስ ለምን ይሆን? በየትኛውስ ቃል እንደገፋለን? የምናስደስተው ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን? መቼም ቢሆን እግዚአብሔር ያላለውን ብለኻል በሚሉ ዋሾዎች ተደስቶ አያውቅም። ሊደሰትም አይችልም። ከራሱ አንቅቶ የሚናገረው የሐሰት አባት የሆነው ዲያብሎስ ብቻ ነው።
እግዚአብሔር የሰጠውን ሕግ የሚያጸናውና የሚሽረው ራሱ እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ ሰው እንዴት የኪዳኑን ሕግ ራሱ ለራሱ ስሜት ያሻሽላል?
የሙሴን ታቦተ ሕግ ተከትለናል ማለት እግዚአብሔር ያላለውን በራስ ፍላጎት እንደሚመች አድርጎ ማቅረብ ነው እንዴ?
ሌላው መነሳት ያለበት ነገር፣ ዛሬ የኪዳኑን ጽላት እንጠቀማለን የሚሉ ሰዎች የኦሪቱ የጽላት ሕግ፣ ቃል ኪዳን የተሰጠው ለማነው? የሚለው ነው።

 በማያከራክር መልኩ የቃልኪዳኑ ታቦት ሕግ የተሰጠው ለእስራኤል ዘሥጋ ብቻ ነው። ይኽ ሆኖ ሳለ እናንተን ያ የኪዳን የሕግ ውል የጨመራችሁ በየትኛው የብሉይ ኪዳን ቃል ላይ ነው?  እግዚአብሔር ውሉን በሙሴ ፀሐፊዎች አማካይነት በአራቱ ብሔረ ኦሪት ጽፎ ሰጥቷቸዋል። የእናንተስ ውል በነማን በኩል፣ መቼና የት ቃል ተገባላችሁ? ብለን እንጠይቃቸዋለን።
ምክንያቱም እስራኤላውያን አፋቸውን ሞልተው እንዲህ ሲሉን እናገኛቸዋለን።
ዘዳግም 5 ፣2
አምላካችን እግዚአብሔር በኮሬብ ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ።

ያ ቃልኪዳን ከፈረሰና የመስዋእቱ አገልግሎት ከተቋረጠ 2ሺህ ዘመን አልፎታል። ከዚያ በኋላ ከእስራኤላውያን ውጪ እግዚአብሔር የታቦት ቃልኪዳን የገባላቸው ሌላ ሕዝቦች የሉም። ኧረ በጭራሽ አይኖርምም። ምክንያቱም ያ ውል የተገባው ለተወሰነ ሕዝብ ብቻ ስለሆነ ሁሉን ያካተተ አዲስ ውል ያስፈልግ ስለነበር ለተወሰነ ሕዝብ በድጋሜ ቃል የሚገባበት ምክንያት የለም።
ሮሜ 9፣4
እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና፥ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና"

ነገር ግን ሕዝቤ ያልተባለን ሕዝቤ ለማለት አህዛብ ሁሉ ወደመጠራቱ እንዲገቡ አዲስ ቃል ኪዳን አስፈልጓል።
ሮሜ 9፣26 እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም በተባለላቸውም ስፍራ በዚያ የሕያው እግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉ፥ ይላል።

በዚህም ምክንያት ለአንድ ሕዝብ ብቻ ተሰጥቶ የነበረው ሕግ ቀርቶ ሁሉን የሚመለከት ሕግ እንዲመጣ ማስፈለጉን በአዲስ ኪዳን የኦሪቱ የመስዋእት አገልግሎት ከእንግዲህ አይታሰብም ተብሎ ትንቢት ተነግሯል።

ኤርምያስ 31፣31
እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር።

 ለምን አዲስ ቃልኪዳን መግባት አስፈለገው? ምክንያቱም፣

ኤርምያስ 31፣32
ከግብጽ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር።

ስለዚህ በሰማያዊው መስዋእት በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተሻለ ኪዳን ስለተገባልን አሁን ልንናገርበት ጊዜው ባልሆነ የዚህ ምድር ሥርዓት አይደለንም። ጳውሎስ ድሮ ነበረ፣ አሁን ግን የለም ይለናል።

ዕብራውያን 9፣5
በላይዋም ማስተስሪያውን የሚጋርዱ የክብር ኪሩቤል ነበሩ፤ ስለ እነዚህም ስለ እያንዳንዳቸው ልንናገር አሁን አንችልም።
ምክንያቱም፣
ዕብራውያን 7፣22
እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል።
ስለዚህ አብርሃም አባታችን፣ ሙሴ መሪያችን፣ እግዚአብሔር አምላካችን በማለት ለስሕተት መሸፈኛ አድርጎ ማቅረብ አያድነንም። አብርሃም አባታችን፣ እግዚአብሔር አምላካችን ይሉ የነበረ፣ ነገር ግን የሚነገራቸውን ቃል እኛ ከሁሉ ቀድመን ያወቅን ነን በሚል ትምክህት ለመቀበል ያልፈለጉትን ሊቃውንተ አይሁድን እንዲህ ብሏቸዋል።

ዮሐንስ 8፣47
ከእግዚአብሔር የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማል፤ እናንተ ከእግዚአብሔር አይደላችሁምና ስለዚህ አትሰሙም።

ስለዚህ በዚህ ዘመንም የቀደመችው ሃይማኖት በማለት ራስን በመካብ ብልጫ አይገኝም። ከአይሁድ የቀደመ ሃይማኖት የለምና። ነገር ቀድሞ በመገኘት አብርሃም አባታችን፣ ሙሴ ፈለጋችን ነው፣ ማለት ከስህተት አያርቅም። ምክንያቱም አብርሃምና ሙሴ የተቀበሉትንና የፈፀሙትን ሕገ እግዚአብሔር ሳይሸራርፉና ሳያሻሽሉ በማድረግ እንጂ የነሱ ተከታይ መሆን የሚቻለው በስማቸው በመነገድ ግን በሕጉ በሌሉበት ሁኔታ የሙሴ ተከታዮች በማለት ራስን ካልሆነ ማንንም ማታለል አይቻልም።
ስለሆነም የዛሬ ታቦትና ጽላት ከሙሴ ዘመን ጋር በጭራሽ አይገናኝም። እንዲቀየርና እንዲሻሻል ከእግዚአብሔር የተሰጠ ሕግ አልነበረም። ፊተኛውና ኋለኛው ጸሐፊ ራሱ እግዚአብሔር፣ ጽሕፈቱም ሕግጋቶች ነበሩ። የተጻፈውም በሲና ተራራ ነጎድጓዳማ ድምጽ መካከል እንጂ በጥቃቅንና አነስተኛ የእንጨት መላጊያ ውስጥ አልፎ የዚህ ምድር በሆነች እጅ ብልሃት አይደለም።
የእጅ ብልሃት ይኽ ነው።
Share this article :

+ የተሰጡ አስተያየቶች + 1 የተሰጡ አስተያየቶች

Anonymous
March 7, 2016 at 7:58 PM

ኸረ ባክህ? አይገናኝም? ታዲያ አንተ ለምን የሚገናኝ ሰርተህ አትገለገልበትም። እንዴ? ሁሌ እንደ ህፃን ስታለቅስ ልትኖር ነው እንዴ?

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger